ተወልደው ባደጉበት በምዕራብ ጉጂ ዞን ቀርጫ ወረዳ ጉራቹ ጀልዶ ቀበሌ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። በወቅቱ በትውልድ አካባቢያቸው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽ ባለመሆኑ ከትውልድ አካባቢያቸው 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተጉዘው ዲላ ከተማ ነው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከተታሉት። ለትምህርት ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸውና ንቁ ተማሪ እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ ታደሰ ኤዴማ የዕለቱ የስኬት እንግዳችን ናቸው።
ጎበዝ ተማሪ እንደነበሩ የሚናገሩት አቶ ታደሰ፤ በ12ኛ ክፍል ያመጡት ከፍተኛ ውጤት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መግባት የሚያስችላቸው ቢሆንም፣ እርሳቸው ግን በወቅቱ ዩኒቨርሲቲ መግባትን አልመረጡም። ለዚህም ዋና ምክንያታቸው የ12ኛ ክፍል ፈተና ተፈትነው ውጤት እስኪመጣ በሚል የጀመሩት የጥሬ ወርቅ ንግድ ነው። ከግለሰቦች ገንዘብ በመበደር ውጤት እስኪመጣ በሚል የጀመሩት ይህ የንግድ ሥራ በወቅቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ሆኖ ፍሬውን ማጣጣም ጀምረዋልና ፊታቸውን ወደ ትምህርት ማዞር አልሆነላቸውም።
ገና በለጋ ዕድሜያቸው ገንዘብ የቆጠሩትና የንግድን ጣዕም ማጣጣም የጀመሩት አቶ ታደሰ፤ በወቅቱ በጥሬ የወርቅ ንግዱ 20 ሺ ብር ያተርፋሉ። ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባ ጥሩ ውጤት በማምጣታቸው ደግሞ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት ጓጉተዋል። ይሁንና የወርቅ ንግዱን እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸው በኋላ የሚገኘውን ውጤት ለማወዳደር ጊዜ አልፈጁም። እናም ዩኒቨርሲቲ ገብተው የዲግሪ ምሩቅ ቢሆኑ በወር ደምወዝ 420 ብር እንደሚያገኙ አወቁ። ሁለቱንም ሚዛን ላይ በማስቀመጥ ሚዛኑ ወዳጋደለበት አዘነበሉ። እናም ተምረው በወር 420 ብር ከመጠበቅ ይልቅ የጀመሩትን የጥሬ ወርቅ ንግድ አጠናክረው ቢያስቀጥሉ ውጤታማ እንደሚሆኑ በማመን ሙሉ ጊዜያቸውን ለንግድ በመስጠት ትምህርትን ደህና ሰንብት አሉት።
እንደዋዛ የጀመሩት የጥሬ ወርቅ ንግድ ዛሬ ላይ ለደረሱበት ስኬት መሰረት የጣለላቸው መሆኑን የሚያስታውሱት አቶ ታደሰ፤ በአሁኑ ወቅት በስፔሻሊቲ ቡና ላኪነት፣ በሆቴልና በነዳጅ ማደያ ሥራ ተሳትፈው ለበርካቶች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
የአርሶ አደር ልጅ እንደመሆናቸው የቤተሰቦቻቸው ፍላጎት ከንግዱ ይልቅ በትምህርት እንዲገፉ ፍላጎታቸው ነበር። ወላጅ አባታቸውና አብዛኛው የቤተሰብ አባል ቡና አምራችና አቅራቢ እንደነበሩም ያስታውሳሉ።
ከትምህርት ባስበለጡት የወርቅ ንግድ አምስት ዓመታትን ካሳለፉ በኋላ ባገኙት ትርፍ መኪና በመግዛት የንግድ ሥራቸውን ለመቀየር ጉዞ አንድ ብለው ጀመሩ። አቶ ታደሰ፤ የንግድ ሥራቸውን ለመቀየር የወሰኑት በቀዳሚነት የወርቅ ንግዱ ህጋዊ ባለመሆኑና ህጋዊ የሆነ ሥራ መሥራት እንዳለባቸው በማመን ነው፤ ከወርቁ ሲወጡ የቡና ንግድን በቀዳሚነት መርጠው ወደ ሥራው ገቡ።
ወላጅ አባታቸውን ጨምሮ አጠቃላይ ቤተሰቦቻቸው በቡና ንግድ የሚተዳደሩ በመሆናቸው ምክንያትም ዘርፉን ለመቀላቀል ማገዶ አልፈጁም። በወቅቱም አቅጣጫቸውን ወደ ቡናው በማድረግ ከአካባቢው አርሶ አደር ቡና አበጥረውና ለቅመው ወደ ማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ ጀመሩ። ወርቅ ሸጠው ባገኙት ትርፍ የገዙት መኪና ደግሞ ንግዱን ለማቀላጠፍ በብዙ መልኩ አገዛቸው።
የቡና ንግዱ ውጤታማ እየሆነ ሲመጣ ታዲያ፤ ‹‹ቡናውን ለምን ወደ ውጭ አገር አንልክም›› በማለት በ2000 ዓ.ም በዘመነ ሚሊኒየም ባርኩሜ ቡና ላኪ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅታቸውን አቋቋሙ። የድርጅቱ መጠሪያ ባርኩሜ መሆኑም ወቅቱ የኢትዮጵያውያን ሚሊኒየም በመሆኑና ባርኩሜ ማለት ደግሞ በኦሮሚኛ ፍቺው ሚሊኒየም እንደሆነም አጫውተውናል።
ከዘመኑ ጋር የተወዳጀው ባርኩሜ ቡና ላኪም ከኢትዮጵያውያን ሚሊኒየም ማለትም ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ ለተለያዩ የዓለም አገራት ስፔሻሊቲ ቡናን በመላክ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ለአገሪቷ እያስገባ ይገኛል።
ቡናን ወደ ለውጭ ገበያ በመላክ ሂደት ውስጥም የተለያዩ ተግዳሮቶች እንደገጠሟቸውም አቶ ታደሰ ይገልጻሉ። በተለይም ለኤክስፖርት ገበያው አዲስና ጀማሪ መሆን ከልምድ አንጻር ከባድ እንደነበር ያስታውሳሉ። ይሁን እንጂ፤ ኤክስፖርት ማናጀር በመቅጠር በትንሽ በትንሹ በመላክ የኤክስፖርት ገበያውን መለማመድ ችለዋል።
በአሁኑ ወቅትም ሰፊ ቁጥር ያላቸውን የውጭ አገር ደንበኞች ማፍራት የቻሉት አቶ ታደሰ፤ በተለያዩ የዓለም አገራት በሚዘጋጁ ኤግዚብሽኖች በመሳተፍም የገበያ ትስስር መፍጠር ችለዋል። ባርኩሜ ቡና ላኪ ድርጅትም ኤክስፖርት የሚያደርገው ቡና ስፔሻሊቲ ቡና ሲሆን፤ በዋናነት የገበያ መዳረሻዎቹም አሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ቻይና፣ ታይዋን፣ ኮሪያ፣ ጃፓንና ሌሎችም ይገኙበታል።
የዛሬ 15 ዓመት ቡናን ወደ ውጭ ገበያ መላክ የጀመረው ባርኩሜ ቡና ላኪ በአሁኑ ወቅት በርካታ ደንበኞችን በማፍራት ተደራሽነቱን እያሰፋ እንደሚገኝ ያጫወቱን አቶ ታደሰ፤ ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ለውጭ ገበያ የሚያቀርበውን ቡና ከአርሶ አደሮች እየገዛ ፈልፍሎ፣ አበጥሮና ለቅሞ ለገበያ ያቀርብ እንደነበር ያስታውሳሉ።
አሁን ደግሞ በምስራቅ ጉጂ ዞን አናሶራ ወረዳና ሻኪሶ ወረዳ ላይ የራሳቸውን ቡና ልማት እያካሄዱ ይገኛሉ። አጠቃላይ የቡና እርሻ ቦታቸው ስፋትም 190 ሄክታር ሲሆን፣ ከዚህ የሚያገኙትን ቡና በጥራት በማምረት በጥንቃቄና በተገቢው መንገድ በማዘጋጀት ደረጃውን የጠበቀ ስፔሻሊቲ ቡና በተሻለ ዋጋ ለውጭ ገበያ እያቀረቡ ይገኛሉ።
ባርኩሜ ቡና ላኪ፤ ስፔሻሊቲ ቡና ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ የሚሠራ በመሆኑ ሥራው ከፍተኛ ካፒታል እንዲሁም ቡናውን ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚፈለግ እንደሆነ አቶ ታደሰ አስረድተዋል።
እሳቸው እንደሚሉት፤ ስፔሻሊቲ ቡናን በስፋት ለመላክ ትልቅ አቅም ይጠይቃል። ያም ቢሆን ታዲያ ድርጅቱ እጅግ ጥራት ያለውን ቡና በዓመት ከ40 እስከ 50 ኮንቲነር ወደ ውጭ ገበያ በመላክ ከፍተኛ መጠን ያለው የውጭ ምንዛሪ ያስገባል።
በ50 ኮንቲነር ስፔሻሊቲ ቡና የሚገኘው ገቢም ከ150 እስከ 200 ኮንቲነር ከሚገኘው ሌላ ቡና ጋር ሲወዳደር እኩል አልያም እንደሚበልጥ አቶ ታደሰ ይገልጻሉ። ወደ ውጭ በሚልኩት ቡና በዓመት እስከ ሶስት ሚሊዮን ዶላር የሚያገኙ ሲሆን፤ ዘንድሮም ከ80 እስከ 90 ኮንቲነር ስፔሻሊቲ ቡና ለመላክና አምስት ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት አቅደው እየሠሩ ናቸው።
አቶ ታደሰ፤ በ190 ሄክታር የቡና እርሻቸው ላይ ከሚያለሙት ቡና በተጨማሪ በጉጂ ዞን በተለያዩ ከአካባቢዎች ከሚገኙ አርሶ አደሮችም ቡና ይገዛሉ። በተለይም ቀይ ቀይ የሆነውን ቡና ብቻ በማሰባሰብ በአልጋ ላይ አድርቀው በጥራት ለማዘጋጀት በርካታ አርሶ አደሮችን ይዘው ይሠራሉ። ቡና አልምቶ ለሚያቀርብላቸው አርሶ አደርም በኪሎ ከሁለት ብር እስከ ሶስት ብር ተጨማሪ ክፍያ በመፈጸም እንዲሁም የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ አርሶ አደሩ የበለጠ አምራች እንዲሆን ያደርጋሉ። በአሁኑ ወቅትም ኦርጋኒክ ሰርቲፋይድ በመሆን የበለጠ ተጠቃሚ መሆን የቻሉ በርካታ አርሶ አደሮች ስለመኖራቸውም አቶ ታደሰ አጫውተውናል።
ድርጅቱ በጉጂ አካባቢ ብቻ አምስት የሚደርሱ የቡና መፈልፈያዎች እንዳሉት ተናግረው፣ በእያንዳንዱ መፈልፈያ ጣቢያ ከ400 እስከ 500 የሚደርሱ አርሶ አደሮች ስለመኖራቸውም ይገልጻሉ። በአንድ የቡና መፈልፈያ ጣቢያም ከ40 እስከ 50 መኪና ቡና ይፈለፈላል ይላሉ።
በስፋት ከተሰማሩበት የቡና ወጭ ንግድ በተጨማሪ ነዳጅ በማደል ሥራ የተሳተፉት አቶ ታደሰ፤ በክልል ከተሞች ማለትም በነገሌ ቦረና፣ ክብረ መንግሥት፣ አርሲ ነገሌና በሌሎችም ቦታዎች ኖክ የነዳጅ ማደያዎችን አቋቁመው ለየአካባቢዎቹ ማህበረሰብ ነዳጅ እያቀረቡ መሆናቸውን ያብራራሉ።
ትምህርታቸውን ገታ አድርገው ወደ ወርቅ ንግድ የገቡት አቶ ታደሰ፤ የንግድ ሥራቸው መሰረቱን እያጸና ውጤታማ በመሆኑ ወደ ቡና ንግድ ተብተዋል፤ ቀጥለውም ነዳጅ ማደያዎችን በተለያዩ የክልል ከተሞች ከፍተዋል። እንዲህ እንዲህ እያሉ የንግድ ሥራ ዘርፎችን ለማስፋፋት በሚያደርጉት ጥረት እግዚአብሔርም ተጨምሮበት በቅርቡም በመሀል አዲስ አበባ ቦሌ ደረጃውን የጠበቀ ባለ አራት ኮከብ ሆቴል ገንብተው አገልግሎት በመስጠት ለከተማዋ ድምቀት ጨምረዋል።
የሆቴሉን ስያሜም በትንሽ ልጃቸው ስም መሰየማቸውን የጠቀሱት አቶ ታደሰ፤ የሆቴል ኢንቨስትመንትን ሲቀላቀሉም ይህ የመጀመሪያቸው እንዳልሆነ አጫውተውናል። ተወልደው ባደጉበት አካባቢ በምዕራብ ጉጂ ዞን በቀድሞ አጠራሩ አገረማርያም በአሁኑ ወቅት ደግሞ ቡሌ ሆራ በሚባለው ከተማ አገረማርያም ሆቴልን ገንብተዋል። ከሆቴሉ አገልግሎት በተጨማሪ በከተማው የመጀመሪያ የሆነውን ፎቅ በመገንባት ቀዳሚ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ከተማዋ ፎቅ በፎቅ እንደሆነችና የተለያዩ ተቋማትም መገንባታቸውን ይናገራሉ፤ ለዚህም እርሳቸው የገነቡት አገረማርያም ሆቴል መሰረት የጣለና በከተማዋ ፎቅ መስራት እንደሚቻል ማሳያ እንደሆነ ይገልጻሉ።
በሆቴል ሥራቸው የመጀመሪያ ከሆነው አገረማርያም ሆቴል ያገኙትን ልምድና ዕውቀት በማዋሃድ ሁለተኛውንና ትልቁን ኬና ሆቴል መገንባት የቻሉት አቶ ታደሰ፤ ሆቴል ብዙ ብር ባይገኝበትም ጥሩ ስም እንደሚገኝበት ነው የሚናገሩት።
