የምትፋጀውን ጸሀይ ለመሸሽ ስል ለረጅም ሰዐት ከቤት አልወጣሁም ነበር።ከሰዐት ወደ አመሻሽ ሲሳብ ቀን ሙሉ ካላየሁት ደጅ ጋር ተያየሁ።የጸሀይዋን ማረጥ ተከትዬ ብቻዬን ስሆን የምተክዘውን ትካዜ እየተከዝኩ ወደ አንድ ሄጄበት ወደማላውቀው ሰፈር አመራሁ።ትካዜ አቅል እንደሚያሳጣ ዛሬ ነው ያወኩት።ለብዙ ዘመን ተክዤ አውቃለው እንደዛሬው ግን ከማላውቀው ሰፈር ከማላውቃት ሴት ጋር አገናኝቶኝ አያውቅም።አንዴ ብቻ ነው ያየኋት..አልደገምኳትም..አልሰለስኳትም።በአንድ ጊዜ እይታ ብቻ ግን ለዘላለም ያየኋት ያክል ሲሰማኝ ነበር።ገጽዋ እሳታማ ነው..ከቤት እንዳልወጣ እንደከለከለችኝ የሰባት ሰዐት ጸሀይ።ጠይም ሆኖ እንደ ጸሀይ መድመቅ እንዴት ይቻላል? ሀሳብ ሰለበኝ።
አንድ ጊዜ አየኋት..ከአፍታ ላነሰ፣ ከላመል ለተቆረሰ ጊዜ።አንድ ጊዜ ብቻ ነው ያስተዋልኳት..ከቅጽበት ለጎደለ.. ከኢምንት ለተገመሰ ጊዜ..በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን ምኗም ሳይቀር በትካዜ በራደ አእምሮዬ ውስጥ ተቀርጾ ነበር።
ሁለት አይነት ሴት ናት..እየሳቀች የምትጸሙን።በአንድ ጊዜ ሁለት ነፍሷን አየሁት..አንዴ ሳቅ አንዴ ደግሞ ዝም ብላ።ዝምታና ሳቋን በአንድ ጊዜ አየሁት።የመጀመሪያው.. ከእሷ ውበት መለስ ካለች እንደ አስፓልት ከጠየመች ጓደኛዋ ጋር ታክሲ እየጠበቁ ቆመዋል።አጠያየማቸው አንድ አይነት ነው..።ምን እንደሆነ ባልደረስኩበት ለሁልጊዜ በሚናፍቀኝ ወሬዋ ጓደኛዋን እያወራች በራሷ ወሬ የኮረኮሯት ያክል እየሳቀች አየኋት።በራስ ወሬ እንዲህ እንደሚሳቅ አላውቅም ነበር።ወሬኛው እኔ እንኳን በወሬዬ ስንቶችን ሳስቅ በራሴ ወሬ ፈገግ ብዬ እንኳን አላውቅም።ሳቋ ውብ ዜማ ሆኖኝ ውስጤ ተቀመጠ።ትካዜዬ በሳቋ ደንግጦ ላይመለስ ጥሎኝ ጠፋ።ከዛሬ በኋላ መቼም የምተክዝ አይመስለኝም.. ሳቋ ለዘላለም የተሸከምኩትን የእናቴን ውቃቢ ከላዬ ላይ ያባረረልኝ ይመስለኛል።ሁለተኛው..ይሄን ሳቋን ያጸለመችበት ምዕራፍ ነው።ሰው እንደዛ ስቆ እንደዛ ዝም ይላል? በሳቅ የፈካ ፊቷን ከየት እንዳመጣችው ባልደረስኩበት ጽሞና ሞላችው።ብዙ ነገሯ ገረመኝ..ውበቷ፣ በአንድ ጊዜ ከሳቅ ወደ ዝምታ ያደረገችው መመለስ።ተጠራጠርኳት.. እንደ እኔ በትካዜ መሄጃ ያጡ ነፍሶችን ለመታደግ ሰው የሆነች መሰለኝ..ደግሞም አመንኳት..ልቤ ግን በዚች ሴት እንግዳ ሀሳብ ተጠምዳ ነበር።
የሆነ ለዘላለም የምረግመው ገላው ላይ የጃማይካዊው የቦምማርሌ ስዕል ያለበት ሰማያዊ ታክሲ መጥቶ ይዟት እስከተሰወረ ጊዜ ድረስ በዛ ቦታ ስለ እሷ እያሰብኩ ተገትሬ ነበር።እሷን በጫነው ታክሲ ቀናሁ።አብረዋት በተሳፈሩ መንገደኞች፣ አብሯት በተቀመጠው ሰው ቀናሁ።በሾፌሩ.. ከእሷ እጅ ላይ ሂሳብ በሚቀበለው ወያላ ቀናሁ።በዝምታና ሳቋ ተለክፌ ወደ ቤቴ ተመለስኩ።ያን ዝምታና ሳቅ በልቤ ሳሎን ላይ ሰቅዬ ለዘላለም አስታውሰዋለው።ይሄ ከዛ ቦታ ስሸሽ ለራሴ የገባሁት የማይታጠፍ ቃል ኪዳን ነበር።
አንዳንድ ቀኖች እንዲህ ናቸው..ወይ ከህይወት ያጎላሉ ወይ ጎደሎ ይሞላሉ።የእኔ እጣ ፈንታ ምን እንደሆነ አልደረስኩበትም።ቤት ስደርስ ሚስቴ አስጠላችኝ።በዛ ፈገግታ..በዛ ጽሞና በማንም እንደማልተካው ያወራሁለት የሚስቴ ፈገግታና ዝምታ አስጠላኝ።ለአፍታ ባየኋት ሴት ውበትና ፈገግታ ተረትቼ ለዘመናት የገነባሁትን ትዳሬን ገፋሁት።ሚስቴ እንደ እሷ እንድትስቅ፣ በአንድ ጊዜ ብዙ አይነት ሴት እንድትሆን ብዙ ለፋሁ አልሆነም።በሚስቴ ሴትነት ውስጥ ያቺን ለአንድ ጊዜ ያየኋትን ሳቂታ ሴት ፈለኳት አላገኘኋትም።በእንግዳ ባህሪዬ እኔም ሚስቴም ተቸገርን።ራሴን እንደ ድሮው መፍጠር ግን አልቻልኩም።ወደ ትካዜዬ ተመለስኩ..ዳግመኛ ይጎበኛል ብዬ ወዳላሰብኩት ትካዜዬ ዳግመኛ ላልወጣበት ተዘፈኩበት።በትካዜዬ ውስጥ እንደ ድሮው እናቴ ብቻ አልነበረችም እናቴን የማትመስል ሌላም አንዲት ሳቂታ ሴት ነበረችበት።
ትካዜ የአእምሮ መሞት ነው..የልብ መሰለብ ነው።ትካዜ ነፍስ ከስጋ ጋር ስትኳረፍ ዝም የምትለው ዝምታ ነው።ስጋ ከነፍስ ጋር ሲቃየም የሚደብተው ድባቴ ነው።ሰው ከተከዘ ከሙላቱ እየጎደለ ነው።ከስፋቱ እያነሰ ነው።የእኔ ትካዜ ግን ይሄን ሁሉ አልነበረም በልጅነቴ ያጣኋት እናቴ በሀሳቤ ውስጥ እየተሰነቀረች የምተክዘው ትካዜና ዝም የምለው ዝምታ ነው።ችግሮቼን አምኜ ስለማልቀበል ይሆን እንጃ እንደዛ ነው የሚመስለኝ።
በልጅነቴ ውቃቢ ሲርቀኝ የኖርኩ ልጅ ነኝ።ዛሬም በልጅነቴ ከማውቀው ውቃቢ ጋር ተገናኝቻለው።እናቴ በልጅነቴ ያልተገባ ነገር ሳደርግ ‹ምነው ውቃቢ ራቀህ? ትለኛለች።እኔን ብቻ አይደለም ቤቱ ውስጥ ያለውን ሁሉ በዚህ ንግግሯ ነው የምትቀበለው።ግራ በገባት አንድ ቀን ላይ ራሷንም ‹ምነው አሁንስ ውቃቢ ራቀኝ ብላ ታውቃለች።ውቃቢ ምን እንደሆነ አላውቅም ብቻ በዛ የልጅነት ጭንቅላቴ ከእናቴ ንግግር ተነስቼ ውቃቢ ማለት የፈጣሪ ሌላኛው ስሙ ይመስለኝ ነበር።እና ደግሞ ለፈጣሪ የቀረበ..እምነት የሚጣልበት ሌላ ሀይል ይመስለኛል።ከእናቴ ንግግር ተነስቼ ሁለት አምላክ ያለ ይመስለኝ ነበር።እናቴ አንድም ቀን ‹ምነው አግዚአብሄር ራቀህ..ወይም ደግሞ ምነው መላኩ ራቀህ ብላኝ አታውቅም።እንከኖቼ ሁሉ ከማላውቀው ውቃቢ ጋር የተያያዙ ነበሩ።በዚህም ሁለት አምላክ እንዳለ ይሰማኝ ነበር።ዛሬም ያልተገባ ነገር ሳደርግ ራሴን ‹ምነው ውቃቢ ራቀኝ እላለው..ውቃቢ ምን እንደሆነ ግን አላውቅም።
ውቃቢ ርቆኛል..በትካዜዬ ውስጥ ወደማላውቀው ቦታ ሄጄ በማላውቃት ሴት የተፈጠረ ውቃቢ።እናቴ ልክ ነበረች? ብቻ አላውቅም የማላውቀው ውቃቢ እንደራቀኝ ግን እርግጠኛ ነበርኩ።ሰው እንዴት ለምን እንደተሳቀ በማያውቀው ሳቅ ይረታል? ሰው እንዴት ለአንዴ አይቷት ዳግመኛ በማያገኛት ነፍስ ታሪኩን ያበላሻል? ሰው እንዴት የልጅነት ጠዋቱን በከሰዐት አመሻሹ ይሸሸጋል? ራሴን እንዲህ እጠይቃለው።እውነትም ውቃቢ ርቆኛል።ዳዴ ባልኩበት ጠዋቴ ላይ ያገኘኋትን ሚስቴን ምኑንም በማላውቀው ከሰዐቴ ላይ ማሳዘኔ ከውቃቢ መራቅ በላይ እንደሆነ ደረስኩበት ቢሆንም ግን ሳቂታዋን ሴት መርሳት አልቻልኩም።
ህይወት የፈታይ ቀሰም ናት..ፈትል የተጠመጠመባትና የሚጠመጠምባት።እናም የምንኖረው በህይወት ቀሰም ላይ ለመጠምጠምና የተጠመጠመን ለመፍታት ነው።ሳናውቃቸው የሚመጡ መጥተውም የማይደገሙ የህይወት አንድ ጊዜዎች አሉ።ልክ ሳቂታዋን ሴት እንዳየሁበት ደግመን የማንስቅባቸውና ደግመን የማንተክዝባቸው አንድ ጊዜዎች።አለም ላይ ምን ይደገምልህ ቢባል ያቺን እሷን ያየሁባትን ቅጽበት እል ነበር። ምን ይናፍቅሀል? ላለኝ እሷን ያየሁባትን አፍታ ስል ደግሜ ደጋግሜ የምመልሰው መልስ ነበረኝ።አይኖቼ ሰላሳ ስምንት አመት ሲያስተውሉ የእሷን መሳይ ውበት አላስተዋሉም ነበር።አእምሮዬ ለአርባ አመት ለቀረበ ዘመን ሲተክዝ የእሷን መሳይ ትካዜ አላስተናገደም ነበር።የእሷን መሳይ መገረም አልጎበኘውም ነበር።
በዛች እንደ ሀምሌ ሰማይ በጠየመች ሴት መልክ የሚስቴ ቀይ ዳማ መልክ አስጠላኝ።በከለሯ እንዳልጎመጀሁ ሚስቴ ጠይም እንድትሆንልኝ መሻት ጀመርኩ።በመልካሟ ሚስቴ ላይ ሸፈትኩ።ጨከንኩባት።ምን ያክል ራስ ወዳድ እንደሆንኩ የተሰማኝ..ከምንምነት አንስታ ሰው ያደረገችኝን መልካሟን ሚስቴን ምኗንም በማላውቃት ሴት ለመቀየር የተነሳሁ ቀን ነበር።እንደዛም ሆኖ አልተጸጸትኩም..በትካዜዬ ውስጥ ይያት ብዙ ቀን ወደ ጠይሟ ሴት ሰፈር ሄድኩ…ጭራሽ ያልነበረችን ሴት ፍለጋ።ውቃቢ ርቆኝ የለ?
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/ 2015 ዓ.ም