በዓለማችን በአብዛኛው ለሰው ልጅ ልብስ መልበስ ሰብዓዊ፣ ሞራላዊና መንፈሳዊ ግዴታው ነው፡፡ አዳምና ሔዋንን ዕጸ በለስ አትብሉ የተባለውን ትዕዛዝ ሲጥሱ ዕርቃናቸውን መሆናቸው ታወቃቸው፤ ተፋፈሩ የበለስ ቅጠል ቀነጣጥሰው ለራሳቸው ግልድም አደረጉ፡፡ እነሆ ከዚያም በኃላ ልብስ ለሰው ልጆች ገበና ሸፋኝ ብቻ ሳይሆን ጤንነቱን የሚጠብቅበት፣ ብርድንና ሙቀትን ወይም የፀሀይ ሐሩርን የሚከላከልበት፣ ባህልና እምነቱን የሚገልፅበት ማጌጫው ጭምር ሆነ፡፡
ይህን ፅሁፍ ለማዘጋጀት ያነጋገርናቸው በፋሽን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች፤ ‹‹ፋሽን ሰው የወደደው፣ ገበያ የለመደው ወይም የሚስበው መገልገያ ቁሳቁስ፣ ልብስ እና ጌጣጌጥን የመሳሰሉትን ያካትታል›› ይላሉ፡፡ በሰዎች ቅቡል፣ ተመራጭና ተወዳጅ የሆነውን ዓይተው ደጋግመው የሚያመርቱትንና ለገበያ የሚያቀርቡትን ‹ፋሽን› እንደሚሉትም ይናገራሉ፡፡ ስለተሠራ ሳይሆን ሥራውን ሰው ሲወደው እና ሲለምደው ከዚያም በብዛት ሲገለገልበት ፋሽን ተብሎ ይታሰባል፡፡
‹‹የፋሽን ኢንደስትሪ በአገራችን ከውጪዎች ጋር ሲነፃፀር በዘርፉ ገና ጅማሮ ላይ ነን›› የሚሉ የዘርፉ ባለሙያዎች የፋሽን አልባሳትን የሚሰሩት በቅብብሎሽ ነው፡፡ አንድ ፋሽን ተሰርቶ ይወጣና ከ20 እስከ 30 ሺ ልብስ ይሠራና ለሽያጭ ይቀርባል፡፡ በብዛት ገበያው ሲቀበለውም ፋሽን ይሆናል፡፡
የፋሽን ንድፍ ወይም ዲዛይን ብዙውን ጊዜ አልባሳትን ከመስፋት፣ ለመዋቢያ የሚሆኑ ቁሶችን ከመቀመር፣ ከማዋቀር ፣ ከመሥራትና ለአገልግሎት ከማብቃት የዘለለ ሚና አለው፡፡ ዲዛይን በራሱ ሰገላዊ ጥበብ (scientific art) የሚታይበት ታስቦና ታልሞ የሚከወን መሆኑንበዘርፉ ባለሙያ የሆኑት ዴቪድ ካርሰን ያስረዳሉ ፡፡ ክንውኑ የታለሙ ዕሳቤዎችን ኪንን ቀምሮ የሚያካትት ነውም ይላሉ፡፡
የፋሽን ንድፍ ሰባት አላባውያን (elements) አሉት የሚሉት ዴቪድ ካርሰን ፤ እነዚህም የማንኛውም ዕይታ ንድፍ መሠረታዊ የአሠራር ዓይነቶችን የሚያካትቱ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ፋሽንና ንድፍ ሰባት አላባውያን ማለትም ቀለም፣ ቦታ /ስፋት/፣ ቅርፅ፣ መስመር /ሥሪት ወይም ዓይነት/ ዕሴትና ጥራትን ያካትታሉ ሲሉ ያስቀምጣሉ፡፡
ቀለም፣ስፋት፣ ቅርፅ፣ መስመር /ሥሪት ወይም ዓይነት/፣ ዕሴትና ጥራት የፋሽን ሥራው ንድፍ ወይም ዲዛይን በቀላሉ በሰው ዕይታ ውስጥ እንዲገባ የሚረዱ ናቸው፡፡ ዲዛይን ወይም ንድፍ ለፋሽን መሠረታዊ፤ በጣም ጠቃሚ ወይም ዋጋ እንዲኖረው የሚያግዝ ሲሆን ትኩረት የሚጭሩ እና ዕሴት የሚጨምሩ ጥበቦችም ያሉበት መሆኑን በጽሑፋቸው አስቀምጠዋል፡፡
ለዚህም ግራፊክ ዲዛይነሮች የጠቀስናቸውን የንድፍ አላባውያንን በማካተት ምስል ከሳች ሆኖ የተወሰነ ስሜት የሚፈጥር ፣ዐይንን በውስን አቅጣጫ የሚያጥር (የሚከት) ወይም በርካታ ስሜቶች የሚያጭር የፋሽን ዲዛይኖችን ይሠራል፡፡ እነዚህም የፋሽን ንድፍ አላባውያን ማንኛውም ከሳች ምስሎች የሚፈጥሩ፣ ለንድፍ አውጪዎችም በንድፍ መርሆዎች ላይ እንዲያተኩሩ የሚረዱ ናቸው፡፡በዚህም በንድፍ አላባውያን ላይ ተመሥርተው የሚሠሩ የንድፍ ባለሙያዎች ለዓይን ደስ የሚል መልክና ቅንብር የሚፈጥሩ ናቸው፡፡
ገፃዊ ዕይታ አሠራር (graphic design) ማንኛውም ምስላዊ የጥበብ ፈጠራ ሥራ ከግምት በመክተት የሚከወን ሲሆን ውስጣዊ ንድፍም ፣ አርማ ፣ማስታወቂያ ወይም የዘመናችን መረብ ዲዛይን (web design) ሚና ያለበት ነው፡፡
ቀለም ለፋሽን ንድፍ ቅንብር ስሜት የሚጭር ነው፡፡ የብርሃን ሞገዶች በአንድ ቁሳዊ ነገር ላይ ሲረጩና ተንፀባርቀው ሲመለሱ በሰው ዓይን (ኦፕቲክ ነርቭ) ላይ ስሜት ይፈጥራሉ፡፡ ይህም ቀለም የሚባለውን ወሳኝ ነገር ይከሰታል፡፡ የጥበብና የንድፍ ባለሙያዎች ቀለምን የሚጠቀሙት የፋሽን ሥራው፤ ዕይታው ውስጥ እንዲገባና እንዲገለፅ (እንዲነገር) ነው፡፡ቀለምን የንድፍ ባለሙያዎች ስሜትን ፣ ብርሃንን ፣ ጥልቀትን እና ዕይታን ሰዎችን ለመሳብ ለመማረክ ይመርጡታል።ይህም በቀለም ንድፈ ሀሳብ ተመርኩዘው የሚሠሩት ነው፡፡ ይህም ቀለሞችን በመቀላቀል ፣በማዋሃድ እና በማቀናበር – የቀለም ንድፎችን ለመፍጠር የሚረዳ ነው፡፡
መስመር ሁለት ነቁጥ (ነጥብ) የሚገናኙበት ነው፡፡ አግድማዊ፣ ሰያፍና ፣ ሽቅባዊ መስመሮች ዓይንን ወደ ተወሰነ አቅጣጫ የሚወስዱ ቅንብሮች ናቸው፡፡ በዚህም በተለያዩ መስመሮች መስተጋብር ውህደት የሚስብ ከቀጥታ መስመር ባለፈ ያማረ ጥለት ይፈጥራሉ፡፡
በንድፍ ሥራ ውስጥ ዕሴት የሚያመላክተው የፋሽን ሥራውን ብርማ (ብሩህ) እና ጸሊም ቀለማትን ነው፡፡ የቀለም ዕሴት በብዛት ቀስ በቀስ የሚከሰት ነው፡፡ የእዚህም ማሳያዎች በአንድ ቀለም ላይ ያሉ ልዩነቶችን ከቅለት እስከ ክቡድ ጽልመት የተደረደሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ አርቲስቶች የተለያዩ የቀለም ዓይነቶችን ይጠቀማሉ፤ይህም ብዙዎችን ለማስደመምና ሥራቸው እንዲሰምርላቸውና እንዲነገርላቸው ገበያ እንዲስብላቸው ብሎም ተወዳጅነት እንዲፈጥርላቸው ነው፡፡
ሌላው ስፋት እና ቦታ የሚባለው የታሰበ የፋሽን ንድፍ ሥራን ሌሎች እንዲያዩት የሚጋብዝ ነው፡፡ አዎንታዊ ቦታ በንድፍ ቅንብር ውስጥ የሚወስደው ቦታ ነው።ቅርጽ በጣም መሠረታዊ ሆኖ ቁመትና ዓይነት የሚገለጽበት ነው፡፡ በንድፍ የታጀበ ሁለት ልኬታዊ ቦታ ነው፡፡የግራፊክ ዲዛይን ባለሙያዎች የሚጠቀሙበት መስመር፣ ቀለም፣ ዕሴትን በማካተት በሦስት አቅጣጫዊ ቅርጽ ሰዎች ቀልባቸውን እንዲስብ የሚያደርግ ነው፡፡
በሚሊተሪ ተራ ልብስ ሲገበያዩ ያገኘናቸው ወይዘሪት ለምለም ገብረእግዚአብሔር፤ ፋሽን ተከታይ ሲሆኑ የአልባሳት ምርጫቸው ላይ ቀለም እና ስፌት ላይ ያተኮረ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ስፌቱን መርጠው ለልብስ ሠፊ እንደሚሰጡና፤ ጊዜው ያለፈባቸው አልባሳታቸውን በብዛት ለታረዙ እንደሚሰጡ አጫውተውናል፡፡
በተመሳሳይ መገበያያ ስፍራ ያገኘናት ከድጃ ሁሴንም ምርጫዋ ቀለም ላይና ስፌት ላይ ቢሆንም ከእምነቷ ጋር በማይፃረር መልኩ ረጃጅም ቀሚሶችንና የሚዛመዱ ሻሾችን አሠርታ እንደምትጠቀም
ትናገራለች፡፡ የጨርቅ ምርጫዋ በቀልም ላይ የተወሰነ ቢሆንም ተማሪ ሀቢባ ሳሊም ልዩ ልዩ ምስል ያለባቸውን ጨርቆች እንደምትመርጥና በተለይ ቁመቷ አጭር በመሆኑ፤ ከላይ ወደ ታች መስመር ያለባቸው አልባሳትን እንደምታስቀድም ጠቁማለች፡፡ ይህም ከላይ የጠቀስነው ፋሽን ሰው የወደደው ገበያ የለመደው ቁስ እና ልብስ ነው ለሚለው ማሳያ ነው፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 21/2015