በማንኛውም ነገር ማብቂያ ላይ ሆነን እንመልከት። የተጀመረው ትምህርት ማብቂያው ላይ፤ የእጮኝነት ጊዜ አልቆ ወደ ትዳር ሊገባ ያለበት ቦታ ላይ፤ ልጅ ተረግዞ ሊወለድ የሰዓታት እድሜ በቀረው ወቅት፤ ጦርነት ባለቀበትና የሰላም አየር በሙላት በሚነፍስበት ጊዜ ወዘተ። እንዲህ ባለጊዜ ውስጥ ሆነን ስናስብ ከመነሻው እስከ አሁን ድረስ ያለውን ጊዜ ስናስብ የሚሰማን ስሜት አለ፤ ጀምሮ በመጨረስ ውስጥ የሚወለድ ስሜት፤ ከስሜት ውስጥ የሚወጣ እውቀት። ጥያቄው ግን ስላለፈው ሳይሆን ስለወደፊቱ ነው፤ ዛሬ ጀምረን የሆነ ቀን ልናሳካው ስለምናስበው ነገር፤ ከእዚህ እስከ እዚያ ስለሚሆን።
የምናብ ታሪካችን ሦስት ወጣቶችን ያስተዋውቀናል። ሦስት ሆነው ክፍል ተጋርተው አብረው የሚኖሩ ረጅም የጓደኝነት ታሪክ ያላቸው ወጣቶች። ትላንት በትምህርት ቤት ውስጥ ዛሬ በሥራው ዓለም። የቅርብ ጊዜ ምሩቃን ደግሞም በሥራ ላይ የተሰማሩ አዲስ ሰራተኞች ናቸው። በአዲስ አበባ ኑሮ ሁሉም ቤት ተከራይተው መኖር የሚያስችል ደሞዝ ስለሌላቸው አንድን ቤት ለሦስት ለመጠቀም ወስነው በፈጸሙት የኪራይ ቤት ውስጥ ይኖራሉ። ሦስቱም አብረው ዩኒቨርስቲ ውስጥ በአንድ የመኝታ ክፍል (ዶርም) ውስጥ የኖሩ ስለነበረ አብረው መኖሩ አልከበዳቸውም። አንዳቸው የሌላቸውን ባህሪ ጠንቅቀው ያውቃሉ፤ በድካምም በብርታትም። መንደርደሪያ ታሪካችን በሦስቱም ውስጥ ያለ ሊለውጡት ያልቻሉት የየራሳቸው ድካምን የሚያነሳ ይሆናል።
አንድ ቀን መታረም በሚገባው ጸባያቸው ዙሪያ ንግግር ያደርጋሉ፤ ከንግግራቸው የወጣውን ፍሬ ነገር ቀጥሎ እናንሳ። በቅድሚያ ሃሳብ የተሰጠበት ባንክ ውስጥ የሚሰራው ወጣት ነው። የባንከሩ ከትላንት እስከ ዛሬ እየተከተለ የመጣው ችግር ከስልክ ጋር የተገናኘ ነው። ስልክ ሲያወራ ድምጹን ዝቅ አድርጎ ማውራት ስለማይችል በዙሪያው ያለውን ሰው ይረብሻል። የድምጽ ብክለት መንስኤ ስለሚሆን ይማረሩበታል። የትምህርት ቤት አመሉ አሁንም የለቀቀው ባይሆን በስራ ቦታ እንደ ባንከር ቁጥብ መሆን ስላለበት እየቀነሰ እንደሄደ አስተውለዋል፤ ነገርግን ጠባቧን የኪራይ ቤት ያጨናንቃታል። እርሱ እያለ ሰው በጥሞና ማሰብ እንደማይችል ነገሩት፤ የድምጽ ብክልትም ሆነ ብክነት መንስኤም ነህ እያሉት ወቀሱት፤ እርሱም በጥሞና ሰምቶ ለማስተካከል ከራሱ ጋር አወራ።
ሁለተኛው ወጣት የተቀጠረው በግል ተቋም ውስጥ ሲሆን በሽያጭ ክፍል ውስጥ ይሰራል። የእርሱ የቀድሞውም አሁንም ፈጽሞውኑ ሊለቀው ያልቻለው ችግር የሰዓት ነው። ነገሮችን በጊዜ የማድረግ ልማዱ አነስተኛ ነው። ከእንቅልፉ ለመነሳት የጓደኞቹን ቅስቀሳ ይፈልጋል። በተማሪነት ጊዜ የጠዋት ክፍለጊዜ በነበረው ጊዜ በሰዓት ክፍል ለመድረስ ሲል ቁርስ የሚያመልጥበት ሁኔታም ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ አሁንም አርፍዶ ወደ ስራ በመግባት ቅሬታ ቀርቦበታል። ጠዋት አርፍዶ ተነስቶ ጓደኞችን ይህን አድርጉልኝ ይህን አቀብሉኝ በማለት የእነርሱንም ጊዜ ይበላል። በሚሰራበት ድርጅት ውስጥ ከሰዓት ጋር በተገናኘ ለተነሳለት ቅሬታ የአዲስ አበባን ሰልፍ ምክንያት ቢያደርግም እርሱን አልፈው የሚመጡት ቀድመውት እንደሚመጡ ተነግሮት ምክንያቱ አሳማኝ እንዳልሆነ ተረድቶታል። እንደው መቼ ይሆን ከመጨረሻ ሰዓት መንደፋደፍ የምወጣው እያለም እራሱን ይጠይቃል። ጓደኞቹ ግን ዛሬም እርሱን ከመቀስቀስ አልቦዘኑም።
ሦስተኛው ወጣት መንግስታዊ ባልሆነ ግብረሰናይ ድርጅት ውስጥ ነው የተቀጠረው፤ የስራ ሃላፊነቱም ጀማሪ የፕሮጀክት ሰራተኛ ነው። የእርሱ ችግር ደግሞ ውሸት ነው። ካልዋሸህ ደሞዝ አይከፈልህም የተባለ ይመስል ለውሸት የሚሰራ ያስመስለዋል። አንዳንድ ሰው ውሸት የሚያወራው እውነትን ማውራት ዋጋ ስለሚያስከፍለው ነው። ውሸት ማውራት እስካልታወቀ ድረስ ለሁሉም የተፈቀደ እስኪመስል ድረስ ከቀላል እስክ ትላልቅ ውሸት መዋሸት የተለመደ ነው። ይህ ወጣት ግን እውነት መናገር ዋጋ ቢያስከፍለውም ሆነ ባያስከፍለው ምክንያት ፈልጎ ውሸትን መወሻት ይወዳል። ጓደኞቹ በዚህ ባህሪው ብዙ ጊዜ ታዝበውታል፤ እንዲተውም መክረውታል፤ የእርሱ ምላሽ ለእኔ ሁሉም ቀን ኤፕሪል ዘ ፉል ነው የሚል ነው። ኤፕሪል ዘ ፉልን ምክንያት በማድረግ የውሸት ህይወቱን ለመደበቅ በመሞከር።
ሦስቱ ጓደኛሞች እንዲህ በመሰለ ባህሪያቸው ውስጥ ሆነው አንዳቸው ሌላኛውን ለመሞረድ እየሞከረ አብረው ናቸው። ከእነርሱ ታሪክ ተነስተን ዛሬ አቅደን ልንደርስበት ወደ ምንፈልገው ነገር ለመድረስ የሚረዱንን ሦስት ነጥቦች እናንሳ። ድምጽ፤ ጊዜ እና እሴት።
ድምጽ
የሰው ልጅ ወደ ምድር ሲመጣ የሚያደርገው የመጀመሪያ ነገር ድምጽ ማሰማት ነው። የሚያሰማው ድምጽ ደግሞ የጩሕት፤ የህጻን ልጅ ጩኸት፤ አድማጩ የማይሰለቸው የምስራች ጩኸት።
