የጥቅምት 24 2ኛ ዓመትን መታሰቢያን አስመልክቶ የተሠጠ አጭር ማብራሪያ፡-
ዕለቱን የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አስበውት እንዲውሉ ይጠበቃል። በሠራዊታችን በኩል በመከላከያ ጠቅላይ መምሪያን ደረጃ በልዩ ሥነ-ሥርዓት፤ እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ የሠራዊታችን ልዩልዩ ክፍሎች አመራርና አባላት፤ ሲቪል ሰራተኞች ታስቦ ይውላል።
እንደሚታወቀው ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ/ም አሸባሪውና ክህደት የማይሰለቸው ሕወሓት ሀገር የማፍረስ ተግባሩን ይፋ ያደረገበት ዕለት ነበር። ቀድሞ ተዘጋጅቶ እና የተለያዩ ስልቶችን ተጠቅሞ፤ በተመሳሳይ ቀንና ሰዓት በሠራዊታችን በተለይም በሰሜን ዕዝ ላይ ሀገራችን ቀርቶ ለዓለም እንግዳ እና ኢ-ተገማች በሆነ መልኩ ጭፍጨፋ የተፈፀመበት ቀን ነው።
ጥቅምት 24ን ስናስብ የአሸናፊ እና ተሸናፊ ትርክትን ለመፍጠር ወይም ቂምና ጥላቻ እንዲነግስ ሳይሆን እንዲህ ዓይነት ታሪክ እንዳይደገም ትውልድ እንዲማርበት ለማድረግ ነው።
ሀገሩን ለመከላከል ብሎ ከጥንት አያት ቅድመ አያቶቹ የወረሰውን የሀገር ፍቅር ስሜት እና ጀግንነት ለማስቀጠል መስዋእት እየሆነ ከራሱ በፊት ሕዝብን አስቀድሞ ተልዕኮውን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እየተወጣ የነበር ሠራዊት ነው።
ትግራይ ክልልም በፍፁም ወታደራዊ ዲሲፕሊንና ሕዝብ አክባሪነት ከሃያ ዓመታት በላይ ተግባሩን ሲወጣ ቆይቷል። ይሁን እንጂ በመለዮው ጥላ ስር ክፉና ደጉን አብረው ያሳለፈ፤ ወገኔ፤ ጓዴ ብሎ ባመናቸው መከዳቱን፤ ደግመን ደጋግመን ስናስበው ለማመን የሚከብድ ከአዕምሮ በላይ የሆነ ቃላት የማይገልፀው ጭካኔ ነበር። ይህ ተግባር እኛ ኢትዮጵያውንን የማይመጥን መጥፎ የታሪካችን ጠባሳ ስለሆነ ዕለቱን ስናስብ ከእንደዚህ አይነት ጥፋቶች ላለመላመድና ላለመውረስ ፤ እንዲህ አይነት ጥፋት በራሱ፤ አጥፊዎችም የሚያጠፋ እንደሆነ የምንማርበት አጋጣሚ አድርጎ ማሰብ ይገባል።
የተቋማችን ሪፎርም ዋናውና ማጠንጠኛ የሆነው ነጥብ ገለልተኛና የሀገሩን ሉዓላዊነት የሚጠበው ተቋም መገንባት መቻል ነው። ይህ አቅጣጫ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ትክክል ስለሆነ ብቻ ሳይሆን በተግባር ጥቅምት 24 ገለልተኛ ያለመሆን ችግር ምን ያክል ዋጋ እንደሚያስከፍል ያሳዩን በመሆኑ ነው፤ ገለልተኛ የምንሆንበት አንዱ ከብሔርተኝነት እሳቤና ተግባር ነው። ወያኔ ከዚህ ባለመፅዳቱ ነው ሠራዊታችን ያስጨፈጨፈው። የኔ የሚለውን የብሄር ታጣቂ በዘር አነሳስቶ፤ ኮትኩቶና አሰማርቶ ሌላውን የኢትዮጵያ ሠራዊት በብሔር ሳይለይ፤ በሃይማኖት ሳይለይ፤ በፆታ፤ በእድሜ ሳይለይ በጀምላ ዘግናኙን ወንጀል የፈፀመው።
