በድርጅታችን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ በጠቅላላ የአዕምሮና የአካል ደህንነት (General Wellness) ላይ የሚያተኩር ሥልጠና ተሰጥቶ ነበር። ሥልጠናውን የሰጡት የጤና እና የስፖርት ባለሙያዎች፤ እንዲሁም ለበርካታ ዓመታት ሥልጠና በመስጠት ልምድ ያዳበሩ ባለሙያዎች ናቸው።
በሥልጠናው ላይ አንደኛው ባለሙያ ጥናት ጠቅሶ ‹‹መቀመጥ አዲሱ ሲጃራ ነው (sitting is the new smoking)›› ሲል ሰማሁት። ወዲያውኑ የመጣልኝ አገር ቤት የማውቀው አባባል ነው። ‹‹መቀመጥ መቆመጥ›› የሚባል አባባል አለ። መልዕክቱም፤ ለረጅም ጊዜ መቀመጥ ደካማ ያደርጋል፣ ያልፈሰፍሳል፣ ህመምተኛ ያደርጋል፣ ሽባ ያደርጋል… በአጠቃላይ ቆማጣ ያደርጋል እንደማለት ነው።
በሌላ በኩል ስንፍናን ለመግለጽ የሚጠቀሙት ነው። የማይሰራ፣ የማይንቀሳቀስ፣ ለረጅም ጊዜ የሚቀመጥ ብዙ ሥራ ያልፈዋል። የአባባሉ መሰረት የገጠሩ ማህበረሰብ ነው፤ በግብርና የሚተዳደረው ማለት ነው። በገጠሩ ማህበረሰብ ደግሞ ተቀምጦ የሚሰራ ሥራ የለም፣ በመንቀሳቀስ ነው። እናም ለረጅም ጊዜ የሚቀመጥ ሰው ብዙ ሥራ ስለሚያልፈው ችግረኛ ይሆናል። ይህ እንግዲህ በገበሬው ዓውድ ሲታይ ነው፤ ተቀምጦ የሚሰራ ሥራ ብዙም ስለሌለ ማለት ነው። በተቋማት ዓውድ ካየነው ግን ለመቀመጥ የሚያስገድዱ ሥራዎች አሉ። ወደ ሥልጠናው ልመለስ።
‹‹መቀመጥ አዲሱ ጭስ›› የሚለውን የባለሙያዎች ማብራሪያ ከሰማሁ በኋላ የበይነ መረቡን ዓለም ማሰስ ጀመርኩ። ከአውሮፓውያኑ 2020 ጀምሮ በዚሁ ጉዳይ ላይ የተሰሩ ጥናቶችና መጣጥፎች ብዙ ናቸው። መቀመጥ አዲሱ አደገኛ ጭስ ነው። ‹‹መቀመጥ መቆመጥ›› የሚለው የአገር ቤቱ አባባል ችግሩን በሚገባ ይገልጸዋል።
ይሄ ነገር የሚመለከተው እኛን ነው። እኛን ማለቴ ሥራዎችን ቁጭ ብለን በኮምፒተር የምንሰራ ሰዎችን ማለቴ ነው። በተለይም የፋይናንስ ተቋማት (ለምሳሌ ባንኮች) ውስጥ የሚሰሩ ሠራተኞች የሥራው ባህሪ ያስገድዳቸዋል። የብዙ ተቋማት ሥራዎች ቁጭ ብሎ የሚሰሩ ናቸው።
ደግነቱ የባለሙያዎቹ ምክር ግን አትቀመጡ የሚል አይደለም። ቢያንስ በተወሰኑ ደቂቃዎች ውስጥ መነሳት አለብን የሚል ነው። ለምሳሌ የሻይ ቡና ሰዓታችን ላይ እዚያው ወንበር ላይ ሆነን ሻይ ከማዘዝ ይልቅ ሻዩ ወይም ቡናው ያለበት መሄድ። ቁርስ ወይም ምሳ የተቀመጥንበት ወንበር ላይ ሆነን ከማዘዝ ምግቡ ያለበት መሄድ ማለት ነው።
እዚህ ላይ ነው እንግዲህ ብዙ ነገሮችን የምንታዘብ። ብዙዎቻችን አንዴ ከተቀመጥን መነሳት ይከብደናል፤ የሥራው አስገዳጅነት እንዳለ ሆኖ፤ የአንዳንዶቻችን ግን የስንፍና ነው። ስንፍና መሆኑን ለማወቅ ደግሞ እስኪ እነዚህን ነገሮች ታዝባችኋል?
ሙሉ ጤነኛ ሆኖ ሁለተኛ ፎቅ ለመውጣት ከአምስት እስከ አሥር ደቂቃ ቆሞ ሊፍት የሚጠብቅ የለም? ለ1.5 ኪሎ ሜትር መንገድ እስከ 20 ደቂቃ ቆሞ ታክሲ የሚጠብቅ ወይም ረጅም ሰልፍ የሚሰለፍ የለም? አንዳንድ ጊዜ እኮ የሰልፉ ርዝመት ራሱ ከሚሄድበት ቦታ እኩል ሊሆን ይችላል! ምንም ሥራ ሳይዝ ወንበር ላይ ቁጭ ብሎ ሻይ ቡና ወይም ምግብ ከውጭ የሚያስመጣ የለም? ላለመንቀሳቀስ ማለት ነው።
እነዚህ ችግሮቻችን ስንፍና ወለድ ናቸው። አንዳንዶቹ ደግሞ አጉል ጉራ እና ክብር የሚመስሉን ናቸው። ይሄ ምናልባትም ሀብታም፣ ታዋቂ እና ባለሥልጣን የሆኑ ሰዎችን የሚመለከት ይሆናል። የባለሥልጣናቱ ከደህንነት አንፃር ቢሆን እንኳን የታዋቂ ሰዎች ደግሞ ‹‹እንዴት በእግሩ ይሄዳል!›› መባልን ይፈሩ ይሆናል። ችግሩ ግን የማጣትና የማግኘት ጉዳይ ሳይሆን የጤና ጉዳይ ነው። ትዝብቱ በቤታቸው ውስጥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉትን አይመለከትም።
ባለሙያዎቹ እንደሚሉት ደግሞ ችግራችን ለረጅም ጊዜ መቀመጣችን ብቻ አይደለም። አቀማመጥ ራሱ ሥርዓት አለው፤ ከፕሮቶኮል ወይም ከቄንጥ አንፃር ሳይሆን ከጤና አንፃር ማለት ነው። ጀርባችን የወንበሩን የኋላ ድጋፍ መደገፍ እንዳለበት ባለሙያዎች ቢመክሩም፤ ብዙዎቻችን ግን ይህን ልብ አንለውም። ኩርምት ብለን ተቀምጠን የምናየው ነገር ላይ ብቻ እናፈጣለን።
እንዲህ በቀላሉ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ መከላከል የምንችላቸውን ነገሮች ነው በቸልተኝነት የሚያጠቁን። የሆነ ህመም ይይዘንና ወደ ጤና ተቋም እንሄዳለን፤ ከዚያ በኋላ የጤና ባለሙያዎች ሲነግሩን ነው ለመንቀሳቀስ መንደፋደፍ የምንጀምር። ላለመሞት ከመንደፋደፍ ግን ላለመታመም ጥንቃቄ ብናደርግ ጤናማ ዕድሜ ይኖረን ነበር። ለዚህም ‹‹ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ›› የሚል ብሂል አለን። በነገራችን ላይ ሐኪሞች ራሱ እንደሚሉት ታሞ በህክምና መዳን ካለመታመም ጋር እኩል አይሆንም፤ በእርግጥ ይሄን ለማወቅ የግድ የጤና ባለሙያ ምስክርነትም አያስፈልገውም።
ከምግብ በኋላ ትንሽ መንቀሳቀስ እንዳለብን ይመከራል፤ ዳሩ ግን ብዙዎቻችን አናደርገውም። ምናልባትም በጣም ቸግሮን (ትራንስፖርት ጠፍቶ) ካልሆነ በስተቀር አስበንበት፣ ለጤና ጠቃሚ ነው ብለን አናደርገውም።
ስፖርት ሲባል ብዙ ጊዜ እንደ ጂም እና ቴኳንዶ የመሳሰሉት ብቻ ናቸው የሚመስሉን። ባለሙያዎች እንደሚሉት ግን ለአካላዊ ጤንነት ከእግር ጉዞ ጀምሮ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ጠቃሚ ናቸው። እኛ የምንሰራው ለጤና እንጂ የግድ በቴኳንዶ ወይም ቦክስ ለመወዳደር አይደለም፤ ጡንቻ ለማፈርጠም ወይም ደረት ለማስፋት ብቻ አይደለም።
