“ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር ናት፤ የባሕር በር ካላገኘች ግን ሀገር መሆን አትችልም”- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሐሙስ የመንግሥትን የ2017 የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በትናንት ዕትማችን የምክር ቤቱ አባላት ላነሷቸው ኢኮኖሚ ነክ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጧቸውን ምላሽ እና ማብራሪያዎች ማቅረባችን ይታወሳል። በዛሬው ዕትማችን በሀገር ውስጥ ፖለቲካ፣ በሰላም፤ በፀጥታ፣ በባሕር በር፤ በዲፕሎማሲ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ ይዘን ቀርበናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፦ የፀጥታ እና የሰላም ጉዳይን በተመለከተ፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሰላምና የፀጥታ ችግር ዋነኛው መንስኤ የተሳሳተ የፖለቲካ አመለካከት ነው። ስሁት የሆነ የፖለቲካ እሳቤ ውጤት ነው። ይህን በዋና ዋና ማሳያዎች ለማሳየት አንደኛው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የስንፍና ፖለቲካ የወለደው ችግር ነው። የስንፍና ፖለቲካ ተንሰራፍቷል በኛ ሀገር። በዚያ ምክንያት የስንፍና ፖለቲካ ግጭት፣ ፀብ፣ ተቃርኖን ይወልዳል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ ሰዎች ወይም ፖለቲካል ኤሊትስ የሚባሉትን በደንብ በአንክሮ ማየት የቻላችሁ እንደሆነ፤ በድሮው ዘመን መሳፍንቶች፣ መኳንንቶች እንደሚባለው ዓይነት ነው።

በድሮ ዘመን መሳፍንቶች፣ መኳንንቶች ሳትሠራ አትብላ የሚለውን መርሕ አይቀበሉም። ሳይሠሩ፣ እጃቸው አፈር ሳይነካ፣ አርሶ አደር አርሶ ካመረተው ልክ እንደ ባለመብት ይካፈላሉ። ሳትሠራ አትብላ እነርሱ ጋር አይሠራም። ከዚህ ቀደም ገበሬው ያረሰውን እጃቸው አፈር ሳይነካ፣ ጭቃ ሳይነካ እንደሚካፈሉት መኳንንቶች ናቸው፤ የዛሬ ዘመን ሰነፍ ፖለቲከኞች። ሥራ አያውቁም፣ ሥራ አይወዱም፣ ሥራ አይሠሩም። ሥራ ካልሠራ ደግሞ ሰው አልተማረም፣ መሐይም ነው ማለት ነው።

የእውቀት ዋነኛው ምንጭ ልምድ/ኤክስፔሪያንስ ነው። ክፍል/ክላስ ውስጥ ተቀምጠን የሰማነው ወሬ አይደለም፣ በሥራ ተመንዝሮ ሥራ ውስጥ የሚገኝ እውቀትና ልምድ ነው ሰውን አዋቂ የሚያሰኘው። ሥራ የማይሠሩ፣ ግብር የማይከፍሉ፣ አገልግሎት/ሰርቪስ የማይሰጡ ፖለቲከኞች በዝተዋል። እኛ ሀገር አርብቶ አደር አለ። አርሶ አደር አለ። ላብ አደር አለ። አሁን ደግሞ አውርቶ አደር ተጨመረበት።

አውርቶ አደሮች ዋና ሥራቸው አባልተው መብላት ነው። ካላባሉ አይበሉም። ካላጋጩ ትርፍ አያገኙም። ወይ ግብረሠናይ ድርጅት/ ከኤንጂኦ ደመወዝ፤ የኤንጂኦ ካልተመቸ ደግሞ የጎፈንድሚ ደመወዝተኛ ናቸው። እነዚህ ሰነፍ ፖለቲከኞች ሥራ የማያውቁ፣ ሥራ የማይወዱ፣ ሰርቪስ የማያውቁ፤ ሠርቪስ ማለት የግድ የመንግሥት ብቻ አይደለም፤ አንድ የቤተክርስቲያን አማኝ ግቢውን በነፃ ካፀዳ፤ አንድ መስጂድ የሚመላለስ ሰው ግቢውን ካፀዳ ሰርቪስ ነው፤ ሽማግሌ፣ አዛውንት ካገዘ ሠርቪስ ነው። በክረምት በነፃ ካገለገለ ሠርቪስ ነው። ምንም እጅ ምናምናቸው ንፁሕ ሆኖ ብቻ፤ ነገር ሸርክቶ መብላት ልማድ ያደረጉ ሰዎች ግጭት ካልተፈጠረ ትርፍ አያገኙም። ኮሪዶር ስህተት ነው፣ አሁን ጋዝ አውጥተናል ስህተት ነው፣ ህዳሴ ስህተት ነው፣ ምንም ትክክል የለም እነርሱ ጋር። ትክክል ኪሳቸው የሚገባ ገንዘብ ብቻ ነው። ይሄ አንዱ ስብራት ነው።

ሁለተኛው የኃይል ፖለቲካ ነው። መሻቴን፣ ፍላጎቴን፣ እሳቤዬን፣ በኃይል ማስፈጸም እችላለሁ። ክላሽ ካነገትኩ የኔ መሻት ይሳካል ብለው የሚያምኑ በሕዝብ የተመረጠን መንግሥት በኃይል እና በወሬ እናፈርሳለን ብለው የሚያስቡ፤ ኃይል በብቸኝነት የመጠቀም ሥልጣን የመንግሥት መሆኑን የማይቀበሉ፤ በመግደል መሸነፍ እንጂ ማሸነፍ እንደሌለ የማያምኑ ሰዎች ናቸው። ለምሳሌ የተከበሩ የምክር ቤት አባል የዝቋላውን ጉዳይ አንስተዋል። እንዳሉት በዝቋላ አንድ ሰው፣ አንድ አባት ተገለዋል። እየተጣራ ነው፤ ማን እንደገደላቸው። ተጣርቶም ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋ አደርጋለሁ።

እዚህ ጋር ግን ሊሠመርበት የሚገባው ሁለት፣ ሦስት ነገር አለ። አንደኛ የሃይማኖት ተቋማት የታጠቁ ሽፍቶች መሸሸጊያ ከሆኑ፤ እንደዚህ አይነት አደጋ ሊያጋጥም ይችላል። የሃይማኖት ቦታ የሃይማኖት መሆን አለበት። ሲሸሹ የሚደበቁበት ከሆነ፤ ሲከፋቸው ገድለው ሊሄዱ ስለሚችሉ ማለት ነው። ሁለተኛው የዝቋላው ምን ይገርማል። 12 ዓመት ተምሮ ፈተና ሊፈተን የሚሄድ ሰው ላይ የሚተኩሱ ሰዎች አሁን ዝቋላ አንድ አባት ቢገሉ ምን ይገርማል።

ችግሩ የግድያው መንፈስ/ስፕሪት ነው፤ ፈተና አትፈተን ብሎ የሚገድል፣ ማዳበሪያ አትውሰድ ብሎ የሚገድል፣ ትምህርት አትማር ብሎ የሚገድል ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ ካለ፤ የትም ሞት አለ ማለት ነው። “ልብ ሲያውቅ፣ ገንፎ ያንቅ” ይባላል በአማርኛው። ልባችን ያውቀዋል እኮ ነገርየውን። ምንም ድብብቆሽ አይደለም። እነማን ገዳይ እንደሆኑ ግልጽ ነው። “ልብ ሲያውቅ፣ ገንፎ ያንቅ” የሚባለው እያወቅነው የምናድበሰብሰው ጉዳይ ሲሆን ነው።

ግድያ ሽንፈት ብቻ ነው የሚያመጣው። “በመግደል አይሳካልንም” ብሎ ማመን ያስፈልጋል። እንደዚያ ካልሆነ በኃይል ፍላጎትን ማስፈጸም፣ ያው ማለቂያ የለውም፣ ዛሬ የመጣው እኔ ከሆንኩ፣ ነገ ደግሞ ታገሰ በኃይል፣ ከዛ ደግሞ አንደኛው በኃይል ይቀጥላል ማለት ነው። መቆም አለበት።

ሦስተኛው ግን አባባሽ፣ ገፊ ምክንያት ነው። አንደኛው ድህነት ነው። ሥራ አጥነቱ ስላለ በቀላሉ ወጣቱን መዘወር/ማኑፕሌት ማድረግ ይቻላል። ድህነት ካልቀነስን፣ ሥራ ካልፈጠርን በስተቀር ችግሩን ለመቅረፍ ያስቸግራል። ኋላቀርነት አለ። ኋላቀርነታችን ጥግ የለውም። ኮሪዶር ያምራል ግን ምን ዋጋ አለው ብልፅግና ነው የሠራው። ኋላቀርነት ነው ይሄ። እንኳን ብልፅግና ሌላም ሀገር መጥቶ ቁም ነገር ከሠራ ምን ችግር አለው። ጥሩ ይሁን እንጂ ሥራው። ኋላቀር እሳቤዎች እኔ ካልሆንኩ የሌላው ሰው ሥራ፣ ሥራ አይደለም ብለን ማሰብ። ዘረኝነት ፤ ሥር የሰደደ አስቀያሚ በሆነ መንገድ የሚገለጽ ማለት ነው። ዘረኝነት ልኩን ሲስት ለሰው ልጅ ፀር፣ ጠንቅ ይሆናል። ሰው መብቱ፣ ባህሉ፣ ቋንቋው፣ መከበር አለበት ጥያቄ የለውም። ያ ከተከበረ በኋላ ግን እኔ ብቻ ብሎ ሌላውን የሚያጠፋ ከሆነ፤ አደገኛ ነው።

እነዚህ እሳቤዎች የውጭ ጣልቃ ገብነት ታክሎበት፤ የኛ የባንዳነት ስሪት ደግሞ በመስፋቱ የሚያጋጥም ችግር ነው። አንደኛው የስንፍና ፖለቲካ። ሁለተኛው የኃይል ፖለቲካ፤ አባባሹ ደግሞ ድህነት፣ ዘረኝነት፣ ሥራ አጥነት፣ የውጭ ጣልቃ ገብነት እና ባንዳነት ችግሮቻችን ናቸው። ብሔራዊ ጥቅም/በናሽናል ኢንተረስት ላይ፤ አይ በዚህማ አልደራደርም የሚል ሥነ-ልቦና የሌለን መሆኑ ነው። ይሄን ያመጣው የስንፍና ፖለቲካ ነው።

ቀደም ሲል የተከበረው ምክር ቤት አባል በማኅበራዊ ድረ ገጽ ስብሰባ ያደርጋሉ፣ ሰላም እያደፈረሱ፣ ሰላም ይላሉ ለተባለው እኔ በተለየ መንገድ ነው የማየው። ባለፈው ዓመት በጣም ያስደሰተኝ የተቃዋሚዎቻችን እንቅስቃሴ በድረ ገጽ የነበረው ስብሰባ ነው። ምክንያቱም በአማርኛ መደመርን አንቀበልም ብለው መደመር በተግባር/ኢን-አክሽን (in-action/ ስላሳዩ ማለት ነው።

እኛ ያልነው እኮ የኢትዮጵያን ጉዳይ ፋኖም፣ ሸኔም፣ ወያኔም፣ ማንኛውም ሰው ይነጋገር ነው። በኢትዮጵያ ጉዳይ እንነጋገር ነው። አብረን እንሥራ ነው። ሸኔ በፍፁም አይታሰብም እንዴት ከአማራ ጋር ለመሥራት ይታሰባል ብሎ ወጋን። ከአማራ ጋር ስብሰባ ተቀመጠ። ፋኖ እንዴት ሸኔን አትገሉትም እናንተ ራሳችሁ ሸኔ ናችሁ አለ። ከሸኔ አውራ ጋር ተቀመጠ። ስብኃትን ለምን ትፈታላችሁ ብሎ ጮኸ ስብኃት ጋር ተቀመጠ። መደመር ይኸው ነው በቃ። ይህን ስብሰባ በጥሩ መንገድ ነው ያየሁት። መጠናከር አለበት። መደመር ኢንአክሽን ነው።

እነደዚህ አይነት አራምባና ቆቦ ቢሰበሰብ የገረወይና መዓት ውጤት ያመጣል ወይ ያላችሁኝ እንደሆነ ድምፅ ብቻ ነው። ምክንያቱም መጀመሪያ የሚያግባባ ነገር ያስፈልጋል። ኦሮሚያን እገነጥላለሁ፤ ኢትዮጵያን እጠረንፋለሁ፤ የሚል ኃይል በምንም ቋንቋ ተግባብቶ እንደሚሠራ አላውቅም። የሚያግባባ ጉዳይ ካለ ግን መደመር መነጋገር ጥሩ ነገር ነው። በቀና መንገድ ብናየው ከተቻለ ስብሰባውንም በድረ ገፅ እስከሆነ ድረስ ቢታገዝ ጥሩ ነው ለማለት ነው።

አንድ አደገኛ ጭልፊት በአውስትራሊያ ተገኘቷል። ይሕ ጭልፊት “firehawks” ይባላል። እዚህ በረሃ ውስጥ እሳት ሲቃጠል እነዚህ ጭልፊቶች ናቸው ከዚያ በረሃ ሄደው አንድ እሳት የያዘ እንጨት ወስደው ሌላ ቦታ እንጨቱን ጥለው ይለኩሳሉ። አይታችሁ ከሆነ በረሃ

ሲቀጣጠል ዋና እሳቱን የሚያባብሱ እነዚህ እሳት ጫሪ ጭልፊቶች ናቸው። በአውስትራሊያ የሚገኙ ናቸው። ለምን ያላችሁ እንደሆነ ልክ እንደ ሰው፣ ሰው ተደብቆ አድፍጦ አድኖ ተኮሶ እንደሚገድለው እሳት ሲለኮስ፤ እሳት ያስፋፉና ያን እሳት ሸሽቶ የሚሄድ ተሳቢ በራሪ ነገር ሲያገኙ ያድናሉ። ለመብላት ያቃጥላሉ።ተፈጥሮ በጣም ከባድ ነገር ነው።

እንደነዚህ አይነት እሳት ጫሪ ጭልፊቶች እዚህ አካባቢ አሉ። ኢትዮጵያን ስትባላና ስትጋጭ ትርፍ እናገኛለን ብለው የሚያስቡ እሳት ጫሪ ጭልፊቶች አሉ። እነሱን አውስትራሊያዎች አውቀው መከላከል ጀምረዋል። ኢትዮጵያውያንም በእኛ አካባቢ ያሉ እሳት ጫሪ ጭልፊቶችን ማወቅ ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው። ካወቅን መከላከል ከባድ ስለማይሆን ማለት ነው።

ይህ እንዳለ ግን የታሰሩ ፖለቲከኞች በተባለው በተደጋጋሚ እንዳነሳሁት ፖለቲከኛ ፖለቲከኛ ስለሆነ ብቻ የሚታሰር ከሆነ ጠያቂዎች የት ይታሰሩ ነበር። እዚህ ያላችሁት ሰው የፖለቲካ ሰው በመሆኑ ብቻ አይታሰርም። ይህን ትተን ግዴለም ለአንዳንዶች እንደረግነው ቢታይላቸውስ፤ በእርግጥ ጥፋት ነው አራት ኪሎ በጉልበት ጥሩ አይደለም፤ ተሳስተዋል ምሕረት ያድርግላቸው ዓይነት ቢባል ችግር የለውም። ጥፋት የላቸውም ከሆነ ግን ያው ፍርድ ቤት ይዞቷል ፍርድ ይጨርሰው። በዚህ አግባብ መመልከት ጥሩ ይመስለኛል።

