ዕድሜዋ ዘጠኝ ዓመት እስኪሞላ ሕይወቷ መልካም ነበር። ቤተሰብ ስለእሷ ያለው ፍቅር የተለየ ነው። ወላጅ እናቷ ዘወትር በስስት ያዩያታል። እሷም ብትሆን ትምህርት ቤት ውላ ስትመጣ ቤቷን ትናፍቃለች።
ይህ ዕድሜ ለፋንቱ ፉጄ የተለየ ነበር። የልጅነት ሕይወቷ በፍቅር የተቃኘበት፤ የቤተሰቧ ዓለም በፍሰሀ የተሞላበት ድንቅ ጊዜ። ፋንቱ ዛሬ ላይ ሆና ያለፈውን ሁሉ ስትቃኝ ዓይኗ በዕንባ ይሞላል። መንፈሷ ይረበሻል። አሁንም ቢሆን አልፎ ያላለፈው ታሪክ ከኋላ እየወጋ ሊያቆስላት፣ ሊያደማት ይሞክራል።
ፋንቱ ወደ ኋላ ልመለስ ካለች ትዝታዋ ከልጅነቷ ያደርሳታል። ይህ ጊዜ ለእሷ በክፉ ትውስታዎች የተቃኘ ጥቁር ዳመና ነው። እንደምንም ዳመናውን ልግፈፍ ካለች ደግሞ አንደበቷ ሁሉን ይተርካል። ውስጠቷ አንዳች ሳያስቀር ያለፈውን ይመሰክራል።
ፋንቱ የልጅነት ዓለሟን ዛሬም ድረሰ አትረሳውም፤ በጊዜው እንደ እኩዮቿ ሮጣና ፈንጥዛ አሳልፋለች። ይህ ዕድሜዋ ለእሷ የተለየና ብርሃናማ ነበር። ይህ መሰሉ ደስታ ግን ከአስር ዓመቷ በኋላ አልዘለቀም። በድንገት ወላጅ እናቷን በሞት ተነጠቀች። ቅስሟ ተሰበረ፣ ሕይወቷ ጨለማ የዋጠው እስኪመስል ተሰማት። የልጅነት ዓለሟ በእናቷ ሞት መልኩን ቀየረ።
ፈተና
የፋንቱ እናት ካረፉ በኋላ የቤተሰቡ ሕይወት እንደቀድሞ ቀጠለ። ቤቱ ትልቅ ሲሳይ ቢነጠቅም መሽቶ መንጋቱ አልቀረም። ሁሉም በራሱ ዓላማና መስመር መንገዱን ቀጥሏል። ፋንቱ ገና በልጅነቷ ሞት እናቷን ቢነጥቃትም በሀዘን ቤት አልዋለችም። እንደቀድሞው ትምህርቷን ቀጠለች።
ውላ ስትገባ እናቷን እያሰበች ሆድ ይብሳታል። አሁን እንደትናንቱ ራሷን የምትደባብሳት ፣ ሳይርባት የምታጎርሳት እናት የላትም። ዛሬ ትናንት አይደለም። በር ከፍታ ስትገባ ይከፋታል። የጎደለው ሲበዛ አንገት ትደፋለች፣ ታለቅሳለች፣ ታኮርፋለች። ያለችበት ዕድሜ የእናትን ጉያ ይሻል፣ የእምዬን ቁልምጫና ልምምጥ ይፈልጋል። በፋንቱ ሕይወት ይህ ሁሉ ዓለም ጎድሏል። ዛሬም ከቤት ስትገባ ዕንባዋን የሚያብስ፣ ብሷቷን የሚረዳ ሁነኛ ሰው ጎኗ የለም።
እንዲህ በሆነ ቁጥር የፋንቱ የልጅነት ሆድ ሆድ ይብሰዋል። አሁን አባቷ መላውን ቤተሰብ የማስተዳደር ሀላፊነት ወድቆባቸዋል። ትናንት ግማሽ አካላቸውን በሞት ወስዶባቸዋል። ለልጆቻቸው ፍቅር ቢኖራቸውም የእናትን ጎዶሎ መተካት አይሆንላቸውም ።
ፋንቱ ሁሌም ሟች እናቷን እያሰበች፣ ትናፍቃለች። ሁሌም በሀሳብ ተክዛ ታለቅሳለች። ያም ሆኖ ከትምህርት ቤት ውላ መግባቷ ቀጥሏል። እናቷን በሞት ብታጣም ዛሬም ትምህርቷ አልተቋረጠም። ትምህርት ቤት ውላ በጊዜ ቤት ትመለሳለች። ወጥታ በገባች ቁጥር የእናቷ አቀባበልና ሳቂታ ፊት በዓይኖቿ ውል ይላል። ትዝታዋን ይዛ ወደ ውስጥ ትዘልቃለች። በትካዜ ተውጣ ምሽቱን ትገፋለች።
የአባት ውሳኔ
ቀናት በወራት እየተተኩ ዓመታት መንጎድ ይዘዋል። የጊዜው መሮጥ የልጆችን ዕድሜ ጨምሯል። የአባወራውን ሀሳብ ቀይሯል። የነፋንቱ አባት ከሚስታቸው ሞት በኋላ ሕይወት ሲፈትናቸው፣ ኑሮ ሲያንገዳግዳቸው ቆይቷል። ያለ ግራ ጎን የሙት ልጆችን ማሳደግ ቀላል አይደለም። ያለ አጋር ኑሮን በድል ማሸነፍ፣ ሕይወትን እንዳሰቡት መወጣት ፈተናው ይበዛል።
አሁን አባወራው ከአንድ ውሳኔ የደረሱ ይመስላል። ብቸኝነት ከብዷቸዋል። ሀዘን አንገት አስደፍቷቸው ኖረዋል። ከዚህ በኋላ በዚህ መቀጠል አይኖርባቸውም። በቀሪ ጊዜያቸው መልካም ትዳርን ይሻሉ። ቤተሰባቸውን ቤተሰብ አድርገው ሕይወት መዝራት፣ ዳግም ወግ ማየት ፍላጎታቸው ሆኗል።
የፋንቱ አባት እንዳሰቡት ሆኖ በአዲስ ትዳር አዲስ ሕይወት ጀምረዋል። ከዚህ በኋላ ብቸኝነት እንደማይጎዳቸው ያውቃሉ። ሀዘን ይሉትን አርቀው በአዲስ ሕይወት ኑሮን ጀምረዋል። አሁን ጎዶሏቸው በግራ ጎናቸው ሞልቷል። ከእንግዲህ አዲሷ ወይዘሮ ለእሳቸው ሚስት፣ ለልጆቻቸው እናት ትሆናለች።
ፋንቱ አሁን በትምህርቷ ገፍታለች። በዕድሜዋ ጨምራለች። ዛሬ አስተሳሰቧ በስሏል። አንዳንዴ እናቷን እያሰበች ብትተክዝም እንደቀድሞው ከጥልቅ ሀዘን አትገባም። በቤታቸው ያለውን የሕይወት ለውጥ ግን በቀላሉ የተቀበለችው አይመስልም። እንጀራ እናቷ ወላጅ እናቷን የምትተካ አልመስል ካላት ቆይቷል። የምትለው፣ የምታደርገው ሁሉ በበጎ አይታያትም። ትንሽ ትልቁ ያስከፋታል። በየሰበቡ ታኮርፋለች፣ ባስ ሲልም ታለቅሳለች።
የፋንቱ እንጀራ እናት የልጅቷ ሁኔታ የተመቻት አይመስልም። በየሰበቡ ትቆጣታለች፣ በየአጋጣሚው ትጨክናለች። አባት በሚስታቸውና በልጃቸው መሀል ያለውን አለመግባባት አውቀዋል። ያም ሆኖ ከሚስታቸው ለልጃቸው አያደሉም። ከሚስት ጥፋት መኖሩን እያዩ ልጃቸውን ይቆጣሉ፣ ይህን የምታውቀው ሴት የባሏን ፍላጎት እየሞላች የልጃቸውን ኩነኔ ታበዛለች። ለእሳቸው ደግ መስላ ፋንቱን ታስቆጣለች፣ ታስገርፋለች።
ይህ እውነት በቤተሰቡ መለመድ ሲጀምር በደል መብዛት፣ ክፋት መጨመር ያዘ። ሁሌም ከልጃቸው ወደ ሚስታቸው የሚያደሉት አባት መፍትሄ የለሽ ሆኑ። እንዲህ መሆኑ አዲሷን ሚስት ‹‹ክፉ እንጀራ እናት›› አሰኝቶ የፋንቱን ልብ ውጭ አሳደረ።
የፋንቱና የእንጀራ እናቷ አለመግባባት ይበልጥ ስር ሰዷል። አሁንም በአባወራው ወሳኝነት የመጣ ለውጥ የለም። ይህ እውነት መደጋገም ሲጀምር ፋንቱ ተወልዳ ካደገችበት ቤት ልትወጣ ግድ ሆነ። ከዘመድ ቤት ተጠግታ የማታ መማር ብትጀምርም ሕይወት እንደቀድሞው አልሆነም። የሰው ቤት ኑሮ እንዳሻት የምትሆንበት፣ እንደፈለገችው የምታዝበት አይደለም።
አሁንም ፋንቱና የሰው ቤት ኑሮ አልተለያዩም። ትምህርቷን እየተማረች ከስምንተኛ ክፍል ደርሳለች። እንደዋዛ ከቤት መውጣቷ ዋጋ እያስከፈላት ቢሆንም ከእንጀራ እናቷ በደል በመላቀቋ እፎይታ አግኝታለች። አባቷ ልጃቸው ከቤት ከወጣች በኋላ ከሚስታቸው ጋር ኑሮን ቀጥለዋል። ፋንቱ ይህን ስታስብ ሆድ ይብሳታል፣ እልህ ይይዛታል። ትናንት በሞት ያጣቻት እናቷን እያሰበች ትተክዛለች።
አንድ ቀን
አንድ ማለዳ ከፋንቱ ጆሮ የደረሰው ክፉ ዜና መላ ሰውነቷን በድንጋጤ አራደው። ይህን ድንገቴ ወሬ በአጋጣሚ መስማት ለፋንቱ ቀላል የሚባል አይደለም። አሁን ወላጅ አባቷ በድንገት ማረፋቸውን እየሰማች ነው። ፋንቱ ፈጥኖ ከውስጧ የገባውን ክፉ ሀዘን መቋቋም ተሳናት። የእናቷ ሞት ሳያንስ የአባቷ መርዶ መከተሉ ሀዘኗን አክፍቷል።
ፋንቱ አባቷን ከቀበረች በኋላ ባይተዋርነት ተሰማት። እንደ ልጅ ከቤት ተቀምጣ ሀዘኗን ለመወጣት ሁኔታዎች አይመቹም። አሁን ሁሉም ነገር በእንጀራ እናቷ ቁጥጥር ስር ሆኗል። እሷና ከአባቷ የሚወለዱ እህት ወንድሞቿ ቤታቸውን ‹‹ቤታችን›› ለማለት ይቸገራሉ። የሚኖሩበት ቤት የቀበሌ ቢሆንም እንዳሻቸው የሚያዙበት አልሆነም። ሀይለኛዋ እንጀራ እናት በዋዛ ፊት የምትሰጥ አይደለችም።
ውሎ አድሮ እነፋንቱ የቤቱ አካል ከሆነ የከሰል መሸጫ ሱቅ ኑሯቸውን መሰረቱ። አባት በሕይወት በነበሩ ጊዜ ቤቱን ለመኖሪያ ጭምር ሲጠቀሙበት ቆይተዋል። ቦታውን ለኑሮ የመረጡት እነፋንቱ ገለልተኛ መሆናቸው ከእንጀራ እናታችን ‹‹አያጋጨንም ›› ሲሉ አሰቡ። ኑሯቸውን በሱቁ አድርገውም ወራትን ቆጠሩ።
ውሎ አድሮ
የነፋንቱ ከቤቱ መጠጋት እንጀራ እናትን ያሰደሰተ አይመስልም። ልጆቹ እንደዋዛ ቤተኛ መሆናቸው ሲያሳስባት ከርሟል። ጥቂት ቆይታ ያመጣችው መላ ግን የልቧን መሻት ከወነ። ልጆቹ የሚኖሩበትን ሱቅ የንግድ ፈቃድ አወጣችበት። እንዲህ በሆነ ማግስት በሱቁ ያሉ ልጆች ከቤቱ እንዲወጡ ምክንያት ሆነ። ከእነሱ ይልቅ ‹‹ሕጋዊ ናት›› የተባለችው ሴት ቤቱን ከእጇ አድርጋ ለመረከብ አልዘገየችም።
እንዲህ በሆነ ጥቂት ጊዚያት ውስጥ የፋንቱ ኑሮ ተቃወሰ። ሳታስበው አባቷንና መኖሪያ ጎጆዋን ያጣችው ወጣት ምርጫው ጠፋት፣ መውደቂያና ማረፊያ ቸገራት። አሁን የፋንቱ እግር ሮጦ የሚገባበት የዘመድ ቤት የለም። ‹‹አለሁሽ›› የሚላት፣ ዕንባዋን የሚጠርግላት ‹‹አይዞሽ›› ባይ ጎኗ አልተገኘም። ስለዚህ የመጀመሪያ ምርጫዋ የጎዳና ጥግ ሆኗል። ጎዳናን ከነስጋቱ ስትቀበለው ሌላ ዕድል አልነበራትም።
ፋንቱ ቆም ብላ ለማሰብ ሞከረች። ከእንግዲህ ‹‹የኔ›› የምትለው ፣ ወዳጅ ዘመድ ጎኗ የለም። አሁን የት ጠፋሽ፣ የት ገባሽ ባይ አስታወሽ እንደሌላት አረጋገጠች። ጎዳናው ግን ካለው ሁሉ አልነፈጋትም። ጥርጊያ መንገዱ በእንግድነት ተቀበላት። በዚህ ሰፍራ ቤቴ፣ አጥሬ፣ ውርሴ ይሉት ጉዳይ አይሰማም። ሁሉም ከስፍራው መስሎ ተመሳስሎ ይኖራል።
ቦታው እንደ መኖሪያ ቤት ‹‹እፎይ›› የሚሉበት አይደለም። በዚህ ስፍራ ዕንቅልፍ በዋዛ አይገኝም፣ ሰላማዊ ሕይወት ይርቃል፣ ኮቴ ኮሽታው ያሳቅቃል። በዚህ ቦታ የሚያድሩ ነፍሶች ሕይወትን የሚቀበሉት ከነሙሉ ችግሩ ነው። በተለይ ሴቶች ብዙ ገፈትን ይቀምሳሉ። ብዙዎቹ ተገዶ መደፈርን፣ በድንገት ልጅ መውለድን፣ ለሱስ መጋለጥን አያመልጡትም።
ፋንቱ ጎዳና በወጣች ማግስት በእነዚህ ችግሮች መሀል ተራመደች። ብቸኝነትን ሽሽት ባል አገባች። ኑሮን ለመግፋት የተሻለ በምትለው አማራጭ ሁሉ ባዘነች። በየጊዜው እያገባች ከምትፈታቸው ባሎች ሁለት ልጆች ወለደች።
ለእሷ ሁሌም ትዳር ብላ የምትጀምረው ውጥን ተሳክቶ አያውቅም። ሁሉም ባሎች የተለያየ ዓመልና ሱስ አላቸው። ከአንዱ ‹‹ሕይወት በቃኝ›› ስትል ሌላው ይቀርባታል። ከዚህ ስትላመድ ባህሪው ያስከፋታል። እሱም ልጅ አስይዟት ይጠፋል። መልሳ ሌላ ትቀርባለች። ተመሳሳይ ሕይወት ይገጥማታል።
ፋንቱ የመጀመሪያ ልጇን የወለደችው ከጎዳናው ነበር። ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ከአስፓልቱ ዳር። ዕለቱን ባጣደፋት ምጥ ስትንቆራጠጥ ብትውልም ማንም ለእርዳታ ከሆስፒታል አላደረሳትም። ድንገት ግን የህጻኑ መወለጃ ደረሰ። ቁርጥ ሲሆን መንገደኞች ተሰበሰቡ፣ የሰንበት ተማሪዎች ደረሱ ። እናት በሰላም ተገላግላ ወንድ ልጇን ታቀፈች። ህጻኑ አርባ ቀን ሲሞላው የቤተክርስቲያኑ ወጣቶች ዳግም ተመልሰው ክርስትና አስነስተው ወግ ማዕረግ አሳዩዋት። በደስታ ሲቃ ያዛት፡፤ ውለታውን በምስጋና መለሰች።
ያልታሰበ
ፋንቱ ጥቂት ቆይታ ልጇን እንደያዘች ተክለሃይማኖት ቤተክርስቲያን ከሚገኝ ገዳም ገባች። እንዲህ ማድረግ የተለመደ አይደለም። ችግሯን ያሰተዋሉ መነኩሴዎች አልተቃወሟትም። ከቀመሱት እያጎረሷት ኑሮ ቀጠለች። ለጊዜው እፎይታ ተሰማት። በዕምነቷ ጸንታ በሃይማኖት በረታች። ይህ መንገዷ ብዙ አልቀጠለም።
አንዳንድ ባህሪዋ ከገዳሙ መነኮሳት ጋር አልተስማማም። እነሱ በየጊዜው ቡና ማፍላቷን አልወደዱም። አጥብቀው ተቃወሟት። ፋንቱ ጠብና ነገር ብታበዛ ከቦታው በዘበኞች ተባረረች። ከግቢው ስትወጣ የጎዳና ሕይወት እጁን ዘርግቶ ተቀበላት። ሸራ ወጥራ፣ ጎጆ ቀልሳ ኑሮን ቀጠለች። በላስቲክ ቤቷ ሌላ ልጅ ወለደች። ኑሮ ከበዳት፣ ሕይወት ፈተናት።
ውሎ አድሮ ለዓመታት ስትመላለስ የኖረችበት ጉዳይ ተሳካ። ለአንገቷ ማስገቢያ የቀበሌ ቤት አገኘች። ፈጣሪን አመስግና ሁለት ልጇቸዋን ይዛ መኖር ጀመረች። ብዙ አልቆየችም የሶስተኛው ልጇ አባት ትዳር ብሎ ቢቀርባት አመነችው። ኑሮ እንደታሰበው አልሆነም። ልጇ በወጉ ሳይጠነክር እሱም ተለያት። እንዳሰበችው አንዳች አልረዳትም። ለሌላ ሕይወት አገሩ እንደገባ ሰማች።
ዛሬ ላይ
ፋንቱ በተለያዩ ጊዚያት ከሶስት አባቶች የወለደቻቸውን ልጆች ብቻዋን ማሳደግ ግዴታዋ ሆነ። አሁን የልጆቿን ጉሮሮ ለመድፈን ልፋቱ የእሷና እሷ ብቻ ነው። እንዳሻት ሮጣ እንዳታድር በየጊዜው የሚነሳባት የልብ ህመም ፈተናዋ ነው። ሁሉን ትታ እንዳትቀመጥ የእሷና የልጆቿ ሆድ ጊዜ አይሰጥም ። ፋንቱ በየቀኑ ጎዶሎ ለመሙላት ትሮጣለች። ልጆቿ አልደረሱም። ችግሯ አብሯት አለ።
አሁን ፋንቱና ሶስት ልጇቿ በጠባቧ ቤት መኖር ይዘዋል። እናት እነሱን ለማሳደግ የማትሆነው የለም። ስትጠራ ‹‹አቤት ፣ ወዴት›› ብላ ትላካለች። ስትታዘዝ አሻሮውን ቆልታ ፣ ልብስ ታጥባለች፤ እንጀራውን ጋግራ ሌላ እንጀራ ፍለጋ ከምገባ ማዕከሉ ትደርሳለች። የተሰጣትን አንድ እንጀራ በወጥ ይዛ ልጇቿን ታቃምሳለች።
ይህ ብቻ አይበቃትም ለነገው ሆድ ነገን ታስባለች። ከዛም ባሻገር ያለው ነገ ያስጨንቃታል። ሕይወት በፋንቱ ቤት እንዲህ ቀጥሏል። ትናንት ብዙ አልፏል። ነገ ስለሚሆነው አታውቅም። ሁሌም በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆና ተስፋ ታደርጋለች። ተስፋ ትናንትን አልፋበታለች፣ ዛሬን ኖራበታለች፣ ነገን ታልምበታለች።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ኅዳር 10/ 2015 ዓ.ም