የማዕድናት አለኝታ ቦታ የሚለየውና ዳታ የሚያመነጨው ኢንስቲትዩት

በኢትዮጵያ የሚገኙ የማዕድን ሀብቶችን ለይቶ ለማወቅ የሚያስችሉ ጥናቶች ይደረጋሉ፡፡ ጥናቶቹም የትኞቹ ማዕድናት የት ቦታ፣ በምን ያህል መጠን እንደሚገኙ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡

የማዕድኑ ምንነትና የሚገኝበት ቦታ ከታወቀ እና ከተለየ በኋላ ለኢንቨስትመንት ክፍት እንዲሆን በዘርፉ መሰማራት ለሚፈልጉ ኢንቨስትሮች /ባለሀብቶች/ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር ሀገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንድታገኝ ትልቅ ግብዓት በመሆንም ያገለግላሉ፡፡

የማዕድናቱን ምንነትና መገኛ ቦታ ለይቶ ማወቅ ብቻ በቂ ስለማይሆን በጥናቶቹ የተገኙ መረጃዎችን ዘመኑ በሚመጥን መልኩ አደራጅቶ ማስቀመጥም ያስፈልጋል፡፡ በጥናት የተለዩ ማዕድናትን መረጃ በመሰብሰብ አደራጅቶ፣ አጠናክሮና ተንትኖ በዘርፉ ኢንቨስትመንት መሰማራት ለሚፈልጉ አካላት ተገቢ መረጃ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ መረጃ ከማመንጨት በዘለለ መረጃው ዘመኑ በሚፈልገው መንገድ እንዲደራጅና ለመረጃ ፈላጊ አካላት በቀላሉ እንዲደርስ ማድረግ ይገባል፡፡

ማዕድን ለማልማት ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ እና ረጅም ጊዜን የሚጠይቅ እንደመሆኑ በዘርፉ መሰማራት የሚፈልጉ ባለሀብቶች ወደ ሥራው ከመግባታቸው በፊት ማግኘት የሚገባቸውን ትክክለኛ መረጃ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል።

ይህ ካልሆነ ግን በማዕድን ፍለጋ መስማራት የሚፈልጉ አካላት ለከፍተኛ የሀብት ብክነትና ድካም ሊዳረጉ ይችላሉ፤ ችግሩ በዚህ ብቻ አያበቃም፤ ባለሀብቶች በዘርፉ መሰማራትን እንዳይደፍሩ ያደርጋል፡፡

በሀገሪቱ የማዕድን ሀብቶች ላይ በተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች የተደረሰባቸውን ግኝቶች በተመለከተ የተደራጀና የተጠናከረ መረጃ መኖሩ ባለሀብቱ ብዙ ሳይደክም የሚፈልገውን መረጃ በቀላሉ አግኝቶ ወደ ቀጣዩ የልማቱ ተግባር እንዲገባ ያስችላቸዋል፡፡

በማዕድን ዘርፍ ዳታ በማመንጨት ረገድ የረጅም ጊዜ ልምድ ካላቸው ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት አንዱ ነው። ኢንስቲትዩቱ በአዋጅ ከተሰጠው ሥልጣንና ተግባር ዋናው ዳታ ማመንጨት ነው፡፡ በዚህም ከ50 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበተ ነው፡፡ የማዕድናት የአለኝታ ቦታ ልየታ ጥናት እያደረገ የሚያመነጨውን መረጃ /ዳታ/ በዳታ ማዕከልና በቤተመጻሕፍት /ላይብረሪ/ በማከማቸት መረጃውን ለሚፈልጉ አካላት በማሰራጨት ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡

የዳታ ማዕከሉና ቤተመጻሕፍቱን /ላይብረሪውን/ በዘመናዊ መልኩ በማደራጀት ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን የተሠሩና እየተሠሩ ያሉ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ አደራጅቶና ተንትኖ ለተጠቃሚ በሚፈለገው ልክና መልክ ያቀርባል፡፡ መረጃውን በሶፍትና በሀርድ ኮፒ በማድረግ በቀላሉ ተደራሽ እያደረገም ይገኛል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በማዕድን ዘርፉ ላይ ባከናወናቸው በርካታ ተግባሮች አማካኝነት በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ መረጃዎችን ማፍራት ችሏል፤ መረጃዎቹንም ለሚፈልጉ አካላት ተደራሽ አድርጓል፡፡ እነዚህ መረጃዎችም በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሀብቶች፣ በዘርፉ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ አካላት፣ ከዩኒቨርሲቲዎቹ ወደ ተቋሙ ለሚሄዱ የጂኦሎጂ ተማሪዎች፣ የኢትዮጵያን ጂኦሎጂ ለሚያጠኑ የውጭ ሀገር ተመራማሪዎች እና ሌሎች መረጃ ፈላጊዎች ይሰጣል፡፡ ኢንስትቲዩቱ መረጃውን ለመረጃ ተጠቃሚዎች የሚያደርሰበት የራሱ አሠራር ያለው ሲሆን፤ መረጃዎች በነፃ የሚሰጥበትና የሚሸጥበት አሠራር እንዳለው ይታወቃል፡፡

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ኢጃራ ተስፋዬ ኢንስቲትዩቱ ዋነኛ ሥራ ዳታ ማመንጨት መሆኑን ይናገራሉ። ኢንስቲትዩቱ የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው እንደመሆኑ እስካሁን ብዙ ዳታዎችን ማመንጨት እንደቻለ ይገልጻሉ፡፡ ዘንድሮ ብቻ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዳታዎች ለፈላጊ ባለድርሻ አካላት በመሸጥ ተደራሽነቱን እያሰፋ መምጣቱን አመላክተዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ ኢንስቲትዩቱ የማዕድናት አለኝታ ቦታ በመለየትና ዳታ በማመንጨት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው፡፡ የሥነ ምድር መረጃ ሲባል የማዕድን ፍለጋ፣ የጂኦተርማል፣ የሥነ ምድር አደጋ እና የመሳሰሉት ሥራዎች ላይ የተለያዩ ማጥኛ ዘዴዎች ተጠቅሞ ያጠናል። በጥናቱ የተገኘውን መረጃ ለሚመለከታቸው አካላት ተደራሽ ያደርጋል፡፡ በዚህ መሠረት የማዕድን አለኝታ ልየታ ጥናት በሚያካሄድበት ወቅት ጥናቱ በሚካሄድባቸው ክልሎች ካሉ ባለሙያዎች ጋር ይሰራል፡፡

የክልል ባለሙያዎች እንዲሳተፉ የሚደረግበት ዋንኛ ምክንያት በመጀመሪያው በማዕድኑ አለኝታ ቦታ ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች የሥራ ላይ ልምድ እንዲወሰዱ ነው፡፡ ሁለተኛው ሥራው ጥያቄ ሊፈጥር የሚችል መሆን ስለሌለበት አብረው ሠርተው እንዲያዩና እንዲያውቁት ለማድረግ ሲሆን፤ ሦስተኛው የማዕድን ልየታ ሥራ ሪፖርት ከተጠናቀቀ በኋላ በአካባቢው ላይ የተደረገው የአለኝታ ቦታ የልየታ ግኝት ውጤት እንዲደርሳቸው የሚደረግበት አሠራርን ተከትሎ እየሰራ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡

‹‹ኢንስቲትዩት በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት እስካሁን ባመነጨው የሥነ ምድር ዳታ መጠን ልክ ያመነጨ ሌላ ተቋም የለም። ጥናቶችን በጥልቀት በመሥራትም ይታወቃል። የእያንዳንዱ ማዕድን ክምችት መረጃው በአግባቡ ተሰብሰቦ፣ ተደራጅቶና ተተንትኖ በላይብረሪ እንዲቀመጥ ተደርጓል። በወርቅ፣ በክሮማይት፣ በኒኬል፣ ሊትየም፣ ጂኦተርማል እና በሌሎችም ረገድ የተደረጉ ጥናቶችና የተገኙ ላቦራቶሪ ግኝቶችን የተመለከቱ ብዙ መረጃዎች ተሰርተዋል›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የዳታ ማዕከሉ መረጃዎች እንደሚያ መላክቱት፤ ኢንስቲትዩቱ ዳታ የሚያመነጭ እንደመሆኑ ዳታ ማዕከል እና ልዩ ቤተመጻሕፍት አለው፡፡ ልዩ ቤተመጻሕፍት የተባለው ዋና ምክንያት ከየሀገሪቷ ብቸኛ የሥነ ምድር የተለዩ መረጃዎችን የያዘ ነው፡፡ በሀገሪቷ ከሚገኙ የክልሉ የማዕድን ቢሮዎች፣ በኢንስቲትዩቱም ሆነ በሌሎች አካላት የሚሰበሰበውን መረጃ በማሰባሰብ፣ አደራጅቶ ያሰራጫል፡፡ የዳታ ማዕከሉ መረጃዎችን በሁለት መልኩ በሶፍትና በሀርድ ኮፒ አደራጅቶ ይይዛል፡፡ በሶፍት ኮፒ የተደራጁትን መረጃዎች ተጠቃሚው በቀጥታ /በኦንላይን/ መስጠት እንዲቻል በማድረግ ደንበኞች ወደ ተቋሙ መምጣት ሳይጠበቅባቸው ባሉበት ቦታ ሆነው በኦንላይን የሚፈልጉትን አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላል፡፡ በአሁኑ ወቅት አገልግሎቱን ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነው፡፡

የኦንላይን አገልግሎቱ እስኪጀመር ድረስ ደግሞ ደንበኞችን ለማርካት በኢሜልና በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ አማራጮች የሚፈልጉት መረጃ እንዲያገኙ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል። የመረጃዎችን ሀርድ ኮፒ የሚፈልጉ ደንበኞች እንዲሁ ኢንስቲትዩቱ ድረስ በመምጣት ማግኘት የሚችሉ ሲሆን፤ በተለይ ካርታዎች የሚፈልጉ ደንበኞች በአካል ተገኝተው ካርታውን መግዛት እንደሚችሉ አመላክተዋል።

ዳታ ማዕከሉ ለደንበኞች የሚሰጣቸው ዋነኛ መረጃዎች በሥነ ምድር ላይ የተሰበሰቡ ቴክኒካል ሪፖርቶችና ካርታዎች ናቸው፡፡ ዳታ ማዕከሉ ኢንስቲትዩት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ለ56 ዓመታት የተሰበሰቡ በርካታ መረጃዎችን የያዘ እንደመሆኑ ብዙ ዓይነት መረጃዎች አሉት። ከእነዚህም መካከል የጂኦሎጂ፣ የሃይድሮሎጂ፣ የኢንጂነሪንግ፣ የፊዚክስ፣ የተለያዩ በጂኦሎጂ ላይ ተሰሩ እና ሌሎች በርካታ መረጃዎችን መጠቀስ ይቻላል፡፡ በአጠቃላይ በዳታ ማዕከል 18 ሺ የሚጠጉ መረጃዎች መኖራቸው ይታወቃል፡፡ እነዚህ መረጃዎች በሶፍት ኮፒ እና በሀርድ ኮፒ የተሰበሰቡ ናቸው፡፡

መረጃዎች በማዕድኑ ዘርፍ ላይ ለተሰማራ ማንኛውም ዓይነት ኢንቪስተር፣ በዘርፉ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ አካላት፣ ከዩኒቨርሲቲዎቹ ለሚመጡ ጂኦሎጂ ተማሪዎች፣ ከውጭ ሀገራት የኢትዮጵያን ጂኦሎጂ ሊያጠኑ ለሚመጡ የውጭ ሀገር ተመራማሪዎች እና ሌሎች መረጃ ፈላጊዎች ይሰጣሉ፡፡ መረጃዎቹ በሁለት ዓይነት መልኩ የሚሰጡ ሲሆን በግዥ እና በነፃ የሚሰጥበት አሰራር ተቀምጧል፡፡ ተማሪዎች ከሆኑ ተማሪ መሆናቸው የሚገልጽ ደብዳቤ ከዩኒቨርሲቲው አጽፈው የሚያመጡ ከሆነ የሚፈልጉትን መረጃ በነፃ የሚያገኙበት አሠራር እንዲኖር ተደርጓል። ከተማሪዎች በስተቀር ማንኛውም መረጃ ፈላጊ የሚፈልገው መረጃ ዓይነት በገንዘቡ ገዝቶ መጠቀም የሚችልበት አሠራር ተዘርግቷል፡፡

በተመሳሳይ የማይፈለጉ ኮንፊደንሻል መረጃዎች (በተለያዩ ምክንያቶች ይፋ እንዳይሆኑ የሚፈለጉ) ይፋ እስኪሆኑ ድረስ ለማንም የማይሰጡና የማይሸጡ ናቸው፡፡ ኮንፊደንሻል የሚባሉ መረጃዎች አንዳንድ ድርጅቶች ማዕድን ፍለጋ ላይ ለመሰማራት ፍቃድ ወሰደው ጥናት ያጠናሉ። ፍለጋው አድርገው ሲጨርሱ በቃን ብለው ወደ ማዕድን ማውጣት ገብተው መረጃው ይፋ እንዲሆን ሲፈልጉ መረጃው ወደዳታ ማዕከሉ ሊገባ ይችላል፡፡ በድርጅቱ እጅ እስካልደረሰና እንዲሰጥ እስካልተፈለገ ድረስ ኮንፊደንሻል ስለሆነ ለማንም አይስጥም፡፡

