በአገራችን ውስጥ ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት ችግር መኖሩ ይታወቃል፡፡ ችግሩ ለዘመናት የተከማቸ መሆኑንም በተለያዩ አካላት በተለያዩ ጊዜያት የተከናወኑ ጥናቶች ያለመክታሉ፡፡ በተለይም በከተሞች አካባቢ የሚታየው የመኖሪያ ቤቶች ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱና የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ዝቅተኛ መሆኑ፣ በመላው የኢትዮጵያ ከተሞች የ1.2 ሚሊዮን የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ጉድለት መኖሩን ጉዳዩን በበላይነት የሚያስተዳድረው መንግሥታዊ አካል የከተማና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ችግሩን ለመፍታት መንግሥት በየጊዜው የተለያዩ ስልቶችን በመጠቀም በርካታ ጥረቶችን ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ችግሩ እየባሰበት መጣ እንጂ አልተሻሻለም፡፡ እንዲያውም በአገሪቱ ውስጥ እየጨመረ ከመጣው ኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ ችግሩ አሁን ላይ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ በተለይ በመዲናችን አዲስ አበባ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ እጅጉን አሳሳቢ ሆኗል፡፡ የመኖሪያ ቤት ችግር ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የሚወጡ የነገ አገር ተረካቢ ወጣቶችንም ጭምር የሚፈታተን የዘመኑ ተግዳሮት እየሆነ መጥቷል፡፡ በወጣትነታቸው ቤተሰብ ላይ ሸክም የሆኑ ዜጎች እየበዙ ነው፡፡ ፍቅረኛሞች በመኖሪያ ቤት ዕጦት ምክንያት ትዳር መመሥረት ተስኗቸዋል፡፡ ብዙዎቹ የመንግሥትና የግል ድርጅት ሠራተኞች ከወር ደመወዛቸው ከግማሽ የሚበልጠውን ለመኖሪያ ቤት ኪራይ ለመክፈል ይገደዳሉ፡፡
በሌላ በኩል መገናኛ ብዙኃኖቻችን በቤት ሽያጭ ማስታወቂያዎች ተጨናንቀዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ እንደአሸን ከፈሉ ኤፍ.ኤም ሬዲዮዎችና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃንን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን የአየር ሰዓት የተቆጣጠሩት እነዚሁ የቤት ሽያጭ ማስታወቂያዎች መሆናቸውን ማንም የሚታዘበው ሃቅ ነው፡፡ እንደዘወትር ጸሎት በየዕለቱ፣ እንደሰበር ዜና በየሰዓቱ፤ በዜና እወጃ ሰዓት ደግሞ በየደቂቃው የሚነበቡልንና የሚነበነቡልን እነዚሁ የማይመለከቱን የቅንጡ ቪላዎችና አፓርትመንቶች የሽያጭ ማስታወቂያዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ማስታወቂያዎች የሚነግሩን ቤቶች በስፋት እየተገነቡ እንደሚገኙ ነው፡፡ በእርግጥ በስፋት እየተገነቡ «እንድንገዛቸው» ሳምንቱን ሙሉ በየቀኑ ያለእረፍት 24/7 በሚዲያዎቻችን እየተዋወቁልንና ለገበያ እየቀረቡልን ያሉት «ቤቶች» አይደሉም፡፡ የተንጣለለ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ያላቸው፣ ሃያ አራት ሰዓት ንቁ ሆኖ የሚጠብቅ የደህንነት ካሜራ የተገጠመላቸው፣ መዋኛ ገንዳ፣ መሮጫ ትራክ ጭምር ያለው የስፖርት ሜዳ፣ መንፈስን የሚያድስ ውብ የመዝናኛና የመናፈሻ ስፍራ ያላቸው «ቤቶች» ናቸው፡፡
