ጉዳዩ አዲስ መሳይ እየሆነ እንጂ የምሩን አዲስ ሆኖ አይደለም። እንደው ለደንቡ ያህል እናንሳው እንጂ ችግሩ መቼም የማይፀዳ፤ ታጥቦ ጭቃ ነገር ነው። ሁሌ ወደ ኋላ፤ ተራመደ ሲሉት እንደ በሬ ሽንት የኋልዮሽ ይንገዳገዳል። ”ምኑ?” ለምትሉ፣ የምዕራባዊያኑ ተግባርና ደባ።
እንደሚታወቀው አሁን አሸባሪው ትህነግ የለም። አለ ከተባለም ያለው በአንዳንድ ወገኖች መንፈስ ውስጥ ብቻ ነው። እውነቱ ይህ ከሆነ፣ እሱ በሌለበት ስለ እሱ ህልውና የሚጨነቁ መኖራቸው ከምን የመጣ ነው ብሎ ማለት ይቻላል? ባጭሩ ማለት የሚቻለው ኢትዮጵያን የማጥቃት ግልፅ (ድሮ ድብቅ ከሆነ) አጀንዳና በዘመናዊ ቅኝ አገዛዝ ስር ለማድረግ ያለመ፤ ያፈጠጠ ቂልነት የወለደው ስግብግብነት ነው።
ይህንን ስንል ዝም ብለን አይደለም። አሜሪካ መራሹ ምእራቡ አለም ምን ያህል፣ በተቀነባበረና በተናበበ አሰራር በኢትዮጵያ ላይ እያካሄዱት ያለውን ከስም ማጥፋት የዘለለ የማጥቃት ተግባር እንዳለ ስለምናውቅ ነው። ይህንን መሬት ለማስረገጥ በዚሁ በኦክቶበር ብቻ ከተደረጉት የተወሰኑትን ብቻ እናንሳ።
በተቀነባበረና በተናበበ … ሁኔታ፣ በአገራትና ትላልቅ ተቋማት (ከመስራቾቹ አንዷ በመሆን የመሰረተችው የተባበሩት መንግስታት ሳይቀር) ከሚሰሩት በባሰ በሚዲያው (ሚዲያው የእነሱ አንደበት መሆኑ ቢታወቅም) እየተሰራ ያለው የከፋ ነው።
በሚዲያው ከተሰሩት ፀረኢትዮጵያ እንቅስቃሴዎች መካከል The New York Times (October 9 2022), The Chicago Tribune (Oct. 2022) – በዚሁ እለት፣ ከዚሁ ጋዜጣ ጋር በተናበበ መልኩ ”ሪፖርት” ያለውን የለቀቀው The Crisis Group, The Guardian (Oct. 23 2022) – ይህም ሌላው የሪፖርቱ ግልባጭ ነው፤ አሁን በዚሁ ሰሞን ደግሞ Forbs, ussanews እና ሌሎችንም መጥቀስ ይቻላል (በእነ newsnow የሚለቀቀው ሳይረሳ ማለት ነው)።
የዚህ ጽሑፍ አላማ የእነሱን ከሁሉ ነገሩ ጋር የተጣላ ትርክት እዚህ መድገም ባለመሆኑ የእነሱን በዚሁ ትተን ስለ ነበረው፣ የተካሄደው ጠርነት አንዳንድ ጉዳዮችን እናንሳ። እርግጥ ነው፣ ዛሬ እንዲህ በሰፈረው ቁና ሊሰፈር፣ ወደ ጦርነት ዘሎ የገባው አሸባሪው ትህነግ ነው። ያቅራራውም ቡድኑ ነው። በመከላከያ ላይ የለሌ ጭካኔን ተግባራዊ በማድረግ ወደ ለየለት የአገር ክህደትና ጦርነት የገባው እሱው ነው።
አገርና ህዝብንም አሳልፎ ለባእድ የሰጠውም፤ የዚህ ሁሉ ወጣት፣ ሴቶችና ህፃናት ደም ይፈስ ዘንድ ምክንያቱ ይኸው ቡድን ነው። በመከራ የተሰራ ሀብትና ንብረት ይወድም ዘንድ እሳቱን የለኮሰው እሱው ነው። ይሁን እንጂ ከላይ የጠቀስናቸውም ሆኑ መሰሎቻቸው እየካዱት ያለው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ፣ በቻሉት ሁሉ ቡድኑን ነፃ ለማድረግ ነው።
”ለመሆኑ ጦርነቱ በማንና በማን መካከል ነበር?” ብለን እንጠይቅና ለእነሱ ግልፅ በሚሆን መልኩ (የሚያውቁት ቢሆንም) መልስ እንስጥ። ከዛሬ ጀምሮ ጨርሰው ይፋቱን ዘንድም እንነገራቸው። አለመታደል ሆኖ ጦርነቱ በአንድ እናት ልጆች መካከል መካሄዱ ይታወቃል። የአንድ እናት ልጆች ይሁኑ እንጂ የተነሱበት አላማ ፍፁም ተቃራኒ ሲሆን የተቃርኖው ማእከልም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ናቸው። ባጭሩ፣ ኢትዮጵያን የማፍረስ እኩይ ዓላማ እና ኢትዮጵያን የማዳን ዓላማ ባነገቡ ሀይሎች መካከል ነው።
ጦርነቱ የነበረው በአገር ወዳዶችና አገር ጠሎች መካከል ነው። ጦርነቱ የነበረው በሽብር ቡድኖችና ፀረሽብር ቡድን መካከል ነበር። ጦርነቱ የነበረው የህግ የበላይነት ይከበርና አይከበር በሚሉ ወገኖች መካከል ነው። ጦርነቱ የተጀመረው ስልጣን በዲሞክራሲያዊ መንገድ መሸጋገር አለበትና የለበትም በሚሉ አካላት መካከል ነው።
ጦርነቱ የማህበረሰቡን እሴቶች ድምጥማጣቸውን ካላጠፋሁ በሚሉና የለም ንክች አታደርጋትም በሚሉ ወገኖች መካከል ነው። ጦርነቱ በአገር ግንባታ ተግባር ላይ በተሰማራ አካልና በአገር ማፍረስ ተግባር ላይ በተሰማሩ አካላት መካከል ነበር። ውጊያው የከፋፍለህ ግዛው ፖለቲካን በማራመድና ባለማራመድ፤ በማስቀጠልና ባለማስቀጠል መካከል ነበር።
ጦርነቱ የሩዋንዳውን ኢንተርሀምዌይ በኢትዮጵያ መድገም በሚፈልግና የለም አታደርጋትም በሚሉ ሀይሎች መካከል እንደ ነበር አሳምረው የሚያውቁት ምእራባውያን፣ የተለመደውን ”አሳስቦኛል …”፣ ”ከንክኖኛል …” ማለትን እንኳን በመተው ጭራሽ ሁሉም ነገር ወደ ነበረበት እንዲመለስ እየፈለጉ ነው ያሉት።
ጦርነቱ ዲሞክራሲያዊ ስርአትን በመገንባትና ባለመገንባት፤ የአገር ሉአላዊነትን በማክበር፣ ማስከበርና ባለማክበርና ባለማስከበር መካለል ነበር ሲካሄድ የነበረው። በመሆኑም፣ አገርን በማዳን ተግባር ላይ የተሰማራው ሀይል አሸነፈ። ይህ ደግሞ የነበረ፣ ያለና የሚኖር እንጂ ዛሬ የሆነ፣ ድንገት መጥቶ አይደለም። ከላይ የጠቀስናቸው የምእራቡ ዓለም ሚዲያዎችም ሆኑ እነ ብሊንከን፣ ሳማንታ ፓወርና ቡድናቸው፣ የአውሮፓ ህብረት፣ ዩኤን … ያልተገነዘቡት ይህንን ነው።
ጦርነቱ ደካማ መንግስት በመፍጠርና ጠንካራ ስርአትን በማስቀጠል መካከል የነበረ መሆኑን ጠንቅቀው የሚያውቁት የምእራቡ ዓለም ሚዲያና ባለ ስልጣናት ልክ እንዳላወቁ ሁሉ፣ ዛሬም፣ ለሌለው አሸባሪው ሕወሓት ወገባቸውን አስረው ለሌላ እስትንፋሱ ይፀልያሉ፤ ለተዝለፈለፈ ጉልበቱ መቅኔ ለመሆን ይታትራሉ።
“የአገር መከላከያ ሠራዊት ዋንኛ ተልዕኮ የሽብር ቡድኑን ወታደራዊ አቅም ማዳከምና ቡድኑ ሰብዓዊ ጋሻ ያደረጋቸውን ንጹሓን ዜጎች ነጻ ማውጣት ነው” የሚለውን የመከላከያ መግለጫ እንኳን መስማት አይፈልጉም። ይህ መግለጫ እነሱ ጋ ሲደርስ ዘር ማጥፋት ሆኖ ቁጭ ይላል። እራሳቸው ያስገቧቸውን ከ5 ሺህ በላይ ትራኮች ረስተው (ቡድኑ ለጦርነት ማዋሉ አንድ ጉዳይ ሆኖ) እርዳታ ማድረስ እንኳን አልተቻለም በማለት መክሰስን ስራዬ ብለው ተያይዘውታል።
የመከላከያ መግለጫም የሚነግረን ይህንኑ ሲሆን፤ ጉዳዩንም እንደሚከተለው ነበር ያስቀመጠው፤ ”ሽብር ቡድኑ ንጹሓን ዜጎች ጉዳት ደርሶባቸዋል በሚል በርካታ ያቀናበራቸው ሐሰተኛ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማስረጃነት መገኘታቸው ይፋ መደረጉን ሊቀበሉ አልፈለጉም። አሸባሪው ትህነግ ንጹሓን ዜጎችን አደጋ ላይ በመጣል ሐሰተኛ ተጎጂዎችን በመፈብረክ በርካታ ያቀናበራቸው ሐሰተኛ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማስረጃነት መገኘታቸውን” እያዩ አለማየትን፤ እየሰሙ አለመስማትን የመረጡ ሲሆን፣ የተሻለ ሆኖ ያገኙት ግን አሁንም ኢትዮጵያን ማፍረስ ላይ መጠመድን ነው።
ይህ ሁሉ አይቶ እንዳላየ ሰምቶ እንዳልሰማ፤ መገለጫው ብዙ ቢሆንም፤ እኛ ግን ለራሳችን ጉዳይ በቂና ከበቂ በላይ ስለሆንን የራሳችንን ጉዳይ ለራሳችን ተውልን ! ተውን !!! (Leave US alone!!!)
ግርማ መንግሥቴ አዲስ ዘመን ጥቅምት 22/2015