የብዙዎችን አንጀት ሲያቃጥል የነበረ ሌባ ወይም ወንጀለኛ ሲያዝ የብዙዎችን አንጀት ያርሳል። አንጀት የሚያርሰው ደግሞ አስደማሚው የፖሊስ ጥበብ ነው። ሙያቸውን በጥቅም በሚሸጡ የሙያ ከሃዲዎችና በስንፍና ሙያውን ባስደፈሩ አንዳንድ ምግባረ ብልሹ ፖሊሶች ወቀሳዎች ቢኖሩም፤ እያወራን ያለነው ግን ለሙያቸውና ቃል ኪዳናቸው ታማኝ ስለሆኑት ፖሊሶች ነው።
ለዚህ ሀሳብ መነሻ የሆነኝ ባለፈው ሳምንት ከአዲስ አበባ ታግቶ ተወስዶ በፖሊስ የክትትል ጥበብ የተገኘው የሕጻን ሳሙኤል ዮሐንስ ዜና ነው።ይህን ዜና እንዳየሁ ትዝ ያለኝ ከ12 ዓመታት በፊት (2003 ዓ.ም) ባደኩበት አካባቢ የተፈጸመ አንድ የፖሊስ ጥበብ ነው። ያ የፖሊስ ጥበብ ዛሬ ድረስ በአካባቢያችን ሰዎች የሚታወስ ነው፤ ለብዙዎች ማስተማሪያ የሆነ ነው። ነገሩ እንዲህ ነው።
ከአካባቢያችን አንድ ወጣት ሥራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ይመጣል። የቀን ሥራ ሲሰራ ቆይቶ አንድ ቋሚ ሥራ ያገኛል። በአንድ የጤና ተቋም ውስጥ በጥበቃ ሰራተኝነት ተቀጠረ። ከቆይታ በኋላ በታማኝነት የተሰጠውን ኃላፊነት በህሊና ቢስነት ወደ ጎን ትቶ መዝረፍ አማረው። የሥራ መደቦቹን ለጊዜው እርግጠኛ ባልሆንም ከጥበቃ ሰራተኝነት በኋላ ካርድ ክፍል መግባት እንደቻለ ታሪኩን የሚያውቁ ሲያወሩ ሰምቻለሁ። እስከ 8ኛ ክፍል የትምህርት ማስረጃ ስላለው ከዛሬ 12 ዓመት በፊት ካርድ ክፍል ለመቀጠር በቂ ነው።
ልጁ 12 ሺህ ብር እና ቁሳቁስ ሰርቆ ተሰወረ። ለሕይወት ዘመኑ የሚበቃ ገንዘብ ያገኘ ስለመሰለው ወደ ትውልድ አካባቢው ሄደ። የትውልድ አካባቢውን መልከዓ ምድር እንኳን የአዲስ አበባ ፖሊስ የወረዳው ፖሊሶች እንኳን አያውቁትም።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ሥራውን መሥራት ጀመረ። የተጠቀሙትን ዘዴ እዚህ ላይ ለመዘርዘር ቦታ አይበቃም፤ የተጠቀሙትን ተጠቅመው ልጁ የተወለደበትን ወረዳ ዋና ከተማ አወቁ። በቀጥታ ከአዲስ 220 ኪሎ ሜትር ወደ ደራ ጉንደ መስቀል ገሰገሱ። እዚያ እንደደረሱ ከወረዳው ፖሊሶች ጋር ተገናኙ። ፖሊሳዊ መረጃዎችን ከተለዋወጡ በኋላ ልጁ ከሚኖርበት ቀበሌ ሊቀመንበር ጋር እንዲያገናኟቸው አደረጉ።
በነገራችን ላይ እነዚህ ሁሉ ነገሮች የሚደረጉት በጥንቃቄ ነው። አካባቢው ገጠራማ ስለሆነ መረጃው ከተሰማ ልጁ ይሰወራል። ሁሉንም ነገር በምሥጢር ከጨረሱ በኋላ የፖሊስ ልብሳቸውን ቀይረው በሲቪል መንቀሳቀስ ጀመሩ። ልጁ ያለበት ቀበሌ ሲደርሱም ያገኙትን ሰው ሁሉ ይጠይቁ የነበረው ፖሊስ መሆናቸውን ሳይገልጹ መንገድ የጠፋባቸው መንገደኛ መስለው ነው።
