የፈታኙ ማስታወሻ
የ2014/15 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና በዩኒቨርሲቲዎች ይሰጣል የሚል ወሬ የተሰማው ቀደም ብሎ ነበር። ከወሬ አልፎ ተግባራዊ ይደረጋል የሚል እምነት አልነበረኝም። ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎችን ወደ በዩኒቨርሲቲ ማጓጓዝና መመገብ ብዙ ገንዘብ ይጠይቃል። ከገንዘቡም በላይ አፈፃፀሙ የዩኒቨርሲቲዎችን አቅም እንደሚፈትን መገመት አያዳግትም። የትምህርት ሚኒስቴር “ከመስከረም 20 እስከ ጥቅምት አጋማሽ በዩኒቨርሲቲዎች ግቢ ውስጥ ምንም ተማሪ እንዳይኖር” የሚል መመሪያ ማስተላለፉን ስሰማ እንኳን የምር ተግባራዊ ይደረጋል ብዬ አላመንኩም። ብዙም ሳይቆይ “ወደ ሌላ ዩኒቨርሲቲ ሄዳችሁ መፈተን የምትፈልጉ መምህራን በየትምህርት ክፍላችሁ ተመዝገቡ” የሚል ጥሪ ሲመጣ ጉዳዩ ቁርጥ መሆኑን ለማመን ተገደድኩ። አንድ የስራ ባልደረባዬ ስለዚህ ጉዳይ ምን እንደማስብ ሲጠይቀኝ እንዲህ ብዬ መለስኩለት።
“እኔ ወታደር አይደለሁም። ዘምቼ ሀገሬን አሁን ከሚወጓት የውጭና የውስጥ ጠላቶች ልጠብቃት አልችልም። ገበሬ ሆኜ ሰብል በማምረት ወገኖቼን አልቀልብም። ጥበበኛ ሆኜም በጥበብ የሀገሬን ስም አላስጠራም። እኔ መምህር ነኝ። ለሀገሬ አስተዋፅኦ ላበረክት የምችለው በሙያዬ ነው። ሙያዬ የሚጠይቀውን ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ ነኝ። መንግስት ጥበቃ እንዲያደርግልኝ፤ ምግብና መኝታ እንዲሰጠኝ እፈልጋለሁ። በተረፈ የተመደብኩበት ቦታ ሄጄ ልፈትን ዝግጁ ነኝ” አልኩት። ጓደኛዬም አቋሙ ከእኔ ጋር ተመሳሳይ ነው። በብዙ ሀገራዊ ጉዳዩች ዙሪያ ተቀራራቢ አቋም አለን። የተሰጠንን ፎርም ሞልተን ለመመለስ ጊዜ አልወሰደብንም።
ከሳምንታት ቆይታ በኋላ ተማሪዎች የሚፈተኑበት ዩኒቨርሲቲ ግልፅ ተደረገ። በዚህ ወቅት እኛም የምንፈትንበትን ዩኒቨርሲቲ ለማወቅ ጓጓን። እንዲያውም የእኛ ምደባ በመዘግየቱ ቅሬታ ተሰማን ማለት ይቻላል። ምደባው በመዘግየቱ የየግል ጉዳዮቻችንን ለማስቀድም ተቸገርን። ቀኑ እየቀረበ ሲሄድ “በምናስተምርበት ዩኒቨርሲቲ እንድንፈትን ፈልገው ይሆናል” የሚል ጥርጣሬ አደረብን።
