ለህዝብ አገልግሎት የሚሰጡ እንደ መንገድና የኤሌክትሪክ አቅርቦት ያሉ የመሰረተ ልማት አገልግሎቶችን እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት በተለመደው አካሄድ ለኅብረተሰቡ ተደራሽ የሚያደረገው መንግሥት ነው። በበለፀጉት አገራት ደግሞ እነዚህን አገልግሎቶች በግል የመሥራትና የማስተዳደር ሥራ በስፋት ሲሠራ ይታያል፡፡ በአንዳንዶቹ አገራትም መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በጥምረት በመሆን የየራሳቸውን ድርሻ በመያዝ የሚሠሩበትም አካሂድ አለ፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥትም ከግል ባለሀበቱ ጋር እነዚህን አገልግሎቶች በጥምረት ለመስጠት የሚያስችለውን አሠራር በአዋጅ ቁጥር 1076 /2010 አጽድቆ ወደ ሥራ ከገባ ሰነባብቷል፡፡ የአዋጁን መፅደቅ ተከትሎ የተቋቋመው ቦርድም ሰባት ነጥብ ሰባት ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የመንገድና የኃይል ፕሮጀክቶችን በመለየት ለግሉ ዘርፍ ክፍት በማድረግ ወደ ሥራ ለመግባት በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።
የኢኮኖሚ ባለሙያዎች መንግሥት የግል ባለሀብቶችን በመሰረተ ልማት አቅርቦት ግንባታ ለማሳተፍ የጀመረው እንቅስቃሴ ተገቢና ወቅቱ የሚያስገድደው ቢሆንም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚጠበቅ ያሳስባሉ።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የፋይናንስ ሥራ አመራርና ልማት ኮሌጅ ዲን ዶክተር ለሜሳ በይሳ እንደሚሉት ከዚህ ቀደም በመንግሥት በጀትና በህዝብ ድጋፍ ብቻ ትልልቅ መሰረተ ልማቶችን ለማከናወን የተሠሩ ሥራዎች ቢኖሩም አብዛኞቹ ውጤታማ አልነበሩም።
አንዳንዶቹ ፕሮጀክቶች በርካታ ሚሊዮን ብሮች ተመድቦላቸው ሥራቸው ቢጀመርም የተለያዩ ምክንያቶች እየቀረቡ በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ሲጠናቀቁ አይታይም። ይህንንም ተከትሎ በመዘግየታቸው ብቻ የሚጠይቁት ተጨማሪ ወጪ አለ። እንደዚህም ሆኖ ጊዜ ፈጅተው ወጪ ጨምረው ሲጠናቀቁም ከፍተኛ የጥራት መጓደል የሚታይባቸውም በርካቶች ናቸው።
በዚህም የተነሳ ህዝቡ ማግኘት ያለበትን አገልግሎት በወቅቱ እንዳያገኝ ከመሆኑ ባሻገር መንግሥትም ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረገ ይገኛል። በመሆኑም ትልቅ አገራዊ ፋይዳና ህዝባዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለውጭ ባለሀብቶች ክፍት ማድረጉ አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም።
ነገር ግን ለባለሀብቶቹ የሚሰጡት ፕሮጀክቶች ሦስት መሰረታዊ ጥያቄዎችን የሚመልሱ መሆን አለባቸው የሚሉት ዶክተር ለሜሳ። የመጀመሪው ለውጭ ባለሀብቶች የሚሰጡት ፕሮጀክቶች በመንግሥትም ሆነ በአገር ባለሀብት መከናወን ያልቻሉ ልምድ ያልተያዘባቸው ሊሆኑ ይገባል። በሁለተኛ ደረጃም ከሚከናወኑት ፕሮጀክቶች ኢትዮጵያውያን ከዘርፉ ተቀብለው የሚያስቀሩት የእውቀትና የቴክኒካል ብቃት እንዲኖር በስምምነት የሚዘጋጅ አስገዳጅ ሁኔታዎች መኖር አለባቸው።