ሁለተኛው ከፖለቲካ ወገን ነፃ መሆን ነው። ይህን ስንልም አሁንም ማሳያው ጥቅምት 24 ነው። የታላቋና ታሪካዊት ሀገር ኢትዮጵያ ሠራዊት ከመሆን ይልቅ ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ወግኖ የፓርቲውን የፖለቲካ ዓላማም እንደ ሃይማኖት ቀኑና አምኖና ከዛም በላይ ሰለባ ሆኖ ከሽብር ቡድኑ ሕወሓት አስተሳሰብ ውጭ ያለውን በለመደው የፓርቲው ክህደት ሠራዊታችን ግማሹን ግብዣ ብሎ ጠርቶ የፈሪ ዱላወን ያሣረፈባቸው። ስለዚህ ከብሔር፤ ከፖለቲካ፤ ከሃይማኖት ወገንና ገለልተኛ ተቋም መገንባት አለበት ተብሎ ስራ በተጀመረ አጭር ጊዜ ውስጥ መልካም ውጤት መመዝገብ የቻለው ከጉዳታችንም ጭምር በተግባር መማር ስለቻልን ነው።
ሌላው በመከላከያ መሪ መዝሙር “ከመሞት በላይ እንሙት ደማችን ሺ ጊዜ ይፍሰስ፤ አየር አፈሯ ይባረክ ምንጊዜም ስሟ ይታደስ። “የዘመርንላት ኢትዮጵያን ከሞት በላይ ሊገሉን የሞከሩት፤ እንዴት ጥሰን አልፈን የማይሞት ታሪክ እንደሰራን፤ እንዴት ከችግር ወደ ድል መሸጋገር እንደቻልን ያሳየንበት ዕለትም ነው።
ሠራዊታችን ላይ ጠላቶቻችን ሊሳለቁ ቢያስቡም፤ ሥርዓትና የሥርዓቱ መሪዎች እንደሌላት ሀገር፤ ጠባቂ ሠራዊት እንደሌላት ሀገር፤ ከማን ጋር ነው የምንደራደረው ቢሉንም፤ ሠራዊታችን እንዲበተንና በትዕቢት እጅ እንዲሰጥ ቢጋበዙም፤ ጠቢቡ “እጅ ስጥ አለኝ ፈረንጅ፤ እጅ ተይዞ ሊወሰድ? ምን እጅ አለ የሳት ሰደድ፤ አያውቅም እንዴ ክንዴ እንደሚያነድ” ብሎ ሎሬት ፀጋየ ገ/መድን እሳት ወይ አበባ የግጥም መድብሉ ለአፄ ቴዎድሮስ መቅደላ ስንብት እንደፃፈው። እጅ ስጡ ያሉንን እብሪተኞች፤ የሠራዊታችን እጅ ቀምሰው፤ ብረት በሚያቀልጥ ክንዳችን ራሳቸው እጅ መስጠት ጀምረዋል።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በሀገር ውስጥና በውጭም ያለው በጥቅምት 24 የደረሰብንን ግፍ በአንደበታቸውም ጭምር ሲናገሩ ሰምቶ፤ ዛሬም በክብሩ ፤ በኢትዮጵያ ጉዳይ ሳይደራደር ከጎናችን ሆኖ በሁለንተናዊ ድጋፍ ላልተለየን ሕዝባችን ከፍተኛና ልባዊ ምስጋና እናቀርባለን።
እኛም እንላለን የኢትዮጵያን ሕዝብ ይዘን፤ ኢትዮጵያንና ከፈጣሪ በታች ጠባቂ ሠራዊቷን ማሸነፍ ከቶ አይቻልም።
ኢትዮጵያ በልጆቿ መስዋዕትነት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች።
የመከላከያ ሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም