አዲስ አበባ፡- በተሳሳተ መንገድ መድሃኒቶችን በማዘዝ በተጠቃሚዎች ጤንነት ላይ ጉዳት የሚያስከትሉ የጤና ባለሙያዎች ተጠያቂነት አነስተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድ ሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስ ልጣን አስታወቀ፡፡
በባለስልጣኑ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ምርቶች ደህነንነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ አስናቀች አለሙ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ ህግ መሰረት መድሃኒት ለታማሚዎች ማዘዝ የሚችሉት እንደየደረጃቸውና እንደመድሃኒቱ ዓይነት ሃኪሞች፣ የጤና መኮንኖችና ነርሶች ናቸው። ይሁንና የጤና ባለሙያ ሆነው ከህጉ ውጪ መድሃኒት በተሳሳተ መንገድ በማዘዝ በታማሚዎች ላይ ለሚያደርሱት የጤና ጉዳት ተጠያቂነታቸው ዝቅተኛ ነው፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ፤ መድሃኒቶች ለታማሚዎች ሲታዘዙ የምዝገባ ስርዓት አለመኖር፣ የህገ ወጥ አሠራሮች መበራከትና በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የጤና ባለሙያዎቹን ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል በቂ መረጃዎች አለመኖራቸው ለተጠያቂነታቸው ዝቀተኛነት ከፍተኛውን ድርሻ ወስደዋል፡፡ በተመሳሳይም በህጋዊ መንገድ ከመድሃኒት ትዕዛዝ ጋር በተያያዘ በተጠቃሚዎች
ላይ ለሚፈጠሩ የጤና ችግሮች ባለው የህክምና አሰጣጥ ውስብስብነት፣ በህብረተሰቡ ግንዛቤ አናሳነትና በመረጃዎች እጥረት ምክንያት የጤና ባለሙያዎቹ ተጠያቂነት ዝቅተኛ ነው፡፡
ከህጉ ውጪ አግባብ ባልሆነ መንገድ መድሃኒቶችን ለታማሚዎች በማዘዝ የሚፈጠሩ የጤና እክሎች ተጠያቂነትን እንደሚያስከትሉ የገለጹት ዳይሬክተሯ፤ በተለይ የጤና ተቋማት የመድሃኒት ማዘዣ ወረቀቶችን ተጠያቂነት ባለው መልኩ ማሰራጨትና መቆጣጠር እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል፡፡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በሀገሪቱ ተመሳሳይ የመድሃኒት ማዘዣ ወረቀቶች እንዲኖሩ ባወጣው ስታንዳርድ መሠረት የጤና ተቋማቱ መጠቀም እንደሚገባቸውም ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ስታንዳርድ ውጪ የመድሃኒት ማዘዣ ወረቀቶችን ማሰራጨት በቅድሚያ የጤና ተቋማቱን በመቀጠልም ድርጊቱን የፈፀሙ የጤና ባለሙያዎችን የሚያስጠይቅ መሆኑንም ዳይሬክተሯ አያይዘው የገለጹ ሲሆን፤ እስከአሁንም አግባባዊ ካልሆነ ከመድሃኒት ትዕዛዝ ጋር በተያያዘ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በኩል ተጠያቂ የሆኑ የጤና ባለሙያዎችና የጤና ተቋማት እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሚያዝያ 1/2011
በአስናቀ ፀጋዬ