በጎጥ በረት ውስጥ የተፈለፈለውና የጎሳ ጡጦ ጠብቶ ያደገው አሻባሪው ትህነግ የአራት ኪሎ ቤተ-መንግስትን በወረራ ተረክቦ በትረ-ስልጣኑን አስጠብቆ በቆየባቸው 27 አመታት ሲለው በዴሞክራሲ ስም እያላገጠ፤ ሲያሰኘው ደግሞ በኃይል እየደፈጠጠ አምርሮ የሚጣላትን አገር ሲያስተዳድር ቆይቷል።
‹‹እንዳሻዬ አዛዥ ናዛዥ እንዳልሆን ያደርጉኛል›› በሚል ስጋት ከእሱ የተለየ አመለካከትና ሃሳብ ያላቸው ወገኖች ሁሉ የተለያዩ ቀለሞችን በመቅባት፣ የፈጠራ ስም በመለጠፍና ሰበብ አስባብ በመፈለግ በቀጥታም ሆነ በረቀቀ መንገድ ሰውሯል፤ አስሯል፤ ገድሏል ፤ አስገድሏል።
ቡድኑ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ የሚፈፅመው የበደልና የግፍ ጽዋ ሞልቶ መፍሰሱን ተከትሎ፤ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች በከፈሉት መራራ መስዋትነት ሳይወድ በግድ እጁ ተቆልምሞ ከአራት ኪሎ ቤተ-መንግስት ከተባረረና መቀሌ ከመሸገ ወዲህም የቀደመ እብሪትና የጥፋት ሱሱ ሊላቀቀው አልቻለም።
በጎሰኝነት አስተሳሰብ፣ በመጥበብ ፖለቲካ የተካኑት አሻባሪዎቹ የትህነግ አመራሮች በኢትዮጵያ ህዝብ ትግል ከስልጣን ተብራው ከመሪነት ርካብ በወረዱ ማግስት ጀምሮም በዚህ ስብእናቸው ከቀደመው ዘመን በላይ ወርደው፤ ዘቅጠው ታይተዋል።
ኢትዮጵያን የሚፈልጓት እነርሱ እስከገዟትና የበላይነትን ይዘው እስከቀጠሉ ብቻ መሆኑንም በተጨባጭ አስመስክረዋል። እግሬ አውጭኝ ብለው መቀሌ ከመሸጉ ጀምሮም ለውጡን እና የለውጡን ሀይል ሲያጥላሉና ሲቃወሙ፤ የለውጡ ትሩፋት ለትግራይ ህዝብ እንዳይደረስ እንደ ጎሊያድ መንገድ ሲዘጉም ተስተውለዋል።
በለመዱት የከፋፍለህ ግዛ መርህ በጎሳዎች፣ በብሔሮችና በአጠቃላይ በህዝቡ መካከል “encouraging blood feuds“ የእርስ በርስ ጥላቻና መርዝ ሲያሰራጩ ሲያራግቡም ከርመዋል። ስለ ጦርነት እየዘመሩም አደባባይ ወጥተዋል። ኢትዮጵያን መምራት የምንችለው ‹‹እኛ›› ብቻ ነን በሚል ፍፁም ድንቁርና ኢትዮጵያ ከምታክል አገር ይልቅ እነርሱ ለምዕራባውያን ፍላጎት የተሻሉ ስለመሆናቸውን ደስኩረዋል።
የአገር ክብር ዘብ የሆነውን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ለዘመናት ከአለት አፅንቶና ከምሰሶ አበርትቶ ያቆመውን መከላከያ ሰራዊት ሳይቀር ከክብር በታች ለማውረድና ለመከፋፈል ብዙ ደክመዋል። የሐሰት ወሬ በስፋት አሰራጭተዋል። ወታደራዊ ሚስጥርን የሚጥሱ መግለጫዎችን ሳይቀር አሳልፈው በመስጠት ሀገርን ለውጭ ባዕዳን ከማጋለጥ እንደማይቆጠቡ በግልፅ አስመስክረዋል።
ይባስ ብሎ መንግሥት ለሰላም የዘረጋውን እጅ እንደሽንፈት በመቁጠር የቡድኑ አባላትና ጋሻ ጃግሬዎች የስልጣን አባዜ የሚያመጣው እብደት ‹‹ከእኛ በላይ ላሳር›› በሚል ትእቢት ተወጥረው፣ ከሁሉም በላይ ጤንነታቸውን በሚያጠያይቅ መልኩ ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የኢትዮጵያ ቀይ መስመር ተላለፉ። ፡
አገርን ዳር ድንበር ከማስጠበቅ ባሻገር ለትግራይ ህዝብ ኮቾሮአቸውን አካፍለው፣ የኮዳ ውኃቸውን ለግሰው፣ ደመወዛቸውን ለትምህርት ቤት ግንባታ ቀንሰው ለመስጠት በማይሰለቹ የሰሜን ዕዝ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት በመፈጸም የእብደትና የእብሪት ጥጋቸውን በአደባባይ ገልጸዋል።
ቀን በጠራራ ፀሐይ አንበጣ ሲያብርሩና የትግራይን አርሶ አደር ሰብል ሲያጭድ የዋሉ የሰራዊቱ አባላት እንኳን በእውን በህልማቸው እንኳን ለማሰብ ፈፅሞ በማይችሉት መልኩ ከድካም እንዳረፉና ትጥቃቸውን እንደፈቱ ምሽት ላይ ድንገት ከጀርባ ወግተዋቸዋል። ሰራዊቱ መሳሪያውን ለማንሳት፣ ለመገመትም ሆነ ለመጠራጠር እንኳን ጊዜ ባላገኘበት ፍጥነት ከውስጥና ከውጭ ጥቃት ፈጽመውበታል።
ከሀዲዎቹ የደደቢት ሽፍቶች በታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ በማይታወቅ መልኩ አመታትን አብራቸው ጦር ሜዳ የተሰለፈን፣ አብሮ የተዋደቀን፣ አብሮ የበላና የጠጣውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመክበብ እንደ ጠላት ሰቅጣጭና በጣም ዘግናኝ በሆነ መልኩ ጨፍጭፈዋል።
ኢ-ሰብአዊ የመሆናቸውን ጥግ በሚያስመሰክር መልኩ ከሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር በእጅጉ በወረደ መልኩ ከጭፍጨፋው የተረፉትን የመከላከያ ሠራዊት አባላት በሙሉ ሰብስበው የለበሱትን ወታደራዊ ሬንጀር ልብስ አስወልቀው፣ ትጥቃቸውን አስፈትተው፣ ጫማቸውን አስወልቀው ረሸነዋል። የጠላት ወታደር ላይ እንኳን ለመፈፀም በሚከብድ መልኩ ጥይት ላለማባከን በማለት አስተኝተው ከባድ ተሽከርካሪ ነድተውባቸዋል።
በዚህ የባንዳ ተግባር በርካታ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ቢጨፈጨፉና መስዋትነት ቢከፍሉም በርካቶች ‹‹ለወያኔማ እጃችንን አንሰጥም›› በሚል እጅግ በላቀ ቆራጥነትና አስደናቂ ጀግንነት ተዋግተው የጠላትን ከበባ ሰብረው መውጣት ችለዋል።
መከላከያ ሰራዊቱም በደረሰበት ክህደት ልክ ሳይሆን ሀገርን በሚያድን መልኩ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የሚያስችል ወታደራዊ ስምሪት በማድረግ የአሸባሪው ቡድን አባላት በቀበሮ ዋሻ ውስጥ ለመቀርቀር ረጅም ጊዜም አላስፈለገውም። ፍጹም በሆነ ጀግንነት የቡድኑን ሀገር የማፍረስ ተልእኮ ተቋቁሞ አስደናቂ በሆነ መልኩ አገርን ታድጓል።
የፌደራል መንግስት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የቀረበለትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ክልሉን ለቆ ሲወጣ፣ “ለውሻ ከሮጡለት፣ ለልጅ ከሳቁለት” እንደሚባለው የአሸባሪው ትህነግ አመራሮች በእነርሱ ኃይል የተገኘ ድል በማስመሰል ከተንቤን በረሃ አዋራቸውን አራግፈው መቀሌ ገብተዋል።
ለህዝብና ለአገር ደንታ የሌላቸው የሽብር ቡድኑ አመራሮች የፌደራል መንግስቱን ውሳኔን እንደ ድክመት በመመልከትና ‹‹ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲኦልም ቢሆን እንወርዳለን›› በሚል አብሪት ጦርነቱን ወደ ከትግራይ አጎራባች ክልሎች በማሻገርም አፋርና ወደ አማራው ክልል በመግባት የግፍ ተግባራቸውን ቀጥለዋል።
ጦርነቱን ገፍተው በገቡበት አጎራባች ክልሎች፣ ወጣት ሴቶች፤ ህጻናትና አዛውንቶች ጨፍጭፈዋል። ደፍረዋል። የእምነት ተቋማትን አቃጥለዋል። ለመተካት የማይቻሉ ቅርሶች ሰርቀዋል፤ አወድመዋል። በድሃ ህዝብ የተሰሩ ክሊኒኮች፤ ሆስፒታሎች ዘርፈዋል፤ አቃጥለዋል። በርካቶችን ከቀያቸው አፈናቅለዋል፤ ለረሃብ አጋልጠዋል።
የዘረፉትን ዘርፎ ወደ ትግራይ ከመውሰድ ባለፈ መውሰድ የማይችሉትን አቃጥለዋል። አርሶ አደሮች ወዛቸውን ጠብ አድርገው ያለሙትን ሰብል ዘርፈዋል። የአርሶ አደሮችን ቤት በሞርታር አረር አንድደዋል።
ትህነግውያኑ ሌላው ቀርቶ የአምልኮ ተቋማቶችን ሳይቀር አውድመዋል። አቃጥለዋል። ቤተእምነት መቅደስ ውስጥ ሳይቀር ተፀዳድተዋል። ቤተ እምነቶችን እንደ ዳንኪራ ቤት በመመልክት መጠጥ ሲጠጡና ሲደንሱም ታይተዋል።
ከሃዲው ቡድንና አባሪዎቹ ኢትዮጵያን በሁሉም አቅጣጫ በማዳከም ለማንበርከክ አስፍስፈው ለመሻታቸው ብዙ ቢታታሩም የኢትዮጵያን ስም ጠርቶ፣ ስለ ኢትዮጵያ ሰይፍ አንስቶ ተሸንፎ የማያውቀው ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችንን ክንድ ግን መቃወም አልሆነላቸውም።
በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከቤተ መንግስት ወንበር ላይ ተነስተው አገሬ ከእኔ ስልጣን፣ ክብር፣ እውቀት፣ ነፍሴ በላይ ነች በሚል ወደግንባር መዝመት ተከትሎ ይበልጥ የተነቃቁት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች፣ በአጭር ቀናት ውስጥ ወራሪውና ተስፋፊው ቡድን እንደለመዱት ድባቅ አድርገውታል።
ጠላት ለበርካታ ወራት የዘረፈውን ሀብት በመጠቀም በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ህዝብ በማስገደድ ያሰራውን ባለብዙ እርከን ኮንክሪት ምሽግ በተቀናጀ እቅድ፣ አመራርና ቴክኖሎጂ በመታገዝ በአነስተኛ መስዋዕትነት ሰባብረውታል።
