ዓለምአቀፍ የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ሊካሄድ በጣት የሚቆጠሩ ቀናቶች ብቻ ቀርተውታል። ኤክስፖውም አምራችና ገዥን ጨምሮ በዘርፉ ኢንቨስት የሚያደርጉ፣በገንዘብ፣በሀሳብ፣በእውቀትና በቴክኖሎጂ እገዛ ለማድረግ ፍላጎት ያላቸው፣በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ባለድርሻ አካላት የሚያሳትፍ ነው። ዛሬም ድረስ ዓለም አቀፍ ስጋት በሆነው የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ፣እንዲሁም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ላለፉት ሁለት አመታት በተካሄደው ጦርነትና በሌሎችም ምክንያቶች የማዕድን ዘርፉ ተቀዛቅዞ መቆየቱ ይታወቃል።
በአሁን ወቅትም ከማምረት እስከ ገበያ ባለው ሰንሰለት ውስጥ ተቀዛቅዞ የነበረውን የማዕድን ዘርፍ ማነቃቃት ያስችላል የተባለው ኤክስፖ ሊጀመር ቀናቶች ቀርተውታል። በኢትዮጵያ አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚካሄደው የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ ላይ በዘርፉ ልማትና ቴክኖሎጂ ተሞክሮ ያላቸው የውጭ ኩባንያዎችና የሀገር ውስጥ የዘርፉ አምራች ኢንደስትሪዎችን በማገናኘት በሚኖረው ሚናም ትልቅ አቅም ይፈጠራል የሚል እምነትም አሳድሯል።
በህዳር ወር መጀመሪያ ላይ በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል ተብሎ ስለሚጠበቀው የማዕድንና ቴክኖሎጂ ኤክስፖ በተመለከተ የማዕድን ሚኒስቴር የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ፌቨን ተሾመ እንዳስረዱት፤የማዕድን ቴክኖሎጂ ኤክስፖው በዘርፉ ላይ የሚገኙትን ኩባንያዎች እርስበርስ በማስተዋወቅ የገበያ ትስስርና የቴክኖሎጂ የልምድ ልውውጥ እንዲኖራቸው ማድረግ ብቻ ሳይሆን፣እንደ ባንክ ያሉ የፋይናንስ ተቋማትንም በማሳተፍ ተቋማቱ ዘርፉን በገንዘብ በመደገፍ አበርክቶ እንዲኖራቸውም ዓላማ ያደረገ ነው። የሀገር ውስጥና የዓለምአቀፍ የዘርፉን ኩባንያዎችና የፋይናንስ ተቋማት በጋራ በማሳተፍ ዘርፉን በማነቃቃት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብንም ታሳቢ ያደረገ ጭምር ነው።
በተለይም ዓለም አቀፍ የዘርፉ ኩባንያዎች የማዕድን ቴክኖሎጂ በማስተዋወቅ በኩል የሚኖራቸው ሚና ከፍ ያለ በመሆኑ የሀገር ውስጥ አምራች ኢንደስትሪዎች ልምድና ተሞክሮ እንዲያገኙ ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በማዕድን ዘርፍ ለተሰማሩ ዓልምአቀፍ ኩባንያዎች፣ለማዕድን ዘርፉ የሚያግዙ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብና በመጠቀም ልምዱ ያላቸውን በኤምባሲዎች አማካኝነት አስቀድሞ ጥሪ አድርጓል። ጥሪው ከተደረገላቸው መካከልም ጣሊያን፣አውስትራሊያ፣ፈረሳይ፣ከአፍሪካ ሀገራትም የዘርፉ ባለድርሻዎች ጥቂቶቹ ሲሆኑ፣ጥሪው የደረሳቸው አብዛኞቹ አገራትም ፍላጎታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ላይ እጅግ ተፈላጊ የሆኑ የማዕድን ሀብቶች ቢኖሩም፣በተለያየ ምክንያት የገበያ ዕድል ያልተፈጠረላቸው መኖራቸውንና በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ የሚያነሱት ጉዳይ እንደሆነ ያስታወሱት ዳይሬክተሯ፤የማዕድን ቴክኖሎጂ ኤክስፖው እንዲህ ላሉ ክፍተቶች መፍትሄ እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል።
እንደርሳቸው ገለጻ፤ ለሶስት ቀናት ክፍት ሆኖ ከሚቆየው ኤክስፖ ከጉብኝት ባለፈ በተለይም ጊዜንና ጉልበትን በሚጠይቅ አድካሚ ሁኔታ በየእለቱ የሚንቀሳቀሱ ባህላዊ የማዕድን አልሚዎች ወይም አምራቾችን ድካም የሚያቃልል፣እንዲሁም በባህላዊ መንገድ ሲያለሙ የሚባክነውን ማዕድን ለማስቀረትና በጥራት መጓደልም የሚያጋጥማቸውን ችግር ለመፍታት የሚረዳቸው ጠቃሚ ነገር እንደሚያገኙ ይጠበቃል።
ሁሉን አቀፍና አሳታፊ የሆነ ዓለም አቀፍ ኤክስፖ ማካሄድ የተለመደ መሆኑን ያስታወሱት ዳይሬክተሯ፤ኢትዮጵያም በማዕድን ዘርፍ ኤክስፖ በማዘጋጀት አንዷ ሀገር ለመሆንና ለቀጣይ መሠረት ለመጣልም እንደጅማሬ የሚወሰድ መሆኑን አመልክተዋል። ከኤክስፖው እንደሀገር ስለሚጠበቀው ውጤትም እንደገለጹት፤የሀገር ውስጥ የዘርፉ አምራች ኢንደስትሪዎችና ላኪዎች በዓለምአቀፍ የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው፣ተወዳዳሪ ሆኖ ገበያውን ሰብሮ ለመግባት የሚያስችል አቅም ለመፍጠር የሌሎችን ተሞክሮ እንዲያገኙ፣በተለይ ደግሞ ባህላዊ የማዕድን አምራቾች ያለባቸው የገንዘብ አቅም እንዲፈታላቸው ከባንኮች ጋር ትስስር የሚፈጥሩበት ሁኔታ እንዲመቻችላቸው፣የቴክኖሎጂ ሽግግር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ከሚጠበቀው ውጤት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው። በዓለምአቀፉ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ እምቅ የሆነ የማዕድን ሀብት እንዳላት ግንዛቤ እንዲኖራቸው ከማስቻሉ በተጨማሪ የዘርፉ ኩባንያዎች ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ እንዲያዞሩም ያግዛል።
ኤክስፖውን የሚያዘጋጀው ማዕድን ሚኒስቴር ተባባሪ ከሆኑት ተቋማት ጋር የውል ስምምነት በመፈራረም ዝግጅቱን የተሳካ እንዲሆን ጥረት እያደረገ ሲሆን፣በዚህ ረገድም የኢትዮጵያ አየርመንገድ ይጠቀሳል። አየርመንገዱ ከውጭ ለሚገቡ የኤክስፖ ተሳታፊዎች በመጓጓዣ እና በሆቴል አገልግሎት ላይ በሚስብ የዋጋ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በማድረግ አጋዥ ሆኖ ይሰራል። የኢትዮጵያን የማዕድን ፖሊሲ በማስተዋወቅና በዘርፉ ኢንቨስትመንትን ለመሳብና የውጭ ኩባንያዎችም በሀገሪቱ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለማየትም ዕድል ይሰጣል። የማዕድን ቴክኖሎጂ ኤክስፖው በተዘዋዋሪ የቱሪዝም ኢንደስትሪው ገቢ ላይ የራሱን አስተዋጽኦ ያበረክታል። ከዚህ አኳያ ኤክስፖው ዘርፈብዙ ጥቅሞች ይገኝበታል ተብሎ ይጠበቃል።
በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እድገት ውስጥ ጉልህ ሚና ይወጣሉ ተብለው ከተለዩት ዘርፎች አንዱ የሆነው ይህ የማዕድን ዘርፍ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ለማስቻል በመንግሥት በኩል እየተደረገ ስላለው እንቅስቃሴ፣በሀገር ውስጥ የኤክስፖው መዘጋጀት ስለሚኖረው ፋይዳና በኤክስፖው የሚፈጠረውን አጋጣሚም በመጠቀም ረገድ በዘርፉ ላይ የሚገኙትን በተለይም በላኪነት ሥራ ላይ ከተሰማሩ መካከል አንዳንዶችን ጠይቀን ሀሳባቸውን አካፍለውናል። በቅድሚያም ሀሳባቸውን ያካፈሉን የኤ ዋይ ኤስ ኤስ ፕሪሸስ ስቶን ኤንድ ጂውለሪ ኤክስፖርተር ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤት አቶ ዓለምነህ የሻነህ ናቸው።
አቶ ዓለምነህ ኩባንያቸው ከኤክስፖው ምን እንደሚጠብቅና አገኛለሁ ስለሚለው ጥቅም ላቀረብንላቸው ጥያቄ‹‹የኤክስፖው አስፈላጊነት ወይንም ጥቅሙ የሚያጠያይቅ አይሆንም። ላኪ የሚለው ስያሜ በራሱ ገበያ ፈላጊ ማለት ነው። ለላኪውም ሆነ ለሀገር ጠቀም ያለ ገቢ የሚገኘው የውጭ ገበያ ሲገኝ ነው። በተለይ ደግሞ ኤክስፖው በሀገር ውስጥ መዘጋጀቱ ተጠቃሚነቱ የበለጠ ነው የሚሆነው። ላኪው ወጭ ሳያወጣና በብዙ ድካም ውስጥ ሳያልፍ ገዥዎች ያለበት ድረስ መጥተው ይገዙታል። ደንበኞችንም ለማፍራት እድል ያገኛል። ይሄ ትልቅ ጥቅም ነው። ›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል። እንደ አቶ ዓለምነህ፤ እስካሁን ባላቸው ተሞክሮ የኢትዮጵያ ማዕድን በብዙ የዓለም ሀገራት ተፈላጊ ነው።
የኤክስፖው መዘጋጀት እነርሱንም ተጠቃሚ ያደርጋቸዋል። ብዙዎችም ይመጣሉ። ለአብነትም የኢትዮጵያን የኦፓል ማዕድን በብዛት በመግዛት ህንዶች ቀዳሚ ናቸው። እርሳቸውም ከህንድ ጋር ባላቸው የገበያ ግንኙነትና በተለያዩ ሀገራት በሚካሄዱ ኤክስፖዎች ላይ ባገኙት የመሳተፍ አጋጣሚ የህንድ የማዕድን ነጋዴዎች ከኢትዮጵያ የገዙትን የኦፓል ማዕድን ገበያ ላይ ሲያቀርቡ ለደንበኛቸው ማዕድኑ የኢትዮጵያ እንደሆ ነው የሚገልጹት።
ደንበኞቻቸው ፈልገው ከእነርሱ መግዛታቸው በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያ ማዕድን በተለይም ኦፓል ተፈላጊ እንደሆነ ማሳያ ነው። በማዕድን ሀብቱ ባለቤቶች በሆኑት ኢትዮጵያውያን ሲቀርብላቸው ደግሞ ገዥዎች የበለጠ ይደሰታሉ የሚል እምነት አላቸው። ግብይቱ ከሁለተኛ ወገን ከሚሆን ቀጥታ መሆኑንም ይፈልጉታል። ደንበኛም በመያዝ ቋሚ ተጠቃሚ ለመሆን ያስችላቸዋል። ኤክስፖው በሀገር ውስጥ መዘጋጀቱ እንዲህ ያለ ጥቅምም እንዳለው ነው የተናገሩት።
