የኦሮምኛ ቋንቋ ድምጻዊ ነው:: ነገር ግን የሚዘፍነው ለኦሮሞ ብቻ አይደለም:: ሙዚቃ የዓለም ቋንቋ ናት የሚለውን ብሂል በሚያሳይ መልኩ ሙዚቃዎቹ ኦሮምኛ ቋንቋን ፈጽመው በማያውቁ ሰዎች ዘንድ ሁሉ የተወደዱ ናቸው:: እስካሁን ከ260 ዘፈኖች በላይ ተጫውቷል፤ ስድስት አልበሞችንም ለሕዝብ አድርሷል:: ይህ ሰው አሊ ቢራ ይባላል:: ለወራት የጤና እክል አጋጥሞት በሆስፒታል የከረመ ሲሆን በመጨረሻም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል:: ይሁንና በሕይወት እያለ በሙዚቃው ብዙዎችን አንድ ያደረገው ድምጻዊ በሞቱም ቢሆን ያን ተግባሩን አላቋረጠም:: መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሄር ቋንቋ እና ሃይማኖት ሳይለየው በአሊ ሞት አብሮ አዝኗል:: እኛም በዛሬው የዝነኞች ገፃችን የዚህን የሰላም እና የአንድነት ምልክት የሆነ የጥበብ ሰው ወርቃማ የሙዚቃ ሕይወት ልንቃኘው ወደድን:: እነሆ…
አሊ የተወለደው 1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ነው:: እናት እና አባቱ ያወጡለት ሥም አሊ መሐመድ ሙሳ ይባላል። ይሁንና ገና የ14 አመት ታዳጊ እያለ የኦሮሞን ሙዚቃ ለማሳድግ በተቋቋመው አፍረን ቀሎ የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ሲገባ በቡድኑ ውስጥ ሌላ አሊ የሚባል ልጅ በመኖሩ ሁለቱን ለመለየት መጀመሪያ ከሚያዜመው “ቢራ ዳ ባሬ” ዘፈን ወስደው “አሊ ቢራ” የሚለው ስም ተሰጠው። አሊ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በመድረስ ጅዲዳ እና በልዑል መኮንን ትምህርት ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ወደ አዲስ አበባ በመሄድ በካቴድራል ትምህርት ቤት ተከታትሏል። አሜሪካን አገር በሚገኘው የሳንታ ሞኒካ ኮሌጅም የሙዚቃ ትምህርት እንደተከታተለ ይነገራል።
አሊ ቢራ ለመጀመሪያ ጊዜ መድረክ ላይ መዝፈን የጀመረው በ15 ዓመቱ ማለትም በ1955 ዓ.ም ድሬዳዋ ውስጥ በአፍረን ቀሎ ባንድ ውስጥ በአጃቢ ድምጻዊነት ነው:: ከዚያም በክቡር ዘበኛ ኦርኬስትራ ተቀጥሮ ለሶስት ዓመታት ተጫውቷል። ችሎታው እየጎለበተ ሲሄድም አይቤክሥ ባንድን በመቀላቀል ለሥምንት ዓመታት የሙዚቃ ሥራውን በዲ-አፍሪክ ሲያቀርብ ቆይቷል። በአሊ ዙሪያ የተጻፈው የምስራቁ ዋርካ የተሰኘ መጽሀፍ ስለወቅቱ ሁኔታ እንዲህ ሲል ያብራራዋል::
