ዕለቱ ልዩ ነው። ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ መንግስት እና በሕወሓት መካከል የሰላም ስምምነት መፈረሙ እነተሰማ መንግስቴ፣ ዘውዴ መታፈሪያ እና ገብረየስ ገብረማሪያምን በደስታ አስክሯቸዋል። የፈጠረባቸው የደስታ ስሜት በቃል የሚገለፅ አልነበረም። ዛሬ የተለየ ሃሳብ ይዞ የሚሟገት የለም። ሁሉም ከምንም በፊት ሰላም ቀዳሚ ነው ብለው ተስማምተዋል። የስምምነት ፊርማው መከናወኑ ደግሞ በመላ ሰውነታቸው የደስታ ስሜት እንዲሰራጭ ምክንያት ሆኗል።
እየተሳሳቁ ስለቀጣዮቹ የተስፋ ዓመታት እየተወያዩ በቴሌቪዢን የሁለት ሰዓት ዜና ሲጀምር፤ ተሰማ የግሮሰሪውን አስተናጋጅ ይርጋን ጠራው። የቴሌቪዥኑን ድምፅ ከፍ እንዲያደርግ አዘዘው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በአርባ ምንጭ ከተማ ተገኝተው በደቡብ አፍሪካው ንግግር ኢትዮጵያ ያቀረበችው ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ማግኘቱን እና የሰላም ስምምነቱ መፈረሙን በሚመለከት ለሕዝቡ የእንኳን ደስ አላችሁ መልክት በማስተላለፍ ላይ ነበሩ። ሁሉም የመጠጥ ቤቱ ተስተናጋጆች ሀሳባቸውን ሰብሰብ አድርገው ጆራቸውን ጥለው በተመስጦ ያዳምጣሉ።ወሬ የለም ኮሽታም አይሰማም ሁሉም ፊቱም አእምሮውም ያለው ቴሌቪዚኑ ላይ ነው።‹‹ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መንግስት የትግራይ ሕዝብን ወደ ቀደመው የአገሩ ስሜት ለመመለስ በሚሰራው ሥራ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ አብረን እንድንቆም በታላቅ ትህትና እጠይቃችኋለሁ።›› አሉ ። ይሄንኑ የሰላምና የመተሳሰብ ጥሪን ተከትሎ ገብረየስ አቀርቅሮ እንባው ወደ መሬት አንጠባጠበ።
ተሰማ መንግስቴ እና ዘውዴ መታፈሪያ መላ ሰውነታቸውን አንቅተው ዜናውን በመከታተል ላይ በመሆናቸው ልብ ብለው የገብረየስን እንባ አልተመለከቱም። ዘውዴ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ብልህ ናቸው ብሎ ለማወደስ ‹‹ ብልህና ቅባት ብርሃን እና መብራት።›› አለ። ተሰማ የሰማው አልመሰለውም። ተሰማ ግን ዘውዴን በደንብ ሰምቶት ስለነበር ፈገግ አለ። ቀጠል አድርጎ ‹‹ ድሮም ነገሮች ሲያበሳጩህ እየተማረርክ እንጂ መቼም ካለኔ ብቃት ያለው መሪ የለም ብለህ የምትናገረው ከልብህ አልነበረም። ይሔው መበለጥህን አምነህ ተቀብለሃል። በእርግጥም አካሄዳችን ትክክል ነበር። አካሄዳችን በብልሃት ብርሃን መሆንን በማሰብ ነው። ደግሞ ማመን ያለብህ የትኛውንም ነገር የሚመራው አንድ ሰው ነው። ሁሉም መሪ መሆን አይችልም። አንድ ሰው ይመራል ሌላው ደግሞ እንደየደረጃው ያግዛል፤ ይከተላል ።›› አለው።
ዘውዴ ፈገግ አለ። ‹‹ እንደበፊቱ አልተከራከረም በእውነት አምኛለሁ። ቀድሞም ቢሆን የምንፈልገው ሰላም ብቻ ነው። አንድም ቀን እኔ መሪ ልሁን ብዬ አላውቅም። ጠቤ ለምን ሰው ይሞታል? ብቻ ነበር፤ የሰው ሞት በዚህ መንገድ ካበቃ ፤ በዛሬው ዕለት ብቻ ሞት የተጋርጠበት ሕዝብ የሞት ጥላ ስለተገፈፈለት እንኳን ማመስገን እና ማወደስ መስገድም ቢያስፈልግ መስገድ እችላለሁ።›› አለ።
ገብረየስ እንባው ደረቀ፤ ለቅሶ ወደ ሳቅ ተቀየረ። ከትከት ብሎ ሳቀ። ወደ ዘውዴ እየተመለከተ፤ ‹‹ ስትወድ እና ስታሞገስ ወደር የለህም። ስትጠላ እና ስታንኳስስም ተወዳዳሪ አይገኝልህም። አንዳንዴ ሁሉ ነገርህ ግራ ይገባኛል። ስሜትህ ከፊትህ አልፎ ሆድህ ውስጥ ገብቶ እንዳንገፈገፈህ ጉሮሮህ ያሳብቃል። ስትደሰትም ተመሳሳይ ነው፤ በወፍራሙ ደስታህን ትገልፃለህ፤ ይሔ በእውነት ትልቅ ፀጋ ነው።›› አለና ቀድሞ የጀመረውን ሳቅ ቀጠለበት። ሁልጊዜ ግን ስሜታዊ ሳይሆን ስሌታው ለመሆን ሞክር፤ ነገሮችን ራቅ አደርጎ በብስለት ማየት ያስፈልጋል ብሎ በንግግሩ ጎሰም ከማድረግ አላለፈም።
ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹ ሁልጊዜ ዘውዴን የማየው ሲማረር ብቻ ነው። ስለሰላም ሲያወራ አዳምጬ አላውቅም። ‹ሊጣላ የመጣ ሰበብ አያጣም› እንደሚባለው በቅድሚያ ጠብ ለመጫር አስቦ ስለሚመጣ ሰበብ ፈልጎ እየተጣላ ይወጣል ብዬ አስብ ነበር። ዛሬ ግን ሁሉም ሰው ምን ያህል ሰላምን እንደሚፈልግ አይቻለሁ። መቼም እስከዛሬ ጦርነት የሆነው ሰዎች ሰላም ሳይፈልጉ ቀርተው አይደለም። ግን ደግሞ የግድ ሲሆን ሆነ፤ አሁን ዋናው ነገር ሰላም መስፈኑ ነው። ሰላምን መሻት ያተርፋል እንጂ አያከስርም፤ አክሳሪው ጦርነት ነው። ከጦርነት ማንም አያተርፍም፤ አሸናፊም ተሸናፊም የለም። ሰላም ሲሰፍን ሁላችንም አትራፊ እንሆናለን። እስኪ አስቡት በዛሬዋ የሰለም ስምምነት ብቻ በጥይት ይሞት ከነበረው ስንቱ ተርፏል። ለጥይት መግዣ ይውል የነበረው ዶላርም በኪስ አድሯል።›› ብሎ ንግግሩን አቆመ።
ዘውዴ ቀድሞም ቢሆን ስለሰላም ስምምነቱ መሳካት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ የደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ‹‹መላው ኢትዮጵያውያን እንኳን ደስ አላችሁ ከተቃጠልንም በኋላ ቢሆን ተምረናል። ልናስወግደውና ልናስቀረው ይገባ የነበረ ቀውስን ማስቆም ችለናል። በአስቸጋሪ መንገድም ቢሆን ተምረናል።›› ብለው በቲውተር ገፃቸው የሰላሙን ስኬት ሲያበስሩ የተሰማው ደስታ የተለየ ነበር። ስለስምምነቱ ቀድሞ መስማቱን እና ያም የተለየ የደስታ ስሜት ፈጥሮበት እንደነበረ ሲገልፅ ገብረየስ እና ዘውዴም አፀፋዊ ምላሽ ሰጥተዋል። ነገር ግን ዘውዴ ከእነርሱ በላይ እንደዛ በደስታ መፍነክነኩ እጅግ አስገርሟቸው ነበር። ዘውዴ ዜናውን እንደሰማ የተሰማው ደስታ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ቆየ። ገብረየስ እና ተሰማ ግን ደስታቸው ግለቱን እየጠበቀ ከፍ አለ።