የማዕድንና የቴክኖሎጂ ኤክስፖው የተወጣለት ስለመሆኑ ከወዲሁ መናገር ባይቻልም እየተደረገ ያለው ቅድመዝግጅትና የያዛቸው ዓላማዎች ስኬታማ ሊሆን እንደሚችል ግምት የሚያሳድር መሆኑን መነሻ በማድረግ አቶ ዓለምነህን ጠይቀናቸው፡፡ እሳቸውም በማዕድን የላኪነት የሥራ ዘርፍ ላይ በቆዩበት ጊዜያቶች በኢትዮጵያ በተለያየ ጊዜ የማዕድን ኤግዚቢሽኖች እንደተካሄዱ ከመገለጹ ውጭ አላጋጠማቸውም። መኖሩን ቢያውቁ ኖሮ ግን ይሳተፉ እንደነበር ነው ያስታወሱት። ‹‹እንኳንም በሀገሬ ላይ ተዘጋጅቶ፣ በዶላር ከፍዬ በሌላ ሀገር ተሳትፌያለሁ። ከዚህ ቀደም በሀገር ውስጥ አላጋጠመኝም›› በማለት አብራርተዋል። የአሁኑ ግን ኤክስፖ የመጀመሪያቸው ነው። ከዝግጅቱም ለኩባንያቸውም ሆነ ለሀገር የሚጠቅም ትልቅ ውጤት ይገኛል የሚል ተስፋ አድርገዋል።
ሮዳስ የከበሩ ድንጋዮች ጌጦችና ቅርጾች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ባለቤት አቶ ሄኖክ ግርማ ግን ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የማዕድን ኤግዚቢሽኖች መዘጋጀታቸውንና እርሳቸውም መሳተፋቸውን ነግረውናል። በዘርፉ በላኪነትና በአምራችነት የካበተ ልምድ ያላቸው የውጭ ወይም ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን እንዲሁም ቴክኖሎጂን ባካተተ ያሳተፈ እንዳልነበር ነው የገለጹት። አቶ ሄኖክ እንዳሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው የማዕድን ሀብት ብቻ ሳይሆን የማዕድንን ጥቅምና ያለውን ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ግንዛቤ አልተፈጠረም የሚል እምነት አላቸው። የማዕደን ጌጣጌጥን አክብረውና ፈልገው የሚጠቀሙት ጥቂት ናቸው።
ከሀገር ውስጥ ይልቅ የውጭ ማህበረሰብ የተሻለ ግንዛቤ ስላለው የዋጋውንም ውድነት ይረዳሉ። የማዕድን ቴክኖሎጂን ለማዘጋጀት እየተደረገ ካለው እንቅስቃሴ በይዘቱም ሆነ በተሰጠው ትኩረት ጥሩ ነገር ይጠብቃሉ። ኤክስፖው ስለማዕድን ጥሩ ግንዛቤ ያላቸውንና በዘርፉ ላይ የሚሰሩትንም የሚያሳትፍ በመሆኑ በሀገር ውስጥ የሚገኘውን አምራችና ላኪ በማነቃቃት እንዲሁም ማህበረሰቡ የተሻለ ግንዛቤ እንዲኖረው ከማድረጉ በተጨማሪ የዘርፉን የገበያ ችግር በመቅረፍ ረገድ ያለውን ፋይዳ የጎላ ያደርገዋል።
የዓለም አቀፍ ገበያው ከማዕድን ዘርፎች በዋናነት የሚጠቀሱት እንደ ኦፓል፣ኤመራልድ፣ሳፋየር የመሳሰሉ የኢትዮጵያን የማዕድን አይነቶች በተዘዋዋሪ ከሌሎች ነጋዴዎች ከሚገበዩ ከመገኛው ሀገር መግዛት መቻላቸው አመኔታቸውን ከፍ ያደርግላቸዋል። ‹‹ኢትዮጵያም ብራንድ ለመሆን ያስችላታል›› ብለዋል።
