አወዛጋቢው ደራሲ

ኅሩይ የማን ነው? ንጉሤስ ከወዴት አለ? አውግቸውስ ማነው?… ሁሉንም ፈልጎ አንዱን ከማግኘት፣ አንዱን ፈልጎ ሁሉንም ማወቅ ይቀላል። ይኼ አንዱ፤ ይህ እርሱ ብዕርን በእጁ ብቻ ሳይሆን በልቡም ጭምር የሚጨብጥ አንድ አውታታ ምስኪን ደራሲ ነው። በሥራው የሚያስደምም፣ በስምና ኑሮው የሚያወዛግብ፣ ብዕሩ የማይነጥፍ፣ ልቡም የማይነትብ ታላቅ ደራሲ ነው። አንዳንዴ ሕይወቱንም ጭምር የሚደርስ ይመስላል። ከጎጃም ተነስቶ አዲስ አበባ፣ ከቤተክርስቲያን ወደ ጎዳና፣ ከቅኔ እስከተሰበረ የሕይወት መቅኔ፣ ከመርካቶ እስከ…እያለ በመጽሐፍት ሻጭነትም፣ ከ20 በላይ መጽሐፍትን እስከመጻፍ የበቃም ደራሲ ነው።

በሥራዎቹ ካልሆነ በስተቀር በስም ጠርቶ ስለ እርሱ ለማውራት ሳያዳግት አይቀርም። ምክንያቱም ስሞቹም እንደሥራዎቹ በየአቅጣጫው፣ በየፊላው ስርና በየፊናው የተከማቹ በመሆናቸው ነው። አንዳንድ በእርግጠኝነት ሚዛን ያልተለኩትን እንኳን ብንተው ለአብነት የሚሆኑ ሦስት ስያሜዎች አሉት። ገና ሲወለድ ወላጆቹ የሰየሙትና የሚያውቁት “ንጉሤ ሚናስ” በሚል ነበር።

ቀጥሎ ደግሞ በሁለተኛነት “ኅሩይ ሚናስ” ያወጡለት እጅግ የሚወዱት አንድ አጎቱ ቢሆንም በዚህ ስም ሲጠሩት የነበሩም ቀላል አይደሉም። ከእነዚህ ሁሉ በኋላ የመጣው “አውግቸው ተረፈ” የተሰኘውን ስሙን እንኳን በኑሮ መሃል ድንገት ለራሱ የሰየመው ስም እንጂ የትውልድ ቀዬው በዚህ አያውቀውም። በአንድ ወቅት መርካቶ ውስጥ ብዙዎች የሚፈልጉት መጽሐፍ ሻጭ ነበር። ወደ አውግቸውነት የተለወጠው የዚህን ጊዜ ራሱን ሲያስተዋውቅ ነበር። የኋላም የብዕር ስሙ ይኼው ሆነ።

እንግዲህ ስለእርሱ በስም ከማውጋት ይልቅ በሥራው ማውሳት ሳይቀል አይቀርምና “ወይ አዲስ አበባ” የሚለውን መጽሐፍን እንጥቀስ…እስቲ ታዲያ ከአውግቸውና “ወይ አዲስ አበባ” ከሚለው ማንስ ነው ታዋቂ? ማንስ ነው ዝነኛ? ከባለቤቱ ይልቅ መጽሐፉ፣ ከሠሪው ይልቅ ሥራው፣ ከአናጢው ይልቅ ብርኩማው ዝነኛ ነው ላለማለት አይቻልም። እንግዲህ በዚያም ሲሉ በዚህ ንጉሤ የሚሉት ስሙ ሳይነግስ ቀረና የመጠሪያውን ዙፋን በአውግቸው ተረፈና በኅሩይ ሚናስ ተያዘ።

