• በአማራ ክልል በደረሰው ጉዳት የተሰማውን ሀዘን ገለጸ
• አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት እንደሚ ደግፍ አስታወቀ፤
አዲስ አበባ፡- የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዲፒ) በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደርና በክልሉ በሰሜን ሸዋ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች በተከሰተው ግጭት ጠንሳሾችን እና ተሳታፊዎችን ለህግ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት እንደሚደግፍ አስታወቀ።
የኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዲፒ) በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ትናንት “የህዝቦች ወንድማማችነትና
የአብሮነት መልካም እሴቶች በአፍራሽ ኃይሎች ተልዕኮ አይደናቀፍም” በሚል ርዕስ በሰጠው መግለጫ እንዳመለከተው፤ ሰሞኑን በአማራ ክልል የኦሮሞ ብሄረሰብ አስተዳደርና በክልሉ በሰሜን ሸዋ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች በፖለቲካ ቁማርተኞች ቀስቃሽነት ግጭቶች መከሰታቸውና በሰው ህይወት፣ በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። አጥፊዎችን ለህግ ለማቅረብ በጸጥታ አካላት የሚደረገውን ጥረት ይደግፋል።
በህዝብ ደም በሚነግዱ የፖለቲካ ቁማርተኞች የተፈፀመው ጥፋት በየትኛውም መልኩ ተቀባይነት የሌለውና ማንኛውንም ህዝብ የማይወክል መሆኑን ኦዲፒ ይገነዘባል ያለው ፓርቲው፤ ኦዲፒ የተፈጠረውን ችግር ለማረጋጋት እና ተመሳሳይ ችግር ዳግም እንዳይከሰት ለመከላከል ከአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) እና ከአማራ ክልላዊ መንግስት ጋር
በመቀናጀት በመስራት ላይ እንደሚገኝ ገልጿል።
ኦዲፒ በግጭቱ ለጠፋው የሰው ህይወት፤ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን፤ በግጭቱ ውድ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች ጥልቅ ሀዘን የተሰማው መሆኑን ገልጾ ለተጎጂ ቤተሰቦችም መፅናናትን ተመኝቷል። የጥፋት ድርጊቱንም አጥብቆ ያወግዛል ብሏል፤ ኦዲፒ በመግለጫው።
በሰላም አብሮ የሚኖሩትን ወንድማማች ህዝቦች ለማጋጨት የሚደረግን ማንኛውም ሙከራና ድርጊት ለማክሸፍ ኦዲፒ ዛሬም እንደትናንቱ ጠንክሮ እንደሚሰራ አመልክቶ፤ ህዝቦች ለዘመናት ባካበቱት የአብሮነት ዕሴት እና የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ሴራውን ያከሽፋል ብሏል።
በዚህ አጋጣሚም የኦሮሞ ህዝብ በተለመደው የአቃፊነት ባህሉ ወንድም ከሆነው የአማራ ህዝብ እና ከሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ያለውን አብሮነት በማጠናከር፤ በክልሉ በህዝቦች መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚደረጉ የጥፋት ኃይሎችን ሴራ ለማጋለጥ እና ለማክሸፍ እንዲንቀሳቀስ ጥሪውን አስተላልፏል።
ኦሮሚያ የሁሉም ኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ቤት እንደሆነች ኦዲፒ በጽኑ ያምናል ያለው መግለጫው፤ በክልላችን የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች አሁን የደረስንበት የለውጥ ምዕራፍ ላይ እንድንደርስ ከኦሮሞ ህዝብ ጋር አንድ ሆነው ከመሪው ፓርቲ ኦዲፒ ጎን ተሰልፈው ታግለዋል። ውድ መስዋዕትነትም ከፍለዋል ሲል ገልጿል።
ኦዲፒ የህዝቦች ወንድማማችነት፤ የኢትዮጵያን አንድነት እና የለውጡን እንቅስቃሴ ለመገዳደር የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ እና የከሰሩ የፖለቲካ ኃይሎችን ከመላው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን፤ እንዲሁም ከለውጥ ኃይሎች ጋር በመተባበር በጽናት የሚታገላቸው መሆኑንም አስታውቋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 2/2011
በ ጌትነት ምህረቴ