ለቅሶ የምስራች ሆኖ የሚቆጠርበት ቅጽበት ህጻን ልጅ ወደ ምድር የሚመጣበት ቅጽበት ነው። ከህጻንነት ወደ አዋቂነት በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ጮክ ብሎ ማልቀስ እየቀነሰ እንዲመጣ የሚጠበቅ ነው። እየቀነሰ መምጣት ብቻም ሳይሆን በሳቅ እየተተካ እንዲመጣ በብርቱ የሚጠበቅ። ከዚህ በተቃራኒ በሆነ ጊዜ ግን ለአድማጭ ምቾትን የማይሰጥ ይሆናል።
ዛሬ ባለንበትና መድረስ በምንፈልግበት መካከል ባለው እርቀት መካከል ድምጽን ማሰማት የሕይወት ጉዞ ይፈልጋል። ሃሳባችንን ማድረስ የምንችልበት ድምጸት። ስለ ራሳችን ድምጽ ማሰማት፤ ስለ ሌሎች ድምጽ ማሰማት፤ በድምጽ ተከበን መውጣት በድምጽ ተከበን መግባት። አንድን ምእራፍ ጀምረን በጨረስንበት ሂደት ውስጥ በብዙ ድምጾች መካከል እናልፋለን። በድምጾቹ ተረብሸን ከጉዞ መስተጓጎል ወይንም ድምጾቹን እንደ አመጣጣቸው ተቀብለን በማስተናገድ ወደ መዳረሻችን መድረስ።
ከእዚህ እስከ እዚያ ውስጥ የበረከተውን ድምጽ እንዴት ማስተዳደር እንደሚቻል ማሰብ ጥበብ ነው። ትላንት እኛ ዛሬ በምንሄድበት መንገድ ውስጥ ያለፉ ሰዎች የሚሰጡት ምክር ድምጽ ነው። በልቦናቸው ውስጥ የሚሰማን እግራችንን ወደ ክፉ እንዳንመራ የሚነግረን ድምጽ ነው። ህሊናችን በጥሞና ስናዳምጥ ለሕይወታችን ምሪትን የሚሰጥ ድምጽ አለ፤ የሕሊና ድምጽ የሚባለው። በውስጣችን እንዲሁም በአካባቢያችን የሚሰማንን ድምጽ በመግፋት የሕይወት አካሄድ ውስጥ የምንገኝ ከሆነ በኪሳራ ውስጥ የምንገኝ እንሆናለን። መንፈሳዊ ልምምድ ያላቸው ሰዎች ደግሞ መለኮታዊ ድምጽን ይሰማሉ። ድምጽ ስንወለድ ጀምሮ እስክንሞት ድረስ ይሰማል። አስተዋይ ሰው ድምጽን ይለያል፤ ድምጽን ተከትሎ እርምጃ ከመውሰዱ በፊት ድምጹ ወዴት እንደሚያደርሰው ያስባል፤ ድምጽን ሲያወጣ ሊያንጽ እንጂ ሊያፈርስ አይደለምና።
አንዳንድ ሰዎች ድምጻቸውን ጮክ አድርገው በመጮህ ውስጥ መፍትሔ እንደሚያገኙ ያስባሉ። ድሮ ድሮ የምናየው አንድ የሙስና ማስታወቂያ ነበር። ባለጉዳይ ሲጉላላ ወንበር ይዞ ወጥቶ “ወንበሩ ላይ ቆሚ ልጮህ ነው” ብሎ የሚጮህ ባለጉዳይ።
ሚዲያው ድምጽን በማሰማት መፍትሔን ለመፈለግ ይሰራል። የሕዝብ ተወካዮች ለመረጣቸው ህዝብ ድምጽ ለመሆን ከምክርቤት ይሰየማሉ፤ የሚያምኑትን በድምጻቸው ሲደግፉ፤ የማያምኑበትን ሃሳብ ደግሞ ድምጽ ይነፍጉታል። ዴሞክራሲ በሰፈነባቸው አገራት ድምጽን መሰረት ያደረገው አሰራር ትልቅ ትርጉም አለው። በቀላሉ ድምጽ ማግኘት አይቻልም፤ የተገኘውን ድምጽ በአግባቡ መጠቀም ደግሞ የተመራጩ ሃላፊነት ነው።