ጥፋት የሌላቸው አድርገን እያመንን ከሆነ ነገ ለሚፈጠረው ጉዳይ አስቸጋሪ ይሆናል። በእኔ እሳቤ ከሰዎቹ መታሰር ኢትዮጵያ ምንም ትርፍ አታገኝም። ቀለብ ነው የምታወጣው። ትርፍ የለውም። ቢፈቱ ነው የሚሻለው። ግን ደግሞ ሕግ መከበር አለበት። የሕግ ሥርዓቱ ያጎደለው ካለ በዛ ቢታይ መልካም ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሰው ጋዜጠኛ ስለሆነ፤ ሰው ፖለቲከኛ ስለሆነ አይታሰርም። ወደፊትም አይታሰርም። በተቻለ መጠን የዲሞክራሲ ዓውዱ እንዲሰፋ ያስፈልጋል። ሥልጣን ካልሰጣችሁን ምን ዲሞክራሲ አለ። ስናጠፋ ካልፈታችሁን ምን ዲሞክራሲ አለ፡ ከተባላችሁ እንደዚህ ዓይነት ዲሞክራሲ ዓለም ላይ የለው።

አሁን የዓለም የዲሞክራሲ ቁንጮ አሜሪካ ነች። አይደለም! ፕሬዚዳንት ትራምፕ ዲሞክራሲ ለማድረግ ፈልገው የፕሬዚዳንት ባይደን ቡድን ካቢኔአቸው ውስጥ አልቀላቀሉም። አሸንፈው ወሰዱ። ግን ዲሞክራሲ ነው። የእኛንም በዚሁ መነፅር ማየት ነው ጠቃሚ የሚሆነው።

ለማሸነፍ በሃሳብ ልቀን ለመገኘት ብቻ ነው መሞከር ያለበት እንጂ ከተሸነፍን በኋላ ያስቸግራልና። እስረኛን በዚህ አግባብ ብንመለከት ጥሩ ነው። ሕግ ማስከበር ያስፈልጋል። ምሕረት ማድረግም ያስፈልጋል። ለሰዎች ይቅርታ ማድረግ ተገቢ ነገር ነው። እኛ መንግሥት ነን የግል ጉዳይ፤ የግል ቂም የለብንም። ሥርዓት ነው የምናስከብረው። ይቅር መባል ካለበት ይቅር እንላለን። ከጋራ ጥቅማችን ሲባል። በሕግ መጠየቅ ካለበት በሕግ እንጠይቃለን እንጂ ግለሰቦች በመታሰራቸው ምንም የሚገኝ ፋይዳ በግሌም አለ ብዬ አላምንም። መንግሥትም የሚያምንበት አይመስለኝም።

እናንተም እንደዚሁ በዛ መነፅር ባናየው ጥሩ ነው ለወቀሳም ብቻ ከሆነ ችግር አለ። በዚህ በኩል የገደሉ ሰዎች እንዴት አትጠይቁም እየተባለ በሌላ በኩል ደግሞ ግድያ የሚያፋፍሙ ሰዎች አይጠየቁ እየተባለ ያስቸግራል። ሕግ እያስከበሩ መሄድ ይቅርታ ሲያስፈልግ ደግሞ ይቅር ማለት ተገቢ ነው።

ከማኅበረሰቡ ምን ይጠበቃል ሰላምን ለማስከበር ለተባለው፤ ማኅበረሰቡ ሳይሸሽግ እንደጀመረው አንደኛ አትግደሉኝ ማለት አለበት። ሁለተኛ አትግደሉልኝም ማለት አለበት። እሱን ብቻ ሳይሆን በእሱ ስም ሰው እንዳይገድሉ አትግደሉልኝ እናንተም እትሙቱልኝ። አንደኛ ልማርበት ልጆቼ ፈተና እንዳይፈተኑ አትከልክሏቸው። የትምህርት ገበታ እንዲዘጋ አታድርጉ። ልሥራበት ማዳበሪያ እንዳይመጣ አታድርጉ። ሰላም እፈልጋለሁ። ጉዳይ ካላችሁ ተወያዩ። እኔ አሁን ነቅቻለሁ።

ለምሳሌ ኦሮሚያ ከሆነ ይህ ጉዳይ ያለው፤ ማንም ለኦሮሞ የሚያስብ ሰው ይደራጃል ምርጫ ይመጣል። ይወዳደራል። ዴሞክራሲ ነው ካሸነፈ ይወስዳል። ለአማራ የሚያስብ ሰው ይደራጃል። ይታገላል እንደእናንተ። ያሸንፋል ይወስዳል። ማጋደል አያስፈልግም ሕዝቡ ማንን እንደሚመርጥ ያውቃል። ማኅበረሰቡ ማለት ያለበት አትግደሉኝ፣ አትግደሉልኝ፤ አትሙቱልኝ ሰላም ነው የምፈለግው ነው።

ይህን በቅርቡ የአማራ ሕዝብ በግልፅ አሳይቷል። በአደባባይ ወጥቶ በቃኝ ሥራ እፈልጋለሁ። ሰላም፣ ልማት እፈልጋለሁ። አትረብሹኝ ብሏል። ይህ ለኦሮሚያው ለትግራይም፣ ለደቡቡም ለሁሉም ይመለከታል። ሕዝቡ ወጥቶ በቃኝ ማለት አለበት። የአማራ ሕዝብ ሰሞኑን ያስተላለፈው መልዕክት ለሁላችን ነው። ለእኛም ለሌላውም ነው። ልማት ሰላም እፈልጋለሁ። መንግሥትም ሥራውን ይሥራ የምትረብሹኝም አቁሙ ነው ያለው ለዚህ ደግሞ የሕዝብ ጥያቄ የከበረ ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል።

በተጨማሪ ሕዝቡ ማድረግ ያለበት ማንኛውንም ሰው ለወደፊት ምርጫ ሲመጣ በብልፅግና ወይንም በሆነ ፓርቲ ስም ተሸሽጎ እንዳይሔድ ምን ሠርተህ ታውቃለህ ግብር ከፍለሃል፣ ወይ ታማኝ ነው፣ ወይ ማንን አገለገልክ ብሎ መጠየቅ አለበት። በትንሽ ያልታመነ በትልቅ ሊታመን አይችልም። በትንሽ ያላገለገለ ፕሬዚዳንት ሲሆን ብቻ አገልጋይ ሊሆን አይችልም። አገልጋይነት የሚለመደው ከታች ነው።

እንደ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያልሠራ ሰው አሁን የፖለቲካ ሰው ሆኖ ሲያድግ ትላላቅ ልማት አይሠራም። መጠየቅ ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን ሰው ውሃ ልኩን መጠኑን እያወቀ ይሄዳል ማለት ነው። አሁን ሁሉም እንደ ድሮው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባሉን ነው። እኔ ፈላጭ ነኝ፣ ቆራጭ ነኝ፣ አድራጊ ነኝ ይላል። አንዲት ቀበሌ ላይ ቁም ነገር ሳይሠራ ማለት ነው። ይህን ሕዝቡ እየጠየቀ ማጥራት ያስፈልጋል።

እኛ ሞክረናል። በተቻለ መጠን ከተቃዋሚ ፓርቲም፣ በፓርቲ ውስጥ ከማይካተቱ ሰዎችም፣ በውጭ አገር ያሉም፣ በተለያየ ደረጃ መጥተው ሰዎች በእኛ መንግሥት ውስጥ በሥራ እንዲሳተፉ ሰፊ ሙከራ አድርገናል። በትልልቅ ቦታዎች። ያየነው ውጤት ግን ሥራ ሠርቶ የማያውቅ ሰው ምንም ብትሰጡት ያው ነው። እዚህም መጥቶ ሥራም ይዞ ሥልጣንም ይዞ ልክ በነበረው መንገድ መሄድ ይፈልጋል። ለመማር ዝግጁ የሆኑ ደግሞ ወደፊትም የተሻለ ተስፋ ያላቸው ይመስለኛል። በዚህ አግባብ ማኅበረሰቡ የራሱን ሚና ቢጫወት።

አንፃራዊ ሰላም አለ ይባላል። ይህ አንፃራዊ ሰላም የት ነው ያለው፡ ለተባለው፤ ሰላም ሁሌም አንፃራዊ ነው። አዎንታዊ እና አሉታዊ ሰላም (ፖዘቲቭ ፒስ፣ ኔጌቲቭ ፒስ) የሚባል አለ። ጥይት ባይተኮስም የሰው ልጅ እንቅልፍ የሚነሱ ብዙ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ። ሰላም ማለት ጦርነት አልቦ ብቻ ማለት አይደለም። ሁልጊዜ የሚገነባ ልንከታተለው የሚገባና ሥራ የሚፈልግ ጉዳይ ነው። ይህም ሆኖ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ አንፃራዊ ሰላም አለ ወይ ካላችሁ ቀላል ነው።

የለውጡ ጊዜ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልል ግጭት ነበር። ብዙ ሰው ሞቷል፤ ተፈናቅሏል። ዛሬ ያ ነገር የለም። አንፃራዊ ሰላም አለ ማለት ነው። ከጥቂት ጊዜ በፊት በሶማሌና በአፋር ክልል በይገባኛል ምክንያት ሰዎች ይፈናቀላሉ፤ ይጋደላሉ። ቢያንስ ዛሬ ያ ነገር የለም። አንፃራዊ ሰላም አለ ማለት ነው። አንፃራዊ ነው። ጌዲኦና ጉጂ ወንድማማች ናቸው ተጣልተው፣ ተጋጭተው ሰው ተፈናቅሏል። አሁን የለም ሰላም ነው። አንጻራዊ ሰላም አለ ማለት ነው። ይህ እኮ በዚህ ዘመን ነው ድሮ አይደለም።

ቤኒሻንጉል ክልል በጣም ብዙ የታጠቁ ኃይሎች ውጭ ሀገር ሠልጥነው የመጡ ህዳሴ እንዳይሠራ የሚፋለሙ ብዙ ነበሩ። ብዙዎቹ በሰላም ገብተዋል። በንጽጽር ቤኒሻንጉል አሁን ሰላም ነው። አንጻራዊ ሰላም አለ ማለት ነው። ደቡብ ክልል ክልል መሆን አለብን በሚል ሒሳብ በተለይ ወላይታና ሲዳማ አካባቢ ታስታውሳላችሁ የነበረውን ነገር። አሁን የለም አንፃራዊ ሰላም አለ ማለት ነው። ግጭት ሲፈጠር ብቻ ነው እንዴ ትግራይ ክልል ሙሉ ውጊያ ነበር። ከሁለት ዓመት በፊት ቢያንስ እስካሁን ባለው ሁኔታ የለም። አንፃራዊ ሰላም አለ ማለት ነው።

አማራና ኦሮሚያ በጣም ብዙ ቦታ ነበረ። አሁን ቀንሷል። አምና በነበረው ልክ ሁለቱም ጋር የለም። አንጻራዊ ሰላም አለ ማለት ነው። ለምንድነው ይህን አንፃራዊ ሰላም ማየት ያቃተን ያላችሁ እንደሆነ አንስታይን አንድ ነገር ይናገራል። “There is hard to crack prejudges than an atom” ይላል። “prejudges” የሆነ አስተሳሰብን “crack” ማድረግ “atom crack” ከማድረግ በላይ ከባድ ነገር ነው። አንዴ ሰላም የለም ብሎ ሰው ጭንቅላቱ ውስጥ ስላስገባ ፤ ሰላምን በንጽጽር ለማየት ይቸገራል እንጂ አንፃራዊ ሰላም አለ። ባይኖርማ ግብርና አያድግም ፣ኢንዱስትሪ አያድግም ፣ማዕድን አያድግም። ፍጹም/አብሶሉት ነው? አይደለም።

ሰላም አላት? የላትም። በርካታ የተፈናቀሉ ተመልሰዋል። የተፈናቀለ ሰው አሁንም አለ? አዎ አለ። ለተሠራው ሥራ እውቅና እንስጥ/ሪኮግናይዝ እናድርግ፤ ለቀረው ደግሞ ሳናካብድ፣ ሳናጋንነው በልኩ እንሠራበታለን ብለን እናስቀምጣለን። እና አንፃራዊ ሰላም አለ። የሚቀር ችግር ደግሞ አለ። አሁንም ሰዎች ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዳይገቡ የሚያደርጉ ኃይሎች አሉ። እነዚህን በተባበረ ክንድ መልክ ማስያዝ ያስፈልጋል። የእኛ የፀጥታ ተቋማት የኢትዮጵያ መከላከያ፤ የኢትዮጵያ ፖሊስ የኢትዮጵያ ደኅንነት ተቋማት እንደ ኬንያ እንደ ዑጋንዳ፣ እንደ ሩዋንዳ፣ እንደ ናይጄሪያ አይደሉም።

የኬንያ ወታደር ሌላ የውጭ ዜጋ ሀገሩን እንዳይደፍር የሚከላከል ሊሆን ይችላል። የእኛ ወታደር ማዳበሪያ አጃቢ፣ ተማሪ አጃቢ፣ የሕዝብ በዓላት አጃቢ ለማንኛውም እንቅስቃሴ በየቀኑ የማናስገባው ጉድ የለም። ደግሞ ከእኛ ብሶ እኛ እንወቅሰዋለን። ሳንከፍለው ሕይወቱን ሰጥቶ እንደሀገር እያጸናን ከእኛ ብሶ እንወቅሰዋለን። ይሄ በተወሰነ ደረጃ መታየት ያለበት ጉዳይ ነው። ከዚህ አንጻር ለውጡ ምን ፍሬ አመጣ፣ ምን አሻሻለ የሚል ጉዳይም አብሮ ተነስቷል።

የተከበረው ምክር ቤት አንድ መዘንጋት የሌለበትና ሁሌም መታወስ ያለበት ጉዳይ ኢትዮጵያ ውስጥ በገጠመን የለውጥ ሂደት እንዲህ ተቀምጠን መነጋገር በራሱ ዘንግታችሁት ነው እንጂ ኢትዮጵያ አለቀላት እኮ ተብሏል። ኤምባሲዎች እኮ ይውጡ ተብሏል፤ እረሳችሁት እንዴ? እንኳን እኛ በእስክብሪቶ ብቻ የመጣነው ቀርቶ እዚሁ ጎረቤት ሀገር እኮ ወታደር መንግሥት ቀይሮ ምን እየሆነ እንዳለ በሱዳን እናያለን።

ኢትዮጵያን ከመበታተን፤ ኢትዮጵያን ከመፍረስ ታድጓል። ኢትዮጵያን ካለችበት አዘቅት ወደከፍታ እንድትወጣ ሥራ ተጀምሯል። ብዙ ፈተናዎች አሁንም አሉ ግን ውጤቱ መዘንጋት የለበትም። ኢትዮጵያ ተርፋለች። ዛሬ ኢትዮጵያ ትበተናለች የሚል ስጋት ብዙዎቻችሁ ውስጥ የለም፤ ታውቁታላችሁ። እኔ ጋር የለም አልሰጋም። ኢትዮጵያን ለመበተን የሚያስችል ኃይል አለ ብዬ አላስብም። እዚህም እዛም ጉዳዮች ይኖራሉ ግን መበተን አይችሉም።

ወደዚህ የመጣው፤ በሪፎርም ውስጥ የሄድንበት በጣም ዋይዝ የሆነ የሪፎርም አፕሮች ነው እንጂ ብዙ ሀገራት፤ በእኛው ሰፈር፤ በእኛው አካባቢ መሰል ሥራ ጀምረው እንደሀገር እንደዚህ መነጋገር ወደማይችሉበት ደረጃ ደርሰዋል። ዛሬ ሱዳን ካርቱም ላይ እንኳን ፓርላማ ጥቂት ሰዎች ሰብሰብ ብለው መነጋገር ይችላሉ እንዴ? ሱዳን እኮ በጣም ትልቅ ሀገር አሁን ያለበት ነገር የማይገባው ሀገር ነው። እና ተርፈናል የሚለውን በደንብ ማሰብ፤ አንጻራዊ ሰላሙንም በዛው አንጻር ማሰብ ያስፈልጋል።

ትግራይን በሚመለከት ለተነሳው ፕሪቶሪያ ለትግራይ ሕዝብ እፎይታ አምጥቷል። ለትግራይ ሕዝብ ልጆቻቸውን በየቀኑ ከማጣት ታድጓል። ለኢትዮጵያ ደግሞ አዲስ ባህል ፈጥሯል። ለካ መንግሥት እያሸነፈ ማጥፋት እየቻለ ሰላም ይበልጣል ብሎ ውጊያ አቁሞ፤ ለተዋጉት ፣ ለተፋለሙት ኃይሎች መንግሥት ይሠጣል የሚል ለብዙ ሀገራት ልምድ የሚሆን፤ ለእኛም ልምድ የሚሆን አዲስ ባህል ፈጥሯል።

ከዚህ ውጭ ግን ሰርቪስን ብንመለከት ትግራይ ቴሌኮሙኒኬሽን አልነበረም፣ መብራት አልነበረም፣ ባንክ አልነበረም፣ የአየር ትራንስፖርት አልነበረም ትምህርት አልነበረም፣ ፋብሪካዎች ሥራ አቁመዋል ይሄ ሁሉ እኮ ጀምሯል፤ ትርፍ አይደለም እንዴ ስልክ የለም ማለት እኮ እዛና እዚህ ያለ ቤተሰብ አይገናኝም ማለት ነው።

ትግራይ ክልል መንግሥት አልነበረም፤ መንግሥት ተቋቁሟል። ለአንድ ክልል ለትግራይም ይሁን ለኦሮሚያ፤ ለኦሮሚያም ይሁን ለደቡብ መንግሥት አስፈላጊ ነገር ነው። መንግሥት ከፈረሰ መንግሥትን መልሶ ማደራጀት በጣም ፈተና አለበት። ደካማም ቢሆን መንግሥት ኖሮ ክፍተቱን እየሞሉ መሄድ ነው የሚያስፈልገውና መንግሥት ተፈጥሯል።

የተፈናቀሉ ሰዎችን በሚመለከት ራያ መቶ ፐርሰንት ፀለምት ተመልሷል እኮ የተፈናቀለ ሰው። ትርፍ ነው ይህም። ምን ቀረ ታዲያ ያላችሁ እንደሆነ ወልቃይት የተፈናቀሉ አልተመለሱም። ዲዲአር አልተፈጸመም። በጣም ብዙ ትርፍ ነው ፕሪቶሪያ ያለው። የቀረው ምንድነው ወልቃይት። እሱስ መመለስ አለባቸው። በተደጋጋሚ ታውቃላችሁ መንግሥት የጸና አቋም ነው ያለው። የተፈናቀሉ የእኛ ዜጎች ወንድሞቻችን ወደቀድሞ ቀያቸው መግባት አለባቸው። ለዚህ ደግሞ በሁሉም ወገን ያሉ ኃይሎች ተባባሪ መሆን አለባቸው። ዲዲአርስ? መፈጸም አለበት።

ምክንያቱም የታጠቀን ኃይል በመንግሥት በጀት ለረጅም ጊዜ ማቆየት ልማት ይጎዳል፤ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ክልሉን ይጎዳዋል። መፈጸም አለበት። ጀምረን ነበር ታውቃላችሁ አልቀጠለም። እነዚህን ሁለት ጉዳዮች አንዳንዴ የፌዴራል መንግሥት ችግር አድርጎ ለመሳል ይሞከራል። ስህተት ነው። የፌዴራል መንግሥት ትግራይ ያለውን ጉዳይ በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ከፍተኛ ፍላጎት አለው።

ትግራይ ሳትቀየር ኢትዮጵያ ብቻዋን ትቀየራለች የሚል እምነትም የለንም፤ እውነት ለመናገር። ለዛ ነው ቅድም እንደተባለው የታሰሩ እስረኞች ለመፍታት፣ ስንፈታም ያ ሁሉ ጩኸት የነበረው ሰላም ስለሚሻል ነው። አስሮ ማቆየት ስለሚከብድ አይደለም። በዚህ የሚገኝ ሰላም ካለ ዕድል ለመስጠት ነው።

በትግርኛ አንድ አባባል አለ። “ን አንጩዋ ፀኣረ ሞቷን ድሙ መጻወቲታ” ይባላል። ይሄ ምን ማለት ነው ድመት አይጥ ይዛ የምታንገላታው እሷ ጨዋታዋ ስለሆነ ነው። ለአይጧ ግን ጻረሞት ነው። ለአንዳንዶች ውጊያው ጨዋታ ሊሆን ይችላል። ለሕዝባችን ግን ጻረሞት ነው። ለአንዳንዶች ስለውጊያ እያነሱ መናገር ምንም ጉዳት የሌለው ሊሆን ይችላል፤ ስለማይሞቱ። ለወጣት ግን ጉዳት ነው። እና የትግራይ ሕዝብ እንደምታውቁት ዊዝደም ያለው ሕዝብ ስለሆነ በብዙ ምሳሌያዊ አነጋገር እነዚህን ነገሮች ሲገልጻቸው ለድመት ጨዋታና ቀልድ ለአይጥ ግን የመኖርና የመጥፋት ጉዳይ ነው በሚል ይገልጸዋል።

አሁን ትግራይ ውስጥ አንደኛ የትግራይ ሕዝብ መቶ ፐርሰንት ጦርነት አይፈልግም። መቶ ፐርሰንት ጥርጥር የለውም ይሄ። አይቶታላ ምንም ትርፍ የለውም። ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ ከዓለም አቀፍ ሁኔታ ውጪ፤ ዓለም ትግራይና ምናምን ቢዋጉ ደንታው አይደለም ብዙ ውጊያ እያስተናገደ ስለሆነ። ጆሮም የለውም ጊዜም የለውም። ዓለም ጊዜ ቢኖረው ኖሮ ሱዳንን ያዳምጥ ነበር። የዓለምን ነገር አለመገንዘብ፤ የዘመኑን የውጊያ ስልትም አለመገንዘብ፤ አሁን እንደድሮው ተራራ መያዝ ተራራ መልቀቅ ማሰብ፤ እንዳያችሁት ነው፤ ኢራንና እሥራኤልን ያዋጋው ተራራ አይደለም። ዘመኑ ተቀይሯል።

አንዳንዶች ደግሞ መንግሥት ተወጥሯል ይላሉ። መንግሥት በሸኔ በፋኖ ተወጥሯል ወታደር ስለተበታተነበት አሁን ነው ጊዜው ደግሞ የሚሉ ሰዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ታሪክ መለስ ብሎ ማየት በቂ ነው። ሶማሌ ኢትዮጵያን ስትወር ወታደር አልነበረም። እንኳን የተበተነ ወታደር አልነበረም። ጣሊያን ኢትዮጵያን ስትወር ወታደር አልነበረንም። ከበሮ ነው የነበረን። እና ኢትዮጵያ ራሷን ለመከላከል የግድ ሰልፍ የያዘ ወታደር አያስፈልጋትም። ታሪኳ እሱን አያሳይም። እኛ የተሻለ አቅም አለን ግን ያም ቢሆን ሌሎቹ በዛ መሰላት የለበትም።

ሌላው የሚያሳዝነው ጉዳይ ግን የሚያግዙን ሰዎች አሉ። የሚያግዙን ሀገራት አሉ። እንኳን እናንተን ራሳቸውን ማገዝ አይችሉም። ሞራል ቲፎዞና ማገዝ ለየብቻ ነው። ስታዲየም ተቀምጦ ማጨብጨብና ኳስ ሜዳ ገብቶ መጫወት ለየብቻ ነው። በትላልቅ ውጊያ እንኳን እንደምታዩት መደጋገፍ ችግር ሆኗል፤ እንኳን በሰፈር ውጊያ። ምክንያቱም የዓለም ኢኮኖሚ ከዓለም ተርፎ ሰው ለማገዝ የሚያስችል ነገር ብዙ የለም። እነዚህ ስሁት ግምገማዎች ናቸው። ትግራይ የሚያስፈልገው ሰላም ነው። ትግራይ የሚያስፈልገው በንግግር በውይይት ጉዳይ መፍታት ነው።

ለዚህ በተከበረው ምክር ቤት አንድ መልዕክት ማስተላለፍ የምፈልገው የሁሉም እምነት ተወካይ የሃይማኖት አባቶች እዚህ አላችሁ። ሌላ ምንም ሥራ የላችሁም በፍጥነት ትግራይ ወደ ግጭት ጦርነት እንዳይገባ ሥራችሁን አሁን ጀምሩ። ከተጀመረ በኋላ ብትናገሩ ዋጋ የለውም። አሁን ባለሀብቶች፣ ኤምባሲዎች፣ ምሑራን አሁን ውጊያ እንዳይጀመር፤ ምክንያቱም አሁን ከተጀመረ ከዚህ በፊት የምናቀው አይደለም ይበላሻል ነገር።

አሁን ሚናችሁን ተወጡ። በእኛ በኩል በትግራይ በኩል አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የለንም። ከቻልን ማልማት ነው የምንፈልገው። ትግራይ ላሉ ለትግራይ ሕዝብም ለኢትዮጵያ ሕዝብም መታወቅ ያለበት ጦርነት አያስፈልገንም። በሰላምና በውይይት ጉዳያችንን መፍታት ይቻላል። ዛሬና ትናንትና አንድ አይደለም በብዙ ነገር። እና ይቅር።

ሎሬት ፀጋዬ ከጻፋቸው ግጥሞች አንድ የሚያስደንቀኝ ነገር አለ። እንዳይነግርህ አንዳች እውነት እውነቱን ፈልቅቀህ እንዳታወጣ ደንስ ጎበዝ ደንስ ጀግና ከረባትህን አውልቅና ይላል። ለምን እውነቱን ላለማወቅ በጭፈራ ራስህን ሸውድ ነው ግጥሙ የሚለው። ጠንቀቅ ማለት ጥሩ ነው፤ ስለማይጠቅመን ከግጭት ሰብሰብ ብለን በንግግርና በውይይት ጉዳያችንን መፍታት ያስፈልጋል።

አማራ ክልልም ይሁን ኦሮሚያ ትግራይ ሌላም ክልል ልዩነት ካለ በንግግር መፍታት ያስፈልጋል። ቅድም አንድ ወንድሜ እንዳሉት ያንን ለማድረግ የሚያስችል አቅም ያለው የፓርላማ አባል ካለ ማድረግ አለበት። ሰዎች ሕግ አክብረው፤ ሕገመንግሥት አክብረው፤ ክላሽ አውርደው፤ ሃሳብ ታጥቀው እንዲመጡ የበኩላችሁን ማድረግ ይጠበቅባችኋል።

ምክክሩን በሚመለከት ሁላችሁም እንደምታውቁት ሁሌ የማይገኝ ዕድል ነው። ምክክር ኢትዮጵያ ውስጥ ሲለመን የነበረ ጉዳይ ነው። አሁን ዕድል መጥቷል እንጠቀምበት። ብዙ አጀንዳ ተሰብስቧል፤ ከፊሉ ለፖሊሲ ግብዓት ይሆናል ከፊሉ ለሕግ ማሻሻያ ይሆናል። ከፊሉን እንነጋገርበታለን። የተነሳ ሁሉ መልስ ያገኛል ማለት አይደለም። ቢያንስ የሕዝብ ጥያቄ መሆኑ ታውቆ እንወያይበታለን። ሁሉም ግለሰብ ሁሉም ፓርቲ ቢሳተፍበት ጥሩ ነው።

ትግራይን በሚመለከት ግን በፍጥነት ወደ ውይይት መገባት እንዳለበት ይሰማኛል። ምክንያቱም አንደኛ የትግራይ ሕዝብ ውይይት ያውቃል። ሁለተኛ ጉዳዮች አሉት። ፌዴራል መንግሥት ላይ የሚያነሳው አለ አማራ ላይ የሚያነሳው አለ ኦሮሚያ ላይ የሚያነሳው አለ። ያን ጉዳይ ማውጣት አለበት። ይሄን ይሄን ጉዳይ አርቁ አስተካክሉልኝ ወንድሞቼ ከሆናችሁ ይሄን ይሄን ጉዳዮች ፍቱልኝ ማለት አለበት። በዚህ ምንም አያጣም።

የመሐሉ ዘመን የተባለው ምንድነው ለተባለው የመሐል ዘመን ማለት በሽግግሩ ማጠናቀቂያና በጸናው ሥርዓት መጀመሪያ ላይ ማለት ነው። ስድስት ዓመታት

ብልፅግናን ፈጠርን፡ the biggest poletical reform በዚህ ሀገር ታሪክ ውስጥ ብልፅግናን መፍጠር በራሱ ትልቅ ነገር ነው። የነበረውን የሰፈር ፓርቲ ኮንቨርት አድርጎ ሀገራዊ ማድረግ ራሱ ትልቅ እመርታ ነው። እኛ ያደረግነውን እኮ ሌሎች አልቻሉም፤ ገና በማኅበራዊ ድረገጽ ነው ያሉት፤ አንድ መሆን አልቻሉም።

ከዛስ የተቋም ሪፎርም፤ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም፤ ኢኮኖሚ ሪፎርም እያልን የሠራናቸው ሥራዎች ከሽግግር አውጥተውን የጸና ሥራ መጀመሪያ ላይ ስላለን ነው መሐል ያልነው። ይሄኛው እያለቀ ይሄን፤ እየጀመርን ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ብዙ ድካሞች ይፈጠራሉ። የለውጥ ድካም የሚጀምረው መሐል ላይ ነው። መጀመሪያ ላይ ሁሉም ጉልበት አለው። በኋላ ያለው ነገር የሚጨበጥ የሚነካ ይሆናል። ለምሳሌ አዲስ አበባን እንቀይራት የሚለው ጉዳይ አያጣላም። አዲስ አበባን ለመቀየር ግን ማፍረስ ሲጀመር ያነጋግራል።

ቅድም እንደተባለው አብዛኛው ተነሽ ካሣ ተከፍሎታል፤ ሕጋዊ ከሆነ። ግን መቶ ፐርሰንት ምንም አይነት እንከን የለውም ሥራችን ሊባል አይችልም። ሊኖር ይችላል፤ የተጎዳ ሰው እየመረመርን እናስተካክላለን። ሰፊ ሥራ ስለምንሠራ አንዳንድ ሰው መሐል ላይ ከተጎዳ በቅንነት እየፈተሹ መሄድ ያስፈልጋል። ካለ እንደዛ አይነት ጉዳይ። ይሄን ከተሞች እንደሚያደርጉ ተስፋ አደርጋለሁ። እኔም እከታተላለሁ። አብዛኛው አካሄዳችን ግን አፍርሶ ማባረር ሳይሆን ምትክ እየሰጡ ካሣ እየከፈሉ መሄድ ነው። ሥራ እንደዚህ አይነት ችግር አለበት። ለምንድነው የመሐሉ ዘመን የሚመጣብንን ፈተና እንጠንቀቅ ያልነው፤ ባለፈው ብዙ ፈተና አይተናል፤ እንዳንለማመደው ነው። ውጊያ ይምጣ ምን ችግር አለው ባለፈው ተዋግቻለሁ እንዳንል።

የባለፈው ውጊያ ብዙ አክስሯል ሌላ ኪሳራ እንዳይመጣ ማለት ነው። ብዙ ድል አግኝተናል እኛ። ባለፉት አምስት ስድስት ዓመታት ብልፅግና ለኢትዮጵያ የሠራቸውን የኢኮኖሚ ሥራዎች ካለ ማጋነን ሃምሳ ስልሳ ዓመት አልተሠራም ኢትዮጵያ ውስጥ። ምንም ጥያቄ የለውም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ መሠረታዊ/ሲግኒፊካንት የሆነ ለውጥ አለ። ይሄ ግን እንዳያኩራራን መድረስ ያለብን ቦታ ሳንደርስ አንቆ እንዳያስቀረን። ኮሜርሻል የይቅር፣ በካፒታል የሚቆጠር የኢኮኖሚ ፍሎው ይቅር፣ ወደ ኳሊቲ እድገት እንግባ። ዕዳ ቀንበር መሆኑ ይቅር፣ ራሱ መሠረታዊ ለውጥ /ሲግኒፊካንት ቼንጅ ነው። በጣም ትልቅ ለውጥ ነው። ግን እንዳያኩራራን አልቀን እንድንሠራ ድልን ማቀድ መጠበቅ እንድንችል ነው።

መሐል ወደፊት መስፈንጠርም ያስችላል ወደኋላ ደግሞ ሊያንሸራትተንም ይችላል። ለዚህ ነው ነቅተን የመሐሉ እስረኛ እንዳንሆን ያልነው። ለምሳሌ ኖኪያ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የዛሬ 15 ዓመት ገደማ ኖኪያ በሞባይል ሽያጭ ውስጥ በዓለም 40 በመቶ ገደማ ሼር ያለው ሁላችሁም የምታውቁት ነው። እዚህ ካለን ሰዎች ብዙዎቻችን ኖኪያ ይዘን ሊሆን ይችላል። ኖኪያ ስማርት ስልክ ሲመጣ ከኛ ወዲያ ማን ምን እንዳያመጣ ነው ብሎ ሲዘናጋ ስማርት ስልክ ገበያውን እንዳለ ወስዶ ኖኪያ ሕልውናውን ለማስቀጠል/ሰርቫይቭ ማድረግ ተቸገረ። በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ፖለቲካም እንደዛው ነው። ድሮ የነበረው ሜካኒካል ፖለቲካ አሁን ያለውን ዲጂታል ፖለቲካ አልቻለውም። ልክ እንደ ኖኪያ ነው የሆኑት። እንትናን አይወድም እንትና። ያ የመጣው ለምንድነው ኖኪያ ናቸው እነዚህ ቆመው ቀርተዋል።

ስማርት ስልክ ባለበት ዘመን ራሳቸውን መለወጥና ራሳቸውን ለአዲሱ ፖለቲካ ማዘጋጀት አልቻሉም። እንደዚህ ዓይነት ችግር እንዳይገጥመን ነው፤ እኛም ከዘመን ጋር የምንዘምን፣ ዘመንን የምንዋጅ፣ አብረን የምናድግ እንድንሆን፣ ባለበት እንዳንቆም ካስፈለገ የመሐል ዘመን ፈተናን መገንዘብ ያስፈልጋል። ለዛ ነው መሐል ዘመን ላይ የተወያየነው።

ዲፕሎማሲን በሚመለከት፣ እንደተባለው ዓለም ኢተገማች በሆነ መንገድ ነው እየተጓዘ ያለው። ምንም መጨበጫ የለውም። ጠዋት ውጊያ፤ ከሰዓት እርቅ፤ ነገ ጥል ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ እንደእኛ ዓይነት ደሃ ሀገር ጥንቃቄ የተሞላበት ጉዞ ያስፈልገዋል። አንደኛ ወዳጆች አሉን። ወዳጆቻችንን መጠበቅ ያስፈልጋል። ሁለተኛ የማይወዱን አሉ። እነሱን ደግሞ ማለዘብ ያስፈልጋል።

እኛ ጉዟችን እንዴት ነው? ልክ እንደጃርት፤ ጃርት በክረምት ትቸገራለች ብርድ ያጠቃታል። ብርዱን ለመሸሽ ሲጠጋጉ የጃርት ልብስ እሾህ ስለሆነ ፈጥነው የሚጠጋጉ ከሆነ ይወጋጋሉ። ከተራራቁ ደግሞ ብርድ አለ። እንዴት ነው ብርዱንና እሾሁን አስታርቀን ክረምቱን የምናልፈው ካላችሁ ትክክለኛውን መካከለኛ እስክናገኝ ቀስ ብለን መጓዝ ነው። እንዳንወጋጋ ቀስ ብለን ልክ ስንጠጋጋና ብርዱ ሲቀንስ በዚያ መቀጠል ነው። አሁን ያለው ዲፕሎማሲ እንደሱ ነው። እንዳንወጋ፣ እንዳይበርደን ሚዛን ጠብቆ መጓዝ ይፈልጋል። ዝምብሎ ከሚጮኸው ጋር መጮህ አያስፈልግም። የዓለም ሁኔታን ደግሞ በንቃት መከታተል ያስፈልጋል። እዛ ውስጥ ብሔራዊ ጥቅም በሚያስከብር መንገድ ወዳጆቻችን ጋር ያለውን ነገር በሚያዘልቅ መንገድ በጥንቃቄ አማካኝ ስፍራችንን ሳንለቅ መጓዝ አለብን ከባድ ስለሆነ።

የእኛን ጎረቤቶች በሚመለከት ከጎረቤት ውጪ ኢትዮጵያ ሕልውና የላትም። ከኢትዮጵያ ውጪ ደግሞ እነሱ ሕልውና የላቸውም። አንዳችን ለሌላችን በጣም አስፈላጊ ነን። ይህም የወረስነው ችግር ነው። ኢትዮጵያን ስንወርሳት ድንበር አልተበጀላትም። ሁሉ ጋር አከራካሪ ነው። ሱዳን ጋር አከራካሪ ነው፣ ኤርትራ ጋር አከራካሪ ነው። ድንበር አልተበጀም። የንግድ ሥርዓት አልተበጀም። ትክክለኛ ስምምነት የለም። ኮንትሮባንድ ነው። ልክ እንደማንኛውም ዕዳ የወረስነው ነው።

ግልፅ ያለ ድንበርና ግንኙነት ኖሮን ሳይሆን ያልተፈቱ ያደሩ ጉዳዮች ነበሩ። በዚያ ምክንያት ወጣ ገባ የሚል ነገር አለ። የእኛ እምነት ልክ እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ነው። እንደችግኝ ተካይ ነው። ዛሬ በእረፍት ችግኝ ተክለናል እዚህ ቦታ። ነገር ግን የዛሬ ሦስት ወር ወጥቼ ዛፍ አልጠብቅም። ዓመት፣ ሁለት ዓመት፣ ሦስት ዓመት፣ አራት ዓመት ቆይቶ መልካም ዘር ከሆነ ጊዜውን ጠብቆ ዛፍ ይሆናል።

በእኛና በእኛ ጎረቤቶች መካከል ያለው ተግባቦት እንደዛ ነው። መልካም ዘር እንዘራለን። ለምሳሌ ቀይ ባሕር እንነጋገር ያስፈልጋል። በሰላም፣ በንግድ ሥርዓት ብለን እንናገራለን፤ እንተክላለን። መልካም ዘር ነው። ጊዜውን ጠብቆ ዛፍ ይሆናል። በግጭትና በኃይል አናደርግም። በሰላማዊ መንገድ በንግግር ይሆናል። ለምን? ለሁሉ ጥቅም። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ሰላም ካጣችና ከተጎዳች ከኢትዮጵያ ያላነሰ የእኛ ጎረቤቶች ይጎዳሉ።

አብዛኛው ኢኮኖሚ የተሳሰረ ነው። ለምሳሌ ጥቁር ገበያ የሚባለው ግማሽ ያህሉ የሚሠራው እኮ ጎረቤት ሀገር ነው። ይሄ ኢኮኖሚ ብዙ ስለሚሸከም ይጎዳል። እኛ እንዳንጎዳ እንድንፀና ግን ደግሞ እነሱን እንድናከብር ሉዓላዊ መሆናቸውን እንድናከበር ለምሳሌ፣ ኤርትራ ሉዓላዊ ሀገር ናት በግድ የኢትዮጵያ አካል እንድትሆን እኛ አንፈልግም። መብቷ ነው ሀገር መሆን። ያ ፍላጎት የለም። ጅቡቲ ሉዓላዊ ሀገር ናት። መከበር አለበት። ሶማሌ ሉዓላዊ ሀገር ናት መከበር አለበት ጥያቄ የለውም።

ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር ናት፤ የባሕር በር ካላገኘች ግን ሀገር መሆን አትችልም። ይህ በእነሱ ወገን መከበር አለበት። አብሮ ለመኖር ያለው ነገር ሰጥቶ መቀበል ነው። ይሄ ባሕር የሚመጣው በገንዘብ ነው፤ በላን ሶ አፕ ነው ንግግር ያስፈልጋል። በንግግር መሆን አለበት። ይሄ ሲሆን በዚህ ብርጭቆ ውስጥ አንድ ውሃ ሞልቼ አንድ ጠጠር ብጥልበት ይታወካል። ለምን? አነስተኛ መጠን ያለው ብርጭቆና የያዘውም ውሃ አነስተኛ ነው።

ጣና ሄጄ አንድ ጠጠር ብወረውርበት ጣና አይታወክም። የእኛ ጎረቤቶች ማወቅ ያለባቸው ኩሬና ሐይቅን መለየት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ በትናንሽ ጠጠር አትታወክም። በትናንሽ ጠጠር አትበተንም። ኢትዮጵያ ትልቅ ባሕር ናት። ትልቅ ሀገር ናት። ይሄን መገንዘብ ያስፈልጋል። ሲፈልጉ እንደሚያውኩ ማሰብ ተገቢ አይደለም። ኢትዮጵያ የሚያውካትን ተከላክላ መልማት ትችላለች። ምክንያቱም ትልቅ ናት።

ሁከቱ የሚጎዳው ኩሬዎችን ነው። ሐይቆችን አይደለም። ይህን በደምብ ተገንዝቦ ሰብሰብ ማለት ያስፈልጋል። ይሄ 130 ሚሊዮን ሕዝብ ያለው ሀገር በንፅፅር እጅግ ከፍተኛ ሀብት ያለው ሀገር ከጎረቤቶቻችን ጋር አይወዳደርም፤ የዘመነ ወታደር ያለው ሀገር፣ ቴክኖሎጂ የታጠቀ ሀገር ውጊያን አማራጭ አድርጎ ካሰበ በየትኛውም መመዘኛ ለውድድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም። ግን ውጊያ ክፉ ነገር ነው።

ለምሳሌ በኤርትራ በኩል ውጊያ እንደሚነሳ አይነት ወሬዎች ይሰፋሉ። በእኛ በኩል ግን አንዲት ጥይት አይተኮስም። ምክንያቱም እኛ ብዙ የሚያጓጓን ነገር አለ። ብዙ የሚያጓጓ ፕሮጀክት በእጃችን አለ። መሥራት እንፈልጋለን። በእኛ በኩል ውጊያ አንፈልግም። ኤርትራ ወንድም ሕዝብ ነው፣ የሱማሌ ሕዝብ ወንድም ሕዝብ ነው፣ ሱዳን ወንድም ሕዝብ ነው ተባብረን ማደግ እንፈልጋለን።

የእኛን ማክበር፤ የእኛን ሰላም መፈለግ ግን በእነሱም ወገን በዛው ምጥጥን እንዲያዩት እንፈልጋለን። ከሁሉም ጎረቤት ጋር ከሞላ ጎደል ሰላማዊ የሚባል ግንኙነት ነው የነበረን ማስቀጠል እንፈልጋለን። ባለፉት ሰባት ዓመታት ከአንድም ጎረቤት ጋር ውጊያ አልገባንም ወደፊትም አንመርጥም። ትብብር፣ ሰላም፣ ንግግር፣ ውይይት ብቻ ነው የምንፈልገው። ህዳሴ ለእኛ ብቻ አይደለም ለሁሉም ነው ያለቀው። ወደ ኤርትራ ኤሌክትሪክ ማስገባት እንፈልጋለን፣ ወደ ሱዳን ማስገባት እንፈልጋለን፣ ወደ ሶማሊያ እንፈልጋለን በጋራ ማደግ እንፈልጋልን። ይህ አስተሳሰብ የሁሉም ስሜት እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ።

በእኛ በኩል እያንሰራራን ነው፣ ልማት እያመጣን ነው፣ እያደግን ነው፤ ይሄ እንዳይበላሽብን ከሁሉም ወንድሞቻችን ጋር በሰላም መኖር እንፈልጋለን። በሰላም የማያኖር ጉዳይ ካለስ? ራሳችንን እንከላከላለን። ለዛም ብዙ የሚያሰጋ ነገር በኢትዮጵያ ወገን የለም። የተከበረው ምክር ቤት በእርግጠኝነት እንዲገነዘብ የምፈልገው፣ ኢትዮጵያ አትበታተንም። ራሷን ለመከላከል በቂ አቅም አላት። ኢትዮጵያ ትበለፅጋለች። ለመበልፀግ የሚያበቃ በቂ አቅም አላት። ኢትዮጵያ ትፀናለች። ለመፅናት የሚያበቃ በቂ አቅም አላት። ኢትዮጵያ ጠላቶች ነበሯት፤ አሏት። ዓይናቸው እያየ ግን እናንሰራራለን። አመሰግናለሁ!

በጋዜጣው ሪፖርተሮች

አዲስ ዘመን እሑድ ሰኔ 29 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You