እ.ኤ.አ በ1977 መጀመሪያ አካባቢ አሊ ከአይቤክስ ባንድ ጋር ኮንትራት መፈራረሙን ተከትሎ የዛምቤዚ ክለብንና የዲ አፍሪክ ሆቴልን ለቆ በራስ ሆቴል ስራ ጀመረ:: በወቅቱ የደንበኞ ቁጥር በመቀነሱ ምክንያት የአይቤክስ ባንድ በራስ ሆቴል የሚያቀርበውን ዝግጅት ቅዳሜ ማታ ብቻ ለማድረግ ተገዶ ነበር:: ማህሙድ አህመድንና ሌሎቹ ስመ-ጥር ሙዚቀኞችን ያቀፈው አይቤክስ ባንድ አሊን ማግኘቱ የተቀዛቀዘውን የሆቴሉን ደንበኛ በማነቃቃት ገቢው ከፍ እንዲል ማድረግ እንደሚችል በማመን ነበር 1000 ብር የወር ደመወዝ ሊከፍሉት የተስማሙት:: አሊ የስራ ስምምነቱን ከመቀበል ባለፈ በአጭር ጊዜ ውስጥ በ2000 ብር የአይቤክስ ሙዚቃ መሳሪያዎችን አክሲዮን መግዛት ቻለ::
እ.ኤ.አ በ1979 የአሊና የአይቤክስ ባንድ ወዳጅነት ጠንክሮ “አማሌሌ” የሚል መጠሪያ የተሰጠውን ለእርሱ አራተኛ ከባንዱ ጋር የመጀመሪያ የሆነውን አልበም ለገበያ አበቃ:: የአልበሙ መጠሪያ የሆነው “አማሌሌ” ዘፈን አሊ ባደገበት በምሥራቁ የሀገሪቱ ክፍል የሚዘወተር ባህላዊ ዘፈን ሲሆን፤ አሊና ማህሙድ አህመድ በኦሮምኛና በአማርኛ እየተቀባበሉ በዘመናዊ መልኩ ሊጫወቱት ችለዋል:: አይቤክስ ሙዚቃ ቤት የአልበሙ አሳታሚና አከፋፋይ ሲሆን በወቅቱ ኦሮሞዎች ስራውን የተቀበሉበት የደስታ ስሜት ዛሬ ድረስ በሕይወት ያሉ እማኞች በመገረም ያስታውሳሉ። “የሰዉ አቀባበልና ከአልበሙ ሽያጭ የተገኘው ትርፍ ከጠበቅነው በላይ ነበር” ይላል የሙዚቃ ቤቱ ባለቤት አቶ ጣሃ አህመድ (የማህሙድ አህመድ ወንድም) ስለአልበሙ ሲያስታውስ:: የአልበሙ ሽያጭ አስጨንቆት የነበረው ሙዚቃ ቤት የካሴቱን ዋጋ ከተለመደው 15 ብር ወደ 12 ብር እንዲወርድ አድርጎ የነበረ ሲሆን ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ቁጥሩ እጅግ የበዛ ሕዝብ አልበሙን በእጁ ለማስገባት በመፈለጉ ማዳረስ እንኳን አልተቻለም:: የመግዛት አቅምና አጋጣሚውን ያገኘ አልበሙን ተረባርቦ ገዛ:: ያልቻለው ደግሞ አንዱ ከአንዱ እየተዋዋሰ አልበሙን ይኮመኩም ያዘ::“አማሌሌ” አልበም በወቅቱ የነበረውን ፖለቲካዊ ውጥንቅጥ ከፍቅርና ከባህል ጋር ደባልቆ እያላቆጠ ለአደባባይ ቢያቀርበው የብዙዎችን ጆሮ አጠመደ፤ ከብዙዎችም አንደበት አልጠፋ አለ::
…እ.ኤ.አ 1979 የአይቤክስ፣ ዳህላክ እና ዋቢ ሸበሌ ባንዶች ያለፈ ታሪክ ከል የለበሰበት ዓመት ነበር:: ሱዳኖች የባንዶቹን መሳሪያ ተጫዋቾች ሀገራቸው ወስደው እንዲጫወቱ ስላግባቧቸውና ስምምነት ላይ ስለደረሱ ሶስቱም የሙዚቃ ቡድኖች ነፋስ እንዳየው ገለባ ብትንትን ብለው ፈረሱ። ይሄን ተከትሎም አንዳንድ የአይቤክስና የዳህላክ ባንድ አባላት ተሰባስበው ዋልያስ ባንድ በሚል ስያሜ በሂልተን ሆቴል መስራት ጀመሩ:: ማህሙድ አህመድም ባንዱን ተቀላቀለ:: ለአሊ ግልፅ ባልሆነ ምክንያት የአይቤክስ ባንድ አባላት ወደ ሂልተን ሄደው ስራ እንደጀመሩ በእሱ ምትክ ተክሌ ተክለእግዚ ቡድኑን እንዲቀላቀል አደረጉ። ከእነዚህ የሙዚቃ ቡድኖች የተረፉት ሌሎች ሙዚቀኞች በመሰባሰብ ሌላ ባንድ መስርተው በራስ ሆቴል ለመስራት ሃሳብ አቀረቡ:: የራስ ሆቴልም አሊን የሚቀላቅሉት ከሆነ ብቻ ሃሳባቸውን እንደሚቀበል አስታወቀ:: ሙዚቀኞቹም በመስማማታቸው ሙሉቀን መለሰ /ከዳህላክ ባንድ/፣ ዳዊት ሰንበታ /ቤዝ ጊታር ተጫዋች/፣ ግርማ ወልደሚካኤል /ሳክስፎን ተጫዋች/፣ ሽመልስ በየነ /ትራምፔት ተጫዋች በጋራ ሆነው ኢትዮ ስታር ባንድን መሰረቱ:: ኢትዮ-ስታር ባንድ ከራስ ሆቴል ኩኩ ሰብስቤ፣ ግርማ ጭብሳና ሌሎች ዘፋኞችን ጨምሮ በመያዝ ጅቡቲ፣ የመንና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በመዘዋወር የሙዚቃ ስራውን ማሳየት ችሏል። በጥቅሉ አሊ በራስ ሆቴል ለ7 ዓመታት የሰራ ሲሆን ከዚህም ውስጥ 3ቱን ዓመት ከአይቤክስ ባንድና ቀሪውን 4 ዓመት ደግሞ ከኢትዮ-ስታር ባንድ ጋር አሳልፏል:: አሊ ከዚያ በኋላ ከሀገር በመውጣት በተከታታይ ወደ ሳወዲ አረቢያ ፤ ስዊድን እና አሜሪካ በመሄድ የኖረ ሲሆን በርከት ላሉ ዓመታትም ከሀገር ርቆ ነበር::
አሊ ቢራ ከመዝፈንም ባሻገር ፒያኖ ፣ ጊታር ፣ እና ሊድ የተባሉ የሙዚቃ መሣሪያዎችን እንደሚጫወትም ይነገራል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ብዙዎች አሊን ከድምጻዊነትም በላይ በታጋይነት ያነሱታል:: በፈረንጆቹ 2019 ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ስለዚህ ጉዳይም ተጠይቆ ነበር:: አሊም እንዲህ ሲል መልሷል:: “የተመልካቹና ስለኔ የሚያወራ ሰው የሚያውቀውን ነው የሚያወራው። ታጋይ መሆኔን ወይም እምቢተኛ ከሆንኩኝ የሰው ትርጓሜ ነው። ስለ አሊ ቢራ የዛ ሰው ትርጓሜ ነው። ስለዚህ እኔ ሰዎች አሁን እንዳልሽኝ ታጋይ ነው ሲሉ፤ እርግጥ ታጋይ ማለት ትልቅ ነገር ነው። ስለ ሀቅ የሚታገል ከሆነ። እኔ የሀቅ ታጋይ ነኝ ብዬ ነው ራሴን የምፈርጀው። አንዳንድ ሰዎችም እንደዛ ይሉኛል። በተቃራኒውም የሚሉኝም አሉ። የሀቅ፣ የመብት፣ የሰላም፣ የበጎ ነገር ታጋይ ነኝ እላለሁ።”
አሊ ዓለምአቀፍ ሰው ነው:: በርካታ ቋንቋዎችን አቀላጥፎ ይናገራል:: አቀላጥፎ ከሚናገራቸው ቋንቋዎች ውስጥ ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ሶማሊኛ፣ አፋርኛ፣ ሃረሪኛ፣ አረብኛ እና እንግሊዝኛ በዋናነት ይጠቀሣሉ። ሙዚቃዎቹም ዓለም አቀፍ መልእክቶችን የያዙ ናቸው:: ስለዚህ ጉዳይም ሲያወጋ እንዲህ ይላል:: “በኦሮምኛ ሲን ጃለዳ” ካልኩ በአማርኛ እወድሻለሁ ማለት ነው። በእንግሊዘኛ “አይ ላቭ ዩ” ማለት ነው። በኦሮምኛ “ሲን ጃለዳ” ስለሆነ በሌሎች ቋንቋዎች መተርጎም አይችልም ማለት አይደለም። ተተርጎሞ ‘ግሎባል’ [ዓለም አቀፍ] ይሆናል። በፈረንሳይኛ፣ በቻይንኛም ይሁን በፈለገው ቋንቋ እወድሻለሁ፣ እወድሻለሁ ነው። አንድ ጊዜ አፍረንቀሎ ውስጥ ሳለን ሳንሱር ተደርጎ ነበር። ዘፈን በአማርኛ ተርጉሙና አምጡ ተብለናል። እኛ ማታ ለኮንሰርት ተዘጋጅተናል። እና ሁሉንም ነገር (ወደ 30 ዘፈን) በአማርኛ ተርጉሙ ተባልን። በኦሮምኛ “ጃለላ” ፍቅር ማለት ነው። ዘፈኑ ውስጥ ለአንዲት ልጅ ወይም ለፈለገው ነገር ፍቅር ሊኖረው ይችላል። ሰውየው “ጃለላ” ማለት ምንድን ነው? ሲለኝ ፍቅር ነው እላለሁ። ‘አዎ፤ [ፍቅር ማለት እንደሆነ] እናውቃለን፤ ግን እናንተ የምትሄዱበት መንገድ ይህ ፍቅር ምን አይነት ነው?’ አለኝ። ይታይሽ እንግዲህ አንድን ቃል በሁለት ቦታ ለመክፈል አይደለም “ጃለላ” የተባለው። “ጃለላ” ፍቅር ነው። የእናት፣ የአባት፣ የአገር [ሊሆን ይችላል]። ሙዚቃ መልዕክቱን ለሰው የሚያደርሰው የአንድ ቋንቋ ብቻ ሆኖ አይደለም። የዓለም ነው። በጎም መጥፎም ቢሆን። ሁሉም ቦታ ስላለ [ነው]።”
ሰዎች በሙዚቃው እና በዓለምአቀፋዊ ስብእናው ቢያውቁትም እሱ ግን ራሱን የሚገልጸው በተማሪነት ነው:: ”እኔ ተማሪ ነኝ። እኔ ብቻ ሳልሆን ምድር ላይ ወደ 7 ቢሊዮን ከምናምን ተማሪዎች አሉ። ከነዛ መሀል አንዱ ነኝ። ራሴን የማየው በዛ አይነት መንገድ ነው። ዛሬም እማራለሁ፤ ነገም እማራለሁ፤ ትላንትም ተማርኩኝ።”ብሏል::
አሊ ቢራ ታዋቂ በሙዚቃው ሙያ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ለሚቆጠሩ ዓመታት ላበረከተው አስተዋፅኦም ከጅማ እና ድሬዳዋ ዩኒቨርሰቲዎች የክብር ዶክትሬት ተሸላሚ ለመሆን የበቃ ሲሆን ባለፈው አመትም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እጅግ ትልቁን የክብር ሽልማት፤ የወርቅ ኒሻን ለአርቲስት አሊ አበርክቷል:: ባለቤቱ ሚስስ ሊሊ ማርቆስም በገዳ ሥርዓት መሠረት የ ‘ኦርሜሱ‘ (ኦሮሞ ማድረግ) ሥነ ሥርዓት ተደርጎላት ‘ኢሊሊ ቢራ‘ ተብላ ተሰይማለች:: ትርጉሙም የፀደይ አበባ ማለት ነው:: ከዚህም ባለፈ በጣም በርካታ ሽልማቶችን ከተለያዩ አካላት በየጊዜው ተረክቧል::
የአሊ ቢራ ዜና እረፍት ከተሰማ በኋላ በርካቶች ኀዘናቸውን በተለያየ መንገድ ገልጸዋል:: የተወሰኑትን እንደሚከተለው አስቀምጠናቸዋል::
“የአሊ ቢራ አሻራና ውርስ ፤ ፍቅር ፤ ስምምነትና ሰላም ነው!!”
አዴ ሊሊ ማርቆስ (የአሊ ቢራ ባለቤት)
“የአንጋፋው ድምጻዊ ዓሊ ቢራ ህልፈት ለኢትዮጵያ ጉዳት ነው። በዜማዎቹ ህብረትን፣ ጽናትንና ባህልን አቀንቅኗል። ለብዙዎችም አርአያ ሆኗል። ላደረግከው ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግንሃለች።”
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
“ዓሊ የነፃነት፣ የእኩልነት እና የእውነተኛ ወንድማማችነት ድምጽ ነው”-
የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ
አሊ ቢራ የተናገረውን የተገበረ፤ የዘፈነውን ሁሉ የኖረ የትውልዱ ህያው የፍቅር፣ የሀገር ወዳድነትና የፅናት ተምሳሌት ነው:: አሊ የሚጠበቅበትን ሁሉ አድርጎ አርፏል። አንጋፋው ከያኒ፣ የነፃነትና የፍትሕ ታጋዩ፣ የምስራቁ ዋርካ ነብስህ በሳለም ይረፍ። ለመላው ቤተሰቦቹ ወዳጆቹና አድናቂዎቹ ሁሉ መፅናናትን እመኛለሁ!! ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ!!”
የአዲስ አበባ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ
‘ቀልድ የሚያውቅ ታላቁንም ታናሹንም የሚያከብር ልዩ የጥበብ ሰው ነበር’
ድምጻዊ መሐሙድ አህመድ
“አሊ ቢራ ምሉዕ ሙዚቀኛ ነው” –
የሙዚቃ ባለሙያ ሰርጸ ፍሬስብሃት
አሉ ፈጣሪ የሰጠውን ሁሉ ለእኛ ሰጥቶናል:: ሕይወቱንም በዓላማ ኖሮታል:: የኖረው ለራሱ ሳይሆን ለሕዝብ ነበር
ፖለቲከኛ ጃዋር መሀመድ
ድምጻዊ አሊ ቢራ በስፋት በሚታወቅበት የኦሮምኛ ሙዚቃ ስልት አጨዋወቱ ወደር ያልተገኘለትና አረብኛን ጨምሮ በተለያዩ ቋንቋዎች የመጫወት ችሎታው ቋንቋውን የማይረዱትን አድማጮችን ሳይቀር ቀልብ መግዛት የቻለ ሀገራችን ካፈራቻቸው ስመ ጥርና አንጋፋ ድምጻውያን መካከል አንዱ ነበር
አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ)
በክቡር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ አሳዛኝ ህልፈት የተሰማኝን ኀዘን እየገልፅኩ፤ ለቤተሰቦቹ ፣ ለአድናቂዎቹ እናም በእግዚአብሔር ፈቃድ ለረጅም ዘመናት በሙያው ላገለገለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ መፅናናትን እመኛለሁ::
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/ 2015 ዓ.ም