እሷ ከትውልድ አገሯ ርቃ ወደ ከተማ ስትዘልቅ መልካም ኑሮን ከጥሩ እንጀራ አስባ ነበር፡፡ በርከት ያሉ የአገሯ ልጆች ከቀያቸው ርቀው ስኬታማ
ሆነዋል፡፡ ገንዘብ አግኝተው ጥሪት ይዘው ከብረዋል፡፡ ያሻቸውን መንዝረው፣ የፈለጉትን ገዝተው ሸጠዋል፡፡
ከእነሱ መሀል አብዛኞቹ ወደ መንደር ሲመለሱ ዓይን ያርፍባቸዋል፡፡ ተከታያቸው ይበዛል፡፡ አድናቂ አክባሪያቸው ያይላል፡፡ በእነሱ አነጋገርና አለባበስ ተገራሚው ብዙ ነው፡፡ እነሱ ከተማ ኖረው ከተሜ ሆነዋል፡፡ ገጠሩን ርቀው፣ አምረው፣ ዘምነዋል፡፡ ሁሌም ይህን ያዩ የገጠር ልጆች በከተሜዎቹ ዘመንኞች ይማረካሉ፡፡ ምኞታቸው እነሱን መሆን ነው፡፡ ሃሳባቸው ዘመነኞቹ በሄዱበት መንገድ መቀጠል ነው፡፡
ዘለቃሽ ተሰማ ከቀናት በአንዱ የጉራጌ ምድር ጉንችሬን ርቃ መሀል አዲስ አበባ ገባች ፡፡ ከተማውን ባየች ጊዜ ከልብ ወደደችው፡፡ እውነትም ያገሯ ልጆች ከቀየው ቢወጡ፣ ቢርቁ እንደማይፈረድ ገባት፡፡ ከተማው ከአገሯ ይበልጥ ያምራል፡፡ በዚህ ስፍራ ሁሉ የደመቀ የተዋበ ነው፡፡
ከዚህ የሚታይ ውበት ባሻገር ሰርቶ ስለመለወጥ አሰበች፡፡ አዎ! ከበረታች፣ ከጣረች እንደሌሎች የማትሆንበት አልታያት አለ፡፡ በእርግጥ የከተማ ሕይወት እንደገጠር አይደለም፡፡ እሸቱ ከጓሮ፣ ወተቱ ከጓዳ እንዳሻው
አይገኝም ፡፡
ዘለቃሽ እግሮቿ ከከተማ መሀል ሲገኙ የኑሮውን ልዩነት አውቃለች፡፡ አሁን ራሷን ለማሸነፍ የመጀመሪያ ምርጫዋ ሰርቶ ማደር ብቻ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ ላቧን ጠፍ አድርጋ ፣ በጉልበቷ ማደር አለባት ፡፡ አዲስ አበባ እህቷን ጨምሮ የቅርብ ዘመዶች አሏት፡፡ ሁሉም ለፍተው ያድራሉ፡፡ የከተሜ እንግድነቱን ማርዘም አላሻትም፡፡ መተዳደሪያ ካለችው ሥራ ተቀጥራ መስራት ያዘች፡፡
ከሆቴሉ ኩሽና …
ዘለቃሽና አዲስ አበባ ከተገናኙ ጊዜያት
ተቆጥረዋል፡፡ ከአንድ ሆቴል ተቀጥራ የወጥቤት ሙያን ይዛለች፡፡ ስራው እረፍት ይሉት የለውም፡፡ በየቀኑ ለሚመጡ ደንበኞች በሰአት ምግብ ማድረስን
ይጠይቃል፡፡ የእጅ ሙያዋን ያዩ አሰሪዎቿ ዘለቃሽን ወደዋታል፡፡ እሷ ጉልበት ሙያዋን አትሰስትም ፡፡ የታዘዘችውን አጣፍጣ ታዘጋጀለች ፡፡ ከጠዋት እስከ ማታ ከኩሽና የማትወጣው ሰራተኛ ሲመሽ ድካም ይጥላታል፡፡ ጥቂት ጎኗን አሳርፋ ለነገው ስራ ትዘጋጃለች፡፡
በየቀኑ ዘለቃሽና አድካሚው ስራ
ይገናኛሉ፡፡ ሁሌም ከሽንኩርቱ ፣ ከበርበሬው፣ ከእሳት ከውሃው ስትል ትውላለች፡፡ የእጇን ሙያ የወጧን ጣዕም የለመዱ ደንበኞች ሆቴሉን አዘውትረዋል፡፡ አሰሪዎቿ ሙያዋን አይተው፣ ጉልበቷን ተጠቅመው ገበያቸውን
አድርተዋል፡፡ ዘለቃሽ ባተሌነቷ ቀጥሏል፡፡ ቀን ስትሰራ ውላ ማታ ዕንቅልፍ ይጥላታል፡፡ ድካም ያሸንፋታል፡፡
ዘለቃሽ ሌት ነግቶ ወፍ ሲንጫጫ ከምዳጃዋ ቀጠሮ አላት፡፡ በዚህ ሰአት የእሷን እጅ የሚሹ ደንበኞች ቁርስ ይጠብቃሉ ፡፡ ይህን አዋቂዋ ሴት የጠዋት ግዴታዋን አጠናቃ ለምሳው ዝግጅት ትፈጥናለች፡፡ ከሰዓታት በኋላ የሆቴሉ ደንበኞች ምግብ ይሻሉ፡፡ ፍላጎታቸው ሞልቶ የሃሳባቸው እንዲደርሰ አሁንም የዘለቃሽ እጆች
ይናፈቃሉ፡፡
ዘለቃሽ ለእሷ ተብሎ የተዘጋጀ የመኝታ ክፍል የላትም፡፡ ሁሉም በስራ ውሎ ወደቤቱ ሲገባ ከምድጃዋ ስር ፍራሽ አንጥፋ አረፍ ትላለች፡፡ ሁሌም ውሎ አዳሯ ኩሽናው መሆኑ አስከፍቷት አያውቅም፡፡ እሷ የዛሬ ጉዳቷ ለነገ ተስፋ መሆኑን ታውቃለች፡፡ የአሁኑ ልፋቷ ቆይቶ እንደሚከፍላት ሲገባት ድካሟን ትረሳለች፡፡ ይህን እያሰበች ዓይኖቿ በዕንቅልፍ ይከደናሉ፡፡ አካሏ በድካም ዝሎ ማንኮራፋት ፣ መቃዥት ትጀምራለች፡፡
አንድ ቀን ምሽት
ዘለቃሽ በዚህ ቀን እንደተለመደው በድካም ስትባዝን ውላለች፡፡ ከጠዋት አስከማታ ለደንበኞች ወጥ ስትሰራ ፣ ምግብ ስታዘጋጅ ፣ የታዘዘችውን ስትከውን አምሽታለች ፡፡ የዛሬው ድካሟ ከወትሮው ቢለይ ጎኗን ልታሳርፍ ከኩሽናው ፍራሽ አረፍ ፣ ጋደም
ብላለች ፡፡ አንዳንዴ ድካም ሲጠናባት የወደቀችበትን ትረሳለች፡፡ እንዲህ በሆነች ጊዜ ያለችበትን ሳታውቅ ሌቱ ይነጋል፡፡ ወፍ ይንጫጫል፡፡
ዕንቅልፍ እንደ ሞት
ዘለቃሽና ዕንቅልፍ ከተገናኙ ቆይተዋል፡፡ ባተሌዋን ሴት የድካም ፈረስ ሽምጥ እየጋለበ ከተለመደው ቅዠትና ኩርፊያ አድርሷታል፡፡ ሌቱ ጭር ብሏል፡፡ አሁን የኩሽናው ግርግር አይሰማም፡፡ በዚህ ቦታ እንደቀኑ የሚነድ እሳት የሚዘጋጅ ወጥና እንጀራ የለም፡፡ ዝም ፣ ጭጭ እንዳለ ሌቱ ገስግሷል፡፡ ዘለቃሽ እንደወትሮዋ ትወራጫለች፣
ትቃዣለች፡፡
ከአንድ ጥግ ሆነው ሁኔታዋን የሚያስተውሉ ፈጣን ዓይኖች በድርጊቷ ተስበዋል፤ ይህች ሴት ፈጽሞ የምታይ፣ የምትሰማ ፣ አይደለችም፡፡ ድካም አቅሏን አስቶ ራሷን አስጥሏታል፡፡ አሁን ንቁዎቹ ዓይኖች ይበልጥ ፈጠዋል፡፡ የዚህች ሴት ሁኔታ ለሌላ እርምጃ የሚጋብዝ መሆኑ የገባው ጎልማሳው አስተዋይ ቀስ እያለ ወደውስጥ ዘልቋል፡፡
ሰውየው አርምጃውን አጥፍቶ፣ ትንፋሹን ውጦ አጠገቧ አስኪደርሰ ማንም እንዳለየው
አረጋግጧል፡፡ በዚህ ሰአት፣ በዚህ ስፍራ ሁሌም ከእሷና እሷ በቀር በኩሽናው ማንም አይገኝም፡፡ እሷም ብትሆን አሁን እንዳለች አይቆጠርም፡፡ ዕንቅለፍ አሸንፎ
ረቷታል፡፡ ድካም አንገዳግዶ ጥሏታል፡፡ ይህን ያስተዋለው የሌሊቱ አድፋጭ በፈጣን ርምጃ ከጎኗ ደርሶ ልብሷን መግፈፍ ፣ አፏን ማፈን ጀምሯል፡፡ ሰውዬው ያቀደውን ፈጽሞ እስኪጨርስ ዘለቃሽ በከባድ ዕንቅልፍና በጠንካራ እጆች ስር
ውላለች፡፡
ዘለቃሽ በውድቅት ለሊት ካለችበት ደርሶ የደፈራትን ሰው ለይታዋለች፡፡ በሆቴሉ ካሸር ሆኖ የሚሰራ የአሰሪዎቿ የቅርብ ዘመድ ነው፡፡ ይህን ብታውቅም እሱን መክሰስና መውቀስ አልቻለችም፡፡ ሀፍረትና ድንጋጤ ውስጧን ሰቅዞ ያዛት፣ ድርጊቱ ተስፋ አስቆርጦ አንገት አስደፋት፡፡
ባተሌዋ ሴት ከሆነባት ድርጊት በኋላ ቤቱን መልቀቅ ፣ እንጀራዋን መተው አልሆነላትም፡፡ ይህን ልሞክረው ብትል ጦሟን ታድራለች ፣ ማረፊያ መጠጊያ ታጣለች፡፡ ሰርቶ ከማደር ሌላ ምርጫ የሌላት ሴት በወጥ ቤት ስራዋ ገፋች፡፡ አሁንም ስለእሷ ኩሽና ማደር ደንታ የሰጠው የለም፡፡
ቀን በድካም የምትባዝነው ሴት ሌቱን እንደቀድሞው የሰላም ዕንቅልፍ አትተኛም፡፡ ‹‹ኮሽ›› ባለ ቁጥር እየባነነች፣ ኮቴ ስትሰማ እየደነገጠች ከማለዳው ትደርሳለች፡፡ ውሎዋ ከወትሮው አይለይም፡፡ ከእሳት ከድስቱ ተጥዳ ለሌሎች ሆድ ትሮጣለች ፤ ለብዘዎች ፍላጎት ትደክማለች፡፡ ምሽት ድካምና ስጋት አይርቋትም፡፡ ሚስጥሯን ቋጥራ፣ ህመሟን ውጣ ስለ ነገ ታልማለች ፣ ለዚህ ሃሳብ አትሰንፍም ፣ ተስፋ አትቆርጥም ፡፡
ከጊዚያት በኋላ
የዘለቃሽ ብርታት ዛሬም ከእሷ ጋር ነው፡፡ የዕለት ግዴታዋ አልተቋረጠም፡፡ ትዕዛዝ አክብራ ስራዋን ትከውናለች፡፡ ጉልበቷን ትገብራለች፡፡ ከሰሞኑ የሚሰማት ድካም ግን ከወትሮው የተለየ ሆኗል፡፡ የምትሰራው ምግብ ሽታ ይረብሻት ይዟል፡፡ የምትቀምሰው ከሆዷ አልረጋ እያለ አስጨንቋታል፡፡ የሆነችውን ባታውቅም ስለእሷ የጠረጠሩ ሁኔታውን ገምተዋል፡፡
ዘለቃሽ አሁን ማርገዟን አውቃለች፡፡ ይህ እውነት ገሀድ ከሆነ ጀምሮ የአሰሪዎቿ ዘመድ ቤቱን ትቶ ጠፍቷል፤ የልጅ አባት መሆን ያልፈለገው ገንዘብ ያዥ ስሙን ጠብቆ፣ ድርጊቱን ለመሸሸ መወሰኑ እሷን አስደንግጧል፡፡ ጉዳዩን የሰሙ ባለሆቴሎች የዘመዳቸውን ሃጢያት ማባባሰ አልፈለጉም፡፡ ሁኔታውን እንደተለመደ ድርጊት ቆጥረው ችላ ብለውታል፡፡
ስራና መኖሪያን ያልተነፈገችው ዘለቃሽ የዕለት ስራዋን ቀጥላለች፡፡ ማርገዟን ካወቀች ወዲህ ህክምና የሄደችው ለአንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ አሰሪዎቿ ጉልበትና ሙያዋን ማጣት አልፈለጉም፡፡ እሷም እንደቀድሞው ከእሳት ከምድጃው ውላ የታዘዘችውን ትሰራለች ፡፡
ቀኑ መግፋት ይዟል፡፡ የዘለቃሽ እርግዝናም
እንዲሁ፡፡ በድካም ስትናውዝ የምትውለው ሰራተኛ ግዴታዋን አጠናቃ ሲመሽ ከኩሽናዋ ታርፋለች፡፡ ማንም ስለእሷ መወደቅ መነሳት ደንታ የለውም፡፡ ማንም ስለእሷ ጤና አይጨነቅም፡፡ ውሎአድሮ ዘለቃሽ ድካሙን መቋቋም ተሳናት፡፡ ጎንበስ ቀና ማለቱ ደከማት፡፡ እናም ወሰነች ፡፡ ቤቱን ትታ፣ ስራውን ለቃ ልትወጣ ቆረጠች፡፡
ዘለቃሽ ጓዟን ሸክፋ ከሆቴሉ ስትርቅ እግሯ ያመራው ወደ እህቷ ቤት ሆነ፡፡ እህቷ ካገሯ ስትመጣ ተቀብላታለች ፡፡ ሰርታ እንድታድር ራሷን እንድትችል አግዛታለች፡፡ አሁን ግን ከራሷ አልፋ ሌላ ፍጥረት ይዛባት እየመጣች ነው፡፡ እህት እንዲህ መሆኑን ባትፈቅድም ፊት አልነሳቻትም ‹‹ይሁን›› ብላ ተቀበለቻት፡፡
ዘለቃሽ በእህቷ ቤት አንድ ቀን እንዳደረች ሆስፒታል ልትሄድ ተነሳች፡፡ ያለፉትን ወራት በሀኪም እጅ ሳትታይ ቆይታለች፡፡ በሆስፒታሉ ደርሳ ህክምናዋን እንደጀመረች ወደቤት እንዳትመለስ ተነገራት፡፡ አጋጣሚ ሆኖ ልጇ ሊወለድ ተቃርቧል፡፡ በድንገት የመጣችው ዘለቃሽ ድንገቴ ምጥ አፋፋማት፡፡ ከቆይታ በኋላ ዘለቃሽ ሴት ልጇን ታቀፈች፡፡ ዓይኗን በዓይኗ አየች፡፡
አራስዋን ተቀብላ በቤቷ አቅም እንደወጉ ያደረገችው የዘለቃሽ እህት ያላትን አቃምሳ ፣ የቻለችውን ሞክራ ጥቂት ቀናት አገዘቻት፡፡ ቆይቶ ግን ዘለቃሽ በእህቷ ቤት መኖሩ ከበዳት ፡፡ በዚህ መቀጠሉ ለእሷም ለልጇም የሚመች አልሆነም፡፡ ጊዜ ወስዳ ደጋግማ አሰበች፣ ከራሷ መክራ ለውሳኔ ደረሰች፡፡
ጉዞ ወደ ገጠር
ዘለቃሽ ከዓመታት በፊት በእንጀራ ፍለጋ ሰበብ የለቀቀችውን መንደር ዳግም ተመለሰችበት፡፡ እግሯ ወደትውልድ ቀዬዋ ሲያመራ ቀድሞ ታስበው የነበረው የመሻሻል ሕይወት በዓይነ ህሊናዋ ተመላለሰ ፡፡ አሁን የትናንቱ ህልም ቅዠት ሆኗል፡፡
እሷ ቀድሞ እንደምታውቃቸው ብርቱዎች አልሆነችም፡፡ እንደሌሎች ተለውጣ አምራ ደምቃ አልመጣችም፡፡ ፈጽሞ ከተሜ አትመስልም፣ ልብሷ አያምርም፣ ገንዘብና ጌጥ የላትም፡፡ ትናንት አሷን ብቻ ለሚያውቃት መንደር አንድ ሕይወት ጨምራ ፣ ልጅ በጀርባዋ አዝላ ታይታለች፡፡ አሻግረው ያዩዋት ሁሉ ርቆ እንደኖረ እንግዳ ሮጠው አልተቀበሏትም ፡፡ ከእሷ ያለው ተራ ጓዝና ጉስቁልና፣ ከአንዲት ጨቅላ ጋር ብቻ ነው፡፡
ዘለቃሽ ወደ እናቷ ቤት አልፋ ገባች፡፡ እናት ፊት አልነሷትም፡፡ ጓዟን ከነልጇ ተቀብለው ቤት ‹‹ለእንቦሳ›› ሲሉ በፈግታ ተቀበሏት፡፡ ኑሮና ችግር በእጅጉ ያጎሳቆላት ሴት መልሳ ከገጠር ሕይወት ተፋጠጠች፡፡ ልጇን በጀርባዋ አዝላ፣ ከእርሻ ከገበያው ዋለች፡፡ አሁንም ዘለቃሽ ኑሮ አልተመቻትም፡፡ ደስታ ራቃት፣ በየቀኑ ይከፋት፣ ሆድ ይብሳት ያዘ፡፡
ሶስት ዓመታትን የዘለቀው የገጠር ሕይወት በሚቆረቁር ኑሮ ታጅቦ እንደዋዛ ነጎደ፡፡ ምቾት ይሉትን እውነት ለአፍታ ያላየችው ዘለቃሸ ልቧ መልሶ ሩቅ መንገድ አሰበ፡፡ ከተማ ብትመለስ እንደሚበጅ ገምታ ጓዟን ሸካከፈች፡፡ ልጇን አዝላ አዲስ አበባ ስትገባ መገኛዋ ትታው የሄደችው የእህቷ ቤት ሆነ፡፡
ዘለቃሽ ከሶስት ዓመታት በኋላ ልጇን ይዛ የእህቷ እንግዳ ሆነች፡፡ አስራአምስት ቀናትን እንደቆየች ግን ሕይወት በእህት ቤት አልመች አላት፡፡ ከሞሰብ የማይቆርሱበት፣ ከድስት የማይጨልፉበት ቤት ሆኖ አሳቀቃት፡፡ እሷ ብትችልም ልጇ ለዚህ ይሉኝታ አልደረሰችም፡፡ ያየችውን አምጡ ትላለች፡፡ ሲከለክሏት ታለቅሳለች ፣ ትጮሃለች ፡፡
ይህ አጋጣሚ ዘለቃሽን አስመረራት፡፡ በድንገት ከእህቷ ቤት ወጥታ ልመና ጀመረች፡፡ ጥቂት ቆይታ ደግሞ በየቤቱ ልብስ ማጠብ ፣ መላላክ ያዘች፡፡ እንዲህ ማድረጓ ለእሷና ለልጇ ዳቦ መግዣ አላሳጣትም፡፡ የምታገኘው ገንዘብ ለወለል አዳር ተረፋት፡፡
ሲመሽ ከፍላ እያደረች ከመሳቀቅ ‹‹እፎይ›› አለች፡፡ ለእህቷ ተከራይታ እንደምትኖር ተናግራለች፡፡ ጥቂት ቆይታ ደግሞ አሻሮ መቁላት ጀመረች፡፡ ገቢዋ ከቀድሞው የተሻለ ሆነ፡፡ የሚከፈላትን ይዛ የሚከራይ ቤት
ፈላለገች፡፡ የአቅሟን አላጣችም፡፡ ከአንዲት ሴት ቤት መኖር ጀመረች፡፡
ኑሮ በቤት
አሁን ዘለቃሽ ከዓመታት እንክርት በኋላ የራሴ ከምትላት ጎጆ ማደር ጀምራለች፡፡ ማለዳ ወጥታ ሲመሽ የምትመለስባት ትንሽዬ ቤት እግር
አታዘረጋም፡፡ ብትጠባትም አልተከፋችም፡፡ በምስጋና ተኝታ ታድርባታለች፡፡ አሁን ላይ የሚያሳስባት ቢኖር የልጇ ባህርይ ነው፡፡ ያለ አንዳች ምክንያት ስታለቅስ ትውላለች፡፡ ውላ ስትገባም ለሊቱን ሙሉ ስታለቅስ ታድራለች፡፡
ይህ ጩኸትና ለቅሶ ለአከራይዋ
አልተመቸም፡፡ ድምጽ በሰማች ቁጥር ትበሳጫለች፡፡ ዘለቃሽን እየጠራች፣ አየተቆጣች ታስጠነቅቃለች፡፡ የህጻኗ ችግር
አልታወቀም፡፡ ጨኸቷ ፣ ለቅሶዋ ቀጥሏል፡፡ አንድቀን የዘለቃሽ አከራይ ትዕግስት ተሟጠጠ፡፡ በድንገት በሯን በርግዳ ገባች ፡፡ የዛሬው ሁኔታዋ ከወትሮው ይለያል፡፡ በእጇ ቢላዋ ይዛለች፡፡ ዓይኗ ፈጧል፣ ፊቷ
ተለውጧል፡፡ ሴትዬዋ ሺሻ ከምታጨስበት ፍራሽ ተነሰታ መምጣቷ ነው፡፡ ሁኔታዋን ያየችው ዘለቃሽ ቤቷን ለቃ ለመውጣት ፈጠነች፡፡
ዘለቃሽ ልጇን ለማሳደግ በሌሎች አማራጮች
ሮጠች፡፡ አሁን ለእኔ የምትለው ማረፊያ የላትም፡፡ በድንገት የለቀቀችው ዳግም ቤት ለልመና ዳርጓታል፤ አጋጣሚ ሆነና ችግሯን ያዩ ልበ ቅኖች ከኩሽናቸው እንድታድር
ፈቀዱላት፡፡ ትንሽዋን ልጅ ይዛ የጎን ማረፊያዋን ብታገኝ ስጦታውን በምስጋና ተቀበለች፡፡ ከማዕድቤቱ እያደረች የቀን ስራዋን ቀጠለች፡፡
አሁን ልጇ ነፍስ ማወቅ ጀምራለች፡፡ አራት ዓመት ሲሞላት ትምህርትቤት ገብታለች፡፡ ከትምህርት ውላ ስትመለስ ዘለቃሽ ተስፋዋ ለመለመ፡፡ ያለአባት የምታሳድጋት ልጅ ለቁምነገር መብቃቷ ስለነገ እንድታስብ ምክንያት ሆነ ፡፡ ቆይቶ ግን ልጇ የሚጥል በሽታ እንዳለባት አወቀች፡፡ ይህ እውነት እናትን በእጅጉ አሳዘናት አንድ ልጇን ያየባት ህመም በእሷ አቅም የሚድን አለመሆኑ አሳሰባት፡፡
