አንዳንዴ የእኛ ነገር ያናድዳል::ዓለም ከሚሄድበት አቅጣጫ በተቃራኒው መጓዝን ፋሽን አድርገነዋል:: ዓለም እየተጋገዘ እና እየተደራጀ ከአመት አመት አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሲፈጥር እና ህይወቱን ሲያሻሽል እኛ ግን በተቃራኒው እየተደራጀን አንዳችን አንዳችንን ለማጥፋት ስንለፋ እንውላለን:: ያሳፍራል:: አሁን ደግሞ አዲስ የመጣው ፋሽን ሰውን ማገት እና ገንዘብ መጠየቅ ነው:: አስገራሚ ነው::እንዲህ አይነት ሀሳብ እንደ ስራ ፈጠራ እና እንደ ገቢ ምንጭ አድርጎ ማሰብ አሳዛኝ ክስተት ነው::
ይህን ያልኩት የሰሞኑ የህጻን ሳሙኤል እገታ ነው::ለ11 ቀናት የቆየው እገታ በፖሊስ ጥንቃቄ የተሞላው እንቅስቃሴ መጨረሻውን አግኝቷል::አሁን ላይ ህጻኑ ወደ እናቱ እቅፍ ተመልሷል:: አስገራሚው ነገር ግን በአንድ ሰራተኛ ብቻ ተፈጽሟል ብለን ያሰብነው ወንጀል ለካስ በተቀናጀ መልኩ ሶስት ሰዎች በጋራ የፈጸሙት እና ለረዥም ጊዜ ያቀዱት መሆኑ ነው::ያስገርማል::ሰው እንዴት የሰው ልጅ አግቼ ገንዘብ አገኛለሁ ብሎ ያቅዳል::ይሄ እኮ እንኳን ሊታቀድ በህልም እንኳን ሊታይ የሚገባው ነገር አልነበረም::
እዚህ ጋር የምስራቅ ጎጃም ዞን ስለ ወንጀሉ አፈጻጸም ያሰፈረውን መረጃ እናንብብ…. “የእገታ ወንጀሉን ያቀነባበረው ብሩክ/አማረ ቸኮል የተባለ እና አዲስ አበባ ውስጥ በቀን ስራ የሚተዳደር ግለሰብ ሲሆን ፤ለዚህ ሀሳብ መነሻ የሆነውም መርጌታ ሚስጥሩ ይግዛው የተባለ የስጋ ዘመዱ ከምዕራብ ጎጃም ደጋዳሞት ወረዳ ለስራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ይሄድና ከብሩክ/አማረ ቸኮል ጋር ተገናኝቶ ስራ እያፈላለገ ለተወሰነ ጊዜ አብረው ይቆያሉ::
ከዚያም መርጌታ ያሰበውን ስራ ማግኘት አልሳካለት ሲል ስራ ጠፋ ወደ አገሬ ልመለስ ነው ብሎ ብሩክን ሲያማክረው ፤ ለምን አንድ የሀብታም ልጅ የሆነ ህፃን አግተን ብር አንቀበልምና አያልፍልንም ይለዋል ፤ መርጌታ ሚስጥሩም እንዴት አርገን በምን መልኩ ማገትና ገንዘብ መቀበል እንችላለን ሲለው ፤ቀላል ነው ከጎንደር ወይም ከጎጃም አካባቢ መጥታ አዲስ አበባ ሀብታም ቤት ውስጥ የገባች ሰራተኛ ካገኘህ አፈላልግና እሷን አግኝተን በማሳመን ህጻን ይዛ እንድትጠፋ ካደረግን በኋላ ህጻኑን ደብቀን ከቤተሰቡ ብር ተቀብለን እንለቀዋለን በሚል ይመካከሩና ይስማማሉ ፤
በስምምነታቸው መሰረትም መርጌታ ሚስጥሩ ወደ ባህርዳር ተመልሶ በፊት የሚያውቀውን አንድ ጓደኛውን አግኝቶ ሀሳቡን ግልጽ ሳያደርግ አዲስ አበባ ሀብታም ቤት ውስጥ የገባች የቤት ሰራተኛ የሚያውቃት ካለች እንዲያስተዋውቀው ወይም እንዲያፈላልግለት ይጠይቀዋል ፤ይህ የባህርዳሩ ጓደኛውም ህጻኑን ሰርቃ የተሰወረችውን ውዴን ቀድሞ ያውቃት ስለነበር ያስተዋውቀውና ስልክ እንዲለዋወጡ ያደርጋል ፤ በመቀጠል መርጌታ ሚስጥሩ ወደ አዲስ አበባ በመመለስ ከመጀመሪያው ሀሳብ አመንጭ ከብሩክ ጋር በመሆን ውዴ ላይ ይደውሉና ተቀጣጥረው መርካቶ አካባቢ አግኝተዋት ተዋውቀው የተወሰነ ከተጫወቱ በኋላ ሀሳቡን ሲነግሯት ለጊዜው ፍቃደኛ አልሆንላቸው ስትል በተለያየ መንገድ ጀንጅነው ያሳምኗታል ፤ውዴ በሀሳቡ ከተስማማች በኋላ አሁን ካለሁበት ቤት በፊት የነበርኩበት ቤት ስለሚሻል ተመልሼ ከበፊቱ ቤት ልግባና ህጻንም ስላለ እሱን ብናወጣ ይሻላል በሚል ተስማምተው ቀደም ሲል ከወጣችበት ቤት ተመልሳ በመግባት በንግግራቸው መሰረት ጥቅምት 6ቀን 2015 ዓ/ም ህጻን ሳሙየል ዩሀንስን አታላ ከቤት ይዛ ትሰወራለች ።”
እንግዲህ ከዚህ የምንረዳው ነገር የአንዳንድ ሰዎች አእምሮ ምን ያህል የተበላሸ እንደሆነ ነው::ስራ ጠፋ ሲባል ለምን ልጅ አናግትም የሚል ፤ ያለማቅማማት የሚስማማ፤ ከመስማማትም አልፋ የክፋት ሀሳብ የምታመነጭ ሴት እነዚህ ሁሉ አንድ ላይ ሆነው የፈጸሙት አስደናቂ ወንጀል ነው::ይህ ነጠላ ክስተት አይደለም::ሌሎችም እንዲህ አይነት ታሪኮች በቅርቡ በተደጋጋሚ እየሰማን ነው::ለምሳሌ ያህል በመተማ ወረዳ ይህ አይነት ዜና በቀናት ልዩነት ውስጥ ሁለቴ ተሰምቷል::የመተማ ፖሊስ የፌስቡክ ሁለቱን ታሪኮች እንደሚከተለው ይገልጻቸዋል::
የመጀመሪያው እነሆ በምዕራብ ጎንደር ዞን በመተማ ወረዳ በመቃ ቀበሌ ላይ የእገታ ወንጀል የፈፀመ ግለሰብ በፅኑ እሰራት መቀጣቱን የልዩልዩ ወንጀል መርማሪ ንዑሰ ክፍል ሀላፌ ሳጅን መሀመድ ሁሴን ገለፁ።ለክፍላችን ለመተማ ወረዳ ፓሊሰ የመንግሰት ኮሚዩኒኬሸንና ሚዲያ ክፍል እንደገለፁት ተከሳሸ ጌታሁን እያየ የተባለው ካልተያዙ 3 ግብረአበሮቹ ጋር በመሆን መሰከረም 27ቀን 2015ዓ.ም መተማ ወረዳ መቃ ቀበሌ ወይን አንባ ከተባለው ልዩ ቦታው ከቀኑበግምት 11:00 ሰዐት ሲሆን የግል ተበዳይ አበራ መኮነንን አግተው በመውሰድ 800,000(ሰምንት መቶ ሸህ ብር) ጠይቀው ለ4ቀናት ያህል ካቆዩ በኃላ ከቤተሰቦቹ ጋር ተደራድረው 400,000(አራት መቶ ሸህ ብር) በማስከፈል ጥቅምት 1ቀን 2015ዓ.ም ሊለቁት ችለዋል። የመተማ ፖሊስ በኋላ ላይ ባደረገው ክትትል ተከሳሹን ከዘረፈው የተወሰነ ገንዘብ ጋር ይዞት አስፈርዶበታል ፤ የተገኘውንም ብር ለባለቤቱ መልሷል::
ሁለተኛው ታሪክ ደግሞ እንዲህ ይላል “በምዕራብ ጎንደር በመተማ ወረዳ በማጠቢያ ንዑሰ ወረዳ በተደጋጋሚ ማህበረሰቡን እያገቱ ያሰመረሩ ግለሰቦች በፅኑ እሰራት መቀጣታቸውን የማጠቢያ ንዑሰ ወረዳ የታክቲክ ምርመራ ክፍል ሀላፌ ረ/ኢ/ር ጌታቸው አሰረሴ ገለፁ።”ይላል:: ዘገባው እንደሚያስረዳው እነዚህኞቹ ደግሞ ሰፋ ያለ የማገት ልምድ ያላቸው ናቸው::የተወሰኑት ተይዘው ፍርድ ተቀብለዋል::
ሁሉም ታሪኮች የሚያሳዩን ይህ ነገር እንደ ልማድ እየተስፋፋ መምጣቱን ነው:: በየቦታው ብናየው እንዲህ አይነት ብዙ ታሪክ መኖሩ አይቀርም:: አግተው ገንዘብ ባይጠይቁ እንኳ አባብለው ሰውን ለሴተኛ አዳሪነት ፤ ለጉልበት ስራ እና መሰል ነገር የሚመለምሉ በዝተዋል::ሰው ተባብሮ ሰርቶ ራሱን እና ሀገሩን ይቀይራል እኛጋ ሰዎች የሚተባበሩት ለወንጀል ሆኗል::እንደቀልድ ልናየው አይገባም::ካሁኑ በጋራ ካልታገልን ነገ ከነዚህ ወንበዴዎች ሰለባዎች መሀከል እኛም ልንገኝ እንችላለን::
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2015