የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ከማረጋገጥ አንፃር በየትኛውም ክፍለ ዓለም እየተሰራ ያለው ስራ በቂ ነው ማለት አይቻልም። ይህም ሆኖ ግን በርካታ ስራዎች በተለያዩ መንገዶች እየተሰሩ መሆኑ ደግሞ አይካድም። በኢትዮጵያም የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ከማጉላት አንፃር በየዘርፉ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ግልፅ ነው። ነገር ግን በተለይ ሴቶች ድምፃቸው እንዲሰማና እነርሱን የሚመለከቱ ዘገባዎች በተለያዩ መንገዶች እንዲቀርቡ እየተሰራ ያለው ስራ አሁንም በቂ እንዳልሆነ ይነገራል።
ጋዜጠኛና የሴት መገናኛ ብዙሃን ማህበር ነባር አባል ፀጋ ታሪኩ እንደምትናገረው በስርዓተ ፆታ እኩልነት ዙሪያ የመገናኛ ብዙሃን ምንም አይነት ሚና አልተጫወቱም ማለት አይቻልም። ነገር ግን ከብዛታቸው አንፃር የስርዓተ ፆታ እኩልነት እንዲያረጋግጡ ከፍተኛ ሚና ይጠበቅባቸዋል። በተቻለ መጠን በሚሰሯቸውና በሚያስተላልፏቸው ፕሮግራሞች ውስጥ ለስርዓተ ፆታ በቂ ጊዜ በመመደብ በሴቶች ጉዳይ ዙሪያ በማህረሰቡ ውስጥ ያሉ የተዛቡ አመለካከቶችን በመቅረፍ ብዙ ስራዎች ሊሰሩ ይገባል።
አንዳንድ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ያላቸውን አምድና የአየር ሰዓት ለስርዓተ ፆታ ጉዳይ በማመቻቸቱ በኩል ክፍተቶች ቢኖሩም ሌሎች በሚሰሯቸው ዘገባዎች ውስጥ የሴቶችን ጉዳይ አካተው ሲሰሩ ይታያል ትላለች።
ከዚህ ውጭ በዜናዎች፣ በፕሮግራሞች፣ በአምዶችና በሚነሱ ወቅታዊ የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ውስጥ ሴቶች ሃሳብ እንዲኖራቸው ወይም የስርዓተ ፆታ ጉዳይ ተካታች እንዲሆን ምን እየሰሩ እንደሆነም ለማየት ተሞክሯል። በዚህም በአሁኑ ጊዜ ከስርአተ ፆታ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተሻሉ አማራጮችና ስራዎች እንዳሉ ተመላክቷል።
ይሁንና አሁንም ድረስ የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ከማረጋገጥና በስርዓተ ፆታ ዙሪያ የሚታዩ የተዛቡ አመለካከቶችን ከመቅረፍ አኳያ ብዙ ይቀራል። መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ባለቤቶች እንዲሁም ሃላፊዎች የስርዓተ ፆታ እኩልነት ጉዳይን ዋነኛ ትኩረታቸው አድርገው መስራትና አንዳንዴ ደግሞ በሚሰሯቸው ፕሮግራሞች፣ አምዶችና ዜናዎች ውስጥ የሴቶችን ጉዳይ አካታች አድርገው መስራት እንዳለባቸውን በዚህ ረገድስ ሚናቸው ምን ሊሆን እንደሚችል ለመለየት ተሞክሯል።
ከዚህ በመነሳት ከመንግስት በኩል በፖሊሲ ደረጃ የስርዓተ ፆታ ስራ በመንግስት ተቋማት ውስጥ በመደበኛነት እንዲሰራበት መደረጉንና በመንግስት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ውስጥ ቢሮ ተቋቁሞለት እንደ አንድ የስራ ዘርፍ ሆኖ እየተሰራበት መሆኑን ነው ጋዜጠኛ ፀጋ የምትናገረው።
ነገር ግን አብዛኛዎቹ ተቋማት ራሱን የቻለ የስርዓተ ፆታ ጉዳይን የሚመለከት ዴስክ ወይም ቢሮ እንዲኖራቸው ስራ መሰራት እንዳለበትም ነው የምትጠቁመው። ከዚህ ባለፈ መንግስት በመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ውስጥ ያሉ ኤዲቶሪያል ፖሊሲዎች ከስርዓተ ፆታ መነፅር አንፃር ዝርዝር ይዘቶቻቸው ምን እንደሚመስሉ መልሶ መቃኘት፣ አዲስ የሚቋቋሙትም በዛ ደረጃ ይዘው እንዲመጡ ማድረግና ፍቃድ ከመሰጠቱ በፊት በጉዳዩ ላይ ትኩረት መደረግ እንደለበትም ጋዜጠኛ ፀጋ ታመለክታለች።
ኃላፊ በመሾም ደረጃም የግልና የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ላይ የሚታዩ ችግሮች መኖራቸውን የምትናገረው ጋዜጠኛ ፀጋ፤ ተቋማቱ ሴት አመራሮች ቢበዙላቸው የስርአተ ፆታ ጉዳይ ይበልጥ ትኩረት ሊያገኝ እንደሚችልም ትጠቁማለች። በባለሙያዎችም በኩል ያለውን ክፍተት ስልጠናዎችን በማመቻቸት መቅረፍ ከመንግስት እንደሚጠበቅም ታሳስባለች።
አቶ ቃለወንጌል ምናለ በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረስብ ድርጅት ምክር ቤት የፕሮግራምና ዴቨሎፕመንት አማካሪ ሲሆኑ ምክር ቤቱ በቅርቡ በአዋጅ የተቋቋመ ሲሆን የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን የሚወክል፣ የሚመራ፣ የሚያስተባብርና ዘርፉን የሚቆጣጠር ሲሆን በዚሁ ዘርፍ የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
ሚዲያው የስርዓተ ፆታ ጉዳይን ከማጉላት አንፃር በእርግጥም ሚናውን እየተወጣ ነው ለማለት ዝርዝር ጥናት ይፈልጋል። ሆኖም ከብዙ አንግል ማየት ይቻላል። ለአብነትም ሴቶችን ምን ያህል አካቷል፣ ሴቶች ሴክተሩን ከመምራትና በባለቤትነት ከመያዝ አንፃር፣ በጋዜጠኝነትና በኃላፊነት ከመስራት አኳያስ ያላቸው ሚና ምን እንደሆነ መፈተሽ ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከሚፈለገው ማህበረሰባዊ ለውጥ አኳያ በስርዓተ ፆታ ዙሪያ የሚሰራው ስራ ምን ያህል ነው? ምን ያህልስ በቂ ነው? የሚለውን መጠየቅ ይገባል። ከዚህና ከሌሎችም አንፃር ከታየ ሚዲያው የስርዓተ ፆታ እኩልነትን ከማረጋገጥ አንፃር ብዙ ክፍተት አለበት የሚል እምነት አለ።
ይህንኑ ክፍተት ለመሙላትም ብዙ ስራ መስራት ይጠበቃል የሚሉት አቶ ቃለወንጌል፤ በተለይ የሲቪል ማህረሰቡና ሚዲያው ተቀናጅተው በቅርበት መስራት እንዳለባቸው ይጠቁማሉ። በሌላ በኩል ደግሞ በስርአተ ጾታ ጉዳይ ዙሪያ የሚሰራው ስራ ማህበረሰባዊ ለውጥና ሽግግር ከማምጣት አኳያ ምን ያህል በቂ ነው የሚለውን መመልከት እንደሚገባ ይገልፃሉ።
የስርዓተ ፆታ እኩልነት ላይ ስራዎች አጠናክሮ መስራት እንደሚያስፈልግም ይጠቅሳሉ። ነገር ግን የሲቪል ማህበራት ይህን ክፍተት እንዴት ያዩታል ምክንያቱስ ምንድን ነው? የሚለውን ለመመለስ ዝርዝር ጥናቶች እንደሚስፈልጉ ነው የሚጠቁሙት። ምክር ቤቱም ይህንን ክፍተት በመረዳት ከሚመለከታቸው አካላትና ከተለያዩ የስርዓተ ፆታ ተኮር ድርጅቶች ጋር ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ያስረዳሉ።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ህዳር 8/2015