ሰሞኑን በእጄ የገባውን የታዋቂዊ አሜሪካዊ የፖለቲካ ሳይንቲስት ፍራንሲስ ፉኩያማን በባህላዊ ወረት/Cultural Capital/ላይ በጥልቀት ትንታኔ የሚያደርግና ሞጋች ማለፊያ መጽሐፍ ፤ “The Great Disruption እያነበብሁ፤ በዚሁ ጋዜጣ ባህላዊ ወረቶቻችን በአግባቡ ስራ ላይ ከዋሉ ለእርቅ፣ ለመደመርና ለሀገራዊ ምክክር ያላቸውን ፋይዳ ያመላከትሁባቸውን መጣጥፎች አስታውሼ የሰሞኑን የሰላም ስምምነት ለማዝለቅ ያላቸውን የማይተካ ፋይዳ ለማነሳሳት ጉድ ጉድ ስል ፤ ዛሬም የባህላዊ ወረቶቻችን እንጥፍጣፊ ከኢትዮጵያዊነት ጽዋ ጨርሶ አለመድረቁን አረጋገጥሁ። ቀደም ሲልም በተለያዩ እጅን በአፍ በሚያስጭኑ ሰናይ ተግባራት ዛሬም አብሮነታችን ከጎሳ፣ ከሃይማኖትና ከሌላ ማንነት በላይ መሆኑን አረጋግጠውልኝ ተስፋየን ሲያለመልሙት ቢባጁም ሰሞነኛው ክስተት ግን የተለየ ነው። ምንም እንኳ ሚዲያዎቻችን ባላየ ባልሰማ ቢያልፉትም።
ሰሞኑን ኮሜዲያን እሸቱ መለሰ በካሊፎርኒያ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ለሚገነባ ዘርፈ ብዙ ግልጋሎት የሚሰጥ ተቋም እርስት መግዣ በዩቲውብ በቀጥታ ስርጭት 1 ሚሊየን ዶላር ለማሰባሰብ ሲነሳ ኢትዮጵያውያን ከሀገር ቤትና ከመላው ዓለም ኦርቶዶክስ፣ እስላም፣ ፕሮቴስታንትና ዋቄ ፈና ሳይሉ፤ አማራ ፣ ትግሬ ፣ ኦሮሞ፣ አፋር ፣ ሶማሌና ሌላ ሳይሉ ፤ ሀብታምና ድሀ ሳይሉ፤ ከአረብ ሀገር የቤት ሰራተኛ እስከ ተሳካለት ዲያስፓራ ፤ ኢትዮጵያዊና ኤርትራዊ ሳይሉ በመረባረብ አሳክተውታል። ይህ ዛሬም ከጥንት ሲወራረሱ የመጡ ባህላዊ ወረቶቻችን ተዳፈኑ እንጂ አልጠፉም ብሎ አፍን ሞልቶ ለመናገር የሚያስደፍር ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ኮሜዲያን እሸቱ የባህላዊ ወረቶቻችንን ዕምቅ አቅም ገላልጦ አሳይቶናል። በዚህ ላይ መጨመር የሀገሬው ኃላፊነት ነው።
ባለፉት ሁለት አመታትም ሆነ ከዚያ በፊት በሀገራችን የሆነውን ሰቆቃና ግፍ መለስ ብሎ አስታውሶ የሰሞኑን የኮሜዲያን እሸቱን አርዓያነት ያለው ተግባር በአንክሮ ላስተዋለ ኢትዮጵያ እውነትም ቅኔ ፣ ሰምና ወርቅ ናት ቢል አልተሳሳተም። ኢትዮጵያዊነት ከየትኛውም ማንነት በላይ መሆኑን ኮሜዲያን እሸቱና በሰሞኑን ሰናይ ተግባር የተሳተፉ መላ ኢትዮጵያውያን እማኝ ናቸው። ዳሩ ግን ባለፉት ጥቂት አመታትም ሆነ ከዚያ በፊት አንገታችንን የሚያስደፉ የጭካኔና የግፍ ጥጎችን ታዝበናል። እዚህ ማህበራዊ ቀውስና ስብራት ላይ የደረስነው ግን በአንድ ጀንበር አይደለም። ቢያንስ ላለፉት 50 አመታት ባህላዊ ወረቶቻችን በመሸርሸራቸው ነው እዚህ ላይ የደረስነው።
በነገራችን ላይ ከፍ ብዬ በጠቀስሁት የፉክያማ መጽሐፍ የሰው ልጅ አኩሪ ወጉንና ባህሉን እያጣ የመጣው ከኢንዱስትሪ አብዮት ማግስት ጀምሮ ነው። በዚህ ተጽዕኖ ያልተነካ ሀገር የለም። መተማን ፣ መተሳሰብ ፣ መረዳዳት ፤ ትዳር መያዝ ቤተሰብ መመስረት እየተቀዛቀዘ ፤ ፍቺ እየተበራከተ፤ ልጆች ከጋብቻ ውጭ እየተወለዱ፤ ዕምነትንና ሃይማኖትን ማጥበቅ እንደ ኋላቀርነት እየተቆጠረ፤ የበይነ መረብ መፈጠርን ተከትሎ ልጅ ከወላጅ ፣ ሚስት ከባል እየተራራቁ ፤ በብቸኝነትና በጭንቀት ትውልድ እየተሰቃየ ፤ ትውልዱ ለልቅ ወሲብና ሌላ ሱስ እየተጋለጠ ይገኛል ።
