የሰው ልጅ በምድር ሲኖር ደስታና ኃዘን፤ ማግኘትና ማጣት፤ ወጥቶ መውረድም ሆነ ወርዶ መውጣት … ሊፈራረቁበት ግድ ነው። ከልጅነት እስከ እውቀት ባለው እድሜያቸው ሁሉ የሞላላቸው ሰዎች የመኖራቸውን ያህል፤ ጥረው ግረው እንኳን፣ የችግርን ተራራ ለመናድ ቀርቶ የእለት ጉርስን ለማሸነፍ የሚቸገሩ በርካቶች ናቸው። ከእነዚህ በተቃራኒው ደግሞ በሚያደርጉት ትንሽ ጥረት የችግርን ገመድ በጣጥሰው በማለፍ ከራሳቸውም አልፈው ለሌሎች ጋሻና መከታ የሚሆኑም አይጠፉም። ያም ሆነ ይህ ግን፣ ሰው፣ ያው ሰው ነውና፣ እንደ ሁኔታና ገጠመኙ፣ ውሎና አዳሩ … በሕይወቱ ውስጥ ሊፈተን የግድ ነው።
ይህ ፈተና ግን ማምሻ ላይ ሲሆን ጡጫው ይበረታል፤ የችግሩ ግዝፈትም ያይላል። አበው “የማታ እንጀራ ስጠኝ” ለማለታቸውም ምስጢሩ ይኸው ነው። ”ማታ” እንደ ስሙ ማታ ነው፤ ጨለማ ነው። ሮጠው የማይቀድሙበት በመሆኑም ሰው በማምሻው (በእርጅናው) ጊዜ አረፍ ይልበት ስፍራን፣ እርፍ ይልበት ጊዜን ይፈልጋል። ይህ ሳይሆን ሲቀር ደግሞ ትንሿ ጎዶሎ ብዙ እየሆነች በችግር ላይ ችግር እየተደራረበ፣ መፈጠርን እስከመጥላት ሊያደርስ ይችላል። ”አያድርስ” ይሏል ይሄኔኔ ነው። ”ላያስችል አይሰጥም”ም እንደዛው።
እማማ ተስፋዬ ኃይሌና አቶ ኮችሜ እድሜያቸው ለአቅመ አዳም ቢደርስም ትዳርን የመሠረቱት ግን ዘግየት ብለው ይመስላል። እንደ ዛሬው እርጅና ሳይጫጫናቸው መልካቸውም፣ ጉልበታቸውም ሳይከዳቸው በፊት ሁለቱም ቆፍጣና፣ ሠርተው የማይደክሙ፣ ሮጠው የማይጠግቡ ነበሩ። በዚህ እድሜያቸው ደግሞ አንዱ ለአንዱ ነውና የተፈጠሩት ሁለቱም ልባቸው ተከጃጅሎ ፍቅር ጣላቸው፤ ፍቅራቸውንም ያጣጥሙት በአንድ ጎጆ ጥላ ስር ተሰብስበው ክፉና ደጉን፤ ኃዘንና ደስታውን … በጋራ ይገፉት ዘንድ ትዳር የሚባለውን የማኅበራዊ ተቋም መሠረት ልክ የዛሬ 40 ዓመት ገደማ መሠረቱ።
ምንም እንኳን ይህ ፍቅራቸው በልጆች በረከት የታጀበ ባይሆንም፣ እነሱ ግን አንዳቸው ለአንዳቸው ክንድ ሆነው አንዱ ሲደክም ሌላው እያበረታ አንተ ትብስ፤ አንቺ ትብሺ እየተባባሉ በፍቅር ለመኖራቸው ግን እንቅፋት አልሆነባቸውም።
ልጅ ባይኖራቸውም ፍቅር አስተሳስሯቸው እማማ ተስፋዬ ጠላ እየነገዱ፣ አቶ ኮችሜ ደግሞ ልብስ እየሰፉ ኑሯቸውን በአቅማቸው ”ጥሩ” በሚባል ሁኔታ ሳይርባቸው፣ ሳይጠማቸው፤ ለእድሬ፣ ለእቁቤ … ብለው የሚያወጡት ገንዘብ ሳይቸገሩ፤ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ሽሮ ሜዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለወርሐዊ የቤት ኪራያቸው 2ሺህ ብር እየከፈሉ እዚህ ደርሰውም ነበር።
