የመንግስት ግዥና ንብረት ባለስልጣን፤ በአገር ደረጃ የግዥ ሥርዓትን መዘርጋት፣ የተዘረጋው ሥርዓት መሥራት አለመሥራቱን ማረጋገጥና ጥናት ማድረግ ብሎም ለውጦች ካሉ ማሻሻል እና በአዋጅና መመሪያ መሠረት መተግበሩን ይከታተላል። በግዥ ላይ መንግስትን የማማከር፣ በአገር ደረጃ ግዢን የተመለከቱ ስልጠናዎችን መስጠት፣ ማንዋል ግዥን ወደ ኤሌክትሮኒክስ የመለወጥ፣ ንብረትን የመቆጣጠር፣ ግዥ ላይ በሚሰጡ መደበኛ እና መደበኛ ባልሆኑ ጥቆማዎች መሰረት ኦዲት የማድረግ ሥራን ይሠራል። ግዥና ጨረታ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን በአቤቱታ ሰሚ ዳይሬክተር በኩል መስማትና ልክ እንደ ከፊል ፍርድ ቤት የቦርድ የዳኝነት ሥርዓት መስጠትም የባለስልጣኑ ዋነኛ ተግባር ነው። እነዚህን መሠረት በማድረግ ተቋሙንና አሰራሩን የተመለከቱ ጥያቄዎችን ይዘን ከባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ ጋር ቆይታ አድርገናል።
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል የተቋማት ግዥዎች በተለያዩ መንገዶች ይፈጸሙም እንደነበር ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት የሚተገበረው ከፌዴራል እስከ ክልል የተሰናሰለው የግዥ ሥርዓት በመጀመሩ ምን ማትረፍ ተችሏል?
አቶ ሐጂ፡- ለረጅም ዓመታት ግዥ የሚፈጸመው በገንዘብ ሚኒስቴር ስር ባለ አንድ ዳይሬክተር ነበር። በዚህን ጊዜ እያንዳንዱ ተቋም የየራሱ ህግ ነበረው። በኋላ ሲታይ የዓለም ግዥ አካሄድ በዚህ መልኩ ስላልሆነ በዚያው በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ከዳይሬክተር ከፍያለ ዩኒት ይዞ ተቋቋመ። በኋላ የዓለም ባንክም ሆነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ፈንድ በዓለም የሌለ አካሄድ ነው በማለታቸው፤ ራሱን ችሎ እንዲወጣና ከተጽዕኖ ነፃ ሆኖ እንዲሠራ የሚል አቅጣጫ ተቀመጠ። ይህ ብቻ አይደለም በርካቶቹ በውጭ ጫና ውስጥ ነበሩ። ለምሳሌ ቀደም ሲል ገቢዎች ሚኒስቴር ገቢ ዳይሬክተር ተብሎ በገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ነበር። ነገር ግን የዓለም ባንክም ሆነ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ፈንድ በዓለም የሌለ ተሞክሮ ነው ብለው፤ በሒደት ወደ ሚኒስቴር ደረጃ አደገ።
ብዙዎቹ ወደዚህ የደረሱት የዓለምን ተሞክሮ ወስደው ነው። ስለዚህ ይህ ተቋምም 1997 ዓ.ም የግዥ ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ተብሎ ተመሰረተ። የሚኒስትሮች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1263 መሰረት ደግሞ ባለስልጣን ሆነ። በዚህም የተጨመሩለት ኃላፊነቶችና ሥልጣኖች አሉ።
ባለስልጣን ሲባል አደረጃጀቱ ሙሉ ለሙሉ የተለወጠበት ሁኔታ አለ። በፊት ከነበረው ኃላፊነት በተጨማሪ የምርምር ሥራዎችን እንዲሰራ የታሰበ ሲሆን፤ ተጠያቂነትና ሚዛናዊነት እንዲኖር ተደርጎ የተቋቋመ ነው። ገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ በዳይሬክተር እያለ ተጠሪነቱ ለሚኒስትር መስሪያ ቤቱ ስለሆነ በዚያው ይቀራል። አሁንም ተጠሪነቱ ለገንዘብ ሚኒስቴር ነው። አሁን ግን በነፃነት ብዙ እርምጃ መሄድ ይችላል፤ የጥቅም ግጭት የሚፈጠር ከሆነ ባለስልጣኑ በራሱ የሚወስናቸው ጉዳዮች ይኖራሉ፤ ተጠሪ ስለሆነ ብቻ ህጉ የማይለውን ነገር አይሠራም።
አዲስ ዘመን፡- የመንግስት ግዥና ንብረት አስተዳደር ከኤጀንሲ ወደ ባለስልጣን ከተሸጋገረ በኋላ ተልዕኮውን እንዴት እየተወጣ ነው?
አቶ ሐጂ፡– ከባድ ነው። እዚህ አገር ላይ ሌብነት አለ ከተባለ አንዱ በየከተማው መሬት አካባቢ ያለው ሌብነት ነው። ሁለተኛው ገቢዎች አካባቢ ከታክስ አሰባሰብ ጋር ያለው ሲሆን፤ ሦስተኛው ግዥ ነው። ግዥ ሙሉ ለሙሉ ችግር አለበት ብሎ መውሰድ ይቻላል። እኛ እንደ ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ብንቋቋምም 169 የፌደራል ተቋማት አሉ። ከትልቅ እስከ ትንሽ ያለውን ግዥ ሁሉ አንቆጣጠርም።
በዋናነት እየሠራን ያለነው ማሰልጠን፣ ማብቃት፣ ኦዲት ማድረግ፤ ጨረታዎች ላይ ክርክር ሲመጣ ክርክሩን ማየት፤ ወጥቶ መገምገም ነው። ከየቦታው ጥቆማዎች ይመጣሉ፤ ጥቆማዎቹንም ያያል። ተልዕኮውን መቶ በመቶ አሳክቷል የሚል እምነት የለኝም። ምክንያቱም ሌብነት ባልቆመበት ሙሉ ለሙሉ አሳክተናል ማለት አንችልም። ነገር ግን ባለስልጣኑ በርካታ ተግባራትን አከናውኗል።
ለምሳሌ ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ላይ ጥቆማ ደረሰን። ሙሉ ለሙሉ የአገሪቱን ግዥ ሥርዓት ወደ ጎን በመተው የሚሰራበት ደረጃ ላይ ደርሰው ነበር። ከገንዘብ እና ትምህርት ሚኒስቴር ጋር ተነጋግረን ሄደን ኦዲት አድርገን ከፍተኛ ችግር አገኘንበት። መልሰን ሙሉ ኦዲት ሲደረግ ብዙ ተጠያቂነትን የሚያስከትሉ ጉዳዮች መኖራቸውን ተረዳን። አንድም ግዥ ሥርዓት ተከትሎ የተሠራ ሥራ አልነበረም። አንድ ህንፃ ማሰራት ቢያስፈልግ አንዱን ጠርቶ ማሰራት ነበር፤ ውል የለም፣ ተጠያቂነት የሚባል ነገርም የለም። በዚህ የተነሳ በርካታ ሰዎች ከኃላፊነታቸው ተነስተዋል።
መዝገብ እየተጣራ ለመርማሪ ፖሊስም አስፈላጊ ሰነዶች ተሰጥተዋል። ሰነዶቹ ተጣርተው ማለቅ አለባቸው። አንዳንዶቹ የፓርላማ አባልም ስለሆኑ ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ ለህግ ማቅረብ የግድ ይሆናል። ከዚህ ውጭ ሌሎች በርካታ ዩኒቨርሲቲዎችም አጠቃላይ በጀታቸውን እስከተወሰነ ድረስ እስከማስያዝ ደርሰናል።
አርሲ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ግዥ በጠቅላላ በትውውቅ ነበር። ያጠፉትን ማስተካከል አለባቸው ብለን አጠቃላይ በጀታቸውን ይዘናል። ወደ ሥርዓት መግባት አለባቸው። በጀት የህዝብ ነው። ደመወዝ የሚከፍለው እኮ ህዝብ ነው። መንግስት የምንለው ከህዝብ ሰብስቦ፤ መልሶ ለህዝብ የሚሰጥ ነው። በዚህ ደረጃ ብልሹ አሰራር ካለ ሙሉ ለሙሉ በጀት ማቆም ይቻላል። ከዚያም የሚመለከተው አካል ይጠራል፣ ይገመገማል፣ ይነገረዋል። ስህተቱን ካረመ በኋላ በጀቱ ይለቀቃል። በዚህ ልክ እየያዝን ደጋግመን ኦዲት አድርገን አንቀብልም ያሉን አካላት ደመወዛቸው ሲያዝ እስከ ትልልቅ ኃላፊዎች ድረስ ጩኸት ነበር። በኋላ ግን እስከ ፕሬዚዳንት ድረስ መሳሳታቸውን አምነውና ተፀፅተው ወደ ህግ የሚሄደውን ወደ ህግ በመውሰድ በጀቱ እንዲቀጥል አድርገናል።
ስልጠናም እየሰጠን ነው። ዋናው ችግሩ ዩኒቨርሲቲው የተወሰኑ አቅራቢዎች ብቻ የሚሳተፉበት ነው። ጨረታ ቢወጣም እንዴት እንደሚከላከሉት አይታወቅም፤ ግን የሚያሸንፉት የተለመዱት ናቸው። አሁን ያንን የተበላሸ አሰራር አስተካክለዋል።
አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲም በተመሳሳይ የተበላሸ አሰራር ነበረበት። የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት ፈላጭ ቆራጭ ነበር። ኮንስትራክሽን ዋጋ ላይ እራሱ ይወስናል። እንጀራ ግዢ ላይ የፈለገውን ዋጋ ይጨምራል። ግን ጭማሪ የራሱ ቀመር አለው። ማን ቀመሩን እንደሚወስን አሰራር አለ። አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የነበረው ግዥ፣ ሥነ-ምግባርና ፀረ ሙስና፣ ኦዲተር ከሥራ ውጪ ነበር። ፕሬዚዳንቱም አይሰራም፤ ምክትል ፕሬዚዳንቱ በሁሉም ፈላጭ ቆራጭ ነበር። ሰውየው አሁን በህግ አግባብ እየተጠየቀ ነው።
ሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ እንጨት ግዥ ላይ ያጋጠመን፤ እዚያው ፋይናንስ ግዥ የነበሩ አካላት ነጋዴዎች ናቸው። ስለዚህ በየቀኑ ክስ ነበር። በጣም የተበላሸ አሰራር ነበር። እዚያም የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ሰጥተን፣ ጥፋቱን የሚሰሩ ግለሰቦች ከኃላፊነት ተነስተው ተጠያቂ እንዲሆኑ አድርገናል። ለምሳሌ ጨረታ አውጥተው ያሸነፈው አካል እያለ ያላለፈውን ይመርጣሉ። በዚህ ብቻ እስከ 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር መንግስት እንዲያጣ አድርገዋል። ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ላይ የጎላ ባይሆንም እንዲስተካከል ተደርጓል።
የዩኒቨርሲቲዎች ነገር በጣም ውስብስብ ነው። ስለዚህ ስለተቋሙ ቀድመው ተንብየው መሥራት ይጠበቅባቸዋል። በወቅቱ ተገቢውን ሥራ ሳይሰሩ ቆይተው ለግዥ ድንገት ልዩ ፈቃድ ይጠይቃሉ። ልዩ ፈቃድ ደግሞ በግዥ ትርጉም አለው። ይህ ማለት ግዥው ለሆነ አካል እንዲሰጥ ፈልገዋል ማለት ነው። ይህ ካልሆነ በህጋዊ መንገድ መሥራት ይችላሉ።
ግዥ ማለት አስቸጋሪ ባህሪ ያለው ነው። ኃላፊው ከእቅድ ይነሳል። ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት 169 ከሚሆኑ የፌደራል ተቋማት ውስጥ 60 የሚሆኑት የፌደራል ተቋማት የግዥ እቅድ አላቀረቡም። አሁን የበጀት ዓመቱን ሩብ ዓመት አጠናቀናል። ህጉ የሚለው ደግሞ ቀድማችሁ እስከ ሃምሌ 30 አሳውቁ ነው። ፓርላማ የአገሪቱን በጀት ካፀደቀ በኋላ ተቋማት እቅዳቸውን ከልሰው ይልካሉ። ልክ ይህ በጀት እንደተፈቀደ ተቋማት የግዥ እቅድ ማዘጋጀት አለባቸው። ግን ብዙ ተቋማት ብድግ ብለው የግዥ እቅድ ያቀርባሉ።
ዓመቱን ሙሉ ቁጭ ብለው በመጨረሻ አካባቢ ከፍተኛ ግዥ የሚያቀርብበት ምክንያትም አንዱ በዚህ የተነሳ ነው። በዚህ ወቅት ደግሞ ወደ ጨረታ አይሄድም፤ ወደ ልዩ የግዥ ፈቃድና ውስን ጨረታ፣ ለአንዱ ቀጥታ መስጠት ወደሚለው ይሄዳል። አልፎ አልፎ የተወሰኑ ተቋማት ደግሞ እቅዳቸው እና ሥራቸው ተናቦ የሚሄዱ አሉ። በርካታ ተቋማት ግዥ የሚያካሂዱት፣ ስልጠና የሚሰጡት በዓመቱ መጨረሻ ነው። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው?
በአሁኑ ወቅት ስልጠና እየሰጠን ነው። 169 የፌደራል ተቋማት ስልጠና ሰጥተን አጠናቀናል። የግዥ ጉዳይ የሚመለከታቸውና ለምሳሌ ፋይናንስና ግዥ፣ የውስጥ ኦዲትና ለመሳሰሉት ከ5000 ያላነሱ ሰዎች ስልጠና ሰጥተናል። ስልጠናውን የምንሰጠው በመጀመሪያ ሩብ ዓመት ሲሆን፤ እውቀቱን ይዞ ዓመቱን ሙሉ እንዲሠሩ ነው። አንዳንዶች ስልጠና የሚሰጡት ዓመቱን ሙሉ ቁጭ ብለው ግንቦት ላይ ነው። ይህ ዓላማ ቢስ፣ የባከነ፣ የሌብነትና ገንዘብ እንዳይተረፍ የሚሰጥ ስልጠና ነው። ማሰልጠን ካለብንና መጠናቀቅ ያለባቸው በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የዝግጅት ምዕራፍ ወቅት መሆን አለበት።
እኛ የመጀመሪያው ሩብ ዓመት ስልጠና እንሰጣለን። በሁለተኛው ሩብ ዓመት የሰጠነው ስልጠና ውጤት ማምጣት መቻሉን ወጥተን ግምገማ እናደርጋለን። ሙስና መቀነስ አለመቀነሱን፣ የግዥ እቅድ መኖር አለመኖሩን እናያለን። የግዥ እቅድ የሌለው አካል አይስተናገድም። የገንዘብ ሚኒስቴር በጀታቸውን ሊለቅ ይችላል። አሁን ግን ደብዳቤ አዘጋጅተን እያሰራጨን ነው። ለፓርላማ፣ ለገንዘብ ሚኒስቴር የግዥ እቅድ የሌላቸው ስለሆነ በጀታቸውን ያለአግባብ የሚጠቀሙ ተቋማት ብለን እናሳውቃለን። 60 የፌደራል ተቋማት የግዥ እቅድ የላቸውም።
አዲስ ዘመን፡- በእርስዎ አባባል 60 የፌደራል ተቋማት የግዥ እቅድ የላቸውም። ታዲያ ግዥ እንዴት ይፈጽማሉ?
አቶ ሐጂ፡– እንግዲህ ኃላፊነት ከተጠያቂነት ጋር መንግስት ለእያንዳንዱ ኃላፊ ሰጥቷል። አንድ ብቸኛ ተቋም ይህን ሁሉ ተቋም እየኮረኮመ ማስተካከል አይችልም። በተለይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ የሚመሩት በሚኒስትር ነው። ግንባር ቀደም መሆን አለባቸው የእኛ አለቆች ናቸው። ሚኒስቴር ሆኖ የግዥ እቅድ ከሌለው ሚኒስቴር ነኝ ማለትም አይችልም። ለምን ከተባለ የዚህ አገር 70 ከመቶ በጀት የሚውለው ለግዥ ነው። ከ761 ቢሊዮን ብር የአገሪቱ በጀት ውስጥ 560 ቢሊዮን ብር እና ከዚያ በላይ ለግዥ ይውላል። ይህ የውስጥ ገቢን ሳይጨምር ነው። አንዳንድ ተቋማትም ከውጭ ብድርና እርዳታ የሚያገኙ አሉ፤ ይህን ሳይጨምር ነው።
የእኔም ተቋም ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ 70 በመቶ በሚሆነው በጀት ካልታቀደ ተቋም አይደለም ወደሚለው ድምዳሜ ይወስደናል። በዚህ ልክ ከፍተኛ ክፍተት አለ። ዩኒቨርሲቲዎች ሙሉ ለሙሉ እቅዳቸውን አቅርበዋል።
አዲስ ዘመን፡- ሚኒስቴር ሆኖ የግዥ እቅድ ያላቀረበ አለ?
አቶ ሐጂ፡- ሚኒስቴር ጨምሮ 60 የሚሆኑ የፌደራል ተቋማት እቅዳቸውን አላቀረቡም። ስማቸውን መዘርዘር አልፈልግም፤ ምክንያቱም ወደ ፓርላማ እና ገንዘብ ሚኒስቴር ሄዶ እርምጃ ከተወሰደ በኋላ ዝርዝሩን መውሰድ ይቻላል። እነዚህ 60 ተቋማት እቅድ አልባ ቢሆኑም ግዥ ይፈጽማሉ። ዛሬ እኮ ግለሰብ እንኳን ያቅዳል። አንድን የመንግስትን ተቋም የሚመራ ኃላፊ ግን እቅድ የለውም ማለት ምን ማለት ነው? የጠፍ ብር አይደለም፤ በዚህ ልክ ችግሮች አሉ። እንግዲህ ሁሌ ሥራ አለ፤ ችግር አለ፤ ግን ተጠናክሮ ተልዕኳችን ለማሳካት መሥራት ጠቃሚ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በመንግስት ግዥ ላይ ከሚነሱ ችግሮች አንዱም የጥራት መጓደልና በወቅቱ አለማቅረብ ነው። የችግሩ ምንጭ ምንድን ነው?
አቶ ሐጂ፡– በመንግስት ግዥ ላይ የጥራት ችግር የሚነሳው በዋናነት የሚመለከተው የግዥ አገልግሎትን ነው። በግዥ አገልግሎት ላይ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ችግር አለ። አንደኛው የችግር መነሻ እና መድረሻ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ያለው ገበያ የተረጋጋ አለመሆን ነው።
‹‹ኮመን ዩዘር አይተም›› ሲገዛ ውል የሚገባው ለዓመትና ለሁለት ዓመት ነው። ውል በሁለት ቦታ ይገባል። አንደኛው፤ የግዥ አገልግሎት ጥቅል ውል ይገባል። ዝርዝር ውል ደግሞ እያንዳንዱ ተቋም ይገባል። አቅራቢው ጥቅል ውል ከገባ በኋላ የገበያው ሁኔታ በጣም ይቀያየራል። በዚህ የተነሳ የንግድ ማህበረሰብ ፊት ለፊት መጥተው ቅጣት እንቀበላለን እንጂ ማቅረብ አንችልም ይላሉ። ለምሳሌ ነዳጅ በሊትር ከ30 ብር በአንድ ጊዜ ወደ 60 ብር ዋጋው አድጓል። ሁላችንም ለነዳጅ በጀት ይዘናል። አሁን ግን ዋጋው በእጥፍ ሲጨምር፤ ከሌላ በጀት ወደዚህ ማምጣት ሊጠበቅብን ነው። የኮንስትራክሽን ዘርፍም በዚህ ሁኔታ ትልቅ ፈተና ያለበት ነው። ግብዓቶች በጣም እየጨመሩ ነው። በዚህ የተነሳ ፕሮጀክቶችና ሌሎች ሥራዎች የሚቆሙበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው።
ሌላው በመንግስት ግዥ መጀመሪያ ናሙና ይመጣል፤ ከዚያ ይታያል። ክፍያ የሚፈፀመው በውሉ መሰረት ሲቀርብ ነው። ነገር ግን ጅቡቲ ወደብ ላይ ገዥ ካገኙ ወዲያውኑ አየር በአየር ይሸጣሉ። በዚህ የተነሳ ወደአለማቅረብ የሚሄዱ አሉ። ተሳክቶ እንኳን ቢመጣ ሌብነቶች አሉ። ለምሳሌ የደንብ ልብስ ብቻ ብንወስድ፤ በናሙና የሚወሰደውና የሚቀርበው በቀለም የሚመሳሰል ይሆንና በጥራት ከናሙናው ጋር የማይጣጣም ይመጣል። ወረቀት 100ሺ ደስታ የሚገዛ ቢሆን፤ እያንዳንዱን ነጥሎ ማየት አይቻልም። በዚህም ከጥራት በታች የሆነ ይቀላቀላል። አንደኛ ደረጃ ተብሎ ሦስተኛ ደረጃ ይቀርባል። በአጠቃላይ በዚህ ዙሪያ የጥራት እና በወቅቱ አለማቅረብ ችግር አለ።
አንዳንድ ተቋማት ደግሞ ወዲያውኑ የሚፈልጉ ናቸው። ለምሳሌ ቀለም እና ወረቀት የሚጠቀም ተቋም አቅራቢው እስኪያቀርብ ሥራውን ማቆም ስለሌለበት በግዴታ ወደ ልዩ ፈቃድ ይመጣል። በራሳችን እንግዛ የሚሉ በርካታ ጥያቄዎች ቀርበውልናል። ለምሳሌ ለዩኒቨርሲቲዎች ክፍት አድርገናል። የትምህርት ጥራትን ለድርድር አናቀርብም። ከትምህርት ጥራት ጋር በቀጥታ የሚገናኙትን ራሳቸው እንዲገዙ ለቀናል። የትምህርት ጥራት ከወደቀ አገር ይወድቃል። የዓለም ገበያ መዋዠቅ በተለይም በራሺያና ዩክሬን ጦርነት የተነሳና፣ በአቅራቢዎች በወቅቱ አለማቅረብና የጥራት መጓደል ችግሮች አጋጥመውናል።
ተቋማት ራሳችን ለምን አንገዛም? የሚል ጥያቄ አላቸው። እኛ ደግሞ በወቅቱ አለማቅረባችን ሌላው ችግር ነው። ይህን ለማቃለል ያደረግነው ጥረት ቢኖር ባለፉት ሁለት ዓመታት፤ በመጀመሪውና ሁለተኛው ሩብ ዓመት የተመደበው አቅራቢ ማቅረብ ካልቻለ፤ የግዥ አገልግሎት ራሳችሁ ፈልጋችሁ ግዙ ብለናል።
አዲስ ዘመን፡- ግዥ ለመፈፀም ሲባል ብቻ የቢሮ ወንበር፣ ቀለም እና የመሳሰሉትን በየዓመቱ የሚቀያይሩ አሉ። ይህ በግዥ ህግ ተገቢ ነው?