ድምጻችንን መጠቀም ባለብን ሰዓት መጠቀም ይሁንልን፤ ከጩኸት መለስ የሆነ፤ ለመፍትሔ የሚሆን። ከእዚህ እስከ እዚያ ውስጥ ድምጽ አለ፤ በአግባቡ ተመርምሮ ሊሰማ የሚገባው እንዲሁም በአስተዋይነት ከእኛ ሊወጣ የሚገባው። በድምጽ ብክለት ብቻም ሳይሆን በድምጽ ብክነትም እንዳይጎዳ የምንጠነቀቅለት።
ጊዜ
ከእዚህ እስከ እዚያ ባለው ጉዞ ውስጥ የሚያልፍ ጊዜ አለ። ጊዜ የሰው ልጅ ትልቁ ሃብት ነው። ተጀምሮ ያለቀ ነገር ውስጥ የጊዜ ቦታ በምንም የሚተካ አይደለም። ሥራው ሊሰራ ይችላል፤ ነገርግን በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ተሰራ የሚለው ትርጉም ይሰጣል። ጊዜን በአግባቡ በመጠቀምና ባለመጠቀም ውስጥ የሚኖር አስተውሎት በሕይወታችን ውስጥ ያለው ተጽእኖ ቀጥተኛ ነው። ጊዜ ከፈጣሪ የሚሰጥ አንድ ሰው ለሌላ ሰው ሊሰጠው የማይችል ከሃብቶች ሁሉ ልዩ ሃብት ነው።
ጊዜን የምንጠቀምበት መንገድ በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ተጽእኖ መረዳት ያስፈልጋል። እያንዳንዱ ሰው የተሰጠው የጊዜ አካውንት አለው። በተሰጠው ጊዜ ውስጥ መልካሙን አድርጎ እንዲያልፍበት የሚጠበቅ። ዛሬ አዲስ ነገር ለመጀመር ስናስብ ከእዚህ እስከ እዚያ የምንለው ነገር እንዳለን እሙን ነው። ዛሬ ባለንበትና በምንደርስበት መካከል የጊዜ ትርጉም ትልቅ ነው። መኪና መንጃ ፈቃድ መማር የሚያስብ ሰው ትምህርት በጀመረበትና መንጃፈቃዱን ከእጁ በሚያደርግበት ሂደት ውስጥ የሚያወጣው ጊዜ አለ። ጀምሮ የጨረሱትና ጀምረው ያልጨረሱት መካከል ያለው ልዩነት የጊዜ ነው። ምናልባት በሚገባ ትምህርት ባለመውሰድና የሚገባውን ጊዜ ባለመመደብ አንዳንዱ ከሚጠበቀው ጊዜ ያለፈን ጊዜን ሊወስድ ይችላል።
ጊዜ ራሳችን የማንፈጥረው ቢሆንም የማርዘምም ሆነ የማሳጠር ሃላፊነት ግን በእጃችን ነው። ውሳኔዎቻችን ተጽእኖ ከሚያሳድሩበት ነገሮች መካከል አንዱ ጊዜ ነው። በሱስ ውስጥ የሚያልፉ ሰዎች ከሱስ ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት ምንነበረበት ያኔ ገና ከጀምሩ ከሱስ እርቀው ቢሆን ኖሩ ስንል እናስባለን። በጊዜ ሂደት ውስጥ ሱስ የፈጠረው ተጽእኖ እድሜያቸውን ለማሳጠርም ምክንያት ይሆናል። አመጋገቡን በጊዜ ማስተካከል የሚገባው ሰው አመጋገቡን ባለማስተካከሉ ምክንያት በጤንነቱ ላይ የሚያመጣው ተጽእኖም እንዲሁ በምሳሌነት ልናነሳው እንችላለን። በወንጀል ውስጥ ተሰማርቶ እድሜውን በእስርቤት ውስጥ የሚገድል ሰው እንዲሁ ጊዜውን በማሳጠር ሃላፊነትን የወሰደ ሰው ነው። ጊዜን ማብዛትም ሆነ ማሳጠር በሕይወት አካሄዳችን ውስጥ የሚገኝ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል።
ከእዚህ እስከ እዚያ ባልነው ነገር ውስጥ ከፈጣሪ እርዳታ ጋር ስኬት ከእኛ ጋር እንዲሆን ለጊዜ የምንሰጠውን ግምት መመርመሩ አስፈላጊ ነው። ዛሬ ከአጠገባችን ያሉ ህጻናት ነገ አድገው ከአጠገባችን አይሆኑም፤ ለእነርሱ ልንሰጠው የሚገባን ጊዜ ዛሬ ላይ ማዋል ካልቻልን ነገ ላይ ጸጸት ሊሆን ይችላል የሚተርፈን። ዛሬ ጊዜያችንን ባልተገባ ሁኔታ ከመጠቀም ገንዘብን በአግባቡ መጠቀም እንዳለብን እንደምንረዳ ሁሉ ጊዜንም እንዲሁ መጠቀም አለብን። በእዚህና በእዚያ መካከል ጊዜ አለ፤ ጊዜ አለ፤ አዎ ጊዜ አለ፤ በአግባቡና በጥንቃቄ ልንጠብቀውም ሆነ ልንይዘው የሚገባ የማይዳሰስ ሃብት። የሚዳሰሰውን ማግኘት እንድንችል የምንጠቀምበት የማይዳሰስ ሃብት። ከልጅነት እስከ እውቀት የሚደረገው ጉዞ ሁሉ ትርጉም የሚያገኝበት። እያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ትርጉም የሚያገኝበት። ለመስጠትም ሆነ ለመቀበልም፤ ለመታመም ለመዳንም፤ ለመራመድም ሆነ ለመቀመጥ ወዘተ ትርጉም የሚሰጥ፤ ጊዜ።
እሴት
በትላንት ጉዞ ውስጥ የተወለደ የእሴት ሕይወት አለ። ትላንት የሚያውቀን ሰው ዛሬ ሲያየን በእሴት መነጽር ይመለከተናል። ትላንት በሆነው ሁናቴ ዛሬን ፊቱን ሊያጠቁርብንም ይችላል፤ ወይንም በደስታ ሊቀበለን። “እርሱ እኮ እንዲህ ነው”፤ “እርሷ እኮ እንዲህ ናት” የሚል ተቀጽላ ስምም ይኖረን ይሆናል። በጉዞ ውስጥ እሴት ያጋጥመናል፤ የሚገነባ እንዲሁም የሚፈርስ። የሚገነባም ሆነ የሚፈርሰው የእሴት ሕይወት እንዲሁ የሚገኝ አይደለም። አንድን ነገር ጀምረን ለመጨረስ በምናደርገው ጉዞ ውስጥ የምናልፍበት መስመር ውስጥ እሴት ቦታን ይይዛል። እሴታችን ነገራችንን ሊያፈጥን፤ ሊያዘገይ እንዲሁም ሊያጠፋው ይችላል። እሴት የሚያጋጥም ልናጠፋው የማንችለው የህይወታችን አካል ነው።
ሰዎች እንዲሆኑልን እንደምንፈልግ ብቻ ሳይሆን እኛም እንዴት ልንሆንላቸው እንደሚገባ ማሰብ ከእዚህ እስከ እዚያ ባለው ጉዞ ውስጥ አስፈላጊ ነው። ስለ እሴት ዘማርያን ዘምረዋል፤ ደራስያን ደርሰዋል፤ የፍልስፍና ሰዎችም የፍልስፍና መስመራቸው አድርገው ተፈላስፈዋል፤ ጉዞው ሁሉ በእሴት ውስጥ የራሱ የሆነ ትርጉም አለው። አንድን ስራ ሁለት ሰዎች ይዘውልን ቢቀርቡ ለሁለቱም የምንሰጠው ምላሽ አንድ አይነት ላይሆን ይችላል፤ እሴትን የተመረኮዘ ሆኖ ምላሻችን ሊለያይ ይችላል። በእሴት ውስጥ ነገሮች የራሳቸውን መልክ አላቸውና።