ዛሬ ዝናውን እንድናነሳለት ያደረገን በሥራው ነውና ምን ሠርቶ…እንበል። ደራሲነት፣ ተርጓሚነትና አርታኢነት መታወቂያዎቹ ናቸው። በድርሰት ሥራው ከፍ ተደርጎ የሚነገርለት “ወይ አዲስ አበባ” እና “እብዱ” የተሰኙት የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብ የሆኑ መጽሐፍቶቹ ናቸው። የመጀመሪያውን በ1979ዓ.ም ሁለተኛውንም በ2002ዓ.ም አስነብቦ አድናቆትን ተቀብሎባቸዋል። “እነ ወተቴ”፣ “የሙኒት ምርጫ”፣ “ኒኒ በርጋጊዋ”፣ “ማሞ ቢጩ”፣ “ስለሺና ስምንተኛው ሺ”፣ “ሁለት ሌሊት ከዲያቢሎስ ጋር” የሚሉትን መጽሐፍቶች በመሃል ሲያስነብብ ቆይቷል። ግራ ቀኝ እያለ ደግሞ ጋዜጣና መጽሔቶችንም አስሷል። “ኒኒ በርጋጊዋ” በዚሁ የአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ጽፎ በማስነበብ በሰዓቱ እጅግ ተወዳጅ የሆነለት ሥራው ነበር።

በመጽሔቶች ላይም እየጻፈ በርከት ያሉትን ምርጥ ጽሁፎችን አስነብቧል። በርከት ያሉ የውጭ መጽሐፍትን በመተርጎም ከራሱ ሥራዎች ባልተናነሰ ገኖባቸዋል። በዚህ ሥራውም ያገኘው አድናቆት፣ ያካበተው ዝና ቀላል አይደለም። ለትርጉም ሥራው የመጀመሪያ የሆነችው “ያንገት ጌጡ” ስትሆን ቀጥሎም የሄኔሪ ባልዛክን “ሚስኪኗ ከበርቴ”፣ የሀርሎድ ሮቢንሰን “ባይታወር” እና “ጩቤው”፣ የሲዲኒ ሺልደን “ደመኛው ሙሽራ” የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናቸው።

ከሕይወት ጨለፍታ…ፊታችንን ወደ ውልደትና ትውልድ ቀዬው አሻቅበን ከተመለከትን ሥፍራው ወደ ብዙ ዕውቅ ደራሲያን ወንዝ ያሻግረናል። የተወለደው በ1943ዓ.ም ሲሆን የተወለደውም በጎጃም፣ ከጎጃምም በቢቸና አውራጃ ውስጥ ነበር። ልጅ ሆኖ በጎጃም አሉ በተባሉ አብያተ ቅኔያት ሁሉ ዞሯል። ሰንብት…ዳዊት…ድጓ…ብቻ ከሁሉም ጠግቦ በልቷል። በዚያን ጊዜ እንደ ሚፈጽመው ግብሩ ቢሆንማ ኖሮ እንደ ወላጆቹና እንደቀዬው እሳቤ ሁሉ ጳጳስ አሊያም ቄስ፣ ዲያቆን አሊያም ሰባኪ ወንጌል በሆነ ነበር። ግን አልሆነም…የያኔውን በንጉሤነቱ የተመኙለትንና ያዩለትን ወደፊታቸውን ትቶ ወደ ፊቱን ፍለጋ ወጣ። ያየውን እየተከተለ ደራሲውን አውግቸውን ለመሆን በ1960 ዓ.ም አዲስ አበባ ገባ።

