የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ‹‹ማዕድን አዲስ የንጋት ተስፋ ለክልላችን›› በሚል መሪ ቃል ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በባህርዳር ከተማ በቅርቡ የማዕድን ኢንቨስትመንት ልማት ንቅናቄ አካሂዷል። በንቅናቄውም በተለያየ በማዕድን ልማት ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ተሳትፈዋል። የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከ ዑማና የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለን ጨምሮ ዘርፉን የሚመሩ አካለት ተገኝተውበታል፡ በኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝና በሰሜን ኢትዮጵያ በተከሰተውና አሸባሪው ሕወሓት በአማራ ክልል ላይ በፈጸመው ወረራ ምክንያት ይህን መሰል መድረኮችና ንቅናቄዎች ረዘም ላሉ ጊዜያት ሳይካሄዱ ቆይተዋል፤ ይህም ዘርፉ ይበልጥ እንዲቀዛቀዝ ምክንያቶ ሆኖ ቆይቷል።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተካሄደው ጦርነት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከዘርፉ ተጠቃሚ የነበረውን፣ ለአገር ኢኮኖሚ እድገት የበኩሉን አስተዋጽኦ በማበርከት ሚና በነበረው የማዕድን ዘርፍ እንቅስቃሴ ላይ ያሳደረው ጫና ከፍተኛ ነው። በተለይ ደግሞ በአማራ ክልል ዋና ዋና የሚባሉ የማዕድን ሀብቶች መገኛ ስፍራዎች በጦርነት ቀጠና ውስጥ መሆናቸው ችግሩን የከፋ አድርጎታል።
ይህን የተቀዛቀዘውን የማዕድን ልማት በማነቃቃት እንደ አገር በተለያየ ዘርፍ በመንቀሳቀስ ጠንካራ ኢኮኖሚ በመገንባት የማትበገር ኢትዮጵያን ለመፍጠር እየተደረገ ባለው ጥረት አገሪቱ ያላትን እምቅ የማዕድን ሀብት እንዲህ ባሉ የንቅናቄ መድረኮች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ይገባል። መድረኩ በዘርፉ በመሥራት ላይ የሚገኙትን ለማበረታታት አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችንም ለመሳብ አማራጭ መፍትሄም ነው።
በማዕድን ኢንቨስትመንት ልማት ንቅናቄ መድረኩ ላይ ለኢንዱስትሪና ለግንባታው ዘርፍ እንዲሁም ለጌጣጌጥ የሚውሉ የማዕድን አይነቶች ለእይታና ለአዳዲስ ኢንቨስትመንት መሳቢያ ቀርበዋል፤ የውይይት መድረክም ባካተተው በዚህ መርሀ ግብር ላይ ዘርፉ በአገር የኢኮኖሚ እድገት ላይ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ የሚረዱ አስተያየቶች ተንሸራሽረውበታል። በዚህም በዘርፉ የተከናወኑ በጎ ሥራዎችና በክፍተት የተለያዩ ሀሳቦች ተነስተዋል።
ከተነሱት ሀሳቦች መካከል በህገወጥ ማዕድን አዘዋዋሪዎች የሚፈፀመው የግብይት ችግር ዛሬም የዘርፉ ማነቆ ሆኖ መቀጠሉን የሚያመለክተው አንዱ ሲሆን፣ የቁጥጥርና ክትትል መላላት ለችግሩ ሥር መስደድ ምክንያት መሆኑም ተጠቁሟል።
በክልሉ ከሚገኘው፣ በዋጋው ውድነትም ሆነ ስማቸው በስፋት ከሚነሳው የከበሩ ማዕድናት መካከል የኦፓል ማዕድን ይጠቀሳል። የኦፓል ማዕድን ኢትዮጵያ ውስጥ በአማራ ክልል በተለይ ደላንታ ወረዳ ውስጥ በስፋት ይገኛል። የአካባቢውም መለያ ጭምር ሆኗል።
በመድረኩ ስለዚህ የኦፓል ማእድን ያነሱት የደላንታ ወረዳ ነዋሪ ገቢ በማስገኘት በአገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ ላቅ ያለ ሚና ሊኖረው የሚችለው የኦፓል ማዕድን በአካባቢያቸው ቢኖርም ማዕድኑ እንኳን የአገር ኢኮኖሚን ሊያሳድግ ቀርቶ በቅርበት የሚኖረውንም ማህበረሰብ ኑሮ እየለወጠ አይደለም ሲሉ በቁጭት አስገንዝበዋል። ለዚህም ምክንያቱ በህገወጥ ማዕድን አዘዋዋሪዎች የሚፈፀመው ግብይት፣ ህገወጥነትን ለመከላከልም ጠንካራ የሆነ የአሰራር ሥርአት አለመዘርጋት መሆኑን ይጠቅሳሉ።
