ያለ መታደል ሆኖ ያለፉትን ሁለት አመታት እንደ ኢትዮጵያዊ የአስተሳሰብም የስራም አቅጣጫችን ሆኖ የሰነበተው የሰላም ፍለጋ ነበር። በነጋ በጠባ ስንሰማቸው የነበሩ የጦር ሜዳ ውሎ ዜናዎች የዜጎች መፈናቀልና ሞት ሲያረዱን ቆይተዋል። በመንግስት ሆነ በግለሰቦች /ባለሀብቶች ይሰሩ የነበሩ ስራዎችንም በጦርነቱ ጥላ ያጠለባቸው ነበሩ። ስለሀገር እድ ገት ስለራስ መለወጥ ለማሰብ ፋታ የሚሰጡም አልነበሩም።
በጦርነቱ በርካታ የኢኮኖሚ አውታሮች፤ የህዝብ መገልገያ ተቋማትን ጨምሮ ግለሰቦች ጥረው ግረው ያፈሯቸው ንብረቶች ወድመዋል። በዚህም የልብ ስብራትና ተስፋ መቁረጦች ተስተውለዋል።
ችግሩ በኢኮኖሚው ረገድ የውጭ ተጽእኖ ጨምሮ አላግባብ ለመበልጸግ በሚፈልጉ አካላት በበርካታ ፈተናዎች ውስጥ ለማለፍ ተገዷል። በዚህ የተፈጠረው የዋጋ ግሽበት /የኑሮ ውድነት የእያንዳንዱን ዜጋ በር አንኳክቷል ፤ ዜጎችንም ብዙ ዋጋ አስከፍሏል።
ዛሬ ነገሮች እየተለወጡ ነው። ምን አልባትም ብዙዎቻችን ባልጠበቅነው መንገድ የተጀመረው የሰላም ድርድር በጦርነቱ ምክንያት ከገባንባቸው ችግሮች ለመውጣት መልካም አጋጣሚ ይዞ መጥቷል። በመሰረቱ ሰው ስለሆንን ብቻ ጦርነትን ልንቃወም፣ ልናወግዝ፤ ሰላምን ልንሰብክ ይገባናል።
ከዚህ የተነሳም ስለነገ ተስፋ ያሰነቀን፤ ከጦርነትና ከጦርነት አሳዛኝ ወሬ ያወጣንን የሰላም ሻማ እንዳይጠፋ ዜጎች የበኩላችንን ሁሉ መወጣት ይጠበቅብናል፤ በጦርነቱ እየተፈተነ ያለው ኢኮኖሚያችን ጠንክሮ እንዲቆም ጠንክሮ መስራት ይኖርብናል።
ስለ ሰላም የሚጠብቀን ትልቁ በአውሮፓና አሜሪካ ተቀምጠው የሰላም ስምምነቱን እያወገዙ ያሉ አካላትን እኩይ ሴራ ማክሸፍ ነው። ይህ ስራ ስለ እንደ ግለሰብ ሆነ እንደ ሀገር የቱን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በድፍረት ለሌላው ወገናችን ከመስበክ /ከማስረዳት የሚጀምር ነው።
የሰላም ጉዳይ ለአንድ አካል የሚሰጥና በዛ አካል በጎ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ እንዳልሆነ፤ ከዛ ይልቅ የሰላም ጉዳይ የመላው ህዝባችን ትልቁ አጀንዳ እንደሆነ መረዳት፤ ለዚህ የሚሆን የኃላፊነት መንፈስ መፍጠር ወሳኝ ነው።
ሌላኛው ደግሞ በሀገር ውስጥ ተቀምጠው የውጭ ኃይሎችን አጀንዳ ለማስፈጸምና የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ በሙስና የሚዘፈቁና ሰው ሰራሽ የኑሮ ውድነትን የሚፈጥሩ ብሎም የሚያባብሱትን መታገል ነው።
እነዚህ ሁለት አካላት በሀገር ውስጥ ሊያደርሱት የሚችሉት ጥፋት ከፍተኛና አውዳሚ ቢሆንም እኛ እንደ ኢትየጵያዊ አስበን በጋራ መንቀሳቀስ ከቻልን እግራቸው ቄጠማ፤ ሀሳባቸው መና ሆኖ መቅረቱ የማይቀር ነው።
የተጀመረው የሰላም/የእርቅ ጉዳይ ፍሬ ማፍ ራቱን ተከትሎም /ሰላሙ የመላው ህዝባችን ፍላጎት ስለሆነ/ ትኩረታችንን ፈጥነን ወደ ልማት ማድረግ ይጠበቅብናል። ይህን የምናደርገው ደግሞ በጦርነቱ የወደሙ ኢኮኖሚያዊ አቅሞችን ለመገንባት ብቻ ሳይሆን የበለጸገች ሀገር በመፍጠር ተመልስን ወደግጭትና ጦርነት እንዳንገባ ተጨባጭ ማስተማመኝ ለማግኘት ጭምር ነው።
ከዚህም በላይ ሰላማችን ለማደፍረስ ሁሌም እጃቸውን የማይሰበስቡ የውጭ ኃይሎች እጅ አቅም እንዲያገኝ የተዳከመ ኢኮኖሚ ሊፈጥርላቸው የሚችለውን የተሻለ እድል ለማክሰም፤ የተሻለ ኢኮኖሚ ባለበት መሆኑ ወሳኝ ነው።
አንዳንድ ምእራባውያን ሀገራት በታዳጊ ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግቢያ መሳሪያቸው የሀገራቱ /የታዳጊ ሀገራቱ የኢኮኖሚ አቅም ጣልቃ ገብነትን መሸከም የሚያስችል አቅም ባለቤት አለመሆኑ ይታወቃል፤ ከዚህ አንጻር ኢኮኖሚያችንን ለማሳደግና የምንሄድበት መንገድ እራስን ከጣልቃ ገብነት የመከላከያ አቅም የማበልጸግ ጉዞ መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው፤
