አቶ አለማየሁ ማሞ ይባላሉ:: በጋዜጠኝነትና በደራሲነት በርካታ ዓመታትን አሳልፈዋል፤ ዛሬም ኑሯቸው ከኢትዮጵያ ውጭ ቢሆንም በትጋት ፣ ያለመታከት የተለያዩ መጽሀፍትን እየጻፉና እያሳተሙ አንባቢያንን ማስደሰታቸውን ቀጥለዋል:: በሕይወት ጉዟቸው የሰበሰቡትን እውቀት “ለትውልዱ ይድረስ” በሚል ውሳኔ እየጻፉ እያሳተሙ አገራቸው መጥተው እያስመረቁ ለገበያ እያቀረቡና አልፎ አልፎም ወጣቶች ከእኔ ሕይወት ተማሩ በማለት ልምዳቸውን እያካፈሉ እዚህ ደርሰዋል:: እኛም ተዝቆ ከማያልቀው የሕይወት ልምዳቸው የስራ ቆይታቸው አሁን ስላሉበት ሁኔታና የቀጣይ እቅዶቻቸውን በማንሳት የዚህ ሳምንት የሕይወት ገጽታ አምዳችን እንግዳ አድርገናቸዋል::
አቶ አለማየሁ ማሞ 1958 ዓ.ም አዲስ አበባ ቀበና አካባቢ ነው ተወልደው ያደጉት:: የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርትቸውንም ቀበና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ኮከበ ጽባህ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል::
“…እኔ ምንም እንኳን የሚጎላብኝ ኢትዮጵያዊነቴ ቢሆንም ትውልዴና እድገቴ አዲስ አበባ ከተማ ነው:: በአንደኛ ደረጃም ሆነ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በምማርበት ወቅት የደረጃ ተማሪ ነበርኩኝ ፤ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያሉት ደረጃዎችም የእኔ ነበሩ፤ በጊዜው ቀለሜዋ ከሚባሉ ተማሪዎች ተርታ የምሰለፍ ነበርኩ ፤ በተለይም አማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋ በጣም ይስቡኝ የነበረ ሲሆን ውጤቴም ከፍ ያለ ነበር ” ይላሉ::
ይህ የቋንቋ ፍቅራቸው ደግሞ ኋላ ላይ ለገቡበት የጋዜጠኝነትም ሆነ የድርሰት ዓለም ከፍ ያለ አቅምን የፈጠረላቸው ስለመሆኑ የሚናገሩት አቶ አለማየሁ ማንኛውንም መጽሀፍ ጋዜጣ መጽሔትና ሌሎችንም ማንበባቸው ደግሞ ዛሬ ላሉበት ደረጃ አብቅቷቸዋል::
አቶ አለማየሁ ስለ ትምህርት ቤት ቆይታቸው ሲናገሩ “…ከምንም በላይ በጣም አጠና ነበር፤ ከትምህርቱ ፈንጠር ባለ ሁኔታም የተገኘውን መጽሀፍ ከጓደኞቼ ጋር ተቀባብሎ ማንበብም ልምዴ ነበር:: የሚገርመው ነገር በወቅቱ የነበረው ተማሪ ለማንበብ የተፈጠረ ነበር ብል ማጋነን አይሆንም:: ይህንን ያልኩበት ዋናው ምክንያት ደግሞ ካለው የማንበብ ፍቅር የተነሳ ለእድሜያችን ያልተፈቀደ መጽሀፍን ለማንበብ እንኳን እንሻማ ነበር”::
አቶ አለማየሁ ጎበዝ ተማሪ ይሁኑ እንጂ በተለያዩ አገራዊ ምክንያቶች በሚመኙት ወይም በሚፈልጉት ልክ በትምህርታቸው አልገፉም:: ትምህርታቸውን ከ12ተኛ ክፍል አቋርጠው ሌሎች የሕይወት መንገዶችን መከተልም ነበረባቸው::
“…እንደ አለመታደል ይሁን ኋላ ላይ ደግሞ ለበጎ ብቻ በማላውቀው ሁኔታ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ወስጄ ውጤቴን እየጠበኩ ባለሁበት ጊዜ ብሔራዊ ውትድርና የሚባል አገልግሎት ታወጀ:: ውትድርናው ደግሞ ለመሄድ ፍቃደኛ ያልሆኑ ወጣቶችን እየጎተተ እሳት ውስጥ የሚከት ነበር:: እኔ ደግሞ በዛ ሕይወት ውስጥ የማለፍ ሃሳብ ስላልነበረኝ በጣሙን ግራ ተጋባሁ” በማለት የገጠማቸውን ይናገራሉ::
