ትናንት በወጡበት የስኬት ከፍታ፣ በወጡበት የብቃት ሰገነት እምቢ! አልወርድ…አሻፈረኝ! ብሎ ዛሬም ድረስ መክረም እንደምን ይቻላል… አስችሎት መቻልን ያሳየ እንቁ ሙዚቀኛ ግን ወዲህ አለ። ብዙዎች ወጡ! ወጡ! ሲባል ከምኔው እንደሆን ወርደው በሚፈርጡበት የሙዚቃ ኢንዱስትሪው ውስጥ የሌላውን ሳይነካ የራሱንም ሳያስነካ፣ ሳያዳልጠውና ዝናው ሳያሰምጠው ደርሶ ዛሬም በሌላ ከፍታ ከፍ ብሎ ታይቷል።
“አንድ ቃል” ድሮም ለሚገባው አንድ ቃል ነው። ተወዳጁ ድምጻዊ ሚካኤል በላይነህ ከሰሞኑ በአንድ ቃል ምርጡን! የአልበም ሥራ ይዞ መጥቷል። እርሱ ይወደዳል። ሥራው ይናፈቃል። እንደተወደደ ሥራውን ለናፈቁ ሁሉ እንደ አዲስ ዓመት ገጽ በረከት ሆኗል። ሙዚቀኛ ነኝ ብሎ ለራሱ እንኳን ሳያምንበት በጀመረውና በሠራው ሥራ አድናቆትና ክብርን ተጎናጽፏል። ለረዥም ጊዜያት በሙዚቃና ሙዚቀኝነት ሲዋልል ኖሯል። ሆኖም የሙዚቃን ጠረን ምገው፣ ሥራውን በመጀመር አድማጭ ከተዋወቃቸው ጊዜ አንስቶ በክብራቸው እንዳሉ አሉ ከሚባሉ ጥቂት በጣት የሚቆጠሩት ጋር ነው። የአድማጩን የሙዚቃ ጥም ያረካ፣ የጥበብን አንጀት ያራሰ ድምጻዊ ነው። ደግሞ ድምጻዊ ብቻ ሳይሆን የግጥምና ዜማ ደራሲም ጭምር ነው። ሦስቱ የአልበም ትርንጎዎች በ20 ዓመታት ውስጥ ያፈራቸው የሥራ ፍሬዎቹ ናቸው።
ተወልዶ ያደገው እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው። የተወለደው በኮተቤ ቢሆንም ያደገው ግን እዚህ ሰፈር ነው እዚያ ነው ለማለት ሳይከበድ አልቀረም። በልጅነቱ ከቤተሰቡ ጋር አብሮ ለኑሮ ያልዘመተበት ሰፈር አልነበረም። በዚያም ቢሉ በዚህ ቤታቸው ውስጥ የታጨቁ የሙዚቃ ካሴቶች አይጠፉምና ጓደኞችም ጭምር ነበሩ። ሙዚቃ መስማትና መውደድ እንጂ ሙዚቀኛ እሆናለሁ የሚል ሃሳብ እንኳን አልነበረውም። እንዲያው የሙዚቃ አድባር በእጇ ላይ ጣለችው እንጂ እንደ እርሱ ሙከራዎች ቢሆንማ ኖሮ ለሙዚቃው ከፍቅር ሌላ ባልኖረው ነበር። እንዲው የሙዚቃ ህልም አልሞ አያውቅም። ስለመሆን ከተባለ ህልሙ ሀኪም የመሆን ነበር። ግን ሳይሳካለት ቀረና ወደ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ አቅንቶ በኢንዱስትሪያል ኤሌክትሪክ ሲቲ ዲፕሎማን ጨብጦ ወጣ። በዚህም ደስተኛ የሆነ አይመስልም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ቀደም ሲል መሰናዶ ትምህርት ቤት ውስጥ ጀምሮ የተላለፈው አንድ መስመር እንደነበር ውስጡ በደም ነብስ ቢያምንም ለውስጡ ቅሬታ መፍትሄ ሰጥቶ ማስተካከሉ ግን አልመጣለትም።
ካለው ተሰጥኦ አንጻር መሆን የነበረበት የማህበራዊ ሳይንስ ተማሪ ነበር። ሚካኤል መርጦ የገባው ግን የተፈጥሮ ሳይንስን ነው። ፍላጎቱና ድርጊቱ ለየቅል እንደሆነበት ሰው ግራ ተጋባ። ለመውደቅ የሚያበቃ ችሎታ ባይኖረውም ሳያልፍ ቀረ። ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጎራ ብሎ እንደገና በሌላ ዘርፍ በግሉ በመማር እሱንም አጠናቀቀ። በሁለቱም ዘርፎች እየሠራ፣ በሁለት እግሩ ቆሞ አሻቅቦ የሚመለከተው ግን ሌላ ነገር ነበር። ብዙ ነገሮች እየመጡ ፊቱ ድቅን ይላሉ።
በተለይ የንግዱ ዓለም ጥሪ ሁሌም ከጆሮው እንዳቃጨለ ነው። ማቃጨል ብቻ አይደለም ገብቶም የአቅሙን ያህል ታግሏል። በወሬ ወሬ አንዳንዶች “ሻወርማ (ጣፋጭ የመንገድ ላይ ምግብ) በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የጀመረው ሚኪ ነው” ይላሉ። በእርግጥ የመጀመሪያው ስለመሆኑ እርሱም በውል ባያውቀውም አለ ተብሎ ለመናገር በማይቻልበት ጊዜ እንደጀመረ ይናገራል። ደግሞ ቀደም ሲል በመሃል ቦሌ “ፐርፕል” የተሰኘ ካፍቴሪያ ከፍቶ ነበር። ቤቱ ታዋቂ ከሆነ በኋላ በጊዜው አሉ የተባሉ ሙዚቀኞች ሁሉ መገናኛቸው እዚያ ካፍቴሪያ ውስጥ ነው።
እነ ኤሊያስ መልካ፣ ጆኒ ራጋ፣ ላፎንቴና ሌሎችም ከቤቱ እየመጡ ፊት ለፊት ያገኛቸውም ነበር። እንዲያውም በአንድ ቆየት ባለ ቃለ ምልልሱ ውስጥ እንደተናገረው፤ ቴዲ አፍሮ በዚያው በቦሌ በከፈተው የራሱ ሬስቶራንት ውስጥ ይዘፍን እንደነበርና እሱም ከዚያ እንደማይቀር ይናገራል። ሚካኤል ያ ቅር ቅር የሚያሰኘው ነገር ምን እንደነበር አሁን ሳያወቀው አልቀረም። ብዙም ትኩረት ያልሰጠው የሙዚቃ ፍቅሩ ውስጡ ታፍኖ ሲለበልበው የነበረ መሆኑን ተረዳ። ከሚመለከታቸው ነገሮች ጋር ነብስያው አብራ ነጎደች። ተከትሎም ወደ ኮንኮርድ ሆቴል ሄደ። በጊዜው ትልቅ የሙዚቃ ዝግጅቶችና ልምምዶች የሚካሄዱበት ስፍራ ነበር። አስቀድሞ ተግባብቷቸዋልና ከልምምድ ክፍሎች ውስጥ እየገባ ፒያኖውን፣ ጊታሩን…ብቻ ከዓይኑ የገባውንና ቀልቡ የሳበውን ሁሉ እያነሳ ያጫውታቸዋል። የእንግሊዝኛ ሙዚቃ ሽታ ሽው! ያለበትም የዚህን ጊዜ ነበር። በእነ ጂሚ ግሬፍ፣ ጄምሬቭስና ሳምኩክ ሙዚቃዎች በተመስጦ ባህር ይሰምጣል። ደግሞ መለስ ይልና ከሀገር ውስጥ በነ ሰይፉ ዮሐንስ፣ ግርማ በየነና ተሾመ ምትኩ ሙዚቃዎች በስሜት እየዋኘ ተሰጥኦውን በችሎታ ያጎለብተው ጀመረ። “እጅግ ደስ የሚለውን ሕይወት ያሳለፍኩት ኮንኮርድ በነበረኝ ቆይታ ነው” ሲል ይናገራል።
ከዚህ በኋላ ነበር ለሙዚቃ ፍቅር ብቻ ሳይሆን ዕውቀትም ግድ እንደሚለው በማሰብ ወደ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት በመግባት የፒያኖ ሙዚቃ መሣሪያ መማር ጀመረ። በመሃል ግን ተምሮ ሳይጨርስ ሌላ ዕድል አጋጥሞት ሙዚቃን ሊጫወት አቋርጦ ሄደ። “መዲና ባንድ” በሩን ከፍቶ ጠበቀው። እኚያን የእንግሊዝኛ ሙዚቃዎች መድረክ ላይ መዝፈን ማንጎራጎር የጀመረውም እዚህ ነበር። ለዚህ ሁሉ ዛሬው ያቺ የጅምር ትናንትናው መዲና ነበረች። በዚያው በመዲና መድረክ ላይ እጅግ አንጋፋ ከምንላቸው ጋር በአንድ መድረክ ቆሞ ለመሥራት ችሏል። ከፊት ጥላሁን ገሠሠ ነበር። ማህሙድ አህሙድ፣ ሀመልማል አባተ፣ ምኒልክ ወስናቸውና ሌሎችም ከነበሩበት መድረክ ላይ መታየቱ ለእርሱ ትልቁ ስኬት የነበረ ስለመሆኑ ተናግሮታል።
ያኔ ገና ሙከራን የማይታክተው ሚካኤል የሙዚቃን እጅ ከሳመ በኋላም ወዲህ ወዲያ ማለቱን አላቆመም ነበር። መሆንን አይጠላም። ሁሉንም ሆኖ የማየትና የመሞከር ጉጉቱ እንጥሉ ስር ናት። ብዙ እንዲያማትር ያደረገው ነገሮችን የማወቅ ፍላጎቱ ነበር። “በአንዱ ቦታ ሰንጥቄ እንደምወጣ አውቀው ነበር” እያለም እዚህም እዚያም ሲል ከዳኒ አይሬ ጋር በአይሬ የሬዲዮ ፕሮግራም፣ ቪላቬርዲ… ከሙከራዎቹ ናቸው። እንደገና ከአራት ዓመታት በፊት አንድ የሙዚቃ መተግበሪያን እውን ለማድረግ ተፍ! ተፍ! ሲል በኮቪድ ወረርሺኝ ተይዞ የጉዞ መስመሩን ጠምዝዝዞ ሳያስበው ወደ ማገገሚያ ሆነ። አሁን ላይ ሆኖ ባለፈው ልጅነቱ፤ ብሆን ኖሮ ብለህ የምትመኘው ምንድነው ሲባል “ዕድሉን አግኝቼ ዲያቆን ሆኜ ቢሆን ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር” ይላል። የቀረው ይሄው ነው… ምኞት እንደነበረው የገለጸላቸው አንድ አባትም “ልጄ መቼም ላንተ ባይለው ነው” እንዳሉት ያስታውሳል።
ሙዚቃ ከአድማጭ ጆሮ አልፎ፣ ሥርዓተ ውህደቱን በልብ ውስጥ ከውኖ፣ በመላ ደም ስር ውስጥ ገብቶ ሀሴትና ስሜት ሲፈነጥቅ ማለት በርሱ ሙዚቃዎች ውስጥ ነው። በደፈናው ምናልባትም ሁለት ዓይነት የሙዚቃ አድማጮች አሉ። የመጀመሪያዎቹ ከመልዕክቱ ይልቅ የሙዚቃው ምቱ ስልቱ በእንብርክክ የሚያስኬዳቸውና ከዳንስና ቡጊ! ቡጊ! ጋር ዘና እያሉ ከሚነጥር ስሜት ጋር ደስታቸውን በአስረሽ ምቺው ማጣጣም የሚፈልጉ ናቸው። ሁለተኛዎቹ ደግሞ የምን ከበርቻቻ…በማለት እረጋ ሰከን ካለ ስሜት ጋር በግጥምና ዜማው መንፈስ የሚፈሱ ናቸው። መጨፈር ቢያምራቸው እንኳን እንደ ሳልሳ ዳንሳ፣ አለፍ ካለም ፍሰት ያለው ማሪንጌን የሚመርጡ ዓይነት ናቸው፤ ሁለቱንም የሚወዱ ሦስተኛዎቹ እንዳሉ ማለት ነው።
መነሻዬን ስቼ እንዳልጠፋ አነሳሴ የሚካኤል በላይነህ ሙዚቃዎችን በፍቅር እፍ! የሚሉባቸው አድማጮች የትኞቹ ናቸው ለሚለው ነው። መደምደሚያውም ሁለተኛ ላይ ያሉት አድማጮች አብልጠው ሚካኤል በላይነህን ይመርጡታል። እጅግ ሞቅ ያለና ለጭፈራ ስልቱ፣ ለዳንስ ወረድ ወረድ አመቺ መስለው የሚታዩ የሙዚቃ ሥራዎቹ እንኳን ከውጫዊ ይልቅ ውስጣዊ የስሜት ጥልቀት ያላቸው ናቸው። እያደመጧቸው ከምቱ ጋር ብቻ ነሁልለው ግጥምና መልክዕክታቸውን ዘለው የሚያልፏቸው አይደሉም።
ሚካኤል በአንድ ሠርግ ላይ ተገኝቶ ሠርጉን በመታደም ላይ ነበር። ከታዳሚው መሃል ድንገት ከዓይኑ ውስጥ የውበት ቀለም በብርሃን ፈሰሰ። የተመለከታትን ቆንጆ ኮረዳ እንደማረከችው የሚማርክበትን ዘዴ እያሰላሰለ ጠጋ አላት። ኮከብ የገጠመ ዕለት ጥቅሻም ፍቅር ነውና የገባው ነገር ሳይገባት አልቀረም። በኋላ ከተጋቢው መሃል ተግባብተው ሲለያዩ “በትልልቅ ሠርጎች መሃል ትንንሽ ሠርጎች አሉ” የሚለውን የባለዕጣዎችን መፈክር በልባቸው እያሰሙ ይመስላል። ቢሆንም ግን በሰዓቱ ልጅቷ የምትሠራው በውጭ ሀገር ውስጥ ነበር።
ሌላ አስቸጋሪው ነገር ደግሞ ከምትሠራበት “ኢትሀድ” በቅርቡ በዚያው ወደ አሜሪካን ሀገር የመሄድ ህልምና ዕቅድ ነበራት። ከዚያ በፊት ግን ከሚካኤል በላይህ ጋር ቀጠሮ ነበራቸው። እመጣለሁ ብላዋለች። በቀናት መካከል ሲጠብቃት አንድ ቀን ከቤቱ ውስጥ ቁጭ ብሎ ሳለ ድንገት የሆነ የሙዚቃ ሰማይ ተከፈተለት። ከነበረበት ሶፋ ላይ ብድግ ብሎ እንደሄደ ከፒያኖው ፊት ተቀመጠናም የፒያኖውን ቁልፎች እየነካካ እንዲህ አለ፤
“ሰርክ የማይታክተኝ
አለሁሽ ጠባቂ
…
ትመጪ እንደሆን
ትመጪ እንደሆን
አለሁ እኔ ሳላጎል
በፍቅር እንዳለሁ”
የሚለውን ተወዳጅ ዜማ በድንገተኛ የምናብ ጽንስ አምጦ ወለዳት። ፍቅሩንም አበጀባት። ቀደም ሲል የመጀመሪያ ባለቤቱን በሞት ተነጥቆ አስከፊና መራራ ጊዜያቶችን ሲያሳልፍ ቆይቷል። አጋጣሚው ለተሰበረው ልቡ ካሳ ባይሆንም ምናልባትም ግን ሽሮለታል። አዲስ ተስፋና አዲስ ነገን መመልከት ጀምሯል።
ከዚህ ቀደም “አንተ ጎዳና”፣ “ናፍቆትና ፍቅር” በሚሉ በእነዚህ ሁለት አልበሞቹ መወደድና ክብርን ሸምቷል። በአልበሞቹ የአድማጩን ልብ የደስታ ፈንዲሻ አድርጎታል። አሁን ደግሞ ሦስተኛው የሆነውን አልበም “አንድ ቃል” ከሚል መጠሪያ ጋር አቅርቧል። ነሐሴ 17 ቀን 2016ዓ.ም የአልበም ሥራውን በራሱ የዩትዩብ ገጽ ላይ ከቀለቀቀው በኋላ የአድማጩ ልብ በድጋሚ መፍካቱን ቀጠሏል። “ምንም የሚጣል የሌለው ልቅም ያለ ሥራ!” ያሉም ብዙዎች ናቸው።
“እኔ ሱፍ አበባ
አንች የኔ ጸሐይ
በዞርሽበት ሁሉ
እየዞርኩ የምታይ”
ከአዲሱ አልበም ውስጥ “ውስጠ ወይራ” ከሚለው ሙዚቃ የሚቀነጨብ ስንኝ ነው። የግጥሙ ደራሲ ሠለሞን ሳህለ (ያማል) ነው። ራሱ ሚካኤልን ጨምሮ ሌሎች ብርቱዎችም በተሳተፉበት በዚህ አልበሙ ውስጥ እጅግ ጠንከር! ጠንከር! ያሉ የግጥም ሽመሎች ያረፉበት ነው። ከመሃከል አንዱ የሆነው “ውስጠ ወይራ” ርዕሱ እንደሚነግረንም በቀላሉ አንድደው የማይፈጁት የሙዚቃ ሥራ ነው። “ትመጪ እንደሆን…” ከላይ ዜማ ለሸለማት ባለቤቱና የሁለት ልጆቹ እናት አሁን ደግሞ “ጠይም” ብሏታል። አንድ ቃልና ማለዳም የሙዚቃ ጀንበር መውጫ ናቸው። እንዳሉትም ሁሉም ልቅም ያሉ ናቸው።
የግሉ የስሜት ነጎድጓድ ከሆኑ የአልበም ሥራዎቹ ባሻገር ማኅበራዊ አንደምታ ያላቸውን መልዕክት አዘል የፕሮጀክት ሙዚቃዎቹም በርካታ ናቸው። በኤች አይ ቪ ኤድስ፣ በአካባቢ ጥበቃና በአፍሪካ ህብረት ዙሪያ የተዜሙ ዜማዎቹም ተወዳጅ ናቸው። “ማለባበስ ይቅር” የሙዚቃው ግጥምና ዜማ ደራሲ እንዲሁም ፕሮዲዩሰር ራሱ ሚካኤል በላይ ነህ ነው። በመቀጠልም “መላ መላ” ነበር። “መሌ ሀራ” አሊ ቢራ የተሳተፈበት ሌላኛው ሥራው ነው። ቀረብ ባለው ጊዜ ውስጥ ደግሞ በጣም ተወዳጅ የሆነለትን “ከፍ እንበል በሥራ” ስለ ዓባይ በተዜመው ሙዚቃ ከዜማው ጀምሮ ከፍተኛውን ሚና ተጫውቶበታል።
በአንድ ወቅት ሚካኤል ነሸጥ አድርጎት ወደ ቲያትሩም ገባ። አንድ ቲያትር ካዘጋጀ በኋላም በገባበት ሹልክ ብሎ ወጣ። በኋላ ምነው ብለው ቢጠይቁት “አይ…ይኼ የኔ ሰፈሬ አይደለም” ሲል ጥሎ እብስ! አለ። ያደረገው ነገር ትልቅነት ነበር። የራስን ቦታና ተሰጥኦ ማወቅ አውቆም መተገበር የብዙዎች ችግር መሆኑን በግልጽ የምንመለከተው ነው። ይህን ያደረገው የርሱ ትክክለኛው ቦታና ጥሪ የሙዚቃው መንደር መሆኑን በመረዳት ነበር፤ በሰው ሙያው ውስጥ ገብቼ አልፈተፍትም ሲል መለስ ማለቱ።
ሦስት አልበሞችን ያወጣው ሚካኤል በላይነህ ሦስት ጊዜ ሙዚቃ በቃኝ ብሎ ከሙዚቃ ዓለም መንኖ ነበር። ከሙዚቃ መንደር ለማምለጥ ኮርቻና ግላሱን አልብሶ ቼ! ያለው ፈረስ እየወሰደ አንከላውሶ መልሶ ከዚያው ያመጣዋል። አሁንስ በቃኝ ብሎ ሸክፎ የወጣውን ሻንጣ መልሶ ይዞት ይገባል። ሄድ መለስ እያለ ሦስት ጊዜ ፊቱን ቢያዞርም ቆርጦ የሚቆርጥ አንጀት አጣና አንዱም ሳይሳካ ቀረ። በአንድ ጊዜም እንደልማዱ አሁንስ ተገላገልኩት ብሎ ከቤቱ እንዳለ ከዕለታት በአንዱ ቀን ስልኩ አቃጨለ። ሚካኤል ስልኩን አየው ግን የማያውቀው ቁጥር ነበር። እንዳነሳው ሃሎ! ከማለቱ “አዲስ ባንድ ላቋቁም ነበርና እባክህን አብረህ አቋቁመኝ…” የሚል የቀልድ ድምጽ ነበር። ድምጹ የማን እንደሆነ ግን አውቆታል። ኤሊያስ መልካ ነበር። ኤሊያስ መልካን አብዝቶ ይወደዋል። እጅግም ይቀራረቡ ነበር። አንተማ ሙዚቃ ማቆም የለብህም የሚለውን የኤሊያስን ሃሳብና ድምጽ ለመጋፋት አልተቻለውም።
ልቡ አፈንግጦ ሲሄድና ልቡ እየሸፈተ ሲመጣ…አስቀደሰ፣ ቀጠለ፣ በመጨረሻም ሰለሰ! “ሚኪ ተመለስህ መጣህ አይደል” ሲሉት “ምን ላድርግ ሙዚቃ እኮ ልክፍት ነው” ይላል። በእርግጥም ልክፍት እንጂ ሌላ እንዲህ የሚያደርገው ምን ይኖራል። ከነ ልክፍቱ ሙዚቃን እያሳደደ ሳይሆን እያሳደደችውም 20 ዓመታትን ሰነበተ። ከነ ልክፍቱም ሦስት አልበሞችን አስደመጠን። ከ”አንድ ቃል” በኋላ ከሰሞኑ ይህቺን ቃል አለ “ቀደም ሲል በሠራኋቸውም ሆነ በሌሎች ዘንድ አድማጩ በርታ! ጎበዝ ሲል ነበር የማውቃው ከዚህ አልበም መለቀቅ በኋላ የሚወደውሉልኝ አብዛኛዎቹ ሰዎች እናመሠግናለን! ነው የሚሉኝ” አለ። ያሉት ቃል ጠፍቶ አይደለም። ያሉት በምክንያት ነው። እጅግ በተጠማ ሰዓት ጥምን ለቆረጠ “እናመሠግናለን!” እንጂ ሌላ ምን ይባላል…
ሙሉጌታ ብርሃኑ
አዲስ ዘመን ጳጉሜን 3 ቀን 2016 ዓ.ም