የሚመጡባቸው መንገዶች የሰብዓዊ መብት ጥሰትና እርዳታ መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። የሰላም ስምምነቱ በሰብዓዊ መብት ጥሰትና ከጦር ወንጀል ጋር በተያያዘ የሚመጣውን ጫጫታ ጸጥ ባያሰኘውም እንደሚቀንሰው ይታወቃል። እርዳታ እያንጠለጠሉ ወደሀገራችን የሚያደርጉትን ጉዞ ለመግታት ግን እንደ ሀገር ብዙ መስራት ብዙ መጣር የሚጠይቅ ይሆናል።
የተሻለ የኢኮኖሚው አቅም የገነቡ ሀገራት የውስጥ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ የመግባት ጉዳይ ብዙም የሚሞከር አይደለም /ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችም የሚያሳዩት ይህንኑ ነው፤ ይህ የሚያሳያን በኢኮኖሚ በደረጀን በጠነከርን ቁጥር ዛሬ ለእያንዳንዱ የውስጥ ችግራችን መፈጠርና መባባስ ቀዳሚ ምክንያት የምናደርገውን የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ማስቆም እንደምንችል ነው።
መንግስት በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆኑ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለመታደግ እየሄደባቸው ያሉ መንገዶችን አየተመዘገቡ ላሉ ውጤቶች አበረታች ቢሆኑም ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገት ጉዳይ የመንግስትን ብቻ ሳይሆን የመላውን ህዝብ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው።
አሁን ባለንበት የፈተና ወቅት /የሀገር ህልውና ሳይቀር ችግር ውስጥ ወድቆ በነበረበት ወቅት/ መንግስት በሀገሪቱ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የተፈና ቀሉ ዜጎችን መልሶ ከማቋቋም አልፎ እያንዳንዱ ዜጋ እየገጠመው ላለው የኑሮ ውድነት ምላሽ ይስጥ ማለት የማይሞከር ብቻ ሳይሆን ሊታሰብም የማይገባው ነው። የዜጎችን በተለይም የባለሀብቱን ርብርብ የሚጠይቅ ነው።
በመንግስት በኩል ከሁሉም በላይ ዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት መፍጠር ለሚያስችሉ ትልልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችና የስንዴ ምርትን ለማሳደግ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥቶ መንቀሳቀስ ይኖርበታል።
የበርካታ ያደጉ ሀገራት ተሞክሮ የሚያመላክተን የእያንዳንዱ ዜጋ ስራ መስራትና አምራች ሆኖ ራስን መቻል ለአጠቃለይ ሀገራዊ ኢኮኖሚ እድገትና መነቃቃት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ነው።
በተለይም ጥሮ ተጣጥሮ በምግብ እህል ራስን መቻል በአንድ ወገን አጠቃላይ ኢኮኖሚውን የሚደግፍ ሲሆን በሌላ በኩል መንግስት በቢሊየን የሚቆጠር ወጪ በማውጣት ከሚያከናውነው ድጎማ ተላቆ እንደ ሀገር ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው ትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ ትኩረት እንዲያደርግ የሚረዳ ይሆናል።
ባለፈው አመት በሀገር አቀፍ ደረጃ መተግበር ጀምሮ በርካቶችን ተጠቃሚ ያደረገው የጓሮ አትክልት ልማት ከወረት ተላቅቆ የሚቀጥል ከሆነ በዚህ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ይታመናል። እንደዚህ አይነት ትንንሽ የሚመስሉ ሀገራዊ ፋይዳቸው ግን የጎሉ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ በማድረግ ረገድ የህዝቡ ቀጥተኛ ተሳታፊነት ወሳኝ ነው። የሚመለከታቸው አካላትም ስራዎች ከወረት ተላቀው፤ በተጀመሩበት ሞቅታ እንዲቀጥሉ ህብረተሰቡን በመከታተልና በመደገፈ ቀጣይነት ያላቸውን ስራዎች መስራት ይጠበቅባቸዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2015