ሕዝብ በመንግስት ተቋማት ላይ እምነት እያጣ ፤ ግለሰብ ለግለሰብ አልተማመን እያለ መሆኑን በዚሁ መጽሐፍ በመረጃ ተደግፎ በስፋት ተተንትኗል። ከ70 አመታት በፊት በመንግስት ተቋማት ላይ አሜሪካውያን የነበራቸው ዕምነት 70ና80 በመቶ ይደርስ ነበር። ዛሬ ላይ ግን ወደ 20ና 30 በመቶ አሽቆልቁሏል። ዛሬ ላይ ከመራጩ ግማሹ በተለይ የትራምፕ ደጋፊ የ2020 ምርጫ ተጭበርብሯል ብሎ የሚያምን ነው። ከአራት አሜሪካውያን ሶስቱ የአሜሪካ መደበኛ ሚዲያዎችን አያምኑም።
በሀገራችን ያለውን ሁኔታ ለመግለጽ ጥናት የሚጠይቅ ቢሆንም፤ ዜጎች በመንግስት ተቋማት ላይ የነበራቸው ዕምነት ከአንዳንዶች በስተቀር እየተሸረሸረ መሆኑን ለመናገር ሞራ ገላጭ መሆንን አይጠይቅም። ዛሬ በሀገራችን እየተስተዋሉ ያሉ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውሶች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከባህላዊ ወረቶቻችን ኪሳራ ጋር የሚያያዙ ናቸው። የሀገር ሕዳሴም ሆነ ብልጽግና ያለ ባህላዊ ወረቶቻችን ህዳሴና ትንሳኤ እውን ሊሆን አይችልምና በዚህ ረገድ ብዙ ስራ ይጠበቅብናል። የግብረ ገብ ትምህርት መጀመሩ፤ ስርዓተ ትምህርቱ ላይ የተደረጉ ለውጦች፤ በሃይማኖት ተቋማት ተሓድሶና አጠቃላይ ማህበረሰባዊ ውጤት ካልታገዘ መጭው ዘመን ከዚህ የከፋ እንደሚሆን ልብ ማለት ያሻል።
ሰሞኑን በፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪካ በሕወሓትና በኢፌዴሪ መንግስት በቀድሞዎቹ የናይጀሪያና የኬኒያ ፕሬዝዳንቶች አደራዳሪነት ስለተደረሰው የሰላም ስምምነት ሳብሰለስል፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በተለይም ላለፉት ሁለት አመታት በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል የተካሄደውን ጦርነት ጨምሮ የተለያዩ ጽንፈኝ ሀይሎች የፈጸሟቸውን ለጆሮ የሚቀፉ፣ ለመስማት የሚከብዱ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችን እና ነውሮችን እያሰብኩ ነው ። በየተቋማት የተንሰራፋውን ብልሹ አሰራርና ሙስና፤ የግብይት ስርዓቱ መገለጫ እየሆነ የመጣውን ገፈፋ ፤ በንግዱ ማህበረሰቡ እየተስተዋለ ያለውን ስግብግብነትና አልጠግብ ባይነትና የስነ ምግባር ችግር ባስተዋልሁ ቁጥር ሀገር በተቋምና በሕግ ብቻ እንደማይቆም እያረጋገጥሁ ነው።
ከገባንበት ሁለንተናዊ ቀውስ ለማገገምም ሆነ በሀገራችን ዘላቂ ሰላምና አንድነት ለማረጋገጥ የጣልናቸውንና የረሳናቸውን ባህላዊ ወረቶች እንዲያንሰራሩና መልሰው እንዲያቋጠቅጡ ሌት ተቀን መስራት ይጠበቅብናል። ይህን ማድረግ ካልቻልን ብልጽግናችን ሙሉ ሊሆን አይችልም። ለመሆኑ ለሀገራችንና ለተቋማት ስራ አካላት ጤንነት የልብ ትርታ የሆነው ባህላዊ ወረት ምንድን ነው፤
ከዚያ በፊት ባህል ፣ ባህላዊ ወረትስ ምንድን ነው የሚለውን ለመግባቢያ ያህል እንመለከታለን። ባህል ሁሉንም የሚያስማማ የሚያግባባ ወጥ የሆነ ትርጉም ብያኔ ባይኖረውም የአንድ ማህብረሰብ ወይም ሕዝብ ዕምነት፣ ልማድ ፣ ወግ በኪነ ጥበብ እና በስነ ጥበብ ተዳውሮ ፣ ተሸምኖ ፣ ተንሰላስሎ የመገኘት፣ የመገለጥ ዥጉርጉር ሕብራዊ ቀለም ነው። በደስታ፣ በሀዘን፣ በስራ፣ በሃይማኖት፣ በትምህርት ፣ ወዘተ . የሕይወት አንጓዎች ይገለጻል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ባህልን፦ የህብረተሰብ የአኗኗር ዘዴ ፣ ወግ፣ ልማድ፣ እምነት፣ …። በማለት ሲተረጉመው።
የደስታ ተክለ ወልድ የአማርኛ መዝገበ ቃላት በበኩሉ ባህል፦ ልማድ ፣ ደንብ ሲል ይፈታዋል። የእንግሊዘኛው ሜሪያም ዌብስተር መዝገበ ቃላት በበኩሉ ዘርዘር አድርጎ ይተረጉመዋል። ይበልጥ ግልፅ እንዲሆንና የትርጓሜውን ስፋት ለመገንዘብ እንዲረዳ በመገኛ ቋንቋው እንዳለ አስቀምጨዋለሁ።
culture: the beliefs, customs, arts, etc., of a particular society, group, place, or time: a particular society that has its own beliefs, ways of life, art, etc.: a way of thinking, behaving, or working that exists in a place or organization (such as a business)
1 . Cultivation, tillage
2 . The act of developing the intellectual and moral faculties especially by education
3 . Expert care and training <beauty culture>
4 a . Enlightenment and excellence of taste acquired by intellectual and aesthetic training
b . Acquaintance with and taste in fine arts, humanities, and broad aspects of science as distinguished from vocational and technical skills ,
ባህላዊ ወረት ( Cultural capital ) የሚለው ሀረግ ፔሬ ቦርዴው በተባለ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ማብቂያ ላይ የተነሳ የስነ ሕብረተሰብ ተመራማሪ እንደተፈጠረ የተለያዩ የዘርፉ ድርሳናት ያትታሉ። ባህላዊ ንብረት በማህበረሰብ ውስጥ ያለን ተቀባይነት ቦታ ከፍ ለማድረግ ዕውቀትን፣ ፀባይና ክህሎትን የማሳደግ የማካበት ሂደት ነው። ባህላዊ ንብረት በግለሰብ፣ በማህበረሰብ ከፍ ሲልም በሕዝብ በሀገር ይሰላል። የበለፀገ ባህላዊ ንብረት ያካበተ ግለሰብ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ከፍ እንደሚያደርገው ሁሉ ያደገ የለማ ባህላዊ ንብረት ያለው ማህበረሰብ ሕዝብ በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍ ያለ ተቀባይነት ይኖረዋል።
