የሠርግ ሥነ-ሥርዓት የተቃናና የደመቀ እንዲሆን አስቀድሞ መዘጋጀት ወሳኝ ነው። አስቀድሞ የታሰበበት ሠርግ የተሳካና ያማረ ይሆናል። የሠርግ ነገር ሲታሰብ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ነገሮች አንዱ የሙሽሪት ቬሎ ነው። ሙሽሪት ቬሎዋ ከሠርጓ ስድስት ወር አስቀድማ መምረጥ ይኖርባታል ይላሉ ባለሙያዎች። ከሠርጓ ሁለት ሳምንት በፊትም በእጇ ማስገባት አለባት፡፡
ሙሽሪት ቬሎዋን ከመግዛቷ ወይም ከመከራየቷ በፊት የትኛው እንደሚስማማት ወይም እንደሚማርካት መወሰን ይገባታል። በየቬሎ ቤቱ በመሄድ በርካታ ምርጫዎች ልትመለከት ትችላለች። ምርጫዋን ከያዘች በኋላ ምን ማድረግ ይገባታል?
በመጀመሪያ የሠርጓ ሥነ-ሥርዓት በምን መልኩ እንደሚከናወን ልታወቅ ይገባል። ምክንያቱም የቬሎ መግዣ ወይም መከራያ ዋጋ ውድ በመሆኑ ለፕሮግራሙ የሚስማማውን የቬሎ ዓይነት ልትወስን ይገባታል። ለምሳሌ የሠርግ ሥነ-ሥርዓቷ በቤተክርስቲያን የሚከናወን ከሆነ እጃቸው ጉርድና ግልጥ ቬሎዎች ተቀባይነት ላይኖራቸው ይችላል። የሠርጓ ሥነ-ሥርዓት ቀለል ያለ እንዲሆን ከፈለገች ደግሞ የምትመርጠው የቬሎ ዓይነት የተለየ ይሆናል፡፡
የሠርጓ ዕለት በየትኛው ወር እንደሚከናወን ማወቁ አስቀድሞ ከግምት ውስጥ የሚገባ ጉዳይ ነው። በሀገራችን የሚያዝያ ወር የሠርግ ወቅት ቢሆንም የበልግ ዝናብ የሚኖርበት በመሆኑ ሙሽሪት ቅጥያና ተጎታች የሌለው ወይም ተጎታቹ የሚነቀል ቬሎ ልታደርግ ይገባታል። ይህም ቬሎዋ በጭቃ እንዳይበላሽ ይረዳታል። እንዲሁም ከጀርባቸው በጣም ከፍት የሆኑ ቬሎዎች በዝናብ ወቅት ለብርድ ያጋልጣሉና ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡
ቬሎን በመምረጥ ሂደት ሌላው ወሳኝ ነገር የሙሽሪት የአካል ሁኔታ ነው። ርዝመት፣ እጥረት፣ ውፍረትና ቅጥነት ቬሎን ለመምረጥ ወሳኝነት አላቸው። ከሰውነት ጋር የሚሄድ ቬሎ ለሙሽሪት ድምቀትን ይሰጣል። የቬሎ ዓይነቶች ቅርፅ፣ ቡፍ ያለና ክብ ባለተጎታች በመባል ይታወቃሉ። “A” ቅርፅ ያለው ቬሎ ለማንኛዋም ሴት የሚሰማማ ነው። ቡፍና ክብ ያለው ሙሽሪት ጎላ ረዘም ብላ እንድትታይ ያደርጋታል፡፡
አጭር ሴት አንገቱ በጣም ክፍት ያልሆነ፣ ወገቡ የወረደና አጭር እጅጌ ወይም ባካውት የሆኑ ቬሎዎች ይሰማሟታል። ተጎታች ያለው ቬሎ ለአጭር ሴት አይመከርም። እንዲሁም አጭር ሻሽ ልታደርግ ይገባታል። በጣም ቡፍ ያለ ቬሎዎች አጭር ሴትን ይበልጥ አጥራ እንድትታይ ስለሚያደርጋት ምርጫዋ ባይሆኑ ይመረጣል። ረዘም ብለው ጠበብ ያሉ ቬሎዎች ለአጭር ሴት ተመራጭ ነው፡፡
ረጅም ሴት አጠር ብላ እንድትታይ ወገቡ ወረድ ያሉና ቡፍ ያሉ ቬሎ ልትመርጥ ይገባታል። ሰፊ ቬሎ ሙሽሪት ወደጎን ሰፋ ብላ እንድትታይ ስለሚያደርጋት ቁመቷን ይከተዋል። አንገቱ ከፍ ያለና ፒትልስ ቬሎዎች ለረጅም ሴት አይመከርም። ባካውትና ማንገቻ የሌላቸው ቬሎዎች ለረጅም ሴት ተመራጭ ናቸው። እጀ ሙሉ ቬሎዎችም እንዲሁ ለረጅም ሴት ተስማሚ ናቸው። ረዘም ያሉ ሻሾችም ለረጅም ሴት ይስማማል፡፡
መካከለኛ ቁመትና ውፍረት ያላት ሙሽራ የትኛውም ዓይነት ቬሎ ይስማማታል። ፋሽን ሆኖ የመጣውን ቬሎ ብትለብስ ደምቃና አምራ ልትታይ ትችላለች። በቬሎ ምርጫዋ ላይ ምንም ተፅዕኖ አይኖርባትም፡፡
ወፍራም ሴቶች በተለይ ጡታቸው በጣም ትልቅና አንገታቸው አጭር ከሆነ ግልጥና ባካውት ቬሎዎችን ሊያደርጉ አይገባም። እንዲሁም ቡፍ ያሉ ቬሎዎች ወፍራም ሴት ይበልጥ ወፍራ እንድትታይ ያደርጋታል። ወፍራም ሴት በሳተን የተሠሩና ጠበቅ ያሉ ቬሎዎች ምርጫዋ ልታደርግ ይገባታል። የትከሻዋን ውፍረት ለመሸፈንም ትንሽ እጅጌ ያላቸው ቬሎዎች ብታደርግ ጥሩ ይሆናል። አንገቷ ወጣ ብሎ እንዲታይ አንገታቸው ገለጥ ያሉ ቬሎዎች ብትመርጥም መልካም ነው።
እንደ መካከለኛ ቁመት ውፍረት ያላት ሴት ሁሉ ቀጭን ሴትን በርካታ የቬሎ ምርጫ አላት። እንደፓሪ ያሉና ጥብቅ ያሉ ቬሎዎች ቀጨን ሴትን የበለጠ ስለሚያከሷት ብዙም አይመረጡም። በቲውል የሚሠሩና ቡፍ የሚሉ ቬሎዎች ቀጭን ሴትን ውበት ያላብሷታል፡፡
እንግዲህ ሙሽሪት እነዚህን ሁሉ ነገሮች ከግምት ካስገባች በኋላ መሆን አለበት የቬሎ ምርጫዋ ማከናወን ያለባት። ከዚህ በኋላ የሠርጓ ዕለት አምራና ደምቃ ትታያለች፡፡
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም