ልጆች የፈጣሪ ስጦታ ናቸው። ብዙ ጊዜ ሕጻናት በውልደት ቤተሰብን ሲቀላቀሉ የሚኖረው ደስታም ቃላት ብቻውን ከሚገልጸው ስሜት በላይ ሊሆን ይችላል። ብዙዎች እንደሚያምኑት ልጆች በወላጆች ሕይወት ላይ የሚጨመሩት ደማቅ ቀለም አለ። ይህ እውነታ ለበርካቶች ታላቅ ሀሴት ሆኖም ማንነትን ሲቀይር፣ የመኖር ህልምን ሲፈታ ይስተዋላል።
ሕጻናት ወደዚህች ምድር ሲመጡ ከሚኖራቸው በረከት ባሻገር የሚገጥሟቸው ፈተናዎች በርካታ ናቸው። አንዳንዴ ከጤና መጓደል ጋር የሚወለዱ ልጆች ችግራቸው በቀላሉ ላይታወቅ ይችላል። በህክምና ክትትል መፍትሄ ከሚገኝላቸው ታማሚ ሕጻናት ባለፈ ችግራቸው ስር ሰዶ የእድሜ ልክ ስቃይን የሚቀበሉ ጥቂቶች አይደሉም።
እንዲህ በሆነ ጊዜ ሳቅ ፈገግታ ለቅሶ ይሆናል። ደስታና በረከት ትርጉም ያጣሉ። የልጇን ትኩሳት የማትሻው እናት ሕይወቷ በፈተና ይታጠራል። ልጅን ወልዶ ከመሳምና ማቀፍ በላይ የከፋ ስጋት የሚሆነው ጤና ማጣትም ለመላው ቤተሰብ ምቾት አልባ ሕይወትን ያቀብላል።
ሕጻናት ሲወለዱ ከሚገጥማቸው የአፈጣጠር ችግሮች ውስጥ አንዱ በነርቭ ዘንግ ላይ የሚፈጠር ክፍተት ነው። በህክምና አጠራሩ ‹‹ስፓይና ቢፊዳ ኤንድ ሀይድሮ ሲፋለስ›› በመባል ይታወቃል። ይህ ህመም የነርቭ ዘንግ ክፈተትና የጭንቅላት ውሀ መቋጠር ችግር ስለመሆኑ በጥናት ተረጋግጧል። ‹‹ስፓይና ቢፊዳ›› የነርቭ ዘንግ ክፍተት ወይም የህብለ ሰረሰር በትክክል ያለማደግ ሂደት ነው።
የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ችግሩ በቅድመ ወሊድ ጊዜ ሊከሰቱ ከሚችሉ አስጊ የጤና እክሎች ጋር ይያያዛል። የነርቭ ዘንግ ከጀርባ የመሀለኛው ክፍል የላይኛውንና የታችኛውን ይዞ ከሀያ አንደኛው እስከ ሀያስምንተኛው የእርግዝና ቀናት መዘጋት የሚኖርበት የራስ ቅልና የህብለ ሰረሰር ዘንግ ክፍተት ነው።
ሀይድሮ ሴፋለስ ደግሞ በጭንቅላት ውስጥ ከመጠን ያለፈ ፈሳሽ መኖር ሲሆን፤ በእርግዝና ወይም ከወሊድ በኋላ በኢንፌክሽን ምክንያት የሚፈጠር ችግር ነው። የሀይድሮ ፌላሰስ ህመም ስለመከሰቱ ከሚጠቁሙ ምልክቶች አንዱ የጭንቅላት መጠን በፍጥነት መጨመርና ማበጥ ነው። ይህ ችግር የተከሰተባቸው ሕጻናት የቀዶ ህክምና ማግኘት ከቻሉ ከመጠን በላይ የተከማቸውን ፈሳሽ ማስወገድ ይቻላል። እንዲህ መሆኑ የነርቭ ህዋሳቶች የከፋ ጉዳት ሳይደርሰባቸው ለመታደግ ያግዛል።
ሁለቱም አይነት የጤና ችግሮች የሚከሰቱት በፎሊክ አሲድ እጥረት ምክንያት ሲሆን፤ አብዛኞቹ ሕጻናት በግንዛቤ እጥረትና በአገልግሎት ተደራሽነት ማጣት ሳቢያ ተገቢውን የቀዶ ህክምና ሳያገኙ የሚቀሩ ናቸው። ጭንቅላትና ህብለ ሰረሰርን ይዞ ጭራ እስከሚባለው የአካል ክፍል የሚዘልቀው የነርቭ ጉዞ እስከ ዳሌና የጀርባ አጥንት የሚቀጥል ዑደት አለው።