ባህል ማለትም የህብረተሰብ የአኗኗር ዘዴ ፣ ወግ ፣ ልማድ፣ እምነት ፣ ወዘተ . በሂደት በዕውቀትና በክህሎት እየበለፀገ፣ እየዳበረ ሲሄድ ለሀገር ሰላም ፣ አንድነት ከፍ ሲልም እድገት የላቀ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በተቃራኒው ባህል በዕውቀት ፣ በክህሎት ካልበለፀገ አይደለም ለሀገር ሰላምና ዕድገት መዋል ይቅርና የማህበረሰቡን እሴቶች ጠብቆ ማቆየት ካለማስቻሉ ባሻገር የዕለት ተዕለት ችግሮችን እንኳ መፍታት የሚሳነው ይሆናል። ባህላዊ ወረት እንደ ኢኮኖሚያዊ ወረት ማለትም ገንዘብ በአግባቡ ኢንቨስት ተደርጎ ሰላምን፣ ፍቅርን ፣ እርቅን ፣ መነጋገርን፣ መቀባበልን ፣ መከባበርን ፣ መተባበርን ፣ አንድነትን፣ ወዘተ . እውን ማድረግ ካልቻል እንደባከነ እንደከሰረ ሊቆጠር ይችላል።
ሀገርን ሕዝብን ከግጭት ፣ ከቀውስ ፣ ከመፈናቀል፣ ከመጠራጠር ፣ ከጥላቻ ፣ ከበቀል ፣ ወዘተ . መታደግ አልቻለማ። እስኪ ለአንድ አፍታ ባህሎቻችንን እምነቶቻችንን ወይም ባህላዊ ወረቶቻችንን ከዚህ አኳይ እንመዝናቸው። ባክነዋል ወይስ በአግባቡ ስራ ላይ ውለዋል ! ? አሁን ከምንገኝበት ሀገራዊ ቁመና አንጻር ባክነዋል ቢባል የሚያስኬድ ይሆናል። ታዲያ እነዚህን ባህላዊ ወረቶቻችንን እንደ ጦር ዕቃ ለብሶ እንደ ጥሩር ደፍቶ መውጣት መግባት ፣ መመላለስ ለምን ተሳነን ! ? መልሱ ቀላል ነው። ላይ ላዩን እንከውናቸዋለን እንጂ አንኖራቸውም።
በቃል እናነበንባቸዋለን እንጂ በልባችን አላተምናቸውም። ”ባለንጀራህን ፣ ጎረቤትህን እንደ ራሳህ ውደድ ”የሚሉ አብርሀማዊ እምነቶችን ማለትም ክርስትናን ፣ እስልምናንና አይሁድን እየተከተልን እንዴት በጥል ግድግዳ ተለያየን ! ? በአንድ አምላክ በዋቄ ፈና እያመን ኢ ሬቻን በየአመቱ እያከበርን እየከወን ይቅር መባባል ለምን ተሳነን !? መልሱን ለማግኘት ሚስጥሩን ለማወቅ ሞራ ማስገለጥ ወይም ኮከብ ማስቆጠር አያሻም። መልሱ ቀላል ነው ። እሱም ባህላዊ ወረቶቻችንን በካዘና ቆልፈን አስቀመጥን እንጂ ስራ ላይ ስላላወልናቸው ( ኢንቨስት ) ስላላደረግናቸው ነው። የሰላም ስምምነቱን ሆነ ሀገራዊ ሰላምና አንድነት በዘላቂነት እውን ለማድረግ የተቆለፈባቸውን ባህላዊ ንብረቶች ከካዘና አውጥቶ በእያንዳንዱ ዜጋ ላይ በፍጥነት ማፍሰስ ኢንቨስት ማድረግ ይጠይቃል ።
በኢኮኖሚክስ አስተምህሮ ባህል ከተፈጥሮ ፣ ከሰውና ከአካላዊ ፣ ቁስ አካላዊ ( physical ) ቀጥሎ 4ኛው ንብረት ሆኖ መጠናት ፣ መተንተን ከጀመረ ከራርሟል ። በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ለሀገር ዕድገትና ለዘላቂ ሰላም አስተዋጾ ያበረክታል ። ሰላም በሌለበት ኢኮኖሚያዊ ዕድገትም ሆነ ብልፅግና ሊታሰብ አይችልምና። ለሀገር ግንባታ በአዎንታዊም ሆነ በአሉታዊ ወሳኝ ሚና ከሚጫወተው ፓለቲካዊና አስተዳደራዊ ስርዓት በተጨማሪ ለዘመናት እንደ ሕዝብ ፣ እንደሀገር አጋምዶ ያቆየን ባህላዊ ወረታችን ነው ።