“ወይ አዲስ አበባ” ያለው የዚህን ጊዜ ይሆን…ገና እንደመጣ ከመንፈሳዊው ዓለም ወጥቶ ወደ ውጭ አልተመለከትም።“ቀጨኔ መድኃኔዓለም ገባሁና አልስማማ ሲለኝ ቀጥሎ ወደ ቅድስተ ማርያም ሄድኩ። በዚያም አንድ ጓደኛዬን ስላገኘሁት ዝም ብዬ ከዚያው ለአንድ ዓመት ተቀመጥኩ። የተማሪዎች ማደሪያ ስለነበረ ቅዳሴ እንማራለን ብለን ተመልሰን ገባን። እየተማርን በመሃል እናቋርጥ ስለነበረ ከዚያም አባረሩን” ሲል በአንድ ወቅት በአንደበቱ ተናግሮ ነበር። እናም ከዚህ መባረር በኋላ ነበር የበረንዳ አዳሪ ሆኖ የውጪዋን አዲስ አበባን የተዋወቃት። ከጓደኛው ጋር ሆነው ቁራሽ እንጀራና ፍርፋሪ እየተመገቡ በመጽዋቹ ቸርነት ለስድስት ወራት ያህል ዘለቁ።

የጎዳናው ሕይወት ለ17 ዓመቱ አውግቸውና ጓደኛው እጅግ አስከፊና እንግዳ ነበር። ኑሮን በእንዲህ ለመዝለቅ እንደማይቻል እየገባቸው በየግላቸው ያብሰለስሉት ነበር። እናም አንድ ሌላ የሕይወት መንገድ የግድ ነበር። ዓይናቸውን ወዲህና ወዲያ እየወረወሩ በየፊናቸው አዲስ ሕይወት ፍለጋ ያማትሩ ጀመር። አውግቸው ከነበረበት ጎዳና ተራምዶ በቀጥታ ወደ ጡረታ ሰፈር ሄደ። አንድ ተስፋ የሚሆነውንም ነገር አገኘ። ከአንድ ልበ ብርሃን ጋር ተገናኝቶም እርሱን እየመራ ወደሚፈልገው ቦታ ሁሉ ማድረስ እንደ ሥራ ገባበት። ትንሽዬ ሳንቲም እየተከፈለውም ከዚሁ ሰው ጋር ለሁለት ዓመታት ተቀመጠ።

ማየት ላልቻለው ዓይን እየሆነለት ሲመራውና የገባበት ገብቶ ሲወጣ ከተማዋን ከእግር እስከ ራስ ከማወቅም ከሰዎች ጋር መተዋወቁንም አትርፎበታል። እንደገና ሌላ የተሻለ ዕድል አገኘ። አለቃ ነብዩ ልዑል የተባሉ አንድ ሌላ ልበ ብርሃንን እየመራ በወር 12 ብር ይከፍሉታል። አለቃው የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪ ስለነበሩ የግላቸው ቢሮም ነበራቸውና የአውግቸው ሥራ እጅ ይዞ በመምራቱ ላይ ብቻ አልቆመም።

ያነብላቸዋል። የሚፈልጉትንና የሚሉትንም ይጽፍላቸዋል። የሚሉትን መጽሐፍ እየፈለገ፣ ከሚፈልጉት ቦታ ላይ ያገላብጥላቸዋል። ከእኚህ ሰው ጋር እንዲህ ባለ መልኩ የዘለቀው ለአንድ ዓመት ብቻ ቢሆንም፤ ምናልባትም ግን ትልቁን የሕይወት መዳረሻ መሠረት ያኖረው በዚህን ጊዜ ነበር ለማለት ይቻላል።

ከዚህ በኋላ አውግቸው እንደገና ከፍ ያለበትን ሌላ የሕይወት አጋጣሚ ተገናኘ። በጓደኛው ጥቆማ ተቀጥሮ ወደ መጽሐፍት ንግድ ገባ። ሕይወቱን መጽሐፍቱን በመሸጥ ሳይገታ ትምህርቱን የመማር ሃሳብ በራለት። ቀን ቀን መጽሐፍ በመሸጥ ሲኳትን ውሎ ማታ ማታ ደግሞ ካቆመበት 3ኛ ክፍል ትምህርቱን ቀጠለ።

