ከቅርብ ወራት ወዲህ ወፈፌው ይልቃል እንደዚህ ቀደሙ በየቀኑ ሌሊት ሌሊት እየተነሳ መጮሁን አቁሟል። ወትሮ ሰማይ የአህያ ሆድ ሲመስል መጮህ የጀመረ የሚያቆመው ማታ የሌሊት ወፎች ከዋሻቸው ወጥተው ውር ውር ማለት ሲጀምሩ ነበር። አሁን ላይ ግን ዋርካው ስር ከሚገኘው ድንጋይ ላይ ቆሞ የሚጮኸው ለሰፋራችን ሰዎች መልዕክት ለማስተላለፍ ሲፈልግ ብቻ ነው። ጩኸቱም እንደዚህ ቀደሙ በወፈፌነት የሚታለፍ ባለመሆኑ፤ ሁሉም በምስራቋ ኮከብ የሚገኙ የእድራችን እና የሰፈራችን ሰዎች በጥሞና እየተከታተሉ በጭብጨባ ያጅቡታል።
ወፈፌው ይልቃል አዲሴ የዛሬውን ንግግሩን የጀመረው « በድሎ ካሱኝ ፣ እሾህ ይዞ እጄን ዳብሱኝ ፤ ምን የሚሉት እብሪት ነው? » በማለት ነበር። ነገር ግን የይልቃል አዲሴን ውስጠ ወይራ ንግግር የተረዳው አብሿሙ ክንፈ ጉደታ ሁሉም የሰፈራቸው ሰው አባባሉን እንዲረዳው መብራራት እንዳለበት ጠየቀ።
ወፈፌው ይልቃል አዲሴም በአብሿሙ ክንፈ ጉደታ ንግግር ተስማምቶ የተናገረውን አባባል በምሳሌ ለማስረዳት አስቦ ንግግሩን እንዲህ ሲል ቀጠለ…. የአንድን ገበሬ በሬ ጎረቤቱ ይሰርቀዋል። በሬውን የሰረቀው ጎረቤትም የጠፋውን በሬ አብሮ አፈላላጊ ሆኖ ቀረበ። በሬ የጠፋበት ሰውዬም በሬውን ቢፈለግ ቢያስፈልግ በሬውን የበላው ጅብ አልጮህ ይለዋል። ከቀናት በኋላ ግን በሬውን ጎረቤቱ እንደሰረቀው ይደርስበታል። ነገር ግን ምስክር ስለሌለው ‹‹በሬዬን መልስልኝ›› ሳይል በውስጡ ስለበሬው ያወጣ ያወርድ ያዘ።
ይህ በእንዲህ እያለ አንድ ቀን ሌባው ጎረቤት በሬ የጠፋበትን ሰው «ጌታው እንደው ያ በሬ ጠፍቶ መቅረቱ ነው?» ሲል ይጠይቀዋል። በሬ የጠፋበትም ሰው ምን ቢል ጥሩ ነው? «ሌባው አብሮ እያፈላለገ እንዴት በሬው ይገኛል ብለህ ነው?» ሲል መለሰለት።
የባይደን አስተዳደር እና አንዳንድ ምዕራባውንም እኛን እርስ በርስ ካጣሉ በኋላ ራሳቸው አስታራቂ ሆነው ይመጡልሃል። የሰውዬውን በሬ ሰርቆ አብሮ እንደሚያፈልገው ሌባ ማለት ነው፤ ብሎ ይልቃል አዲሴ ንግግሩን ሳይጨርስ በሰፈራችን ተዋቂው የቅኔ መምህር የንታ (የኔታ) ፍሬው እንደሚፎክር ሰው ከተቀመጡበት ድንጋይ ላይ ተነስተው፤ የባይደን አስተዳደር እና አንዳንድ ምዕራባዊንም በምስራቋ ታላቅ ሀገር የሚገኙ እድሮችን እና ሰፈሮችን እንዲበጠበጡ እና ከእነአካቴውም እንዲጠፉ ለማድረግ የእረጅም ጊዜ እቅድ አውጥተው ሲሰሩ ኖረዋል። ለእዚህ እቅዳቸውም በሰብዓዊ እና በዴሞክራሲዊ መብቶች ሰበብ ከፍተኛ እረብጣ ገንዘብ መድበው ተመለክተናል በማለት ንግግራቸውን ጀመሩ።