በግለሰቡና በሌሎች የመድረኩ ተሳታፊዎች በተመሳሳይ የተነሳው ቅሬታ፣ ቁጭትና ተቆርቋሪነት የተለመደ ነው። በህገወጥ ተግባር ላይ ለተሰማሩት ማበረታቸው የተደረገላቸው እስኪመስል ድረስ ነው ችግሩ የዘለቀው።
ህይወታቸውን እየሰጡ ከአፈር ጋር ታግለው የሚያለሙ ግለሰቦችና ማህበራትን ቅሬታ ለምን መፍታት አልተቻለም ? የሚለው ዛሬም ድረስ የመወያያ አጀንዳ ሆኖ መቀጠሉን በንቅናቄ መድረኩ የቀረቡ አስተያየቶች ማሳያ ናቸው።
በመድረኩ ተሳታፊዎች ስለተነሱት ሀሳቦችና አጠቃላይ የንቅናቄ መርሃግብሩን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡን የአማራ ክልል ማዕድን ሀብት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሌ አበበ፤ በመድረኩ ኦፓል ማዕድን በህገወጥ መንገድ ከአገር እየወጣ ነው። ይህንንም እያደረጉ ያሉት በዘርፉ የተሰማሩ ቻይናውያንና ህንዳውያን ናቸው። ይህም የሆነው መንግሥት ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ሳይሰጥ በመቅረቱ ነው። በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል? የሚል ጥያቄና አስተያየት እንዲሁም ከቀረጥ ነጻ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ፣ ከመሰረተ ልማት ማሟላት ጋር የሚያያዙ ሌሎች ልማቱን ሊያበረታቱ የሚችሉ ሀሳቦች መነሳታቸውን ይጠቅሳሉ።
አቶ ኃይሌ እንዳሉት፣ የተነሱት አስተያየቶች አግባብነት አላቸው። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ኦፓል ማዕድን በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚታወቅ (ብራንድ) ነው። ሆኖም ግን ዘርፉ ለህገወጥ ተጋላጭ መሆኑ የአገርን ጥቅም አሳጥቷል።
ባለፈው በጀት ዓመት ክልሉ ከኦፓል ልማት ወደ ሰባት ሚሊየን ዶላር ገቢ አስገኝቷል። በክልሉ ከሚገኘው የማእድን ሀብት ክምችት መጠን አኳያ ከዚህም በላይ ገቢ ማስገኘት ይጠበቃል። እንዲህ ያለውን ክፍተት ለመሙላት እንደሚገባ በክልልም በአገር ደረጃም ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው።
ዘርፉ በመዋቅር እንዲታገዝ ማድረግ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ከተደረጉ ጥረቶች መካከል ይጠቀሳል። ወረዳዎች በቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርጉ የአሰራር ሥርአት ተዘርግቷል። ሥርአቱ ህገወጥነትን ለመከላከል አንዱ መፍትሄ ተደርጎ ይወሰዳል። በዞን፣በወረዳ በክልል ደረጃ በየመዋቅሩ ክትትልና ቁጥጥር የሚያደረግ የፀጥታ ኃይልን ያሳተፈ ግብረኃይል ተቋቁሟል። ግብረ ኃይሉን ማጠናከር ያስፈልጋል። በተጨማሪም በተመረጡ ወረዳዎች የማዕድን መገበያያ ማእከሎች መኖር አለባቸው። ይህንንም ተፈጻሚ ለማድረግም እንቅስቃሴ ተጀምሯል።
የንቅናቄ መርሃግብሩ የወደፊት ስኬቶችን ታሳቢ ባደረገ ኢንቨስትመንትን ማጠናከር እንዲሁም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከፈተውን ጦርነት ከመመከት ጎን ለጎን የልማት ሥራውን ማጠናከርን ታሳቢ ያደረገ ነው። በግብርናው እና በሌሎችም የልማት ዘርፎች እንደ አገር ስኬት ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚደረገው ሁሉ የማዕድን ልማቱም በክፍለ ኢኮኖሚው ላይ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት በተመሳሳይ በትኩረት እንዲሰራ ባለድርሻውን በማነቃቃት እየተሰራ ነው።