አቶ ሐጂ፡- ይህን ቀለል አድርገን ብንረዳው። ለምሳሌ እኔ አሁን ያለሁበት ቢሮ ከ48 ዓመት በፊት መንግስቱ ኃይለማርያም እንደ ቢሮ ይጠቀሙበት የነበረ ሲሆን፤ የጠበቀኝ በዚያን ጊዜ የነበረ ምንጣፍ ነው። ከዚያም ወዲህ አስር ኃላፊዎች የተፈራረቁበት ምንጣፍ ላይ መቀመጥ ስላልነበረብኝ እንደአቅማችን ቢሮውን ለማስዋብ ሞክረናል። በእርግጠኝነት ግን ቀጣይ የሚመጣው ኃላፊ ይህን አያፈርሰውም። በርካታ ጊዜ ያልታደሰ ቢሮ ቢፀዳ ችግር የለውም፤ ግን በጥራት ላይ ጥራት አይመከረም። የሥራ ሥነ-ምህዳርና ቢሮ አካባቢ ቢፀዳ መልካም ነው፤ ግን በጣም የቅንጦት መሆን የለበትም። ይልቅስ እያስቸገረ ያለው በተባለው ደረጃ እና ጥራት ተሰርቷል ወይ የሚለውን መመልከት ተገቢ ነው።
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ ተቋማት ግዥ ለመፈፀም በተወሰኑ ተቋማት ላይ ብቻ የሚንጠለጠሉበት አሰራርስ እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ሐጂ፡– እኔ ይህን የምረዳው በተደጋጋሚ የሚመረጡ አቅራቢዎችና ነጋዴዎች ጥቂትና የተለመዱ ናቸው የሚባለውን ከላይ ለአብነት አርሲ ዩኒቨርሲቲን አንስቻለሁ። ላለፉት ስድስት ዓመታት ግዥ በሙሉ የሚፈፀመው በሦስት ግለሰቦች የተያዘ ነው። ይህ ስህተት ነው። ዕድሉ ሰፋ ማድረግ ቢቻል ጥቅም ይገኛል። ነገር ግን በግልጽነትና በተወዳዳሪነት ብሎም ጥራትን በጠበቀ መንገድ ከሆነ ምንም ማድረግ አይቻልም።
አሁን ላይ በኮንስትራክሽን ላይ የሚስተዋለው አዘግይተውና 18 ወራት ካለፈ በኋላ ዋጋ ለማስጨመር ፕሮጀክቶችን የሚያዘገዩትንና ህዝብና መንግስትን የሚያከስሩትን በሙሉ ከሲስተም እንዲወጡ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ጋር እየሰራን ነው። በጣም ሀቀኛ የሆኑትንና በወቅቱ ያጠናቀቁትን ደግሞ ተጨማሪ ፕሮጀክት እንሰጣለን፤ ህጉን ጠብቀን። በተለይ ኮንስትራክሽን ዘገየ ማለት በጣም በርካታ ገንዘብ ያስጨምራል። ሆን ብሎ በእንዝላልነት መንግስትን ወጪ ማስወጣት ወንጀል ነው። ለአብነት በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት ፕሮጀክቶች በሙሉ ከተባለው ቀድመው የሚጠናቀቁ ናቸው። በዚያ መንገድ ፕሮጀክቶችን መምራት ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- የግዥ ሥርዓት ላይ የሚስተዋሉ ህፀፆችን ለማስተካካል ሲባል፤ ኢትዮጵያ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ጀምራለች። ይሄ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?
አቶ ሐጂ፡– ይህ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ዓለም በጣም የተጠቀመበት ነው። ይህ በየቦታው መዞርን፣ ማወቅ መተዋወቅንና ድርድርን የሚያስቀርና ቢሮ ሆኖ ማከናወን የሚያስችል ነው። በዓለም ላይ በዚህ ሥርዓት የሚጠቀሙ አገራት ከ5 እስከ 25 ከመቶ የሚሆነውን በጀታቸውን ማትረፍ ችለዋል። እኛ ሙሉ ለሙሉ ስላልጀመርን በዚህ ዓመት እቅዳችን የበጀታችንን አንድ በመቶ መቆጠብ ነው። ጨረታ የሚያወጡ ተቋማት ለጨረታ የሚያወጡት ወረቀትና ቀለም በጣም ብዙ ነው፤ በዚህ ላይ ሌሎች ደባዎች አሉ። በዚህ ሥርዓት ከቦታ ቦታ መሄድ አስገዳጅ ሳይሆን ካሉበት ቦታ ሆነው መመዝገብና መወዳደር ይቻላል። ወረቀትና ቀለም አለቀ የሚል ሰበብና የመሳሰሉትን ችግሮች ያስቀራል። የትኛውም ዓለም ክፍል ሆኖ መወዳደር ይቻላል ማለት ነው። አሰራሩ ከሙስና የፀዳ ነው። በአፍሪካ አገራት ጀምረው ስኬታማ ሆነዋል። በዚህ የተነሳ በጣም አትራፊ ነው። ግን ፈተናዎች አሉ።
አዲስ ዘመን፡- በኤሌክትሮኒክስ ግዥ የሚወዳደሩት በ‹ኦንላይን› ነው። ስለድርጅቶች ትክክለኛነት ማረጋገጫው ምንድን ነው?
አቶ ሐጂ፡– ይህ ሥርዓት ዘርፈ ብዙ ግልጋሎት የሚሰጥ ነው። ይህ ሲስተም ከንግድ ሚኒስቴር ጋር የተገናኛ ነው፤ የንግድ ፈቃድ ሙሉ መረጃዎችን የሚያሳይ ነው። በወቅቱ የሚጠበቅበትን ወቅታዊ ክፍያ ስለመክፈሉ ከገቢዎች ሚኒስቴር ጋር ተገናኝቷል፤ የባንክ ዕዳ እንዳለበትና እንደሌለበት ከባንክ ጋር የተሳሰረ ነው። ክፍያ የሚፈፀመው በቴሌ ሲስተም በኩል ነው። ደህንነቱ እንዲጠበቅና ስትራቴጂክ ቲሙን የሚመራው ደግሞ የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመዴአ) ነው። ስለዚህ በዚህ ሥርዓት የተሳሰረ በመሆኑ ለማረጋገጥ ቀላል ነው። ሌላው ቀርቶ የኤሌክትሮኒክስ ፈቃድ የሌለው አካል በጨረታው ቢወዳዳር ሲስተሙ የኤሌክትሮኒክስ ፈቃድ የለውም ብሎ ያሳያል።
ባለፈው ዓመት ዘጠኝ ተቋማት በዚህ ስርዓት ግዥ ፈጽመው፤ ስድስቱ ተሳክቶላቸዋል። በዚህ ዓመት ደግሞ 63 አዳዲስ ተቋማት ወደዚህ ሥርዓት ገብተዋል። ካለፈው ዓመት ጋር 72 የፌደራል ተቋማት ይሆናሉ ማለት ነው። የቸገረን ከሚኒስቴር ጀምሮ በለመድነው ሥርዓት እንግዛ ብለው ወደ እኛ የሚመጡ አሉ። ይህ ሃሳብ የሚመጣው ከግዥ ባለሙያ ነው። ይህ የሚደረገው በአካል የሚያገኙትን ደንበኛቸውን ማግኘት ስለማይፈቅድ ነው። እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት ደግሞ መብራት ይጠፋል፤ ኢንተርኔት ይቋረጣል በሚል ነው። እኛም በኦንላይን ግዥ፣ ጨረታ ማውጣትንና ውል ማስተዳደር የመሳሰሉትን አስመልክቶ ለተቋማት ስልጠና እየሰጠን ነው። አሁን የቀረን አቅራቢዎች ላይ ነው። እስከ አሁን 3000 የሚሆኑ አቅራቢዎች ተመዝግበዋል። በአገሪቱ ያለው አቅራቢ ከዚህ በላይ ነው።
ከታህሳስ ጀምሮ በኤሌክትሮኒክስ ሲስተም ያልተመዘገበ አቅራቢ በማንኛውም ጨረታ ላይ መሳተፍ አይችልም። ለዚህ ደግሞ ተቋማችን ስልጠና ይሰጣል። በዚህ ሳምንት 1000 አቅራቢዎችን ጠርተን እናሰለጥናለን። ከዚህ በፊትም ሁለት ጊዜ ሞክረናል፤ ግን የሚመጣው ሰው በቀጥታ የማይመለከተው ነው። ከአሁን በኋላ በየሱቁ እየዞሩ መግዛት ሙሉ ለሙሉ ያቆማል። በዚህ ሲስተም የማይደሰቱ የግዥ ሰዎች አሉ። ምክንያቱም ድሮ እንደለመዱት የሻይ ቡና የሚባል ነገር ይቀርባቸዋል። የኤሌክትሮኒክስ ሲስተም ይህን ሥርዓት ሙሉ ለሙሉ ያስቀራል።
በሁለተኛው ዙር 51 የፌደራል ተቋማት ወደዚህ ሲስተም ይገባሉ። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስተቀር በ2015 ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ወደዚህ ሲስተም ይገባሉ። ሲስተሙ በ40 ዩኒቨርሲቲዎች ይዘረጋል። በእርግጠኝነት በዚህ ዓመት መጨረሻ ከዩኒቨርሲቲዎች በስተቀር ሁሉም የፌደራል ተቋማት በኤሌክትሮኒክስ ሲስተም የሚከናወን ሥርዓት ውስጥ ይገባሉ። በመሆኑም በ2016 ዓ.ም አቅራቢዎቻችን በዚህ ደረጃ ዘምነው መገኘት አለባቸው።
አዲስ ዘመን፡- ቀድሞ የኤሌክትሮኒክስ ግዥ ስርዓት በዘረጉት ስድስት ተቋማት ምን ለውጥ ተገኘ?
አቶ ሐጂ፡– ሥርዓቱን በተገበሩ ስድስቱ ተቋማት የወረቀትና ቀለም ብክነት እንዲሁም ሙስና ቀርቷል። ብዙ ሃብት መቆጠብ ተችሏል። የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በቴክኒክ የሚመራው እሱ ነው፤ ቀደም ብሎ ወደ ሲስተሙ ስለገባ ተጠቅሟል። እቅድም የሚያቀርበው በዚህ ነው። በዚህ ዓመት 100 የሚሆኑ የፌደራል ተቋማት እቅዳቸውን ያቀረቡትም በዚሁ ሲስተም ነው። በርካታ ተቋማት ወደ ሲስተሙ ለመግባት ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ ነው። እኛም ሲስተሙን ስንተገብር ከአገሪቱ 761 ቢሊዮን ብር በጀት ውስጥ አንድ ከመቶ እናድናለን ብለን እየሠራን ነው። ከሌብነትና ንክኪም የፀዳ ይሆናል።
አዲስ ዘመን፡- ተጨማሪ ሐሳብ አልዎት?
አቶ ሐጂ፡– የክልልም ይሁን የፌደራል ተቋማት የሥራ ኃላፊዎች ግዥ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑን መረዳት አለባቸው። ግዥ ለግዥ ባለሙያ ብቻ አይተውም፤ የበላይ ኃላፊዎች ክትትልና ትኩረት ይፈልጋል። የግዥ እቅድ የሌላችሁ ተቋማት ያላችሁት ሌብነት ውስጥ ነው። የግዥ እቅድ ሳይኖር ግዥ መፈፀም ደረቅ ወንጀል ነው። ማንኛውም ተቋም ያለእቅድ ግዥ ቢፈጽም ህገ-ወጥ ነው። አጥብቀን እንከታተላለን፤ ለፓርላማም እናሳውቃለን። ገንዘብ ሚኒስቴርም በጀት መከልከል እንደሚችል እናሳያለን። ሚዲያዎችም በዚህ ደረጃ መሥራት አለባቸው። እቅድ የሌላቸውን 60 የፌደራል ተቋማት ስለምናሳውቅ መጠየቅ ይጠበቅባችኋል።
ሌላው በርካታ ተቋማት የሚያነሱት የተሽከርካሪ እጥረት ነው። አገሪቱ ያለችበት ሁኔታ ይታያል። መንግስት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ነው። ባለፈው ዓመትም በጦርነት ውስጥ ስለነበርን የመኪና ግዥ አልተፈፀመም። በዚህ ዓመት ግን አቅም በፈቀደ መጠን ግዥ ተፈፅሞ ይሰራጫል። በመጨረሻም የተቋም ኃላፊዎች ከተመደበው በጀት 70 ከመቶ ለግዥ የሚውልን ሃብት በመሆኑ ያለዕቅድ ግዥ መፈጸም ቀጥታ ሙስና መሆኑን ማስታወስ እፈልጋለሁ።
አዲስ ዘመን፤ ለቆይታችን አመሰግናለሁ።
አቶ ሐጂ፤ እኔም አመሰግናለሁ።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 23/2015