አባባ ኮችሜ እጅግ በጣም ጎበዝ ልብስ ሰፊ ስለነበሩም በመንደሩ ያሉ ሰዎች ሁሉ የተቀደደባቸውን ልብስ የሚያስጠግኑት እሳቸው ጋር ነው። ጨዋታ አዋቂ የሰፈር አድባር ስለነበሩም ለሥራ የሚቀመጡበትን ቦታ የሚያደምቁላቸው ጓደኞችም ነበሯቸው።
በዛው ሽሮሜዳ ላይ ከቤታቸው አቅራቢያ ነበር የልብስ ስፌት ሥራቸውን የሚሠሩት፤ አቶ ኮችሜ ለሥራቸው ልዩ ፍቅርና ክብር የነበራቸው በመሆኑ ልክ ፊርማ እንዳለበት ተቀጣሪ ሠራተኛ ጠዋት በሰዓቱ ሥራቸው ላይ ይገኛሉ። ምሳ ሰዓት ሲደርስም የልብስ መስፊያ ማሽናቸውን ሸፈን አድርገው ወደ ቤታቸው በመሄድ ቤት ያፈራውን ቀምሰው፤ ቡናቸውን ጠጥተው በሰዓቱ በሥራ ገበታቸው ላይ ተመልሰው ሥራቸውን ያጠናቅቃሉ። በዚህም ለቃላቸው ታማኝ፤ በሥራቸውም ምስጉን ስለመሆናቸው ይነገርላቸዋል።
ከዓመታት በፊት በአንደኛው ቀን ግን የእስከ ዛሬውን ድካማቸውን ገደል የሚከት፤ ሕይወታቸውን የሚያጨልም አጋጣሚ ተፈጠረ። አባባ ኮችሜ እንደተለመደው በሥራ ገበታቸው ላይ በጠዋት ነበር የተገኙት። ”… ይስፉልን” ብሎ ደንበኞቻቸው ያመጡላቸውን ልብስም ሲሰፉ ነው ያረፈዱት። ምሳ ሰዓት ደረሰና በተለመደው ሁኔታ ባለቤታቸው አዘጋጅተው የሚጠብቋቸውን ምሳ ለመቅመስ፤ ቡናይቱንም ጠጥተው ወደ ሥራ ለመመለስ ወደ ቤታቸው አዘገሙ። ነገር ግን እለቱ ለአስራ አራት ዓመት እንዳሳለፉት ጊዜ የቀና አልነበረም። እንደውም ጎዶሎ ነበር ማለት ይቻላል።
አባባ ኮችሜ ምሳ በልተው የቀረውን ልብስ ሊሰፉ ወደ ቦታቸው ሲሄዱ 11 ዓመት ማንም ምንም ያልነካውን፤ የመተዳደሪያና መጦሪያ የልብስ ስፌት መኪናቸውን (ሲንጀራቸው) በቦታው አጡት። ዓይናቸውን ማመን ያቃታቸው አባት ደጋግመው አዩ። ከራሳቸው ጋር ተነጋገሩ። ቦታቸውንም የተሳሳቱ ሁሉ መሰላቸው። ውስጣቸው ”… ሊሆንማ አይችልም” ሲል እውነቱን ለመቀበል አቅማማ። ግን፣ በዚህ ሁኔታቸው፣ ጥርጣሬያቸው … ብዙ ሊቆዩ አልቻለም። እውነት ነው፣ ጉሮሯቸውን፣ መጦሪያቸውን፣ ልጃቸውን ሌባ ወስዶታል።
የልብስ ስፌት መኪናቸው ለእሳቸው ጧሪ ልጃቸው ነው። በእሱ ሠርተው በሚያገኙት ገንዘብ ነው የራሳቸውንም የባለቤታቸውንም ጉሮሮ የሚደፍኑት። ለአንገት ማስገቢያቸው የቤት ኪራይ የሚከፍሉት። ብቻ፣ የልብስ ስፌት መኪናው ካልነው በላይ ለእሳቸው ወሳኝና የሕልውናቸው መሠረት ነበር። ግን ምን ዋጋ አለው፣ አሁን ከእሳቸው እጅ ወጥቷል፤ አሁን በእጃቸው የለም። ደግመው አይገዙት ነገር፣ ከእጅ ወዳ’ፍ ከሆነው ኑሯቸው ተርፎ ያስቀመጡት ቤሳ የላቸውም። ብቻ በጊዜው ሁሉ ነገራቸው የሆነውን ንብረታቸውን ሲያጡ ደንግጠው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ገብቷቸው፣ ዝም ብለው ወደ ቤት ተመለሱ።
ይህ ሁኔታ ግን ቀስ በቀስ ቅስማቸውን እየሰበረው፣ እየተናደዱ፣ በዛም ላይ ችግር እየመጣ፤ አልፎ ተርፎም የሚላስ፣ የሚቀመስ እየጠፋ መጣ። አባባ ኮችሜም አዕምሯቸው እየታመመ፣ ጠንካራና ጎበዝ የነበሩት ሰው ከሰው መገናኘት እያስጠላቸው ሄደ። እንደ ቀልድም ተኝተው በሚውሉበት አልጋ ላይ ቀሩ።
ያ በሥራ ይወጠር የነበረው አዕምሯቸው ሥራ ፈታ። በዛ ላይ ሳያስቡት በሌባ ምክንያት ለችግር መጋለጣቸው አሳዘናቸው። ይህንን ማብሰልሰላቸው ደግሞ ለአዕምሮ ጤና ችግር ዳረጋቸው። የሚያስተኛ፣ የሚያቀና ልጅ የሌላቸው አባባ ኮችሜ እንደ ቀልድ አልጋው ላይ እንዳሉ አይናቸው ማየት ተሳነው። ጆሮአቸውም ከመስማት አቅሙ እየቀነሰ … እየቀነሰ … መጣ። እያለ … እያለም በደንብ መስማቱን አቆመ።
አሁን ለእማማ ተስፋዬም ሆነ ለአባባ ኮችሜ ኑሮ እጅግ በጣም ፈታኝ ሆኗል። ቁጭ ብሎ ከመፋጠጥ ሌላ የሚያደርጉት ነገር የለም። ወጥቶ ምጽዋት ለምኖ ለመብላት እንኳን ጉልበት ያስፈልጋል። እነሱ ደግሞ ጉልበታቸው ዝሏል። ዓይንን ያህል ብርሃን አጥተዋል። ጧሪ የሌላቸው ሁለት ምስኪኖች በጠባቧ ክፍላቸው ውጥ ኩርችም ብለው ውለው ያድራሉ። እግዚአብሔርን የፈሩ ጎረቤቶቻቸው ያላቸውን ያካፍሏቸዋል። ካልሆነም ጾም ውለው … ጾም ያድራሉ።
አሁን ላይ እማማን እያሳሰባቸው ያለው ነገር ረሃቡና ችግሩ ብቻ አይደለም ባለቤታቸው አባባ ኮችሜ አዕምሯቸው ጤናማ ስላልሆነ ”ይጠፋብኛል”፣ ”መንገድ ወድቆ ሳልቀብረው እቀራለሁ …” የሚለው ጉዳይ ነው። ይህንን በመፍራትም እማማ ተስፋዬ ጎረቤት እያገዛቸው በሰንሰለት ወይ በገመድ አስረው ለማስቀመጥ ተገደዋል።
ሌላው የእነዚህ አሳዛኝ ጥንዶች ፈተና የቤት ኪራይ ጉዳይ ነው። በጉልምስና እድሜያቸው አግኝተው የራሳቸውን ጎጆ መቀለስ አልቻሉም። ዛሬም በእድሜያቸው መጨረሻ ለአንገት ማስገቢያቸው የሚከፍሉት ነገር አጥተዋል። ብዙ ፈተና እያሳለፉ፣ እንደ ምንም በቆሸሸ ቤት ውስጥ እየኖሩ፣ ምንም ባይበሉ እንኳ እየቻሉት ቤት ኪራይ ሲደርስ ግን ሰቀቀኑ እንቅልፍ ይነሳቸዋል። እስካሁንም በፀሎትና በደጋጎች ድጋፍ ነው ያሉት።
አሁን ግን ሁሉ ነገር ከብዷቸዋል። እንደ ሕፃን ስቅስቅ ብለው እያለቀሱ “እግዚአብሔርን ግደለን ብንለው አልሰማ አለን፤ ሞት በልመና እንደሆነ አይገኝ” ይላሉ። ዛሬ ላይ ባሉባቸው ተደራራቢ ችግሮች ምክንያት የሚፈራውን ሞት ”የት ነው ያለኸው?” በማለት እስከ መለመን ደርሰዋል።
ለእነዚህ አቅመ ደካሞች አሁን ላይ ዙሪያው ገደል ሆኗል። ጊዜው እጅጉን ከብዷቸዋል። በመከራ ላይ መከራ እየተደራረበባቸው ነው። እስከ ዛሬ ባይወልዱም ልጅ የሚሆኗቸው ሰዎች ነበሩ። ዛሬ ላይ ግን ሁሉም ለራሱ ኑሮ እየፈተነው በመሆኑ ከራሱ እልፎ ለእነሱ የሚተርፍ ልጅ የለም። የጤናቸው ጉዳይ አሳሳቢ ነው። እማማ ተስፋዬ በሚችሉት አቅም ተንቀሳቅሰው ቢያንስ የእለት ጉርሳቸውን እንዳያመጡ አባባ ኮችሜ በሆነች አጋጣሚ ከቤት ከወጡ መመለስ ስለማይችሉ ይጠፉባቸዋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ 40 ዓመታትን በትዳር አብሮ ለኖረ ሰው ቀላል አይደለም። ለማረፊያ የሚሆን ቤት ቢከራዩም አሁን ላይ ኪራዩን መክፈል አቅቷቸዋል። እማማ ተስፋዬ ይህንን ሁሉ ሲናገሩ እንባቸው እንደ ጎርፍ ይወርዳል። አታልቅሱ ሲባሉም ሌት ተቀን ሥራዬ ምን ሆነና ይላሉ።
በዚህች ሰዓትና እድሜያቸው፣ እሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው ከእንባቸው ሌላ ምንም ሀብት በእጃቸው፣ ምንም ዘመድ ከጎናቸው፣ ምንም አይነት ጉልበትም ይሁን አቅም የላቸውም።
በመሆኑም ደግ ልብ ያላቸው ኢትዮጵያውያን አይጠፉምና ትንሽ ነገር አድርጎ የፈጣሪን በረከት ለማግኘት ጊዜው አሁን ነው እንላለን። እንዲህ ያሉትንም ሰዎች መጎብኘት ጥሩ በመሆኑ፤ መልካም ማድረግም ለራስ በመሆኑ፣ መደጋገፍም ሆነ መረዳዳት ሰውኛ በመሆኑ፤ እንደ ሰውም እንደ ዜጋና ወገንም መደጋገፍ ግዴታም ጭምር በመሆኑ … አቅማቸው የሚፈቅድላቸው ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ይህንን የእነ እማማን ስቃይ በመረዳት የነፍስ ሥራ ይሠሩ ዘንድ ጥሪያችን በማስተላለፍ ዝግጅታችንን ስንደመድም መልካም ወሬን በመጠበቅ ነው።
እፀገነት አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2015