በአሁኑ ወቅት ተመሳሳይነት ያላቸው ፕሮጀክቶችን አንድ የውጭ ድርጅት ደጋግሞ ሲሠራ ይታያል። ይሄ የሚሆነው የካፒታል ችግር ስላለ ብቻ ሳይሆን በየደረጃው በቂ የእውቀት ሽግግር ባለመደረጉ ነው። ስለዚህ እንደ አገር በየትኛውም ዘርፍ የሚመጡ ባለሀብቶች ያላቸውን እውቀትና ልምድ እያስቀረን የአገር ውስጥ ባለ ሀብቱና መንግሥት የሚኖራቸውን ተሳትፎ ማጎልበት ይጠበቃል።
ለምሣሌ የውጭዎቹ ባለሀብቶችስ ሦስት መንገድ ከገነቡ አራተኛውን በአገር ውስጥ አቅም መገንባት የሚያስችል የእውቀት ሽግግር ማድረግ፤ ልምድን ማዳበር ይጠበቃል። ይሄ ሳይሆን ቀርቶ በእያንዳንዱ ፕሮጀክት የውጭ ባለሀብቶችን ተሳትፎ እየጠበቅን በሌለን አቅም ለውጭ ባለሀብቶች እየከፈልን በማሠራት የምንቀጥል ከሆነ ኢኮኖሚውን ማቀጨጭ ይሆናል ይላሉ።
ዶክተር ለሜሳ የመፍትሄ ሀሳብ ያሉትንም ሲጠቁሙ ከመንግሥት ጋር የውል ፍፅፅም በሚካሄድበት ወቅት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፤ በየዘርፉ የሚማሩ ተማሪዎችና ከፕሮጀክቶቹ ጋር የሚገናኙ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች መረጃ የሚያገኙበትን ህጋዊ ሁኔታ ማመቻቸት አለበት። ፕሮጀክቶችን የሚከታተሉ አካላትም ለቁጥጥር ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ባልተናነሰ የእውቀት ሽግግሩ በተገቢው መንገድ እየተከናወነ መሆኑን መከታተል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
መንግሥት ለመንግሥትና የግል አጋርንት ክፍት ያደረጋቸው መስኮች የሚጠይቁትን እውቀት፤ ቴክኖሎጂና ካፒታል ያለው ባለሀብት በአገር ውስጥ የለም፡፡ በመሆኑም ወደ ውጭ ማማተሩ የግድ ነው፡፡ የውጭ ባለሀብቶች ደግሞ ከጥቅማቸው ውጭ የሚያዩት ነገር ስለሌለ ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቃል የሚሉት ደግሞ የአፍሪካ ንግድ ምክር ቤት አስተዳዳሪ አቶ ክቡር ገና ናቸው።
እንደ አቶ ክቡር ገና ማብራሪያ ከህዝብ ቁጥር መጨመርና ከአገሪቱ እድገት ጋር በተያያዘ የመሰረተ ልማት አቅርቦት ፍላጎቱ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ ይገኛል። በአንፃሩ የመንግሥት አቅም በገንዘብም ሆነ በእውቀት ውስን በመሆኑ የሚቀርበውን ጥያቄ በወቅቱ መመለስ አይችልም። በመሆኑም መንግሥት ለህዝቡ አገልግሎት ለመስጠት አቅሙ ውስን የሆነባቸውን ዘርፎች ለባለሀብቱ ክፍት ማድረጉ ተገቢ ነው።
ነገር ግን በተቻለ መጠን ዘላቂ ልማትን ታሳቢ በማድረግ የአገር ውስጥ ባለሀብት እድሉን የሚጠቀምበትን ሁኔታ መፈተሽ ይጠበቃል። የውጭ ባለሀበቶች ጠንካራ በመሆናቸው ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በተያዘው በጀትና ጊዜ እንደሚያጠናቅቁ ይታወቃል። መታየት ያለበት ግን ይሄ ብቻ አይደለም። በውጭ ባለሀብቶች የሚሠሩ ግንባታዎች በወቅቱ በጥራት መጠናቀቃቸው ያለው ጥቅም እንደ ተጠበቀ ሆኖ በአገሪቱም ኢኮኖሚ ሆነ በግለሰቦች ላይ የሚፈጥረው ተጽዕኖ እንዳለ መታወቅ አለበት።
በአንድ በኩል የሚከፈለው በውጭ ምንዛሬ በመሆኑ የውጭ ምንዛሬ ያስፈልጋል፤ በሌላ በኩል የውጭ ባለሀብቶች ሥራቸውን ሲያጠናቅቁ ብራቸውን ይዘው የሚወጡ በመሆኑ አገር ቤት የሚቀር ጥሪት አይኖርም። በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ግንባታ ቢካሄድ ግን አንደኛ ክፍያው በኢትዮጵያ ብር ይሆናል፡፡
ሁለተኛም ባለሀብቱ ያተረፈውን ብር መልሶ ኢንቨስት የሚያደርገው በአገር ውስጥ ስለሚሆን የካፒታል እጥረትንና ሥራ አጥነትን ለመቀነስ ትልቅ አቅም ይፈጥራል። በመሆኑም መንግሥት ሙሉ ለሙሉ እንኳን ባይሆን በየፕሮጀክቶቹ ኢትዮጵያውያን ሊሠሩት የሚችሉትን እድሉ እንዲሰጣቸው ማመቻቸት እንደሚጠበቅበት ይናገራሉ።
በተመለከተ የውጭ ኩባንያዎች የራሳቸውን ሠራተኛ የሚያመጡት በሚፈልጉት ደረጃ እዚህ ስለማይገኝ ነው የሚሉት አቶ ክቡር ገና። የእውቀት ሽግግሩን በተመለከተ ያላቸውን ሀሳብ እንዲህ ያብራራሉ። የካበተ ልምድ ያለውና የሰለጠነ ባለሙያ ማፍራት የገንዘብ አቅምን (ካፒታል) ለመፍጠር ከሚወስደው ጊዜ በላይ ይጠይቃል። ካፒታል ዕርዳታን ጨምሮ በተለያዩ ሁኔታዎች በአጭር ጊዜ ሊገኝ ይችላል በራስ የመሥራት አቅምን ግን በአንድ ጀምበር ማብቃት አይቻልም።
በኢትዮጵያ የእውቀት ሽግግሩ ደካማ መሆን ግን ዕድሉን ካለማግኘት ብቻ ሳይሆን እውቀት ለመቀበልም ሆነ ለመኮረጅ ብቁ ባለመሆን የተፈጠረ ነው። ለዚህ ደግሞ የትምህርት ጥራቱ መጓደል አንዱ ምክንያት በመሆኑ የመምህራን አቅም የትምህርት አሰጣጡ ካሪክለሙን ጨምሮ መፈተሽ ያስፈልጋል።
የአብዛኛዎቹ የእስያ አገራት እድገት የተመሰረተው በመኮረጅና ልምድና ተሞክሮን በፍጥነት በማስፋፋት ነው። በኢትዮጵያም ቢሆን ከዚህ በፊት ልምዱ እንደነበረ ማሳያ የሚሆኑ በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። ለምሣሌ የአትዮጵያ አየር መንገድ ከአሜሪካውያን ወደ ኢትዮጵያውያን ሲዛወር በወቅቱ ብቃት ያላቸው ሠራተኞች ስለነበሩ ከአስተዳደር እስከ ቴክኒካል ሥራዎች በአገር ውስጥ በመተካት ሳይንገራጭ ማስቀጠል ተችሏል። የእውቀት ሽግግሩ ላይ ትኩረት መሰጠት አለበት ሲባል ግን እውቀት ብቻ ሳይሆን የሥራ ዲሲፕሊኑንም መውረስ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።
የሚነሱት ሥጋቶች ተገቢ ናቸው በመሆኑም በመንግሥት በኩል አስፈላጊው የጥንቃቄ ዝግጅት ተደርጓል የሚሉት ደግሞ በገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር የግልና የመንግሥት አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጄነራል፤ የአቅም ግንባታና እውቀት ሥራ አመራርና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አሸናፊ አበራ ናቸው።
