ልጆች እንዴት ናችሁ፤ ትምህርት እንዴት ይዟችኋል? በደንብ እያነበባችሁ ነው አይደል? ከመጀመሪያው ጀምሮ ማንበብን ልምምድ ካደረጋችሁ ውጤታማ ትሆናላችሁ። ስለዚህም ጎበዝ ተማሪ ለመሆን ስታቅዱ ቅድሚያ ቦታ መስጠት ያለባችሁ ለንባብ ነው። ዛሬ የተማራችሁትን ዛሬው ማንበብ ትልቅ ጥቅም አለው ። እናም ዛሬ የተማራችሁትን ነገ አነበዋለሁ ማለት የለባችሁም። ተጨማሪ ነገሮችን በማከልም አቅማችሁን ማጎልበት ይገባችኋል። በተለይም ተሰጥኦዋችሁን የሚያጎለብቱላችሁ ነገሮች ለእናንተ ጠቃሚ ናቸውና ልምዳችሁ ልታደርጓቸው ይገባል።
ልጆች ለረጅም ዓመት ቀርቶ የነበረው የስድስተኛ ክፍል ሚኒስትሪ ፈተና ዘንድሮ እንደሚጀመር ታውቃላችሁ አይደል? አዎ !እኔም ዛሬ ይዤላችሁ የመጣሁት በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ተፈታኝ የሆኑ የስድተኛ ክፍል ተማሪዎችን ነው። ስለዚህም ስለዝግጅታቸውና አዲሱን የትምህርት ስርዓት እንዴት እየተቀበሉት እንዳለ ይነግሩናል።
ትምህርት ከተጀመረ ገና በወራት የሚቆጠር ጊዜ ስለሆነም የትምህርት አጀማመሩንና ለሌሎች ተማሪዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸውም ይነግሩናልና እናንተ ተሞክሯቸውን ለመቅሰም በሚገባ አንብቡት።
መጀመሪያ ያነጋገርናት ተማሪ ምህረት ግዛቸው ትባላለች። ከላይ እንዳልናችሁ የዘንድሮ የስድስተኛ ክፍል ተፈታኝ ናት የምትማረው ደግሞ ካራአሎ ቅድመ መደበኛና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው። በትምህርቷ በጣም ጎበዝና ከሌሎች ልጆች ጋር ማንበብ የምትወድ ነች። በትምህርት ቤት በተለያዩ ክበባት ውስጥ በመግባት ትሳተፋለች። በዚህም በርካታ ለውጦችን በራሷ ላይ እንዳመጣች ትናገራለች። በተለይም ክበባት ውስጥ መሳተፍ ልዩ ተሰጥኦዋን እንድታውቅና እንድትቀጥልበት እንዳደረጋት ታስረዳለች።
ልጆች ምህረት በጣም ጎበዝና የደረጃ ተማሪ ነች። የስድስተኛ ክፍል ተፈታኝ በመሆኗ ደግሞ የበለጠ ማንበብና መዘጋጀት እንዳለባት አምና ጠንክራ እያነበበች ትገኛለች።
በተለይም የአጠናን ልምዷን ከፍ አድርጋ ከጓደኞቿ ጋር ጭምር ታነባለች። ለዚህ ደግሞ የትምህርት ቤታቸው ምቹነት እንደተስማማት ታስረዳለች። በተለይ የንባብ ፓርክ መኖሩ እንደፈለጋት ከጓደኞቿ ጋር በመሆን እንድትወያይ አግዟታል። ቤተ መጻሐፍት ገብቶ በሹክሹክታ ከማውራትም ታድጓታል። ስለዚህም ቤቷ ስትሄድ ብቻ ሳይሆን በእረፍት ጊዜዋ ጭምር ትምህርት ቤት ውስጥ ሆናም ነጻነት ኖሯት እንድታነብ ረድቷታል።
ዛሬ የተማረችውን ዛሬ ታጠናለች፤ ለነገ የምትለውም የላትም። ጎን ለጎን ለፈተና ያግዙኛል ብላ የምታስበውን አጋዥ መጸሐፍትም ታነባለች። ለዚህ ደግሞ አዲሱ ሥርዓተ ትምህርት እንዳገዛትም ታነሳለች። የትምህርቱ ዝግጅቱና የመማር ማስተማሩ ሥራ ብዙ ምቹ ሁኔታን የፈጠረላት እንደሆነም ታምናለች። ከስር ከስር የሚሰጣቸውን ትምህርት በሶፍት ኮፒና በሀርድኮፒ ስለምታገኘው ለማንበብ ተመችቷታል።
ምህረት በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት ነገሮች እንደቀለሉም ትናገራለች። ለአብነት አድርጋ ያነሳችልንም ታችኛው ክፍል ድረስ ወርዶ ማጥናትን ነው። ‹‹አዲሱ የትምህር ስርዓት ለሁሉም በእኩል ደረጃ የተጀመረ ስለሆነ ያለንበትን የክፍል ደረጃ ብቻ እንድናነብና እንድንዘጋጅ ነው የሚያደርገው። ትምህርቱ ለክፍል ደረጃው በሚመጥን መልኩ የተዘጋጀ በመሆኑ ደግሞ ውጤታማ ተማሪ እንደሚያደርገን አምናለሁ›› ብላናለችም።
ልጆች ምህረት ለእናንተ ምክሮችን መለገስ ትፈልጋለች። የመጀመሪያ ያደረገችውም ትምህርታችሁን ከምንም በላይ አስቀድሙ የሚል ነው። ምክንያቱም በእርሷ እምነት ትምህርት ማንኛውንም ነገር መለወጥ የሚችል ስለሆነ ነው። ማንም ሰነፍ ሆኖ አልተፈጠረምና ጠንክራችሁ አንብቡ፤ ጎበዝ ለመሆንም ጣሩ ትላለች። የመጠቀምና የመስራት ጉዳይ ልዩነቶችን ያመጣልና ሁልጊዜ አሸናፊ ለመሆን ትጉ ባይ ናት።
ልጆች ምህረት መሆን የምትፈልገውም መምህር ነው። ምክንያቷን ስታነሳም ማንኛውም ሙያ ያለመምህር መብቀልም ፤ መኖርም አይችልም ብላ ማመኗ ነው። እናም ብቁ ተማሪዎችን አፍርታ ለአገሯ ማበርከት ትፈልጋለችና ሙያውን መርጠዋለች።
እንደ ምህረት ሁላ በካራ አሎ ቅድመ መደበኛና መጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት የምትማረው ዮርዳኖስ ዳኜ ስትሆን፤ እርሷም የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ናት። በአዲሱ ስርዓተ ትምህርት የሚጀመረውን አገር አቀፍ የስድስተኛ ክፍል ፈተና ትወስዳለች። ስለዚህም ገና ከአሁኑ ራሷን ለፈተናው እያዘጋጀች ነው። በዋናነት ዝግጅቷን እያደረገች ያለችውም ፕሮግራም አውጥታ በማጥናት ነው። ጎን ለጎን ባላት ጊዜ ቤተሰቧን ታግዛለች።
አዲሱ የትምህርት ስርዓትን በጣም ወዳዋለች። ምክንያቱም በእርሱ ውስጥ አገሯን ማየት ጀምራለች። ስለውጪው ባህልና ወግ ሳይሆን ስለ አገሯ እየተማረች በመሆኑም ደስተዋ ወደር የለውም። ምክንያቱም የማታውቀውን ባህል፤ ወግ እያወቀች ነው። አገር ወዳድነትን እየተማረችበት ነው። በስነምግባር ዙሪያ የሚሰጡ ትምህርቶችም መኖራቸው ደስታን ፈጥሮላታል። ከሁሉም በላይ ግን ልዩ ተሰጥኦዋ አውቃ እንድትጓዝ እድልን ስለሰጣት ደስተኛ ናት።
ልጆች በእነዮርዳኖስ ትምህርት ቤት ልዩ የመማር ማስተማር ሥራ መከናወኑም ለፈተና ዝግጅታቸው እጅጉን እንደሚያግዝ ነግራናለች። ለአብነት የጠቀሰችልን ትምህርት ቤቱ ለተማሪዎች በማሰብ የቅዳሜ ትምህርትን ማስጀመሩን ነው። ትምህርቱ ሲሰጥ ከሰኞ እስከ አርብ የተማሩትን የሚከለስበት በመሆኑ ደስተኛ አድርጓታል። ምክንያቱም ለጥናት ነገሮችን እንድታስተካክል መንገድ ከፍቶላታል። በዚያ ላይ ከሰኞ እስከ አርብ በነበራት ቆይታ ምን ያህል እውቀት እንደጨበጠች የሚያረጋግጥላት እንደሆነ አይታበታለች። ስለዚህም ተማሪዎች የተፈጠረላቸውን መልካም አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመው ውጤታማ መሆን እንዳለባቸው ትመክራለች። እኛም ተማሪዎቹ እንዳሉት በተለይም ተፈታኞች ጊዜያችሁን በአግባቡ መጠቀም እንዳለባችሁ
ሳንጠቁም አናልፍም። መልካም ሰንበት ይሁንላችሁ !!
ጽጌረዳ ጫንያው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20/2015