ረሃብ ቅጽል ስሟ እስኪመስል መገለጫዋ ሆኖ ቆይታለች። የዘመናት ጠላቷ ድህነት ከገናና ስሟ እየቀደመ ገፅታዋን ሲያጠለሽ መኖሩም ለዚሁ ነው። ዛሬ ግን ‹‹… ትናንት ዛሬ አይደለም›› በማለት ለዘመናት ተጣብቷት የኖረውንና ገጽታዋን ያጠለሸውን ድህነት ከጫንቃዋ ልታወርድ ማርሽ ቀይራ ተነስታለች። ኢትዮጵያ። ለዚሁ ነው በምግብ እራስን የመቻል ጅማሮዋን በስንዴ ሰብል ልማት አጠናክራ መቀጠሏም።
በምግብ እራስን ስለመቻል ሲነሳ ታዲያ ዋነኛው የዳቦ ጥያቄ ነውና በዋነኛነት የስንዴ ፍላጎቷን በአገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን እየተጋች ነው። ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በይቻላል መንፈስ ስንዴን በመስኖ አልምታ ህዝቡን ልታጠግብ ከራሷ አልፋም ለሌሎች ልትተርፍ አንድ ብላለች። ‹‹የሚያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል›› እንዲሉ ታዲያ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየለማ ያለው ስንዴ አይን ያጠግባል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም በእርዳታ የምትቀበለውን ስንዴ ጨምሮ በየዓመቱ ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ከውጭ ይገባል። ለዚሁ የስንዴ ግዢም በየዓመቱ ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ይጠየቃል። ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ምርት ሙሉ በሙሉ ለመተካት ካለፈው በጀት ዓመት ጀምሮ ትርጉም ያለው ሥራ እየሠራች ትገኛለች። በተለይም የኩታ ገጠም የግብርና ሥራና የመስኖ ልማት ሥራዎቿን በማቀላጠፍ የጥረቷን ፍሬ ለዓለም ማሳየት ጀምራለች። በዚህም በ2014 በጀት ዓመት በአገር ደረጃ 60 ሚሊዮን ኩንታል ገደማ የስንዴ ምርት ማግኘት የቻለች ሲሆን፤ በ2015 ዓ.ም በአገር አቀፍ ደረጃ በበጋ መስኖ ከለማው 1ነጥብ3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት እና ከመኸር ማሳ 153 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ለማስገኘት እየተሰራ ነው።
ዘንድሮ በሚሊዮኖች ኩንታል የሚቆጠር ስንዴ ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ እንደምታቀርብ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ይፋ ማድርጋቸው ይታወሳል። እኛም ይህን በማስመልከት በብዙ ጥረትና ልፋት እንዲሁም በይቻላል መንፈስ ከፍተኛ የመንግሥት ትኩረት አግኝቶ የለማው ስንዴ የግብይት ስርዓቱ እንዴት ነው፤ ከአገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ የሚቀርብበት አካሄድ ምን ይመስላል፤ በተለመደው የግብይት ሂደት ማስተናገድ ይቻላል ወይ፤ በአገሪቱ ያለው የንግድ ስርዓት በተለይም በደላላ ሰንሰለት ውስጥ እንዳይገባ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ተሠርተዋል ወይ፤ የሚሉና መሰል ጥያቄዎችን በማንሳት የሚከተለውን አጠናክረናል።
ኢትዮጵያ በምግብ እህል እራሷን ለመቻል በምታደርገው ጥረት በተለይም ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ የበጋ መስኖ ስንዴን ከሁለትና ሶስት ጊዜ በበለጠ ማምረት እንደሚቻል ማየት መቻሉን ጠቅሰው፤ የይቻላል አስተሳሰብን በማስረጽ የበጋ መስኖ ስንዴ ለሁለተኛ ጊዜ እየተመረተ መሆኑን በኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ አያልሰው ወርቅነህ ገልጸዋል።
እንደሳቸው ማብራሪያ በአርሶ አደሩ የተመረተውን የስንዴ ምርት የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን ባደራጃቸውና በየደረጃው በሚገኙ የገበሬዎች ህብረት ሥራ ማህበራት አማካኝነት ተሰብስቦ ለገበያ ተደራሽ የሚደረግ ይሆናል። ይህ የህብረት ሥራ ኮሚሽን ድርሻ ነው። ስንዴ ብቻም ሳይሆን በቆሎም አንዱ ተፈላጊ ምርት እንደሆነ የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፤ በተለይም ፋብሪካዎችና የተለያዩ የምግብ አቀናባሪዎች በስፋት የሚፈልጉት በቆሎ መሆኑን ገልጸው፤ ምርቱን ለእነዚህ አካላት ተደራሽ ማድረግ እንዲቻልም በዘንድሮ ዓመት ብቻ 68 የሚደርሱ የህብረት ሥራ ማህበራት ተለይተው ምርቱን ከአርሶ አደሮቻቸው ሰብስበው ለሚፈለገው አካል ለማቅረብ ዝግጅታቸውን ማጠናቀቅ እንደቻሉ ነው ያነሱት።
68 የሚደርሱ ማህበራት 208 ዘመናዊ መጋዘኖችን ማዘጋጀታቸውን ጠቅሰው፤ መጋዘኖቹ ስምንት ሚሊዮን ሁለት መቶ ኩንታል እህል የመያዝ አቅም ያላቸው መሆኑን አስረድተዋል። ማህበራቱ በዋናነት የሚገኙት በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በደቡብና በሲዳማ ክልል ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ህብረት ሥራ ኮሚሽን በዋናነት አቅዶ እየሠራ ያለውም በስንዴ እና በበቆሎ ምርት ላይ እንደሆነነ ነው ዳይሬክተሯ ያስረዱት። በዘንድሮ ዓመት ስንዴ ከአንድ ሚሊዮን አንድ መቶ 76 ሺ ኩንታል በላይ፤ በቆሎ ከሁለት ሚሊዮን 37 ሺ ኩንታል በላይ በድምሩ ሶስት ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ 13 ሺ ኩንታል በቆሎና ስንዴን ለማገበያየት የህብረት ሥራ ማህበራቱ በዝግጅት ላይ እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
ለዚህም ከ11 ቢሊዮን ብር በላይ ለግብይቱ የሚያስፈልግ መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሯ፤ ይህንን ገንዘብ ለማግኘትም ሁለት መንገዶች መታሰባቸውን ነው የገለጹት። አንደኛው የህብረት ሥራ ማህበራቱ በራሳቸው ፋይናንስ አቅምና በራሳቸው የማከማቻ መጋዘን ሲሆን፤ የበለጠ ምርት ለማከማቸትና ለማገበያየት እንዲቻል ድጋፎች የሚያስፈልጉ ይሆናል። በተለይም የፋይናንስ ተቋማት ብድር የሚያመቻቹ ከሆነና የምርት ማከማቻ መጋዘንም እንዲሁ ማቅረብ የሚችሉ አካላት ትብብር ካደረጉ ከ4 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማሰባሰብ እንደሚችሉ ታውቋል።
ይሁንና በአሁን ወቅት ማህበራቱ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል በቆሎ እንዲሁም 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት በራሳቸው የፋይናንስ አቅምና ባላቸው የማከማቻ ቦታ ለማገበያየት ተዘጋጅተዋል። የህብረት ሥራ ማህበራቱ ምርትን በዋናነት ተደራሽ የሚያደርጉት ለዓለም የምግብ ድርጅት፣ ለአደጋ ስጋት ኮሚሽንና ለሌሎች እርዳታን ለሚያቀርቡ ተቋማት ነው።
‹‹የህብረት ሥራ ማህበራቱ ምን ያህል ስንዴ ማቅረብ ይችላሉ፤ ምን ያህል መጠን ያለው ስንዴስ ለውጭ ገበያ ተደራሽ ያደርጋሉ፤ የሚለውን የሚከታተለው የህብረት ሥራ ኮሚሽን አጠቃላይ የገበያ ስርዓቱ እንዴት ይመራል የሚለውን አይከታተልም›› ያሉት ዳይሬክተሯ፤ ኮሚሽኑ በተዘረጋው የገበያ ስርዓት ውስጥ ገብቶ ስንዴውን ለአገር ውስጥና ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዲችሉ ክትትል ያደርጋል ብለዋል።
በዚህም መሰረት በተለይም በስንዴ ኤክስፖርት በኦሮሚያ አራት የህብረት ሥራ ማህበራት፣ በአማራ ሶስት፣ ሲዳማ ላይ አንድና ደቡብ ላይ አራት የህብረት ሥራ ማህበራት ኤክስፖርት ለማድረግ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ አስረድተዋል። በእነዚህ አራት ክልሎች የሚገኙ የህብረት ሥራ ማህበራት በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ከሁለት ሚሊዮን ስምንት መቶ ሃምሳ አምስት ሺ ኩንታል ስንዴ በላይ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እራሳቸውን አዘጋጅተዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ነጻነት ተስፋዬ በበኩላቸው የስንዴ ምርትን በዘመናዊ ግብይት ሥርዓት ለማገበያየት መዘጋጀቱን አስረድተዋል። የስንዴ ምርትን በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መምራት የሚያስችል ዝግጅት የተደረገ መሆኑን በመግለጽ በተያዘው በጀት ዓመት ስንዴን ማገበያየት ይጀመራል ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከ15 ዓመታት በፊት ምርቶችን ማገበያየት የጀመረው በበቆሎና ስንዴ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ነጻነት፤ በወቅቱ የስንዴ ምርታማነት በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ ግብይቱ ከወራት ያለፈ ዕድሜ እንዳልነበረው አንስተዋል። ይሁንና በአሁን ወቅት መንግሥት በስንዴ ምርት ላይ እያከናወነ ባለው ተግባር ምርታማነቱና የገበያ መዳረሻው እየሰፋ የሚሄድ በመሆኑ በዘመናዊ የግብይት ሥርዓት መምራት አስፈላጊ እንደሆነ ነው ያስረዱት።
መንግሥት በወሰደው ተነሳሽነት ከፍተኛ መጠን ያለው ስንዴ መመረት መቻሉን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይም ምርትና ምርታማነት እያደገ እንደሚሄድና ከአገር ውስጥ አልፎ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚቻል መሆኑን አስረድተዋል። ይሁንና የግብይት ስርዓት ከሌለ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ብቻ በቂ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ትክክለኛው ቦታ እንደሆነ ነው ያስረዱት።
ምርት ገበያ ከዚህ ቀደም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጨምሮ በአገር ውስጥ ለግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ የሚሆኑ የተለያዩ ምርቶችን መገበያየት የሚያስችል ልዩ የመገበያያ መስኮት ተከፍቶላቸው ይስተናገዳሉ። በዚህ መሰረትም ስንዴን ተጠቅመው ዱቄት፣ ፓስታ፣ ማካሮኒና ሌሎች ምግቦችን ለሚያመርቱ ፋብሪካዎች ስንዴን በሚፈልጉት መጠን መግዛት የሚችሉት ከኢትዮጵያ ምርት የገበያ ነው። ይህም አርሶ አደሩ ላመረተው ምርት የተሻለ ዋጋ በወቅቱ ማግኘት እንዲችል ያደርገዋል፤ በመላው አገሪቱ በሚገኙ 25 የምርት ገበያ ቅርንጫፎች አርሶ አደሩ ምርቱን በቀላሉ ማቅረብ የሚያስችለው ይሆናል።
የገበያ መረጃ ለግብይት ስርዓቱ ዋናውና ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ በአሁን ወቅት ስንዴ እንደሌሎች ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ የሚገለጽ ዋጋ የሌለው ቢሆንም በቀጣይ ግን ምርት ገበያው የስንዴን ዋጋ በማውጣት ግልጽ ያደርጋል። ይህም አርሶ አደሩ የገበያ መረጃ እንዲኖረው ከማድረግ ባለፈ ተደራዳሪ ያደርገዋል። የስንዴ ግብይቱ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል ሲከናወን በሚኖረው የንግድ እንቅስቃሴ ግብርና ታክስ በአግባቡ መክፈል ይችላል። ይህም አገሪቷ ማግኘት የሚገባትን ገቢ ማግኘት እንድትችል ያደርጋታል።
በምርት ገበያ ሥርዓት ማገበያየት ለግብይቱ ሕጋዊ የክፍያና የርክክብ ሥርዓት ከመዘርጋት ባለፈ የምርት ጥራትና ብዛትን በማሳደግ ረገድም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ፤ አርሶ አደሩ በተለይም በሚያመርታቸው ምርቶች ላይ የተሻለ ጥራት ማምጣት እንዲችል ያግዘዋል ብለዋል። ማንኛውም ምርት በምርት ገበያ በኩል ሲከናወን የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት ያገኛል። ይህም ማለት አርሶ አደሩ ምርቱን ወደ ምርት ገበያ በሚያቀርብበት ወቅት ባቀረበው የምርት መጠን ልክ ከባንክ ብድር ማግኘት እንደሚችል አስረድተዋል። ይህም አርሶ አደሩ ሙሉ ክፍያውን እስኪያገኝ ድረስ አስቸኳይ የሆኑ ግዢዎችን መፈጸም ያስችለዋል።