ዳይሬክተሩ እንደሚያራሩት የመንግሥትና የግል አጋርነት ጥቅም ብቻ ሳይሆን ጉዳቶችና ሥጋቶችም ያሉበት ነው። ከኢትዮጵያ ቀድመው ይሄንን የልማት አካሄድ የተከተሉ አገራት ጥቅሙንም ጉዳቱንም አስተናግደው አልፈዋል። በዋናነት ሊከሰቱ ከሚችሉት ችግሮች መካከል ጠንካራና ጥቅምን የሚያስጠብቅ ስምምነት አለማድረግ አንዱ ነው። የመንግሥትና የግል አጋርነት በኮንትራንት ውል የሚሠራ ሲሆን ኮንትራቱም ከአስራ አምስት እስከ ሰላሳ ዓመት ሊደርስ የሚችል በመሆኑ በነዚህ ጊዚያቶች በሙሉ ሊፈጠሩ የሚችሉትን ሁኔታዎች ታሳቢ ያደረገ ጥቅምን የሚያስጠብቅ ስምምነት ማድረግ ያስፈልጋል። ጨረታው የሚወጣው ውድድሩም የሚከናወነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ስለሚሆንና አብዛኞቹ ተወዳዳሪዎች ልምድ ያላቸው የውጭ ባለሀብቶች ናቸው። በመሆኑም ውሉ ሲፈፀም ከፍተኛ የዓለም አቀፍ የሕግ እውቀት ስለሚጠይቅ በዚህ የሰለጠነና ልምድ ያለው ባለሙያ ያስፈልጋል። ካልሆነ ስምምነቱ ሲደረግም ሆነ ፕሮጀክቶች ሲከናወኑ አገርና ህዝብን ሳይሆን ባለሀብቱን ወደ መጥቀም ያዘነብላሉ።
የመንግሥት ዋናው አላማ በቀጣይ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን በመንግሥትና በአገር ውስጥ ባለሀብት ለማከናወን አቅምን መገንባት ነው ያሉት ዳይሬክተሩ። ለዚህም ፕሮጀክቶች ለአገር ውስጥ ባለ ሀብቶች አቅሙ ሲኖር ያለ ውድድር የሚሰጥበትም ዕድል መኖሩን በመግለፅ፤ የውጭ ባለሀብቶችም ሲወዳደሩ የአገር ውስጥ ባለሀብትን እንዴትና በምን ያህል ማሳተፍ እንዳለባቸው፤ አስተዳደር ክፍላቸውን ሲያቋቁሙ ሠራተኛ ሲቀጥሩ ግብዓት ሲያቀርቡ በአገሪቱ ያለውን አቅም እንዴት መጠቀም እንዳለባቸው በሕግ የተቀመጠ መሆኑን ተናግረዋል። የእውቀትና የልምድ ሸግግሩንም በተመለከተ መንግሥት ትልቅ ትኩረት የሰጠበት እንደሆነ በማስታወስ በሚኒስቴሩ የእውቀት ሽግግርን የሚቆጣጠርና የሚከታተል የእውቀት ሥራ አመራር ዳይሬክቶሬት መቋቋሙን ተናግረዋል።
በየትኛውም አገር አያንዳንዱ መንግሥት የራሱ የሆኑ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች አሉ በኢትዮጵያም አሁን ያለው መሰረታዊ የህዝብ ፍላጎት የመሰረተ ልማት ነው። በመሆኑም ይሄንን እንዲያፀድቅ የተቀመጠው ቦርድ ቅድሚያ በመስጠት ለግል ባለበቶች ተሳትፎ ክፍት ያደረጋቸው የመንገድና የኃይል ማመንጨት ፕሮጀክቶችን ነው።
መንግሥት የመደራደርም ሆነ የመቆጣጠር አቅሙንም ልምዱንም እያዳበረ ሲሄድ ወደሌሎችም መግባቱ አይቀርም ያሉት ዳይሬክተሩ እስካሁን የተሠሩ ሥራዎችንም ሲያብራሩ፤ በኃይል ማመንጨቱ በኩል በአሁኑ ወቅት ስድስት የሶላር ፕሮጀክቶችና ሰባት ኃይድሮ ፕሮጀክቶች ተለይተዋል። በመንገድ በኩል ደግሞ ሦስት የፈጣን መንገድ ግንባታዎች አሉ።
በፀሐይ ብርሃን ኃይል ለማመንጨት የተያዙት ሁለት ፕሮጀክቶች የኩባንያዎች መረጣ ተካሂዶ መስፈርቱን ያሟሉ ኩባንያዎች ፕሮፖዛል እንዲያቀርቡ በዝግጅት ነው። አራት የኃይል ፕሮጀክቶች ላይ ደግሞ የቅድመ ብቃት ማጣሪያ ለማድረግ ጨረታ ሊወጣ እየተዘጋጀ ሲሆን ቀሪዎቹ የኃይልና የመንገድ ፕሮጀክቶች የአዋጭነት ጥናት እየተካሄደባቸው እንደሆነም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2011
በራስወርቅ ሙሉጌታ