አቶ አለማየሁ ከብሔራዊ ውትድርና ማምለጫ የተለያዩ ሙከራዎችን ማድረግ ጀመሩ፤ ከሙከራዎቻቸው መካከል ደግሞ የመጀመሪያ ያደረጉት የኢትዮጵያ አየር ሃይል ሄዶ የአብራሪነት ሥልጠና መጠየቅ ነበር፤ በወቅቱ ጥያቄው ተቀባይነት ቢያገኝም የብሔራዊ ፈተና ውጤት ግን ስለሚያስፈልግ ያንን አምጡ ተባሉ፤ ውጤቱን ለማግኘት ደግሞ አምስት ወር መጠበቅ ግድ ነበር፤ አቶ አለማየሁ አምስት ወር ተሸሽገው የሚያመልጡበት ስላልነበራቸው ወደሌላ ሙከራ ዞሩ:: የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ጠቅላይ መምሪያ በመሄድ አመለከቱ ፤ እነሱም ቢሆኑ የብሔራዊ ፈተናው ውጤት እንደሚያስፈልግ ገለጹላቸው፤ ነገር ግን ውጤቱ እስከሚመጣ መርከበኛ መሆን እንደሚችሉ ተገለጸላቸው::
“… በወቅቱ የ12ተኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ውጤት እስኪመጣ 5 ወር ያህል መጠበቅ ነበረብኝ:: እዚህ ጋር ደግሞ እንደ አገር የታወጀ ብሔራዊ ውትድርና ነበር:: እሱን ለማምለጥ የሚያስችለኝ አቅም ወይንም ደግሞ ተሸሽጌ የማልፍበት አካባቢ ቢኖረኝ ኖሮ የፈተናዬን ውጤት እጠብቅ ነበር:: ይህ ባለመሆኑ ግን ወታደር ላለመሆን የተለያዩ አማራጮችን ማየት ነበረብኝ:: በዚህም የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ጠቅላይ መምሪያ ማመልከቻዬን ተቀብሎ በመርከበኝነት መሰልጠን እንደምችል ሲነግረኝ በመደሰት በ1975 ዓ.ም ሰኔ ወር ላይ ተቀላቀልኩ” በማለት ሁኔታውን ይናገራሉ::
የኢትዮጵያ ባህር ሃይል ጠቅላይ መምሪያን ከተቀላቀሉ በኋላም አዲስ አበባን ለመጀመሪያ ጊዜ ለቀው ወደማያውቋት አስመራ ከተማ ለሥልጠና ሄዱ:: አስመራ ቴክኒክ ማሰልጠኛ ማዕከል በመግባት ለአራት ወር መሰረታዊ የመርከበኝነት ትምህርት፤ እንዲሁም ለተጨማሪ አራት ወራት ደግሞ መደበኛ ትምህርትን ተከታትለው ጨረሱ::
“… በወቅቱ ልጆቻቸውን ሸሽገው የማስቀረት አቅም የነበራቸው ሰዎች አስቀርተዋል:: የእኔ ቤተሰቦች ግን ሸሽገው ከውትድርና የማስቀረት አቅም አልነበራቸውም:: ስለዚህ እኔና እኔን መሰል የአቅም ማነስ ያለባቸው ቤተሰብ ልጆች ወደ ውትደርና መሄድ አልያም ሌላ አማራጭ መፈለግ የግድ ነበረብን፤ ቤተሰቦቼም ባህር ሃይል መምሪያ ተቀላቅያለሁ ስላቸው መርቀው ከመሸኘት ሌላ አማራጭ አልነበራቸውም” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ::
” …እንኳን ከአዲስ አበባ ከቤተሰቤም ቤት ለአንድ ቀን እንኳን ወጥቼ አድሬ የማላውቀው ልጅ በሌላ አቅጣጫ አዲስ ሕይወትን ጀመርኩ፤ የሚገርምሽ ሕይወት 360 ዲግሪ ትሽከረከራለች ይባላል፤ ይህ እውነት መሆኑን ያወቅኩት በዛን ወቅት ነው:: ሁኔታውን ከባድ የሚያደርገው ደግሞ እኔና መሰሎቼን ከመንደር ወጣትነት ወደ ብቁ ወታደርነት ለማድረስ የሚደረገው ሥልጠና የስፖንጅ ፍራሽ አልነበረም ፤ ቆይታውም የጫጉላ ሽርሽር ተብሎ የሚጠራ አልሆነም ” በማለት የማያውቁትን ዓለም መቀላቀል ምን እንደሚመስል ይገልጻሉ::