ይህ የጥፋት እቅዳቸው እንዲሳካ ለእነአይተ ጭሬ ልድፋው የጥፋት እና እልቂት ተልዕኮ በመስጠት የእድራችን እና የሰፈራችንን ጠባቂ የሆነውን ቅራት በተኛበት እንዲጨፈጨፍ አይዞህ ግፋ በለው አሉ። «ለውሃቤ ዝናም፤ ማየ ከልእዎ …..ለዝናቡ ጌታ ውሃ ነሱት ወይም አባት ላም ይሰጣል ፤ ልጅ አጓት ይነሳል » እንዲሉ አባቶች፤ አይተ ጭሬ ልድፋውም ዘመዶች ስንት እና ስንት ውለታ የዋለውን ቅራት በተኛበት አረደው።
በአንዳንድ ምዕራባዊያን ግፋ በለው እየተባለ ቅራቶችን በተኙበት የጨፈጨፈው አይተ ጭሬ ልድፋው በጦርነቱ የሚያሸነፍ መስሎት «ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው» በማለት ሲፈጠር ጫካ ይዟት የገባትን እና ለዓመታት ከጫካ ወጥታ የማታውቀውን፤ በሸረሪት ድር የተወረረችውን ከበሮ የሸረሪት ድሯን እንኳን ላራግፍ ሳይል በችኮላ አስረሽ ምችው! ይል ያዘ።
የንታ ፍሬው ንግግራቸውን ቀጠሉ… በቅራታችን ላይ የፈጸሙትን አስነዋሪ ጭፍጨፋ እንደ ጀግንነት ቆጥረውት ‹‹መብረቃዊ ጥቃት›› አካሄድን ሲሉ ታበዩ። «ሕወሓት ቀሞት ውስተ እደ ልሳን …..በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ » እንዲሉ ይህም የምስራቋን ኮከብ ሙሉ ህዝብ ክፉኛ አበሳጨ። የተቆጣው ህዝብም በተላላኪው አይተ ጭሬ ልድፋው ላይ ዘመተ። መብረቃዊ በሆነ በሁለት ሳምንትም የጸረ ማጥቃት ምላሽ አይተ ጭሬ ልድፋውን በዓለም ፊት አዋረዳቸው።
በምስራቋ ኮኮብ ህዝብ እና መንግስት ጀብዱ ወዳጆቻችን ሲደሰቱ ጠላቶቻችን ደግሞ ክፉኛ ተደናገጡ። የባይደን አስተዳደር እና አንዳንድ ምዕራባዊንም አይተ ጭሬ ልድፋውን ከተቀበረበት በርሃ ለመመለስ በሰብዓዊ ድጋፍ ስም ያዙኝ ልቀቁኝ አሉ ። ለምስራቋ ኮኮብ መንግስት እና ቅራቶች እንዲሁም ህዝብ ያለስም ስም መስጠት ጀመሩ ።
በጭፍጨው ምንም እንዳልሰሩ እና የእነሱ እጅ እንደሌለበት አስመስለው በምስራቋ ኮኮብ በሚገኙ እድሮች እና ሰፈሮች ሰላም ማምጣት የሚቻለው የባይደን አስተዳደር እና አንዳንድ ምዕራባዊንም ከተሳተፉበት ብቻ ነው አሉ። ካልሆነ ግን ሰላም ማምጣት አይቻልም ። «ከምላሳችን ጸጉር ይነቀል ! » ሲሉ ተደመጡ። በሬ ሰርቆ አብሮ አፈላላጊ እንደሆነው ሌባ ማለት ይህ አይደል ?