ገብረየስ ‹‹ እኔን ደግሞ ያስገረመኝ የዘውዴ እንዲህ መደሰት ብቻ አይደለም። የሰላም ስምምነቱ ያስደሰተው እኔን እና እኔን መሰል በቁጥር ትንሽ ተብለው ሊገለፁ የሚችሉ ሰዎች ብቻ ይሆናሉ ብዬ ገምቼ ነበር። የሰላም ስምምነት አድራጊ የመንግስት ሃላፊዎች ራሳቸው ስለሰላም ስምምነቱ ሲገልፁ እየተጠቀሙት ያለው ቃላት አስደስቶኛል። በእርግጥም ሁላችንም ወንድማማቾች ነን። ሰላም በመሆኑ ያሸነፈው የሆነ ወገን ሳይሆን ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ራሷ መሆኗን ያሳያል። በዛ ላይ ሁላችንም ቁስላችንን ማከክ አቁመን ወደፊት መጓዝ ይኖርብናል፤ የሚለው የአምባሳደር ሬድዋን ገለፃ፤ በእውነት ልቤን ነክቶታል። ደስታዬ በሳቅ ብቻ ሳይሆን በእንባም የታጀበ እንዲሆን አስገድዶኛል።›› ብሎ አይኖቹ በእንባ ተሞሉ።
ተሰማ በበኩሉ፤ ‹‹አዎ! አምባሳደሩ ትክክል ናቸው። ከትናንትናው ችግራችን መቋሰላችን ይልቅ የነገው ሰላምና አንድነታችን ይበልጣል። የትናንቱን ቁስል እያስታወሱ ማከክ መልሶ ቁስሉን ከማመርቀዝ ውጪ ምንም ዓይነት ጥቅም የለውም። ስለዚህ ትኩረታችን የነገው ተስፋችን ላይ መሆን አለበት። የትናንቱ መማሪያ ታሪክ ነው። ከዛ ውጪ ምንም ልንቀይረው የምንችለው ነገር የለም። ትናንትን የሙጥኝ ብሎ መብሰክሰክ ለዛሬው የኢትዮጵያውያን የተሻለ ዕድገት እና ብልፅግና ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ያደርገዋል። ልክ የማይገኝ ነገርን እንደመፈለግ ነው። ይሔ ደግሞ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። ስለዚህ ስላለፈው ጦርነት ሳይሆን ስለተገኘው ሰላም፤ ስለቱሩፋቱ እያሰብን ስለመጪው ጊዜ ብሩህነት እየተደሰትን እንኑር።›› አለ።
በሌላ በኩል ‹‹ ትክክል ነው። ዛሬ ምንም ተቃውሞ የለኝም። ሆድና ግንባር አይሸሸግም እንደሚባለው የምሸሽገው ምንም ነገር የለም። በደስታ ሰክሬያለሁ። ምክንያቱም ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ውስጥ ስትገባ አለመደሰት፤ ወይም ሰላም መሆን የለበትም ብሎ መሟገት እጅን በእጅ እንደመቁረጥ ነው። የገዛ ወገኖቻችን እንደውም ራሳችንን በራሳችን ለማጥፋት እንደማሰብ ነው። ደስታዬን መሸሸግ አልችልም፤ ብትገረሙም ሆነ ብትታዘቡ የሚገደኝ ነገር የለም።›› አለ ዘውዴ።
ገብረየስም ‹‹ ስለሰላም ስምምነቱ ሲነገር መቼም ቢሆን ማር የማይጥማቸው እንደሚኖሩ አያጠያይቅም። አንዳንዶች በውጪ የሚኖሩ ዲያስፖራዎች ፤አንዳንዴም ኢትዮጵያዊ አይደለንም የሚሉ ከሃዲያን ሳይዋጉ ተዘረጉ እንደሚባለው የሰላም ስምምነቱ አይሳካም ብለው ይሁን ወይም የሰላም ስምምነቱ አስቆጭቷቸው ብቻ ምንም በማይገባ መልኩ የሰላም ስምምነቱን እንደማይቀበሉ የአሜሪካንን አደባባይ ዘግተው ካልተንከባለልን ብለዋል። ሰላም በመስፈኑ ፈርተዋል።እኛ ግን አንፈራም ድጋሚ ወደ ጦርነት እንገባለን ብለንም አንሰጋም። ለሰላም ቃል ገብተናል። ›› አለ።