ምርት ገበያው በስፋት እየመጣ ያለውን የስንዴ ምርት በዘመናዊ መንገድ ለማገበያየት ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም ምርታቸውን ወደ ውጭ ገበያ መላክ የሚፈልጉ አምራቾችና አቅራቢዎች ዓለም አቀፍ ገበያውን የሚመጥን የጥራት መለያቸውን የኢትጵያ ምርት ገበያ በሚሰጣቸው ደረጃ ያውቁታል። ይህም አርሶ አደሩ የልፋቱን ዋጋ ማግኘት እንዲችልና የበለጠ በጥራት እንዲያመርት ያግዘዋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የስንዴ ምርትን ወደ ምርት ገበያ በማምጣት በድጋሚ ለማገበያየት ሲዘጋጅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የኢንደስትሪ የምክክር መድረክ ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከደረጃዎች ባለስልጣን፣ ከኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩትና ከሌሎች ጋር አድርጓል። ከዚህ በተጨማሪም በስንዴ ግብይት ውስጥ ከተሰማሩ አቅራቢዎች፣ ላኪዎችና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ጋርም ምክክር ተደርጓል። ይህም በቀጣይ ግብይቱ ሲከናወን በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ያስችላል።
በስፋት የተመረተው የስንዴ ምርት በህገወጥ መንገድ ለኮንትሮባንድ ንግድ እንዳይጋለጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልጋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶች በህገወጥ መንገድ ተሽጠው አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን ገቢ እንዳታገኝ ትቀራለች። መሰል ችግሮችም በስንዴ ግብይት እንዳይፈጠር የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በጋራ መሥራት ይገባቸዋል። በተለያዩ የፌዴራልና የክልል ተቋማትን ቅንጅት በመጠቀም በየደረጃው ያለውን ቁጥጥር አጠናክሮ የኮንትሮባንድ ስንዴን ግብይት ጤናማ ማድረግ ይቻላል። የኮንትሮባንድ ንግዱን በጋራ ለመከላከል የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዝግጁ እንደሆነ አስረድተዋል።
የስንዴ ምርትን ለአገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ አርሶ አደሩ የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም እንደሚችል የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ አንደኛ አርሶ አደሩ ሰፊ ምርት ካለው በቀጥታ ወደ ምርት ገበያ በማቅረብ መገበያየት ይችላል፣ ሁለተኛው በህብረት ሥራ ማህበራት ተደራጅቶ ማቅረብ ይችላል፣ ሶስተኛው ለአቅራቢዎችና ለተለያዩ ኩባንያዎች በማቅረብ በእነሱ አማካኝነት ወደ ምርት ገበያ ይቀርባል። አርሶ አደሩ ምርቱን በእነዚህ አማራጮች ለገበያ ማቅረብ ከቻለ መሀል ላይ ያለውን ደላላ በማስቀረት ተጠቃሚ መሆን ይችላል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ጎተራዋ ከምታስገባው ስንዴ ባሻገር ለሌሎች አገራት ስንዴ ለመላክ መሰናዳቷ ሁለት ታላላቅ መልዕክቶችን የያዘ ነው። የመጀመሪያው በምግብ እራስን መቻል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለስንዴ ግዥ የሚለውን የውጭ ምንዛሬ ማስቀረት ነው።
ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለሌሎች ለመትረፍ የጀመረችው ጉዞ ስሟን ከማደስ ባሻገር ፋይዳው የጎላ በመሆኑ፤ ስኬቱ ለሌሎችም ዘርፎች አዲስ አቅም እና ጉልበት ሆኖ ይቀጥላል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ህዳር 7/2015