እውነት ለመናገር ሰላም ለማምጣት በሚል አንዳንድ ምእራባዊን የገቡበት እድር እና ሰፈር ከመፍረስ ውጭ አንድም ቀን ህልውናውን ሲያስቀጥል ታይቶ አይታወቅወም። ይህ ደግሞ በተለያዩ ሃገራት የታየ ሃቅ ነው። ብለው ንግግራቸውን ጨርስው ሲቀመጡ ከታዳሚው የሞቀ ጭብጨበ ተቸራቸው።
የየንታ ፍሬው ንግግር ሲያልቅ ወፈፌው ይልቃል አዲሴ ከቆመበት ቀጥሎ ‹‹በነገራችን ላይ አንዳንድ ምዕራባዊያን የምስራቋን ታላቅ ሀገር ለማፍረስ እና ለማተራመስ ቆርጠው ከተነሱ ውለው አድረዋል። በርካታ በደሎችን ፈጽመውባታል። ሁሉንም በደሎችን መቁጠር ሊያዳግተን ይችላል። ነገር ግን የተወሰኑትን በወፍ በረር ማየቱ ሳይሻል አይቀርም።›› በማለት ጉሮሮውን እህ….እህ.. እያለ ጠራረገ ።
ሴራ አንድ፡- በአጼዎቹ ዘመን አንዱ የምስራቋ ኮኮብ ንጉስ ለጉብኝት ወደ አሜሪካ ተጋበዙ። በጉብኙቱም ንጉሱን ነጥብ ለማስጣል ተልዕኮ የተሰጣት ጋዜጠኛ በነጩ ቤተመንግስት ተዘጋጅታ ትጠባበቅ ነበር።
ንጉሱም አሜሪካ በገቡ ማግስት ለነጥብ ማስጣል የተዘጋጀችው ጋዜጠኛ ተልዕኮዋን ለማስፈጽም ንጉሱን ለቃለ መጠየቅ እንዲተባበሯት በአስተርጓሚያቸው በኩል ጠየቀች። ንጉሱም ለቃለ መጠይቁ ተባበሯት። ንጉሱ እና ጋዜጠኛዋ ቃለ ምልልስ የሚያደርጉበት ሰዓት ደርሶ ቃለ ምልልሱ ተጀመረ።
በቃለ ምልልሱ መካከል ጋዜጠኛዋ ሆነ ብላ «እርስዎ እኮ በነጩ ቤተ መንግስት የገቡ የመጀመሪያው ጥቁር መሪ ነዎት፤ በዚህ ምን ተሰማዎት? » ስትል ጠየቀቻቸው። ንጉሱም በንዴት ጡፈው «እንዴት እኔን ጥቁር ትያለሽ!? እኔ ጥቁር አይደለሁም ! የዘር ሃረጌ ከጠቢቡ ሰለሞን የሚመዘዝ የአይሁድ እንጂ !» ሲሉ መለሱ። ይች ንግግር ቀላል ልትመስለን ትችላለች። ነገር ግን በወቅቱ የአፍሪካ አባት እየተባሉ የሚሞካሹትን ንጉስን በመላ ጥቁር አፍሪካዊ እንዲወገዙ ለማድረግ ሆነ ተብሎ የተደረገ የአሜሪካኖች ወይም የምዕራባዊን ሴራ ነበር።
ሴራ ሁለት፡- ኒወዮርክ ታይምስ የተባለው ጋዜጣ ከላይ የተጠቀሱትን የምስራቋ ኮኮብ ንጉስ በአስር ዓመት ውስጥ ሁለት ጊዜ የዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሰው ብሎ መረጠ። ይህን ተከትሎ ምዕራባዊን የምስራቋን ታላቅ ሀገር ንጉስ እና ህዝቦቿን ለማጥፍት በዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ ጥናት እስከማስጠናት ድረስ ተጓዙ። የዚህን እውነታ ማረጋገጥ ከፈለጋችሁ ዘ ላየን ኦፍ ጁዳ ኢን ዘኒው ወርልድ ( THE LION OF JUDAH IN THE NEW WORLD ) የሚለውን መጽሃፍ ተመለከቱ።
