ከህዳር 1 ቀን 2015 ዓ.መ ጀምሮ ለሶስት ቀናት ለህዝብ ክፍት ሆኖ የቆየው በኢትዮጵያ የተካሄደው የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ የዘርፉን ተዋናዮች ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ ጎብኝዎችንም ቀልብ የሳበ እንደነበር በማጠቃለያ ፕሮግራሙ ላይ ተገልጿል።በህብረቀለማቸው የሚያምሩ የተለያዩ የከበሩ ማዕድናትና ጌጣጌጦችን ይዘው በኤክስፖው ላይ የቀረቡትም ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚገኘው የማዕድን ሀብት ለጎብኝዎች በማስረዳትና በማስተዋወቅ ጭምር ሚናቸውን ሲወጡም ተስተውሏል።እንዲህ በኤክስፖው ሚናቸውን ሲወጡ ከነበሩት መካከል ደግሞ ሶዞ የተባለው የማዕድን ጌጣጌጥ ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ይጠቀሳል።
የኩባንያው ባለቤት ወይዘሮ ባንቻለም ማሩ በኤክስፖው ስለነበራቸው የሶስት ቀናት ቆይታቸው እንደገለጹልን ፤ኩባንያቸው እሴት የተጨመረባቸውን የማዕድን ውጤቶች ለገበያ ለማቅረብ ብቻ ሳይሆን፣ የ15 አመት የሥራ ተሞክሮውንም ለሌሎች ልምድ ይሆናል፣ እግረመንገድም የኢትዮጵያን የማዕድን ሀብት ከውጭ ለሚመጣው ለማስተዋወቅ በሚል እሳቤ ነው ኤክስፖው ላይ የተሳተፈው።ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የተለያዩ የከበሩ ማዕድናት ሀብት ባለቤት ስለመሆኗ የማያውቁ ዜጎች መኖራቸውን ለመገንዘብ ችለዋል።ለብዙዎች በማስረዳትና ለጥያቄዎቻቸውም ምላሽ በመስጠት ጭምር ሚናቸውን ሲወጡ ነበር።ኤክስፖው እንዲህ ያለውን እድል በመፍጠሩ ብዙዎችንም በዘርፉ ለመሰማራት የሚያነሳሳ ግንዛቤ ያስጨበጠ ሆኖ አግኝተውታል።
ኢትዮጵያ ሰፊ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ሊሰማራበት የሚችል የማዕድን ሀብት ባለቤት እንደሆነች በዘርፉ በሥራ በቆዩባቸው አመታት ለመረዳት መቻላቸውን የሚናገሩት ወይዘሮ ባንቻለም ትውልዱ ስለሀገሩ ሀብት አውቆና ተገንዝቦ በሥራውም የሚሰማራበት ምቹ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት ያምናሉ።በዘርፉ የሚሰማራ ኢትዮጵያዊ በቁጥር ሲበዛ በዓለም ገበያ ላይ ተጽዕኖ መፍጠር እንደሚቻልም ገልጸዋል።እርሳቸው እንዳሉት እስካሁን ባለው ተሞክሮ በዓለም ገበያ ላይ ዋጋውን እየወሰኑ ያሉት የማዕድኑ ባለቤቶች ኢትዮጵያውያን ሳይሆኑ፣ ገዥዎቹ ናቸው።ይህ አካሄድ ደግሞ ማዕድን አልሚውን፣ እሴት ጨምሮ ለገበያ የሚያቀርበውንም ሆነ ሀገርንም በገቢ ተጠቃሚ እያደረገ አይደለም።ልማቱን በጋራ በማጠናከርና በቴክኖሎጂ አግዞ ማከናወን ሲቻል የገዥዎችን ተጽእኖ ማስቀረትና የሀገርንም ጥቅም ማስጠበቅ ይቻላል።እንዲህ ያለው ኤክስፖም አቅም በመፍጠር ከፍተኛ ሚና አለው ብለዋል።
ወይዘሮ ባንቻለም፣ ባባታቸው እግር ተተክተው ሥራው ውስጥ ቢገቡም የማዕድን ዘርፍ መልካም ዕድሎችም፣ ተግዳሮቶችንም እንዳሉት በ15 አመት ተሞክሮአቸው አይተዋል።እርሳቸው እንዳሉት ስለማዕድን አይነቶች ማወቅና ዘርፉን በእውቅት መምራት አንዱ ክፍተት ወይንም ተግዳሮት ሲሆን፣ ገበያ መፈለግ ደግሞ ሌላው ችግር ነው።ተምሮ እራስን ለማብቃት በሀገር ውስጥ በዘርፉ የሚሰጥ ትምህርት አለመኖርም ፈተና ነበር የሆነባቸው።ከቤተሰብ የወረሱትና በፍላጎትም የገቡበት ዘርፍ በመሆኑ በድረገጽ (ኦንላይን) ትምህርት በመከታተል እራሳቸውን በማብቃት እስካሁን በዘርፉ ለመቆየት ችለዋል።እርሳቸውም ለልጃቸው እውቀት በማካፈልና ስለሥራው ግንዛቤ እንዲኖረው ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።መልካም እድል ብለው ከጠቀሷቸው መካከል ደግሞ የራስን ሀብት (ካፒታል) ለመፍጠር የሚያስችል መሆኑን ነው።