ሁነቱን ፣ ክዋኔውን ፣ መንፈሱን ጠብቆ ተንከባክቦና አልምቶ ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፍ ፣ ማስቀጠል፣ ማክበርና ማስተዋወቅ ትልቅ ኃላፊነትም አደራም ነው። ሆኖም የመጨረሻ ግብ ሆኖ ግን ሊወሰድ አይገባም። ቱባነቱን እንደጠበቀ ማደግ ዘመንና ትውልድ መዋጀት ይጠበቅበታል። አዎ ! የትውልዱንና የዘመኑን ህፀፅ የሚያርም ለምፅ የሚያነጻ ፣ የሚዋጅ መሆን አለበት ። ዘረኝነትን ፣ ጥላቻን ፣ ቂም በቀልን፣ ደባን ፣ መከፋፈልን ፣ ወዘተ . መቤዥ ፣ መዋጀት አለበት ።
ባህላዊ ወረታችንን ይበልጥ በማጎልበት ፣ በማልማትና በማስፋት ለመጻኢ እድላችን ፣ ለነገ ተስፋችን ፣ ለእርቅ ፣ ለሰላም ፣ ለአንድነት ፣ ለሁለንተናዊ ብልፅግና ፣ ወዘተ . ልናውለው ይገባል። ስኬቶቻችንን የምናወድስበት ፣ ፈተናዎቻችንን የምንሻገርበት ነገአችንን የምንተልምበት ጭምር አድርጎ ስለመጠቀም አብክረን ማሰብ ያስፈልጋል። የፍቅር ፣ የእርቅ፣ የሰላም ፣ የአብሮነት፣ የማካፈል ፣ የመተባበር ፣ የመተጋገዝ ፣ የመረዳዳት ፣ የምስጋና፣ ወዘተ . ባህሎች ፣ ልማዶች ፣ ዕምነቶች፣ ሀይማኖቶች ከፍ ሲልም ድምር ባህላዊ ወረቶች ባለቤት እንዲሁም የጥንታዊት ሀገር ባለቤት ሆነን አንድነትን በመከፋፈል ከሰዋን ፣ ፍቅር ከጎደለን፣ እርቅ ከገፋን ፣ ሰላም ከራቀን፣ አብሮነትን በቀዬአዊት ከተካን፣ ማካፈልን በስስት ከቀየርን፣ መተባበርን በመለያየት ከለወጥን፣ ምስጋናን በእርግማን ከተካን ፣ ወዘተ . ምኑን ሙሉኡ ሆነው !?።
ባለፉት ሶስትና አራት አመታት ያለፍንባቸው ሀገራዊ ውጣ ውረዶች ፣ አሳፋሪ ድርጊቶች እውነት የእነዚህ ሁሉ መንፈሳዊና ባህላዊ ፀጋዎች ባለቤት ስለመሆናችን የሚመሰክሩ ናቸው !? እስኪ ሌሎችን አቆይተን ከአዲሱ አመት ወዲህ እንዲሁም ወደፊት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚከበሩ መንፈሳዊና ባህላዊ ሁነቶች የተሸከሙትን ግዙፍ መልዕክቶችና አንድምታዎች አለፍ አለፍ ብለን እየተመልከትን ሒሳብ እናወራርድ።
ፍቼ ጨምበለላ ፣ ቡሔ ፣ ሻደይ ፣ አሸንዳ ፣ ሶለል አይነ ዋሬ ፣ እንቁጣጣሽ ፣ መስቀል ፣ መስቀላዮ ፣ አጋመ፣ ጊፋታ ፣ ኢ ሬቻን ፣ ጋሮ ፣ ቺሜሪ ፣ ወዘተ . በአንድም በሌላ በኩል በተለያዩ የሀገራችን ማህበረሰቦች የሚከበሩ ሀይማኖታዊ ወይም ባህላዊ ክዋኔዎች ናቸው ። ሁሉም ማለት ይቻላል ተስፋን ፣ ፍቅርን ፣ ነፃነትን ፣ አብሮነትን፣ ምስጋናን ፣ እርቅን፣ ይቅርታን ፣ ወዘተ . የሚያውጁ፣ የሚለፍፉ ናቸው ። ግን በነቂስ ወጥተን ለዘመናት በየአመቱ በአደባባይ የምናከብራቸው የምንዘክራቸውን ያህል በዕለት ተዕለት ኑሮአችን አንኖራቸውም ። አንለማመዳቸውም።
ይሁንና ከገጠሙን ቀውሶች ፣ ፈተናዎች መውጣት ማገገምና ማንሰራራት የቻልነው በቀሩን ሽርፍራፌ እንጥፍጣፌ በባህላዊ ንብረቶቻችን መሆኑን ልብ ይሏል ። በተለይ ባለፉት 30 አመታት ቀን ከሌት እንደ ተሰበከው ልዩነት ፣ ጥላቻና ዘርኝነት ቢሆን ኑሮ እርስ በእርስ ተበላልተናል ። ተጨራርሰናል። ለዚህ ነው መዳኛችን ፣ ማገገሚያችንና ማንሰራሪያችን የሆነውን ባህላዊ ወረት ወደሙላቱ መመለስ ለነገ የሚባል ጉዳይ የማይሆነው ። ባህላዊ ንብረታችን ለበጎ አላማ ሲውል ሀገርን ከጥፋት ከእልቂት እሳት እንደሚታደግ በጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች ተመልክተናል ።