የኢትዮጵያ ጀግኖች ኢትዮጵያ ከናዚስት ትህነግና ከሚመራው የሲዖል ሠራዊት ተልእኮ ለማዳን በእያንዳንዱ ግዳጅ ኢትዮጵያ የተከበረች፣ ለአሸናፊነት የተመረጠች፣ ለምስክርነት የተቀመጠች ጀግና የምትወልድ፣ ወልዳ የምታሳድግ አገር መሆኗን በተጨባጭ አስመስክረዋል። ታሪክ ሁሌም የሚዘክረው ጀብድ ፈፅመዋል።
በክህደት መንገድ ተራምዶ ከናፈቀው የአራት ኪሎ ግቢ ለመግባት የመጠው ቡድኑ ያሻውን ማድረግ ተስኖት በመጨረሻ ‹‹በማንኛውም ግዳጅ ወይም ተግባር የላቀ ውጤት›› በሚል እሴት በተገነባው፣ በየትኛውም ሁኔታ በማንኛውም የአየር ፀባይ ማንኛውም ግዳጅ በውጤት የማጠናቀቅ አንፀባራቂ ድል የማስመዝገብ አቋምና አቅም ባለው የኢትዮጵያ ሰራዊትና የቁርጥ ቀን ልጆች ተቀጥቅጦ ወደ መጣበት ተመልሷል።
ቡድኑ ዳግም ተቀጥቅጦ ወደ መጣበት መቀሌ ከፈረጠጠ ወዲህም አመራሮቹ ከህዝብና ከሀገር ሰላም እና ደህንነት ይልቅ የራስን ምቾትና ፍላጎት በማስቀደም፣ ለሰላም የተዘረጋን እጅ በመቁረጥ ሶስተኛ ዙር ጦርነት በመክፈት ለጥፋት የማይደክም መሆኑን አስመስክሯል።
የፌደራል መንግስቱ ለኢትዮጵያ ደህንነት በተለይም ትግራይ ህዝብና ሰላም ሲል ሁሉንም ይቅር ቢለውም፣ አሸባሪው ቡድን በአንፃሩ በግፍ ያፈሰሰው ደም አስክሮት ዳግም ጦርነት ከፍቷል። አገርን እና ህዝብን መካዱን አስቀጥሏል።
ፈተና የሚፀናቸው ችግር የሚያጠነክራቸው፣ ክፉ ቀን የሚያስተሳስራቸው ኢትዮጵያዊያን የሰላም አማራጮች እንደተጠበቁ ሆነው በአሁን ወቅት በቁጣ ተነስተውና በአንድነት ቆመው የሽብር ቡድኑን በሚገባው ቋንቋ እያናገሩት ይገኛሉ።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ሕዝባዊ ሠራዊቱ (ልዩ ሀይላት፣ ፋኖ፣ ሚሊሺያ) ኢትዮጵያን ወደ ሲኦል አወርዳታለሁ ብሎ የዛተውንና የሚዳክረውን የናዚስት የሲዖል ሠራዊት ወረራ እየመከቱና ወደ ግብአተ መሬቱ እየወሰዱት ይገኛሉ።
ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችንም በእያንዳንዱ ግዳጅ በሰከነ መልኩ በሚፈፅመው አገርን ማዳን ተልእኮ ኢትዮጵያ የነኳትን እየሰበረች፣ የደፈሯትን እያሳፈረች ከታሪክ ላይ ታሪክ እየጨመረች፣ ታሪኳን እያደመቀች፣ ስሟን እያገነነች እንድትቀጥል ፍቅርና ውድ ሕይወቱን እየሰጠ ይገኛል።
የሰላም በሮች እንደተከፈቱ ሆነው በአሁን ወቅት ጀግኖች በደም ቀለም ታሪካቸውን እየፃፉ ነው። ጠላትን እየደመሰሱ ወደፊት እየገሰገሱ ነው። የመጨረሻው የድል ቀን ተቃርቧል። የጠላት መዳፈኛ መቃብሩ ተቆፍሯል። አፈር የሚመልሱበት ኢትዮጵያዊያንም ዙሪያ ገባውን ተዘጋጅተዋል። የሚያቆማቸው ማሸነፍ ብቻ ነው። የጠላት የማምለጫ ተስፋው አልቋል። በሮች በሁሉም በኩል ዝግ ናቸው።
ድል ለጀግናው ሠራዊታችን !
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም