ሰሞኑን የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን ትራማዶል የሚባለው መድሀኒት ያለ ሀኪም ፈቃድ እንዳይሸጥ ውሳኔ ማስተላለፉን በመግለጫ ተናግሯል። ይሄ መድሀኒት እስከዛሬ እንደ አንዳንድ ቀላል መድሀኒቶች እንዲሁ ያለ ሀኪም ትእዛዝ ተጠቃሚው የፋርማሲ ባለሙያውን በማማከር ብቻ ይገዛ የነበረ ሲሆን ከአሁን በኋላ ግን የሀኪም ትእዛዝ ከሌለ እንዳይሸጥ ተብሏል። ምክንያቱ ደግሞ ብዙ ወጣቶች በዚህ መድሀኒት ሱስ እየተያዙ በመሆናቸው ነው። ትራማዶልን ከጤና ባለሙያ ትዕዛዝ ውጭ ያለ ማዘዣ መውሰድ ወይም ከታዘዘ ጥንካሬ እና መጠን በላይ ብዙ ጊዜ መውሰድ ወይም ከታዘዘ ጊዜ ገደብ ውጭ ለረጅም ጊዜ መውሰድ ለሱሰኝነት ያጋልጣል። ሰውነት ደግሞ አንዴ ይህን መድሀኒት ከለመደ አሁንም አሁንም አምጡ ይላል። እና ችግሩ ምንድን ነው ካላችሁ መድሀኒቱ የህመም ማስታገሻ በመሆኑ ለጊዜው ለተወሰነ ሰዓት ለተጠቃሚው ዘና የማድረግ ጥቅም ቢኖረውም በዘለቄታው ግን የምግብ ፍላጎት ማጣት፤ ከፍተኛ የራስ ምታት፤ የሰውነት ላብ፤ እረፍት ማጣት፤ እንቅልፍ ማጣት፤ ድካም ስሜት፤ ማስመለስ ሊያመጣ የሚችል መሆኑ ብሎም በተለይ መድኃኒቱን መውሰድ ለማቆም የሚያስቸግር መሆኑ ነው። ከጤና አንጻር ሊከሰት ከሚችለው ጉዳት ባለፈ የማህበራዊ ህይወት ቀውስና ለተለያዩ ወንጀሎች ተጋላጭ መሆን፤ ለድህነት እና ለስነ ልቡና ቀውስም ያጋልጣል።
ሰሞኑን ዶ/ር ናሆም ግሩም የሚባል አንድ የህክምና ባለሙያ በዚህ ዙሪያ የገጠመውን ነገር በማህበራዊ ሚዲያ እንደሚከተለው አካፍሎን ነበር። ዶክተሩ እንዲህ ይላል “ከቀናት በፊት አንድ እድሜዋ በአስራዎቹ መገባደጃ አከባቢ የሚገኝ ታካሚዬ ለመጣችበት ህመም መፍትሄ ይሆናል ብዬ ያሰብኩትን መድሃኒት ሰጥቼያት ተሰናብታኝ ልትወጣ ስትል “አንድ ነገር ላማክርህ ነው እባክህ እርዳኝ” እያለች ማልቀስ ጀመረች። ጉዳዩን በአንዴ ለማስረዳት ፍቃደኛ ባትሆንም ከስንት ግዜ ውትወታ በኋላ ችግሯን ነገረችኝ።
ትራማዶል የሚባል መድኋኒት በቀን ብዙ ፍሬ እንደምትወስድ እና አሁን እሱም አልበቃ ብሏት በመርፌ ሚወጋ መውሰድ መጀመሯን፣ ይሄን መድሃኒት እሷ ብቻ ሳትሆን ብዙ ጓደኞቿ እንደሚወስዱት እና ትምህርት ቤት ውስጥ ጭምር ታዋቂ መሆኑን ጭምር አጫወተችኝ። “መድኀኒት ቤቶች ብር ከተሰጣቸው ያለ ጤና ባለሙያ ትዕዛዝ ይሸጣሉ። አንዳንዶቹ ገና ሲያዩን ምን ፈልገን አንደመጣን ያውቃሉ” አለች።
ከዚ በፊት አንድ መኪና ማጠቢያ ቦታ ማውቀው ልጅ መኪና ውስጥ የስራ ቦታ መታወቂያዬን አይቶ ሀኪም መሆኔን ካወቀ በኋላ “እባክህ በጣም ስላመመኝ (Tramado) ሚባል መድኋኒት በርከት አርገህ እዘዝልኝ” ብሎኝ ያውቃል። በኋላ በደንብ ቀርቤው ስጠይቀው መውሰድ ከጀመረ 2 ዓመት እንደሞላው እና ያለሱ ስራውን መስራት አንደማይችል አጫወተኝ። ማረሚያ ቤት ያሉ ታካሚዎች ህክምና ቦታ ከመጡ ብዙዎቹ ለባለሙያው “ትራማዶል ካልሆነ ሌላ መድሃኒት አያሽለኝም” ሲሉ ብዙ ግዜ ገጥሞኝ ያውቃል። የሌሎቹን ታሪክ ቤት ይቁጠረው!”