የነርቭ ስሮቹ የራሳቸው ልባስ ያላቸው ከመሆኑ ጋርም ውስጣቸው ጭምር የሚያመነጩት ፈሳሽ አላቸው። የነርቭ ዘንግ ክፍተት በእርግዝና የመጀመሪያዎቹ ወራት በጽንሱ ላይ የሚከሰት የአፈጣጠር ችግር ነው። አንዳንድ ሕጻናት ሲወለዱ በጀርባቸው ላይ የሚስተዋለው ዕባጭና የአንጎል ክፍል በሰስ ልባስ ተሸፍኖ መውጣት፣ እንዲሁም የራስ ቅል በፈሳሽ መሞላት የህመሙ መገለጫ ምልክት ናቸው።
ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ የነርቭ ስሮቹ አፈጣጠራቸው በጊዜ ቀመር የተሰላ ነው። ጽንስ ከተፈጠረ ሶስትና አራት ሳምንት ጊዜ ውሰጥ ጭንቅላትና ህብረ ሰረሰር የሚባሉት ተሰርተው ይጠናቀቃሉ። ከዚህ ቀጥሎ የሚኖረው ሂደት ርዝመትና ክብደትን ከመጨመር ባለፈ አዲስ ህዋስ የሚፈጠርበት አይሆንም።
የህብለ ሰረሰር አፈጣጠር የዘገየ ባለመሆኑ ጽንሱን ለአደጋ የሚያጋልጡ ክስተቶች ሲኖሩ በጭንቅላትና በህብለ ሰርስር ታችኛው ክፍል ድረሰ የአጥንት አለመግጠም ክፍተት ሊከሰት ይችላል ። እንዲህ በሆነ ጊዜ ህብለ ሰረሰሩ በአጥንቱ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች እንደክፍተቱ ደረጃ የመውጣት አጋጣሚው የሰፋ ይሆናል።
ከጭንቅላት መፈጠር ጀምሮ እስከ ታችኛው ህብለ ሰረሰር ድረስ ያለው አካል ከእርግዝና መከሰት እሰከ አራተኛው ሳምንት ድረሰ ሊደፈን ይገባል። ይህ ሳይሆን ከቀረ ግን ክፈተት መፈጠሩ አይቀሬ ይሆናል። በተለምዶ ብዙ እናቶች ማርገዛቸውን የሚያውቁት የወር አበባ አለማየታቸውን ተከትሎ ነው። ጥርጣሬቸው ዕውን ሆኖ እርግዝናቸውን እስኪያረጋግጡ በሚኖረው ቢያንስ የአንድ ወር ቆይታ የጽንሱ አዕምሮ ዕድገት ተገንብቶ ተጠናቋል። ይህ አይነቱ እውነት ችግሩን አስቀድሞ ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የዘገየ ያደርገዋል።
ጭንቅላት ከልብ ቀጥሎ የሚፈጠር አካል እንደመሆኑ አስፈላጊ የሆኑ ልባስና ከለላዎች ሊፈጠሩለት የሚገባው በጊዜው ገደብ መሆን አለበት። ጽንሱ በአፈጣጠር ሂደቱ የተስተካከለ ካልሆነ የችግሩ ምንጭ የሚነሳው ከመጀመሪያው አንስቶ ይሆናል። የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ችግሩን ለመከላከል አዳጋች የሚያደርገው ዋንኛ ምክንያት እርግዝና መኖሩ ከመታወቁ በፊት ችግሩ ቀድሞ የመከሰቱ እውነት ነው።
የነርቭ ዘንግ ክፍተት ችግር በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ያለው አሀዝ ሲቃኝ ከሚወለዱ አንድ ሺህ ሕጻናት መካከል አንድ ጽንስ በችግሩ ሊጠቃ እንደሚችል ነው። በተመሳሳይ ይህ ክስተት ባላደጉ አገራት ላይ ሲጠና የችግሩን መጠን የሚያጎላው ሆኖ ተገኝቷል። በሀገራችን ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እንደሚያስረዳውም ከሚወለዱ አንድ ሺህ ሕጻናት መካከል በቁጥር ሰባት የሚሆኑት የችግሩ ሰለባዎች ይሆናሉ። ይህ እውነታም በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ከተቀመጠው አሀዝ በሰባት ከፍ የሚል በመሆኑ የስጋት መጠኑን የሚያሳድገው ይሆናል።