አስር ዓመታትን የዘለቀችበት የኩሽና ሕይወት አደጋ ሊጋረጥበት ጊዜው ደረሰ፡፡ ትናንት በበጎነት ያስጠጓት ሰዎች ዛሬ ቦታውን እንደሚፈልጉት አሳወቋት፡፡ ዘለቃሽ ልጇን ይዛ ማደሪያዋን ከመልቀቅ ውጭ ምርጫ አጣች፡፡ ታዳጊ ልጇ በትምህርቷ የደረጃ ተማሪ ሆናለች፡፡ አልፎ አልፎ የሚጥላት ህመም ከእሷ ቢሆንም ስንፍናን አታውቅም፡፡
የእናትና ልጅ እንክርት
አሁንም ዘለቃሽና ልጇ መኖሪያ ፍለጋ መንከራተት ይዘዋል፡፡ ‹‹አለናችሁ›› የሚል ዘመድ በሌለበት ‹‹ግቡ›› የሚል ወዳጅ ማግኘት ይከብዳል፡፡ አጋጣሚው ግን ብዙ አልዘለቀም ፡፡ አንድ ልበ ቀና ኩሽናቸውን ለመኖሪያ ፈቀዱላቸው፡፡ ዛሬ የዘለቃሽ ልጅ የአስራ አራት ዓመትና የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ናት፡፡
ልጅቷ ከነገ ለመድረስ ብትሮጥም ለህመሟ መፍትሄ አልተገኘም፡፡ ዘለቃሽም ብትሆን አብሯት በኖረው የኪንታሮት ህመም እየተሰቃየች ነው፡፡ በዓይኗ ላይ የደረሰው ጉዳት ጭምር ለዛሬ ችግር ሆኗል፡፡ የኑሮ ውድነት በየስፍራው የሚያሮጣት ብርቱ ሴት በተደጋጋሚ ቤት ለማግኘት ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም፡፡
ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ‹‹መምጫዋ የማይታወቅ›› በሚል ሰበብ ቤት እንዳታገኝ ፣ በሴፍቲኔት እንዳትታቀፍ ደጅ ያስጠኗታል ፡፡ ለብዙዎች የሚደርሰው የእርዳታ ፍጆታም ለእሷ የሰማይ ያህል እንደራቀ ዘልቋል፡፡ አሁን ዘለቃሽ በአካባቢዋ በተጀመረው የምገባ መርሀግብር በቀን አንዴ መጠቀም ችላለች፡፡
ሁሌም የሚሰጣትን ምግብ ቋጥራ ለልጇ ስታካፍል ዓይኖቿ ለምስጋና ወደ ላይ ያንጋጥጣሉ፡፡ ዛሬም ባላለፈው ችግር የምትዳክረው ዘለቃሽ የጠዋቷ ጀንበር ተስፋዋ ነች ፡፡ በእጇቿ ልፋትና በአንድ ልጇ ብርታት ስለ ነገ ብሩህነት ታስባለች ፡፡ ህይወትም ያለለውጥ በተለመደው መልኩ ቀጥላለች፡፡
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ኅዳር 3/ 2015 ዓ.ም