ዝርዝሩ ይቅርና እንዲህ እንዲህ እያሉ ቀጥታ ያለበት ቤት ውስጥ ነው የገቡ። ሰላምታ ከተጨባበጡ በኋላ ነው በእጁ ካቴና የገባው። እጁን በካቴና አስረው ተወልዶ ባደገበት አካባቢ አገር ምድሩ እያየው ሌብነቱን ላገኙት ሁሉ እየተናገሩ ተወሰደ።
ፖሊሶቹ ለአካባቢው ሰዎች ሲነግሯቸው፤ ልጁን ለመያዝ የወጣው ወጪ እና የጠፋው ጊዜ ልጁ ከሰረቀው ገንዘብ ጋር ሲነፃፀር በፍፁም አይገናኝም። ከ12 ሺህ በላይ ገንዘብ ወጥቷል፤ ከአንድ ወር በላይ ጊዜ ወስዷል። ‹‹ይህን ያደረግነው ወጪው እንደሚበልጥ ስተነው አይደለም፤ እንዲህ አይነት ሌባ ከእኛ ማምለጥ እንደማይችል ለማሳየት ነው›› እያሏቸው ነበር።
እንግዲህ ለዚያች ትንሽ ጥፋት (በእርግጥ የስርቆት ትንሽ የለውም) ፖሊስ ያን ያህል ድካም ደክሟል፤ ያን ያህል የኦፕሬሽን ሥራ ተሰርቷል። ለምን ቢሉ! ክህደት ፈጽሟል፣ በአደራ የተሰጠውን ንብረት ዘርፏል። ነገ ከነገ ወዲያ እንደዚያ አይነት ድርጊት እንዳይፈጸም ያደርጋል። እንደተባለውም እነሆ ከዚያ አካባቢ ተመሳሳይ ድርጊት ሰምች አላውቅም። ዛሬ ድረስ ያስታውሱታል።
ከፖሊስ ጥፋተኛን የመቅጣት እንቅስቃሴ ውስጥ የሚያስገርመኝ የሚጠቀሙት ጥበብ ነው። እስኪ አሁን ደግሞ አንድ የትራፊክ ፖሊስ ጥበብ ልንገራችሁ። 2009 ዓ.ም ነው። ከደራ ወደ አዲስ አበባ እየመጣሁ ነው። በዚህ መስመር የሚመጣ መኪና የሚጭነው ሰው የአዲስ አበባን አንበሳ ባስ መስሎ ነው። በዚያ ላይ ከታሪፍ በላይ (እጥፍ የሚሆንበት ጊዜም አለ) ነው የሚያስከፍሉ። ለተጓዦቹ ትራፊክ ሲጠይቅ ይህን ያህል ነው የከፈልን ብላችሁ ንገሯቸው ብለው መደበኛውን እንድትናገሩ ያደርጓቸዋል፤ አለበለዚያ መንገድ ላይ እንደሚያወርዷቸው ያስፈሯሯቸዋል።
በዚህም ምክንያት መንገደኛው ሲጠየቅ የሚናገረው መደበኛውን ታሪፍ ነው። እኔ የምጓዝ ዕለት ረዳቱ የተለመደውን መልዕክት አስተላለፈ። በነገራችን ላይ አንዱ ደፍሮ ቢናገርም ትራፊክ ፖሊሶች ስለማይቀጧቸው ምን አዳረቀኝ ብሎ ነው ዝም የሚል። የዚህን ዕለት የገባው ፖሊስ ግን የቆረጠ ይመስላል።
ቀጥታ ወደ መኪናው ውስጥ ገባ። ከፊቱ ያሉትን ሲያይ የተማሩ የሚመስሉ፣ ከተማ ቀመስ ናቸው። እነዚህን ሰዎች ቢጠይቃቸው እንደሚዋሹት ገብቶታል፤ ምክንያቱም ወንበር እንዲያዝላቸው ከረዳቶና ሾፌሮች ጋር የሚሞዳሞዱ ናቸው።
በቀጥታ አይኑ ያማተረው ወደኋላ ነው። አንዲት ነጭ ሻሽ ያደረጉ መነኩሴ እናት አየ። ረዳቱንም ተጓዡንም እያዋዛ እየቀለደ መነኩሴዋ ጋ ሄደ። አጠገባቸው ቁጭ ብሎ ‹‹ጉዞ እንዴት ነበር?›› እያለ ትንሽ አወራና ስንት እንደከፈሉ ጠየቃቸው። መነኩሴዋ እቅጩን ተናገሩ። ሾፌሩን ጎትቶ አውርዶ ተገቢውን ቅጣት ሰጠው ማለት ነው!