በተለያዩ የዓለም ሀገራት በሚካሄዱ የማዕድን ኤክስፖዎች ላይ በመሳተፍ በተገኘ ልምድ ሀብቱን ለገበያ ከማቅረብ ወደጌጣጌጥ በመቀየር የዓለም ገበያ ፍላጎትን ለማሟላት የሚደረገው ጥረትም ሌላው የአቅም ማሳደጊያ መንገድ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።ወይዘሮ ባንቻለም ‹‹ከተኛንበት እንንቃ›› በማለት በዘርፉ ላይ የሚገኘውም አዲስ ለመሰማራት ፍላጎት ያለውም በጋራ ተባብሮ ዘርፉን በማሳደግ እራሱንም ሀገርንም ተጠቃሚ እንዲያደረግ መልእክት አስተላልፈዋል።ኢትዮጵያ ወደ ሀብትነት የሚቀየርና ኢኮኖሚዋንም ከፍ ሊያደረግ የሚችል የምድር ውስጥ ፀጋ እያላት መጠቀም ባለመቻሏ በእድገት ወደኃላ መቅረቷ እንዲህ ቁጭት እየፈጠረ መሆኑን ነው ከወይዘሮ ባንቻለም መልእክት መገንዘብ የሚቻለው።
ኢትዮጵያ በሀብት ላይ ሆና የሀብቱ ተጠቃሚ መሆን አለመቻሏ ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ላይ የማዕድን ውጤቶች በሆኑ በአንዳንድ ዘርፎች ላይ እየገጠማት ያለው የአቅርቦትና የዋጋ መናር ፈተና የበለጠ ቁጭትን እየፈጠረ እንደሆነ ኤክስፖውን ያዘጋጀው ማእድን ሚኒስቴር ባካሄደው የኤክስፖ ማጠቃለያ መርሃግብር ላይ በአንዳንድ ተሳታፊዎች ተነስቷል።መርሃግብሩ የተካሄደው የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሺዴ፣ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመነት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ፣ በተገኙበት ሲሆን የተለያዩ ጥያቄዎችም ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
በመርሃግብሩ ተሳታፊ ከነበሩት የግልና የምንግሥት ተቋማት አንዱ ሜድሮክ ኢትዮጵያ ሲሆን፣ የኩባንያው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጀማል አህመድ በዚሁ ወቅት፤ መንግሥት ማዕድንን የብልጽግና ምንጭ ነው ብሎ አቋም መውሰዱ አግባብ እንደሆነና በተግባር የሚታይ ለውጥ ዘርፉ ላይ እያሳየ መሆኑን አመልክተዋል።በተለይም ዘርፉን እየመራ የሚገኘው ማዕድን ሚኒስቴር ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ከተጠናከረና ክልሎችም ከታገዙ በሀገር ደረጃ በዘርፉ ከፍተኛ ለውጥ እንደሚመጣ ተስፋ አድርገዋል።ግብርናውም ሆነ የኢንደስትሪ ዘርፉ ግብአቶችን የሚወስደው ወይንም የሚያገኘው ከማዕድን እንደሆነም አመልክተዋል።የግንባታው ዘርፍ ደግሞ ዋና መሠረቱ ማዕድን እንደሆነ መዘንጋት እንደሌለበትም ገልጸዋል።ግብአቱን ሀገር ውስጥ በሚገኝ ሀብት መጠቀም እየተቻለ ሙሉ ለሙሉ ከውጭ በሚከናወን ግዥ ጥቅም ላይ እየዋለ መሆኑን አስታውሰዋል።በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለይቶ መፍትሄ በመስጠት በተጠቃሚነት ላይ መሰራት እንዳለበት ሀሳብ ሰጥተዋል።
አቶ ጀማል እንዳስረዱት በአሁኑ ጊዜ ለግንባታው ዘርፍ የሚውሉ ግብአቶች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎችም የማዕድን ውጤቶች በሆኑ በሚሰሩት ላይም ተግዳሮት እያጋጠመ ነው።ለአብነትም እንዳነሱት እያንዳንዳቸው አምራች ፋብሪካዎች ለማሞቂያ የሚውል ኃይል የሚጠቀሙበት ግብአት በውጭ ምንዛሪ ተገዝቶ ሀገር ውስጥ በሚገባ ፈርነስኦይል በተባለ የማዕድን ግብአት ነው።ይሄንን ሙሉ ለሙሉ በሀገር ውስጥ መተካት የሚያስችል እምቅ ሀብት ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኛል።ሀብቱ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣ ከፀጥታ፣ ከመሬት አቅርቦት በአጠቃላይ ከመሠረተልማት ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመፍታት ለአምራች ኢንደስትሪዎቹ ጥቅም በሚሰጥ መልኩ እሴት በመጨመር ተዘጋጅቶ በፍጥነት ለማቅረብ ጥረት መደረግ ይኖርበታል።
አቶ ጀማል ከወርቅ ማዕድን ጋር በተያያዘም እንደገለጹት፣ እስካሁን ባለው ተሞክሮ በወርቅ ማዕድን እርሳቸው ከሚመሩት ኩባንያ ውጭ ያሉት ምርታማነታቸው ከአቅምበታች ነው።እነዚህን አነስተኛ ወርቅ አምራቾች አቅም በማሳደግ ምርቱ ከፍ እንዲል ማድረግ ከመንግሥት ይጠበቃል።ወደ ማምረት ለመሸጋገር በሂደት ላይ የሚገኙትም ቢሆኑ በፖሊሲና በተለያየ መንገድ የመንግሥት ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል።የሀገር ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከውጭ የሚመጣው ባለሀብት ተግዳሮቶችን ተሸክሞ የሚጓዝ እንዳልሆነም መረዳት ያስፈልጋል።ኢትዮጵያዊው ባለሀብት ሌላ ሀገር ስለሌለው ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ለመሥራት ዝግጁ ነው።ይህን ዝግጁ የሆነ ባለሀብት ደግሞ ከውስጥ አስተዳደር ጀምሮ በተለያየ መንገድ በአቅም ግንባታ በማጠናከር ደግፎ ውጤታማ ማድረግ ይጠበቃል።በዚህ ረገድ ያለውን የቤት ሥራ ለመወጣት በመንግሥት በኩል ስላለው የቤት ሥራ በእለቱ ለተገኙት ለገንዘብ ሚኒስትሩና ለሌሎቹም ጥያቄ አቅርበዋል።
የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርን ወክለው የተገኙት ተሳታፊም በሰጡት ሀሳብ፤ ሲሚንቶና ለግንባታ ማጠናቀቂያ የሚውሉ ሴራሚክ የመሳሰሉ ግብአቶችን በመጠቀም የግንባታው ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ ይወስዳል።ኢኮኖሚው እያደገ ሲሄድ፣ የሲሚንቶ ፍጆታውም አብሮ ያድጋል።አሁን ሀገር በምትገኝበት የኢኮኖሚ የእድገት ደረጃ የሲሚንቶ አቀርቦትና ግንባታው የሚፈልገው ግብአት የሚጣጣም ሆኖ አልተገኘም።በዚህ የተነሳም ትላልቅ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የግንባታ እንቅስቃሴ ፈተና ውስጥ ወድቋል።እንደ ተወካዩ ሀሳብ ይህ ችግር የተፈጠረው ኢትዮጵያ ውስጥ 98 በመቶ የሚሆን ለሲሚንቶ ግብአት የሚውል ሀብት እያለ ነው።የግብአት እጥረት ሊያጋጥም ቀርቶ በዋጋም ቢሆን ባነሰ ሽያጭ መገኘት መቻል ነበረበት።ይህ ሳይሆን ቀርቶ ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ላይ በፋብሪካ የሲሚንቶ የመሸጫ ዋጋ በሌላው ዓለም ላይ ከሚሸጠው ጋር እንኳን ለውድድር የሚቀርብ አይደለም።እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ነው።በሚቀጥለው አስር አመት በኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ የግንባታው ዘርፍ መፋጠን ወሳኝ ነው።ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋ አድጎ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገራት መካከል አንዷ ሆና ለመገኘት የግንባታው ዘርፍ ወሳኝ ነው።የግብርናውም ሆነ የቱሪዝም ኢንደስትሪው፣ ሌላውም ከግንባታ ጋር ይያያዛል።እንደ ሴራሚክ ለመሳሰሉ የግንባታ ማጠናቀቂያዎች የሚውል ጥሬ ሀብት ኢትዮጵያ ውስጥ እያለ በግዥ ከውጭ ገብቶ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።የሲሚንቶ ፍላጎትን ማሟላት የሚችል አቅም እየፈጠረች ስላለችው ጎረቤት ሀገር ኬኒያንም ለአብነት ጠቅሰዋል።ከወዲሁ ካልታሰበበት ወደፊት በእቅድ የተያዙ የግንባታ የልማት እቅዶች እንዳይስተጓጎሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።በጋራ በመሥራት ክፍተቶችን ለመሙላት እየተደረገ ስላለው ጥረትም ጥያቄ አቅርበዋል።
ሌሎችም ተሳታፊ የኩባንያ ባለቤቶች በዘርፉ ላይ ያሉ ማነቆዎችንና ክፍተቶችን አንስተዋል።አንዳንዶችም መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ትኩረት በማጠናከር ለተሻለ ውጤት እንዲሰራ ጠይቀዋል።በዘርፉ ላይ የሚኘውም ባለሀብት በተበታተነና በተበጣጠሰ መንገድ ከሚንቀሳቀቀስ ተደራጅቶ አቅም ፈጥሮ በጋራ እድገት የሚያስመዘግብበትን ሁኔታ ቢፈጥርና በዚህ ረገድም መንግሥት እገዛ ቢያደርግ መልካም እንደሆነ ሀሳብ ቀርቧል።
መንግሥትን ወክለው የተገኙትም ከፍተኛ አመራሮች የየድርሻቸውን የቤት ሥራ መውሰዳቸውን በምላሻቸው አረጋግጠዋል። የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሀብቶች በተለይም ወቅታዊ በሆኑና በተለያዩ ምክንያቶች ባጋጠሙ ችግሮች ውስጥ ጫናዎችን ተቋቁመው ከፍተኛ ሥራ እየሰሩ የሚገኙ ኩባንያዎች መደገፍ አለባቸው በሚል ከአንዳንድ ተሳታፊዎች የቀረበው ሀሳብ ተገቢነት ያለው መሆኑን ገልጸዋል።በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ውጤታማ ሥራ የሰሩት መደገፍ አለባቸው ተብሎ የተነሳው ሀሳብ በመንግሥትም የታመነበት ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል።ኢንቨስትመንት እንዲበረታታና የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን መንግሥት የሚችለውን ሁሉ የሚያደርግና የሚደግፍ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ እንደተናገሩት ኮሚሽኑ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ያበረታታል። ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያም እንዲያቀርቡ፣ ግብአቶችንም ከውጭ ወደ ሀገር እንዲያስገቡ የሚገጥማቸውንም ተግዳሮት በመፍታት፣ ለውጭ ኢንቨስተሮችም ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ኮሚሽኑ የሚጠበቅበትን ተልእኮ ለመወጣት ዝግጁ ነው።
የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ ባለሀብቱ ሰብሰብ ብሎ አቅም ቢፈጥር የተሻለ ውጤት ሊመዘገብ ይችላል በሚል ከተሳታፊዎች የቀረበውን ሀሳብ ተጋርተዋል።ዘላቂ የሆነና ሀገር የምትኮራበት ልማት ሊመዘገብ የሚችለው የሀገር ውስጥ ባለሀብት በሚያደርገው ጥረት እንደሆነም ገልጸዋል። በአስተያየትና በጥያቄ የቀረቡት አንዳንድ ሀሳቦች መንግሥት የሚወስዳቸው የቤት ሥራዎች መሆናቸውንም አመልክተዋል።
የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ዑማ፤ እንደሀገር በግብርናውና በሌሎችም የክፍለኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የተመዘገቡትን ውጤቶች በማዕድን ዘርፍም የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ ጥረቶች ተጠናክረዋል። የማዕድን ዘርፉ አሁን ላይ ለክፍለኢኮኖሚው እያበረከተ ካለው የአንድ በመቶ ድርሻ በሚቀጥሉት 14 እና 15 አመታት ከ17 በመቶ በላይ ድርሻ እንደሚያበረክት ይጠበቃል።ለስኬታማነቱም የፖሊሲ ማሻሻያ እርምጃዎችን ከመውሰድ ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል። በመከናወንም ላይ ይገኛል።
ማዕድን ውድና በክፍለኢኮኖሚ እድገት ላይ ለውጥ የሚያስገኝ ስለመሆኑ እንዲህ በተለያዩ የምንግሥት ሀላፊዎችና በዘርፉ ተዋናዮች ተነስቷል። አላቂ የሆነውን ይህን ውድ ሀብት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የአመራረት ዘዴ በመታገዝ ከብክነት ማዳን፣ ለህገወጥ ተጋላጭነቱን ማስቀረት፣ የግጭት መንስኤም እንዳይሆን መሥራት ይጠበቃል።የማዕድን አምራቾች፣ ላኪዎች፣ አማካሪዎችና ሌሎችንም የዘርፉ ተዋናዮች ካሳተፈው የማዕድንና ቴክኖሎጂ ዓለምአቀፍ ኤክስፖ የተገኙትን መልካም ተሞክሮዎች በመቀመር በሚቀጥለው ጊዜ በተሻለ ለማዘጋጀት ማቀዱን ማዕድን ሚኒስቴር አረጋግጧል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ኅዳር 9/ 2015 ዓ.ም