ቀጥሎ በነበሩት የትምህርት ዓመታት ገሚሱን የቀን ገሚሱን የማታ እያለ 12ኛ ክፍልን ለማጠናቀቀ በቃ። አጠናቆም ወደ ዩኒቨርሲቲ በመግባት ገና የ1ኛ ዓመት ተማሪ ሳለ የፖለቲካው እሳት እየነደደና ነበልባሉ እየተፋፋመ ሲመጣ በነበረው የኢህአፓ እንቅስቃሴ ትምህርቱን አቋርጦ ለመውጣት ተገደደ። ከመጽሐፍት ሻጭነት ወጥቶ እንደሄደውም ተመልሶ ወደ መጽሐፍ ሻጭነቱ ገባ።

ሥራውን እያዳበረም ብዙ ደንበኞችን አፈራ። ከእነዚህ ደንበኞቹም መካከል አንደኛው ስብሐት ገ/ እግዚአብሔር ነበር። አውግቸው በዚህ ሥራው ውስጥ እየጠለቀ ሲሄድ ከመሸጫው ስፍራው እንደተቀመጠ ከመሸጡ ይልቅ ማንበቡ እየገዘፈበት ሄደ። ቁጭ ብሎ እያነበበ ቀልቡን ስለሚሰውረው ገዢው ፊቱ ቆሞ ሂሳቡን ሲጠይቀው ከተመስጦው የተነሳ በደመነፍስ ውሰደው ይል እንደነበረ በወቅቱ የሚያውቁት ይናገራሉ። ምናልባት ለዚህም ይሆናል ከእርሱ ጋር በመጽሐፍ ሽያጭ የነበሩ ጓደኞቹ ሁሉ የኋላ የመጽሐፍ ቤት ባለቤቶች ሲሆኑ እርሱ ግን ብቻውን መቅረቱ…

አውግቸውና ስብሐት…ከተቀራረቡ በኋላ የጻፋቸውን ጽሁፎች እንዲያይለት ለስብሐት ይሰጠው ነበር። ጽሁፎቹን ሲያደንቅለት የነበረው ስብሐትም አውግቸው በኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ውስጥ በአርታኢነት እንዲቀጠር አደረገው። በኩራዝ የነበረው ቆይታ ጥሩም ሆነ መጥፎ ለማለት ራሱ አውግቸውም የሚቸገርበት ይመስለኛል። እዚያ ቦታ ላይ ሁለት ጽንፍ የያዙ ነገሮች ወደ ሕይወቱ እንዲመጣ ምክንያት ሆኗል። የመጀመሪያው ነገር የአርትኦት ሥራው ለደራሲነቱ የሚሆነውን ትልቅ ዕውቀትና አቅም ሸምቶበታል። በሌላ በኩል ደግሞ ፋታ አልባ ያደረገው ሥራው በአዕምሮ ህመም እንዲያዝ አድርጎታል። “እኔ የታመምኩት ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ስሠራ ከጧት ጀምሮ እስከ ምሽቱ ሁለት ሰዓት ድረስ ያለማቋረጥ አነብ ስለነበርም ነው” ብሎ ነበር ሲጠየቅ።

አውግቸው በደራሲነቱ የጻፈው እና ያስነበበው ቁጥር ፈጽሞ የሚመጣጠኑ አይደሉም። ቀን ከሌት እያነበበና እየጻፈ ውሎ ቢያድርም ለመጽሐፍነት አሊያም በሌላ አጋጣሚ ከአንባቢ የደረሱት ግን በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። ይጽፋል… ደግሞም ይጽፋል… ግን እንዴትና ምን ሆነው ከወዴትስ ገቡ? አይታወቅም። ምናልባት ከእርሱና ከእግዜሩ በስተቀር… በአንድ ወቅት ስብሐት ገ/ እግዚአብሔር አውግቸው ይሰጠው ስለነበሩት ጽሁፎቹ ሲያነሳ ካላቸው ነገሮች ውስጥ እንዲህ የሚል ነበረበት፤ “አንድ ጊዜ ርዕስ የሌለው ረዥም ልቦለድ ደርሶ አንብቤው ከመጠን በላይ ተገርሜበት በኋላ ግን ጉድጓድ ውስጥ ጣለው” የሚል ነበር። አውግቸው ምን ተሰምቶት ይህን እንዳደረገ ግን የሚያውቅ አልነበረም። አብዛኛው ሥራዎቹም እንዲህና በመሳሰሉ ምክንያቶች ከማይታዩበት ቤርሙዳ ሰምጠዋል።

