በኢትዮጵያ ውስጥ ቴክኖሎጂን እንደ አንድ ችግር መፍቻ ቁልፍ የመጠቀም ባህል እያደገ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። ከጥቂት ዓመታት በፊት ረጅም ጊዜን፣ ጉልበትን እንዲሁም ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ የሚጠይቁ ጉዳዮች በቀላሉ በቴክኖሎጂና ዲጂታል ዘርፍ ፈጣን መፍትሄ አግኝተው መመልከት ችለናል። ከቅልጥፍና፣ አላስፈላጊ ወጪና ጉልበትን ከመቀነስ አልፎ ጥራትን የሚጨምሩ የአሰራር ስርዓቶችን በዚሁ የለውጥ ሂደት ውስጥ ማምጣት መቻሉን ነው ባለሙያዎች የሚያነሱት።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የፋይናንስ ዘርፉና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ደረጃቸውን ማሳደግ በመቻላቸው ከላይ ያነሳናቸውን ችግሮች ማቃለል ችለዋል። የዲጂታል ኢኮኖሚ አሰራር ስርዓት፣ ከሰው ንክኪ ውጪ የሆኑ ሲስተሞች ውጤታማ እንደሆኑ የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎችን ማቅረብ ይቻላል። ቀደም ባሉት ጊዜያት በርካታ ቅሬታዎችን ሲሰማባቸው የነበሩ አንደ ባንክ አይነት ዘርፎች አሁን ቴክኖሎጂን እንደ መፍትሄ ተጠቃሚዎችን እንደየ ፍላጎታቸው እያስተናገዱ ይገኛሉ። እንዲያም ሆኖ ገና ብዙ መሻሻሎች የሚፈልጉ ጉዳዮች እንዳሉ ግን መዘንጋት የለበትም።
ኢትዮጵያ በሳይንስና ቴክኖሎጂው ዘርፍ አዲስ አብዮት ለመፍጠርና እድገቷን በዚያ ላይ ለመገንባት ቆርጣ ወደ ትግበራ ከገባች ቆይታለች። የ“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ” ሰነድ እና ያንን እውን ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባሮችም ይህንኑ ነው የሚያመለክቱት። ሁሉም ቁልፍ ዘርፎች ዘመኑ የሚጠይቀውን ሳይንሳዊና የቴክኖሎጂ ውጤቶችን እንዲከተሉም የተለያዩ ጥረቶች እየተደረጉ ይገኛሉ። በእርግጥ ዓለም በዘርፉ ከደረሰበት የላቀ ደረጃ አንፃር አገሪቱን ስንገመግም እጅግ ወደኋላ ከቀሩት የዓለም ክፍላት ጋር የምትመደብ መሆኗ እሙን ነው። ይሁን እንጂ ካለፉት ሶስትና አራት ዓመታት ወዲህ ተስፋ ሰጪ ጥረቶችን እየተመለከትን ነው። ለዚህም በግብርናው ዘርፍ ላይ በጎ ውጤት የሚያሳዩ የሳተላይት ቴክኖሎጂና መሰል እንቅስቃሴዎችን እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል።
የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንደሚገባቸው ታዳጊ አገራት ከላይ ካነሳናቸው የስኬት ጅማሮዎች በተጓዳኝ ብዙ ርቀትን መጓዝ እንደሚጠበቅባቸው መገንዘብ ያስፈልጋል። በተለይ በኢትዮጵያ ውስጥ ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ችግሮችን ማቃለል ከሚገባቸው ዘርፎች መካከል የትራንስፖርትና የትራፊክ ዘርፉ ተጠቃሽ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይ ደግሞ ከፍተኛ የተሽከርካሪ ብዛት በሚገኝባት የአዲስ አበባ ከተማ ዘመኑ የፈጠራቸውን የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተግባራዊ ባለመደረጉና ይህንን በሥራ ላይ የማዋል የግንዛቤ ክፍተት በመኖሩ ምክንያት በርካታ ችግሮች እየተፈጠሩ ይገኛሉ። ከሁሉም በላይ ግን ዘርፎቹ የሚመሩበት ዘመናዊ የአሰራር ስርአት አለመዘርጋት ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖ እንደቀጠለ ነው።
አይን አዲስ ንኡስ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ነች። የመኖሪያ ሰፈሯ ጀሞ አንድ ሲሆን፣ የሥራ ቦታዋ መገናኛ በልዩ ስሙ ማራቶን በሚባል አካባቢ ነው። በከተዋ የትራንስፖርት አገልግሎት ችግር ምክንያት በየጊዜው ወደ ሥራ ቦታዋና ወደ መኖሪያ አካባቢዋ ለመድረስ እንደምትቸገር ትናገራለች። ተሽከርካሪ ብታገኝም በትራፊክ መጨናነቅ ምክንያት ከአንድ ሰዓት እስከ ሁለት ሰዓት ለሚደርስ ጊዜ መቆየቷ የተለመደና የእለት ተእለት ተግባሯ እንደሆነ ትገልፃለች። የሚመለከተው የመንግሥት አካል መንገዶችን ከመስራት፣ የትራፊክ መስመሮችን በቴክኖሎጂ በመምራትና ሌሎች የመፍትሄ አማራጮችን ተጠቅሞ መፍትሄ እንዲሰጥ ትጠይቃለች።
ሌላኛው ለዝግጅት ክፍላችን አስተያየት የሚሰጠው ደግሞ የግል መኪና የሚያሽከረክረው አቶ ግርማ ፀሃይ ነው። እርሱ እንደሚለው በተለይ በአዲስ አበባ ውስጥ የትራንስፖርት ዘርፉ እና የትራፊክ እንቅስቃሴው በአግባቡ ስለማይመራ ነዋሪዎች ከሥራ ወደ መኖሪያም ሆነ ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ወጥተው ለመግባት ይቸገራሉ። እርሱ እንደ ዋና ችግር የሚያነሳው በመንገድ ላይ በሚፈጠር ግጭት ምክንያት ተሽከርካሪዎች በቶሎ ባለመነሳታቸውና በዘመናዊ መንገድ መረጃ ሰብስቦ ውሳኔ የሚሰጥበት መንገድ ባለመኖሩ ምክንያት የመንገድ መዘጋጋት መፈጠርን ነው።
ከዚህ ባሻገር የከተማዋን የመንገድ ስርዓት የሚቆጣጠሩ ትራፊኮች መረጃን በቴክኖሎጂ አማካኝነት የመሰብሰብ ክፍተት እንዳለባቸው ማስተዋሉን ይናገራል። ከዚህ ባሻገር ትራፊኮች አሽከርካሪዎችን በህግ ጥሰት የሚቀጡበት ስርዓት ፍትሃዊነት የጎደለውና የአሰራር ክፍተት የሚታይበት እንደሆነም አስተያየቱን ይሰጣል። በኢትዮጵያ ውስጥ የትራንስፖርት ዘርፉ በርካታ መሻሻሎች እንደሚያስፈልጉት አቶ ግርማ ያምናል።
ኢንስፔክተር ዲሮ ፈከኔ በአዲስ አበባ ትራፊክ ፅህፈት ቤት የጎማ ቁጠባ ቅርንጫፍ ስምሪት ክፍል ሃላፊ ናቸው። ኢንስፔክተሩ በጉዳዩ ላይ እንደሚሉት፤ በተለይ በበአዲስ አበባ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ አለ። ይህ ችግር ከመንገድ ጥገናና ጥበት ችግር፣ ከግጭት፣ እንዲሁም በቸልተኝነት የተከለከለ ቦታ አቁሞ ከመሄድና መሰል ችግሮች አንፃር የሚፈጠር ነው። ከዚህ ውጪ አደጋ ሲከሰት፣ አሽከርካሪዎች የደንብ ጥሰት ሲፈፅሙ፣ ስምሪት ወስደው የሚሰሩ የትራፊክ አባሎች ህግን ባልተከተለ መልኩ ደንብ ተላልፈው ሲቀጡ እንዲሁም ሌሎች ተያያዥ ችግሮች በትራፊክ እንቅስቃሴው ላይ እክል ይፈጠራል።
እነዚህን ችግሮች ለማቃለል በሰፊ የሰው ኃይል ስምሪትና በቴክኖሎጂ በሚታገዙ ሥራዎች እንደሚሰሩ ይናገራሉ። ከፍተኛ መጨናነቅ የሚታይባቸው ቦታዎችን ከሰው ስምሪት ባሻገር በካሜራ ታግዞ በቴክኖሎጂ ስምሪቱን ለማቃለል እንደሚሠራ ገልፀው ይህ ግን በቂ ነው የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ።
“ግጭት ሲፈጠር፣ የደንብ መተላለፍ ተፈጥሮ ጥፋተኞች ሲያመልጡ፣ ትራፊኮች አላግባብ አሽከርካሪዎችን ሲቀጡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ዳኝነት መስጠት ያስፈልጋል” የሚሉት ኢንስፔክተሩ አሁን ያለው የቴክኖሎጂ ስርዓት ለችግሩ በበቂ መልኩ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል አለመሆኑን ይናገራሉ። ቴክኖሎጂ የሁሉ ቁልፍ መፍቻ መሆኑን ጠቅሰው አዲስ አበባ ውስጥ ያለውን የትራፊክ ፍሰት ለመቅረፍ ዘመኑ የሚፈቅደውን ቴክኖሎጂ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ምክረ ሃሳባቸውን ይገልፃሉ።
ስማርት ትራፊኪንግን እንደ መፍትሄ
ሚካኤል ታዬ ይባላል። በኢትዮ ቴሌኮም የስትራቴጂክና ፕላኒንግ ሱፐርቫይዘር ነው። በሳይንስ ሙዚየም የስማርት ትራፊኪንግ ሲስተምን ካምፓኒውን ወክሎ ሲያስተዋወቅ ነበር። እርሱ እንደሚለው በሙዚየሙ ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም ከሚያስተዋውቃቸው ቴክኖሎጂዎች ውስጥ “ስማርት ትራፊኪንግ” አንዱ ነው።
“የምናስተዋውቅበት ምክንያት መሰል ቴክኖሎጂዎች ትላልቅ ዳታ ሴንተሮች ይፈልጋሉ። ይህ ብቻ ሳይሆን ፈጣን የሆነ የኢንተርኔት ‘5ጂና 4ጂ ኔትወርክ’ አቅርቦትም ስለሚጠይቁ ነው” የሚለው ሚካኤል፤ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን እውን ከማድረግ አንፃር ኢትዮ ቴሌኮም የራሱን ድርሻ ወስዶ በመስራት ላይ እንደሆነ ይናገራል።
እንደ ሚካኤል ታዬ ገለፃ “ስማርት ትራፊኪንግ” ከተለመደው የትራፊክ ክትትል፣ ቁጥጥርና ፍሰትን የማሳለጥ ሂደት ይለያል። እርሱም የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን (አርቴፊሻል ኢንተለጀንት እና አይ ኦ ቲ ዲቫይሶችን) ተጠቅሞ የሚሰራ ነው። ይህም ሰፊ የሰው ሃይል ስምሪትን፣ ጉልበትና አላስፈላጊ ወጪን ይቀንሳል። በዚህም በሰከንዶች እያንዳንዱን የትራፊክ ፍሰትና እንቅስቃሴ ያሳያል።
“ስማርት ትራፊኪንግ ቴክኖሎጂ ሴንሰር (መጠቆሚያዎችን) በግራና በቀኝ ባሉ መንገዶች ላይ ተጠቅሞ መረጃ ይሰበስባል” የሚለው ሚካኤል፣ ይህንን መረጃ ተጠቅሞ የትራፊክ መብራቱ መሄድን መፍቀድና መከልከል በየትኛው ቅፅበት መወሰን እንደሚኖርበት ለመወሰን በቀላሉ እንደሚጠቁም ይናገራል። በዚህም ከፍተኛ መጨናነቅ ያለባቸው አካባቢዎች ቅድሚያ እንዲያገኙ በማድረግ መጉላላትንና መዘግየትን እንደሚያስቀር ያስረዳል። ሌላው ይህ ቴክኖሎጂ ስማርት ስልኮች ላይ የተጫኑ መተግበሪያዎችን፣ የመንገድ ላይ ትላልቅ ቦርዶችን እንዲሁም መሰል መረጃ ማስተላለፊያ መንገዶችን ተጠቅሞ ለአሽከርካሪዎችም ሆነ ትራንስፖርት ተጠቃሚዎች የተጨናነቁ መንገዶችን እንደሚጠቁም ይገልፃል። በዚህም ተጠቃሚው አማራጭ መንገዶችንና የተሻለ ፍሰት ያላቸውን መንገዶች ተጠቅሞ ያሰበበት እንዲደርስ እንደሚያግዝ ይናገራል። ይህም የትራፊክ ፍሰቱን ለሚከታተሉ ትራፊኮች እፎይታን ከመስጠቱም በላይ ጉልበትና ጊዜያቸውን ወደ ሚፈልጉ ሌሎች የክትትልና ቁጥጥር ሂደቶች እንዲጠቀሙበት እድል እንደሚሰጥ ይናገራል።
ሚካኤል ስማርት ትራፊክ ቴክኖሎጂ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች እነዚህ ብቻ እንዳልሆኑ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል “የትራፊክ ጥሰቶች” አሊያም የህግ መተላለፎች ሲፈጠሩ ያለምንም የሰው ንክኪና ተሳትፎ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (አርቴፊሻል ኢንተለጀንት) አማካኝነት ካሜራዎችን ተጠቅሞ መለየት እንደሚችል ይገልፃል። ይህም ማለት አንድ አሽከርካሪ ህግ ቢጥስና በስፍራው ትራፊክ ባይኖር ቴክኖሎጂው ጥፋተኛውንና አሽከርካሪውን እስከ ሙሉ መረጃው ለይቶ ለቁጥጥር ክፍል የማሳወቅ አቅም እንዳለው ይናገራል።
በተመሳሳይ አሽከርካሪው ጥፋተኛ ባይሆንና በትራፊኩ አላግባብ ቢቀጣም ይህ ቴክኖሎጂ የሰበሰበውን መረጃ ተጠቅሞ ፍትህ ማግኘት እንደሚያስችለው ይናገራል። ቴክኖሎጂው አጥፊዎችን እና የአሽከርካሪውን ባለቤት እስከነ አድራሻው መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂም የተገጠመለት መሆኑን ይናገራል። በአጠቃላይ ጥፋት ተብለው የተቀመጡና የተለዩ ማናቸውም የትራፊክ ህጎች በአሽከርካሪ ሲፈፀም የመለየት አቅም እንዳለው ይገልፃል።
እንደፈ ሱፐርቫይዘሩ ሚካኤል ገለፃ፤ በስማርት ትራፊኪንግ ቴክኖሎጂ አሽከርካሪዎች የተከለከለ ቦታ ቆመው የትራፊክ ፍሰቱን በሚያስተጓጉሉበት ወቅት በፍጥነት ለአሽከርካሪዎቹ በኤስ ኤም ኤስ መልእክት ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ እንዲያነሱ የሚያዝ ሲሆን በስፍራው በቸልተኝነት ሲቆዩ ግን እንዲቀጡ ያመቻቻል። ይህን መሰል ተግባር በቴክኖሎጂው ሲፈፀም “የ5ጂ” ባለ ከፍተኛ ፍጥነት ኔትወርክ የሚጠይቅ መሆኑን በመግለፅ ይህንን ኢትዮ ቴሌኮም የማቅረብ አቅም ላይ እየደረሰ መሆኑን ይናገራል።
“ቴክኖሎጂው የማዘዣ ጣቢያ አለው” የሚለው ሚካኤል፤ በዚህ ጣቢያ ከተማ ውስጥ ያሉ ሁለንም መብራቶች መቆጣጠር እንደሚችል ይገልፃል። ለምሳሌ አንድ የትራፊክ መብራት ብልሽት ቢያጋጥመውና የትራፊክ ፍሰቱ ቢስተጓጉል በመረጃ እጥረት ከጥገና ውጪ እንዳይሆን ቴክኖሎጂው ጥቆማ በመስጠት በቶሎ መፍትሄ እንዲያገኝ እንደሚያስችል ይናገራል። የተሽከርካሪ ግጭት ተከስቶ ፕላን ማንሳት ቢያስፈልግ በትራፊክ ፖሊስ የሚያስፈልገውን ረጅም ሰዓት የሚወስድ ባህላዊ አሰራር ያስቀራል። ፕላን እስኪነሳ መንገዱ ተዘግቶ መጨናነቅ እንዳይከሰትም መፍትሄ እንደሚሆን ነው ቴክኖሎጂውን እያስተዋወቀ የሚገኘው ባለሙያ የሚያስረዳው።
እንደ መውጫ
ከተሞች ሲያድጉ የትራፊክ መጨናነቅ አብሮ ይጨምራል። ስለዚህ ባህላዊውን መንገድ ተጠቅሞ የትራፊክ ፍሰቱን ማሳለጥ አስቸጋሪ ይሆናል። የግዴታ እንደነዚህ ያሉ ቴክኖሎጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል። ቴክኖሎጂዎች ውስን የሰው ኃይል ከመጠቀማቸውም ባሻገር ትክክለኛውን መረጃ የመሰብሰብ አቅማቸው እንዲሁም ፍትሃዊ እርምጃዎችን መውሰድ መቻላቸው ተመራጭ ያደርጋቸዋል። አስፈላጊውን መረጃ በፍጥነት፣ በታማኝነት እንዲሁም በቅልጥፍና አግኝቶ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የመረጃ መተንተን አቅም መፍትሄ ለማስቀመጥ ተመራጭ ናቸው። ቀሪውን የሰው ኃይል፣ በአነስተኛ ቁጥጥር፣ ክትትል፣ ጥገና እንዲሁም ሌሎች የስምሪት ቦታዎች ላይ በማድረግ ህብረተሰቡ በሚፈልገው ሰዓት ወጥቶ ጉዳዩን ሳይጉላላ በጊዜ ጨርሶ እንዲመለስ ማድረግ ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮ ቴሌኮም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መስራት ይኖርበታል።
የ5ጂ ቴክኖሎጂ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች መዘርጋቱም “ስማርት ትራፊክ” ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መሰረተ ልማት መኖሩን የሚያመላክት ነው። በመግቢያችን ላይ የዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው እንግዶች አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ዘርፉ በተለያዩ ችግሮች እየተፈተነ መሆኑን አመላክተዋል። ኢትዮ ቴሌኮም የኔትወርክ መሰረተ ልማቱን ዘመኑ ወደፈቀደው ልህቀት እያደረስኩ ነው ከማለቱም ባሻገር የትራፊክ ፍሰቱን የሚያሰናክሉ ችግሮችን ይፈታል ያለውን ቴክኖሎጂ እያስተዋወቀ ይገኛል። መንግሥትና የሚመለከተው አካል የስማርት ትራፊክ ቴክኖሎጂ መሰረተ ልማትን ተግባር ላይ ማዋል ቢችል የዘርፉን ማነቆዎች ይፈታ ይሆን?
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ኅዳር 6/ 2015 ዓ.ም