የጋሞ የሀገር ሽማግሌዎች እሳት ጎርሶ እሳት ለብሶ ለበቀል ተነስቶ የነበረውን የአርባ ምንጭና የአካባቢውን ወጣት ለምለም ሳር ይዘው ተንበርክከው በመለመን ቁጣውን አብርደው መልሰውታል። ይህን የሀገር ሽማግሌዎች ገድል በጥሞና ለተረዳው የአርባ ምንጩን እሳት ብቻ አይደለም ያጠፉት የአርባ ምንጩን ጥፋት ተከትሎ በመላ ሀገሪቱ ሊዛመት የነበረውን የበቀል ሰደድ እሳት ጭምር እንጅ ። ቁጣ አብራጁ ይህ የጋም አባቶች ልመና ( ጋሞ ወጋ ) እየጠፋ ፣ ትኩረት እየተነፈገው ያለው ባህላዊ ንብረታችን ተጠብቆ ለትውልድ ሲተላለፍ ሀገርን እንዴት ማዳን እንደሚችል ጥሩ ማሳያ ነው ። የጋሞ አባቶች የ2011 ዓ.ም ልዩ የበጎ ሰው ተሸላሚ መሆናቸው በሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘንድ ያለ አንዳንች ልዩነት ዳር እስከዳር አድናቆትን ተቀባይነትን ያተረፈው በዚህ እሳቤ ነው ።
ሰላምን ፣ ፍቅርን ፣ ይቅርታን ለማነፅ ፣ ለመገንባት ከምንሰጠው ትኩረት ባልተናነሰ በየአካባቢው እንደ ጋሞ ወጋ አይነት የሽምግልና ፣ የእርቅ ባህላዊ ካፒታሎቻችንን ላይም መስራት ይጠበቅብናል ። ከዚህ መሳ ለመሳ የአክራሪነት አዝማሚያ ፣ እኩይ አስተሳሰብ እንዲገታ ብሎም ተሸንፎ ከሰላምና ከእርቅ መንገድ ገለል ፣ ዘወር እንዲል ድልብ የሆኑ ባህላዊ ወረቶቻችን ጥንስስ ፣ እርሾ የማይተካ ሚና አላቸው። ሁሉም ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ባህላዊ ንብረቶች ባለፀጋ ስለሆኑ የየራሳቸውን መዋጮ ማበርከትና ወደ ስራ መግባት ይጠበቅባቸዋል።
በየአካባቢያችን ፣ በየቀዬአችን የምናንፀው ፣ የምናቀነቅነው ከባቢያዊ ብሔርተኝነት ወደ አክራሪነት ፣ ፅንፈኝነት የሚያንደረድር ወደገደል አፋፍ የሚገፋ ስለሆነ እነዚህን ባህላዊ ወረቶች በመጠቀም መግታት ያስፈልጋል ። የዜጎች ማንነት እሴት እንደተከበረ ወደ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የሚያደርሰንን ቀና መንገድ በቅንነት መቀላቀል ፣ መያያዝ ይገባል። ይህ ሀገራዊ ብሔርተኝነትም ከገደቡ ፣ ከውሃ ልኩ እንዳያልፍ ጥንቃቄ ማድረጉ እንዳለ ሆኖ ። አይደለም ዘውጌአዊ፣ ወንዜአዊ ብሔርተኝነት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት በአግባቡ ካልተያዘ ፤ የጎረቤቱን የሚጎመጅ ፣ የሚመኝ ፣ የሚመቀኝ ሆኖ የመውጣት አደጋ ስላለው በብልሀት ፣ በማስተዋል ሊቀነቀን ይገባል። በዛድባሬ ይመራ የነበረው “ የታላቋ ሶማሊያ “ አክራሪ ብሔርተኝነት ለዚህ ጥሩ አብነት ነው ።
ባህላዊ ወረቶቻችንን መልሰን እናልማ !
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ኅዳር 9/ 2015 ዓ.ም