የአሸባሪ የሕወሓት ቡድን ከሁለት ዓመት በፊት በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ከፈፀመ በኋላ ራሱን እንደ ሀገር መከላከያ መቁጠር ጀምሮ ነበር። እንደ አንድ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ራሱን በመቁጠርም በታጠቁ ኃይሎች አማካይነት ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል። ጦርነቱ ከተከፈተ ጀምሮ ‹‹የትግራይ መከላከያ ሰራዊት ነኝ›› ብሎ ራሱን የሰየመው አካል፤ የባህርዳር አየር ማረፊያን በሮኬት በመምታት አገልግሎቱ አንዲስተጓልና ከጥቅም ውጭ እንዲሆን እንዲሁም በጥቃቱ ንፁሃን ዜጎችም ሰላባ እንዲሆኑ ማድረጉ ይታወሳል።
አሸባሪው ቡድን ወደ ጎንደርም በተደጋጋሚ ሮኬቶችን በመተኮስም በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን፣ ሰብዓዊ ጉዳትም ማስከተሉ ይታወቃል። በዚህ ብቻ ሳይሆን ጎረቤት ሀገር ኤርትራን በመተንኮስም ወደ አስመራ ከተማ ሮኬት በመተኮስ ጉዳት ማድረሱ የሚታወስ ነው።
ታዲያ አሸባሪው ሕወሓት ራሱን ‹‹የትግራይ መከላከያ ሰራዊት›› ብሎ መሰየምና ህገ መንግስታዊ እንድምታው፣ ከሀገር መከላከያ ሰራዊት የዘረፋቸው የጦር መሳሪያዎችና ዕጣ ፋንታቸው፣ የሕወሓት አካሄድና ፌደራል ሥርዓቱ ላይ የደቀነው አደጋና በቀጣይ ሊያመጣቸው የሚችለው መዘዝ ብሎም መወሰድ ስለሚገባቸው መፍትሄዎች የህግ ባለሙያዎች ሙያዊ ሐሳባቸውን ይሰጣሉ።
በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር እና ጠበቃ አቶ ፀጋዬ ደመቀ እንደሚሉት፤ በአንድ ሉዓላዊ ሀገር ውስጥ በማናቸውም መስመር ሊኖር የሚችለው አንድ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አደረጃጀትና የሀገሪቱ የበላይ አመራር ነው። ከዚህ በዘለለ በአንድ ሀገር ሁለት ዓይነት አቋም ያለው የሀገር መከላከያ ይኖራል ብሎ መጠይቅ በራሱ ግራ የሚያጋባ ነው። ጥያቄውን መጠየቅ ብቻ ሳይሆን እንደዚህ የመሆን ዕድል አለው ብሎ ማሰብ በራሱ ስህተት ነው የሚል እምነት አላቸው።
በየትኛውም ሀገር አንድ የሀገር መከላከያ መኖር አለበት። በዓለም ነባራዊ ሁኔታም እየሆነ ያለውም ይኸው ሃቅ ነው። ይህም በመሆኑ በማናቸውም መመዘኛ በአንድ ሀገር የሚኖረው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱ ሉዓላዊ ጠባቂና ከጦር ኃይል ሁሉ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው። የሕወሓት ቡድን የሰሜን ዕዝን በማጥቃት የዘረፋቸውን የጦር መሳሪያዎች ይዞ የትግራይ መከላከያ ሰራዊት ብሎ ራሱን መሰየሙ በብዙ መንገድ አግባብነት የጎደለው ስለመሆኑና ከሞራልም ሆነ ከህግ አግባብ አንፃር ዋጋ ቢስ ስለመሆኑም ያብራራሉ።
የሽብር ቡድኑ የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመክፈት የዘረፈው ሃብት የመላ ኢትዮጵያን ሃብት እንጂ የተወሰነ ቡድን ሃብት አለመሆኑን መረዳት ይገባል። ይህ የጦር መሳሪያ ሲገዛ ኢትዮጵያ ከሃብቷ ላይ በመቀነስ የተለያዩ ድርድሮችን በማካሄድና ሚስጥራዊ ሰነዶችን በመለዋወጥ የፈፀመችው እንጂ ዝም ብሎ እንደተራ ሸቀጥ ከየትም የተሸመተ አይደለም። እነዚህ የጦር መሳሪያዎች እና ማሽነሪዎች ሀገርን እና ህዝብን ለመጠበቅ እንጂ ለተወሰኑ ቡድኖች ፍጆታ አሊያም ግልጋሎት የተገዙ አለመሆኑም የአደባባይ ሃቅ ነው። ዳሩ ግን በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበረው ከፍተኛ የጦር መሳሪያ ለመጠቀም እና የፌደራል መንግስቱን ለማንበርከክ ሲባል ብቻ በዝርፊያ በተገኘ የጦር መሳሪያ አንድን ቡድን ራሱን እንደ መከላከያ ሰራዊት መቁጠር አግባብ እንዳልሆነም ይገልፃሉ።
የፌደራል መንግስትም የአሸባሪ ቡድን በተለያዩ አጋጣሚዎች ወደ እጁ ያስገባቸውን የጦር መሳሪያዎችን ‹‹መልስ›› ማለት ህጋዊም ሆነ ሞራላዊ መብት አለው። ለዚህም የሚከለክለው አንዳች ነገር የለም ባይ ናቸው። ይህ የጦር መሳሪያ ሲገዛ ኢትዮጵያን ከጠላት ለመጠበቅ እንጂ በሀገር ውስጥ ያለ አንድ ቡድን ታጥቆ ሌላው እንዲያጠቃ መሆን የለበትም። ሕወሓትም ከሰሜን ዕዝ በመዝረፍ የታጠቀውን የጦር መሳሪያ ለፌደራል መንግስት መመለስ እንደሽንፈት ሳይሆን ሕግን ከማስክበር አኳያ ማየት ይኖርበታል።
እንደ አቶ ፀጋዬ ገለፃ፤ ይሁንና ‹‹መሳሪያው ለመንግስት ከመለስኩ እጠቃለሁ።›› የሚል እሳቤ ቢኖር እንኳን በፖለቲካዊ ውሳኔ የሚስተካከል እንጂ መሳሪያውን ታጥቄ ራሴንም እንደአንድ ሉዓላዊ ሀገር የጦር መከላከያ ሰራዊት በመቁጠር እሄዳለሁ የሚለው እሳቤ አግባብ አይሆንም። በማናቸውም መስፈርት ነገሮችን ለማስተካከል የሚቻለውም በጦር መሳሪያ ጋጋታ እና በጉልበት ሳይሆን ህግ፣ ፍትህ እና ርትዕን ባማከለ መልኩ መሆን አለበት ይላሉ።
ከህገ መንግስቱ አኳያ ሲመዘን ደግሞ የሕወሓት ቡድን የታጠቀው መሳሪያ እና አሁን ያለው ቁመና ለሀገር ሉዓላዊነት አደገኛ እንደሚሆን አመለካች ነው። በመሆኑም የሀገሪቱ የህጎች ሁሉ የበላይ የሆነውን ህገ መንግስት ማክበር አስፈላጊ ነው። ይህም በመሆኑ በቡድኑ እጅ የገቡ የሀገር መከላከያ የጦር መሳሪያዎችን ለሀገር ጠባቂ የሆነው አካል ወይንም ባለቤቱ መመለስ ህገ መንግስቱን ከማክበር እንጂ ከሽንፈት መቆጠር የለበትም የሚል አቋም አላቸው የህግ ባለሙያው- አቶ ፀጋዬ።
የሀገሪቱን ህገ መንግስት ዋቢ የሚያደርጉት አቶ ጸጋዬ፤ ‹‹በህገ መንግስቱ አንቀፅ 87 የመከላከያ መርሆች በሚለው መዘርዝር ሥር፤ የሀገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ሚዛናዊ ተዋጽኦ ያካተተ ስለመሆኑ፣ የመከላከያ ሚኒስትር ሆኖ የሚሾመው ሲቪል ስለመሆኑ፣ የመከላከያ ሰራዊት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ በተጨማሪ በህገ መንግስቱ መሰረት አስቸኳይ ጊዜ የሚሰጡትን ተግባራት ያከናውናል፣ የመከላከያ ሰራዊቱም ማናቸውም ጊዜ ለህገመንግስቱ ተገዥ ይሆናል፣ የመከላከያ ሰራዊት ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን ያከናውናል›› ይላሉ። ይህ ማለት ደግሞ በአንድ ሀገር ውስጥ የሉዓላዊነት ጠባቂ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ስለመሆኑ በደንብ ያስረዳል ባይ ናቸው። ታዲያ ከዚህ አኳያ መረዳት የሚቻለው የሀገሪቱን ሉዓላዊነትና ዳር ድንበር መጠበቅ በዋናነት የሀገር መከላከያ ሰራዊት እንጂ የክልሎች ዋነኛ ሚና አለመሆኑን ማጤን ይገባል። ለዚህም የፌደራል መንግስት በትጥቅና በሌሎችም የተሻለ ሆኖ መደራጀትና ሌሎችም እንደ አስፈላጊነቱ መታጠቅ የሚችሉበት አሰራር መዘርጋት አለበት። ሆኖም በማናቸውም መንገድ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የሚገዳደር አካል ከተፈጠረ ሀገር አትፀናም ይላሉ።
በሰመራ ዩኒቨርሲቱ የህግ መምህርና ጠበቃው አቶ ኑሩ መኩሪያ በበኩላቸው፤ በአንድ ሀገር ውስጥ የተለያዩ የሰራዊት አደረጃጀቶች ሊኖሩ የሚችሉበት አጋጣሚ ስለመኖሩ ይጠቁማሉ። በተለይም የፌደራል ሥርዓትን በሚከተሉ ሀገራት እንደ ተጨባጭ ሁኔታው የሰራዊት አደረጃጀቶች ይፈጠራሉ። ስለዚህ ከአንድ በላይ የታጠቀ አካል ይኖራል ወይ የሚል ሃሳብ ከመጣ አዎ ይኖራል የሚለው ሐሳብ ገዥ ይሆናል፤ ይሁንና ለምን ዓላማ እና በማን ኃላፊነት ነው የሚለው ግንዛቤና ግልጽነት ሊኖረው ብሎም ምላሽ የሚሰጠው ህጋዊ ጉዳይ ነው ይላሉ።
የፌደራል ሥርዓቱ በሚፈቅደው መንገድ ክልሎች የየራሳቸው አደረጃጀት እና የሰራዊት ግንባታ ያካሂዳሉ። ለምሳሌ የኢትዮጵያ ሕገ-መንግስት በሚፈቅደው መንገድ ክልሎች የየራሳቸውን የፖሊስ ሰራዊት አደራጅተዋል፤ ለሚፈለገው ዓላማው እየተገለገሉ ነው። ሆኖም የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት የሚጋፋ አደረጃጀት ግን አግባብነት የለውም።
ይሁንና የአሸባሪው የሕወሓት ቡድን አካሄድ በርካቶች የማያውቁትና ብሎም የሀገሪቱን ሕገ መንግስት የተቃረነ አካሄድ ነው። ይህም በመሆኑ የሌሎች ክልሎች የፖሊስ አባላት ያልታጠቁትን የጦር መሳሪያ በሰፊው የታጠቀ እና በሰው ኃይል አደረጃጀቱም ለኢትዮጵያ ስጋት በሚሆን ደረጃ የተዋቀረ ስለመሆኑ ያብራራሉ። በአሁኑ ወቅትም ኢትዮጵያ የገባችበት ቀውስ አሸባሪው ሕወሓት ተጠያቂ መሆኑንና ይህም የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የሚገዳደር አደረጃጀት፣ ሎጂስቲክስና የሰው ኃይል የማፍራትና የማሰልጠን ዕድል በማግኘቱ እንደሆነም የህግ ባለሙያው አቶ ኑሩ ያመለክታሉ።
ኢትዮጵያን በመሰሉ ሀገራት፤ የፌደራል መንግስቱ በማናቸውም ሁኔታ የበለጠ የታጠቀና የሰለጠነ መሆን አለበት። ይህም ሀገር እንደ ሀገር መቀጠል የምትችልበትን እድል ለመፍጠር ነው። በአንድ ሀገር ውስጥ ሉዓላዊነትን ለአደጋ የሚጥል አካል ወይንም የታጠቀ ቡድን መሳሪያውን መፍታት ግድ ይለዋል። በአንድ ሀገር ውስጥ የሀገር መከላከያ ሰራዊትን የሚገዳደር ሰራዊት የገነባ አካል አደገኛ ስለሚሆን፤ በማናቸውም አግባብ መስተካከል አለበት የሚል ሐሳብ አላቸው።
ሕወሓት የትግራይ ውጭ ግንኙነት በሚል አዲስ አደረጃጀት የፈጠረ ሲሆን፣ ይህም አግባብ አለመሆኑን ነው አቶ ኑሩ የሚስረዱት። በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 86 ላይ የውጭ ግንኙነት መርሆች በሚለው ሥር የኢትዮጵያ ህዝቦችን ጥቅም የሚስያጠብቅና የሀገሪቱን ሉዓላዊነት የሚያስከብር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ማራመድ፣ የመንግስታትን ሉዓላዊነትና እኩልነት ማክበር፣ በሌሎች ሀገራት ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ አለመግባት፣ የሀገሪቱን የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ በጋራ ተጠቃሚነትና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ መሆኑን እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ስምምነቶች የኢትዮጵያን ጥቅም የሚስከብሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስከብሩና የህዝቦቿን ጥቅም የማይፃረሩ ዓለም አቀፍ ህጎችና ስምምነቶችን ማክበር፣ ከጎረቤት ሀገሮችና ከሌሎች የአፍሪካ ሀገሮች ጋር በየጊዜው እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚያዊ ህብረትና የህዝቦች አቶ ኑሩ መኩሪያ ወንድማማችነትን ማጎልበት፣ በሀገሮች መካከል የሚነሱ ግጭቶች ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት ማድረግ ሲሆን፤ ይህንን በዋናነት የሚመራው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይሆናል። ዳሩ ግን አሸባሪ ሕወሓት ትግራይ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ ግዛት አካል ሆና ሳለ የትግራይ የውጭ ግንኙነት ብሎ መመስረቱም አግባብነት የጎደለውና ቡድኑ ለህጎች የማይገዛ ስለመሆኑም ያብራራሉ።
አሸባሪው ሕወሓት በበርካታ ምክንያቶች አመጣጡና አካሄዱ አደገኛ ነው። በመሆኑም በቀጣይም የፌደራል መንግስት ብቻ መታጠቅ ያለበትን መሳሪያ ሕወሓት ታጥቆ መቀጠል አይችልም። ይሁንና ግን አሸባሪ ቡድን ክላሽና ቀላል መሰል መሳሪያዎችን መፍታት አለበት ብሎ መከራከር ውሃ አይቋጥርም፤ ምክንያቱ ደግሞ እነዚህን የመሰሉ መሳሪያዎችን አርሶ አደሩ እጅም ገብተዋልና ነው። ሆኖም የሚታጠቀው የጦር መሳሪያ መጠንና ዓይነት ሊወሰንለት እንደሚገባም ነው የሚያስረዱት። ይህም በህግና በአዋጅ የሚደነግግ መሆን እንዳለበት ያስረዳሉ። የሕወሓት አደገኛ አመጣጥና አካሄድም በሌሎች ቡድኖች እንዳይደገም የፌደራል መንግስት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም ይመክራሉ።
ምሁራኑ እንደሚሉት፤ በአንድ ሀገር ውስጥ የተለያዩ የሰራዊት አደረጃጀት ቢኖርም የሀገር ዳር ድንበርን በመጠበቅና ሉዓላዊነት በማስከበር ረገድ በዋናት ኃላፊነቱን የሚወስደው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ነው። ይህ በመሆኑም በአንድ ሀገር በበላይነት የሚደራጀው የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሚያደራጀው የሰው ኃይል፣ የሚሰለጥንበት ታክቲክና ክህሎት፣ የሚመደብለት በጀት፣ የሚፈጽማቸው ተልዕኮዎች ብሎም የሚሰጠው ኃላፊነት የላቀ ይሆናል። ይህንንም በዋናነት የሚፈጽመው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ይሆናል።
በርካታ ሀገራትም ይህን በህገ መንግስታቸው፣ በመንግስታቸው አሰራርና በአስተዳደራቸው በህግ፣ አዋጅ፣ በመመሪያ ይደግፉታል፤ ይተገብሩታልም። ይሁንና ከዚህ በዘለለ የሀገሪቱን ሉዓላዊ ሀገርን የሚገዳደር ኃይል የተፈጠረ እንደሆነ ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ ጥሰቶች ከመፈፀምና ከመበራከት በዘለለ ሽብርተኝነትና ያልተረጋጋ ሀገር የሚፈጥር ይሆናል የሚል ምክር ሐሳብ አላቸው። በመሆኑም የሀገር ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ በአንድ ሀገር ውስጥ መኖር ያለበት አንድ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ብቻ መሆን አለበት ባይ ናቸው።
ክፍለዮሐንስ አንበርብር
አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2015