ልጆች አሳድጎ ማስመረቅ ውስጥ አንድ ከእዚህ እስከ እዚያ ቢሆን በዚህ የጊዜ ገደብ ውስጥ እሴት ላይ የምንሰራው ስራ የራሱ የሆነ ትርጉም አለው። የተቸገሩትን በመርዳት ውስጥ የምናደርገው የትኛውም ጉዞ የሚኖረው ትርጉም በእሴት ውስጥ ሊታይ ይገባዋል። የተቸገሩትን ለመርዳት ገንዘብ በማሰባሰብ ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች የሰበሰቡትን ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ በማዋል ውስጥ ሰዎች እንዲሰጡ ያበረታታሉ፤ የተቸገሩትን የመርዳት ስራም ውጤት ያለው ይሆናል።
አንዳንድ ሰዎች ላይ አስተያየት ሲሰጥ ስራው ጥሩ ነበር፤ ነገርግን ባህሪ የለውም እንጂ ይባላል። ስራው ጥሩ የሆነ ሰው በባህሪውም ጥሩ ቢሆን ሊፈጥረው የሚችለው አዎንታዊ ተጽእኖ ምንያህል ሊሆን እንደሚችል ማሰብ ተገቢነት ይኖረዋል። የእሴት ሕይወትም ከእዚህ አንጻር ትርጉሙ ብዙ ነው።
ምን ጀምረህ ለመፈጸም በእቅድህ ውስጥ አለ፤ አጀማመሩም፤ አካሄዱም እንዲሁም መዳረሻውም በእሴት እንዲሆን አበክረህ ስራ። እህቴ ሆይ በመንገድሽ ላይ የሚመጣ ከመዳረሻሽ ሊያደርስሽም ሆነ ሊያስቀርሽ የሚችለውን ነገር በእሴት ውስጥ ትመለከቺው ዘንድ ይህ መልእክት ለአንቺ ነው።
አመታት እድሜ ሆነው ትርጉም የሚሰጣቸው በምንራመደው እርምጃ ውስጥ መሆኑን መካድ አያስፈልግም። የምንራመደው እርምጃም የሚኖረው ትርጉም በእሴት ውስጥ የተሰመረ ነው። እሴታችን በጉዟችን ውስጥ ያለውን የማይናቅ ቦታን ለመመልከት ኩረጃ የሀገር ችግር ሆኖ የተሄደበትን ሰሞነኛ የትምህርት ሚኒስቴር አካሄድ መመልከት በቂ ነው። እንዴት ትውልዱ ጀምሮ በመጨረስ ውስጥ እሴትን ቦታ ሳይሰጠው ቀረ፤ እንዴት ወዳለመው ዓላማ በዚህም በእዚያም መድረስን አሰበ ብለን ልንጠይቅ ይገባናል።
በመነሻችን ውስጥ ያነሳናቸው ሦስቱ ወጣቶችን ዳግም እናስባቸው።ሦስቱም ድካም አለባቸው። በውስጣቸው ያለው ድካም ግን ከተማሪነት ወደ ሰራተኝነት፤ ከግለሰብነት ወደ ቤተሰብ አስተዳዳሪነት፤ ከተመሪነት ወደ መሪነት ከመምጣት አይከለክላቸውም። ድምጽ፤ ጊዜና እሴት በጥንቃቄ ከተያዙ።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2015