ዳታ ማዕከሉ እነዚህን አሠራሮች ተከትሎ ሥራዎች ይሰራል፡፡ መረጃዎች ስካን በማድረግ በማተም፣ በሀርድ ያሉትን ወደ ሶፍት በመለወጥ ይሰራል፡፡ በሶፍት ያሉት ደግሞ በሀርድ ኮፒም እንዲቀየር ተደርገው የሚያዙበት አሠራርም ተዘርግቷል፡፡ በዳታ ማዕከሉ ያሉ መረጃዎች በርካታ ቢሆኑም የተወሰኑት ማዕድናት ላይ የተሰሩ መረጃዎችን መመልከት ተገቢ ይሆናል። ለአብነትም ወርቅ ላይ የተሰሩ 267 የሚሆኑ መረጃዎች የተሰበሰቡ ሲሆን፤ በብረት ላይ 100 ያህል መረጃዎች ተሰብስበዋል፡፡ ኮፐር፣ ድንጋይ ከሰል እና የመሳሰሉት ሁሉም ማዕድናት በሚባል ደረጃ መረጃዎች ተሰብስበው እንዲያዙ ተደርጓል።

መረጃዎቹ በሀገሪቷ ላይ ከሁሉም አቅጣጫ የሚሰበሰቡት ሲሆን፤ በተለይ በጂኦሎጂ ካርታዎች ሁሉንም ቦታዎች ማካተት ተችሏል። ኢትዮጵያ በኳርተር ሚሊዮን በ250ሺ እስኬል ማካለል ተችሏል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ በጥልቀት በ50 ሺ እስኬል ለመሥራት ሥራው ተጀምሯል፡፡

በኢንስቲትዩቱ በተለያዩ ዘርፎች ያሉ የጂኦሎጂ ባለሙያዎች በየዓመቱ ጥናት የሚያደርጉ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዓመቱ መጨረሻ የጥናቱ ግኝት ሪፖርት ተዘጋጀቶ ከተገመገመ በኋላ በዳታ ማዕከሉ ባሉ የጂኦሎጂ ባለሙያዎች ታይቶ ሪፖርቱ ተጠናቅቆ የሚቀረብና ወደ ዳታ ማዕከሉ እንዲገባ ይደረጋል፡፡ የሚቀረው ነገር ካለ ደግሞ በዚህ መልኩ ይስተካከል ሲሉ መልሰው እንዲስተካከል አድርገው የተስተካከለውን ይቀበላሉ፡፡ መረጃው ተደራጅቶ አስፈላጊ ሥራ ተሰርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ መረጃውን ለመረጃ ፈላጊዎች ምቹ በሆነ መልኩ አድርጎ በመያዝ በሚፈለግ ወቅት በቀላሉ ተደራሽ ለማድረግ ያስችላል ፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ኢጃራ እንዳብራሩት፤ ኢንስቲትዩቱ የሥነ ምድር ዳታን ያመነጫል ሲባል የተቋሙ ባለሙያዎች በየመስኩ በመገኘት ጥናትና ምርምር ያደርጋሉ፡፡ ናሙናዎች ተሰብሰበው ላብራቶሪ ገብተው ትንተና ከተሰራላቸው በኋላ ተገምግሞ ሪፖርቱ ይዘጋጃል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ዘንድሮ የተጀመረው ሥራ ሪፖርቱ በሚቀጥለው ዓመት የሚጠናቀቅ ይሆናል። ምክንያቱም በዘንድሮ ዓመት መስክ ተወጥቶ ናሙናዎች ተሰበሰበው ላብራቶሪ ይገባሉ፤ ከዚያ አስፈላጊውን ሂደት ተጠብቆ ስለሚሰራ ረጅም ጊዜያትን ሊፈጅ ይችላል፡፡

በዚህ ምክንያት አሁን ላይ በዳታ ማዕከሉ ያሉ መረጃዎች እስከ 2015 በጀት ዓመት ድረስ ያሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በመጨረሻም በአሁን ወቅት ወደ ኢንስቲትዩቱ መረጃ ፈልገው የሚመጡ መረጃ ፈላጊዎች የሚፈልጉት መረጃ በሶፍት እና በሀርድ ኮፒ በሚፈልጉት ልክ ተዘጋጅቶ ስላለ በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

ወርቅነሽ ደምሰው

 አዲስ ዘመን ህዳር 6/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You