እንግዲህ ዶክተር ናሆም እንደነገረን መድሀኒቱ ብዙ ወጣቶችን ከጥቅም ውጭ እያደረገ ነው። በዚህም የተነሳ አሁን መንግስት የወሰደው እርምጃ ትክክለኛ ሊባል የሚችል ነው። ነገር ግን ከዚህ ውሳኔ በኋላ ቀጥሎ የሚመጣ አዲስ ጥያቄ ይኖራል። እሱም፤ በዚህ ሱስ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ቀጥሎ እጣ ፈንታቸው ምን ይሆናል? ትራማዶል ስለተከለከለ በአንዴ መጠቀም ያቆማሉ? ካላቆሙስ ወደ ሌሎች አደንዛዥ እና አነቃቂ እጾች ተጠቃሚነት ሊሻገሩ አይችሉም? እንዲህ አይነት ነገርን ለመከላከል ምን መላ ተዘይዷል? እና መሰል ጥያቄዎች ይቀጥላሉ።
እንግዲህ ሁላችንም እንደምናውቀው ሱስ ውቃቢ አይደለም በአንዴ ነቅሎ አይጠፋም። ስለዚህም ትራማዶል ተጠቃሚዎች ትራማዶልን እንደ በፊቱ በቀላሉ ማግኘት ሲያቅታቸው ወደ ሌሎች ሱሶች ይዞራሉ። ይህም ማለት የትራማዶል ገበያ ተዘግቶ የእነ ካናቢስ እና ኮኬይን ገበያ ይጦፋል ማለት ነው። በሱስ ዓለም ሁሌም እንደሚታወቀው ሱሰኛ ከአንድ ሱስ ወደ ባሰው ሱስ ይሄዳል እንጂ ወደኋላ አይመለስም። ተጠቃሚው ትራማዶልን ሲከለከል ከትራማዶል የባሰ መድሀኒት ፍለጋ መውጣቱ አይቀርም። ስለዚህም ስንወስን ውሳኔያችን ልክ እንደ ትራማዶል ጊዜያዊ እፎይታን የሚሰጥ ብቻ ሳይሆን ዘላቂ መፍትሄን የሚያመጣ መሆን አለበት።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሊታወቅ የሚገባው ነገር ሱስ በህግ ሊቆም የማይችል እንደሆነ ነው። ሱስ የሚቆመው በሳይንሳዊ መንገድ ብቻ ነው። ሳይንሳዊው መንገድ ደግሞ ማገገሚያ ማእከላትን በማቋቋም፤ ባለሙያዎችን በማፍራት፤ ከመንፈሳዊ ተቋማት ጋር ተናብቦ በመስራት፤ የአደንዛዥ እጽ አከፋፋዮችን በመቆጣጠር እና ተጠያቂ በማድረግ፤ እና መሰል መንገዶች ነው መፍትሄ የሚመጣው። በሌላ መልኩ አገራችን በአሁኑ ወቅት ህገወጥ ንግድ፤ የገበያ ሳቦታጅ እና ሌሎችም ውንብድናዎች የተስፋፉባት በመሆኗ ሀሰተኛ የሀኪም ማዘዣ የሚያድሉ፤ ከሙያ ስነ ምግባር ውጭ ማዘዣ የሚጸፉ፤ ያለ ማዘዣ የሚሸጡ አልፎም በህገወጥ መልኩ መድሀኒቱን አምጥተው የሚያከፋፍሉ ሰዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ገምቶ መንቀሳቀስ አስፈላጊ ነው።
በመጨረሻም መንግስት እንዲህ አይነት ውሳኔዎችን ለመወሰን ጉዳዩ በሶሻል ሚዲያ እስኪነሳ ድረስ መጠበቅ የለበትም። ይህ ችግር ለረዥም ጊዜ የከረመ እና ሲወራበት የኖረ ነው። ነገር ግን የሚመለከተው መስሪያ ቤት እርምጃ የወሰደው ጉዳዩ ሰሞኑን እንደ አዲስ በማህበራዊ ሚዲያ ሲራገብ ነው ማለት ይቻላል። ይህ ትክክለኛ አሰራር አይመስልም። መስሪያ ቤቱ የዚህ መድሀኒት ፍላጎት በየጊዜው እያሻቀበ ሲመጣ ችግር እንዳለ መገንዘብ ነበረበት። አሁን ላይ ውሳኔውን የወሰነው በዚህ የፍላጎት መረጃ ላይ ተመርኩዞ ከሆነ እሰየው ነው። ካልሆነ እና በሶሻል ሚዲያ ጫና ውስጥ ሆኖ ከሆነ የወሰነው ግን ለከርሞው መታረም አለበት።
ቸር እንሰንብት!
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ሰኞ ጥቅምት 28 ቀን 2015 ዓ.ም