እንደ አንድ የማዕድን ላኪ ከኤከስፖው ምን ይጠብቃሉ ብለን ላቀረብንላቸው ጥያቄ አቶ ሄኖክ ጥሩ የሆነ ግብይት እንደሚኖር፣በገበያም ሆነ ስለማዕድኑ አይነት አዲስ እይታ እንደሚጠብቁ ነው ምላሽ የሰጡት። ‹‹ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ለማንሳት አውስትራላውያን ያገኙትን ብላክ ኦፓል እራሳቸው በዓለም ላይ በሚያዘጋጁት ኤክስፖ ላይ በማቅረብ የሀገሪቱ ባለሀብቶች በጨረታ በውድ ዋጋ መልሰው እንዲገዙት ያደርጋሉ። ከራሳቸው ምድር የተገኘውን በራሳቸው ዜጋ በውድ ዋጋ እንዲሸጥ በማድረግ ማዕድኑ ከፍተኛ ዋጋና ትኩረት እንዲኖረው ያደርጋሉ። እንዲህ አይነት ነገር አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። እኛ ቀጥታ መሸጥ እየቻልን የሌላው ሀገር ነጋዴ ከእኛ ገዝቶ ለገበያ ማቅረብ የለበትም። እኛም በቀጥታ መሳተፋችን አዲስ የዋጋ እይታ እንዲኖረን ያስችለናል›› በማለት አስረድተዋል።
አቶ ሄኖክ ኤክስፖው ሁሉንም ማሳተፍ እንዳለበት ያምናሉ። ስለአስፈላጊነቱም አብነትን በመጥቀስ እንዳስረዱት አንድ የውጭ ሀገር ዜጋ ማዕድኑን ሲገዛ ሻጩ ከየት እንደሆነ ያረጋግጣል። ይሄን የሚያደርገው የሚገዛው ማዕድን ከኢትዮጵያ ከሆነና ሻጩም ኢትዮጵያዊ ከሆነ ማዕድኑን በቁፋሮ ከመሬት የሚያወጣው አልሚም ይጠቀማል የሚል እምነት ስላለው ነው። ከአልሚው ጀምሮ ሁሉም በየደረጃው ተጠቃሚ መሆን ካልቻለ ከዚህ ቀደም እንደሚባለው የደከመው ሳይሆን ሳይደክም ጥቅም ለማግኘት የሚሯሯጠው ብቻ ተጠቃሚ ይሆናል። ይሄ ደግሞ በዘርፉ የሚነሳውን ቅሬታ ለመቅረፍም አያስችልም። ፍትሐዊነትንም አያረጋግጥም። በተለይ ደግሞ የባህል አልሚውንና ሳይንሳዊ የሆነ የገበያ እይታ የሌለውን ተጎጂ ያደርጋል። አምራቹን፣አዘዋዋሪውን፣ላኪውን፣ቀራጩን፣በአጠቃላይ የዘርፉን ተዋናይ የያዘ ኤክስፖ ሲሆን ውጤቱም ያማረ እንደሚሆንና በኢትዮጵያ በዘርፉ ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ በዘርፉ ያለው ሁሉ ተጠቃሚነቱና ተሳትፎው እኩል መሆን አለበት ይላሉ።
በተለያዩ ሀገራት በሚዘጋጁ የማዕድን ኤክስፖዎች ላይ የመሳተፍ እድል ማግኘታቸውን የገለጹልን አቶ ሄኖክ፤በኢትዮጵያ የሚዘጋጀው በተደጋጋሚ ኤክስፖ የማዘጋጀት ልምዱና ተሞክሮ ካላቸው ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ እንዲሆን ባይጠብቁም በሀገር ደረጃ ከዚህ ቀደም ያልተለመደ ነገር ለማምጣት ጥረት መደረጉ በራሱ ትልቅ ለውጥና ሊበረታታ እንደሚገባ ነው ያስረዱት። ይህ መሆኑ በራሱ የሚጨምረው እሴት መኖሩን ነው የገለጹት። እንግዲህ ከአስተያየት ሰጪዎቹም ሆነ ከማዕድን ሚኒስቴር መረዳት የሚቻለው ኤክስፖው ትኩረት የተሰጠውና ትልቅ ውጤትም የሚጠበቅበት ነው። ውጤቱንም በጋራ እንጠብቃለን።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 18/2015