የሰሞኑ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና “ግሩም!” በሚባል ስኬት ተከናውኖ የተጠናቀቀው ከጥቂት ቀናት በፊት ነው። አዲስ ዓይነት አደረጃጀት፣ ሎጅስቲክና አተገባበር በተዋወቀበት በዚህ ዓመቱ ብሔራዊ ፈተና ላይ የመቀመጥ ዕድል ያጋጠማቸው ልጆቻችን ቁጥር ከዘጠኝ መቶ ሺህ በላይ እንደነበረ በኦፊሻል ሪፖርት ተረጋግጧል።
የአስተባባሪዎቹን፣ የፈታኝ መምህራኑን፣ የድጋፍ ሰጭ ባለሙያዎችን፣ የፀጥታ ክፍሉን ባልደረቦች፣ የየክልሎቹንና የየዩኒቨርሲቲዎቹን የሰው ኃይል ቁጥር አንድ ላይ እንደምር ካልንም በፈተናው ጅረት ውስጥ ያለፈው ሠራዊት በሚሊዮኖች የሚገመት እንደሚሆን ለማመን አይከብድም። ልጆቻችን የወረቀት ፈተናውን ሲወስዱ የተቀሩትና በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩት የዘረዘርናቸው ድጋፍ ሰጭዎች ደግሞ ችግሮች እንዳይፈጠሩና ፈተናው በሰላም እንዲጠናቀቅ በተግባርና በሃሳብ ሲፈተኑ መክረማቸው የሚዘነጋ አይደለም።
የፈተና ሥርዓቱን በተሳካ ሁኔታ የመሩትና ያስፈጸሙት የትምህርት ሚኒስቴር መ/ቤት፣ የፀጥታ አካላትና ባለ ድርሻ ተቋማት በሙሉ የአኩሪው ውጤት ተጋሪ ናቸውና ዘግይቶም ቢሆን ከግለሰብ ዜጎች ምሥጋናና አድናቆት ቢዥጎደጎድላቸው ዘግይቷል አያሰኝም። እንደ ወላጅም እንደ ዜጋም ለልጆቻችን ከፍታ የደከሙልንን ሁሉ ክብረት ይስጥልን እንላለን።
በማኅበራዊና በተፈጥሮ ሳይንሶች ተለይቶ የተሰጠው የዚህ ዓመቱ የብሔራዊ ፈተና መርሃ ግብር በስኬት ተጠናቋል ቢባልም መቶ በመቶ ከተግዳሮት ነፃ ነበር ማለት ግን አይደለም። በዚህ ርዕስ ሥር ደግመን የማንከልሳቸው የተወሰኑ ችግሮች አጋጥመው እንደነበር በሚመለከታቸው ተቋማት በኩል በግልጽነት ሲነገር ሰንብቷል። አዳዲስ አሠራሮችን ሁሌም ለመተግበር ሲሞከር ተገማችና ያልታሰቡ ተግዳሮቶች እንደሚገጥሙ የሚጠበቅ ነው። የችግሮቹን ዝርዝርና ስፋት በተመለከተ የዋነኞቹ ተቋማት መሪዎች ሲገልጹ ስለሰነበቱ የተባለውን መልሰን በመድገም አንባብያንን ለማሰልቸት አንሞክርም።
ይህንን የመንደርደሪያ ሃሳብ የምንደመድመው በምሥጋና ብቻ ሳይሆን የሚኖረውን ታሪካዊ ፋይዳ በማስታወስ ጭምር ይሆናል። በዚህ ዓመት የተጀመረው አዲስ የብሔራዊ ፈተና አሰጣጥ ተሞክሮ በሀገራችን ታሪክ የመጀመሪያ የሚባልለት መሆኑ በራሱ ስኬት ይመስለናል። የውጤቱ አንድ አካል ሆኖ መቆጠሩ ብቻም ሳይሆን የወጣኞቹና አስፈጻሚዎቹ ግለሰቦችና ተቋማትም መልካም የታሪክ ተናጋሪዎች መሆናቸውን በመጠቆም ወደ ዋናው ሃሳባችን እንዘልቃለን።
ፈተኟ ተፈታኝ፤
የልጆቿ ብሔራዊ ፈተና ከጉልህ ሳንካ በጸዳ መልኩ በስኬት እንዲጠናቀቅ አንጡራ ሀብቷን ያለ ስስት ሆጨጭ አድርጋና መድባ ዜጎቿንና ተቋማቷን በገፍ በማንቀሳቀስ የልጆቿን ዕውቀት ስትመዝን የሰነበተችው ኢትዮጵያ እርሷ ራሷ በርካታ ብሔራዊ ፈተናዎችን በመጋፈጥ ላይ ያለችው ጥርሷን ነክሳ ስለመሆኑ በሚገባ ይታወቃል። የፈተናዋ ግዝፈትም ልጆቿ ከወሰዷቸው የትምህርት ዓይነቶችና ብዛት በእጅጉ የተወሳሰቡ ባህርይ ያላቸው ናቸው።
እንደ ልጆቿ የአካዳሚክስ ፈተና የእርሷ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች በቀናት ዕድሜ ውስጥ ይጠናቀቃሉ ተብሎ አይጠበቅም። በቀላሉ ለማስረዳት እንዲቻል ወቅታዊውን የሀገሬን ዋና ዋናና ጉልህ የብሔራዊ ፈተና ዓይነቶች “ተፈጥሮና ማኅበራዊ” ተብለው ከተለዩት የተማሪዎቻችን የፈተና ምደባዎች ጋር ሙሉ ለሙሉ ባይመሳሰሉም እያቀራረብን ለማሳየት እንሞክራለን።
ሀ. የማሕበራዊው ዘርፍ ብሔራዊ ፈተናዎቿ፤
አሸባሪው ትህነግ በከፈታቸው ሦስት ያህል ጦርነቶች ምክንያት የሀገሪቱ ሕጋዊና ሥርዓታዊ መዋቅር በብዙ መልኩ መፈተኑ አሌ የሚባል አይደለም። በተለይም በቀዳሚነት የሚጠቀሰውና ቁጥሩ ይህን ያህል ይሆናል ተብሎ ለግምት የሚያዳግተው፤ ከዚህም ሆነ ከዚያ በጦርነቱ ምክንያት የሺህ ምንተ ሺህ ንጹሐን ዜጎችን ሕይወት መቅጠፉ ዋነኛው የወቅቱ የብሔራዊ ፈተናዋ ማሳያ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል።
ዛሬም ድረስ ከተፋላሚዎቹ ወገንና ከንጹሐን ዜጎች ሞቱ ይቀንስ ካልሆነ በስተቀር ሙሉ ለሙሉ ቆሟል ለማለት ያዳግታል። በአጭሩ ለማለት የሚቻለው አሸባሪው ቡድን በጦር ሜዳ እና እርሱ የሚጋልባቸው አጋሰስ የጫካ ቅልብተኞቹ በበቀልና በእኩይ የግፍ ተግባሮቻቸው በአንዳንድ ክልሎች ውስጥ እጃቸውን በንጹሐን ደም እየበከሉ መሆናቸው የሀገራዊ ፈተናውን ውስብስብነት በግልጽ የሚያመላክት ነው።
በዕቡይና በእኩይ ባህርይ አገንግነው በንጹሃን ደም የሰከሩትና የባሩድ ሽታ ወደ አውሬነት የለወጣቸው ግፈኞቹ “የቃየን ወራሾች” የንጹሐንን ነፍስ ከመቅጠፍ ጎን ለጎን በቢሊዮኖች ብር የሚገመቱ የመንግሥትንና የግለሰቦችን ንብረት አውድመዋል፤ በወረራ በያዟቸው አካባቢዎችም በቀላሉ የማይጠግግ የሥነ ልቦና ቀውስ አድርሰዋል። ሕጻናትና አዛውንት እናቶችን ሳይቀር በጭካኔ ደፍረዋል፤ አዋርደዋል። ምናልባትም በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ግፍ በአንድ ሀገር ክልል ውስጥ “ዜጎች” በሚባሉ አውሬዎች መፈጸሙ ታሪኩን ልዩ ሳያደርገው አይቀርም።
ከትግራይ እናቶች ጉያ ሥር ልጆቻቸውን በመንጠቅ የሚፈጽሙት የጭካኔ ግፍ አልበቃ ስላላቸውም የሕዝቡን አእምሮና ስሜት በውሸት ትርክትና ፕሮፓጋንዳ በክለዋል። በአንዳንድ ክልሎች “በነፃ አውጭ” ስም ባደራጇቸው አጋሰሶቻቸው አማካይነትም ብሔራቸው እየተለየና በራሳቸውም ወገኖች ሳይቀር የፈጸሙትንና እየተፈጸሙ ያሉት ጭካኔ የተሞላባቸው ድርጊቶች መጠናቸውም ሆነ ዓይነታቸው ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ደግመን እናስምርበትና ሀገሪቱ እየተፈተነችበት ያለው ውስብስቡ የብሔራዊ ፈተናዋ ቁስል ይህንንና ይህንን ይመስላል።
በጦርነቱ እየወደመ ያለው የገንዘብና የቁሳቁስ ሀብት፣ ሀገራዊው ኢኮኖሚ እንዳይረጋጋና እንዳይረጋ በጨለማ እየተፈጸመ ያለው የኅሊና ቢስ ዜጎች ሴራና ተንኮል ሌላው የማሕበራዊ ፈተናዋ አንዱ ተግዳሮት ነው። ገበያው ጨርቁን ጥሎ ማበዱ፣ የዕለት ጉርስ ለዜጎች ፈታኝ የሆነ ደረጃ ላይ መድረሱ፣ የኑሮ አቀበት ከፍታውን ጨምሮ በዜጎች አቅም የማይገፋ መሆኑ፣ በፍትሕ ሥርዓቱ ውስጥ የሚስተዋለው ዳተኝነትና መጓተት፣ በተለያዩ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሕዝቡን ለእንባና ለምሬት የሚዳርጉት ዘርፈ ብዙ ብሔራዊ ፈተናዎችም ወዘተ. እጅግ ሥር የሰደዱ ናቸው።
በብሔርና በጎጥ ወይንም በአፍቃሬ ራስነት የታጠሩት የፖለቲካ ልክፍተኞች ያልሰከነ አይዲዮሎጂና ጥያቄ፣ “የማሕበራዊ አንቂ” የሚል ስያሜ ለራሳቸው በሰጡ ሳይሞቅ ፈላ “የዘመን እንኩሮዎች” እየተፈጸሙ ያሉት ሁከቶችና መዋከቦችም ዜጎችን ከግራና ከቀኝ እየናጡ እረፍት ነስተዋል። ኢትዮጵያ በዚህም መስክ ፈተናዋ ተጠናቆ አልቋል ማለት አይቻልም። እነዚህ የውስጥ እባጮችና ህመሞች ለሀገሪቱ እንደምን የጎን ውጋት ሆነው እንደሚያስቃስቷት በስፋት እያስተዋልን ነው።
ከውጭ የሚወረወርባት የዲፕሎማሲና የእጅ አዙር ጫናም መልኩና ዓይነቱ ዝንጉርጉር ነው። የቀጣናው ተጎራባች ታሪካዊ ጠላቶች እንቅልፍ አልባ ትንኮሳና ሴራ፣ በሩቅ መንግሥታት የሚውጠነጠኑትና የሚሰነዝሩት የጋሉ የብረት አሎሎ ማስፈራሪያዎችና ማዕቀቦች እንደ እቅዳቸው ታርጌቱን ቢመታላቸው ኖሮ የሚፈጠረው ብሔራዊ ትራዤዲ ውጤቱ ቀላል ባልሆነ ነበር። “እንኳን ከተወረወረ ከታሰበም ያድናል” እንዲሉ ኢትዮጵያን የሚጠብቀው አምላክ ሰለማይተኛና ስለማያንቀላፋ፣ በመሪዎቻችን ብልህ አመራርና ስክነት እንደ ምኞታቸው ሊሆንላቸው አልቻለም።
ሀገሬን ከውስጥና ከውጭ ቀስፎ የያዛት ፈተና እንዳበዛዙና እንደ ባህርይው መዥጎርጎር ቢሆን ኖሮ “ገበርኩ” ብላ በተደነቃቀፈች ነበር። ምሥጋና ለፈጣሪያችን፣ አክብሮት ለመሪዎቻችንና ለሕዝባችን ይሁንና ኢትዮጵያ ዛሬም ቢሆን ቁርጭምጭሚቷ ፀንቶ እንደቆመች ነው። የአውሎ ነፋሱ ወጀብ አላንበረከካትም፤ የጠላቶቿ የተቀናባበረ የሴራ ወጥመድም ከግስጋሴዋ አልገታትም።
ለ. ተፈጥሮ ተኮር ብሔራዊ ፈተናዋ፤
መቼም ትዝብቱ ለራሳችን ይሁንና እንደ እኛ እንደ ኢትዮጵያዊያን ተፈጥሮ የታዘበችው ሌላ ሕዝብ ስለመኖሩ ያጠራጥራል። በውሃ ላይ ተኝቶ ስለ ጥማት የሚተርክ፣ የተባረከ አፈር ከፈጣሪ ዘንድ ተለግሶት ስለ ርሃብ የሚዘምር ሌላ የምድር ወገን ካለ ብናውቀው አይከፋም። የዓለም ማሕበረሰብ ሲረዳን የኖረውና እየረዳን ያለው በእጁ ስንዴ እየዘገነልን፤ በሆዱ እየናቀን መሆኑን በድፍረት መናገሩ ብሔራዊ ክብርን መዳፈር ተደርጎ ሊቆጠር አይገባም።
በተፈጥሮ ሳይንስ ልጆቿን የምትመዝን ሀገር ተፈጥሮን ያለማስገበሯ በተማሪ ቋንቋ ስንፍና፣ በፖለቲካ የማደናገሪያ ቋንቋ የሥርዓቶች ብልሹነት ሲባል መክረሙ እኛንም ሌሎችንም ያሰለቸ ሰበብ ነው። የድህነትን ስም የምናነሳው ልክ እንደ ልብ ወዳጅ “ድህነታችን” በማለት እያቆላመጥን ወይንም እንደ ቅርብ ወዳጅ ቤትኛ በማድረግም ጭምር ነው።
ከተፈጥሮ ጋር ከመኳረፋችን የተነሳ የሚደርሱብንን የድርቅ፣ የአንበጣ ወረርሽኝ ወዘተ. እየዘረዘርን ስሙልን እዩልን ማለቱ፤ “ከሰደበኝ መልሶ የነገረ ገደለኝ” ይሉት ብሂልን ስለሚያስታውሰን እንደለመድነው “ሆድ ይፍጀው” ብለን ማለፉ ይቀላል።
ሐ. “የብሔራዊ ፈተናዎቻችን” አበረታች ውጤቶች፤
የዛሬዋ ኢትዮጵያ ለከበቧትና ፊቷ ለተደረደሩት ፈተናዎች ሁሉ “አጉራህ ጠናኝ” ብላ እጇን ለካቴና አሳልፋ አልሰጠችም። እንዲያውም የሩቅ ታዛቢዎቿ ሳይቀሩ ግራ በተጋባ ስሜት የግስጋሴዋን ፍጥነት እያስተዋሉ “ወደፊት እያስፈነጠራት ያለው ምን ይሉት ኃይል ነው?” እስከማለት መድረሳቸው ለእኛ “ኩራት” ለእነርሱ እንቆቅልሽ የሆነ ይመስላል።
“ሁሉ በእጃችን፤ ሁሉ በደጃችን” እያሉ የሚፎክሩ ሀገራት ሳይቀሩ ግራ የተጋቡበት አንዱ ጉዳይ በጦርነት መካከል ውጤታማ የልማት ተግባራት በርብርብ ማከናወናችን ነው። እዚያ ማዶ ጀግናው የሉዓላዊነታችን አለኝታ የመከላከያ ሠራዊታችንና ከጎኑ የተሰለፉት የሕዝባዊ ሠራዊት ኃይላት እብሪተኛውን የወያኔ ጀሌ እየቀጡ ግፋ በለው በማለት ወደፊት በመገስገስ እብሪቱን እያስተነፈሱለት ይገኛሉ። ወዲህ ማዶ እየተመረቁ ያሉት ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችና የገበሬው ማሳ ሥር የሰደዱ ብሔራዊ ፈተናዎቻችንን ድል በመንሳት ተስፋችንን እያነቃቁ ይገኛሉ። “በአንድ እጅ ጦር፤ በሌላው እጅ ማረሻ” እንዲሉ መሆኑ ነው።