የነርቭ ዘንግ ክፍተት መኖሩ የሚታወቀው ከሕጻኑ ውልደት በኋላ ነው። እንዲህ አይነቱ አጋጣሚ በእኛ መሰል ማህበረሰብ መሀል ተከስቶ ሲገኝ ደግሞ የችግሩን ስፋት ይበልጥ ያጎላዋል። በተጨባጭ ያሉ ማስረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በሀገራችን ካሉ እናቶች ገሚስ ያህሉ በቤታቸው የሚወልዱ ናቸው። ስለዚህም አስቀድሞ ችግሮችን ከመከላከል ይልቅ መፍትሄን የሚሹት ከጉዳታቸው በኋላ ይሆናል። ስለሆነም አደጋው የከፋ ነው።
የህክምና ክትትል ምጣኔው በርከት በሚልባቸው አካባቢዎች የሚገኙ እናቶች ግን ከዚህ በተቃራኒው መንገድ ይጓዛሉ። ችግሩን አስቀድሞ ለመጠርጠር በሚረዱ የህክምና መንገዶች ያልፋሉም። እንዲህ አይነቶቹን ምርመራዎች ለመከወንም የሚችሉበት አጋጣሚዎች ሰፊ ናቸው። ምርመራ ለማድረግ የአልትራ ሳውንድና መሰል ምርመራዎችን ማካሄድ የግድ ይላል። ከዚሁ ጋር ተያይዞም የመመርመሪያ መሳሪያውን የሚጠቀመው ባለሙያ ችሎታና ክህሎት ከተለየ ብቃት ጋር የተዛመደ ሊሆን ይገባል። እንደህክምና ባለሙያዎች እምነት፤ በአልትራ ሳውንድ የምርመራ ሂደት የተለየ ክትትል ተደርጎ ችግሩን በጽንስ ዕድሜ ላይ መለየት ከተቻለ መፍትሄ የሚገኝበትን ዕድል የተሻለ ያደርገዋል።
ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ለነርቭ ዘንግ ክፈተት ሊያጋልጡ ከሚችሉ አጋጣሚዎች አንዱ የመድሀኒቶች አወሳሰድ ሁኔታ ነው። በተለይም ለካንሰርና ለድብርት ተብለው የሚወሰዱ መድሀኒቶች፣ ከአዕምሮ ህመም ጋር የሚታዘዙ እንክብሎች እንዲሁም ለደም ማቅጠኛ፣ ለስኳር ህመምና ለሚጥል በሽታ ሲባል የሚሰጡ ኪኒኖች፣ ለህመሙ መጋለጥ ምክንያት እንደሚሆኑ ይገመታል። ስለሆነም እነዚህ መድሀኒቶች ከሰውነት ውስጥ የሚቀንሱት ኬሚካል በመኖሩ ህመሙ ያላባቸው እናቶች ከእርግዝናቸው በፊት ተገቢውን ምርመራ ሊያደርጉ ግድ ይላል። እንዲህ ከሆነ አስቀድሞ የመከላከያ መድሀኒቶችን በመጠቀም የችግሩን ሰባ በመቶ መቀነሰ ይቻላል።
ለነርቭ ዘንግ ክፍተት ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከል ሌላው በእርግዝና ወቅት ሲጋራ ማጨስና ለኬሚካሎች የመጋለጥ አጋጣሚ ነው። ይህ አይነቱ ሂደት ሕጻናት ከነርቭ ዘንግ ክፍተት ጋር እንዲወለዱ ሰበብ ይሆናል። የዚህ ጤና ችግር ያለባቸው ሕፃናት ሽንትና ሰገራን አለመቆጣጠርን ጨምሮ ለአካል ጉዳት የመጋለጥ ዕድላቸው ሰፊ ነው ።
በዘርፉ የተሰማሩት የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም በነርቭ ዘንግ ክፍተት የተጠቃ ልጅን የወለዱ እናቶች ቀጣዩ ልጃቸውም ተመሳሳይ ችግር ሊከሰትበት ይችላል። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ቀድሞ ያጡትን የፎሊክ አሲድ መድሀኒት በድጋሚ የመውሰድ ልምድን አለማዳበራቸው ነው። እነዚህን ችግሮች አስቀድሞ ለመከላከል እናቶች ለእርግዝና ዝግጁ በሆኑ ጊዜ የፎሊክ አሲድ እንዲወስዱ ማድረግ ተገቢ ይሆናል። የጤና ተቋማትም ለእንዲህ አይነቱ ችግር መሰረታዊ አገልግሎቶችን በማስፋት ተገቢውን ግንዛቤና ድጋፍ የመስጠት ሀላፊነት ይኖርባቸዋል።
አሁናዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ በኢትዮጵያ በየዓመቱ በአስርሺዎች የሚቆጠሩ ሕጻናት ከነርቭ ዘንግ ክፍተት ጋር ይወለዳሉ። ይህን መሰሉን አሳሳቢ የጤና ችግር ለመከላከል ለህብረተሰቡ ተገቢውን ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል። ችግሩ ተከስቶ ሲገኝም በወቅቱ የህክምና አገልግሎት የሚገኝበትን ዕድል በማስፋት የሕጻናቱን ሕይወት መታደግ ይገባል።
ሆፕ ኤስ ቢኤች / Hope –SPH/ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው በሀይድሮሴፋለስ እና ሰፓይና ቤፊዳ ዙሪያ የሚሰራ ግብረሰናይ ድርጅት ነው። ድርጅቱ የተቋቋመው የችግሩ ተጠቂ የሆኑ ልጆች ባሏቸው ወላጆችና ቤተሰቦቻቸው አማካኝነት ነው። ድርጅቱ በዘውዲቱና በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታሎች ወላጆችን የማማከርና ግንዛቤ የማስጨበጥ ተግባርን ይከውናል። የሕጻናቱን ጤና ከፍ ለማድርግ የሚያግዙ የህክምና መሳሪዎችን ከውጭ አገራት በማስመጣትም አስፈላጊ ስልጠናዎችን ይሰጣል።
በህመሙ የተጠቁና መገኛቸው ከአዲስ አበባ ውጭ ለሆኑ ሕጻናት ተገቢውን ድጋፍ ያደርጋ ። ከየክልሉ ለሚመጡ ወላጆችም የማቆያ ስፍራዎችን በማዘጋጀት የሚገጥማቸውን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመታደግ ላይ ነው።
በየዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የስፓይና ቢፊዳና የሀይድሮ ሴፋለስ ቀን ዘንድሮ በሀገራችን ‹‹ድምጻችንን ከፍ እናድርግ›› በሚል መሪ ቃል ከጥቅምት 13 እስከ 20 2015 ዓ.ም ድረስ ይከበራል። እናም ይህ ሳምንት በመንገድ ዳር ግንዛቤዎችና በፓናል ውይይቶች ለህብረተሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ዓላማን ያነገበ ነው። ስለዚህም ተቋማት፣ እናቶች ልዩ ትኩረት ሰጥተው ለችግሩ መፍትሄ መሆን ይኖርባቸዋል። ችግሩ ተከስቶ ሲገኝም ወቅቱን የጠበቀ የቀዶ ህክምና በማካሄድ የሕጻናቱን ሕይወት መታደግ የህብረተሰቡ ኃላፊነት መሆን አለበት። ችግሩ አሳሳቢ በመሆኑም በዚህ ሳምንት የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ላይ መሳተፍ ይገባናል። ጉዳዩ የሁላችንንም ነውና ዓይንና ጆሯችንን ይሻል።
መልካምሥራ አፈወርቅ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 19/2015