እዚያ ውስጥ የነበረው ሰው ሁሉ አንጀቱ ራሰ። ተጓዡ ከዚያ በፊት ተሰላችቶ የነበረው ትራፊኮች በሩ ላይ ብቅ ብለው ምልስ ሲሉ ነበር። ቢናገሩም በኋላ ከረዳቱ ጋር መሰዳደብ ይሆናል እንጂ አይቀጧቸውም ነበር። ያ ፖሊስ በዚያ መንገድ ሰርቶ ሲሄድ ግን አንጀታቸው ራሰ።
እንዲህ አይነት የፖሊስ ሥራዎች አንጀት አርስ ናቸው። እንዲህ አይነት ሥራዎችን ለመሥራት ደግሞ የራሳቸው ጥበብ አላቸው።
ይህ ይሆን ዘንድ ታዲያ ሕብረተሰቡ ተባባሪ ሊሆን ይገባል። ‹‹ፖሊስና ሕብረተሰብ›› የሚለው ፕሮግራም ስሙ ገላጭ ነው። ፖሊስ እንዲህ አይነት ሥራዎችን መሥራት የሚችለው ሕብረተሰቡ ወንጀል ተፀያፊ ከሆነ ነው። ለምሳሌ ከላይ የገለጽኩትን የትራፊክ ፖሊሱን ዘዴ መጠቀም ያስፈለገው አስመሳዮች ስለሆንን እንጂ እዚያ መኪና ውስጥ ያለው ሰው ሁሉ ሊያጋልጥ ይገባ ነበር። ግን እኛም አስመሳዮች ነን፤ አንዳንድ ፖሊሶችም አሳፋሪዎች ናቸው። ቢጠቁሟቸውም በቸልተኝነት ይተውትና ከባለጉዳዩ ጋር መጣላት ይሆናል።
ከምንም በላይ ግን በሕብረተሰቡ ውስጥ ያለው ችግር ጥፋተኛን የመደበቅ አባዜ ነው። ፖሊስ ደግሞ ከሕብረተሰቡ በሚያገኘው መረጃ እና በራሱ የምርመራ ጥበብ እንጂ በጥንቆላ አይደለም የሚሰራ። ሕብረተሰቡ ጥፋተኛን ከደበቀ ለጊዜው የረቀቀ ቴክኖሎጂ ስለሌለን ማግኘት አይቻልም። ስለዚህ ሌባን እና ወንጀለኛን መከላከል የምንችለው ከፖሊስ ጋር በመሆን ነው።
በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው ፋሽን የሕጻናት እገታ ነው። ይህን ነገር ከወዲሁ የሕብረተሰብ ርብርብ ካልተደረገበት አደጋው የከፋ ነው። ነገ የሁላችንንም ቤት ያንኳኳል። ስለዚህ እንዲህ አይነቱን አረመኔያዊ ድርጊት ማስቀረት የሁላችንም የዛሬ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል!
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2015