
ባሌሮቤ፦ በአርሶ አደሮች መካከል ፉክክርን የሚያስተናግድ የገበያ ሥርዓት አለመፈጠሩ ከፍተኛ ቅሬታ እየፈጠረ መሆኑ ተገለጸ።
በኦሮሚያ ክልል ከህዳር 22 እስከ 23 ቀን 2011ዓ.ም የሚከበረው የአርሶ አደሮች የመስክ ቀን በባሌሮቤ ዞን ሲናና ወረዳ በተከበረበት ወቅት አርሶ አደር ሃጂ የቦ እንደገለጹት፤ በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ የስንዴ ምርት ቢኖርም በአርሶ አደሮች መካከል ያለውን ፉክክር የሚያስተናግድ የገበያ ሥርዓት ባለመፈጠሩ በምርታማነት ላይ ጫና ማሳደሩን ጠቁመዋል።
እንደ አቶ ሃጂ የቦ ገለጻ፤ በዓመት እስከ 200 ኩንታል ስንዴ ቢያመርቱም፤ ገበያው ጥራት ያለውን ሆነ ደረጃው የወረደ ስንዴን በገበያ ላይ የዋጋ ልዩነት ባለመኖሩ በአርሶ አደሩ መካከል ያለውን ፉክክር ቀንሶታል። በምርታማነት ላይም ጫና እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል።
የሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል፤ የምርምር ስርጸት የሥራ ሂደት ባለቤት አቶ አማረ ቢፍቱ በበኩላቸው፤ አርሶ አደሮች የምግብ ዋስትናቸውን አረጋግጠው ምርትን በስፋት ለገበያ ቢያቀርቡም በፍትሃዊነት የሚዳኝ የገበያ ሥርዓት ባለመኖሩ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው። ለአብነትም በኢትዮጵያ የቡና ደረጃ በመውጣቱ አርሶ አደሮች ጥራት ያለውን ምርት ለማምረት ፉክክር እያደረጉ ነው። ለስንዴም ደረጃ በማውጣት ተመሳሳይ ሥርዓት ቢኖር ይህ ፉክክር ይፈጠራል ብለዋል።
ከውጭ አገር የሚገቡ የስንዴ ምርቶች የፕሮቲን መጠናቸው ከ12 በመቶ እንደማይበልጥ ጠቁመው፤ በባሌ አካባቢ እስከ 15 በመቶ ፕሮቲን ያለው የፓስታ እና የማኮሮኒ ስንዴ በስፋት እየተመረተ ነው። ይሁንና ይህን ጥራት ያለው ስንዴ በተገቢው ዋጋ ለመሸጥ የሚያስችል የፖሊሲና የስንዴ ገበያ ሥርዓት ባለመዘርጋቱ፤ በከፍተኛ ትጋትና ጥንቃቄ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ላይ ጫና ፈጥሯል። የገበያና ምርታማነት ፉክክር እንዳይጨምርም እያደረገ መሆኑን በመጠቆም እልባት እንዲበጅ አሳስበዋል።
የኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢስሞ ፤ የአርሶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ አያሌ ተግባራት ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ በዚህ መሠረት በርካታ ለውጦች እየተመዘገቡ ቢሆንም በገበያ ሥርዓቱ በአርሶ አደሮች ዘንድ ፉክክር ለመፍጠር የሚያስችል ባለመሆኑ ቅሬታ እያስተናገደ መሆኑን ጠቁመዋል። በመሆኑም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር መፍትሄ ለማበጀት ተገቢው ሥራ ይከናወናል ብለዋል።
ከሲናና የግብርና ምርምር ማዕከል የተገኘው መረጃ እንደሚያሳየው፤ በባሌ ዞን ከመቶ ሺ ሄከታር በላይ መሬት በስንዴ ምርት እየተሸፈነ ሲሆን በአማካይ በሄክታር ከ45 እስከ 50 ኩንታል ስንዴ ይመረታል።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር