በ1880 ዓም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ በሐረር ከተማ ይኖር የነበረው ፈረንሳዊው ገጣሚ ዣን ኒኮላስ አርተር ራምቦ የተወለደው ከዛሬ 168 ዓመታት በፊት ጥቅምት 10 ቀን 1847 ዓ.ም ነበር። ይህን በማስመልከትም ከተለያዩ ምንጮች ያገኘናቸውን ጽሁፎች በአጭሩ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
ሙሉ ስሙ ዣን አርተር ራምቦ ይባላል (Jean Arthur Rimbaud) እአአ ኦክቶበር 20 ቀን 1854 ዓ.ም ፈረንሳይ ቻርሌቪል (Charleville) ነው የተወለደው። የራምቦ አባት በውትድርና ትልቁን የፈረንሳይ ሽልማት “legion of honor” እስከማግኘት የደረሰና በፈረንሳይ የአልጄሪያ ዘመቻ የተሳተፈ የበቃ ወታደር ነበር። ለወታደር አባቱና የገበሬ ልጅ ለሆነችው እናቱ ራምቦ ሁለተኛ ልጅ ነው። የራምቦ አባት ፍሬድሪክ ሪምባው በሞያው ምክንያት ከቤተሰቡ ጋር ስለማይኖር ልጆቹን የመንከባከብና የማሳደጉ ስራ እናታቸው ላይ የወደቀ ነበር። አባት አንዴ የክሪሚያን ጦርነት ሲዋጋ፣ አንዴ ለሰርዲኒያ ዘመቻ ሲጠራ ልጆች እንዳሉት እንጂ ምን ላይ እንደደረሱ የማየት እድሉ አልነበረውም። ባጭሩ ራምቦ እናት እንጂ አባት ምን እንደሆነ አያውቅም ቢባል ይቀላል። ይሁንና አባትየው ቀለል ያለ፤ ተጫዋች እና ለጋስ ነበር ይባላል።
የራምቦ እናት ማሪ ሪምባው በተቃራኒው ኮስታራ ሴት ነበረች። ልጆቿ ያላባት አድገው ከሰው በታች እንዳይሆኑባት ትሰጋ ነበር። በትምህርታቸውም ወደ ኋላ እንዳይቀሩ ትፈራ ነበር። በዚህም ምክንያት በከባድ ቁጥጥርና ዲስፕሊን ነው ያሳደገቻቸው። እንደ ልጅ መጫወት የለ፣ መዝናናት የለ። የራምቦ ህይወት ከቤት ትምህርት ቤት ሆነ። በዛ ላይ እናቱ እስኪሰለቸው ነበር እንዲያጠና የምታስገድደው። በትምህርት ላይ ለሚፈጥሩት ስህተት 100 መስመር የላቲን ግጥሞችን በቃል እንዲይዙ ታደርጋለች አልያም ምግብ ይከለከላሉ። ከዚህም ባለፈ ራምቦ ላቲን ትምህርት ቤት መግባቱን የማይወደው ሲሆን የእናቱን ቁጥጥርም አይፈልገውም ነበር። እናት በተቃራኒው ቁጥጥሯን በማጥበቅ እስከ 16 አመታቸው ድረስ ትምህርት ቤት የምታደርሳቸው ራሷ ነበረች። ይህ ሁኔታ ራምቦን ገና በልጅነት እድሜው እንዲያምጽ አደረገው። የአመጹ መሳሪያ ደግሞ ብዕርና ወረቀት ነበር። ራምቦ ብዕሩን አቀባብሎ መተኮሱን ተያያዘው። ገና 20 ዓመት ሳይደፍን ዛሬም ድረስ ፈረንሳይ ስሙን በክብር እንድትጠራ ያስደረጉትን ድንቅ ግጥሞቹን ጻፈ። ስለነጻነት፣ ስለጀብዱ፣ ስለ ጉዞ!
የራምቦ የመጀመሪያ ግጥሙ ዘ ኦርፋንስ ኒው ይር ጊፍት የሚል ነበር። ኮሌጅ ከገባ በኋላም ከመምህሩ ጋር ቅርርብ የነበረው ሲሆን መምህሩም እንዲጽፍ እና እንዲያነብ ያበረታታው ነበር። ሆኖም መምህሩ እንዲያነብ የሰጠው የቪክቶር ሁጎ ሌ ሚዘረብል መጽሀፍ የራምቦን እናት አላስደሰተም ነበር። የልጆችን ሞራል የሚያበላሽ መጽሀፍ ነው ብላ ያሰበችው የራምቦ እናት የተቃውሞ ደብዳቤ ጽፋም ነበር።
እ.አ.አ በሐምሌ 1870 ዓ.ም የፍራንኮ-ጀርመን ጦርነት ሲቀሰቀስ የአርተር ራምቦ የመደበኛ ትምህርት ጉዞ ተቋጨ። ከዚህ ጊዜ በኋላ ወደ መደበኛ ትምህርት ያልተመለሰው ራምቦ ታታሪ አንባቢ ሆነ። በንባቡም ከአብዮትና አብዮተኝነት ጋር ተዋወቀና ያነበበውን ወደ ተግባር ለመቀየር ወደ ፓሪስ አቀና። ፓሪስ ሲደርስ ያለ ቲኬት ተጉዘሃል ተብሎ ለተወሰነ ጊዜ ከታሰረ በኋላ ተለቀቀ። ከእስር ከወጣ በኋላ አንዴ ቤልጂዬም አንዴ ፈረንሳይ ሲመላለስ ቆየና በመጨረሻም በእናቱ አማካኝነት ወደ ትውልድ ስፍራው ቻርሌቪል ተመለሰ።
ራምቦን ወደ ሀረር ያስመጣው ፒየር ባርዴ የሚባል ፈረንሳዊ ነጋዴና ሀገር አሳሽ (explorer) ነው። ይህ ሰው በአደን (የየመን የወደብ ከተማ) ያቋቋመው የንግድ ኩባንያ በሀረር ለከፈተው ቅርንጫፍ ወኪል ሆኖ እንዲሰራለት የኩባንያው ተቀጣሪ የነበረውን አርተር ራምቦን ይጠይቀዋል። ራምቦም ሳያመነታ ግብዣውን ተቀበለና ባህር ተሻግሮ ወደ ሀረር መጣ። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ባርዴ ራሱ ተጠቃሎ ወደ ሀረር ገባ። ሁለቱ ፈረንሳዊያን ለአምስት ዓመታት ያህል በሰላም አብረው ሲሰሩ ቆዩና በ1885 በግጭት ተለያዩ።
ራምቦ ከባርዴ ከተለየ በኋላ ለ15 ዓመታት የአንኮበር ነዋሪ ከነበረውና ላባቱት ከሚባለው ሌላ ፈረንሳዊ ጋር ሽርክና ፈጥሮ መስራት ጀመረ። ይህም ሰው “የሸዋው ንጉስ ምኒልክ ጠመንጃ በጣም ይፈልጋሉ፤ እኛ እንውሰድላቸውና ትርፋማ እንሁን” የሚል ሀሳብ ለራምቦ አቀረበለት። ራምቦም ትርፉ ስላጓጓው በላባቱት ሃሳብ ተስማማ። ሁለቱ ሸሪኮች በተስማሙት መሰረት በርካታ ጠብመንጃዎችን ከወደብ ጭነው ወደ አንኮበር ነጎዱ። እዚያ ሲደርሱ ግን ንጉስ ምኒልክ አስቀድመው በርካታ መሳሪያዎችን እንደገዙ ተረዱ። እናም ያለሙት ሁሉ መና ሆኖ ቀረ። የታሰበው ትርፍን የማግኘት ህልም እንደ ጉም ተበተነ።
ከዚያ ክስተት በኋላ ራምቦ ከላባቱት ጋር ተለያየ። በማስከተልም ሲዛር ቲያ ከሚባል ነጋዴ ጋር ሽሪክ ሆነ። በዚህኛው ዙር ግን ሀብታም የመሆን ምኞቱ እውን መሆን ጀመረ። ከሁለት ዓመታት በኋላ ግን የቲዩመር እጢ ጉልበቱ ላይ ስለወጣበት ለህክምና ወደ ማርሴ (ፈረንሳይ) ለመመለስ ተገደደ። ህመሙ ወደ ካንሰር ተቀይሮ ኖሮ በዚያው ህይወቱን አሰናበተው።
ከራምቦ የግጥም ስራዎች መካከል ‹‹The Drunken Boat››፣ ‹‹A Season in Hell›› እና ‹‹Illuminations›› የሚሉት ይጠቀሳሉ። ጋዜጠኛ ስንዱ አበበ ‹‹ራምቦ›› በሚል ርዕስ የአርተር ራምቦን ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ለአንባቢያን አበርክታለች። ራምቦ በሐረር ከተማ ሳለ ይኖርበት የነበረው ቤት በአሁኑ ወቅት ወደዚያው በሚሄዱ ጎብኚዎች ይጎበኛል።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 20 ቀን 2015 ዓ.ም