በኑሮ ውስጥ አልጋ በአልጋ የሚባል መንገድ የለምና መውጣት መውረዱም አንዱ መገለጫው ነውና አቶ አለማየሁም ሕይወት ለእሳቸው የሰነቀችላቸውን ነገር ሁሉ ሊያዩ ተገደዱ፤ በሥልጠና ላይ እያሉም ጠዋት በሚሰማው ፊሽካ ተቀስቅሶ መነሳት ፤ ማታ አራት ሰዓት ላይ በግድም በውድም መብራትም ስለሚጠፋ መተኛት የግድ ሆነ::
በዚህ ውስጥ ራስን ለማላመድ እጅግ ከባድ ነበር የሚሉት አቶ አለማየሁ ከዚህ ወታደራዊ ሥነሥርዓት ዝንፍ ማለትም ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ እስከ ጉልበት ስራ ከበዛም እስር ቤት ድረስ የሚያደርስ መራር ቅጣትን የሚያስከትል መሆኑ በራሱ ነገሩን እጅግ እንደሚያከብደው ይናገራሉ:: ‘
አቶ አለማየሁ ሕግና ደንቡ በዚህ ያህል ደረጃ ጥብቅ መሆኑ ከባድ ቢሆንባቸውም እዛ ቦታ ላይ መገኘታቸው ብቻውን ደግሞ አይናቸውን እንዲከፍቱ አደረጋቸውⵆ “… እዛ ቦታ ላይ መገኘት በእውነት አይን ከፋች ነው፤ ምክንያቱም ከቤት ወጥተን የማናውቅ ልጆች ምናልባትም ከሶስት ከማይበልጡ የቤተሰብ አባላት ጋር ክፉና ደግ መነጋገር የለመድን ወጣቶች ፤ ከተለያየ ብሔር ብሔረሰቦች ፣ ቤተሰብና የአኗኗን ዘይቤ እንዲሁም ከተለያየ የትምህርት ደረጃ ከመጡ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ወጣቶች ጋር በአንድ ካምፕ ውስጥ መኖር፣ መነጋገር፣ ማጥናት፣ መውጣት ፣ መግባት ራሱን የቻለ የህይወት ዩኒቨርሲቲ ነው” በማለት ይገልጹታል::
አቶ አለማየሁ ይህ የወታደር ቤት የሥልጠና ጊዜ ለእድሜ ዘመናቸው ሁሉ ለስራ ለማህበራዊ ግንኙነት በጠቅላላው ሕይወትን ለሚያዩበት እይታ ሁሉ የተቃና ነገር እንዲኖራቸው እንዳደረጋቸውም ነው የሚናገሩት::
አቶ አለማየሁ ስለ ወታደር ቤት አንስተው አይጠግቡም ሃላፊነቱ ከባድ ውጣ ውረዱም አድካሚና አሰልቺ ቢሆንም በተለይ እሳቸውና ጓደኞቻቸው ከልጅነታቸው ጀምሮ ይወዱት የነበረውን የንባብ ባህል አጠናክረው እንዲቀጥሉበት ብዙ መጻህፍትን እንዲያነቡ ያስቻላቸው መሆኑን በፈገግታ ይናገራሉ::
“…ይገርምሻል እኔ መጀመሪያ ስቀጠር ያገኘኋቸው ሁሌም እንደምለው አብረውኝ በባህር የቀዘፉ ኋላም በምድር የጻፉ የምላቸው ሁለት ባህረኞች አሉ ፤ እነሱም ዘነበ ወላና እና ጸጋዬ ሀይሉ ብሩ ናቸው:: ከእነዚህ ሁለት ሰዎች ጋር አብረን ነበርን፤ የእኛ ቡድን ደግሞ መጻህፍትን አድኖ የሚያነብ ፤ ማንበብ ብቻ ሳይሆን ባነበብናቸው መጻህፍት ዙሪያ የምንወያይ ነበርን፤ ይህ ደግሞ ምናልባት በኋላ ሕይወቴ ምን ተጽዕኖ እንደሚያመጣ ርግጠኛ ባልሆንም በወቅቱ በጣም የምደሰትበት ነበር:: በዚህም በጣም መልካም ጊዜን አሳልፈናል:: ከመንደር ወጣትነትም ወደ ብቁ መርከበኝነት ተሸጋግረን ቀልጣፋና የአገር ፍቅር ምን እንደሆነ የምናውቅ ወጣቶች ሆነን ወጥተንበታል” ይላሉ ::
እሳቸውና ብዙዎቹ ባህር ሃይሉን የተቀላቀሉት ብሔራዊ ውትድርናን ለማምለጥ ቢሆንም ቅሉ በተሰጣቸው አገርን የማገልገል እድል ግን ታላቅነት ይሰማቸዋል:: ከአስራዎቹ እድሜም ተነስተው ወደበሳል ወጣትነት እድሜ ያሸጋገራቸው ዘመንም ስለሆነ መቼም የማይረሱት ሆኖ አልፏል::
“…አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አስመራን የሚያውቃት ትልልቅ ጸሀፍት በጻፏት ልክ ነው፤ እኔና መሰሎቼ በውስጧ ኖረን በሚያምሩት ጎዳናዎቿ ተንሸራሽረን ጥኡም ቡናዋን ቀምሰን ፤ ከሕዝቧ ጋር በፍቅር ተሳስበን ኖረን ነው:: በተለይም እኛ ከመሃል አገር ለሄድን ሰዎች ሁሉም ነገር ከለመድነው ወጣ ያለ ረቀቅ ያለ ነበርና ይህ ራሱን ችሎ በእኛ የሕይወት ለውጥ ላይ አስተዋጽዖ አድርጓል “ይላሉ::
ስራ በፍሪጌት 1616 ላይ
ሥልጠናው ተጠናቀቀ::አ ቶ አለማየሁና ጓደኞቻቸውም አሁን ብቁ መርከበኛ ሆነዋልና ወደ ስራ ተሰማሩ:: በዚህም እሳቸው ከዘጠኝ ጓደኞቻቸው ጋር ሶቭየት ሰራሽ በሆነችው ፍሪጌት 1616 አውዳሚ መርከብ ላይ ሆነ::
“…ሥልጠናው ተጠናቅቆ ሰርተፍኬታችን እንደታደለን የሰው እጥረት አለ በተባለው ቦታ ሁሉ ሠልጣኙ ተደለደለ፤ አንዳንዶች ምጽዋና አሰብ ሲደርሳቸው እኔና ዘጠኝ ጓደኞቼ ደግሞ ሶቭየት ሰራሽ በሆነችው ፍሪጌት 1616 አውዳሚ መርከብ ላይ ተመደብን ፤ በዚህም ቀይ ባህርን ከራስ ማሳር እስከ ራስ ዱሜራ ፤ጠንቅቀን እንድናውቅ ሆነ” ይላሉ::
በወቅቱ ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ላይ 1 ሺ ኪሎ ሜትር የባህር ክልል ነበራት ፤ ነገር ግን በዛ ካሉ የባህር ክልል ተካፋዮች ሁሉ ኢትዮጵያ የነበራት የመርከብ እንዲሁም የሰው ሃይል መጠን እጅግ ዝቅተኛ የነበረ ቢሆንም አካባቢው ከጠላት የመጠበቅ አስከብሮም ይዞ የመቆየት ሃላፊነቱ ግን እነ አቶ አለማየሁና ጓደኞቻቸው ከፍ ባለ ብቃትና ውጤት ተወጥተውታል::
ይህንን የአገርን ሉዓላዊነት የማስከበር ከፍ ያለ ተልዕኳቸውን ለሶስት ዓመታት ያህል በብቃት ቢወጡም ባላሰቡት መንገድ ግን ከባህር የመውረድ አጋጣሚ ተፈጠረባቸው::
“…የ12ተኛ ክፍል መልቀቂያ ውጤቴ መጀመሪያ 2 ነጥብ 6 ነበር፤ ነጥቡ ኮሌጅ የሚያስገባኝ ቢሆንም በወቅቱ ግን ትምህርት ቤት እንድገባ አልተፈቀደልኝም:: ስለዚህ ውጤቴን ለምን አላሻሽልም ብዬ ወደ አሰብ መደብ በመሄድ እንደገና ስፈተን ከፍተኛ ውጤት አመጣሁ:: ይህ ሲሆን ደግሞ ነጻ የትምህርት እድል ማግኘት እንደምችል ታመነበትና ሆስፒታል ተመድቦ በተለማማጅነት እየሰራ ነጻ የትምህርት እድሉን ይጠብቅ ተብዬ ተላኩ:: በመሆኑም ከመርከቧ ለመውረድ የቻልኩት የትምህርት ውጤቴን ማሻሻሌና በዛ ምክንያት ደግሞ ላገኝ የምችለው መልካም እድል ታሳቢ ሆኖልኝ ነው” በማለት ከመርከብ ስለወረዱበት አጋጣሚ ይናገራሉ::
ባህር ሃይሉ አገልግሎቱን እስካቆመበት ጊዜ ድረስ ያለውንም ጊዜ ያሳለፉት በሆስፒታል ውስጥ አገልግሎት በመስጠት ነው:: ነገር ግን ውጤቱ ጥሩ ነው ውጭ አገር ሄዶ ተምሮ ዶክተር ሆኖ ይመለስ የተባሉት ወጣት የእድል አልያም የአጋጣሚ ነገር ሆኖ ወደ ውጭ የመሄድ ሁኔታው ተቀይሮ ሌላ ነገር መጣ::
“… 1982 ዓ.ም ላይ በዝወይ ግንባር አርነት ኤርትራ ሽምቅ ተዋጊዎችና በእኛ የምድር ሠራዊት መካከል ምጽዋን ለመያዝ ከፍተኛ ጦርነት ተካሄደ፤ በዛ ጦርነት ደግሞ የኤርትራ ሽምቅ ተዋጊዎች ድል ቀናቸውና መሬቱ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር አዋሉት፤ መርከቦቻችንና ጀልባዎቻችን በሙሉ ወደ ባህር ሲያፈገፍጉ መሬት የነበርነው ግን ከዛ ማምለጥ ሳንችል ቀርተን ወደ እስር ቤት ገባን” በማለት ሁኔታውን ያስታውሳሉ::
ሁለት ዓመት ያህል በጦር አስረኝነት ያሳለፉት አቶ አለማየሁ ውጭ የሚያስኬደኝ ከፍተኛ የትምህርት እድል ቀረና የሕይወትን ትምህርት እማር ዘንድ ተገደድኩኝ በማለት ይገልጹታል:: ሁኔታው ለእሳቸው ትልቅ ትምህርት ቤት ነበር ከአዲስ አበባ ወጥተው አስመራ ሲሄዱ ብዙ የማያውቁትን ነገር እንደተማሩ እንዳዩ ሁሉ አሁንም ከለመዱት ነገር ተነስተው ከማያውቋቸው ሰዎች ጋር እስር ቤት መቆየታቸው በሕይወታቸው ተዝቆ የማያልቅ ትምህርትን እንዲያካብቱ አግዟቸዋል::
“…ሰው ጫማ ሳይኖረው በባዶ እግሩ ፣ ያልተጣራ የምንጭ ውሃ እየጠጣ ፣ አሸዋ ላይ ተኝቶ ሲያድር ከምንም በላይ ተስፋ ባጣ ምድረ በዳ ላይ ነገ ምን እንደሚመጣ እርግጠኛ ሳይሆን ሲኖር በሰውየው ላይ የሚያሳድረው የባህርይ ለውጥና ማንነት ምን እንደሆነ ተምሬበታለሁ፤ ይህ ደግሞ የትኛውም ኮሌጅ ብገባ ልማረው የማልችለው ነገር ነው:: ያ ነገር ደግሞ አሁንም ድረስ በሕይወቴ ይንጸባረቃል:: የሚገርምሽ አሁን በስደት ስኖር አብዛኛውን ሰው የሚያስፈራው የሚያስደነግጠው ከፎቅ ካልወረድኩ የሚያስብለው ነገር ለእኔ ምንም ነው:: ምክንያቱም በእንደዚያ ባለው የሕይወት ልምድ ውስጥ ማለፌ አጠንክሮኛል:: ሊከብደኝም አይችልም” በማለት ሁኔታውን ይገልጹታል::
ስራ የለመዱት ከአዲስ አበባ ርቀው የቆዩት በሚያገኙት ገቢ ቤተሰብንም ለመደጎም ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት መርከበኛ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ባዶ እጃቸው የመጡት አዲስ አበባ ቤተሰቦቻቸው ቤት ነበር:: ይህ ሁኔታ ደግሞ ለተማረ እንደሳቸው ደመወዝ ለለመደ ቀላል ባይሆንም የሕይወትን ገጽታ እንደአመጣጡ መቀበል ግድ ስለሆነ አቶ አለማየሁም ሁኔታውን ተቀብለው ለመኖር ተገደዱ::
“…ወቅቱ ከማንኛውም የሠራዊት ክፍል በበለጠ ለእኛ ነበር የመሸብን:: የቤተሰብ ረዳት የነበርኩ ሰው ተረጂ መሆን ነበረብኝ፤ ነገ ምን ይዞ እንደሚመጣም እርግጠኛ ስላልንበርኩ ተስፋ በቆረጠ ሁኔታ ተቀመጥኩ፤ መለስ ብዬ ሳስበው ደግሞ ከዛ አስከፊ ጦርነት ብዙ ጓደኞቼን ካጣሁበት የሰቆቃ እስር ቤት ነጥሎ ያወጣኝ ፈጣሪ በሕይወቴ ዓላማ ነበረው እያልኩም እጽናና ነበር ” ይላሉ::
የተፅናኑበት አምላካቸው ያላሳፈራቸው አቶ አለማየሁ ቀስ በቀስ ክፉው ጊዜ እያለፈ በሕይወታቸው ላይ ተጋርዶ የነበረው ጥቁር መጋረጃም በራሱ ጊዜ እየተገለጠ መጣ:: በተለይም አስመራ ሆነው የሚያውቁት ሠራዊቱን እየተመላለሰ የጥርስ ህክምና የሚሰጠው ዶክተር ጨለማውን ሊገፍላቸው አዲስ ቀን ሊያሳያቸው ቻለ::
“…አንድ የጦሩ አባል ያልሆነ ነገር ግን አስመራ እየመጣ ሠራዊቱን የጥርስ ህክምና የሚሰጥ ዶክተር ነበር በወቅቱ መጥቶ ሲያክመን እንድረዳው እኔ ብቻ እላክ ስለነበር ከልክ በላይ ተግባብተናል:: አንድ ቀን ቁጭ ብዬ ሳስብ ለምን እሱን አላገኘውም ብዬ አገኘሁት እሱም ያንን ልምዴን ስለሚያውቅ በራሱ ክሊኒክ ውስጥ በረዳትነት ቀጠረኝ” በማለት የአዲስ ሕይወት ጅማሬያቸውን ይናገራሉ::
