ወንድ አያቴ ጃጅቷል..ብቻውን እያወራ ብቻውን የሚስቅ ነው። ምን እንደሚል አይሰማኝም ግን ሁሌም ሲያወራ አየዋለሁ። ለመደመጥ የሚከብዱ፣ ለመሰማት ያልደረሱ ልጃገረድ ድምጾች ከአፉ በጆሮዬ ሽው ይላሉ..ሳልሰማቸው..ከአየሩ ጋር ይደባለቃሉ። ይሄ ብቻ አይደለም ጆሮውም ከድቶታል። ሹክሹክታ አይሰማም። አይደለም ሹክሹክታ እኔ ጆሮዬን የምይዝበትን ኃይለኛ ድምጽ እንኳን መስማት ይቸግረዋል። ጆሮው ላይ መጥተው ካላንባረቁበት በስተቀር ጆሮ ዳባ ነው። አለመስማት ብቻ አይደለም በመርሳትም የሚደርስበት የለም። ሦስት ሰዎችን ብቻ ነው የሚያስታውሰው። እኔን፣ አብራው ለሰባ አመት በትዳር የኖረችውን ሚስቱንና ከአልጋው በላይ የተሰቀለውን የሟች ወንድሙን ፎቶ። እኔን ያረሳኝ ሁሌ ነጋ ጠባ አጠገቡ ስለሚያገኘኝ ይመስለኛል። ሴት አያቴን ያረሳት ሰባ ዓመት ሙሉ ስለሚያውቃት ልርሳሽ ቢል ስለማይቻለው ይመስለኛል። አልጋው ላይ የተሰቀለውን የሟች ወንድሙን ፎቶ ያረሳው ከመጃጀቱ ሦስት ቀን ቀደም ብሎ የክርስቶስ ፎቶ እየመሰለው ሲሳለመው ነበር..ለዛ ይመስለኛል። እንደዛ ባይሆን ገና ድሮ ይረሳን ነበር። ሊጠይቁት በሳምንት ሦስት ጊዜ የሚመጡትን ያሳደጋቸውን ሁለት ወንድሞቼን እንኳን ረስቷቸዋል.. ከእጁ በልተው፣ ከእጁ ጠጥተው። በመጡ ቁጥር ፍጹምና አቤል ናቸው ብዬ ማስተዋወቅ የኔ ሥራ ነው።
ፊቱ ቆመው..እጃቸውን ለሰላምታ ዘርግተው ግራ ይገባዋል።
‹አቤልና ፍጹም ናቸው! እለዋለው ድምጼን አግንኜ። በዚህ ሁናቴ የልጅ ልጆቹን ለሁለት ዓመት እንደ አዲስ ተዋውቋቸዋል። ዘር አይውጣለትና እርጅና። አያቴ በመርሳት ተወዳዳሪ የለውም ያልኩት ለዚህ ነው። ዋሸሁ?
ሴት አያቴ ደግሞ ነገር አይገባትም። እንደ ወንድ አያቴ ሳትጃጅ፣ ጆሮዋ ሳይከዳት፣ በመርሳት ሳትጀግን ግን ነገር አይገባትም..ሙድ የላትም። በመደናገርና በማደናገር አንደኛ ናት። እሷን ከማስረዳት ከጆባይደን ቢሮ መረጃ መስረቅ ይቀላል። እንዲችው ልቤን እንዳወለቀችው መሽቶ ይነጋልኛል። ወላጆቼ በሕይወት ስለሌሉ በእኚህ ሁለት ነፍሶች ተከብቤ የምኖር ነኝ። ምን እንደምመስል አይጠፋችሁም። ሁሌ እንደሳኩ.. ሁሌ እንደተሳቀቅኩ ነው። ከወንድ አያቴ ሳመልጥ በሴት አያቴ ድንግርታ እደነቃቀፋለሁ..ግን ሳቆቼ ናቸው..በነፍሴ ላይ ብን የተደረጉ።
እጣ ክፍሌ አንድ አይነት ነው። ለማይሰማው አያቴ እየጮሁኩና ነገር በማይገባት ሴት አያቴ እየተደናበርኩ ወይም ደግሞ ጥርስ ለሌለው ድዳም አያቴ የተፈላውን አጥሚት እየኮመኮምኩ..በጠፍር የተሠራው ወንበር ላይ ቁጭ ብዬ። ወንድ አያቴ አልጋ ላይ ነው..ብቻውን እያወራ። ሴት አያቴ የትም ቦታ አለች..ዓለም ጠባት.. ምድር አንሳት። ለጎኑዋና ለዳናዋ በጠበበ ሰማይና ምድር ውስጥ ያለች ይመስለኛል..እንዴት ላለኝ የትም አያታለውና። እንደ እኔና እንደ ወንድ አያቴ አንድ ቦታ የላትም። ትፈትላለች፣ ትደውራለች፣ ትንጣለች፣ ታልባለች፣ ኩበት ታኮብታለች፣ ዳቦ ትደፋለች፣ ታማለች፣ ቡና ስለማትጠጣ ቡና ብቻ ስታፈላ አላያትም። ሁሉንም ናት..