ብዙዎች ላይ የምንታዘበው ደግሞ አካላዊ ቅርጽ የሚፈለገው ለውበት ብቻ ይመስላል፤ ግን ባለሙያዎች እንደሚሉት የሰውነት አቋም መስተካከል ጤንነት ነው። ደረትን ገልብጦ ለማሳየት ሳይሆን የሰውነታችን ክፍሎች ጤናማ ቅንጅት እንዲኖራቸው ነው። ለዚህም ባለሙያዎች የሚመክሩት ስንቀመጥም ሆነ ስንሄድ ቀጥ ብለን መሆን እንዳለበት ነው። ይህ ደግሞ እግረ መንገዱን ለዕይታም ጥሩ ነው።
በነገራችን ላይ አንዳንድ ልማዶቻችን ሳይንስን መሰረት ያደረጉ መሆናቸው ይገርመኛል። ብዙ ጊዜ ልማድ ሲባል ሙሉ በሙሉ ከሳይንስ ተቃራኒ ነው የሚመስለን። ግን ማህበረሰቡ ሳይንሳዊ ምክንያቱን ሳያውቀው (ማብራራት ባይችልም) በቀጥታ ሳይንሳዊ ጠቀሜታ ያላቸው ልማዶች አሉ። አንድ ሁለት ልጥቀስላችሁ!
ለምሳሌ በገጠሩ ማህበረሰብ ውስጥ የማውቀው አንድ የቆየ ልማድ አለ። ሴት ልጅ ቆማ ውሃ ስትጠጣ ይቆጧታል። እነርሱ የሚቆጧት በዘልማድ ነው። ሴት ልጅ ትሁትና ጭምት መሆን አለባት በሚል ነው። ቆማ መጠጣቱ ትንሽ እንደ ብልግና ስለሚታይ ነው።
የሚገርመው ግን የጤና መረጃዎች እንደሚሉት ቆሞ ውሃ መጠጣት አደጋ አለው፤ ይሄ በቀላሉ መረጃዎችን በማገላበጥ የምናገኘው ነው። በኃይል ተወርውሮ በመውረድ ኩላሊት ላይ ነው የሚያርፍ። ከጉሮሮ ልክ እንደ ፏፏቴ በኃይል ወርዶ ኩላሊትን ይመታል። በተለይ ለሴቶች ደግሞ የማህጸን ግድግዳን ይመታል። ስለዚህ የሚመከረው ቁጭ ብሎ በትንሽ በትንሹ መጠጣት ነው።
ሌላው ልማዳዊ ነገር ደግሞ የቁርስ ነገር ነው። ምንም እንኳን በኦርቶዶክሱ ማህበረሰብ ውስጥ ከፆም ጋር የሚያያዝ ቢሆንም ይሄው ማህበረሰብ ግን ሌላ ልማድ ደግሞ አለው። አንድ ሰው በጠዋት ከቤት ሲወጣ ‹‹አፉ እህል መቅመስ አለበት›› ተብሎ ይታመናል። በባዶ ሆድ መውጣት ሊያጋጥም ይችላል ብለው የሚያምኑት ልማድ አለ። ስለዚህ የግድ ምግብ ቀምሶ መውጣት አለበት።
ይህን ልማድ ከሳይንስ ጋር ስናገናኘው ቁርስ በጠዋት መብላት ይመከራል። ምንም እንኳን በግላዊ ልምዳችን ላይ የሚወሰን ቢሆንም (በጠዋት መብላት አልወድም የሚሉ ስላሉ) ጠዋት ቁርስ መብላት ግን ሳይንሳዊ ጠቀሜታ ያለው ነው። ትራንስፖርት ውስጥ እንኳን ከአፋችን መጥፎ ሽታ እንዳይወጣና ሰው እንዳንረብሽ ያደርጋል።
በአጠቃላይ ብዙ ሳይንሳዊ የሆኑ ልማዶች አሉን፤ በዚህ መሰረት መቀመጥ በልማድም በሳይንስም መቆመጥ ነውና እንቀሳቀስ!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2015