አቶ አለማየሁ ከቤት ወጥተው ስራ መሄድ ደመወዝ ተቀብለው ተስፋቸው መለምለም ያዘ ይህ ሁኔታ ደግሞ ሌላ የስራ በርም ከፈተላቸው:: በወቅቱ ሀኪሞች መደበኛውን የስራ ሰዓታቸውን በመንግሥት ሆስፒታል ያሳልፉና ማታ በግል ክሊኒካቸው ይሰራሉ እሳቸው ደግሞ ይህ ሰው ክሊኒኩ መጥቶ ስራውን እስከሚጀመር ድረስ ታካሚዎችን በመመዝገብና ካርድ በማውጣት ያግዙታል:: አቶ አለማየሁ ግን ስራዬ ይህ ብቻ ነው ብለው አልተቀመጡም ውስጣቸው ያለውን የጽሁፍ ችሎታ አወጡበት ብዙ ጽሁፎችን ጽፈው ለግል ፕሬሶች መላክ ጀመሩ::
“…ወቅቱ ለኢትዮጵያ አዲስ የሆነው የፕሬስ ነጻነት አዋጅ ታውጆ በርካታ መጽሄቶች ጋዜጦች የሚታተሙበት ጊዜ ነበር፤ እኔ ደግሞ ክሊኒክ ቁጭ ብዬ ብዙ ሰዓት ነበረኝና አንዳንድ ነገሮች እየጻፍኩ ለመጽሄቶች ለጋዜጦች መስጠት ጀመርኩ፤ በዚህ ሁኔታ ብቻ 78 ረጃጅምና አጫጭር ጽሁፎችን በተለያዩ መጽሄትና ጋዜጦች ላይ ታተሙልኝ:: የተወሰኑት ሲከፍሉኝ እንደ አዲስ ዘመን ያሉት ጋዜጦች ደግሞ የመማሪያ ድልድዮቼ ነበሩ” ይላሉ::
ይህ ሁኔታ ስላበረታታቸውም አሁን እቅድ ማቀድ ጀመሩ በሚቀጥለው ይህንን ያህል ጽሁፍ ለዚህኛው እያሉም መከፋፈል ያዙ ፤ ነገር ግን ይህንን እቅዳቸው የሚቀድም ያልታሰበ ሁኔታ በሕይወታቸው ተከሰተ:: አቶ አለማየሁም አቅጣጫቸውን ቀየሩ::
ጥሪ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
አቶ አለማየሁ በሚሰሩት ስራ ምክንያት የወቅቱ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ደምሴ ጽጌ ቢሯቸው እንደሚፈልጓቸው ጥሪ ደረሳቸው:: ሁኔታው ትንሽ ግር ቢላቸውም በጽሁፋቸው ላይ ጥያቄ ሊጠየቁ እንደሚችሉ ገምተው መልሳቸውንም በደንብ አስበውና ተዘጋጅተው ወደተጠሩበት ቢሮ ሄዱ::
“…የወቅቱ ፖለቲካ ከበድ ያለ ስለነበር የመሰለኝ በጽሁፌ ውስጥ ችግር ተገኝቶ እሱን እንዳብራራ የተጠራሁ ነበር:: እናም እሱን ለማስረዳትም ዝግጅት አድርጌ ሄድኩ:: ቢሮ ስገባ ዋና አዘጋጁ “ጽሁፎችህን እንወዳቸዋለን ለምን ከእኛ ጋር በጊዜያዊ ቅጥር አብረኸን አትሰራም” ? አለኝ፤ የጠበኩትና የተነገረኝ ነገር ተለያዩ ሲሆኑ ጋዜጠኛ ሆናለሁ የሚል ሃሳብም ስላልነበረኝ በጣም ተደናግጬ ላስብበት ብዬ ወጣሁ”::
ቆም ብለው ማሰብን የፈለጉት አቶ አለማየሁ ጥያቄውን ለመቀበል ሶስት ወራት ወሰደባቸው በእነዚህ ወራቶችም መስሪያ ቤቱን ብቀላቀል ከማገኘው የገንዘብ ጥቅም ባሻገር ለአገሬና ለሕዝቤ ምን አበረክታለሁ የሚለውን ሲያስቡ በተለይም የሕዝብን ችግር ከመፍታት አንጻር ከጋዜጠኝነት የተሻለ እድል እንደማይኖር ስለገባቸው ዘግይተውም ቢሆን የአዲስ ዘመን ዋና አዘጋጅን ጥያቄ ተቀበሉ ቦታውም ለእሳቸው የተባለ ስለነበር አልተያዘም እና በ 347 ብር ደመወዝ በጊዜያዊ (ፍሪላንስ )ሰራተኝነት ተቀጥረው መታወቂያ ተሰጣቸው::
ከፍ ባለ የስራ ሞራልና ተነሳሽነት ስራቸውን የተቀላቀሉት አቶ አለማየሁ ለሚሰሩት ስራ ገደብ አላበጁም፤ ከሞላ ጎደል ሁሉም አምድ ላይ አሻራቸውን አሳርፈዋል ፤ ከመደበኛ ዜና ጀምሮ በምክትል አዘጋጆች እምነት የተጣለባቸው ባለሙያ ስለነበሩ ርዕሰ አንቀጽ እስከመጻፍ ድረስ እድልን ያገኙ እድሉንም በአግባቡ የተጠቀሙና ኮከብ ሰራተኛ ተብለው ከወቅቱ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ እጅ ሽልማትንም የተቀበሉ ሆኑ::
“…አዲስ ዘመን ጋዜጣን ሳስታውስ ሁሌም ደስ የሚለኝ መስኩ ጠባብ አለመሆኑና በሁሉም አቅጣጫ ሊጻፍበት የሚችል መሆኑ ነው:: እኔም በሚገባ ተመላለስኩበት :: በህይወቴም ትልቁ ዩኒቨርሲቲ ነበር:: እየተማርኩ የኪስ ገንዘብ የሚከፈለኝ አይነት ስሜት ነበር የሚሰማኝ:: እስከ አሁን ድረስ እየመነዘርኩ የምበላው ሀብት ካለኝም ያኔ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ያካበትኩት ልምድ ነው::” ይላሉ::
በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ቆይታቸውም በጊዜያዊ ሰራተኝነት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ታይቶ ወደ ቋሚ ሰራተኛ መሸጋገራቸው ተነገራቸው ፤ ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ስህተት እንደሆነና አሁንም ጊዜያዊ እንደሆኑ ሰሙ፤ ሌላው በቂ አቅም እንዳካበቱ ተሰማቸውና ራሴን ችዬ ልስራ አሉ፤ እነዚህ ሁኔታዎች ተገጣጠሙና በግላቸው ለመስራት በማሰብ ራሳቸው መልቀቂያ አስገብተው የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ቆይታቸውን ቋጩ::
አዲስ ዘመንን ለቀው የግል ስራቸውን እስከሚጀምሩ ድረስ በአንድ ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ የትርጉም ስራን መስራት ጀመሩ:: በዚህ ስራቸው ጥሩ ክፍያን ያገኙ ስለነበር ደስተኛም አደረጋቸው:: እግረ መንገዳቸውንም የራሳቸውን መጻህፍት ማዘጋጀት ይዘው ነበር::
በ1993 ዓ.ም ሲዘጋጁ የነበሩ ሶስት መጽሀፍትን ለህትመት አበቁ:: ይህ ደግሞ ለአቶ አለማየሁ ትልቁ የሕይወት ግባቸው ሆነ :: የመጀመሪያውን መሰናክል በማለፋቸውና አንዱ አንዱን እያሳተመ እሳቸው እየጻፉ ዛሬ ላይ ደረሱ::
ስደት
“…የሞኝ ትከሻ ሲመታ ብልህን ያመዋል የሚባል አባባል አለ በወቅቱ የግል ፕሬስ ጋዜጠኞች ላይ ይደርስ የነበረው ነገር እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አልነበረም ፤ እኔም እራሴን በጥንቃቄ ይዤ መጓዜ ጠቀመኝ እንጂ ከክትትል ውጪ አልነበርኩም፤ በጠቅላላው ኢትዮጵያ ውስጥ እየጻፉ መኖር አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ፤ እኔ ደግሞ ከጽሁፍ መለያያት እንደማልችል ስለገባኝ ስደትን መርጬ ወደ እንግሊዝ ሄድኩ ተመልሼ መጥቼ ነበር :: ነገር ግን አሜሪካን ከሄድኩ በኋላ እዛው ቀረሁ” በማለት የስደት አካሄዳቸውን ያብራራሉ::
በሁለት እግራቸው እስኪቆሙ አገሩን፣ አድባሩን፣ አውጋሩን እስኪላመዱ ለመኖር የሚሆናቸውን ነገርም እስከሚያመቻቹ ድረስ ጽሁፍን አልጻፉም ነበር፤ ነገር ግን ሶስት ያህል ዓመታትን በዚህ ሁኔታ ካሳለፉ በኋላ “መኖር አሜሪካ ” የሚለው መጻሀፋቸው ታተመ:: ይህ ፋና ወጊ የሆነው መጽሀፍም ከኋላው 29 ያህል መጻህፍትን አስከትሎ እዚህ ደርሷል::
“…ከትጋቴ ፕሬስ ካካበትኩት ልምድ ለስነ ጽሁፍ ካለኝ ፍቅር ባሻገር በሁለት ክንፎች የምጽፍ መሆኔ እድሌን ሰፊ ያደረገልኝ ይመስለኛል:: በአንዱ ወገን ለጠቅላላ እውቀት የሚበጁ በሌላ በኩል ደግሞ ለመንፈሳዊ እውቀት የሚሆኑ ሁለት አይነት ጽሁፎችን የመጻፍ አቅም አለኝ:: በምንም መልኩ ስራ ፈት ወይም ፍሬ ቢስ ልሆን አልችልም” ይላሉ::
ጥቂቶቹ የኢትዮጵያ ባህር ሃይል አባላት አስደናቂ ግለ ታሪኮች
ይህ መጽሀፍ በአቶ አለማየሁ አገላለጽ አብረዋቸው ለቆረሱ የቀይ ባህርን የጨው ውሃ ለተጋሯቸው ብዙ አብረዋቸው ላሳለፉ ነገር ግን በእድሜያቸው ከፍ ላሉ ከእድሜም ባሻገር አልጋ ላይ ለወደቁ ፤ ከአገልግሎታቸው ባህርይ የተነሳ ትዳር ላልመሰረቱ ፤እሱ ብቻም አይደለም ፈጣሪ ፈቅዶ ራሳቸውን ላልተኩ (ላልወለዱ) አሁን ላይ ጧሪ ቀባሪ ለሌላቸው ባህረተኞች ኑሮ መደጎሚያ ይሆን ዘንድ የመጽሀፉ ሙሉ ሽያጭ ተሰጥቷል ይላሉ::
የቤተሰብ ሁኔታ
አሜሪካን አገር ስሄድ አንድ ሻንጣ ብቻ ይዤ ነው የወጣሁት እዛ ከደረስኩ በኋላ ግን ባለቤቴን ተዋውቄ ተጫጭተን ኋላም ተጋብተን ሁለት ልጆች ወልጃለሁ:: ሴቷና ትልቋ ልጄ በጣም ጎበዝ ባለብዙ ተሰጥኦ ከመሆኗም በላይ በጣም ጎበዝ ተማሪ ስለሆነች 15 ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲዎች ነጻ የትምህርት እድል ፈቅደውላት አሁን ወደ የን ዩኒቨርሲቲ ገብታ የከፍተኛ ትምህርቷን በመከታተል ላይ ናት::
ታናሽ ወንድሟም ዘንድሮ 12ተኛ ክፍል ትምህርቱን እየተከታተለ ሲሆን እሱም ጎበዝ ልጅ ነው:: በሚገርም ሁኔታ ሁለቱም የጽነ ጽሁፍ ዝንባሌው ያላቸው ናቸው:: ከምንም በላይ የንባብ ባህልን ለማውረስ ችያለሁ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ::
መልዕክት
አቶ አለማየሁ በተለይም አገራችን የራሷን ችግር በራሷ እንዳትፈታ በውጭ ሚዲያዎች የሚደርሰውን ጫና አስመልክተው እንደሚሉትም “….ኢትዮጵያ መሰል ጫናዎች ሲደርሱባት ይህ የመጀመሪያ አይደለም ፤ ንጉሠ ነገሥቱ ድምጻቸውን ሊያሰሙ ወደ ሊግ ኦቭ ኔሽን ከሄዱበት ዘመን ጀምሮ አገራችን ከመሰል ጣጣዎች አምልጣ አታውቅም፤ ነገር ግን አሁን የደረስንበት ትውልድ በተሻለ ሁኔታ ሊፈታው ስለሚገባ ሚዲያዎቻችን ራሳቸውን ማብቃት መቻል አለባቸው፤ ለሚነሱብን ጥያቄዎች ሁሉ መልስ የምንሰጥ ሊሆን ይገባል:: መልስ እያለን ዝምተኞች ከሆንን እንጠቃለን:: በመሆኑም ባለሙያው ከሁለት በላይ በሆኑ ቋንቋዎች ራሱን ማብቃት አለበት ፤ ይህ ሲሆን አንድ ሲጠይቁን ሁለት አድርገን መመለስ የምንችል እንሆናለን” ይላሉ::
“…በሕይወቴ የተማርኩትና የእኔ የምለው መርሔ ተስፋ አለመቁረጥ ነው:: ለተስፋ መቁረጥ እጅ እስካልሰጠን ድረስ ከፊታችን ሌሎች አማራጮች ይኖራሉ:: ከወደቅንበት ተነስተን አዋራችንን እያራገፍን ጉዟችንን መቀጠል አለብን” በማለት ለወጣቱ መልዕክታቸውንም አስተላልፈዋል::
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ኅዳር 4/ 2015 ዓ.ም