ካሁን በፊት ፈዘን የምናስተውላቸው የሌሎች ሀገራት መሠረተ ልማቶች ደጃፋችን ደርሰው “ኑና እዩልን” የማለት ደረጃ ላይ ደርሰናል። “በቅርብ ዓመታት ውስጥ የኤሌክትሪክ ኃይል ለጎረቤት ሀገራት እናጋራለን” ስንል የሳቁብን ሁሉ ዛሬ አፋቸውን በእጃቸው ላይ ጭነው ተገርመዋል። “የስንዴ እርዳታችሁን መቀበሉን አቁመን ሌሎችን ለመመገብ አቅደናል” ስንል ያፌዙብንም ወደ እውነታው ስንቃረብ ተገርመው አንዳቸው ከአንዳቸው እየተጠቃቀሱ ለመንሾካሾክ በቅተዋል። አልፎም ተርፎም “ገበታችን ላይ ዳቦ ጣል እያደረጉ” ሲደጉሙን የኖሩት መንግሥታትና ዓለም አቀፍ ተቋማት “በገበታ ለሀገር ስያሜ” እየገሰገሱ ያሉ አስዳማሚ ፕሮጀክቶቻችንን እንደሚጎበኙልን ቀኑ መድረሱን ስናረጋግጥላቸው ከመገረም አልፈው ግራ መጋባታቸው አልቀረም።
እያንዳንዱን ቀን ኢትዮጵያ እየተቀበለች ያለቸው በቁዘማ ሳይሆን አንዳች አዲስ ክስተት እያስተናገደች ነው። እዚህም ልማት፣ እዚያም ልማት – ያውም በጦርት ፍልሚያ ውስጥ ሆና። ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምታስገባቸውን ልጆቿን በብሔራዊ ፈተና ስትመዝን የሰነበተችው ኢትዮጵያ ራሷም በፈተናዎች መከበቧ እውነት ነው። ቢሆንም ግን የእያንዳንዱ ውስብስብ ተግዳሮቶቿ ውል በሚያስደንቅ ፍጥነት እልባት እያገኘ ስለሆነ የግስጋሴዋ ፍጥነት ጨምሯል።
እስከ ዛሬ የት ነበርን? አሰኝተው ላስደመሙን መሪዎቻችን ምሥጋናችን ይድረስልን። ከዕለት ዕለት የድል ብሥራት ለሚያሰማን የመከላከያ ሠራዊታችን ሞገስ ይሁንለት። ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም ሌት ተቀን ለሚተጉ ተቋማትና የሕዝብ ባለውለታዎች ከፍ ያለው አክብሮታችን ይድረሳቸው። ድብርት የተጫጫነው ሀገራዊ ኢኮኖሚያችን በቅርብ ጊዜ እንደሚነቃቃ በሚያውደን የልማት ጠረን እያረጋገጥን ስለሆነ ፈጻሚዎቹንና አስፈጻሚዎቹን “አሹ!” ማለቱ ያበረታታቸዋል።
ዲፕሎማሲያችን በጥበብ እየተመራ መሆኑን ስናይ ልባችን ይሞቃል። ኢትዮጵያ ስትፈተን እንደ ወርቅ እየጠራች እንደምትሔድ በብዙ ማስረጃዎች ማረጋገጥ ይቻላል። “ብዙ ከብት ለማርባት፤ አልቅትን ጠብቆ ውኃ ማጠጣት” ይላል የሀገሬ ሰው። ጥሩ የማስጠንቀቂያ ምክር ነው። የአረቦቹን አባባል ተውሰን ርዕሰ ጉዳያችንን እንደምድም፡- “ውሾቹ ይጮኻሉ፤ ግመሎቹም ይጓዛሉ!” ሰላም ይሁን!
(ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2015