ወጣት ብርሃን ፋንታሁን ይባላል። የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ነው። ጥቅምት 24ን ሲያስታውሰው ቀድሞ እንባ ይቀድመዋል። ምክንያቱም ይህ ጊዜ ዘግናኝና ግፍ የበዛበት ቀን ነው። እንደ ኢትዮጵያዊነት ብቻ ሳይሆን እንደሰውም ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰብ የማይገባው መሆኑን ያነሳል። ተግባሩ በምን አማርኛ መግለጽ እንዳለበትም ግራ ይገባዋል። ‹‹አይደለም የአገር መከታ የሆነ ወታደር ጠላት እንኳን በተኛበት አይታረድም›› ፤ አሸባሪው የከወነው ተግባር ግን ጀግንነት አይሉ ጅልነት በምን መልኩ እንደሚፈረጅ የማይታወቅ ነው። ጀግና የሆነ ሰው ጀግንነቱን ማሳየት ያለበት ሰው አይቶት ፀሐይ ሞቆት ነበር። እርሱ ግን ሰነፍና ተሸናፊ ስለሆነ መከላከያውን የደከመ አዕምሮውን ለማሳረፍ በተኛበት የግፍ ግፉን ፈጽሞበታል።
አሸባሪው ሕወሓት በምንም መልኩ ማሸነፍን እንደማይቀናጅ ስለሚረዳ ስልታዊ የሚባል ነገርን አያውቅም። ፊት ለፊት መጋፈጥንም አይደፍርም። በዚህም በውሸት ፕሮፓጋንዳ ሕዝብን ያሸብራል፤ በጅምላም ይጨፈጭፋል። ይህ ተግባሩ ደግሞ በመከላከያው የጀመረው ነው። ቢያውቀው ኖሮ መከላከያ ለሰዎች ነጻነት ሲል ተራራና ሸንተረሩ፤ ቁሩና ሐሩሩ የሚፈራረቅበት ነው። ለሕይወቱ ሳይሳሳ ቅድሚያ አገሬ ትኑር የሚል ነበር። ሆኖም የአገር ክብር የማይገባው ስለሆነ የጭካኔን ጥግ በእርሱ ላይ አድርጓል።
አሸባሪው ሕወሓት ሁሌ እየሰራው ያለው ተግባር ተመሳሳይ ነው። ይህም ሁለት ነገር ሲሆን፤ የመጀመሪያው አገርን ማጥፋት ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሕዝብን መጨረስ ነው። በዚህ ደግሞ የውጪ አካላት በተከታታይ ሲደግፉት ይታያል። ምክንያቱም የአገርን ውድመት ይፈልጋሉና። ስለሆነም እንደህዝብ መደረግ ያለበት አንድነትን በማጠንከር ያሰበውን ነገር እንዳይሳካለት ማድረግ ነው። ምክንያቱም እርሱ ሁሌ መልካም ነገር ቢደረግለትም ይቅርታና ሰላምን አይወድምና ከምድረገጽ ማጥፋቱ ላይ መስራት ያስፈልጋል። እድል እየተሰጠው ያልተማረን ሰላም ጠል አካል ተንከባክቦ ማኖር ትርፉ ኪሳራ እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልምና እንደ አገር ይህንን አስቦ መስራት ተገቢ ነው።
ሕወሓት በሰራው ሴራና በአደረገው ተግባር መተማመንን ጭምር ነጥቋል። ምክንያቱም ሲያገለግለው የነበረውን ከማረድ በላይ ክህደት የለም። አብሮ አደግን፤ ቤተሰብን ማረድ ደግሞ ነገ አምኖ አብሮ መራመድን በምንም መልኩ ሊያመጣ አይችልም። ስለዚህም እርሱ የነጠቀንን እምነት እኛ መገንባት ላይ መረባረብ አለብን።
‹‹ጥቃቱ ክህደት አንጂ ጀግንነት አይደለም›› – ወጣት ፍጹም ዓለሙ
ወጣት ፍጹም ዓለሙ የጥቅምት ሀያ አራቱን የሰሜን ዕዝ ጥቃት ዛሬም ድረስ በቁጭት ያስበዋል። ህዝብ የሚጠብቅ፣ ለአገር ደጀንና መከታ በሆነ ሠራዊት ላይ ግፍ መፈጸሙ ዛሬም ድረስ እንደሚያሳዝነው የሚገልጸው በተለየ ስሜት ነው።
‹‹የዛሬ ሁለት ዓመት የጥቅምት ሀያ አራትን ጥቃት የሰማሁት በድንገት ነበር። በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ የተፈጸመው ግፍና በደል እንደ አንድ ወጣት ኢትዮጵያዊ በእጅጉ አሳዝኖኛል። በወቅቱ እውነቱን በተረዳሁ ጊዜም ስሜቱን የተቀበልኩት ከዕንባ ጋር ነበር። በጣም የሚገርመው ይህ ክደት የተፈጸመው በራስ ወገን እጅ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ ክፋትን፣ ክህደትን ያመለክታል።
የመከላከያ ሰራዊታችን የህዝብና የአገር ደጀን ነው። በሰራዊቱ መከታነት ድንበር ተከብሮ ህዝብ ሰላም ውሎ ያድራል። ይህን ታላቅ መስዋዕትነት በሚፈጽም ሰራዊት ላይ ያልታሰበ ጥቃት መፈጸም ደግሞ ጀግና አያሰኝም።
አገራችን ኢትዮጵያ ከጥንት አስከ ዛሬ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ኖራለች። ዛሬም ይህ ታሪካዊ ተጋድሎ ከቆራጥ ልጆቿ ጋር እንደዘለቀ ነው። አሁንም በጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን ደጀንነት እንኮራለን። በሰራዊታችን የጀግንነት ውሎ የአገራችን ሉዓላዊነት ተከብሮ ይኖራል።
በእኔ ዕምነት ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ባለበት በቆመበት ሙያ ለአገሩ ከልብ ካገለገለ እንደ መከላከያ ሰራዊት ዘብ እንደቆመ ይቆጠራል። ሁላችንም ባለን አቅም፣ በያዝነው ችሎታ ለሰራዊታችን አጋርነታችንን ልናሳይ ይገባል። ሁሌም ጀግንነት ታሪካችን ነው። ድል ማድረግ ደግሞ ልምዳችን ነው ብሏል።
‹‹የመከላከያ ሰራዊቱ መከዳት የአገር መከዳት ነው›› – ወጣት ፋሲካ ታደለ
ወጣት ፋሲካ ታደለ ጥቅምት 24ትን በተለየ ሁኔታ ታስታውሰዋለች። በሁለት መልኩ ከፍላም ታብራራዋለች። የመጀመሪያው ከአገር አንጻር ያለውን አንድምታ ሲሆን፤ መከላከያ የሌለው አገር የፈረሰ አገር ነው። ስለዚህም አሸባሪው ሕወሓት ሲሰራ የቆየው የፈረሰች አገር እንድትኖረን ነው። ያንን ለማድረግ ደግሞ ሲሰሩ ቆይተው እፎይ ለማለት የተኙትን ወታደሮች በግፍ ጨፍጭፏል። ሁለተኛው እንደሴትነት የሚነሳው ተግባር ሲሆን፤ ሴቶች ላይ ያደረሱት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በዓለም ላይ ጭምር ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ነው።
አገር ለመምራት ሞራል ያስፈልጋል፤ ሕዝብም አመኔታ ሊጣልበት ይገባል። ነገር ግን እነርሱ ሁለቱንም ሳይዙ አገር ካልመራን በሚል ተልካሻ ምክንያት ዛሬ ድረስ በጦርነት ውስጥ እንድንቆይ ፈርደውብናል። ከዚህ አንጻርም የእነርሱ ፍላጎት ግላዊ ጥቅምና ገንዘብ ነው ብዬ እንዳምን አድርጎኛል።
አሸባሪው ሕወሓትና መከላከያ በእርሱ ውስጥ ሕዝብን ሲያገለግሉ የቆዩ ቢሆኑም ሁለቱ የሥራም፤ የወዳጅነትም፤ የቅርበትም ትስስር ነበራቸው። እንደውም የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ነበሩ። ምክንያቱም ሕወሓት መሪ ድርጅት ነበር። ስለዚህም በእርሱ አመራር ውስጥ ሆነው ለአገር ያልሰሩት ነገር የለም። ነገር ግን ‹‹በአጎረስኩ እጄን ተነከስኩ›› ሆነ ነገሩ። በጓደኛ፤ በቅርብ ወዳጅ መከዳት ምን አይነት ስሜት እንዳለው ሁሉም ያውቀዋል። ይህ ነውም በመከላከያና በሕወሓት መካከል የሆነው። ስለዚህም አሸባሪው ሕወሓት እምነትንም እውነትንም የቀበረ ተግባር ፈጽሟል ብንል ማጋነን አይሆንም።
ሕወሓት ትናንትም የራሱ አይደለም አሁንም የራሱ አይደለም። ነገም ራሱን ሆኖ አገር የሚመራ አይሆንም። ይህ ደግሞ የሚመጣው የሌላ እስትንፋስ ሲኮን ነው። ተላላኪና የተባለውን የሚያደርግ በመሆኑ ሁሌ ጦርነትን እንጂ ሌላ አይፈልግም። ለዚህም ማሳያው አገርን ከድቶ፤ መከላከያን ወግቶ ሰላማዊ ድርድር ይደረግ ሲባል፤ ተኩስ አቁም ሲታወጅ አሻፈረኝ ብሏል። ስለሆነም የራሱን ዓላማ ያልያዘ ድርጅት ነውና እስከመጨረሻው ታግለን ልንረታው ይገባል። የአስተሳሰቡ ተከታዮችንም ቢሆን ማስቆም አለብን። ለዚህ ደግሞ አንድነታችን ወሳኝ ነው። አባቶች በዚህ ዙሪያ መስራት አለባቸው።
አሁን አሸባሪው ሕወሓት ተስፋ የቆረጠበት ጊዜ ላይ ይገኛል። ስለዚህም የመጨረሻ የሚለውን የጭካኔ ስራ መስራቱ አይቀርም። ስለሆነም መንግስትም ቆራጥ ውሳኔ ማስተላለፍ ይገባዋል። ሕዝብም እንደ ሕዝብ ማድረግ ያለበትን ያህል ማድረግ ይገባዋል።
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም‹‹ያን ክፉ ዜና በሰማሁ ጊዜ ስለአገሬ በእጅጉ አልቅሻለሁ›› -እማማ ድልድል ገብሬ
እማማ ድልድል ገብሬ ይባላሉ። የእድሜ ባለጸጋ ወይዘሮ ናቸው። እማማ ድልድል በአገራችን ላይ የተቃጣውን ጦርነት ሲያስቡ በእጅጉ ያዝናሉ። የእሳቸው ምኞትና ፍላጎት አገር ሰላም ውላ እንድታድር ሕዝብ በፍቅር እንዲኖር ነው።
‹‹ ኢትዮጵያ አገሬ ዕድሜዬን ሙሉ ጌጤ መዋቢያዬ ሆና ኖራለች። ጉልበት በነበረኝ ጊዜ ያሻኝን ሰርቼ አድሬባታለሁ። ተድሬ የተኳልኩት፤ ወልጄ ወግ ማዕረግ ያየሁት በዚህች ድንቅ ምድር ነው። በእርሷ ላይ ብዙ አግኝቻለሁ። ወድቄ ተነስቻለሁ፣ አዝኜ ስቄያለሁ። ወጣትነቴን አልፌ ከእርጅናው ዘመኔ የደረስኩትም በኢትዮጵያ ክንድ ላይ ነው።
ለእኔ ይህች ምድር ትርጉሟ ይለያል። አልባሽ አጉራሼ፣ አሳዳሪ መኖሪያዬ አገሬ ኢትዮጵያ ናት። ሰላም ውላ ባደረች ጊዜ እፎይታው ለሁላችንም ነው። ሰርተን ለመኖር፣ ተኝተን ለማደር መተማመኛ ይኖረናል። በጦርነት ፈተና ሰላም ባጣች ጊዜ ህመሙ የሁላችንም ነው። ማንኛችንም ብንሆን ያለሰላም ኑሮና ህይወት የለንም።
እውነቱን ተናገሪ ካላችሁኝ ለእኔ ኢትዮጵያ ከልብ ታሳዝነኛለች። እንደውም አንዳንዴ ምን እንደማደርጋት፣ እንዴት እንደምገልጻት ሁሉ ግራ ይገባኛል። ልብስ አይደለች እንደጨርቅ አለብሳት፣ እንደው ምን ላድርጋት? እያልኩ እጨነቃለሁ። ይህን ሁሉ የማስበው ለእሷ ካለኝ የተለየ ፍቅር ነው። ሰላሟ፣ ለሁላችንም ሰላም መሆኑን አውቃለሁ። አገራችን በቸር ውላ ማደሯ ጥቅሙ ለጋራችን ነው።
የዛሬን አያድርገውና እኔ በአገሬ ሰርቼ ተከብሪያለሁ፣ አግኝቼም ኮርቻለሁ። እጄን የሚያውቁ ሙያዬን የሚሹ ሁሉ ወደ እኔ ሲመጡ ማናት ከወዴት ናት ብለው አልነበረም። በእኔ ወጥና እንጀራ ጠላና ጠጅ ያልተዳረ፣ ያልተኳለ የለም። ይህ ሁሉ የሆነው ሰላም በመኖሩ ልዩነት ባለመፈጠሩ ነው።
አሁን ዕድሜዬ ገፍቷል። እንደቀድሞው ሮጬ ማደር፣ ሰርቶ መግባት አይሆንልኝም። ባለኝ አቅም ውዬ ለመመለስ ግን ሰላም እፈልጋለሁ። እስከዛሬ ብዙ ሰምተናል፣ ብዙ ደርሶብናል፣ ጦርነት ያላሳጣን ያልወሰደብን የለም። አሁን ይህ አይነቱ መከራ ቢበቃን ምኞቴ ነው።
አዎ! ይብቃን አገራችን ሰፊ፣ ምድራችን ወርቅ ናት። ተስማምተን፣ ተከባብረን ካደርን፣ ለሁላችንም ትበቃለች። ለሰው፣ ለአውሬና እንስሳው የምትበቃ የማትቆረቁር አገር አለችን። ልንጣላ ልንጋጭ አይገባም። ጦርነት ለማንም አይበጅም። አገር ያፈርሳል፣ ህይወት ይነጥቃል።
እኔ አገሬ ወሎ ወልድያ ነው። ከወጣትነት አስከ እርጅና የዘለቅሁት ግን በአዲስ አበባ ነው። በትውልድ ስፍራዬ ያሉ ወገኖቼ በጦርነቱ ማለቃቸውን ሰምቼ አዝኛለሁ። የዛሬ ሁለት ዓመታ በወታደሩ ላይ ሆነ የተባለውንም አውቃለሁ።
በወቅቱ ያን ክፉ ዜና በሰማሁ ጊዜ ስለአገሬ በእጅጉ አልቅሻለሁ። የጠፋው ህይወት፣ የፈሰሰው ደም ያሳዝናል። ዛሬም ስለአገሬ አብዝቼ እፀልያለሁ። የእኛ መኖር በእሷ ላይ ነውና ስለሰላሟ ፈጣሪዬን ዘወትር እማልዳለሁ።
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም