ሰሞኑን ከአንድ የማህበራዊ ሚዲያ ገጽ ላይ አስተማሪ የሚባል እውነታን ተመለከትኩ። በአካል ጉዳቱ ምክንያት ከቤት ውሎ መንቀሳቀስ ስላዳገተው አንድ ጎልማሳ ታሪክ ። በመጠኑ ለመረዳት እንደቻልኩት ይህ ሰው ባገጠመው ጉዳት ሳቢያ ሰውነቱ ከመንቀሳቀስ ታቅቧል ። የአጋጣሚ ጉዳይ ሆኖም በዊልቸር የመጠቀም አቅም በማጣቱ ከቤት ከዋለ ቆይቷል።
ይህን ያስተዋሉ አንዳንድ ልበ ቅኖች ግን እንደ ብዙዎቻችን ከንፈራቸውን መጠው ብቻ አላለፉም ። ሕመሙ ቢያማቸው ችግሩን ችግራቸው አደረጉት።‹‹እኛ እያለን አንተ ከቤት አትውልም፣ ወድቀህ አትቀርም›› ሲሉም ቀርበው አዋዩት ። ይህን ሰው በጉዳቱ ሳቢያ ከወደቀበት አንስተው በዊልቸር ድጋፍ እንዲጠቀም ፣ ከሌሎች እገዛ ተላቆ በራሱ ድጋፍ እንዲንቀሳቀስ ዕድሉን ሰጡት ።
እነሆ ! የትናንትናው የሰው እጅ ናፋቂ ጉዳተኛ ዛሬ ራሱን ማገዝ ችሏል። እንዳሻው ዊልቸሩን አንቀሳቅሶም ካሰበው መንገድ ሊውል የልቡ መሻት ሞልቷል ።
ወይዘሪት ማሬ ደሴ በልጅነቷ ባጋጠማት ድንገተኛ አደጋ ከወገቧ በታች ያለው አካሏ አይንቀሳቀስም ። ማሬ ከአደጋው በኋላ በከፍተኛ ህክምና ህይወቷን ለማትረፍ ተችሏል። አንድ ዓይኗ ጨምሮ በስነልቦናዋ ላይ የደረሰው ጉዳት ግን አስከዛሬ አብሯት አለ።
ይህ ብቻ አይደለም። ከዓመታት በፊት ችግሯን ያዩ ልበ ቀናዎች በስጦታ የለገሷት ዊልቸር ዛሬ በዕድሜ ብዛት ከጥቅም ውጭ ለመሆን ተቃርቧል። የማሬ ዊልቸር መደገፊያው በገመድ ተተብትቧል ። ጠዋት ማታ ሽቅብ ቁልቀሉል የሚሉት ጎማዎችም በተለምዶ አባባል ‹‹ሊሾ ›› ሆነዋል።በእሷና በሌሎች ጉልበት የሚገፋው ዊልቸር ዛሬ አቅምና ጉልበትን የሚፈትን ሆኗል። ይህ እውነታ የአካል ጉዳተኛዋን ህይወት ከመፈተን አልፎ ተስፋ እያስቆረጠ ነው።
ተደጋግሞ እንደሚነገረው አካል ጉዳተኝነት መቼና እንዴት እንደሚከሰት አይታወቅም። ጠዋት ከቤቱ በሰላም የወጣ አንድ ሰው በሚደርስበት ድንገተኛ አደጋ ምክንያት የአካል ጉዳት ሊከሰትበት ይችላል ።
ችግሩ ይህ ብቻ አይደለም። ከጉዳቱ በኋላ ለእንቅስቃሴ የሚያሥፈልጉ የአካል ድጋፎችን ለማግኘት ሁኔታዎች ቀላል ላይሆኑለት ይችላሉ። መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በሀገራችን አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ የአካል ጉዳት መሳሪዎች እጥረት አለ ። ለጉዳዩ ካለው ትኩረት ማነስ አንስቶ የአቅርቦትና የአቅም ማጣት ችግሮችም ከጉዳቱ ጋር ለሚኖሩ ወገኖች ፈታኝ የሚባሉ ናቸው።
አካል ጉዳተኞች በተለያዩ ምክንያቶች መገለል ይደርስባቸዋል ። እንደሌሎች በስራ ላይ የመሳተፍ ዕድላቸውም ጠባብ የሚባል ነው። አካታች የሚባል አሰተሳሰብና ተሳትፎ በሌለበት ሁኔታ ለመንቀሳቀስ የሚረዱ የአካል ድጋፎች ያለመኖራቸው ጉዳታቸውን ይበልጥ የከፋ ያደርገዋል።
ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ምቹነት የጎደለው የማስተማር ሂደት ከመኖሩ ጋር ተያይዞ በርካቶች በትምህርት ተጠቃሚ አይሆኑም። የመማር ዕድሉን ያገኙ አካል ጉዳተኛ ተማሪዎችም ከሌሎች እኩል ደረጃን ወጥቶ መውረድ ፈተናቸው ይሆናል።
የሰውሰራሽ አካል ድጋፍ በአግባቡ በማይተገበርበት ማህበረሰብ ውስጥ የተገኙ አካል ጉዳተኞች በቤት ውስጥ ተደብቀው ከመኖር የዘለለ አማራጭ ላይኖራቸው ይችላል። ይህ እውነታም ማህበረሰቡ በአካል ጉዳት ላይ ያለውን የተሳሳተ አመለካከት ለማረም የሚያስችል አይሆንም። ከመፍትሄው ይልቅ ችግሩ ጎልቶ በሚታይባቸው አካባቢዎችም አካል ጉዳተኞች ከሌሎች በታች ሆነው ኑሮን እንዲገፉ ይገዳዳሉ።
በሀገራችን ከሚገኙ የሰውሰራሽ አካል ድጋፍ አምራች ተቋማት አብዛኞቹ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት እጥረት አለባቸው ። ይህን ክፍተት ለመሙላትም ተቋማቱ ከኅብረተሰቡና ከዓለም ዓቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች ጋር በትብብር ይሰራሉ።ከዚሁ ጋር ተያይዞ በሰው ሀይልና በባለሙያ ስልጠናዎች ከአቅም በታች የሚሰራበት አጋጣሚው የሰፋ ነው። የሰውሰራሽና የአካል ድጋፍ አቅርቦቶች በአብዛኛው ከውጭ አገራት የሚመጡ ናቸው።
በሀገር ውስጥ በቀላሉ ያለመገኘታቸውም የተጠቃሚዎችን ፍላጎት የሚገድብ ይሆናል። ከአንድ መቶ ሰባት ሚሊዮን በላይ የአካል ጉዳተኞች እንደሏት በሚገመተው አገራችን የጉዳቱ መጠን እስከ አስራሰባት በመቶውን የሚሸፍን ነው ።
በሀገራችን የሚገኙ የቤትና ህንጻ ግንባታዎች ሁሉም በሚባል መልኩ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ የሚባሉ አይደሉም። የሰው ሰራሽ አካልና የአካል ድጋፍ ያላቸው ወገኖች በነዚህ ስፍራዎች በወጉ የመገልገል አጋጣሚውን አያገኙም። በሆስፒታሎች፣ በመስሪያቤቶችና በተለያዩ ተቋማት አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ግንባታዎች ያለመኖራቸው እነዚህን ወገኖች ገለልተኞች እንዲሆኑ ያደርጋል ።
አሁን ላይ በአንዳንድ ቦታዎች ትኩረት እየተሰጠው ከመሆኑ ጋር ጥቂት የሚባሉት ብቻ አካልጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ግንባታዎችን ሲያካሂዱ ይስተዋላል ። ከዚህ ቀድሞ የነበሩት በርካቶች ግን ይህ አይነቱን ልምድ ባለመያዛቸው አካል ጉዳተኞች ከማህበራዊና ኤኮኖሚያዊ ተሳትፏቸው እንዲገለሉ አስገድዷል።
አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ የሚያደርጉ ድጋፎች በተገኙ ጊዜ በትምህርትና በስራ ለመሳተፍ የሚኖሩ አጋጣሚዎች መልካም ይሆናሉ ። ይህን መልካም ዕድል ለማስፋት ደግሞ ለአካል ጉዳተኞች የሚበጁ የአካል ድጋፍ መሳሪያዎች ሊኖሩ ይገባል።
በርካቶቻችን እንደምናውቀው ለሰውልጆች መሰረታዊ ፍላጎት የሚባሉት ምግብ፣ ልብሰና መጠለያ ናቸው። በአካል ጉዳተኞች ዓለም ግን አራተኛ መሰረታዊ ፍላጎት ሆኖ የሚታሰበው የአካል ድጋፍ መሳሪያ መሆኑ እየተለመደ ነው። አሁን ላይ የአካል ድጋፍ መሳሪያዎች የቅንጦት ዕቃ ያህል ዋጋቸው እየጨመረ ነው።
ይህ እውነታ ባለበት አጋጣሚ ዕድሉን ማግኘት ያልቻሉ ወገኖች በእጅ፣ በእግርና በደረታቸው እየተንፏቀቁ ድጋፍ አልባን ህይወት ሊኖሩ ተገደዋል። ክራንችን የመሰሉ የአካል ድጋፍን በማጣት በቀላሉ መስተካከል የሚችል የሰውነት አቋም ለችግር ሲዳረግ ማየቱ የተለመደ ነው።
የእጅና የእግር ድጋፍ አግኝቶ መንቀሳቀስና ምርታማ መሆን የሚችል ሰው ይህን ዕድል በማጣት ብቻ መማር ፣መስራትና በወጉ መንቀሳቀስ ተስኖት ከቤት ይውላል። የሀገራችን ኤኮኖሚ ማነስና የድህነት ጉዳይ አስገድዶን እንጂ የአካል ድጋፍን ማግኘት የፍላጎት ብቻ ሳይሆን የመብት ጥያቄ ጭምር ሊሆን በተገባ ነበር።
ይህን አሳሳቢና መሰረታዊ የሚባል ችግር ለመፍታት የአካል ድጋፎችና የሰውሰራሽ አካላት በአገር ውስጥ በስፋት ሊመረቱ ያስፈልጋል።የአካል ጉዳትን በተሻለ ቴክኖሎጂ ለማገዝ የሚያስችሉ ተቋማትና ባለሙያዎች በሚፈለገው ልክ ሊኖሩን ግድ ነው። የውጭ አገራትን የድጋፍ እጆች ከመሻት የዘለለም በራስ አቅም የሚደራጅና ትኩረት የሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ዛሬን በሰላም ውሎ ያደረ ማንነት ነገ ምን እንደሚገጥመው አይታወቅም። ተደጋግሞ እንደሚነገረውም ማንም ሰው ከአካል ጉዳት ያልራቀና ለችግሩ ፍጹም የቀረበ ነው። በሀገራችን በየጊዜው በሚደርሰው የትራፊክ አደጋ አብዛኞች ለአካል ጉዳተኝነት የሚዳረጉ ናቸው። ይህ አሀዝ ቁጥሩ እየጨመረ በሄደ ቁጥር የትኩረት ወሰኑን ጭምር የሚያመላክት ይሆናል።
ከችግሩ መስፋት ጋር መፍትሄው ያለመቅረቡ ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጠው የሚያስገደድ ይሆናል።በተለይ በቀላሉ በአካል ድጋፎች ሊስተካከሉ የሚችሉ የጉዳት አይነቶችን በህክምና ለመመለስ ለመሳሪያዎቹ አቅርቦትና ለሚያስገኙት ላቅ ያለ ጠቀሜታ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል። መልዕክታችን ነው።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ኅዳር 1/ 2015 ዓ.ም