ከእለታት በአንዱ ምሽት ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሣይንስ ተማሪዎችን እንድፈትን መመደቤን የሚገልጽ መልዕክት በእጅ ስልኬ በኩል ደረሰኝ። ደነገጥኩ። መልዕክቱን ደጋግሜ አነበብኩት። ምንም የተለየ ነገር ለውም። እድሜ ለቴክኖሎጂ! የሚዛን ቴፒን ርቀትና የተለያዩ መረጃዎች ከድህረ-ገፅ አስሼ አገኘሁ። በማግስቱ ወደ ቢሬ ሄጄ የስራ ባልደረቦቼ የት እንደደረሳቸው ጠየኳቸው። አብዛኞቹ ሃዋሳ፤ ወላይታ ሶዶ፤ ባህር ዳር፤ ጎንደር፤ ደብረማርቆስ፤ ዲላና የመሳሰሉት ዩኒቨርሲቲዎች እንደ ደረሳቸው ነገሩኝ። ደስታና ቅሬታ ተምታቱብኝ። ከዚህ በፊት ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ሲያስተምር ወደ ነበረ የስራ ባልደረባዬ ስልክ ደወልኩና ሁኔታውን ነገርኩት።
“አገሩ በጣም ጥሩ ነው። ይህን አጋጣሚ ዳግም ስለማታገኘው ሄደህ ኢትዮጵያን አይተህ ተመለስ” አለኝ። አጭርና ልብ አንጠልጣይ ምክር ነበር። የበለጠ ተበረታታሁ። ስለአካባቢው ለማወቅ ፈልጌ እንጂ ለመቅረት አስቤ እንኳን አልነበረም። ራሴን እስከማውቀው ድረስ ከሀገር ጥሪ የምቀር ሰው አይደለሁም። ኢትዮጵያ ውስጥ እያለሁ “ሄደህ ኢትዮጵያን እይ! የሚለኝ ምን የተለየ ነገር ቢኖር ነው?” የሚል ጥያቄ በውስጤ ተፈጠረ። እስከ ጂማ ድረስ በአውሮፕላን መሄድ እንደምችል ባውቅም ጉዞዬን በአውቶቡስ ለማድረግ ወሰንኩ። አጭር የአውሮፕላን ጉዞ ምቾትና ፍጥነት እንጂ ቀሪ ትዝታ እንደሌለው አውቃለሁ። ጥቂት ቅያሬ ልብሶችና የሚነበቡ መፅሃፍትን ይዤ አዳሬን አዲስ አበባ አደረኩ።
ጎህ ሣይቀድ ላምበረት አካባቢ ከሚገኘው የአውቶቡሶች ማደሪያ ተነስተን ጉዟችንን ወደ ምዕራብ አቅጣጫ አደረግን። በትዝታ መነፅር 23 ዓመታትን ወደ ኋላ ተመለስኩና በብቸኛው ዋሊያ አውቶቡስ ከሶስት ቀናት ጉዞ በኋላ ጋምቤላ የገባሁበትን ጊዜ አስታወስኩ። መንገዱ እንደ አሁኑ ቀላል አልነበረም። ከአዲስ አበባ በመነሳት ጂማ ይታደራል። የሁለተኛው ቀን አዳር መቱ ይሆናል። በሶስተኛው ቀን ከስምንት ሰዓት ጉዞ በኋላ ጋምቤላ ይገባል። ታዲያ ለዚህ ሁሉ ጉዞ ክፍያው ሶስት መቶ ብር እንኳን የሚሞላ አይመስለኝም።
ፀሐይ በአናታችን ትይዩ ስትሆን ምሳችንን በአባ ጁፋር አገር ጂማ በልተን ወደ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ዞርን። እንደ ድሮው “ይህቺ ከተማ ምን ትባላለች?” እያልኩ ሰው መጠየቅ፤ የንግድ ባንክ ፅሁፍ ማየት ወይም የትምህርት ቤት ታፔላ ላይ ማፍጠጥ አላስፈለገኝም። ስልኬን በቀጥታ ቦታ ጠቋሚ (Live Location) ላይ አድርጌ በእጄ መደንቆል ብቻ በቂ ነበር። ስልኬ ሰቃ፤ ሸቤ፤ አሚዮን እያለ የቦታዎችን ስም ይዘረዝርልኛል። ልክ ሰቃን እንዳለፍን የተለየ መልከዓ-ምድር ተቀበለን። ወደ ቀኝ፤ ወደ ግራ፤ ወደፊት ሲታይ ሁሉም ነገር አረንጓዴ ነው። ጥብቅ የተፈጥሮ ደን መስሎኝ ነበር። ነገር ግን በየዛፉ ጥግ ቤትና የቤት እንስሳት፤ ራቅ ብሎም የእርሻ ማሳዎች ይታያሉ። የተለየ ፓርክ ሳይሆን ነዋሪ የጠበቀው የተፈጥሮ ደን መሆኑን አወቅሁ።
የአካባቢው ማህበረሰብ ከደን ጋር ያለው ህብረት ያስገርማል። ደን ሳይመነጥር በስሩ ቤት ይሰራል፤ ቡና ይተከላል። ከአረንጓዴ ዛፎች ጋር በጉርብታና ይኖራል። ዛፎች ከዕለት-ተዕለት ኑሯቸው ጋር ተቆራኝተዋል። እንደ ኮሶ፤ ዋርካና ዝግባ ዛፎች አይን ይማርካሉ። ሌላ ቦታ በብዛት የማይታዩ ናቸው። ከማድነቅም በላይ ስጋት ገባኝ። ጂማ ከተማ ውስጥ በየበረንዳው ተዘርግተው የሚቸበቸቡ የእንጨት ኩርሲዎችን፤ ትንንሽ ተሰኪ ጠረጴዛዎችንና የእንጨት ጌጣጌጦችን ያየ ሰው “የዚህ ደን እጣ ፈንታ ምን ይሆን?” ብሎ መስጋቱ ተገቢ ይመስለኛል።
የቀን ውሎዬን የመመዝገብ (dairy keeping) ልምድ ባይኖረኝም ይህን መሰል ፀጋ እያየሁ ማለፍ ግን ከበደኝ። የኪሴ ማስታወሻዬን አውጥቼ “ምድር ሳትራብ ሰዎች ለምን ይራባሉ?” ብዬ ፃፍኩ። ማንን እንደምጠይቅ እንኳን አላውቅም። ይሄን ሁሉ ፀጋ እያለን ለምን ተራብን የሚል ቁጭት ተናነቀኝ። ሸቤንና አሚዮንን እያቆራረጥን ወደ ቦንጋ ቀረብን። አውቶቡሳችን ምድራዊ አውሮፕላን ነው ማለት ይቻላል። በእርጋታ ቢሄድ አካባቢውን በደንብ አይ ነበር ስል በመኪናው ፍጥነት ቅሬታ ተሰማኝ። ወደ ቦንጋ ስንጠጋ ጎጀብ ወንዝ ከነግርማ ሞገሱ ተቀበለን። ያስፈራል።
እርሱም እንደ ሌሎች ወንድሞቹ ለም አፈራችንን ጭኖ እየተጣደፈ ነው። አባይ፤ ባሮና ዋቤ ሸበሌን በደንብ አውቃቸዋለሁ። ጎጀብም ከእነርሱ እንደ አንዱ ከቤቱ አፈር ጭኖ ለባዕድ ሊያቀብል ይሮጣል። አለመታደል ሆኖ ወንዞቻችን ሀገራቸውን በዳይ፤ የባዕድ ሲሳይ ናቸው። ከሁሉ በላይ የሚያበሳጨው አፈራችንን ጭነው መሄዳቸው ነው። ጎጃብ ወንዝም ደፍርሶ የሚሄደው ያው ለም አፈራችንን ጭኖ ነው። ተረጋግቼ ለማሰብ እንኳን ጊዜ ሳላገኝ መኪናው በፍጥነት አሳለፈኝ።
“እንኳን ወደ ቡና መገኛ ምድር ወደ ከፋ በሰላም መጣችሁ” የሚል ፅሁፍ የያዘ ታፔላ በጨረፍታ አነበብኩ። አውቶቡሱ ከንፋስ ጋር ፉክክር የገጠመ ይመስል ፍጥነቱ ወደ ውጭ ለማየትና ለማንበብ ጊዜ አይሰጥም። በዚህ ቅፅበት ሌላ ነገር ትዝ አለኝ። ለካ የሰው ዘር መገኛ ብቻ ሳንሆን የቡናም መገኛም ነን አልኩኝ። ግን ደግሞ “መገኛ” ብቻ መሆን ምን ዋጋ አለው? የሰው ልጅ መገኛ የሆነችው ሀገራችን ዛሬ የሰው ልጅ የሚራብባት ምድር ሆናለች። የቡና መገኛ ብንሆንም ከቡናችን ምን ያህል እየተጠቀምን ነው? እያልኩ ከራሴ ጋር ሙግት ገጠምኩ።