‹ዓለም ልታልፍ ነው አሉ!› አልኩ አያቴ እንዲሰማኝ ድምጼን ከፍ አድርጌ። ሰሞኑን በዜና የሰማሁትን ሁላችንንም ያስገረመንን የአንዲትን እንስት ውሻ የማግባት ዜና አስታውሼ።
‹ማናት ዓለም? አለኝ አያቴ በሰለለና ብዙም በማይሰማ ድምጽ። ድምጼን ከፍ ስላደረኩ ሰምቶኛል። ደስ የሚለው ነገር አያቴ ከጮሁ ይሰማል።
እኔ ሳልመልስለት ሴት አያቴ ጣልቃ ገባች።
‹ያቺን የጎረቤታችንን ዘዋሪዋን ሴት ማለቱ ነዋ›። ስትል ከኔ ቀድማ ሴት አያቴ መልስ ሰጠች።
በደንብ ስላልጮኸች አያቴ መልስ አልሰጣትም። አያቴ ዝም አለ ማለት አልሰማም ማለት ነው። ሴት አያቴ ሁልጊዜ እየጮሁ ወንድ አያቴን ማስረዳት ሰልችቷታል መሰለኝ ብዙም አትጮህም። ለእኔ ተናግራ እኔ ጮኬ እንዳስረዳላት ነው የምትፈልገው። አሁን ግን ጮኬ ላስረዳላት አልፈለኩም ምክንያቱም እኔ ያልኩት ሌላ እሷ የምትለው ሌላ ነውና።
‹ታዲያ ትለፋ..ብታልፍስ ታዲያ? አለች አያቴ.. ወተቷን እየናጠች።
ወንድ አያቴ ባለመስማቱ ዝም ብሏል ሴት አያቴን ግን ማስረዳት ግዴታዬ ነው። ትክት ባለው ሁናቴ ‹ኧረ የምንኖርባትን ዓለም ማለቴ ነው! ስል ሁለቱም እንዲሰሙኝ ጮሁኩኝ። አጯጯሄ ከወትሮው በተለየ በኃይል ስለነበር ከሴት አያቴ ቀድሞ ወንድ አያቴ የሰማኝ ይመስለኛል። ደግሞም ሰምቶኛል ‹የምንኖረው እኔ ቤት አይደል? ሲል ጠየቀኝ።
‹ምነው አብደሀል እንዴ አንተ ልጅ? ቤቱንም ልትሸጠው አስበሀል? አለችኝ ሴት አያቴ አይታኝ በማታውቀው የጥርጣሬ አይን እያየችኝ።
‹የዓለም ፍጻሜ ማለቴ ነው! ስል ዝግ ብዬ ተናገርኩ። ከዓለም እንዳልወጣሁ ትዝ ሲለኝ ‹ስምንተኛው ሺህ ማለቴ ነው› ስል ለማስረዳት ሞከርኩ።
‹ታዲያ እንደዛ በላ ምን ያደናብርሀል! አለችኝ አያቴ የተደናበርኩት እኔ መስያት።
‹ተደናበርኩ እንዴ? ስል ጠየኳት።
‹እናስ! ተደናብረህ ሰው አታደናብር..› ቆጣ አለች።
ይሄ የዘወትር ታሪኬ ነው። ይሄን ነኝ እኔ..እንዲህ ነው ታሪኬ። ከአምና የተለየ ዛሬ፣ ከትላንት የራቀ አሁን የለኝም። ሁሌም አንድ አይነት ነኝ…እንዲህ እንደአሁኑ። እያደናበርኩና እየተደናበርኩ። አያቴ ውብ ዜማዬ ናት.. የጣፈጥኩት..የጣምኩት..የላምኩት በእሷ ነው። በአያቴ አለመስማት ውስጥ፣ በአያቴ መጃጃት ውስጥ፣ በአያቴ መደናበር ውስጥ ልክ ያልሆኑ ብዙ ልኮች አሉኝ። ማንም ያለበሰውን የዘመን ጌጥ..የጊዜ ፈርጥ ነፍሴ ገሳ ለብሳለች..።
አያቴ ፈተናዬ ናት..ሳልንገላታባት ሳትንገላታብኝ ቀርታ አታውቅም። አንድ ጊዜ ምን ሆነ መሰላችሁ.. በምታዘክረው የጊዮርጊስ ዝክር ላይ ብዙ ሰው በተሰበሰበበት ያሞገስኳት መስሎኝ ‹ጠላሽ መርዝ ነው! አልኳት። ከዛ ንግግር በኋላ ከአያቴ ጋር አይጥና ድመት ሆንን። ለካ የዶሮ አይን የመሰለ ጠላ ነበር የሚባለው። በዘመነኛ ቋንቋ ያሞገስኳት መስሎኝ አስነወርኳት። ምን ልል እንዳሰብኩ ካስረዳኋት በኋላ ነው እንደ ድሮው የሆነችልኝ።
የሆነው ሆኖ ግን ዜማዬ ናት..በልቤ ብቻ፣ በነፍሴ ብቻ የምዘምራት። በሚኖረኝ እልፍ ነገ ውስጥ ትዝታ ሆናኝ የምትቀመጥ። መርምሬ፣ በርብሬ የማልደርሳት.. አስቤ፣ ተስቤ የማልነካት..የሀሳቤና የምኞቴ የህልሜም ወደብ።
እያደናገርኳትና እየተደናገረችብኝ ከእሷ ጋር ዝንተዓለም ያንሰኛል..
እያደናገረችኝና እየተደናገርኩባት ከእሷ ጋር ዘላለማት አሁን ናቸው..
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ኅዳር 2/ 2015 ዓ.ም