«ነገርን ከሥሩ»
ስለ ርዕሳችን መሪ ቃል ጥቂት ማብራሪያ በመስጠት ወደ ንባብ መንገዳችን እንዝለቅ። የምድራችን በርካታ ቋንቋዎች በቤተኛነት ከሚገለገሉባቸው ቃላት መካከል፤ ምናልባትም በቀዳሚነት፤ አንዱ ለዋና ርዕስነት የመረጥነው “አሜን!” የሚለው ቃል ነው። ሥርወ መሠረቱን ከእብራይስጥ ቋንቋ ያደረገው ይህ ቃል የቅርብ ዝምድናው ከሃይማኖቶች ጋር ብቻ የተያያዘ ይምሰል እንጂ አገልግሎቱ ከዚያም ላቅ ይላል።
እርግጥ ነው በአይሁድ፣ በክርስትና በእስልምናም ሆነ በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ ቃሉ እንደ ማረጋገጫ ቀመር አገልግሎት ላይ እየዋለ እንደሆነ አይካድም። እንደ መዛግብተ ቃላት ፍቺ ከሆነ “አሜን!” የሚለው ቃል ከሃይማኖት መጻሕፍት ንባባት ጋር ሲጎዳኝ እውነት ነው ማለት ይሆናል። በጸሎት መሃል “አሜን!” የሚባል ከሆነ ደግሞ “ይሁንልኝ፣ ይደረግልን” እንደ ማለት ነው።
በታሪክ ነገራና ትርክት ጣልቃ የሚገባ ከሆነም “እውነት ነው፣ ያስማማናል” የሚል መልዕክት ያስተላልፋል። በትዕዛዝ መካከል ቃሉ የሚጠራ ከሆነ ደግሞ “እሺ እታዘዛለሁ” የሚል ትርጉም ይኖረዋል። በአጭሩ “አሜን!” የእምነት ወይንም የአቋም ማረጋገጫና የስምምነት መግለጫ ጽንሰ ሃሳብ የተሸከመ ክቡድ (ጽኑ) ቃል ነው ማለት ይቻላል።
«የእርቀ ሰላሙ አሜንታና ቀጣዩ ዝግጅት»
ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ኢትዮጵያ ከፍ ባለ መድረክ ገዝፋና አሸንፋ የወጣችበት ታሪካዊ ቀን ነበር። ይህንን አሸናፊነቷን ሲገልጹ የዋሉት ደግሞ የዓለም መንግሥታት፣ ሕዝቦችና ታላላቅ ሚዲያዎች ጭምር ነበሩ። እስካሁንም በዜናቸው፣ በሀተታቸውና በትንታኔያቸው መሪ ርዕሰ ጉዳይ አድርገው እየዘከሩ ያለው “እንደ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አገላለጽ መቶ በመቶ” በሚባል ደረጃ በደቡብ አፍሪካ (ፕሪቶሪያ) የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት የሰላም ንግግር ስኬትን በዋነኛነት በማጉላት ነው።
እርግጥ ነው አጀንዳው የመላው የዓለም መንግሥታትና የምድራችንን አየር የተቆጣጠሩት ሚዲያዎች ዋነኛ ትኩረት ይምሰል እንጂ እንደ እኛ እንደ ባለጉዳዮቹ ጦርነቱ ያስከፈለው የደም፣ የላብ፣ የሃብትና የሥነ ልቦና ቀውስ ጥዝጣዜው በእኩል ደረጃ እየተሰማቸው ነበር ለማለት ያዳግታል። በዲፕሎማሲ ጦርነቱ፣ በአስፈላጊ መሠረታዊ ወታደራዊ ጉዳዮቻችንና በዕለት ርዳታ አቅርቦት ረገድ አንዳንድ ወዳጅ አገራትና የተራድኦ ድርጅቶች ከጎናችን ተሰልፈው ያበረከቱልንን አስተዋጽኦ ግን የምንዘነጋው ስላልሆነ “አሜን!” በማለት ማመስገንን አንዘነጋም።
የሰላም ንግግሩ “በሰላም መጠናቀቅ” ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ትርጉሙ እጅግ የላቀ ነው። በየቤተ እምነታቸው ዐውደ ምህረት ላይ ለጸሎትና ለዱአ ሲደፉ፣ ሲንበረከኩና ሲሰግዱ ለነበሩት ዜጎች (በተለይም እናቶችና አባቶች) የስምምነቱ ውጤት በፈጣሪ ርዳታ ጭምር እንደተገኘ ስለሚያምኑ እንደ እምነት ቀኖናቸው አመኔታቸው ከፍ ያለ፤ ዕልልታቸውም እጅግ የደመቀ ነው።
ከዚህኛውም ሆነ ከዚያኛው ወገን የደምና የላብ ግብር ለመክፈል በፍልሚያው ጎራ ልጇ የተሰለፈው እናት ወይንም አባት ወይንም ቤተዘመድ የሁለት ወገን ንግግሩ “በሰላም ተቋጨ” ሲባል ደስታቸው እንዴት ስሜታቸውን ፈንቅሎ “አሜን!” እንደሚያሰኛቸው መገመቱ ለማንም የሚከብድ አይደለም።
በወረራውና በጦርነቱ ፍልሚያ መሃል በዱር በገደል ወድቀው ለቀሩት የክፉ ቀን ታዳጊ የመከላከያና የሕዝባዊ ሠራዊት ጀግኖቻችን ለከፈሉልን የሕይወት ዋጋ ክብር ለአጽማቸው! ክብር ለነፍሳቸው! ይሁን በማለት “አሜን!” እንላለን። ንብረታቸው ወድሞ፣ ሀብታቸው ተዘርፎ፣ አካላቸው ጎድሎ፣ ተደፍረው፣ በሥነ ልቦና ቁስል ተመትተውና በመፈናቀል ተንከራታች ሆነው ቀኑ ለጨለመባቸውና እምባቸውን ቀለብ አድርገው መከራቸውን ለተቋቋሙ ዜጎቻችን ክብርና ሞገስ እንዲሆንላቸው ደግመን ደጋግመን አሜንታችንን በአክብሮት እንገልጻለን።
በአገር ላይ የተፈጸመው ግፍ፣ ዕልቂት፣ ወድመትና ጥፋት ታሪካችን በጥቁር መዝገቡ በዝርዝር አስፍሮ ለትውልድ እያቀበለ ስለሚኖር ደግመን ደጋግመን ቁስል እየቀሰቀስንና እየቆሰቆስን መልሰን መላልሰን ከመዘከር እንታቀባለን። የሰላም ንግግሩ ስምምነትም አይፈቅድልንም። ቁርሾና ቂም እየመዘዝንም በደል መተረኩም አይበጀንም። ይልቁንስ ንግግሩ በአሜንታ መቋጨቱ አንድ ነገር ሆኖ እንደ አገር መከናወንና መተግበር ስላለባቸው ጉዳዮች መመካከሩና መወያየቱ ይበልጥ የተሻለ እንደሚሆን እናምናለን።
በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ “መጽሐፈ ነህሚያ” በሚል ርዕስ የሚታወቅ አንድ ድንቅ የታሪክ መጽሐፍ ይገኛል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚተረከው ታሪክ በፋርስ ንጉሥ በአርጤክስስ ዘመነ መንግሥት (ከ464 – 425 ዓ.ም) በአይሁዳዊያን ላይ የተፈጸመ ምርኮና ስደት ምን ይመስል እንደነበር በዝርዝር ይተርካል። በተለይም አይሁዳውያን በትልቅ ክብር የሚኮሩባት፣ የሚመኩባትና “ቅድስት” ብለው የሚያሞካሹዋት የእየሩሳሌም ከተማ እንዴት በጠላቶች እንደተማረከችና ቅጥሮቿም ፈራርሰው እንደወደመች በዝርዝር ይተረካል።
ከምርኮኞቹ መካከል በማራኪያቸው ቤተመንግሥት ውስጥ ያገለግል የነበረው ነህምያ የሚባለው ቀናኢ ሰው በንጉሡ ፈቃድ ወደ እየሩሳሌም ተመልሶ የፈራረሰችውን ከተማቸውን ዳግም ለመሥራት ከምርኮ ከተረፉት ቅሬታዎች ጋር ሲመካከር የተናገረው ድንቅ ንግግር በብዙ የአመራር ጥበብ ተመራማሪዎችና አስተማሪዎች ዘንድ ደጋግሞ ይጠቀሳል።
ለእኛ ዐውድ ሊቀራረብ ይችላል ብለን በማሰብ እንደሚከተለው ከንግግሩ አንድ አንቀጽ እንጠቅሳለን። “ያለንበትን ችግር ይኸው ታያላችሁ፤ እየሩሳሌም ፈርሳለች፤ በሮቿም በእሳት ጋይተዋል። አሁንም ኑና የእየሩሳሌምን ቅጥር እንደገና ተረባርበን እንስራ፤ ከእንግዲህስ መሳለቂያ አንሆንም አልኋቸው” (ምዕራፍ 2 ቁጥር 17)።
እርግጥ ነው ነህምያ ቅጥሩን ሲሰራ ሁሉም “አሜን!” ብሎ ተባብሮት ነበር ማለት አይቻልም። እንዲያውም ተግዳሮቱን የገለጸው እንዲህ በማለት ነበር፡- “ቅጥሩን እንደምንሰራ ጠላቶቻችን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቆጡ፤ እጅግም ተበሳጩ። ተሳለቁብንም።…አነዚህ ደካሞች ምን እያደረጉ ነው? ቅጥራቸውን መልሰው ሊሰሩ ነውን? እንዲዚያ ተቃጥሎ የፍርስራሽ ክምር የሆነውን ድንጋይ ነፍስ ሊዘሩበት ይችላሉን? እያሉ አላገጡብን።” በማለት የክፉዎችን ድርጊት በሚገባ ተርኮታል።
እኛም ዘንድ ቢሆን አንደኛውን ለይቶላቸው የሰላም ስምምነቱን በተመለከተ የሚያካኪሱ፣ የሚያራክሱ፣ የሚያላግጡ፣ የሚቃወሙና የክፋት መርዛቸውን ባገኙት መድረክ ሁሉ ለማቀርሸት የሚቅበዘበዙ ፀረ ሰላሞች በዚህኛውም ሆነ በዚያኛው ወገን ይጠፋሉ ለማለት አይቻልም። ስምምነቱ በገቢር ስለመተርጎሙም በቅንነት የሚጨነቁ አንዳንድ ዜጎች እንደሚኖሩም ይገመታል። እነዚህም ተባለ እንደዚያ ኢትዮጵያ ከአሸናፊነት ክብሯ ዝቅ ብላ ዳግም ለጥፋት መልእክተኞች ጆሮ እንደማትሰጥ በአሜንታዋ አረጋግጣለች። “አውድማ የቆረጠችውን ቆርጣለች፤ ፌጦ በከንቱ ትረጫለች” እንዲል ብሂሉ ዳግም ወደ ጥፋቱ የሚመለሰው “ቡቾ” የምንለው የቤት እንስሳ ብቻ ነው።
በተለኮሰብን የጦርነት ሰደድ እሳት ምክንያት የፈራረሱብን “ቅጥሮች” እጅግ ብዙዎች ናቸው። የአገራዊ ኢኮኖሚያችን “ቅጥር” መናጋቱ እውነት ነው። ሰብዓዊ ጉዳቶቻችንም ገና በአግባቡ ተለይተው አልተጠናቀቁም። የበርካታ ማሕበራዊ እሴቶቻችንና ተራክቧችን “ቅጥሮችም” ክፉኛ ፈራርሰዋል። በጥቅሉ ለመግለጽ ካስፈለገ ምክንያት አልባው ጦርነት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የከፋ ችግርና መከራ ላይ መጣሉን በብዙ ማስረጃ ማረጋገጥ ይቻላል።
ምናልባትም የገጠመን ፈተና በእስከዛሬው ታሪካችን ተፈጽሞ ስለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። ስለዚህም እንደ አገር ለእኛ የከፋ ጉዳት፣ ለዓለም ማሕበረሰብ ደግሞ መሳለቂያና መዘባበቻ ያደረጉንን ፍርስራሾቻችንን እንደገና በተሻለ ሁኔታ አሳምረን ለመገንባት ምን ማድረግ ይገባናል? የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ ለመመለስ በትጋት መሰለፉ ይበልጥ ስለሚመረጥ በመልሶ ግንባታ ረገድ ማድረግ ስለሚገቡን ጉዳዮች አንዳንድ ሃሰቦችን ፈነጣጥቀን እናጠቃልላለን።
በጦርነቱ ምክንያት የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉልን ጀግኖቻችን ወላጆችና ቤተሰቦች መጽናናትና መደገፍ ይገባቸዋል። አይዟችሁ መባልንም ይጓጓሉ። ስለሆነም እንዴት ነው በሀዘን ግርዶሽ የተሸፈኑትን ወገኖቻችንን ሕይወት የምናለመልመው? እንዴትስ ነው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከሰላም ስምምነቱ “አሜንታ” ማግሥት የምንታደጋቸው? ይህን መሰሉ ከፍ ያለ የቤት ሥራ ከፊታችን ገዝፎ እየጠበቅን ስለሆነ በአግባቡ ልንመክርበት ይገባ ይመስለናል።
ንብረቱና ሀብቱ፣ በአንድ ጀንበር ወድሞበት ኑሮውንም፣ ትዳሩንም ሆነ ልጆቹን እንዳጣው እንደ ቅዱሱ መጽሐፉ ጻድቁ ኢዮብ እጃቸውን አጨብጭበው በሁለንተናቸው ባዷቸውን የቀሩትና ድጋፍ የሚፈልጉ ወገኖቻችን ሺህ ምንተ ሺህ ናቸው። የሥነ ልቦና ቀውስ ደርሶባቸው በራቸውን ዘግተው እያነቡ ያሉ ዜጎቻችንም ከግምታችን እጅግ የበዙ ናቸው። የተፈናቀሉትን፣ የተሰደዱትን፣ የተንከራተቱትን እያልን ብንዘረዝር ቆጥረን የምንዘልቀው አይደለም። በአጭሩ የፍርስራሹ ስፋትና ግዝፈት ይህ ልክህ ብለን ልንወስነው የምንችል አይመስለንም።
ተገደውም ሆነ ወደው በዚያኛው ወገን ፕሮፓጋንዳ በመሸነፍ አምላካዊ ጥሪያቸውን በመዘንጋት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ያወገዙ የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎች ያፈራረሱት የጋራ “ቅጥር” መጠገን የግድ ይላል። ተቀዳሚ ባለጉዳዮቹ የኢትዮጵያ ቤተ እምነት መሪዎች እንደ ነህምያ ጨክነውና ቆርጠው “ከመሳለቂያነት” ሊታደጉንም ይገባል።
የኪነ ጥበቡም ቅጥር የተነቃነቀና ስንጥቅ የሚታይበት ይመስላል። በዚህም ዘርፍ የአገሪቱ የጥበብ ቤተሰቦች ብዙ ሥራ ይጠበቅባቸዋል። የአገሪቱ ምሁራን፣ በሀብት የተባረኩ ዜጎች፣ የፖለቲካ ልሂቃንና የማሕበረሰብ አንቂዎች፣ የአካባቢና የፌዴራል መንግሥታት አመራሮች፣ የአገሪቱ ሚዲያዎች፣ ወጣቶችና አረጋውያን ከገጠመን መከራና “ጉስቁልና” ፍርስራሾቻችንን አሳምረንና አስውበን እንድንገነባ እጃችንን በአንድነት ልናበረታታና የድርሻችንን ልንወጣ ታሪካዊው ግዴታና ሰብዓዊው ውዴታ ግድ ይለናል።
በሰላም ንግግሩ መቋጨት ማግሥት የሚጠበቅብን አገራዊ ኃላፊነት በጥቂቱ ይህንን ይመስላል። ቢቻል ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት በሙሉ አሜንታ የዜግነት ድርሻችንን በአቅማችን ልክ ለመወጣት እንጨክን። የማይሆንልን ከሆነ የጥሞና ጊዜ ወስደን ጉዳዩን በሰከነ ስሜት ለመከታተል ኮስተር ብለን እንወስን። በትንሽ በትልቁ እየተቃወምን “ንፋስ እንድንጎስም” ስሜታችን የሚጎተጉተን ከሆነ ደግሞ ለራሳችንና በራሳችን ጊዜ በራችንን ዘግተን እንቆዝም እንጂ የሚሊዮኖችን የተስፋ ብርሃን ለማጨለም የበጋ መብረቅ አንሁን። መንፈሳችንንና ሰብዓዊነታችን በሁከት ሱሰኛነታችን ምክንያት ተጠይፈውንና ንቀውን ጥለው እንዳይረግጡን ለራሳችን ክብር እንስጥ። አሜን! ሰላም ይሁን።
(በጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 26/ 2015 ዓ.ም