ተወልዳ ያደገችው እዚሁ አዲስ አበባ ቀጨኔ አካባቢ ነው። ወቅቱም ነሐሴ 10 ቀን 1939 ዓ.ም ነበር። የአንጋፋው ሀገር ፍቅር ቴአትር የመድረክ ፈርጦች መካከልም አንዷ ነበረች፤ ሙናዬ መንበሩ። እጅጉን ዕውቅናን የገበየችበት በተዋናይነቷ ቢሆንም ተወዳጅ ሙዚቀኛም ነበረች። በተለይ “ጉብልዬ”፣ “ብርቱካኔ” እና “ትዝታዬ” የተሰኙት ሙዚቃዎቿ ደግሞ ታዋቂ ነበሩ። ዘወትር ዓርብ ምሽት በኢትዮጵያ ሬዲዮ ይተላለፍ የነበረውን “የባህል ሙዚቃ ዝግጅት” ይከታተል የነበረ ሰው አይስታቸውም።
ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጥበቡ ዓለም የዘለቀችው በ1952 ዓ.ም ነበር። የሰፈሯ ነዋሪ የነበሩት ታዋቂው የጥበብ ሰውና ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አገር የተዳረበትን “ሙሽራዬ” የተባለውን ሙዚቃ የደረሱት አቶ በሻህ ተክለማርያም ነበሩ ከጓደኞቿ ጋር ለእንቁጣጣሽ ቤታቸው መጥታ ስትጨፍር አይተዋት ይሰሩበት ከነበረው ሀገር ፍቅር ቴአትር ወስደው ያስቀጠሯት። እሷም በወቅቱ ደሃ ቤተሰቦቿን የመርዳት ጉጉት ስለነበራት በእቴጌ መነን ትምህርት ቤት ትከታተለው የነበረውን ትምህርቷን ከ3ኛ ክፍል በማቋረጥ በወር 15 ብር ክፍያ እየተከፈላት ለመስራት ዓይኗን አላሸችም ነበር። በሁለገብ ባለሙያነቷ የምትታወቀው ሙናዬ መንበሩ ለመጀመሪያ ጊዜ ተዋናይነትን የጀመረችው “ምቀኛው ዕድሌ አደረገኝ ሎሌ” በተሰኘው የአርቲስት ቀለመወርቅ ደበበ ድርሰት ነበር። ከዚያ በኋላ በህዝብ ዘንድ እጅግ ታዋቂ ትሆን ዘንድ ያስቻላትን “የቀለጠው መንደር” ቴአትርን ጨምሮ ከመቶ በላይ ተውኔቶች ላይ ለመተወን በቅታለች። ሙናዬን ሳስባት ቀድሞ ከፊቴ ድቅን የሚልብኝ በዚህ ቴአትር ላይ ታደርገው የነበረው እንቅስቃሴ፣ ንግግሯና አጠቃላይ ችሎታዋም ነው።
በሙያዊ ስነ-ምግባሯና ለጥበብ ታዳሚያን በነበራት አክብሮት ሁሌም የምትታወሰው ይህች አርቲስት ለዚህ መገለጫ የሚሆን ብዙ ታሪክም አላት። ሙናዬ በንጉሱ ዘመን ከአራስ ቤት ወጥታ መድረክ እየሰራች ልጇ ሞተችና ተነገራት። በአጋጣሚ የምትተውንበት ገጸ ባህሪ የሚያስለቅስ ስለነበረ እያለቀሰች ጨረሰችው። ከትያትሩ በኋላ ለታዳሚው ተነግሮት አጅቧት ሄዶ በቀብሩ ላይ ተገኘ። ንጉሱም ሰምተው የደመወዝ ጭማሪ ተደረገላት። በ1984 ዓ.ም ደግሞ የመጨረሻ ታዳጊ ልጇ በፈረንሳይ ለጋሲዮን ማዞሪያ ቤቷ አካባቢ በጥይት ተገደለባት። ያን ቀንም ከተማው እየታመሰ እሷ ግን ስራዋን ብላ ሀገር ፍቅር ተገኝታ ነበር። ልምምድ አድርጋ ወደ ቤቷ ስትመለስ ነበር ወሬውን የሰማችው። የካቲት 12 ሆስፒታል ስትደርስ ልጇን አይታው አረፈ።
ሙናዬ ከስራ ባልደረባዋ አቶ በቀለ ወልደጻዲቅ ጋር በመሰረተችው ትዳር አምስት ልጆች አፍርታለች። እነዚህን አምስት ልጆች ወልዳ ባሳደገችባቸው ዓመታት በሙሉ ሀገር ፍቅር ስትሰራ የነበረ ሲሆን፤ ከ40 ዓመታት በላይ በሰራችበት ቴአትር ቤት በ15 ብር ተቀጥራ ከአራት አስርት ዓመታት በኋላም ግን ደሞዟ ከሰባት መቶ ብር ጥቂት ነበር ከፍ የሚለው። እንዲያም ቢሆን ግን ሙያዋን ስለምትወደው ገንዘብ አነሰኝ ብላ አማርራ አታውቅም። በእርግጥ በአንድ ወቅት በወዷጇ አሰለፈች አሽኔ ድጋፍ ካዛንቺስ አካባቢ ግሮሰሪ ከፍታ የነበረ ቢሆንም ሁለት ስራ መስራት አይቻልም ተብላ ቴአትሯን መርጣ ንግዱን ትታዋለች።
ሙናዬ በስራዋ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ኬንያ እና ሱዳን ተጉዛለች። የፈረንሳዩ ጉዞ የራሱ ታሪክ አለው። ሙናዬ በወቅቱ ነፍሰ ጡር ነበረች፤ ይህን የሚያውቁ ሰዎችም ወደ ቴአትር ቤቱ ስራ አስኪያጅ ሄደው ሙናዬ ነፍሰ ጡር ናት መሄድ አይገባትም ብለው ከሰሷት። ቢሮ ተጠርታም ነፍሰ ጡር ነሽ ወይ ተባለች እሷ ግን አይደለሁም ብላ ካደች። ተመርምረሽ አምጪ በመባሏም ጤና ጣቢያ ሄደች። ወቅቱ ደግሞ ጉብልዬ የተባለው ዘፈኗ በጣም ተወዳጅ የሆነበት ጊዜ ነበርና ነርሷ እንዳየቻት አወቀቻት። ምን ሆና እንደመጣችም ጠየቀቻት፤ እንዲህ አይነት ነገር አጋጥሞኝ ነው ስትላት ነርሷ ለሀኪሙ ጉዳዩን ነገረችው። ሙናዬም ነፍሰ ጡር አይደለችም ተባለ። አለቃዋ ይሄን ሲሰሙ በቃ ትሂድ በማለታቸው ፈረንሳይ ሄዳ ስራዋን በአግባቡ ተወጥታ ተመለሰች።
ደግሞ ሌላም ገጠመኝ አላት፤ ወቅቱ 1950 ዓ.ም ነው። “የእድሜ ልክ እስራት” ቴአትር ጅማዎችን አስደምሟል። የማቲያስ በቀለ ድርሰት ነው። ከሃገር ፍቅር ማኅበር ተዋናዮች ደግሞ ሙናዬ መንበሩ ድንቅ ተብላለች። እናም ተወዳጁ ቴአትር ይደገም ተብሎ ቀጠሮ ተይዞለታል። ሆኖም ይታያል በተባለበት ቀን ሙናዬ ታመመች። ለመስራት ብታስብም ህመሙ ካቅሟ በላይ ሆነ። ደግነቱ የሙናዬን ገጸ ባህሪ ያጠናች ባለሙያ አለችና እነሱ ትርዒቱን ሊያቀርቡ ሄዱ። ሙናዬስ ትሉ ይሆናል? እሷማ ከህመሟ ጋ እየታገለች ያላለቀ አንድ የጭቃ ቤት ውስጥ ጋደም ብላለች። ያኔ አቅሙ ስላልነበራቸው ሆቴል መያዝ አይችሉም። የውሎ አበል እንኳን የለም። ወይ መኪናቸው ውስጥ ያድራሉ አለበለዛም ጅምር ቤት ካገኙ ባለቤቱን አስፈቅደው ለጥ ይላሉ። ሙናዬም በእንደዚህ በተገኘ ታዛ ውስጥ ነበር ህመሟን እያማጠች ያለችው። ግና ከህመሟ በላይ በጭካኔ ነፍስን የሚያወጣ አውሬ ከበባት፤ የጅብ መንጋ። እዚህ ላይ ቀልድ የለም። ነፍሷን ለማትረፍ የድረሱልኝ ኡኡታ አሰማች። ተመስገን፤ ፈጥኖ ደራሽ ጎረቤት አይጥፋ። የተንጋጋውን ጅብ ተንጋግተው መጡና ከመበላት አተረፏት።
የሙናዬ የልብ ጓደኛ በላይነሽ አመዴ ናት፤ የሁለቱ ፍቅር ይለይ ነበር። ሙናዬ ጓደኛዋን ስታቆላምጣት በላይነሽ አመዴ ልቅም እንደስንዴ ይወድሻል ሆዴ ትላታለች። አብረው ሰርተዋል፤ አብረውም ኖረዋል። ሙናዬ በትወናዋ ላይ የሚሰጣት ገጸ ባህሪ ብዙውን ጊዜ የኃይለኛ ሴት ቢሆንም በመደበኛ ባህሪዋ ግን ሳቂታ እና ጨዋታ ወዳድ ናት። መዝናናትን እንደምትወድ የምትናገረው ሙናዬ ጭቅጭቅ እና ኩርፊያን እንደምትጠላም ተናግራለች። የአምስት ልጆቿን አባት ከማግባቷ በፊት የነበረውን ባለቤቷን የፈታችውም በአኩራፊነቱ እና ቀናተኝነቱ እንደሆነ ትናገራለች። አብረዋት የሰሩትም ሰዎች ሙናዬ ቂም የማታውቅ አገር ሰው ናት ይሏታል። ይህች የመድረክ ፈርጥ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየችው ነሐሴ 10 ቀን 1995 ዓ.ም ነበር።
አቤል ገብረኪዳን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 27/ 2015 ዓ.ም