በክልሉ ስለሚገኙ እምቅ የማዕድን ሀብቶች፣ ዘርፉ ጥቅም ላይ ቢውል ሊያስገኝ ስለሚችለው ጠቀሜታ ግንዛቤ መፍጠር፣ በዘርፉ ላይ ስለሚስተዋሉ ተግዳሮቶችና ስላለው ምቹ ሁኔታ እንዲሁም ተግዳሮቶችን እንዴት መቅረፍ እንደሚቻልና በጎ ጎኑን ለማጎልበት ደግሞ ወደፊት መከናወን ስላለባቸው ተግባራት የተዳሰሰበት መርሃግብር መሆኑን ሃላፊው አብራርተዋል።
በክልሉ ለኢንዱስትሪ፣ ለግንባታና ለጌጣጌጥ ግብአት የሚውሉ በአምስት ዘርፍ የተከፈሉ 40 የሚደርሱ የማዕድን አይነቶች በጥናት ተለይተዋል የሚሉት የቢሮ ሃላፊው፣ከነዚህ ውስጥም ለአብነት ከፍተኛ ክምችት ያለው ለመኪና ባትሪ ግብአት የሚውል ሊቲየም የተባለ ማዕድን በወሎ አካባቢ እንደሚገኝ ጠቁመዋል። አንድ ቶን ሊቲየም ጥሬ ማዕድን አሁን ባለው ዓለምአቀፍ ገበያ 17ሺ ዶላር ዋጋ አለው ሲሉም ነው ያብራሩት።
ለአውሮፕላን መስሪያ የሚውል ኮባልት የተባለ ማዕድንም በክልሉ አንደሚገኝም አስታውቀው፣ አንድ ቶን ኮባልት ጥሬ ማዕድን 51ሺ ዶላር ይሸጣል ብለዋል። እንዲህ ለተለያየ ግብአት የሚውል ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያለው ማእድን እንዳለም ነው የጠቀሱት። በዘርፉ ያለውን ዓለምአቀፍና የአገር ውስጥ የገበያ ሁኔታ እንዲሁም የማዕድን መገኛዎችን አለመገንዘብ እንደሚስተዋልም ይጠቅሳሉ።
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ የንቅናቄ መርሃግብሩ እንዲህ ያሉ ክፍተቶችን ለመቅረፍ ከማስቻሉ በተጨማሪ በክልሉ የሚገኙ ማዕድናትን አይነትና የሚገኙባቸውን አካባቢዎች በማስተዋወቅ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ጥረት የተደረገበት ነው። ኤግዚቢሽንና ውይይትን በጋራ በማቀናጀት የተካሄደው የንቅናቄ መድረክ በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ከመዳሰሱ በተጨማሪ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት የተመሰገነበትና ቀጣይነት እንዲኖረው መልእክት የተላለፈበት በመሆኑ ዓላማውን ያሳካ ሆኖ ተገኝቷል።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል በተካሄደው ጦርነት አንዳንድ የክልሉ አካባቢዎች በጦርነት ቀጣና ውስጥ መገኘታቸው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በዘርፉ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ አይቀርም። ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ታሳቢ ባደረገው ንቅናቄ ላይ የተጽዕኖው ስጋት በተመሳሳይ ይኖር እንደሆን አቶ ኃይሌ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፤ አብዛኞቹ የማዕድን መገኛዎች ከጦርነት ቀጠና ውጭ በመሆናቸው ስጋት አይሆንም ብለዋል። ለአብነት የሲሚንቶ ፋብሪካ መገንባት የሚፈልግ ባለሀብት አባይ ሸለቆ ላይ፣ ድንጋይ ከሰል ላይ መሰማራት የሚፈልግ ጭልጋ፣ አምባሰል፣ ደብረኤልያስ፣ አንኮበር አካባቢዎች፣ የወርቅ ማዕድን ደግሞ ወበርማ አካባቢ ይገኛሉ።
እነዚህ አካባቢዎች በንቅናቄ መድረኩ ላይ በመጠቆማቸው ከመድረኩ ተሳታፊዎች ብዙዎች ፍላጎት አሳይተዋል። በተለይ በድንጋይ ከሰል ልማት ላይ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ቀርበዋል። ጭልጋ አካባቢ ወደ ሶስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊየን ቶን የሚሆን የድንጋይ ከሰል ክምችት እንደሚገኝ በጥናት ተለይቷል። በድንጋይ ከሰል ልማት ላይ ብዛት ላላቸው አልሚዎች ፍቃድ የተሰጠ ሲሆን፣ ከነዚህም አምባሰል አካባቢ በአምስት መቶ ስልሳ አምስት ሚሊየን ዶላር ወጭ ግንባታ ለማካሄድ አንድ አልሚ በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።
በአገር ውስጥ ባለ ጥሬ ዕቃ በመጠቀም ከውጭ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚገባውን የድንጋይ ከሰል መተካት እንደሚገባ በመንግሥት የተያዘው አቅጣጫ በተለያየ የማዕድን ዘርፍ የተሰማራውን ያበረታታል ያሉት አቶ ኃይሌ፤ ለግንባታ ዘርፍና ለሲሚንቶ አምራች ኢንዱስትሪዎች ግብአት በሚውለው የድንጋይ ከሰል ልማት ላይ የተጀመረውን እንቅስቃሴም ለአብነት አንስተዋል።
የባለሙያም ሆነ የቢሮ አደረጃጀት የማዕድን ልማቱ በሚከናወንባቸው ገጠራማው አካባቢዎች ጠንካራ መሆን ሲገባው ምቹ ሁኔታ የተፈጠረው ሥራውን ለሚቆጣጠረው ከፍተኛ አመራሩ ነው በሚል በአንዳንድ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ስለሚቀርቡ ትችቶች የተጠየቁት አቶ ኃይሌ በሰጡት ምላሽ ‹‹በማዕድን ዘርፍ ላይ ይስተዋሉ የነበሩ ክፍተቶች ከፖሊሲ እንደሚጀምሩ ይናገራሉ። ይህ ደግሞ ለዘርፉ ያለው አመለካከት ዝቅ እንዲል አድርጎታል ነው የሚሉት። እሳቸው እንዳሉት፤ ስራው በፖሊሲ ካልታገዘ ተቋም መገንባት አይቻልም።ለአብነትም የአማራ ክልልን ማንሳት ይቻላል። ዘርፉ አንዴ በግብርና ሌላ ጊዜ ደግሞ ውሃን በተመለከተ በሚመራው አካልና በሌላም ተቋም ሥር እንዲሰራ ሲደረግ ነው የቆየው። ዞንና ወረዳ ላይ ደግሞ መዋቅር የለውም። ማዕድን የብልጽግና መንገዳችን ነው ብሎ ከማሰብ ይልቅ ማዕድንን የግጭትና የፀብ መነሻ አድርጎ የመውሰዱ ሁኔታ ነበር ጎልቶ ይታያል። በዚህ የተነሳ ከላይ እስከታች ባለው አመራር ትኩረት አላገኘም።
አሁን ላይ ግን አሰራሩ ተለውጧል፤ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ሥራዎችና አደረጃጀቶች መለወጣቸውን፣ ክልሉ ማዕድን ኤጀንሲ የነበረው በቢሮ ደረጃ በማደራጀት የካቢኔ መዋቅር ውስጥ እንዲገባ ማድረጉን፣ ዞኖች ላይም በተመሳሳይ የካቢኔ አካል በማድረግ ወደ መምሪያ መቀየሩን፣ ወረዳ ላይ ደግሞ በተመረጡ ወረዳዎች የማዕድን ጽህፈት ቤት ሆነው እንዲያገለግሉ በማደራጀት በትኩረት እየተሰራ ነው ሲሉ አስረድተዋል።
አቶ ኃይሌ በአዲስ አደረጃጀት የተጀመረውን እንቅስቃሴ በማጠናከር ውጤታማ ለመሆን ያልተቋረጠ ሥራ ይሰራል ብለዋል። የንቅናቄ መድረኩም በተለያየ ይዘት የሚቀጥል መሆኑንና በአገር ደረጃ ከህዳር አንድ ጀምሮ የሚካሄደውን ዓለምአቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ መሠረት በማድረግ በባህርዳር ከተማ በተመሳሳይ ከህዳር 10 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።
በማዕድን ኢንቨሰትመንት ንቅናቄ መድረኩ ላይ የተገኙት የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ዑማ፤ ‹‹ኢትዮጵያ በማዕድን ዘርፍ ልታድግና ልትበለጽግ የምትችለው በአገሪቱ ያለው ማዕድን የኢትዮጵያ ነው ብለን ስናምን ነው››ሲሉ አስገንዝበዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው፤ የአሰራር ማነቆዎችን በመፍታት ለማዕድን ልማቱ መፋጠን ክልሉ የሚችለውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል። በክልሉ ያለውን የማዕድን ሀብት ወደ ልማት ለመቀየር ባለሀብቶች መዋለነዋያቸውን በዘርፉ ላይ እንዲያውሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 25/ 2015 ዓ.ም