የፊታቸው ጸዳል በእጅጉ ሰው ያቀርባል፣ ለንግግር ይጋብዛል።በጨዋታቸው መሀል ፈገግ ማለት ልምዳቸው ነው።እያወሩ ፈገግ ይላሉ፣ ፈገግ እያሉ ያወራሉ።ፈጽሞ ለዓይን አይከብዱም። ቀረብ ብሎ ለማውጋት ቀለል ያሉ ናቸው።
ሁኔታቸውን ላስተዋለ ችግር ይሉትን የሚያውቁት አይመስሉም።በፊታቸው ብሩህነት ያያቸው ሁሉ እንዲህ ቢገምት አይፈረድም።በፈገግታቸው ማንነታቸው ተሸፍኖ ኖሯል።በፊታቸው ገጽታ ዕንባን በሳቅ መልሰዋል።ግንባራቸው ኮስታራ አይደለም።ውስጣቸው ግን በሌላ ስሜት ተይዟል። በፈግታ በተሸፈነ፣ በሳቅ ጸዳል በተሰወረ ድብቅ ችግር።
ወጣትነትን በስራ
አባባ ጉግሳ ደሜ ዕድሜያቸውን በመንግስት ስራ ላይ አሳልፈዋል።
ጉግሳ ደሜ በ1960 ዓ.ም ከትውልድ አገራቸው ጊንጪ ወለንኮሚ አዲስ አበባ መጡ።የዛኔ ገና ወጣት ነበሩ። የልጅነት ዕድሜያቸው ለስራ ዝግጁ ነበርና መቀመጥ አልሆነላቸውም። አገራቸው የሚያሳርሱት የአባታቸው መሬት ቢኖርም ከተማውን ወደዱት።
የከተማ ሕይወት እንደገጠር አይሆንም። ኑሮ እንደዛሬው ባይከብድም መተዳደሪያ ያስፈልጋል። ሰርቶ የሚገባ ለኪሱ ገንዘብ፣ ለቤቱ ጥሪት አያጣም። ጉግሳ ይህ ሁሉ አልጠፋቸውም። ቀያቸውን ትተው ሲወጡ ሥራ መያዝ ግድ እንደሆነ ያውቃሉ።
አዲስ አበባ በዘመድ ቤት የቆዩት ጉግሳ የልባቸውን ሊሞሉ ዞር ዞር ማለት ያዙ።ለእሳቸው የሚበጅ የሚመጥን ስራ ለማግኘት ወዳጅ ዘመድ ጠያየቁ። ያገኙትን እየመረጡ፣ የመረጡትን እየተው ጥቂት ቀናት ቆዩ።ወጣቱ እንግዳ በጥሩ ደመወዝ የመንግስት ሰራተኛ መሆን ፍላጎታቸው ነው። እንደብዙዎች በቀን ሥራ ውሎ ራሳቸውን ማድከም አልፈልጉም።እናም ጥቂት ጊዜያት ጠበቁ።
ከጊዚያት በኋላ ከጉግሳ ጆሮ የምስራች ደረሰ። በማዕድን ሚኒስቴር የስራ ቅጥር አገኙ።የጉግሳ ምኞት የመንግስት ሰራተኛ መሆን ነው።የልባቸው ሀሳብ ስለሞላ፣ የመጡበት ዕቅድ ስለተሳካ ደስ አላቸው። የቅጥሩን ሂደት አጠናቀው ስራ ሲጀምሩ በቢሮው የተላላኪነት መደብ ተሰጣቸው።
አዲስ ሕይወት
ጉግሳ በተቀጠሩበት ቦታ አቅማቸውን ሊያሳዩ መትጋት ያዙ።ያሉበት የስራ መደብ ቅልጥፍናን ይጠይቃል።ከስራው ቀድሞ መሮጥ፣ የታዘዙትን ፈጥኖ ማድረስ የግድ ይላል። ይህ እንዲሆን የወጣቱ ተቀጣሪ ጉልበት አልደከመም።‹‹አቤት ወዴት›› እያሉ ስራውን ለማቀላጠፍ ከልባቸው ባተሉ።
የጉግሳ ስራ ፍቅርና ቅልጥፍና በአለቆቻቸው ዓይን ከፍ ያለ ሞገስ አገኘ።ሥራ ወዳድነታቸው፣ ታዛዥነታቸው፣ ሰዓት አክባሪነታቸው ሚዛን ደፍቶ ታየ። ሁሌም ጠንካራ ሰራተኞች እንዲህ በሆኑ ጊዜ ለተሻለ መደብ ይታጫሉ።በስራው የሚከፍሉት ዋጋ በጎ ሆኖላቸው ዕድገትና ለውጥ ያገኛሉ።
ጉግሳ ይህ አይነቱን አጋጣሚ ለማግኘት ጊዜ አልፈጁም።የተላላኪነታቸው የስራ መደብ ወደ መዝገብ ቤት ሹም አሻግሮ የቦታና የደመወዝ ዕድገት አሰጣቸው።
አሁን ወጣቱ ጉግሳ ከተላላኪነት ስራ ወጥተው ቢሮ መቀመጥ ጀምረዋል።አዲሱ የስራ መስክ ከደንበኞች የሚያገናኝ፣ ከሰራተኞች የሚያቆራኝ ነው።ጉግሳ በዋሉበት የስራ መስክ ጥንካሬ አይለያቸውም።የተሰጣቸውን ሀላፊነት በአግባቡ ለመወጣት ይጥራሉ።የሰራተኞችን የግል ማህደር በጥንቃቄ ይዘው ግዴታቸውን ይወጣሉ።
የመዝገብ ቤት ስራ ትኩረትና ሀላፊነት የሚያሻው ነው።ይህን የሚያውቁት ጉግሳ ስራቸውን በአግባቡ ይወጣሉ። የቀደመው ቅልጥፍናና ስራ ወዳድነት ከእሳቸው ጋር ነውና አሁንም ትኩረት አላጡም። ካሉበት ሙያ በተሻለ ደረጃ ሊያቆማቸው ምክንያት ሆነ።
ጉግሳ በአጭር ጊዜ ቆይታ ስራ ከጀመሩበት የተላላኪነት ሙያ ወደሌላ የስራ መደብ ለመሻገር አጋጣሚውን አገኙ።ከነበሩበት የመዝገብ ቤት ስራ ወደሌላ መደብ ተዛውረው እንዲሰሩ ከአለቆች ደብዳቤ ደረሳቸው።የተቀጠሩበት መስሪያ ቤት የስራ ባህርይ በቢሮ ብቻ አይወሰንም።በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የመዘዋወር አጋጣሚው ይበረክታል።
አሁን ጉግሳ ያደጉበት የስራ መደብ በቢሮ የሚወስናቸው አልሆነም።አዲሱ የስራ ዘርፍ በየመስኩ የሚያስወጣ፣ በየአገሩ የሚያዟዝር ሆኗል።እሳቸው በየአጋጠሚው ያላዩት፣ ያልሰሩበት ስፍራ የለም። ከቦታ ቦታ በመኪና እያቋረጡ ከስራው መስክ ተገኝተዋል።ኦጋዴንን በመሰሉ መኪና በማይገባባቸው ስፍራዎችም በአየር ትራንስፖርት ተጉዘዋል።
የዛኔ ቀብሪ ደሀር ፣ ቀላፎና ሌሎች የሱማሌ አካባቢዎች በእሳቸውና በአጋር የስራ ባልደረቦቻቸው የሚሸፈኑ ነበሩ።ጉግሳ ከመስክ ስራቸው በዘለለ በኑሮ በቆዩባቸው አካባቢዎች ዓመታትን ባስቆጠረ ቆይታ ዘልቀዋል።አብረዋቸው ከሚኖሩት ባለቤታቸው ያገኙት ፍሬ ባይኖርም ወለጋ በነበሩ ጊዜ አንድ ወንድ ልጅ ወልደዋል።ባለቤታቸውም ልጅ እንደራሳቸው ተቀብለዋል።
ጉግሳና ዘንድሮ
ጉግሳ ደሜ የዕድሜ ዘመናቸውን በመንግስት ስራ አሳልፈው ዕድሜያቸው በደረሰ ጊዜ በክብር በጡረታ ተሰናበቱ።ዓመታትን በጥንካሬና በድካም ያሳለፈው ጉልበታቸው እረፍት ባገኘ ጊዜ ከቤት ሊውሉ ግድ አለ።ጉግሳ ከጡረታ የሚቀበሉት ገንዘብ ወር የሚያደርስ የጓዳን ቀዳዳ የሚሸፍን አይደለም።
ዓመታትን አብረዋቸው የዘለቁት ባለቤታቸው ጤና ካጡ ቆይተዋል፤ ከእሳቸው የጋራ ፍሬ ባይኖራቸውም የዘመድ ልጆችን እንደራሳቸው አሳድገው ለቁም ነገር አድርሰዋል።ዛሬ ሁሉም በራሳቸው ዓለም የሚሮጡ፣ በግላቸው ሕይወት የሚባዝኑ ናቸው።ጉግሳ ወለጋ ሳሉ የወለዱት ልጃቸው ያቅሙን ይረዳቸዋል።በቅርብ ባይኖርም ወላጅ አባቱን አልዘነጋም።
ጉግሳ ወር ጠብቀው በእጃቸው የሚያስገቡት አንድ ሺ ብር የልብ ሞልቶ አያውቅም።እንዲህ መሆኑ ያለስራ ተቀምጦ በሀሳብ ለሚናውዝ አባወራ ኑሮን አክብዷል።በህመም ቤት የዋሉት ባለቤታቸው ወጥተው መስራት የሚችሉ አይደሉም።ይህን ልሞክር ቢሉ እንኳን ዕድሜና አቅም ማነስ የሚያራምዷቸው አልሆኑም።
አሁን ኑሮ እየከበደ ችግር እየጨመረ ነው።አንዳንዴ አዛውንቶቹ ባልና ሚስቶች የመኖር አማራጭ ይጠፋቸዋል።እንደ ቀድሞው ሮጦ የሚያድር ጉልበት ፣ ሰርቶ የሚገባ አቅም በሌለበት በሀሳብ ሲጨነቁ ይውላሉ።
ጉግሳና ሚስታቸው በደህና ጊዜ ያሳደጓቸው የዘመድ ልጆች ከቤት ብቅ እያሉ ቤት ያፈራውን ያበስሉላቸዋል። አውደ ዓመት በመጣ ጊዜም እንደወጉ ለመሆን ክብር አያሳጧቸውም።እንዲያም ሆኖ አሁን ላይ ኑሮን የሚያሸንፉት አልሆነም።ችግርን እንደሁኔታው ለመወጣት አቅም አንሷቸዋል ።
ሳቂታው አዛውንት
አብሯቸው የኖረው ፈገግታ ችግራቸውን የሸፈነ፣ ሕይወታቸውን የደበቀ ይመስላል። ቀርቦ ያዋየ ፣ የጠየቃቸው ቢኖር ግን ከሳቂታ ፊታቸው ጀርባ የተደበቀ እውነት መኖሩን ይረዳል። ፈገግታ የተሰጣቸው ልማድ መሆኑን ያውቃል። ችግሩ ማን ቀርቦ ያዋያቸው፣ ውስጣቸውን ማን ይወቅላቸው የሚለው ላይ ነው።
እኔ አጋጣሚውን አግኝቼ ከአባባ ጉግሳ ጋር ጥቂት አወጋሁ።ያገኘኋቸው ልደታ አካባቢ ስራ ከጀመረው የተስፋ ብርሃን የምገባ ማዕከል ውስጥ ነበር።ጉግሳ በስፍራው የመቆማቸው እውነት ከምገባ ማዕከሉ የሚያገኙትን ምሳ ለእሳቸውና ለህመምተኛዋ ባለቤታቸው ለመውሰድ ነው። ማዕከሉ እሳቸውን ለመሰሉ አቅመ ደካማ ወገኖች በቀን አንድ ጊዜ የምገባ መርሀ ግብር አለው።
ጉግሳ ሁሌም ሰዓቱን አክብረው በስፍራው ይደርሳሉ።እሳቸውን መሰል ችግረኞች ተቀምጠው በሚመገቡበት ዕልፍኝ የሚሰጣቸውን አመሰግነው ይቀበላሉ። ከሚያገኙት በረከት ግን አንዲት ጉርሻ እንኳን ወደአፋቸው አይሉም።ከቤት ተኝተው የእሳቸውን እጅ የሚጠብቁ ሚስታቸውን ያስባሉ።
እሳቸው የዕድሜ መግፋት ከህመም ያንገላታቸው ወይዘሮ ናቸው።እንደቀድሞው አባወራቸውን ደፋ ቀና ብለው አይቀበሉም።ከጉግሳ እጅ የሚመጣውን በረከት ቀምሰው ለመዋል ደጁን ይናፍቃሉ።ልጃቸው በራሱ ሕይወት የሚኖር የቤተሰብ አሳዳሪ ነው። አንዳንዴ ሲታመሙ ብቅ ከማለት የዘለለ በቅርባቸው የለም።
ዛሬ አቶ ጉግሳና ባለቤታቸው የኑሮ ውድነት ያንገላታቸው ይዟል።ያላቸው አቅም በቀን አንድ ደረቅ እንጀራ የሚያስገዛ አልሆነም።ቀድሞ በሳንቲም የሚገዙት ዕቃ ዛሬ ብር ለውጦት ዋጋው በእጥፍ ጨምሯል።በየቀኑ ሽቅብ የሚንረው ኑሮ ውድነት በተለይ አባወራውን በእጅጉ ያሳስባቸዋል።
በጡረታ ዕድሜ የሚገኙት አዛውንት ያለፉበት የሕይወት ውጣ ውረድ ዛሬን በእፎይታ ሊያኖራቸው እንደሚገባ ያምኑ ነበር።ይህ እንዳይሆን ሕይወት በራሱ ፈተና ሆኖ እያንገላታቸው ነው።ሁሌም ደጋግመው ሲያስቡት የሚገርማቸው የዘንድሮ እህል ገበያ ነገር ነው።በእሳቸው ዕምነት መሬቱ ሰፊ እርሻው የሰጠ ነው። በየዓመቱ የሚገኘው በረከትም ዕልፎችን በወጉ መግቦ ያሳድራል።
ዛሬም የገጠሩ መሬት ብዙ የሚያበቅል፣ የሚያሳፍስ ነው።በከተማ ሲሆን ግን ታሪኩ ይቀየራል።የሚገኘው በረከት ገንዘብ አሸንፎት፣ ለጥቅም አዘንብሏል።የኑሮ ውድነቱ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎችን እያንገዳገደ ነው።
ችግር ያልፈታው ጎጆ
አዛውንቶቹ ባልና ሚስቶች እንዳለፉት መልካም ዘመናት ሁሉ ዛሬም አልተለያዩም።ዕድሜ፣ ህመምና ችግር እየፈተናቸው በአንድ ተቆራኝተዋል።አንዳንዴ ሊጠይቋቸው ብቅ የሚሉ ዘመዶች ከእጃቸው ይረጥባሉ።ወይዘሮዋ የሚያገኝዋትን ይዘው እንደአቅም ለቤት፣ ለሆድ የሚውለውን ያስባሉ።ጥንዶቹ ተደማምጠው ማደራቸው መልካም ሆኗል።አባወራው ከሚያመጡት የሰሀን ምግብ የዕለቱን እየጎረሱ ስለነገው ፈጣሪን ተስፋ ያደርጋሉ።
ጉግሳ በቅርቡ ባጋጠማቸው የጤና እክል ከሆሰፒታል ለሁለት ወራት ተኝተው የቀዶ ህክምና አድርገዋል። እሳቸው ለነገ የሚሉት ገንዘብ የላቸውም። ከቀበሌ ባገኙት የጤና መድህን የነጻ ታካሚ ናቸው።ዛሬን በጤና ቆመው ስለነገ ተስፋ ማድረጋቸው ከአግርሞትም በላይ ለምስጋና አብቅቷቸዋል።
አባወራው ዓውደ ዓመት በደረሰ ጊዜ እንደቀድሞው ቀንዱ የዞረ ሙክት፣ ለመግዛት ገበያ አይወጡም። ከመንደሩ ሰዎች ጋር ቅርጫ አይገቡም።ወይዘሯቸውም ቢሆኑ ለዶሮና ቅቤ፣ ለዳቦና ጠላው መቀነታቸውን አይፈቱም። ዛሬ የትናቱ ታሪክ ከእነሱ የለም።ለዓመት በዓሉ ወግ ደጁን የሚናፍቁ፣ የዘመድ እጅን የሚያዩ ሆነዋል።
ጉግሳ ዓመታትን በቆጠሩበት የመንግስት ስራ ደስተኛ ነበሩ።ጊዜና ጉልበታቸውን ሰጥተው ሀላፊነትን መወጣታቸው ዛሬ በእጅጉ ያኮራቸዋል።አሁን አቅማቸው ሲደክም ጉልበታቸው ሲዝል ያለፈውን ጊዜ ያስባሉ፣ ልጅነታቸውን ያስታውሳሉ። የከፈሉት ዋጋ በዕድሜ ዘመናቸው ለሀገራቸው ያበረከቱት ስጦታ ነውና ቆጭቷቸው አያውቅም።
በስራ ያሳለፈው ጉልበታቸው፣ በድካም የዛለው አካላቸው ዛሬ አቅም አጥቷል።‹‹ይሁነኝ›› ብለው ግን ሰዎችን ‹‹እርዱኝ ፣ አግዙኝ ›› ሲሉ አይጠይቁም። ትናንት ብር ሲቆጥር ደመወዝ ሲያስገባ የነበረ እጃቸው ዛሬ ፈጽሞ ለልመና አይዘረጋም።
አባባ ጉግሳ ኩሩ ናቸው።ችግር ከእሳቸው ባይርቅም የፊታቸው ፈገግታ ይህን አሳብቆ አያውቅም። ሁሌም በሳቂታው ፊታቸው ዛሬን ያደምቃሉ፣ ነገን ይሻገራሉ። ፈገግታቸው የውስጣቸው ሀቅ የሸፈነ ቢመስልም ቀርቦ ያወጋ፣ ያዋያቸው ከእውነቱ ጥግ ይደርሳል። የፈገግታው ቋጠሮ ሲፈታ ያለውን ሀቅ ይረዳል።
ጉግሳ ‹‹ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ›› በሆነው ኑሯቸው ከነገ ለመድረሰ ትግል ላይ ናቸው።ዓመታትን የቆጠረው የትዳር ሕይወታቸው በዕድሜ ብዛት ታጅቦ ማግኘትን ከማጣት ቢያሳያቸውም ዛሬም ለመኖር ሲሉ ተስፋ አይቆርጡም።ፈገግ እንዳሉ ትናንትን አልፈዋል፣ ከዛሬ ደርሰዋል።ነገን አስበዋል። በሳቂታ ፊት፣ በማይፈዝ ፈገግታ።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/ 2015 ዓ.ም