ምን ይሄ ብቻ በአራት አቅጣጫ መውጫና መግቢያ በር፣ አዲስ አበባን በሁሉም አቅጣጫ ለማየት የሚያስችል ሰገነት፣ የራሳቸው የከርሰ ምድር ውሃ ያላቸው…እንኳንስ ልንኖርበት ምን እንደሆነ እንኳን የማናውቀው ሌላም ሌላም ነገር ሁሉ ያላቸው እጅግ ዘመናዊ ውብና ቅንጡ ቪላዎችና አፓርትመንቶች ናቸው ማንም ሳይቀድመን በፍጥነት «ገዝተን» «የቤት ባለቤት» እንድንሆን እየተዋወቁልን የሚገኙት፡፡ በእውነቱ ነገሩ እጅጉን ግራ የሚያጋባና ሲበዛ የሚያስተዛዝብ ነው፡፡
እንደው ማን ይሙት፣ በመኖሪያ ቤት እጦት ችግር እየተሰቃየ ያለው ማን ነው? እንዲህ በብዛት ቤቶች መገንባትና መቅረብ የነበረባቸውስ ለማን ነው? እንዴት ያሉ ቤቶችስ ናቸው መገንባት የነበረባቸው? እሽ ይሁን ደግሞ፣ «ቤቶች» በመሆናቸው ብንስማማና መገንባትም መብት ነው ብለን ብንቀበል እንኳን እንዲህ ዓይነቶቹን እጅግ ውብና ቅንጡ ቪላዎችንና አፓርታማዎችን የሚፈልጉ «የመኖሪያ ቤት ችግር ያለባቸው» ዜጎቻችን ቁጥር ምን ያህል ነው? እርግጠኛ ነኝ፤ ጥናት ቢጠና እንዲህ ዓይነት ቤቶችን የሚፈልጉ «ቤት አልባ» ዜጎቻችን ቁጥር አንድ በመቶ እንኳን የሚሆን አይመስለኝም፡፡
ቀሪው 99 ነጥብ 9 የሚሆነው ሰፊው ሕዝብማ ከተማን ከላይ ወደታች የሚያሳይ ሰማይ ጠቀስ ሰገነት ያለው እጅግ ውብና ቅንጡ ቪላና አፓርታማ ሳይሆን መኖሪያ ቤት ነው የሚፈልገው፡፡ ሃያ አራት ሰዓት ንቁ ሆኖ የሚጠብቅ የደህንነት ካሜራ ሳይሆን ድህነቱን የሚያቃልልበትና ውሎ የሚገባበት፤ ከገቢው እኩል ኪራይ እየከፈለ ሳይሆን ግብር እየከፈለ፣ እንደጋርዮሽ ዘመን ሰው ከቦታ ቦታ እየተንከራተተ ሳይሆን ዘላቂ የሕሊና ሰላምና እረፍት አግኝቶ ተረጋግቶ የሚኖርበት መኖሪያ ቤት ነው የሚፈልገው፡፡ እናም ሁኔታው ብዙኃኑን ለቅሬታና ለብሶት እየዳረገ የሚገኝና ፍጹም ተገቢ ያልሆነ አካሄድ ነውና የሚመለከተው አካል ተገቢውን መፍትሔ ሊፈልግለት ይገባል፡፡
በእርግጥ ከላይ በመግቢያችን እንደጠቆምነው ይህንን አንገብጋቢ የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት መንግሥት አያሌ ጥረቶችን አድርጓል፡፡ በዚህም መሠረት በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን መንግሥት 750 ሺህ ቤት የመገንባት ዕቅድ አስቀምጦ ተንቀሳቀሷል፡፡ በሁለት ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራቱንም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡ የመጀመሪያው ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ላለው የኅብረተሰብ ክፍል በየዓመቱ 50 ሺህ ኮንዶሚኒየም ቤቶች በ1.5 ቢሊዮን ብር ወጪ መገንባት፣ ሁለተኛው ደግሞ ከፍተኛና መካከለኛ ገቢ ላለው የኅብረተሰብ ክፍል የሚሆኑ የሪል ስቴት ቤቶችን በግሉ ዘርፍ እንዲገነባ ዕድሉን ማመቻቸት የሚሉ ናቸው፡፡
የቅርብ ጊዜውን ስንመለከት ደግሞ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር፤ «ተደራሽ የቤት ልማት» በሚለው የዕቅዱ ንዑስ ክፍል በከተማና በገጠር ማዕከላት ተደራሽና ደረጃውን የጠበቀ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት ማሳደግ እንደ ዓላማ፤ በከተሞች የቤት አቅርቦት መጠን አሁን ካለበት 64 በመቶ ወደ 80 በመቶ እንዲያድግ 4,410,400 ቤቶች እንዲገነቡ ማድረግን እንደ ግብ አድርጎ በማስቀመጥ ችግሩ የሚፈታበትን መንገድ አመላክቷል፡፡ የሚገነቡት ቤቶችም በመንግሥት አስተባባሪነት 20 በመቶ፣ በመኖሪያ ቤት ኀብረት ሥራ ማኀበራት 35 በመቶ፣ በግለሰቦች 15 በመቶ፣ በሪል ስቴት ገንቢ ባለሀብቶች 10 በመቶ፣ በመንግሥትና በግል ባለሀብት አጋርነት 15 በመቶ እና በሽርክና (ጆይንት ቬንቸር) 5 በመቶ መሆናቸውንም በዝርዝር አቅዷል፡፡
ይሁን እንጂ ቀደም ብለን እንደጠቀስነው በስፋት እየተገነቡ ያሉት ቤቶች «መካከለኛ ገቢ ላለው የኅብረተሰብ ክፍል የሚሆኑ የሪል ስቴት ቤቶችን በግሉ ዘርፍ እንዲገነባ ዕድሉን ማመቻቸት» በሚለው ሥር ያሉት ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ በራሱ በመንግሥት መረጃ መሠረት አስር በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ አሁን ላይ ከምናየው ተነስተን ነገሩን ስንመረምር ግን እየተገነቡ ያሉት እጅግ ውብና ቅንጡ ቪላዎችና አፓርታማዎች አስር በመቶ ሳይሆን አስር ጊዜ አስር በመቶ ነው የሚመስለው፡፡ በዚህ ላይ በዚህ መንገድ በሪል ስቴቶች አማካኝነት እየተገነቡ ያሉ ቤቶች ዋጋቸው እንኳንስ መካከለኛ ገቢ ላለው የኅብረተሰብ ክፍል ለባለከፍተኛ ገቢዎቹም የሚቻል አይመስልም፡፡ ይህንኑ መሰለኛችን እነሆ በማስረጃ እናስደግፍና እውነት መሆኑን እናረጋግጥላችሁ፡-
«የቤት አቅርቦትና የዜጎች የመግዛት አቅም አዲስ አበባ ውስጥ በሪል ስቴቶች በሚገነቡ ቤቶች» በሚል ርዕስ በ2009 የተደረገ ጥናት እንደሚያመላክተው በመዲናዋ በቤት ግንባታ ላይ የተሰማሩ 125 የተመዘገቡ ሪል ስቴቶች ይገኛሉ፡፡ ይሁን እንጂ መካከለኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል ማዕከል አድርገው ቤት የሚገነቡት 16 ነጥብ 7 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው፡፡ 83 ነጥብ 3 የሚሆኑት ሪል ስቴቶች የሚገነቧቸው ቤቶች ዋጋቸው የመግዛት አቅም አለው ተብሎ ለሚታሰበው መካከለኛ ገቢ ላለው ኅብረተሰብ እንኳን የሚቀመስ አይደለም፤ ባለ ከፍተኛ ገቢዎቹን ወይንም እጅግ ውድ የሚባል ዋጋም ቢሆን መክፈል የሚችሉትን የናጠጡ ከበርቴዎችን ብቻ ነው፡፡ በስፋት እየተገነቡ ያሉትና እንድንገዛቸው በማይመለከተን ማስታወቂያ እያጥለቀለቁን ያሉት ግን እኒሁ ቤቶች «ናቸው»፡፡
ይበል ካሳ
አዲስ ዘመን ሰኞ ኀዳር 5 ቀን 2015 ዓ.ም