ሴራ ሶስት፡- የምስራቋ ታላቅ ሀገር በሶማሊያ በተወረረችበት ሰዓት የምስራቋ ኮኮብ የጦር መሳሪያ ለመግዛት ከአሜሪካ ጋር ተስማማች። የምስራቋ ኮኮብም ለአሜሪካ ረብጣ ዶላሮችን ከፈለች። ይሁን እንጂ አሜሪካ ለጦር መሳሪያ መግዣ የተሰጣትን ረብጣ ዶላር ወደ ካዝናዋ ካስገባች በኋላ ስምምነቱን ወደ ጎን ጥላ የጦር መሳሪያውን አልሰጥም አለች። ለመሳሪያ መግዣ የተከፈላትንም ገንዘብ በልታ ቀረች።
የዚህ ሴራ ዋና ዓላማ ሶማሊያ የከባድ ጦር መሳሪያ የበላይነት እንዲኖራት በማድረግ እና የምስራቋን ኮኮብ በከባድ መሳሪያ አረር አስበልቶ ለማፈራረስ ነበር። ነገር ግን የአሜሪካ እና ምዕራባዊያን ሴራ በምስራቋ ኮከብ ህዝብ እና መንግስት እልህ አስጨራሸ ትግል ሊከሽፍ ችሏል።
ሴራ አራት፡- ሌላው ግፍ ደግሞ አንዳንድ ምዕራባውያን ለምስራቋ ታላቅ ሀገር ካንሰር የሆኑ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንደ አሜባ ተህዋሲን አብዝተው በመፈልፍል እና የብሔር ብሔረሰቦች መብት እስከመገንጠል የሚል በመርዝ የተጠቀለለ ኬክ በማብላት የምስራቋን ታላቅ ሀገር ለመበታተን አበክረው ሰርተዋል። ይህንን ለማሳካትም በነጻ የትምህርት እድል ስም የሰበሰቧቸውን የምስራቋን ታላቅ ሀገር ወጣቶች በገፍ ተጠቅመዋል።
ይህን የአንዳንድ ምዕራባውያንን ተልዕኮ የተቀበሉ የሀገራችን ልጆችም ከወጣትነት እስከ እርጅናቸው ድረስ ባሉበት ቆመው ይሄው ሀገራችን ይበጠብጧት ይዘዋል። ከእነኚህ መካከልም ኤይተ ጭሬ ልድፋው የሚመሩት የሽብር ቡድን አንዱ እና ዋነኛው ነው። ይህ ማለት ግን እነ ኤይተ ጭሬ ልድፋው የሚመሩት የሽብር ቡድን ብቻ ነው ማለት አይደለም።
በነገራችን ላይ የአይተ ጭሬ ልድፋው እና የአሜሪካ የረከሰ ጋብቻ «ሐንካስ በአግረ ዕውር ሖረ፤ ዕውርኒ በዐይነ ሐንካስ ነጸረ፤ ወበክሌሆሙ ወይንየ ተመዝበረ …አንካሰው በዕውሩ ዐይን ሄደ ዕውሩም በአናካሰው ዐይን አየ ፣ በሁለቱም አታክለቴ ተመዘበረ» የሚለው አባባል በደንብ አድርጎ የሚወክለው ይመስለኛል።
ትህነግ እና ምዕራባውያን አትክልታችንን ለመመዘበር እያቦኩ እና እያነኮሩ ያሉት አንካሳ እና እውር ሃሳብ ይዘው ነው። የሚገርመው ደግሞ ራሳቸው ገድለውን፣ ራሳቸው አጎሳቁለውን ሲያበቁ ተበድለናል ካሳ ክፈሉን ይሉናል። ብድሎ ካሱኝ፣ እሾህ ይዞ እጄን ዳብሱኝ !? ማለት ምን አይነት ትዕቢት ነው? እኛ የአባቶቻችን ልጆች ነን፤ ለባንዳዎች እና ለቀኝ ገዢዎች እጅ አንሰጥም። አታክልታችን አናስበላም።
በመጨረሻም አለ ወፈፌው ይልቃል አዲሴ …. ሰዎችን የሚገፋ እና ከእውነት በተቃራኒው የሚቆሙ ሰዎች የመጨረሻቸው መጨረሻ ውርደት እንደሚሆን አያጠራጥርም። ይሄን በአንድ በታላቋ የምስራቋ ሀገር ተረት ላሳያችሁ…
ከዕለታት አንድ ቀን አንድን ነብር አዳኞች ሊገድሉት ያሯሩጡታል። ነብሩም በጣም ይደክምና ሮጦ ማምለጥ እንደማይችል ይረዳል። በዚህ ወቅት ዙሪያውን ሲቃኝ አንድ ጉድጓድ የሚቆፍሩ ሽማግሌ ይመለከታል። ጉድጓድ ሲቆፍሩ የነበሩትን አባትም እንዲያድኑት ይማጸናቸዋል። ጉድጓድ እየቆፈሩ የነበሩት አባት ከቆዳ በተሰራ አቁማዳ (ጆንያ) ይደብቁታል።