አውግቸውን በቅርበት ከሚያውቁት መሃከል አንደኛው ደራሲ አበረ አዳሙ ነው። በአንድ ወቅትም ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ስለ አውግቸው ብዙ ነገሮችን አንስቶ ነበር። “ከአውግቸው ሥራዎች ወይ አዲስ አበባን የሚያክል የለም። የዚህ አጭር ልቦለድ ታሪክም የራሱ የአውግቸው ታሪክ ነው” ብሎ ያምናል። ብዙ ደራሲያን ስለ አውግቸው ጭምትነት በማንሳት ብዙ ማውራትም ሆነ ከሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍን የሚመቸው ዓይነት አነበረም። ከዚያ ይልቅ ለብቻው ቁጭ ብሎ በጥልቀት ማሰብና ከራሱ ጋር ማውጋትን የሚመርጥ ነበር።

በዚህ ላይ ደግሞ ቆራጥና በቃሉ ሕገ ደንብ የሚመራ፣ ያለውንና ያሰበውን ነገር ከመከወን ወደኋላ የማይል ሰው ነው። በ1987ዓ.ም አካባቢም የሆነው እንዲህ ነበር፤ አውግቸው በዚህም ዓመት ማንበብ ያለብኝ መዝገበ ቃላትን ነው ሲል እንደቀልድ ተናገረ። እንዳለውም ቃሉን ጠብቆ በዚያ ዓመት መዝገበ ቃላትን ብቻ ሲያነብ ከረመ። አውግቸው እንዲህ ያለው አስገራሚም ሰው ነበር። “ኅሩይ መጽሐፍትን እየሸጠ በነበረበት ወቅት ጽሁፎቹ በስብሐት በኩል በመጽሔቶች ላይ ይታተሙ ነበር።

ታዲያ ጓደኞቹ አንተን ብሎ ደራሲ ብለው እንዳይዘባበቱበት ስለፈራ የሚጽፋቸውን አጫጭር ልቦለዶች በብዕር ስሙ ነበር የሚያወጣው” ሲል ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ተናግሯል። አውግቸው የብዕር ስሞቹ ብዙ ናቸው በማለትም ብዙዎች የማያውቁት “አዳነ ቸኮል” የተሰኘው የብዕር ስምም የእርሱ መሆኑን ይገልጻል። አውግቸውን በአርታኢነት ወደ ኩራዝ የወሰደው ስብሐት ነው የሚሉ ቢኖሩም እንዳለጌታ ግን ዳኛቸው ወርቁ ነው ይላል።

አስደምሞ አወዛጋቢው…ዝምተኛው አውግቸው አንዳንድ ጊዜ ድንገት እንደ መድፍ እየተተኮሰ በአስገራሚነቱ ላይ አወዛጋቢነትንም ያክልበታል። በ1970ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የሆነውም እንዲህ ነበር…ለዚህ የነሸጠው አሊያም ግንፍል ያደረገው ምን እንደሆነ ባይታወቅም አውግቸው ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያምን ትግል ካልገጠምኩ ሲል ቤተ መንግሥት ድረስ ሄደ። በሩ ጋር ሲደርስ ደምስሩን ገትሮ ወደ ጠባቂዎቹ እያፈጠጠ “ኮሎኔል መንግስቱን ጥሩልኝ!” አለ። በሁኔታው የተገረሙት ጠባቂዎችም “እኮ ለምን?” ይሉታል በግራ መጋባት። “ትግል ልገጥመው እፈልጋለሁ” በማለት ቀጠለላቸው “እኔን ትግል ገጥሞ መጣል ሳይችል እንዴት ነው ሀገር ሊገዛ የሚችለው?” ሲል አምባረቀ። ይኼኔ ወታደሮች አፈፍ አድርገው ሰፈሩበት። ደህና አድርገው ከቀጠቀጡት በኋላ ወደ እስር ቤት ወረወሩት። ቀላል ለማይባል ጊዜም በእስር ሰነበተ።

ደራሲው ሞትን ወደ ሕይወት የለወጠ ጀግና ነው። በ1970ዎቹ አጋማሽ በአዕምሮ ህመም በአማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ አሳልፏል። ለህመሙ መንስኤ ቀደም ሲል በአርትኦት ሥራው ከነበረበት ጫና ባሻገር በኋላም በብቸኝነት በሩን ዘግቶ ሲያነብ የነበረባቸው ጊዜያትም ጭምር ናቸው። ሃሳብና ጭንቀት እያበዛ ድባቴው ሲወቃው ከርሟል። ተደማምሮም ራሱን አጣው። ባጣው ራሱ ውስጥም ለማንም የማይገኘውን ነገር አገኘ። ያገኘውም “እብዱ” የተሰኘውን መጽሐፉን ነበር። ከሥራዎቹ ሁሉ ወጣ ያለና እጅግ አነጋጋሪም ነው። በዚህ ሁኔታ ፈጽሞ ማንም ሰው ይጽፈዋል ተብሎ የማይታሰብ ነበር።

እብድ ጨርቁን ይጥላል እንጂ እብደቱን ጽፎ ያስነብባል ብሎ መጠበቅ እንዴትስ ተብሎ…ግን እርሱ አደረገው። በታሪክ እንዲህ እንደ አውግቸው በአዕምሮ መታወክ ውስጥ ሆኖ መጽሐፍ ለመጻፍ የቻለም ባለመኖሩ በዚህም የመጀመሪያው ሳይሆን አይቀርም። ይህን መጽሐፍ ለየት የሚያደርገው በአዕምሮ ህመም ውስጥ ሆኖ ስለጻፈው ብቻ ሳይሆን በይዘቱም በሥነ አዕምሮ የህክምና ዘርፍ ውስጥ ለምርምርና ለማስተማሪያነት የመሆን አቅም እንዳለው ብዙ ዶክተሮች ምስክርነታቸውን ሰጥተውበታል። ለዚህ ለሠራው ጀብዱም በአማኑኤል ሆስፒታል ውስጥ ከሚገኙ ክፍሎች አንዱን በስሙ ሰይመውለታል። አውግቸው ከተበረከቱለት ሽልማቶች መካከል የ2008ዓ.ም የበጎ ሰው ሽልማት አንዱ ነበር።

የዝነኛው መጨረሻ…ሁሉን አልፎ ከሁሉም ለማለፍ ሲቃረብ ግራጫ የሕይወት ጥላ አጠላበት። ያቺ መነሻው የነበረችው መርካቶ ለመጨረሻው ጥቂት እስኪቀረው መኖሪያው ነበረች። ከሰዎች ጋር ለጨዋታም ሆነ ወጣ ብሎ ከቤቱ ለመራቅ አልተቻለውም። በዚያ ላይ ደግሞ ምኑም ባልገባው የአንገት በሽታ ለመዟዟር ተስኖት በስቃይ አሳልፏል። ትዳር ይዞ ሁለት ልጆችንም ለማፍራት ችሏል። መጨረሻውም ይኼው ነው…ሰኔ ከሰኞው ተጋጠመና ሰኔ 10 ቀን 2011ዓ.ም አውግቸው ኅሩይና ንጉሤንም ይዞ አረፈ። ሞተ። ጻፈ አስደመመ። ጻፈ ተደነቀ። ኖረ አወዛገበ። ሁሉንም ያውቅበታል። ሁሉንም ይችልበታል።

ሙሉጌታ ብርሃኑ

አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2016 ዓ.ም

Recommended For You