ተሰማ ከገብረየስ ከተል አድርጎ ‹‹ አንዳንዶች ስለሰላም ሲወራ እንደሚልፈሰፈሱት ዓይነት አይደለንም። እውነተኛ ጀግኖች ነን። እውነተኛ ጀግና መንፈሰ ጠንካራ ነው። ተኩሶ ከመግደል ይልቅ አስቀድሞ ሰላምን ይመርጣል። ለሰላም ዋጋ ይከፍላል። ገና ሳይጀመር ተስፋ ለማስቆረጥ የሚሞክሩ ስለመኖራቸው አይካድም። ነገር ግን በሰላም ጉዳይ ላይ በአጭሩ ተስፋ አይቆረጥም። ምክንያቱም ሰላም ትልቅ ዋጋ የሚያወጣ ነው›› አለ።
ዘውዴ ደግሞ ‹‹ እውነትህን ነው። እውነተኛ ጀግና ጀግንነቱን የሚያሰየው ተኩሶ በመግደል ሳይሆን በብልሃት ሰላም እንዲሰፍን በማስቻል ነው። ሰላም በምንም መልኩ ቀልድ ሊሆን የሚችል ነገር አይደለም። ጦርነትን መምረጥ ቀላል ነው። ነገር ግን ጦርነትን መምረጥ አላዋቂነት ነው። ዶሮ ብታልም ጥሬዋን እንደሚባለው ቅርብ የሆነ አስተሳሰብ ብዙ የሚያስኬድ አይደለም። ማንኛውም ነገር በስፋትና በጥልቀት ማየት እንጂ በራስ ጉዳይ ላይ ብቻ ማተኮር፤ የቅርብ የቅርቡን እያዩ እልህ ውስጥ መግባት፤ የተሟላ ጠቀሜታ አይኖረውም። የሰው ህይወት ከማንም እና ከምንም በላይ ሊያሳስበን ይገባል። ጀርባዬን እከክልኝ አልደርስበት አልኩ ብሎ ሰበብ በማበጀት እዚህ ያለውን ምስኪኑ የድሃ ልጅ እየሞተ የሚፈልጉትን ጉዳይ በምስኪን ኢትዮጵያውያን በኩል በተዘዋዋሪ መንገድ እንዲፈፀም ጥረት ማድረግ አያዋጣም። ለውጪ ጠላት ጅራትን ከመቁላት እና ከመቅነዝነዝ ጉዳይ አስፈፃሚ ሆኖ በኢትዮጵያ ሰላም ከመመቅኘት ይልቅ ራስን ሰብሰብ አድርጎ ለሌላውም ማሰብ የግድ ነው።›› በማለት በተለይ በውጪ የሰላም ስምምነቱን በመቃወም ሰልፍ በመውጣት ኢትዮጵያውያን ወደ ጦርነት እንዲገቡ ሲገፉ የነበሩ ጭር ሲል አንወድም ዲያስፖራዎች ምን ያህል እንዳበሳጩት ገለፀ።
ተሰማ ደግሞ ‹‹ አንዳንድ ጊዜ ፀባየ ብልሹ፤ በስራው ደካማና መጥፎ ሁኔታዎችን የሚያሳይ ሰው በማይታወቅበት አካባቢ ሔዶ የተሻለ ለመምሰል ቢጥርም አይሆንም፤ ቆይቶ በገዛ ሥራው ማንነቱ መጋለጡ አይቀርም። በጣም የሚገርመው የሰላም ስምምነቱ ተቃዋሚዎች(የግጨት አትራፊዎች) መሬት ሲንከባለሉና ሲንደባለሉ ነበር። በዛ ጊዜ ለቤተሰባቸው ያዘኑ መስለው ታዩ። ሰላም ወዳድ እና ፍትሕ የተጠሙ መሰሉ። አሁን ደግሞ ‹ሰላም ሊሰፍን ነው፤› ሲባልም መልሰው እዛው።
ቀድመው ጦርነት ያስቆጣቸው ለህዝብና ለሀገር አሳቢ መስለው ነበር። በዛ ጊዜ ጅብ በማይታወቅበት ሀገር ሔዶ ቁርበት አንጥፉልኝ እንደሚለው ሆኑ። አሁን የሰላም ስምምነት ሲባል ደግሞ በግልፅ ማንነታቸውን አጋለጡ ። በእውነትም እነርሱ ከሰላም ምን ማትረፍ እንደሚቻል ፍፁም አይገባቸውም። ስለዚህ አንቀየማቸውም፤ እኛ ግን የሰላም ትሩፋትን እያጣጣምን አንገታችንን ደፍተን እንሰራለን። ነገ ቀና ስንል ብዙዎች ያፍራሉ። ›› ሲል ዘውዴ ከወትሮ በተለየ መልኩ ብድግ ብሎ እየሳቀ የዕለቱ ከፋይ መሆኑን ድምጹን ከፍ አድርጎ በኩራት ተናገረ። ቀኑ ሰላም የተሰበከበት የሰላም ቀን ነውና ማንም አልተቃወመውም ፤ ስለ ሰላም የተበረከተ ጸበል የጋበዛቸው ያህል እየተሰማቸው በምስጋና ግብዣውን ተቀብለው ተቃቅፈው እየተሳሳቁ ወጡ። በሰላም ያገናኘን ብለው ተመራርቀው ወደየአቅጣጫቸው አመሩ።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ኅዳር 1/ 2015 ዓ.ም