ዓለማችን ከተፈጠረችበት ጊዜ አንስቶ እጅግ በጣም አስከፊ ሁኔታዎችን አሳልፋለች። አንዳንዶች በታሪክ ምዕራፍ ተከፋፍለው ተፅፈዋል፤ ሌሎች ደግሞ ትኩረት ሳይሰጣቸው አሊያም ሆን ተብለው ታልፈዋል። እነዚህ የታሪክ ምዕራፎች ሲከፈቱ ብዙ ነገሮች ይታያሉ፤ ይሰማሉ።
በነዚህ ታሪኮች አለማችን እጅግ ዘግናኝ የሚባሉ ግፎችን አስተናግዳለች። አንዳንዶቹን ለመስማት ቀርቶ ለማሰብም የሚከብድ፤ የሚያስቸግሩ ናቸው። ይህን ሐሳብ ያጠናክርልን ዘንድ የተወሰኑ ነጥቦችን ማንሳት ጠቃሚ ይመስኛል።
በዚህች ምድር ላይ ከተካሄዱ አሳዛኝ እውነታዎች / ትራጄዲዎች/ መካከል አንደኛው የዓለም ጦርነት በብዙ የሚታወስ ነው። ጦርነቱ የሰውን ልጅ እጄድ ብዙ ዋጋ ያስከፈለ፤ በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ በጥቁርነቱ የሚጠቀስ ነው።
የጦርነት መነሻው እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም በጦርነቱ ግን በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ያልተሳተፉ አገራት አልነበሩም። በዚህ ጦርነት የዓለም ህዝቦች ለሁለት ጎራ ተከፍለው በእሳት ቋያ ተለባልበዋል። ታሪክ ይቅር የማይችለው በደሎች ተፈጽመዋል።
በዚህ ብቻ አላበቃም ከጥቂት አመታት እፎይታ በኋላ ዳግም የተከሰተው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በከፋ መልኩ ዓለምን የሰውን ልጅ ዋጋ አስከፍሏል ።
የአንደኛው ዓለም ጦርነት ተቀፅላ፤ የቂም በቀል መወጣጫ በሆነው የሁለተኛው ዓለም ጦርነትም ከአንደኛው ዓለም ጦርነት እጅግ የከፋ እና ምድር ለመሸከም የከበዳት ሁነት ተከስቶ አልፏል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነትም በምንም ሊተካ የማይችል የሰው ሕይወት ተገብሯል፤ አጥንት ተከስክሷል፤ ደም ፈሷል።
አንዳንድ ክስተቶች በጊዜያቸው አልፈው ጠባሳቸው ግን አሁንም ድረስ የዘለቀ ነው። ለአብነት አሜሪካ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፈርጣማ ክንዷ ለማሳየት ስትል በሰው ልጅ ህሊና ፈፅሞ የማይታሰብ ድርጊት ፈፅማለች። ሄሮሽማ እና ነጋሳኪ በሚባሉ ሁለት የጃፓን ከተሞች ላይ አቶሚክ ቦንብ በማዝነብ።
ዓለም በቀደሙት ዘመናት እነዚህን ብቻ ሳይሆን በርካታ ሰው ሠራሽ አሰቃቂ መከራ እና ስቃዮችን አስተናግዳለን። ይህ ሁሉ ሲሆን ግማሹ በመንፈሳዊ መንገድ ዓለምን በእርቅና ሠላም መንገድ ሲያክም ሌላው ደግሞ እያቆሠላት፤ እያቆሰላት ዘመናትን ተሻግረናል። በመጨረሻ ግን ዓለም ለተከሰቱና ለሚከሰቱ እኩይ ተግባራት በሙሉ ይቅርታ ፍቱን መድሃኒት ሆኖ አግኝታዋለች፤ በዚህም ዛሬን ለመፈወሥ ረጅም ርቀት ሄዳለች።