ብዙም ሳንርቅ ጉም እይታችንን ገደበው። በማን እንደምበሳጭ ባለውቅም ተበሳጨሁ። አንዳንድ ተሳፋሪዎችን እንቅልፍ ከወንበር ጋር ያላትማቸዋል። አንዳንድ ወጣት መንገደኞች ደግሞ ለጓደኞቻቸው እየደወሉ የቦታውን ርቀት ያማርራሉ። ርቀቱ እንጂ ልምላሜው ለምን እንዳልታያቸው እኔ አላውቅም። አልፈርድባቸውም። እኔም የዛሬ 23 ዓመት የኢሉባቦርን ጥቅጥቅ ደኖች አቋርጬ ስሄድ የሚታየኝ ርቀቱ ብቻ ነበር። ይኼ የሁላችንም ችግር ነው። ማንቀላፋት ፀጋዎቻችንን እንዳናይ መጋረጃ ሆኖብናል። የሚጎድለንን ብቻ እያሰብን ማማረር ያለንን ሀብት እንዳናይ ከልሎናል።
አመሻሹ ላይ ሚዛን ገባን። የተያዘልን መኝታ ጥሩ አልነበረም። ያንንም የያዘችልኝ ከእኔ በሰዓታት ቀድማ የደረሰች የስራ ባልደረባዬ ነበረች። እንደምንም አድረን በማግስቱ የተሻለ መኝታ ያዝን። መታጠቢያውና መፀዳጃው ከክፍሉ ውጭ ቢሆንም ንፁህ ነው። ከቤት የወጣነው ለአገራዊ ተልዕኮ እንጂ ለቅንጦት ስላልሆነ መመፃደቅ እንዳሌለብን እናውቃለን። የዚህ ፅሁፍ ዓላማም የጎደለውን በማንሳት ማማረር ሳይሆን የአካባቢውን ውብ ተፈጥሮ ማሳየትና ያላዩት ሄደው እንዲያዩ ማነሳሳት ነው። የከተማው መሬት አቀማመጥ ኮረብታና ሸለቆ ይበዛዋል። ቢሆንም ግን ዋና መንገዱን ተከትሎ ብዙ ዘመናዊ ህንፃዎች ተገንብተዋል። በዚህ ርቀት ላይ እነዚህን የመሰሉ ዘመናዊ ህንፃች ይኖራሉ ብዬ አላሰብኩም። ቁርስ የት እንደሚገኝ ስንጠይቅ ስጋ ቤቶቹን አሳዩን። ሚዛን ላይ ስጋ በፍቅር ይበላል።
አስተናጋጁ ወደ እኛ ሲጠጋ “ለእንግዳ የሚሆን ቁርስ ምን አለ?” አለችው። ከእኔ ቀድማ ሚዛን የገባችዋ መምህርት ነበረች። የመምህርቷ ድፍረትና ጠያቂነት ያስገርማል። ማወቅ የፈለገችውን ነገር ሁሉ ትጠይቃለች፤ ነካክታ ታያለች። አንዳንዱን ቀምሳም ትሞክራለች። ወደ ዩኒቨርሲቲው ስንሄድና ስንመለስ የዩኒቨርሲቲው ሎጂስክ ኃላፊ ዘንድ ደውላ መኪና የምታስመጣልን እርሷ ነበረች። ከሰው መግባባትና ድፍረትን ከታደሉት ሰዎች አንዷ ናት ማለት እችላለሁ።
“ማቾኒ ይሁንላችሁ?” አለን ። እኛ የጠበቅነው “ምላስ ሰንበር”፤ “ዱለት ወይም ቁርጥ” የሚል ነበር። “አዎ ይሁን!” አልን ምንነቱን ሳናውቅ። መቼም የተሻለ ነገር ቢሆን ነው የመረጠልን ከሚል እሳቤ ነው። “ማቾኒ” በዳቃቅ የተከተፈ ስጋ ጥብስ ነው። በሚያምር መጥበሻ በበቆሎ እንጀራ ተሸፋፍኖ መጣልን። በዳጣ እያጠቀስን አጣጣምነው። ዋጋውም ተመጣጣኝ ነው። ከዚያ በኋላ ከሚዛን እስከወጣን ድረስ “ማቾኒ” የእለት ምግባችን ሆኖ ቀረ። የምግቡ ጣዕም ብቻ ሳይሆን ስሙም ለጆሯችን ጣመን። ማቾኒ !
አቅጣጫውን ከጠየቅን በኋላ ታክሲ ተሳፍረን ወደ ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ አመራን። ግቢውን ተዘዋውረን አልጎበኘንም። መማሪያ ክፍሎችና ቢሮዎች አካባቢ ብቻ በስራ ምክንያት ተዘዋወርን። አባጣ-ጎባጣ በበዛበት መሬት ላይ አስገራሚ ህንፃዎች ተሰርተዋል። አንድ ቦታ ላይ ረጅምና ተያያዥ የሆነ ህንፃ ተገንብቷል። በዚህ ርቀት ይሄን የመሰል የህንፃ ዲዛይን አይቶ አለማድነቅ ንፉግነት ነው። ሕንፃው ያረፈበት መሬት ከአንድ የእግር ኳስ ሜዳ አይተናነስም። የተወሰኑ መማሪያ ክፍሎችን በስተቀር ሌሎቹ ክፍሎች ምን ምን እንደሆኑ አላየሁም። “ምን አለ ቢያስጎበኙን?” ማለቴ አልቀረም። ምናልባትም እኔ ከሄድኩ በኋላ ቀሪዎቹን ፈታኞች አስጎብኝተው ሊሆን ይችላል።
ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ዋና ግቢ በሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች አይተን የማናውቀው የተፈጥሮ ስጦታ አለው። አንድ ትልቅ ወንዝ ግቢውን ሁለት ቦታ ከፍሎ ያልፋል። ከአስተዳደር ቢሮዎች ወይም ከአዲሱ ህንፃ ወደ ተማሪዎች መመገቢያ አዳራሽ ለመሄድ ወንዙን ማለፍ ግድ ነው። የመጀመሪያው ቀን ሁላችንም ተገርመን ቆመን አየን። ውሃው ከአለት ጋር እየተላተማ ሲወርድ የሚፈጥረው ድምፅ መንፈስን ያድሳል። ተፈጥሮ ያለገደብ ሲሰጥ እንደዚህ ነው። አብሮኝ ለነበረው ጓደኛዬ እንዲህ አልኩት። “ተፈጥሮን ለማድነቅ ከቻልክ ሚዛን ተወለድ፤ ካልቻልክ ደግሞ ሚዛንን ጎብኝ” አልኩት። ተሳስቀን ወደ ጉዳያችን ሄድን።
መመገቢያ አዳራሹ ፊት የተሰለፉ ተማሪዎች ከመብዛታቸው የተነሳ ጠጠር ቢወረወር መሬት አያርፍም። እነዚህን ተማሪዎች መመገብና ማቆየት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ሳስብው ለዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ያለኝ አክብሮት ጨመረ። በሰልፉ መሃል አቆራርጠን አልፈን መፈተኛ ክፍላችንን አገኘን። የተወሰነ ኦረንቴሽን ወስደን ወንበሮችን አስተካክለን ተለያየን።
ከዋናው ግቢ ከ3 ኪሎ ሜትር ባልበለጠ ርቀት አማን የሚባል ቦታ አለ። የዩኒቨርሲቲው ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የሚገኝበት ክፍለ-ከተማ ነው። ከኮሌጁ ፊት ለፊት አንድ ሰፊ ሜዳ አየን። እስከ አሁን ካየነው የመሬት አቀማመጥ ይህን የመሰለ ሜዳ መኖሩ ገረመንና አብሮን የነበረውን የአካባቢውን ተወላጅ ጠየቅነው። “ይሄ የድሮ አየር ማረፊያ ነው። አባቶቻችን በእጃቸው ቆፍረው የገነቡት አየር ማረፊያ ነበር። ግንባታ እንዳይካሄድበት የከለከለው የአካባቢው ማህበረሰብ ነው። አባቶቻችን ከገጠር ሳይቀር ስንቅ ይዘው መጥተው ሳምንታትን እዚህ ቆይተው ነው የሰሩት።
ለልጆቻችን መጫወቻ ይሆናል እንጂ ግንባታ አይካሄድበትም ብለው ነው የከለከሉት” አለን። “ምናለ ሁሉም ሰው እንደዚህ ቢያስብ?” አልኩኝ። እኔ እንኳን የማውቃቸው የጎባና የአሰላ የድሮ አየር ማረፊያ ቦታዎች እንዲህ የሚጠብቃቸው ሰው አጥተው ነው የተወረሩት። እነዚህ ከተሞች አሁን አየር ማረፊያ የላቸውም። በቅድመ-ስልጣኔ የነበሩ አባቶችን ያህል ማሰብ ያቃተን ትውልድ ስለመሆናችን ማረጋገጫው እንደዚህ ዓይነት ተግባር ነው። እነርሱ ግሬደርና ዶዘር ባልነበረበት ዘመን በእጃቸው መሬት ቆፍረው፤ በትከሻቸው አፈር ተሸክመው የሰሩትን እኛ ተማርን የምንል ልጆቻቸው ለጎጆ መስሪያ ቸረቸርነው። ሚዛን-አማን ላይ ግን ይሄ አልሆነም። አውሮፕላን ባያርፍበትም ልጆች ኳስ ይጫወቱበታል፤ ስፖርት ይሰሩበታል።
በፈተናው ዕለት ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ተኩል በየክፍላችን መገኘት እንዳለብን ተነግሮናል። ምግብ ቤቶች በጠዋት እንደማይከፈቱ ስለገባን ማታውኑ ሙዝ፤ አቮካዶና ዳቦ ገዛዝታን ወደ ማደሪያ ክፍላችን ሄድን። በጣም ቀላል፤ ነገር ግን ትልቅ ሃላፊነት ይጠብቀናል። ምንም እንኳን የድካም ስሜት ባይሰማኝም በጊዜ ተኛሁ። ነገር ግን ንጋት ላይ እንቅልፍ አልወስደኝ አለ። ደግነቱ የሚነበብ መፅሐፍት ስለያዝኩ አልጋ ላይ መገላበጥ አላስፈለገኝም።
ከተባለው ሰዓት ቀድመን በየመፈተኛ ክፍላችን ተገኘን። የተፈታኞችን የመመዘገቢያ ቁጥር እያየን ወደ ክፍል አስገብተን በተዘጋጀላቸው ወንበር ላይ አስቀመጥናቸው። በየወንበራቸው ላይ የመመዝገቢያ ቁጥራቸውን ፅፈን ስለነበር በእጃቸው የያዙትን ካርድ ከተፃፈው ቁጥር ጋር እያመሳከርን አረጋገጥን። ሱፐርቫይዘሩ መልስ መስጫ ወረቀቶችን አምጥቶ ሰጠኝ። ለሌሎች ፈታኞችም ሰጥቶ መምጣቱን አውቃለሁ። ልክ እንደ ጥያቄ ወረቀቱ ግራና ቀኝ እያልኩ ለሁሉም ተፈታኝ አደልኩ። ከስማቸው በመጀመር ሌሎች መሞላት የሚገባቸውን መጠይቆች እንዲሞሉ አደረኩ።
ሱፐርቫይዘሩ ሁለት የታሸጉ ፖስታዎችን አምጥቶ ሰጠኝ። የጥያቄ ወረቀት ነበር። ፖስታው የታሸገ መሆኑን በማሳየት በእነርሱ ፊት ከፍቼ ጥያቄ ወረቀቱን በጥንቃቄ አደልኳቸው። ሰዓቱ እስኪደርስ በመጀመሪያው ገፅ ላይ የተፃፈውን አጠቃላይ መመሪያ እያነበቡ እንዲቆዩ አደረኩ። ገፁን ገልጠው ጥያቄዎቹን ለማየት የሚሞክሩ ተማሪዎችን እየተከታተልኩ አስቆምኳቸው። ብዙም አላስቸገሩኝም። ልክ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ሲሆን ተደወለና ፈተናው ተጀመረ። ዋናው ስራ ከዚህ በኋላ ነበር። መቆጣጠር።
አጠገባቸው ካለው ተማሪ ጋር ለማውራት መሞከር፤ ማንሾካሾክና አጮልቆ ወደ ሌላ ተማሪ ለማየት የሚደረጉ ሙከራዎች ነበሩ። በምልክት ወይም አጠገባቸው ሄጄ ሳስጠነቅቃቸው ወዲያው ከድርጊታቸው ይታቀቡ ነበር። እኔ ቋንቋቸውን አልችልም። እነርሱ አማርኛ በመጠኑ ይሰማሉ። መግባባት ግን አላቃተንም። ትንሽ ለየት ያለ ድርጊት ሳይ አጠገባቸው ሄጄ ቆም እላለሁ። ቀና ብለው ያዩኛል። በጣቴ የማስጠንቀቂያ ምልክት እሰጣቸዋለሁ። አይናቸውን ወደጥያቄቸው ይመለሳሉ። በቃ ! ቀና ብለው እንኳን አያዩም።
በበኩሌ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና የፈተንኩት ከዛሬ 20 ዓመት በፊት ነበር። በወቅቱ ከፈተና ጋር የተገናኘ የስነ-ምግባር ጉድለት እንደ አሁኑ የከፋ አልነበረም። አሁን ያለውን የፈተና ሁኔታ ከሰው ከመስማት ባለፈ በተግባር የማውቀው ነገር አልነበረም። በዚህ ምክንያት ተማሪዎች በጣም ሊያስቸግሩኝ ይችላሉ የሚል አመለካከት ይዤ ነበር የሄድኩት። ተማሪ ቢያስቸግር ምን ማድረግ እንዳለብኝ አውቃለሁ። ከአስር ዓመታት በላይ በመምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ውስጥ ሳስተምር ከፈተና አወጣጥና አፈታተን ጋር የተገናኙ ኮርሶችን እሰጥ ነበር። በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪዎችን ስፈትን የጠበኩትን ዓይነት የስነ-ምግባር ጉድለት አላየሁም። አብረውኝ የነበሩት ፈታኞችም ችግር መኖሩን ሲያወሩ አልሰማሁም።
መጥፎ ድርጊት ስናይ እንደምናወግዘው ሁሉ ጥሩ ነገር ስናይ ማመስገን መልመድ አለብን። እኔ የፈተንኳቸው ተማሪዎች ከዳውሮ ዞን ገሳ ዳልባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጡ ነበሩ። በፈተናው ወቅት ላሳዩኝ መታዘዝና ከበሬታ ከልቤ ላመሰግናቸው እወዳለሁ። በማስተምርበት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ፈተና ስሰጥ የማያቸውን የፈተና ስነ-ስርዓት ጥሰቶች የሚያህል እንኳን አላየሁም። ይሄን ማየቴ ከመገረምም አልፌ ተስፋ እንዲኖረኝ ረድቶኛል።
ብሔራዊ ፈተናን እንደ ቅርጫ ስጋ ሁሉም ተማሪ የሚጋራበት ዘመን ላይ መድረሳችን የማያሳዝነው ሰው ያለ አይመስለኝም። በዚህ ዓመት ይህን ጸያፍ ተግባር ለማስቀረት የተደረገው ጥረት የሚበረታታ ነው። በበኩሌ የችግሩ ዋና ተዋናይ ተማሪዎች አለመሆናቸውን ከዚህ ፈተና ተገንዝቤያለሁ። የትምህርት ቤት አስተዳደር፤ መምህራን፤ ወላጆች፤ በየደራጀው ያለ የመንግስት መዋቅር ሁሉም ራሱን መጠየቅ ያለበት ይመስለኛል።
ወደ ሚዛን ቴፒ ስሄድ በጥርጣሬና በስጋት ነበር። ስመለስ ደግሞ በተስፋና በቁጭት ሆነ። መጀመሪያውንስ ለምን ነበር ስጋትና ጥርጣሬ ያደረብኝ? በ20ዎቹ መጀመሪያ ዕድሜዬ ጋምቤላ ድረስ የሄድኩት ሰውዬ ዛሬ ምን ሆኜ ነው ሚዛን መሄድ ያስፈራኝ? ኧረ ለመሆኑ ማነው እንዲህ እንድንፈራራ ያደረገን? ሚዛን ቴፒ የሚናፈቅ መልከዓ-ምድር፤ የሚወደድ ሰው እንጂ የሚፈራ ምንም ነገር እንደሌለ ማርና ቡናውን የቀመሰ ይመሰክራል። እኔ አንዱ ምስክር ነኝ።
በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና ምክንያት ለምለም መሬት፤ ታይቶ የማይጠገብ መልከዓ-ምድር፤ የዋህና እንግዳ አክባሪ ህዝብ …ተመልክቻለሁ። ሙያዊ ግዴታዬን ለመወጣት ብዬ በስጋት የሄድኩበት ቦታ የሀገሬን ተስፋ ተረድቻለሁ። ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኜ ኢትዮጵያን ጎብኝቼ፤ ትልቅ ተስፋ ሰንቄ ተመልሻለሁ። በስጋት ሄጄ በተስፋና በትዝታ ወደ ቤቴ ገብቻለሁ። አመሰግናለሁ የሚዛን ወገኖቼ። አመሰግናለሁ የገሳ ዳልባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች። ገለታይ! አበቃሁ!
ካብታሙ አየለ (ረዳት ፕሮፌሰር፤ አርሲ ዩኒቨርሲቲ)
ኢሜይል: kabayjim8@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2015