ከተወሰኑ ደቂቃዎች በኋላም አዳኞችም ጉድጓድ የሚቆፍረው ሰው ጋር ይደርሳሉ። «አባቴ በዚህ የመጣውን ነብር አላዩም?» ሲሉም ይጠይቋቸዋል። አባትም «እየቆፈርኩ ስለነበር ቀና ብዬ አላየሁም »ሲሉ ይመልሳሉ።
አዳኞችም ሰውዬውን አምነው ነብሩን ፍለጋ ነብሩ ይሄድበታል ብለው ወደ ገመቱት አቅጣጫ ሮጡ። የአዳኞችን መራቅ የተመለከቱት አባት ነብሩን ከደበቁበት አወጥተው «አሁን አዳኞች ከዚህ ስለራቁ መሄድ ትችላለህ» ሲሉ ይነግሩታል።
ነብሩም አዛውንቱን የዋሉለትን ውለታ ከምንም ሳይቆጥር «እስካሁን እዚህ ደብቀህ ስላቆየኸኝ እርቦኛል። ስለሆነም አንተን እበላኻለሁ» ይላቸዋል።
አባትም «እንዴት እኔ ከገዳዮችህ ደብቄ ባተርፍ ልብላህ ትለኛለህ?» ሲሉ ይመልሱለታል። «የለም እዚህ በጆንያህ ለብዙ ሰዓታት ስላቆየኸኝ እርቦኛል። ስለሆነም እበላሃለሁ »ይላቸዋል።
አዛውንቱም እንስሳት ይጠሩና ይዳኙን እንጂ እንዴት ዝም ብለህ ትበላኛለህ አሉ። ነብሩም ለዳኝነት ይሻላሉ ያላቸውን የዱር እንስሳ ጠራ። ከተጠሩት ዳኞች መካከል አንዷ ቀበሮ ስትሆን ሌላኛዋ ደግሞ ጦጣ ነበረች።
ቀበሮ የተፈጠረውን ነገር አዳማጠች። ነገር ግን ትክክለኛውን ፍርድ ብትፈርድ ነበር ሊበላት ስለሆነ እስካሁን በአቁማዳዎት (በጆንያዎት) ደብቀው ስላቆዩት መበላት አለብዎት ብላ ፈረደች። አዛውንቱም በቀበሮ ፍርድ ስላልተስማሙ ወደ ሁለተኛዋ ዳኛ ጦጣ ሄዱ።
ጦጣም ነብሩ እና ሽማግሌው የተጣሉበትን ፍሬ ነገር ካዳመጠች በኋላ እኔ ፍርድ ለመስጠት ይመቸኝ ዘንድ ዛፍ ላይ መውጣት አለብኝ አለች። ሁለቱም ተሟጋቾች ተስማሙ። ጦጣም እንዴት ሆነህ ነበር ወደ አቁማዳቸው የገባኸው? ስትል ነብርን ጠየቀች። ነብርም ወደ አቆማዳው እንዴት እንደገባ ለማሳየት ወደ አቁማደው ገባ። ጦጣም ሰውዬውን አቁማደውን አፍ ይዞ ነብሩን እንዲያፍነው እና በያዙት ድሉ እንዲቀጠቅጡት ጠቆመቻቸው። አዛውንቱም የጦጣን ጥቆማ ተቀብለው ቶሎ ብለው ነብሩ ሳይወጣ የአቁማዳውን አፍ በእጃቸው ጠቅጥቀው ያዙት። በሌላኛው እጃቸው በያዙት ዱላ ደግሞ ጥሩ አድርገው ቀጠቀጡት። ነብሩም ሞተ። የግፈኞች የመጨረሻ የሚሆነውም ይሄው ነው፤ ተቀጥቅጦ መሞት።
«የሽብር ቡድኑ እና የጥፍት አጋሮቹም የመጨረሻ እጣ ፋንታቸው ተቀጥቅጦ መሞት መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል » ብሎ ንግግሩን ሲያጠቃልል ስብሰባውን የታደመው ሰው ወፈፌው ይልቃል አዲሴን በጭብጨባ ሸኘው።
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ጥቅምት 24 ቀን 2015 ዓ.ም