ኢትዮጵያም የዚህ ዓለም አቀፍ ታሪክ አካል በመሆኗ በሦስት ሺህ ዘመን ተመሳሳይ ታሪኳ ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎች ተጋፍጠውባታል። በውስጥ ጠላቶች ሲነሱባት፤ ከውጭ ጠላቶች ሲያሸብሯት ዛሬ ደርሳለች፤ ወደፊትም ተመሳሳይ ችግሮች እንደማያጋጥሟት ማስተማመኛ የላትም።
በታሪክ አውድ ብዙ ግራጫ ሁኔታዎችን ማለፍ ግድ ከመሆኑ አንጻር፤ ኢትዮጵያ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያለፈችበትን ሁኔታ በቅጡ የማይረዳ ዜጋ ይኖራል ተብሎ አይታመንም። በዚህ ጦርነት ያልከፈልነው ዋጋ የለም። ከብዙ ዋጋ መክፈል በኋላም ወደ ሰላም በሚወስደው መንገድ ላይ ተገኝተናል። እሰየው የሚያሰኝ ጉዳይ ነው።
ስለ ሰላም ጥቅም ሆነ የጦርነትን አውዳሚነት ከኢትዮጵያዊ የተሻለ የሚረዳው አለ ብዬ አላምንም። የቀደሙትን የጦርነት ዘመናት ትተን ባለፉት ሁለት ዓመታት ያሳለፍነው የጦርነት ጊዜ ማየት ብቻ በራሱ በቂ ነው።
በነዚህ ቀናቶች ከፍ ላሉ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመቶች ተዳርገናል። ስሜትና መንፈስን የሚጎዱ የጦርነትና የጥፋት ዜናዎችን ለመስማት ተገደናል። ብዙዎቻችን የዚህ አስከፊ ግዜ ማብቂያውን ረዝሞብን መጨረሻው ቅርብ እንዲሆን አጥብቅን ጸልየናል።
ከሰሞኑ በመንግስትና በሕወሓት መካከል በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተደረሰውን ሥምምነት ተከትሎ እፎይ የሚያሰኙ ዜናዎችን እየሰማን እንገኛለን። ነገዎችንም በተሻለ ተስፋ እንድንጠብቅ የሚያስችል መነቃቃትም በውስጣችን እየተፈጠረ ነው።
ይህንን አገርን እፎይ ያስባለ ስምምነት በበጎ መንፈስ መረዳት ያልቻሉ ኃይሎች የሠላም ስምምነቱን ለማደናቀፍ በአውሮፓ እና አሜሪካ ተቀምጠው ከተቃውሞ ሰልፍ ጀምሮ ያዋጣናል ያሉትን ሁሉ እየሞከሩ ይገኛል።
እነዚህ ኃይሎች ከግጭት አካባቢዎች እርቀው ከመገኘታቸው አንጻር የሰላም ስምምነቱ ትርጉም በአግባቡ መረዳት የቻሉ አይመስሉም። በአገር ውስጥ ለምንኖር የሰላም ስምምነቱ ምን ዓይነት ያልታሰበ ሲሳይ ይዞልን እንደመጣ የተገነዘቡት አይመስሉም። ይልቁንም የጦርነት ከበሮ በመደለቅ አገርና ህዝብን ለተጨማሪ እልቂት ለመዳረግ እየተጉ ነው ።
እነዚህ ሀይሎች ወቅት እየተበቁ አንዴ የሰላም ሀዋሪያ ሌላ ጊዜ የጦርነት ሰባኪ በመሆን ወጥ ባልሆነ ስብእና እየሄዱበት ያለው የትፋት መንገድ መዳረሻው ጥፋት ስለመሆኑ ለማንም ማሰብ ለሚችል ሰው የሚደበቅ አይደለም። ግልፅም ይሁን አደባባይ የሞላው አላማቸው ይሀው ነው።
እዚህ ላይ ላነሳ የፈለኩት የእነዚህ ኃይሎች የጥፋት ተልእኮ አይደለም፤ በዚህ መንገድ እየሄዱበት ካለው መንገድና መንገዱ በቀደሙት ወቅቶች እንደአገር ካስከፈለን ዋጋ አንጻር እውነታው ከሁሉም ዜጋ የተሰወረ ነው የሚል እምነት የለኝም።
ከዛ ይልቅ እኛ የጉዳዩ ባለቤቶች፤ የጥፋቱ ገፈት ቀማሾች ምን ማድረግ አለብን የሚለው ለማንሳት ነው። ለዚህ ደግሞ ዋናው ማድረግ የሚጠበቅብን ለእነዚህ አካላት ጆሯችንን በመንፈግ ለሳላም ስምምነቱ ስኬት የሚጠበቅብንን ሁሉ ማድረግ ነው። ይህን ደግሞ የምናደርገው ሥምምነቱ በእለት ተእለት ህይወት ውስጥ ያለውን ከፍ ያለ ፋይዳ በመረዳት ነው።
ከሰላም ማጣቱ ጎን ለጎን እየተፈታተንን ያለው የኖሩ ውድነት ሆነ ማህበራዊ ምስቅልቅል በአንድም ይሁን በሌላ ከጦርነቱ ጋር የተያያዘ መሆኑን በደንብ ልንገነዘብ ይገባል። የስምምነቱ ተግባራዊነት ለችግሮቹ ዋነኛ መፍትሄ መሆኑንም ማስተዋል ያስፈልጋል።
ከዚህም በላይ ለስምምነቱ ተግባራዊነት የአቅማችንን የምናደርገውም ለነገ ልጆቻችን ከእርስ በእርስ ግጭት የተላቀቀችና የበለጸገች ኢትዮጵያን የማስረከብ ታላቅ አገራዊ ኃላፊነትም ስላለብን ጭምር መሆኑን ማጤን ይገባል።
አንዳንድ አካላት የሰላም ሥምምነቱ በተደራዳሪ በመንግስት እና በሕወሓት ተወካዮች መካከል ተጀምሮ የሚያልቅ እየመሰላቸው ራሳቸውን ለጉዳዩ ሁለተኛ ወገን ሲያደርጉ ይስተዋላል። ይህ ሁኔታ ብዙ የሚያራምድ አይደለም፤ ለስምምነቱ ተፈጻሚነትም እንደ ክፍተት ሊታይ የሚገባ ነው።
እያንዳንዱ ዜጋ የአቅሙን ያህል የሠላም ስምምነቱን መደገፍ፤ ስምምነቱን የሚያደናቅፉ ተግባራትን ከመከወን መታቀብ፤ በመልሶ ማልማት ስራዎች መሳተፍ፤ ከሁሉም በላይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ከሚደረግ የብሽሽቅ፤ የአሸናፊና ተሸናፊ ትርክት ራሱን በማቀብና ኃላፊነትን በመወጣት የሰላሙ ሂደት አንድ አካል መሆን ይጠበቅበታል።
በየትኛውም ስሌት ሁላችንንም ተጠቃሚ የሚያደርገውን ይህንን ሥምምነት አጨብጭቦ መቀበል ብቻ ሳይሆን እስከመጨረሻ ውጤታማ እንዲሆን በያለንበት ቦታ እና ሁኔታ ድጋፍ ማድረግ ይኖርብናል።
አሁን በአገራችን የተጀመረው የሠላምና የይቅርታ መንገድ እሰየው የሚያስብል ነው። የተጀመረውን የሠላም መንገድ የበለጠ ፍሬያማ እንዲሆን በኢትዮጵያዊ ጨዋነትና ሆደ ሰፊነት ሁሉም ዜጋ ኃላፊነቱን መወጣት ይጠበቅበታል።
ዶክተር ጀኔኑስ
አዲስ ዘመን ኅዳር 6/ 2015 ዓ.ም