በመሀል አዲስ አበባ ቦሌ ላይ ሆቴል የመገንባታቸው ምክንያትም ሆቴል ከኤርፖርት ሲርቅ ዋጋው ይቀንሳል፤ ለኤርፖርት ሲቀርብ ደግሞ የሆቴል ዋጋ ይጨምራል ነው። ይህም በቡና ንግድ ምክንያት በተዘዋወሩባቸው የዓለም አገራት ያገኙት ልምድ ነው። ይህን ልምድ መሰረት በማድረግም ዛሬ ላይ ለኤርፖርት ቅርብ ከሆነው መሀል ቦሌ ላይ ባለ አራት ኮከብ የሆነውን ኬና ኢንተርናሽናል ሆቴል ገንብተው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
በሆቴሉ ብቻ ከ100 ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን፤ በቡና ምርትና ዝግጅት ሂደት ውስጥም በቋሚነት 60 ለሚደርሱ ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ከዚህ በተጨማሪም በቀን ከ200 እስከ 300 ለሚደርሱ የኮንትራት ሠራተኞች የሥራ ዕድል በየዕለቱ የሚፈጠር መሆኑን ይገልጻሉ። በቡና ለቀማ ጊዜ ደግሞ ቁጥሩ በእጥፍ የሚጨምር እንደሆነ ያስረዱን አቶ ታደሰ፤ የሥራ ዕድል ለፈጠሩላቸው ሠራተኞችም ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ በወር ደመወዝ እንደሚከፍሉ ይናገራሉ።
ማህበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም ያላሰለሰ ጥረት የሚያደርጉት አቶ ታደሰ፤ በተለይም ቡና በሚያመርቱባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ተማሪዎች በሙሉ በየዓመቱ የትምህርት መርጃ ቁሳቁስ ያቀርባሉ። ትምህርት ቤት፣ መንገድና ድልድይ በመሥራትም ከፍተኛ አበርክቶ አድርገዋል። ከእነዚህም መካከል በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ አካባቢዎች ኡራጋ ጠቤ ቡርቃ ቀበሌና ጉራቹ ጀልዶ ላይ ያሰሯቸው ትምህርት ቤቶች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው። በተጨማሪም በአካባቢው የሚገኙ ወረዳዎች በሚሠሯቸው ማንኛውም የልማት ሥራዎች የበኩላቸውን ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ይገልጻሉ።
‹‹በአሁኑ ወቅት ያለው የቡና ንግድ ስርዓት ዘርፉን ውጤታማ ማድረግ ያስቻለና ሥራውና የሥራው ባለቤት የተገናኙበት ነው›› የሚሉት አቶ ታደሰ፤ ለዚህም መንግሥት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል በማለት መንግሥት ዘርፉን ውጤታማ ለማድረግ የወሰደውን እርምጃ አድንቀዋል።
ቡና ላይ ገና ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅም ጠቅሰው፣ መንግሥት በወሰደው አንድ እርምጃ ተዓምራዊ ለውጥ መምጣቱ አስደሳች መሆኑን ይናገራሉ። በቀጣይም በዘርፉ እየታየ ያለው ውጤት ቀጣይነት እንዲኖረው አርሶ አደሩ ላይ መሥራት አስፈላጊና የግድ መሆኑን ነው ያስገነዘቡት።
በመጨረሻም በሆቴሉ ዘርፍ በስፋት ለመምጣት ማሰባቸውን ያጫወቱን አቶ ታደሰ፤ መንግሥት በሊዝ በሚሰጣቸው ቦታ ላይ ባለ አምስት ኮከብ 30 ፎቅ ከፍታ ያለው ዘመናዊ ሆቴል ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ጠቁመዋል። በቡናው ዘርፍም እንዲሁ ቡናን አበጥሮ በጥሬው ብቻ ከመላክ ይልቅ እሴት በመጨመር ቆልቶና ፈጭቶ ወደ ውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰናዱ ይገኛሉ። ይህም ለዜጎች ተጨማሪ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ የሚኖረው ድርሻ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይሆንም።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/ 2015 ዓ.ም